አስጨናቂ ለሆነው ዘመናችን የሚጠቅም ትምህርት
“በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። . . . ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13
1, 2. የምንከተለው ትምህርት ይህን ያህል የሚያሳስበን ለምንድን ነው?
እየረዳህ ነው ወይስ እየጎዳህ? ለችግሮችህ መፍትሔ አምጥቶልሃል ወይስ አባብሷቸዋል? ‘ምኑ?’ ትል ይሆናል። የምታገኘው ትምህርት። አዎን፣ ትምህርት ሕይወትህን ሊያሻሽል ወይም ሊያበላሽ ይችላል።
2 በቅርቡ ሦስት ተባባሪ ፕሮፌሰሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ የጥናታቸውን ውጤት ጆርናል ፎር ዘ ሳይንቲፊክ ስተዲ ኦቭ ሪሊጅን በተባለው መጽሔት ላይ አውጥተው ነበር። እነዚህ ምሁራን በአንተ ወይም በቤተሰብህ ላይ ይህን ጥናት እንዳላደረጉ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የጥናታቸው ውጤት አንድ ሰው በየጊዜው የሚያገኘው ትምህርት አስጨናቂ የሆነውን ዘመናችንን ለመቋቋም ከመቻሉና ካለመቻሉ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያሳያል። ምሁራኑ በምርምራቸው ያገኙትን ውጤት በሚቀጥለው ርዕስ እንመለከታለን።
3, 4. በአስጨናቂ ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
3 በቅድሚያ ግን ይህን ጥያቄ እንመልከት፦ የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው ቢባል ትስማማለህ? በዚህ የምትስማማ ከሆነ ጊዜያችን አስጨናቂ ዘመን መሆኑን የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች እንደሚታዩህ የተረጋገጠ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ይህ አስጨናቂ ዘመን ሰዎችን የሚነካው በተለያየ መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖች ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመያዝ በሚያደርጉት ፍልሚያ ሳቢያ በመፈራረስ ላይ የሚገኙ አገሮች እንዳሉ ሳታውቅ አትቀርም። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሰዎች እርስ በርስ የሚገዳደሉት ከሃይማኖት ወይም ከዘር ልዩነት የተነሳ ነው። በእነዚህ ጦርነቶች የሚጎዱት ወታደሮች ብቻ አይደሉም። ቁጥር ስፍር የሌላቸው ልጃገረዶችና ትልልቅ ሴቶች ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። እጅግ ብዙ አረጋውያን ምግብ፣ መጠለያና ሙቀት እንዳያገኙ ተደርገዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ብዙ መከራ ይደርስባቸዋል። በዚህ ምክንያት የስደተኞች ቁጥር በጣም ጨምሯል፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች አሉ።
4 ከዚህም ሌላ ጊዜያችን ሰዎች በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር የተዘፈቁበት ዘመን ነው። ይህም በመሆኑ ፋብሪካዎች ተዘግተዋል፣ ሥራ አጥነት በዝቷል፣ ብዙ ሰዎች የጡረታና የሥራ መብቶቻቸውን ተነፍገዋል፤ የገንዘብ ዋጋ አሽቆልቁሏል፤ እንዲሁም ሰዎች የሚመገቧቸውን ምግቦች በዓይነትም ሆነ በመጠን ለመቀነስ ተገድደዋል። ሌሎች ችግሮች መጥቀስ ትችላለህ? አዎን፣ ይቻላል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ እጥረትና በበሽታ ይሰቃያሉ። በረሀብ አጥንታቸው የወጣ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናትን የሚያሳዩ ከምሥራቅ አፍሪካ የሚመጡ ዘግናኝ ፎቶግራፎችን ተመልክተህ ይሆናል። በእስያ ውስጥም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተመሳሳይ የችግር አለንጋ ይገረፋሉ።
5, 6. በሽታ የአስጨናቂው ዘመናችን አንዱ አስፈሪ ሁኔታ ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
5 ሁላችንም በመዛመት ላይ ስለሚገኙት አስፈሪ በሽታዎች ሰምተናል። በጥር 25, 1993 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ሲል አትቷል፦ “በላቲን አሜሪካ ያለው የኤድስ ወረርሽኝ ሥርጭት በአህጉሩ ተስፋፍቶ በሚገኘው ሕገ ወጥ ሩካቤ ሥጋ፣ ግብዝነት እንዲሁም በሽታውን ለመከላከል በቂ ጥረት ባለመደረጉ ምክንያት ከዩናይትድ ስቴትስ ሊበልጥ ተቃርቧል። . . . የበሽታው ሥርጭት ይህን ያህል የበዛው በበሽታው የሚለከፉ . . . ሴቶች ቁጥር በጣም ስለጨመረ ነው።” ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት ባለፈው ጥቅምት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የዩናይትድ ስቴትስ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ‘አሁን ስለ ተላላፊ በሽታዎች ከመጨነቅ የምናቆምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል’ በማለት በጤና አጠባበቅ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ድል መገኘቱን ካበሰሩ ገና ሃያ ዓመታቸው ነው።” ታዲያ አሁን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ሪፖርቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ሆስፒታሎች ‘ድል ተመትተው ጠፍተዋል’ በተባሉ በሽታዎች በሚሰቃዩ ሰዎች እንደገና ተጥለቅልቀዋል። . . . ማይክሮቦች እነርሱን ለማጥፋት ከሚፈለሰፉ አዳዲስ መድኃኒቶች ቀድመው ለመገኘት የሚያስችላቸውን የረቀቀ ባሕርይ በማዳበር ላይ ናቸው። . . . ‘ወደ አዲስ የተላላፊ በሽታዎች ዘመን በመሸጋገር ላይ ነን።’”
6 አንድ ምሳሌ እንጥቀስ። የጥር 11, 1993 ኒውስ ዊክ መጽሔት የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቦ ነበር፦ “በአሁኑ ጊዜ የወባ ተባዮች በየዓመቱ 270 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን ሲለክፉ 2 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን ይገድላሉ ተብሎ ይገመታል። . . . በአጣዳፊ ሁኔታ የሚታመሙትም ሰዎች ቁጥር በትንሹ 100 ሚልዮን ይደርሳል። . . . ይህ በእንዲህ እንዳለ በሽታው በፊት ፈዋሽ የነበሩትን መድኃኒቶች የሚቋቋምበትን ኃይል ይበልጥ እያዳበረ ሄዷል። . . . አንዳንድ የወባ ዓይነቶች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈውስ ሊገኝላቸው የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ።” በፍርሃት የሚያንቀጠቅጥ ዘገባ ነው።
7. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የሚያጋጥማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት እየሞከሩ ያሉት እንዴት ነው?
7 ብዙ ሰዎች በዚህ አስጨናቂ ዘመን ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማግኘት ሲሯሯጡ ሳትመለከት አልቀረህም። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች በመጻሕፍት በመታገዝ ጭንቀትን ወይም አንድን ዓይነት አዲስ በሽታ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ዘዴ ለማግኘት ይጥራሉ። ሌሎች ደግሞ ጋብቻቸውን ከመፍረስ ለማዳን፣ ስለ ሕፃናት አስተዳደግ፣ ከአልኮል ወይም ከዕፅ ሱሰኝነት ለመገላገል ወይም የሥራ ጫናቸውን ቤት ውስጥ ከሚሰማቸው ውጥረት አንፃር ሚዛናዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ምክር ማግኘት እንደማይችሉ በማሰብ ተስፋ ቆርጠዋል። አዎን፣ በእርግጥ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል! አንተስ ከአንድ ዓይነት የግል ችግር ጋር እየታገልክ ነህን? ወይም ጦርነት፣ ረሀብ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ያስከተለው መከራ ደርሶብህ ይሆን? ያጋጠመህ ችግር መፍትሔ የማይገኝለት መስሎ ቢታይህም ‘እንዲህ ባለው አስጨናቂ ዘመን ላይ የደረስነው ለምንድን ነው?’ ብለህ ለመጠየቅ ትገደዳለህ።
8. ጥልቅ ማስተዋልና መመሪያ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ማለት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
8 እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋምና አሁን ከምንኖረውም ሆነ ከወደፊቱ ሕይወታችን እርካታ ለማግኘት ከመቻላችን በፊት ይህን በመሰለው አስጨናቂ ዘመን ውስጥ የምንኖርበትን ምክንያት ማወቅ ያስፈልገናል። ይህን ለማወቅ ደግሞ እያንዳንዳችን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል ብለን መጠየቅና መመርመር ይኖርብናል። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የምናመለክተው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህን በመሰለ ችግር ውስጥ የተዘፈቅንበትን ምክንያት፣ በዘመናት ሂደት ውስጥ በምን ነጥብ ላይ እንደምንገኝና የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ የሚገልጽ ትክክለኛ ትንቢት ማለትም በቅድሚያ የተጻፈ ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ስለሆነ ነው።
ከታሪክ የምናገኘው ትምህርት
9, 10. በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?
