ትሑታን ደስተኞች ናቸው
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። ” — 1 ጴጥሮስ 5:5
1, 2. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደስተኛ መሆንን ትሑት ከመሆን ጋር ያዛመደው እንዴት ነው?
ትሕትናና ደስታ እርስ በርሳቸው ይዛመዳሉን? እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ ዘጠኝ ደስታዎችን ዘርዝሯል። (ማቴዎስ 5:1–12) ኢየሱስ ደስተኛ መሆንን ከትሕትና ጋር አዛምዷልን? አዎን፣ አዛምዷል። ምክንያቱም እርሱ ከተናገራቸው ደስታዎች ብዙዎቹ ከትሕትና ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ትሑት ካልሆነ ስለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ሊያስብ አይችልም። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ትሑታን ብቻ ናቸው። ትዕቢተኞች የዋሆችና መሐሪዎች ወይም ሰላም ፈጣሪዎች አይደሉም።
2 ትሑት መሆን ትክክልና ሐቀኝነት ስለሆነ ትሑታን ደስተኞች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ትሑት መሆን ጥበብ ስለሆነ ትሑታን ደስተኞች ናቸው። ትሕትና ከይሖዋ አምላክና ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ለሚኖረን ጥሩ ግንኙነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲሁም ትሑት መሆን የፍቅር መግለጫ ስለሆነ ትሕትና ያላቸው ሰዎች ደስተኞች ናቸው።
3. ሐቀኝነት ትሑቶች እንድንሆን የሚያስገድደን ለምንድን ነው?
3 ሐቀኛነት ትሑቶች እንድንሆን የሚፈልግብን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ሁላችንም አለፍጽምናን ስለወረስንና ያለማቋረጥ ስሕተት ስለምንሠራ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱ “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 7:18) አዎን፣ ሁላችንም ኃጢአት ሠርተናል፣ የአምላክም ክብር ጎድሎናል። (ሮሜ 3:23) ስሕተት እንደምንሠራ ማመን ከትዕቢት ይጠብቀናል። የራስን ስሕተት ለመቀበል ትሑት መሆን ያስፈልጋል። ሐቀኝነት ደግሞ በሠራነው ስሕተት ምክንያት የሚደርስብንን ወቀሳ እንድንቀበል ይረዳናል። ምን ጊዜም ቢሆን ልናደርግ የምንፈልገውን ነገር በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ስለሚሳነን ትሑቶች የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን።
4. በ1 ቆሮንቶስ 4:7 ላይ ትሑት እንድንሆን የሚያስገድድ ምን ምክንያት ተሰጥቷል?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ ሐቀኝነት ለምን ትሑቶች እንድንሆን ሊያደርገን እንደሚገባ ሌላ ምክንያትም ይሰጠናል። እንዲህ ይላል:- “አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድን ነው?” (1 ቆሮንቶስ 4:7) ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ፣ ባለን ንብረት፣ ችሎታ፣ ወይም በተሳካልን ክንውን መኩራራት ሐቀኝነት አይደለም። ሐቀኝነት በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና እንዲኖረን አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ “በሁሉም ነገር በሐቅ እየሠራን ለመኖር” እንችላለን። — ዕብራውያን 13:18 አዓት
5. ሐቀኝነት አንድ ስሕተት በምንሠራበት ጊዜ እንዴት ሊረዳን ይችላል?
5 ሐቀኝነት አንድ ስሕተት በምንሠራበት ጊዜ በትሕትና ስሕተታችንን እንድናምን ይረዳናል። ስሕተቱን ላለመቀበል ከመከራከር ወይም በሌላ ሰው ላይ ከማሳበብ ይልቅ ስሕተቱ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት ለመቀበል ዝግጁዎች እንድንሆን ያደርገናል። አዳም በሔዋን ቢያሳብብም ዳዊት ‘እኔ ምን ላድርግ፤ ግልጽ ቦታ ላይ መታጠብ አልነበረባትም’ በማለት በቤርሳቤህ አላሳበበም። (ዘፍጥረት 3:12፤ 2 ሳሙኤል 11:2–4) በእውነትም በአንድ በኩል ሐቀኛ መሆን ትሑት ለመሆን ሲረዳ በሌላ በኩል ደግሞ ትሑት መሆን ሐቀኛ ለመሆን ይረዳል ሊባል ይቻላል።
በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ትሑቶች እንድንሆን ይረዳናል
6, 7. በአምላክ ላይ ያለን እምነት ትሑቶች እንድንሆን የሚያግዘን እንዴት ነው?
