በግል ጥናት ትደሰታለህን?
ማንኛውም እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በቂ ጊዜ ቢመድብ ከፍተኛ ደስታ ያገኛል። (መዝሙር 1:1, 2) ሆኖም ብዙ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚሻሙ ብዙ ነገሮች ስለሚደራረቡባቸው በግል ጥናት ላይ የሚፈልጉትን ያህል ጊዜና ጉልበት ማጥፋት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።
ይሁን እንጂ ንቁ የአምላክ አገልጋይ ሆነው ለመቀጠል እንዲችሉ ሁሉም የአምላክን ቃል እውነት አዳዲስ ወይም ጥልቀት ያላቸውን ገጽታዎች በማስተዋል ደስታቸውና ኃይላቸውን ዕለት ተዕለት ማደስ ይኖርባቸዋል። ከአያሌ ዓመታት በፊት ስሜትህን ይቀሰቅሱ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አሁን ያን ያህል አያንቀሳቅሱህ ይሆናል። ስለዚህ በመንፈሳዊ ንቃት ያለን ሆነን እንድንቀጥል የሚያስችለን አዲስ የእውነት ማስተዋል ለማግኘት በደንብ የታሰበበትና ቋሚ የሆነ ጥረት ማድረጋችን ጥሩ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ነው።
በጥንት ዘመን የነበሩት የእምነት ሰዎች የአምላክን ቃል በግል በማጥናት መንፈሳዊነታቸውን ያጠናከሩት እንዴት ነው? በዘመናችን ካሉት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ጥናታቸውን አስደሳች እንዲሁም ፍሬያማ ሊያደርጉ የቻሉት እንዴት ነው? ላደረጓቸው ጥረቶች የሚክስ ዋጋ ያገኙት እንዴት ነው?
በግል ጥናት አማካኝነት ኃይላቸውን አድሰዋል
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ ‘በሙሴ እጅ የተጻፈው የይሖዋ ሕግ መጽሐፍ’ ከተነበበለት በኋላ በጣዖት አምልኮ ላይ ያካሂድ የነበረውን ዘመቻ በፊት ከነበረው ቅንዓት በበለጠ አከናውኗል። ይኸኛውን የአምላክ ቃል ክፍል ከዚህ በፊት አንብቦት እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ መልእክቱን በቀጥታ ከመጀመሪያው በእጅ የተጻፈ ጽሑፍ ላይ ሲሰማ ለንጹሕ አምልኮ በመቆርቆር የሚያካሄደውን ውጊያ እንዲያፋፍም አድርጎታል።—2 ዜና መዋዕል 34:14–19
ነቢዩ ዳንኤል ‘የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን የዓመቱን ቁጥር’ እና የትንቢቱን እውነተኝነት ከኤርምያስ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ከ“መጻሕፍት” [የ1980 ትርጉም] ማስተዋል ችሎ ነበር። እነዚህ መጻሕፍት እንደ ዘሌዋውያን (26:34, 35)፣ ኢሳይያስ (44:26–28)፣ ሆሴዕ (14:4–7) እና አሞጽ (9:13–15) ያሉትን መጻሕፍት የሚያጠቃልሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህ ለአምላክ ያደረ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ተግቶ በማጥናት ያረጋገጠው ነገር የጋለ ጸሎት በማቅረብ አምላክን እንዲፈልግ አድርጎታል። ይህ ሰው ያቀረበው ከልብ የመነጨ ልመና ስለ ኢየሩሳሌም ከተማና ስለ ሕዝቡ በተሰጠው ተጨማሪ ራእይና ማጽናኛ መልስ አገኘ።—ዳንኤል ምዕራፍ 9
“በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን” ያደረገው ኢዮስያስና በይሖዋ ዓይን ‘እጅግ የተወደደው’ ዳንኤል በመሠረቱ በአሁኑ ጊዜ ካለነው ከእኛ የተለዩ አልነበሩም። (2 ነገሥት 22:2፤ ዳንኤል 9:23) በዚያን ጊዜ በነበሩት ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በከፍተኛ ስሜት ተገፋፍተው ባካሄዱት ጥናት ረገድ የግል ጥረታቸው የተሻለ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል፤ ከአምላክ ጋርም ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ትስስር እንዲያበጁ ረድቷቸዋል። ዮፍታሔን፣ ከአሳፍ ወገን የሆነ አንድ መዝሙራዊን፣ ነህምያንና እስጢፋኖስን የመሰሉ ብዙ የጥንት የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚሁ ሊባልላቸው ይችላል። እነዚህ በሙሉ በጊዜያቸው ይገኝ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጥልቀት በግል ያጠኑ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ።—መሳፍንት 11:14–27፤ መዝሙር 79, 80፤ ነህምያ 1:8–10፤ 8:9–12፤ 13:29–31፤ ሥራ 6:15–7:53
አገልግሎቱ የግል ጥናት እንድታደርጉ ይገፋፋችሁ
በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ አገልጋዮቹ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም አላቸው። ይህንንም ንቁ ለመሆንና ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ለመወጣት የግድ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። ያም ሆኖ ግን ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ለጥናትና ለሌሎች ቸል ሊባሉ ለማይገባቸው ጉዳዮች ማዋሉ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል።
