መጽሐፍ ቅዱስ፤ ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የሚበልጥባቸውን ሁኔታዎች መዘርዘር ከጀመረ ገላጭ ቃላት በቀላሉ ሊያልቁበት ይችላሉ። ይህ መጽሐፍ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በስፋት በመሰራጨት ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ዘመናት በመቆየት፣ ወደ ብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም፣ በጸሐፊዎችና በተናጋሪዎች ተደጋግሞ በመጠቀስ፣ ሰዎችን በመለወጥና ከፍተኛ አክብሮትን በማትረፍ ወደር የማይገኝለት መጽሐፍ ነው። በአወዛጋቢነቱም ከየትኛውም መጽሐፍ ሳይበልጥ አይቀርም። መጽሐፉ አቻ የማይገኝለት እገዳ፣ የማቃጠል እርምጃና ጭካኔ የተሞላበት ተቃውሞ ቢደርስበትም ሊጠፋ ያልቻለ መጽሐፍ ነው። ሆኖም ቀደም ባሉት ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ይበልጥ የነበረበት አሁን ግን ሁኔታው የተለወጠ አንድ ነገር አለ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከየትኛውም መጽሐፍ ይልቅ በብዙ ሰዎች የሚነበብ መጽሐፍ ነው ብሎ መናገር የሚቻል አይመስልም።
ሰዎች እቤታቸው ውስጥ የሆነ ቦታ ላይ የተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸው ቢችልም ብዙዎች መጽሐፉን ለማንበብ ምንም ጊዜ እንደሌላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ማንበብ በአንድ ወቅት በብዙዎች ዘንድ የተለመደ የጊዜ ማሳለፊያ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም ሌላ ነገር በመሥራት ማሳለፍ ይመርጣሉ። እስከ ዛሬ ድረስ ማንበብን ያልተዉ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ የማያደክምና ቀለል ያለ ጽሑፍን ይመርጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትኩረት ማሰባሰብን ይጠይቃል። አብዛኛዎቹ ሰዎች ደግሞ ለሚያነቡት ነገር ጠለቅ ያለ ትኩረት መስጠት ትተዋል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ውጣ ውረድ አልፎ እስከ ጊዜያችን እንዲቆይ የተደረገው እንዲሁ በመጽሐፍ መደርደሪያችን ላይ እንዲቀመጥ አይደለም። መጽሐፉን ለማንበብ የሚያስገድዱ ጥሩ ጥሩ ምክንያቶች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እውነታዎች ከዚህ ቀጥሎ ይመልከቱ።
እስከ ጊዜያችን መዝለቁ አያስደንቅም!
መጽሐፍ ቅዱስ የሚል ትርጉም ያለው “ባይብል” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው “ትናንሽ መጻሕፍት” የሚል ትርጉም ካለው ቢብልያ ከተባለው ግሪክኛ ቃል ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የብዙ መጻሕፍት ጥንቅር መሆኑን ያስታውሰናል። እርግጥ አንዳንዶቹ መጻሕፍቱ ትናንሽ አይደሉም። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት ከአሥራ ስድስት መቶ ዓመታት በላይ በፈጀ ጊዜ ውስጥ ነው። ጸሐፊዎቹ ሰዎች ቢሆኑም የጻፉት በአንድ ከሰው በላይ በሆነ አካል ተነሣስተው ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:21) ለቅዱሳን ጽሑፎች ትንቢት የሚሠራው ነገር ለተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ይሠራል። እነዚህ በመለኮታዊ አነሣሽነት የተጻፉ “ትናንሽ መጻሕፍት” ከፍ ባሉ የይሖዋ አምላክ ሐሳቦች የተሞሉ ናቸው። (ኢሳይያስ 55:9) መጽሐፍ ቅዱስ ለረጅም ጊዜ ጸንቶ መኖሩ አያስደንቅም!
መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ አገልጋዮች ምን ጊዜም ከሁሉ የላቀ መጽሐፋቸው ሆኖ ቆይቷል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ከሆነው ከሐዋርያው ጳውሎስ አባባል ጋር ይስማማሉ። እርሱም “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ለትምህርት የሚጠቅም ነው” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለይሖዋ ምሥክሮች የእምነታቸው መሠረት ነው። መሠረተ ትምህርታቸውን የሚወስንና ጠባያቸው ምን መሆን እንዳለበት የሚቆጣጠር ነው። እያንዳንዱ ሰው የአምላክን ቃል የተወሰኑ ክፍሎች በየዕለቱ እንዲያነብና በአድናቆት እንዲያሰላስልባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ከልብ ምክራቸውን ይለግሳሉ።—መዝሙር 1:1–3
መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ
ቅዱሳን ጽሑፎችን የማንበብ ልማድ ባለፉት ጊዜያት ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። የእስራኤል ነገሥታት በእጅ የተጻፈ የሕጉን ቅጂ (በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐቢይ ክፍል የሆነውን) ለራሳቸው እንዲያዘጋጁና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያለማቋረጥ እንዲያሳስባቸው በየዕለቱ እንዲያነቡት ታዘው ነበር። (ዘዳግም 17:18–20) ይህን ትዕዛዝ አለመፈጸማቸው አያሌ ነገሥታትን ለውድቀት ዳርጓቸዋል።
ቅዱሳን ጽሑፎችን የማጥናት ዋጋማነት በሽማግሌው በነቢዩ ዳንኤል ላይ ታይቷል። በእሱ ዘመን ይገኙ የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በግል በማጥናቱ ዳንኤል በባቢሎን ውስጥ በግዞት በነበረበት ወቅት በኤርምያስ የተዘገበ ከፍተኛ ቁም ነገር ያለው ትንቢት ሊፈጸም መቃረቡን ‘በመጽሐፍ ማስተዋል’ ችሎ ነበር።—ዳንኤል 9:2
“ጻድቅና [ለአምላክ ያደረ ሰው” አዓት] የነበረው ስምዖን ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ክርስቶስ ወይም መሲሕ የሚሆነውን ሰው ለማየት በእርግጠኝነት ይጠባበቅ ነበር። ስምዖን ክርስቶስን ሳያይ እንደማይሞት ቃል ተገብቶለት ነበር። ሕጻኑን ኢየሱስን በእጆቹ ታቅፎ ሳለ ከኢሳይያስ ትንቢት ጠቅሶ መናገሩ ስምዖን በዘመኑ ተጽፈው ያለቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በንቃት ያነብ እንደነበረ ያሳያል።—ሉቃስ 2:25-32፤ ኢሳይያስ 42:6.
አጥማቂው ዮሐንስ ይሰብክ በነበረበት ወቅት ሕዝቡ የመሲሑን “መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር።” ይህ የሚያመለክተው ምንድን ነው? ከአይሁዳውያን መካከል ብዙዎቹ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ስለ መሲሑ የሚናገሩ ትንቢቶች ያውቋቸው እንደነበረ ይጠቁመናል። (ሉቃስ 3:15፤ የ1980 ትርጉም) ጊዜው መጻሕፍት እንደልብ የማይገኙበት ወቅት ስለነበረ ነገሩ የሚያስደንቅ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎባቸው በብዙ ድካም በእጅ መዘጋጀት ነበረባቸው። በዚህም ሳቢያ መጻሕፍቱ ዋጋቸው ውድ ነበር፤ እነርሱንም ማግኘቱ አስቸጋሪ ነበር። ሰዎቹ ከመጻሕፍቶቹ ይዘት ጋር በደንብ መተዋወቅ ይችሉ የነበረው እንዴት ነው?
ብዙውን ጊዜ በሕዝብ ፊት ይደረግ በነበረ ንባብ አማካኝነት ነበር። ለምሳሌ በአምላክ የተሰጠው ሕግ በሙሉ በተወሰኑና ቋሚ በሆኑ ወቅቶች እስራኤላውያን በተሰበሰቡበት እንዲነበብ ሙሴ አዝዞ ነበር። (ዘዳግም 31:10-13) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ለሕዝብ ማንበብ በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሙሴስ ከቀደሙት ትውልድ ጀምሮ በሰንበት በሰንበት በምኩራቦቹ ሲያነቡ በየከተማው እርሱን የሚሰብኩ አሉት” ብሏል።—ሥራ 15:21
በዛሬው ጊዜ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት አስቸጋሪ አይደለም። ከእነዚህ “ትናንሽ መጻሕፍት” መካከል ቢያንስ ቢያንስ አንዳንዶቹን ከዓለም ሕዝብ 98 በመቶ የሚሆነው በቋንቋው ሊያገኛቸው ይችላል። በመሆኑም ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለእነሱ ምን መልእክት እንዳለው ለማወቅ አለመፈለጋቸው የሚያሳዝን ነው። የምንኖረው ሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ዘመን ላይ ቢሆንም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ‘ለትምህርት ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል።’ ሥነ ምግባርን፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው ያላቸውን ግንኙነትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ግሩም ምክር ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ ወደፊት ሰላም የሠፈነበት ሕይወት እንደሚመጣ ብቸኛውን አስተማማኝ ተስፋ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ዘወትር ያንብቡት
በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር እንዲያነቡ የማበረታታቱን ተግባር የሥራቸው አንዱ ትልቅ ክፍል አድርገውታል። በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤታቸው የፋብሪካው ሕንጻ ላይ “የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብቡ” የሚል ማሳሰቢያ ጎላ ባሉ ፊደላት ተጽፎ ይታያል። በዚያ በኩል የሚያልፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ቃላት አይተዋቸዋል። ብዙዎቹም ማሳሰቢያውን እንደሠሩበት ተስፋ ይደረጋል።