6 በይሖዋ ላይ ያለን እምነትም ትሑቶች እንድንሆን ይረዳናል። የጽንፈ ዓለሙ ልዑል ገዥ ታላቁ ፈጣሪ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ መገንዘባችን ራሳችንን በጣም ከፍ አድርገን ከመመልከት ይጠብቀናል። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ነጥብ በጥሩ ሁኔታ አስገንዝቦናል። በኢሳይያስ 40:15, 22 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “እነሆ፣ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፣ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቆጥረዋል፤ . . . እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፣ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው።”
7 በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ፍትሕ እንደተጓደለብን በሚሰማን ጊዜ ሊረዳን ይችላል። በጉዳዩ ከመበሳጨት ይልቅ መዝሙራዊው በመዝሙር 37:1–3, 8, 9 ላይ እንደሚያሳስበን ይሖዋ የሚያደርገውን በትሕትና እንጠባበቃለን። ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ ነጥብ ጠቅሷል:- “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።” — ሮሜ 12:19
ትሕትና የጥበብ መንገድ ነው
8. ትሕትና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን የሚያደርገው ለምንድን ነው?
8 ትሕትና የጥበብ መንገድ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንዱ ምክንያት ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከፈጣሪያችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን መርዳቱ ነው። የአምላክ ቃል በምሳሌ 16:5 ላይ “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው” በማለት በግልጽ ይናገራል። በተጨማሪም በምሳሌ 16:18 ላይ “ትዕቢት ጥፋትን ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” የሚል ቃል እናነባለን። ይፍጠንም ይዘግይ ኩሩ ሰው ኀዘን ላይ መውደቁ አይቀርም። ይህም መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም በ1 ጴጥሮስ 5:5 “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል። ኢየሱስ በየግላቸው ይጸልዩ ስለነበሩት ስለ ፈሪሳዊውና ስለ ቀራጩ በተናገረው ምሳሌ ላይም ይህ ነጥብ ተገልጿል። ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ የተቆጠረው ትሑቱ ቀራጭ ነበር። — ሉቃስ 18:9–14
9. በመከራ ጊዜ ትሕትና እንዴት ይረዳናል?
9 ትሕትና የጥበብ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም በያዕቆብ 4:7 ላይ የሚገኘውን “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ” የሚለውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል የበለጠ ቀላል ያደርገልናል። ትሑቶች ከሆንን መከራ እንዲደርስብን ይሖዋ በሚፈቅድበት ጊዜ አናምፅም። ትሕትና በምንኖርበት ሁኔታ እንድንረካና እንድንጸና ያስችለናል። ኩሩ ሰው አይረካም፤ ሁልጊዜ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ይፈልጋል፣ የሚያሳዝነው ሁኔታ ሲያጋጥመው ያምፃል። በሌላ በኩል ደግሞ ትሑት ሰው ኢዮብ እንዳደረገው መከራና ችግር ሲደርስበት ይጸናል። ኢዮብ ንብረቱን ሁሉ አጥቶና በጣም በሚያሠቅቅ ደዌ ተመትቶ እያለ ሚስቱ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” በማለት የትዕቢት መንገድ እንዲከተል መከረችው። ኢዮብ እንዴት ያለ መልስ ሰጠ? የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “እርሱ ግን:- አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።” (ኢዮብ 2:9, 10) ኢዮብ ትሑት ሰው ስለነበረ አላመፀም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በእርሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደውን ነገር ሁሉ ተቀበለ። በመጨረሻም ታላቅ በረከት አገኘ። — ኢዮብ 42:10–16፤ ያዕቆብ 5:11
ትሕትና ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያደርጋል
10. ትሕትና ከክርስቲያን ባልደረቦቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻሽልልን እንዴት ነው?
10 ትሕትና ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ስለሚያስችል የጥበብ መንገድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተገቢ ምክር ሰጥቶናል:- “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።” (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) ትሕትና ከሌሎች ጋር ከመፎካከር ወይም በልጠን ለመታየት ከመሞከር እንድንርቅ ያደርገናል። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ለእኛም ሆነ ለሌሎች ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ችግር ሊፈጥር ይችላል።
11. ትሕትና ስሕተት ከመሥራት እንድንርቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
11 በብዙ ሁኔታዎች ትሕትና ስሕተት ከመሥራት እንድንርቅ ይረዳናል። እንዴት? ምክንያቱም ትሕትና ከልክ በላይ በራሳችን እንዳንመካ ስለሚያደርገን ነው። ከዚህ ይልቅ በ1 ቆሮንቶስ 10:12 ላይ ያለውን “እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር እንከተላለን። ኩሩ ሰው ከልክ በላይ በራሱ ይመካል። በዚህም ምክንያት ከውጭ በሚመጣ ግፊትም ይሁን በራሱ ድክመት ስሕተት መሥራት ይቀናዋል።
12. ትሕትና የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ እንድናሟላ ይገፋፋናል?