9 በየካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ በሚገኘው የኢየሱስ ዋነኛ ትንቢት ላይ ጥሩ ጥናት ቀርቦ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ይህንን ምዕራፍ ብታወጣ በቁጥር 3 ላይ ኢየሱስ ወደፊት የሚገኝበትን ጊዜና የነገሮችን ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ምልክት እንዲነግራቸው ሐዋርያቱ ጠይቀውት እንደነበረ መመልከት ትችላለህ። ከዚያ ከቁጥር 5 እስከ 14 ላይ ኢየሱስ ሐሰተኛ ክርስቶሶች እንደሚነሱ፣ ጦርነትና የምግብ እጥረት እንደሚኖር፣ ዓመፅ እንደሚስፋፋና ክርስቲያኖች እንደሚሰደዱ፣ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት በሰፊው እንደሚሰበክ ተነበየ።
10 እነዚህ ነገሮች በአይሁድ የነገሮች ሥርዓት የመደምደሚያ ቀኖች ውስጥ ተፈጽመው እንደነበረ ታሪክ ያረጋግጣል። በዚያ ዘመን ብትኖር ኖሮ ያ ዘመን አስጨናቂ አይሆንብህም ነበርን? ይሁን እንጂ ሁኔታዎቹ ገና ወደ ከፍተኛ መደምደሚያቸው በመገስገስ ላይ ነበሩ። በኢየሩሳሌምና በአይሁድ ሥርዓት ላይ አቻ የማይገኝለት መከራ በማንዣበብ ላይ ነበር። በቁጥር 15 ላይ ሮማውያን በ66 እዘአ ኢየሩሳሌምን ካጠቁ በኋላ የሆነውን ነገር እናነባለን። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ በቁጥር 21 ላይ የተናገረው መከራ በመጣ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ደረጃው ደረሰ። ይህም በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው መከራ ሲሆን ከተማዋን ካጋጠሟት መከራዎች ሁሉ የሚበልጥ መከራ ነበር። ያም ሆኖ ግን የሰው ልጅ ታሪክ በዚህ እልቂት እንዳላበቃ ታውቃለህ። ኢየሱስም ቢሆን በዚሁ ያበቃል አላለም። ከቁጥር 23 እስከ 28 ላይ በ70 እዘአ ከደረሰው መከራ በኋላ ሌሎች ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተናግሯል።
11. ማቴዎስ ምዕራፍ 24 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ያገኘው ፍጻሜ ከዘመናችን ጋር የሚያያዘው በምን መንገድ ነው?
11 ዛሬ አንዳንዶች ‘ታዲያ ይህ ምን ያስደንቃል?’ ብለው ሊያልፉት ይችላሉ። ነገሩን እንዲህ ብሎ ማለፍ ግን ስህተት ነው። ትንቢቱ በዚያን ጊዜ መፈጸሙ ትልቅ ቁም ነገር አለው። እንዴት? በአይሁድ ሥርዓት ማክተሚያ ላይ የተከሰተው ጦርነት፣ ረሀብ፣ የምድር መናወጥ፣ ቸነፈርና ስደት የአሕዛብ ዘመን ካበቃበት ከ1914 ወዲህ ባለው ዘመን ውስጥ በበለጠ ደረጃ መፈጸም ስለነበረበት ነው። (ሉቃስ 21:24) ዛሬ በሕይወት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ትንቢቱ ዘመናዊ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረበትን አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተመልክተዋል። የተወለድከው ከ1914 ወዲህ ቢሆንም እንኳ የኢየሱስ ትንቢት ሲፈጸም አይተሃል። እነዚህ ሁኔታዎች በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ያረጋግጣሉ። በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ የሚታዩት ሁኔታዎች በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ውስጥ እንደምንኖር በሚገባ ያረጋግጣሉ።
12. ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ገና ምን እንደሚመጣ ልንጠብቅ እንችላለን?