በመላው ዓለም በሚገኙት ከ73,000 በላይ በሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በየሳምንቱ ይካሄዳል። ከሚሰጡት ትምህርቶች አንዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመርጦ የተወሰደን አንድ ክፍል በሰዎች ፊት ማንበብ ነው። በተጨማሪም ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በቤታቸው በየሳምንቱ በግል የሚያነቧቸው ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ይሰጧቸዋል። ይህን ፕሮግራም ተከትለው ዘወትር የሚያነቡ ሁሉ በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ አንብበው ይጨርሳሉ።
ይህ ዝግጅት በዚህ ትምህርት ቤት ላይ ከሚሠራባቸው የመማሪያ መጻሕፍት አንዱ ከሚሰጠው ምክር ጋር የሚስማማ ነው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የግል ፕሮግራምህ ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብን የሚጨምር መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ከማንበብ ብዙ ጥቅም ይገኛል። . . . ይሁን እንጂ የምታነብበት ዓላማ አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘትና ያነበብከውን ለማስታወስ መሆን ይኖርበታል እንጂ አንድን መጽሐፍ ለመጨረስ ብቻ መሆን የለበትም። ያነበብከውን ነገር በደንብ ለማብላላት ጊዜ ውሰድ።”
በይሖዋ ምሥክሮች ታትመው የወጡ ሌሎች ጽሑፎችም መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን ያበረታታሉ። ለምሳሌ በየጊዜው ከዚህ መጽሔት ጋር ጎን ለጎን እየታተመ የሚወጣው የንቁ! መጽሔት ለወጣቶች የሚከተለውን ማበረታቻ አቅርቦ ነበር፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር . . . አንብበኸዋልን? መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ መጽሐፍ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ለምን በትንሽ በትንሹ ከፋፍለህ አታነበውም? . . . “ልበ ሰፊዎች” የነበሩት የቤርያ ሰዎች ‘ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ ይመረምሩ ነበር።’ (ሥራ 17:11) ፕሮግራም አውጥተህ በየቀኑ 15 ደቂቃ ብቻ ብታነብ . . . በአንድ ዓመት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ።” አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች በጥንት ዘመን እንደነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በዘመናችን ያሉትም ክርስቲያኖች ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በደንብ መተዋወቅ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።
ምሥክሮቹ ይህን በአእምሮአቸው በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝብ መነበብ የሚችልበትን ከ20ኛው መቶ ዘመን ጋር የሚሄድ ዘመናዊ ዝግጅት አድርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ የሚሸፍን ንባብ የተቀዳባቸውን ካሴቶች በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል። ይህም ለብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እንቅፋት የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ለማሸነፍ የሚረዳ ጠቃሚ ነገር ሆኗል። አንዳንዶች እነዚህን የካሴት ቅጂዎች እቤት ውስጥ ሲሠሩ፣ መኪና ሲነዱ፣ ወይም ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን ሲያከናውኑ ያዳምጧቸዋል። ቁጭ ብሎ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በካሴት እያዳመጡ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ መከታተል አስደሳች ነው።
በአሁኑ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማያነቡት ከሆነ እንዲህ ማድረጉን ለምን ልማድዎ አያደርጉትም? ይህን ለማድረግ በየቀኑ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ አያስፈልግም፤ ነገር ግን ቅዱሳን ጽሑፎችን በተግባር ማዋሉ በጥበብ እንዲመላለሱና የድካምዎን ዋጋ የሚያዩበት መንፈሳዊ ሕይወት በማግኘት እንዲደሰቱ ስለሚያስችልዎ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ብዙ ናቸው። በተጨማሪም ከብዙ ጊዜ በፊት ለእስራኤላዊው መሪ ለኢያሱ ተሰጥቶት ከነበረው ቀጥሎ ካለው ትዕዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይችላሉ፦ “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።”—ኢያሱ 1:8
የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ይሖዋ ለታዛዥ የሰው ዘሮች ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ ይገልጻሉ። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈውን ቃሉን በትክክል ማወቅ እውነተኛ ደስታ ያመጣል። በተጨማሪም ፍጻሜ የሌላቸው በረከቶች በሚፈሱበት እጅግ ግሩም በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ በገነት ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ያስገኛል። (ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚችሉበት ይህ አጋጣሚ አያምልጥዎ። ይህን ግሩም ሕይወት ለመጨበጥም ይጣጣሩ።