12 ትሕትና ለራስነት ሥርዓት የመገዛትን ብቃት እንድናሟላ ይረዳናል። ኤፌሶን 5:21 “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ” ሲል ይመክረናል። ሁላችንም የራስነትን ሥርዓት ማክበር ያስፈልገን የለምን? ልጆች ለወላጆቻቸው መገዛት አለባቸው። ሚስቶች ለባሎቻቸው፣ ባሎች ደግሞ ለክርስቶስ መገዛት አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:22፤ 6:1) የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች በሙሉ፣ ዲያቆናትም ጭምር ለሽማግሌዎች መገዛት አለባቸው። ሽማግሌዎች በተራቸው በክልል የበላይ ተመልካች ለሚወከለው ታማኝ ባሪያ ይገዙ የለምን? የክልል የበላይ ተመልካች ደግሞ ለወረዳ የበላይ ተመልካች፣ የወረዳው የበላይ ተመልካችም በሚያገለግልበት ክልል ላለው የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ይገዛል። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላትስ ለማን ይገዛሉ? እነርሱ ደግሞ “አንዳቸው ለሌላው” እና ለአስተዳደር አካሉ ይገዛሉ። የአስተዳደር አካሉም “ታማኝና ልባም ባሪያ”ን ሲወክል እርሱ ደግሞ በተራው ለንጉሡ ለኢየሱስ መልስ ይሰጣል። (ማቴዎስ 24:45–47) የአስተዳደር ክፍል አባላትም በማንኛውም የሽማግሌዎች አካል ላይ እንደሚታየው አንዳቸው የሌላውን አመለካከት ያከብራሉ። ለምሳሌ አንዱ አባል በጣም ጥሩ ሐሳብ እንዳለው ያስብ ይሆናል። ነገር ግን ባቀረበው ሐሳብ ላይ በቂ ቁጥር ያላቸው አባላት ካልተስማሙበት ሐሳቡን መተው ይኖርበታል። በእውነትም ሁላችንም ተገዥዎች ስለሆንን ሁላችንም ትሕትና ያስፈልገናል።
13, 14. (ሀ) ትሕትና የሚረዳን የትኛው ልዩ ሁኔታ ሲያጋጥመን ነው? (ለ) ምክር በመቀበል ረገድ ጴጥሮስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
13 በተለይ ትሕትና ምክርና ተግሣጽ መቀበልን ቀላል ስለሚያደርግ የጥበብ መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው። ሁላችንም አልፎ አልፎ ተግሣጽ ያስፈልገናል። ስለሆነም በምሳሌ 19:20 ላይ “ምክርን ስማ፣ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ” የሚለውን ምክር መከተል አለብን። አስቀድሞ በዝርዝር እንደተመለከተው ትሑቶች ሲወቀሱ ወይም ሲገሠጹ አይከፋቸውም። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 12:4–11 ላይ ተግሣጽን በትሕትና መቀበል ጥበብ መሆኑን በመግለጽ መክሮናል። የወደፊቱን መንገዳችንን በጥሩ ሁኔታ ማቅናት የምንችለውና በምላሹም የዘላለም ሕይወትን ሽልማት ማግኘት የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ውጤት ይሆንልናል።
14 በዚህ ረገድ የሐዋርያው ጴጥሮስን ምሳሌ ልንጠቅስ እንችላለን። ከገላትያ 2:14 እንደምንረዳው በጣም ከባድ የሆነ ወቀሳ ከሐዋርያው ጳውሎስ ተቀብሏል። “ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን [ጴጥሮስን]:- አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፣ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት” ብሏል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ተከፍቶ ነበርን? በጊዜው ተከፍቶ እንኳ ቢሆን ቅሬታው ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ” ብሎ እንደጠራው በ2 ጴጥሮስ 3:15, 16 ላይ መመልከት ይቻላል።
15. ትሑታን በመሆናችንና በደስተኝነታችን መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
15 በተጨማሪም በቃኝ የማለት ወይም በትንሽ ነገር ረክቶ የመኖር ጉዳይም አለ። በኑሮአችን፣ በአገልግሎት መብታችን ወይም በተሰጠን በረከት ካልረካን ደስተኞች ልንሆን አንችልም። ትሑት ክርስቲያን “አምላክ ከፈቀደው እቀበለዋለሁ” የሚል ዝንባሌ ሊያድርበት ይገባል። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ ከተናገረው ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ እናነባለን:- “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” አሁንም በድጋሚ ትሕትና የጥበብ መንገድ የሆነበትን ምክንያት ለማየት እንችላለን። ምክንያቱም በኑሮአችን ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል።
ፍቅር ትሑቶች እንድንሆን ይረዳናል
16, 17. (ሀ) ትሑት እንድንሆን የሚረዳንን ከሁሉ የሚበልጥ ጠባይ ጎላ አድርጎ የሚያሳየው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ነው? (ለ) ይህንኑ ነጥብ የሚያስረዳ ምን ዓለማዊ ምሳሌ አለ?