12 እንግዲያው በማቴዎስ 24:29 ላይ የተጠቀሰው “ታላቅ መከራ” ከፊታችን ተደቅኗል ማለት ነው። መከራው አሁን መገመት የማንችላቸውን በሰማይ ላይ የሚታዩ ልዩ ክስተቶችንም የሚጨምር ይሆናል። በዚያ ጊዜ ሰዎች አንድ የተለየ ምልክት እንደሚያዩ፤ ይኸውም ጥፋታቸው የቀረበ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት እንደሚያዩ ቁጥር 30 ያመለክታል። ስለዚሁ ጉዳይ በሚተርከው በሉቃስ 21:25–28 መሠረት በዚያ ጊዜ ሰዎች ‘በምድር ላይ የሚፈጸመውን ከመጠበቅ የተነሣ በፍርሃት ይደክማሉ።’ በተጨማሪም የሉቃስ ትረካ ክርስቲያኖች መዳናቸው መቅረቡን ስለሚያውቁ ራሳቸውን ቀና እንደሚያደርጉ ይገልጻል።
13. ልናተኩር የሚገባን በትኞቹ ሁለት ቁልፍ ነጥቦች ላይ ነው?
13 ‘በዚህ እስማማለሁ። የተነሣው ጥያቄ ግን ይህን አስቸጋሪ ዘመን ለመረዳትና ለመቋቋም የምችለው እንዴት ነው? የሚል አልነበረም?’ ትል ይሆናል። ትክክል ነህ። የተነሣንበት ዋና ነጥብ መሠረታዊ የሆኑትን ችግሮችን ለይቶ ማወቅና እነርሱን መከላከል የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው። ከሁለተኛው ነጥብ ጋር የተያያዘው ሌላው ነገር ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እንድንኖር ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? የሚል ነው። ከዚህ ጋር በማያያዝ መጽሐፍ ቅዱስህን ከፍተህ 2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ አውጣና ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ነገር ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እንድትቋቋም እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል ተመልከት።
ስለ ጊዜያችን የተነገረ ትንቢት
14. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1–5ን ማጥናታችን ይጠቅመናል ብለን ለማመን ምክንያት የሚኖረን ለምንድን ነው?
14 አምላክ ሐዋርያው ጳውሎስን በመንፈሱ በማነሳሳት ጢሞቴዎስ የተባለው ታማኝ ክርስቲያን የተሳካና አስደሳች ሕይወት ለመኖር የሚያስችለውን ጥሩ ምክር እንዲጽፍለት አድርጎ ነበር። ጳውሎስ ከጻፋቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ዋነኛ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በዘመናችን ነው። እነዚህን ትንቢታዊ ቃላት ቀደም ብለህ እንደምታውቃቸው ቢሰማህም እንኳን በሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የሚገኘውን ትንቢታዊ ቃል ልብ በለው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው [ታማኝነት የጎደላቸው፣ አዓት] [የተፈጥሮ አዓት] ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል።”
15. አሁን በ2 ጢሞቴዎስ 3:1 ላይ ይበልጥ የምናተኩረው ለምንድን ነው?