16 ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ትሑቶች እንድንሆን የሚረዳን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማለትም አጋፔ ነው። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች እንደገለጸው ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ የደረሰበትን መከራ በሙሉ በትሕትና ጸንቶ የተቀበለው ለምን ነበር? (ፊልጵስዩስ 2:5–8) ከአምላክ ጋር እኩል የመሆን ሐሳብ ፈጽሞ ያልመጣለት ለምን ነበር? እሱ ራሱ እንደተናገረው ‘አብን ስለሚወድ’ ነበር። (ዮሐንስ 14:31) በማንኛውም ጊዜ ክብርና ምስጋና ለሰማያዊ አባቱ ለይሖዋ እንዲሰጥ ያደርግ የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። ከዚህም የተነሣ በአንድ ወቅት ከሰማዩ አባቱ በቀር ጥሩ እንደሌለ አጠንክሮ ተናግሯል። — ሉቃስ 18:18, 19
17 ይህንን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ከጥንቶቹ የአሜሪካ ገጣሚዎች አንዱ የሆኑት ጆን ግረንለፍ ዊቲየር ያጋጠማቸውን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል። እኚህ ሰው በልጅነታቸው አንዲት ወዳጅ ነበረቻቸው። አንድ ቀን ስለ ቃላት አጻጻፍ ውድድር በሚደረግበት ጨዋታ ላይ እሳቸው የተሳሳቱትን ቃል አጻጻፍ እርስዋ በትክክል ጻፈች። በውጤቱ በጣም አዘነች። ለምን ነበር ያዘነችው? “ያንን ቃል በትክክል በመጻፌ አዝናለሁ። ከአንተ በላይ መሆን ያስጠላኛል። . . . ምክንያቱ ይገባሃል? ስለምወድህ ነው” ማለቷን ባለቅኔው አስታውሰዋል። አዎን፣ አንድን ሰው የምንወደው ከሆነ ያ ሰው የበላያችን እንዲሆን እንጂ የእኛ የበታች እንዲሆን አንፈልግም፤ ምክንያቱም ፍቅር ትሑት ነው።
18. ትሕትና የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንድንከተል ይረዳናል?
18 ይህ ለሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም ለወንድሞች ጥሩ ትምህርት ይዟል። ከእኛ ይልቅ ሌላው ወንድማችን የተለየ የአገልግሎት መብት ሲሰጠው ደስ ይለናል ወይስ የቅናትና የምቀኝነት ስሜት በውስጣችን ይሰማናል? ወንድማችንን በእውነት የምንወደው ከሆነ ያንን ልዩ የሥራ ምድብ ወይም እውቅና ወይም የአገልግሎት መብት በማግኘቱ ደስ ይለናል። አዎን፣ ትሕትና “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” የሚለውን ምክር ለመከተል ቀላል ያደርግልናል። (ሮሜ 12:10) ሌላው ትርጉም “አንዳችሁ ሌላውን ከራሳችሁ በላይ አድርጋችሁ አክብሩ” ይላል። (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ) እንደገናም “በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” ተብለን በሐዋርያው ጳውሎስ ተመክረናል። (ገላትያ 5:13) አዎን፣ ፍቅር ካለን ወንድሞቻችንን ማገልገል፣ ለእነሱ ባሪያ መሆንና ከራሳችን ይልቅ የእነርሱን ደኅንነትና ፍላጎት ማስቀደም ደስ ይለናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ትሕትና ያስፈልጋል። በተጨማሪም ትሕትና ጉራ ከመንዛትና በሌሎች ውስጥ የቅንዓትና የምቀኝነት መንፈስ ከማነሣሳት እንድንርቅ ያደርገናል። ጳውሎስ ፍቅር “አይመካም፣ አይታበይም” በማለት ጽፏል። ለምን? ምክንያቱም አንድ ሰው ጉረኛና ኩሩ እንዲሆን የሚያደርገው ራስ ወዳድነት ስለሆነ ነው። ፍቅር ደግሞ በባሕርዩ ከራስ ወዳድነት ፈጽሞ የራቀ ነው። — 1 ቆሮንቶስ 13:4
19. ትዕቢትና ራስ ወዳድነት ጎን ለጎን እንደሚሄዱ ሁሉ ትሕትናና ፍቅርም አብረው የሚሄዱ ነገሮች መሆናቸውን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ያስረዳል?
19 ዳዊት ከንጉሥ ሳኦልና ከልጁ ከዮናታን ጋር የነበረው ዝምድና ፍቅርና ትሕትና፣ በአንጻሩ ደግሞ ትዕቢትና ራስ ወዳድነት እንዴት ጎን ለጎን እንደሚሄዱ አስገራሚ የሆነ ምሳሌ ይዞልናል። ዳዊት በጦርነት ድል በማድረጉ በእስራኤል የነበሩ ሴቶች “ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም እልፍ ገደለ” እያሉ ይዘፍኑ ነበር። (1 ሳሙኤል 18:7) ሳኦል ትሑት በመሆን ፈንታ በትዕቢት ተውጦ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ እስከ ግድያ የሚያደርስ ከባድ ጥላቻ አደረበት። ይህ ደግሞ ልጁ ዮናታን ከነበረው መንፈስ በጣም የተለየ ነበር። ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ እንደ ወደደው እናነባለን። (1 ሳሙኤል 18:1) ታዲያ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይሖዋ ዳዊትን እየባረከውና ሳኦልን የሚተካው የእስራኤል ንጉሥ ዮናታን ሳይሆን ዳዊት እንደሚሆን ግልጽ እየሆነ ሲመጣ ዮናታን እንዴት ተሰማው? ዮናታን የቅንዓት ወይም የምቀኝነት ስሜት ተሰማውን? በጭራሽ አልተሰማውም! ለዳዊት ከነበረው ከፍተኛ ፍቅር የተነሣ በ1 ሳሙኤል 23:17 ላይ እንደምናነበው “የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፤ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፣ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፤ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል” ሊለው ችሏል። ዮናታን ለዳዊት የነበረው ከፍተኛ ፍቅር አባቱን የሚተካው የእስራኤል ንጉሥ ማን ስለ መሆኑ አምላክ የፈቀደውን በትሕትና ተቀብሏል።
20. ኢየሱስ ትሕትናና ፍቅር በጣም የተቀራረበ ዝምድና እንዳላቸው እንዴት አሳየ?
20 በፍቅርና በትሕትና መካከል ያለውን ዝምድና የሚያጎላልን ተጨማሪ ነጥብ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት የሆነው ነገር ነው። በዮሐንስ 13:1 ላይ “በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” የሚል ቃል እናነባለን። ከዚያ ቀጥሎ ኢየሱስ አንድ ዝቅተኛ ባሪያ እንደሚያደርገው የሐዋርያቱን እግር እንዳጠበ እንናነባለን። ትሕትናን የሚመለከት እንዴት ያለ ኃይለኛ ትምህርት ነው! — ዮሐንስ 13:1–11
21. ለማጠቃለል ያህል ትሑት መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
21 በእውነትም ትሑታን የምንሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ትሑት መሆን ትክክለኛና ሐቀኛ መሆን ነው። ትሕትና የእምነት መንገድም ነው። ከይሖዋ አምላክና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችላል። ትሕትና የጥበብ መንገድ ነው። ከሁሉም በላይ ትሕትና የፍቅር መንገድ ስለሆነ እውነተኛ ደስታ ያመጣልናል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ትሑት በመሆን ረገድ ሐቀኝነት በምን መንገዶች ይረዳል?
◻ በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ትሑት እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ ትሑት መሆን የጥበብ መንገድ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
◻ ትሑት እንድንሆን በተለይ ፍቅር የሚረዳን ለምንድን ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ በትሕትና ራሱን ለይሖዋ አስገዛ። ‘ አምላክን ሰድቦ አልሞተም’
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ ጴጥሮስን በሰዎች ፊት በገሠጸው ጊዜ ጴጥሮስ ተግሣጹን በትሕትና ተቀብሏል