15 እዚህ ላይ የተዘረዘሩት 19 ነገሮች እንደሆኑ ልብ በል። እነዚህን ነገሮች ከመመርመራችንና ከምርመራችን የምናገኘውን ጥቅም ከመመልከታችን በፊት ወደኋላ መለስ ብለን የትንቢቱን አጠቃላይ ሁኔታ እንመልከት። ቁጥር 1ን ተመልከት። ጳውሎስ ወደፊት ምን እንደሚሆን ሲናገር ‘በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን ይመጣል’ ብሏል። የትኛው ‘የመጨረሻ ቀን’ ነው? በርካታ የመጨረሻ ቀኖች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የጥንትዋ ፖምፔ የመጨረሻ ቀን ነበራት፤ ብዙ ነገሥታት ወይም የገዥ መደቦችም የመጨረሻ ቀን ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስም የብዙ የተለያዩ ነገሮችን የመጨረሻ ቀን ይጠቅሳል። ከእነዚህም አንዱ የአይሁድ ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ነው። (ሥራ 2:16, 17) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረለት የመጨረሻ ቀን የኛ ዘመን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችለንን መሠረት ኢየሱስ ሰጥቶናል።
16. በስንዴውና በእንክርዳዱ ምሳሌ የተተነበየው በዘመናችን የሚኖረው የትኛው ሁኔታ ነው?
16 ኢየሱስ ይህን የገለጸው ስለ ስንዴና እንክርዳድ የሚገልጽ ምሳሌ በተናገረ ጊዜ ነበር። ስንዴውና እንክርዳዱ በአንድ የእርሻ መሬት ላይ ተዘርተው እንዲበቅሉ ተተዉ። ስንዴውና እንክርዳዱ ሰዎችን ማለትም እውነተኛና ሐሰተኛ ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክቱ ኢየሱስ ተናገረ። ይህን እዚህ ላይ ያነሣነው ምሳሌው የመላው ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ ከመድረሱ በፊት ረጅም ዘመን የሚያልፍ መሆኑን ስለሚያረጋግጥልን ነው። ይህ የመደምደሚያ ጊዜ ሲደርስ በደንብ ተስፋፍቶ የሚገኝ አንድ ነገር ይኖራል። ይህ ነገር ምንድን ነው? ክህደት ወይም ከእውነተኛ ክርስትና መራቅ ነው። ይህም እጅግ የበዛ የክፋት ፍሬ የሚያስገኝ ይሆናል። ይህ የሚፈጸመው ምድር አቀፍ በሆነ በአንድ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ ሌሎች ትንቢቶችም ያረጋግጣሉ። ዛሬ የምንገኘው በዚያ ጊዜ ማለትም በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ላይ ነው።—ማቴዎስ 13:24–30, 36–43
17. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1–5 ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምን ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጠናል?
17 ይህ ምን ትርጉም እንደሚኖረው አስተዋልክ? ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1–5 በሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን ወይም በመጨረሻው ቀን ክርስቲያኖች መጥፎ በሆነ ፍሬ እንደሚከበቡ ያመለክታል። ጳውሎስ፣ መጨረሻው ቀን መድረሱን የሚያረጋግጡት ዋነኛ ምልክቶች እነዚህ 19 ነገሮች እንደሚሆኑ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በዚህ የመጨረሻ ቀን ከምን ዓይነት ሁኔታዎች ጋር መታገል እንደሚኖርብን ማስጠንቀቁ ነበር። ቁጥር 1 “አስጨናቂ ዘመን” እንደሚመጣ ይናገራል። ይህ ሐረግ ከግሪክኛ የተወሰደ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “አስፈሪ ቀነ ቀጠሮ” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊንየር) “አስፈሪ” የሚለው ቃል በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሁኔታ በትክክል ይገልጻል ቢባል አትስማማም? ይህ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ መግለጫ ዘመናችንን የሚመለከቱ መለኮታዊ የሆኑ ተጨማሪ መግለጫዎችን ይሰጣል።
18. የጳውሎስን ትንቢታዊ ቃላት ስናጠና ይበልጥ ልናተኩር የሚገባን በምን ላይ ነው?
18 ይህን ትንቢት መመርመራችን ጊዜያችን ምን ያህል አስጨናቂ ወይም አስፈሪ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ አሳዛኝ ምሳሌዎችን እንድንመለከት ያደርገናል። የተነሣንባቸውን ሁለት ቁልፍ ነጥቦች አስታውሱ፦ (1) ጊዜያችንን ከባድ ዘመን ያደረጉትን ችግሮች ለይቶ ማወቅና ችግሮቹን እንዴት ልንከላከል እንደምንችል ማስተዋል፣ (2) ተግባራዊ ሊሆኑና የተሻለ ኑሮ ለመኖር የሚረዱንን ትምህርቶች መከተል ናቸው። ስለዚህ አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ደጋግመን ከመጥቀስ ይልቅ በዚህ “አስጨናቂ ዘመን” እኛንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ሊጠቅሙ በሚችሉ ትምህርቶች ላይ እናተኩራለን።
ብዙ ጥቅሞችን አግኝ
19. ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ ተመልክተሃል?
19 ጳውሎስ ዝርዝሩን የሚጀምረው በመጨረሻው ቀን “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ በመናገር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2) ምን ማለቱ ነው? በታሪክ ዘመናት ሁሉ ራስ ወዳድና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ ወንዶችና ሴቶች የጠፉበት ጊዜ አልነበረም ትል ይሆናል፤ ትክክል ነህ። ሆኖም ይህ መጥፎ ጠባይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ጥርጥር የለውም። ብዙዎች በጣም ብሶባቸዋል። ራስ ወዳድነት በፖለቲካውና በንግዱ ዓለም ውስጥ የተለመደና እንደ ትክክለኛ ነገር የሚታይ ሆኗል። ወንዶችና ሴቶች በሌሎች ላይ ምንም ዓይነት ኪሣራና ጉዳት ያስከትል ሥልጣንና ዝና ለማግኘት ይሯሯጣሉ። እነዚህ ራስ ወዳድ ሰዎች በሌሎች ላይ ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት ምንም ደንታ የላቸውም። ሌሎችን ለመክሰስ ወይም ለማታለል ፈጣኖች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ በጣም የተስፋፋ ከመሆኑ የተነሣ ብዙዎች ይህን ትውልድ “ለእኔ ብቻ የሚል ትውልድ” ብለው ለመጥራት ተገድደዋል። በዘመናችን ግብዞችና ራስ ወዳዶች በጣም በዝተዋል።
20. የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተስፋፍቶ ከሚገኘው የራስ ወዳድነት መንፈስ ጋር የሚቃረነው እንዴት ነው?
20 “ራሳቸውን የሚወዱ” ሰዎች ያደረሱብንን ጉዳት በመጥቀስ ያሳለፍናቸውን መራራ ተሞክሮዎች ማስታወስ አንፈልግም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ችግር ለይቶ በመጥቀሱ ከዚህ ወጥመድ እንዴት እንደምናመልጥ ማስተማሩ ስለሆነ እኛን ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቁጠሩ እንጂ ወገን በመለየትና በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ። እንዲሁም እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ።” “በትሕትና አስቡ እንጂ ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ።” ይህ ግሩም ምክር የሚገኘው በፊልጵስዩስ 2:3, 4 እንዲሁም ሮሜ 12:3 ላይ ሲሆን ከ1980 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተጠቀሰ ነው።
21, 22. ((ሀ) ይህ ዓይነቱ ምክር ለዘመናችን ጠቃሚ መሆኑን ያረጋገጠ ምን ትልቅ ማስረጃ አለ? (ለ) የአምላክ ምክር ጤናማ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ምን ዓይነት ውጤት አምጥቷል?
21 ‘ምክሩ ጥሩ ነበር። ግን በዚህ ዘመን ሊሠራ የሚችል አይደለም’ ብሎ የሚከራከር ሰው ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ ምክሩ ለዘመናችንም የሚሠራ ነው። በዘመናችን የሚኖሩ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ምክሩ የሚሠራ ሆኖ አግኝተውታል። በ1990 የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የኅትመት ክፍል ዘ ሶሻል ዳይሜንሽንስ ኦቭ ሴክታርያኒዝም የሚል መጽሐፍ አውጥቶ ነበር። የዚህ መጽሐፍ 8ኛ ምዕራፍ “በካቶሊክ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች” የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን በቤልጅየም አገር ስለተደረገ ጥናት ይገልጻል። እንዲህ እናነባለን፦ “የይሖዋ ምስክሮች እንዲሆኑ የሳቧቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ጥያቄ የቀረበላቸው ሰዎች ከ‘እውነት’ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ጠባዮች እንደሳቧቸው ይናገራሉ። . . . ልባዊ የሆነ ስሜት፣ የወዳጅነት መንፈስ፣ ፍቅርና ኅብረት በጣም ተዘውትረው ከሚጠቀሱት የተለመዱ ጠባዮች መካከል ሲሆኑ ሐቀኝነትና ‘የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን’ በግላቸው ‘ሥራ ላይ ለማዋል’ ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ደግሞ ምስክሮቹ ከፍተኛ ግምት የሚሰጧቸው ባሕርያት ናቸው።”
22 ይህን አጠቃላይ መግለጫ ሰፊ ሌንስ ባለው ካሜራ ከተነሳ ፎቶግራፍ ጋር ልናወዳድረው እንችላለን። ጊዜ ቢኖርና አጉልቶ በሚያሳይ መነጽር ብትመለከተው ኖሮ ደግሞ ግለሰቦችን፣ ማለትም የብዙ ሰዎችን የግል ሕይወት ተሞክሮ ለማየት ትችል ነበር። ከነዚህ መካከል በአንድ ወቅት ሐሳበ ግትር፣ እብሪተኛ ወይም ራስ ወዳድ የነበሩ፤ አሁን ግን ተለውጠው ለስላሶች፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ሌሎች ሰዎችን የሚወዱና ደጎች የሆኑ ጥሩ ባሎችና አባቶች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ በባሎቻቸው ላይ ለመሰልጠን የሚፈልጉና ርኅራኄ የለሾች የነበሩ፤ አሁን ግን ሌሎች ሰዎች እውነተኛውን የክርስትና ሕይወት እንዲያውቁ በመርዳት ላይ የሚገኙ ሴቶችም አሉ። እውነቱን ለመናገር ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች አሉ። እስቲ በግልጽ ተናገርና ከማንም በላይ ከምንም ነገር በፊት ራሳቸውን ከሚወዱ ወንዶችና ሴቶች ይልቅ እንደነዚህ ካሉ ሰዎች ጋር ብትውል ደስ አይልህምን? በዙሪያችን ያሉ ሰዎች እንደነዚህ ያሉ ቢሆኑ ይህን አስጨናቂ ዘመን ለመቋቋም አይቀልም ነበርን? ታዲያ እንዲህ ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መከተል ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን አያደርግህምን?
23. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:2–5ን ማጥናታችንን ብንቀጥል የሚጠቅመን ለምንድን ነው?
23 እስካሁን የተመለከትነው በ2 ጢሞቴዎስ 3:2–5 ላይ ተመዝግበው ከሚገኙት ጳውሎስ የዘረዘራቸው ነጥቦች የመጀመሪያውን ብቻ ነው። ሌሎቹስ? እነሱንም በደንብ ብትመረምራቸው በጊዜያችን ያሉትን ዋና ዋና ችግሮች ለመከላከል ትችል ዘንድ ችግሮቹ ምን እንደሆኑ ለይተህ እንድታውቅና ለአንተም ሆነ ለምትወዳቸው ሰዎች ትልቅ ደስታ የሚያመጣላችሁ የትኛው መንገድ እንደሆነ እንድትረዳ ያስችሉሃልን? ቀጥሎ ያለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እንድትችልና ብዙ በረከት እንድታገኝ ይረዳሃል።
ልናስታውሳቸው የሚገቡ ነጥቦች
◻ በአስጨናቂ ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
◻ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
◻ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5ን በምናጠናበት ጊዜ የምናተኩርባቸው ሁለት ቁልፍ ነጥቦች ምንድን ናቸው?
◻ ብዙ ሰዎች ራስ ወዳድ በሆኑበት በአሁኑ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የይሖዋን ሕዝቦች የጠቀሟቸው እንዴት ነው?
[ምንጭ]
ከላይ በስተግራ ያለው ፎቶ፦ Andy Hernandez/Sipa Press፣ ከታች በስተቀኝ ያለው ፎቶ፦ Jose Nicolas/Sipa Press