ያም ሆኖ ግን በዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰው ዓለም አቀፋዊ የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ጊዜ ላይ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ትጋት በተሞላበት የግል ጥናት አማካኝነት በመንፈሳዊ ንቁ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። አዳዲስ በሆኑና ጥልቀት ባላቸው የአምላክ ቃል ትምህርቶች የሚደሰቱት ወንድሞች የተራቡ ሰዎችን ልብ የመንካትን ከባድ ሥራ መወጣት ይችላሉ። አንድ ሰው ብዙ መንፈሳዊ አሣዎች ሊጠመዱባቸው ይችላሉ ተብሎ በሚታሰብባቸው ቦታዎች ተመድቦ ሲሠራም ሆነ በደንብ በተሠራባቸው በጥቅሉ ለመልእክቱ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ባሉባቸው ክልሎች መሥራቱን ቢቀጥል ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይሆንም።
ዘወትር የአምላክን ቃል ተመገብ
ሌሎች ወንድሞች ምን እንደሚያደርጉ ማወቅህ ዘወትር በምታከናውነው ጥናት የተሻለ ደስታን እንዴት ልታገኝ እንደምትችል ወይም አንተና ቤተሰብህ የጥናት ጊዜን ይበልጥ ዋጋማ በሆነ መንገድ እንዴት ልትጠቀሙበት እንደምትችሉ ሊጠቁምህ ይችላል። አንድ የአምላክ አገልጋይ እንዲያመልጡት ከማይፈልጋቸው ነገሮች አንዱ የአምላክን ቃል ዘወትር ማንበብ ነው። ብዙዎች በየሳምንቱ በትንሹ ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን የማንበብ ግብ አውጥተዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ዓመት አንብበህ መጨረስ ትፈልጋለህን? እንግዲያው ከዚህ የበለጠ ጊዜ ምናልባትም በቀን ግማሽ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ማዋሉ ያስደስትሃል።
መጽሐፍ ቅዱስን ከአንድ ጊዜ በላይ ከዳር እስከ ዳር አንብበኸዋልን? ታዲያ ለሚቀጥለው ጊዜ አዲስ ግብ አውጥተህ ለምን አታነበውም? አንዲት ክርስቲያን ሴት ለለውጥ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በተጻፉበት የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አነበበቻቸው። ቀደም ሲል አልፋቸው የነበሩትን ነገሮች አሁን ከዘመኑ አንጻር ስታነባቸው ልታስተውላቸው ችላለች። ሌላ ክርስቲያን ሴት ባለፉት አምስት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ከተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች አምስት ጊዜ ከዳር እስከ ዳር አንብባዋለች። መጀመሪያ ከዳር እስከ ዳር ወጣችው። ለሁለተኛ ጊዜ ስታነብ እያንዳንዱ ምዕራፍ ያለውን አጠቃላይ ይዘት በአንድ ማስታወሻ ደብተር ላይ በአንድ ወይም በሁለት መስመሮች ታሰፍር ነበር። ከሦስተኛው ዓመት ጀምሮ ተለቅ ባሉ ፊደላት ወደተጻፈው ባለማጣቀሻ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም ተሸጋገረች። በመጀመሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እንዲቻል በኅዳጉ ላይ ከሰፈሩት ጥቅሶች መካከል የተወሰኑ ጥቅሶችን እየመረጠች በማስተያየትና የግርጌ ማስታወሻዎቹን እንዲሁም በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ የሰፈረውን ተጨማሪ መረጃ (አፔንዲክስ) በጥልቀት በመመርመር መጽሐፉን አንብባ ጨረሰች። ለአምስተኛ ጊዜ ስታነበው ደግሞ በመልክአ ምድር አቀማመጥ ረገድ ያላትን እውቀት ለማስፋት በመጽሐፍ ቅዱስ ካርታ እየተጠቀመች አነበበችው። “ለእኔ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ምግብን የመመገብ ያህል አስደሳች ሆኖልኛል” ስትል ተናግራለች።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለግል ጥናት ብቻ የሚገለገሉበት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማዘጋጀቱ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በዚህ ቅጂ ኅዳግ ላይ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦችን፣ ትምህርት ሰጪ ምሳሌዎችን፣ ወይም በሌላ ጊዜ አውጥተው ሊመለከቷቸው የሚችሏቸውን የሌሎች ጽሑፎች ገጾችን በአጭሩ ያሰፍራሉ። አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በምታጠናበት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ላይ በወሩ ውስጥ ያገኘቻቸውን አዳዲስ ነጥቦች በየወሩ መጨረሻ መጻፍ ያስደስታል። “እነዚህን ከፍተኛ ጥቅም የማገኝባቸውን ሰዓታት በናፍቆት መጠባበቄ” ትላለች “በቀጣዩ ወር ሌሎች ግቦችን ዳር ማድረስ እንድችል ይረዳኛል።”
አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦች
ፕሮግራምህ በየዕለቱና በየሳምንቱ ሊሟሉ በሚገባቸው ግዴታዎች እንደተሞላና ያለህን የተወሰነ ጊዜ እንዴት በተሻለ መንገድ ልትጠቀምበት እንደምትችል የሚጠቁሙ ሐሳቦች ማግኘት እንደሚያስፈልግህ ይሰማሃልን? እንግዲያው ለማንበብ ያሰብከው ነገር ከእጅህ አይለይ። ያሉህን የዕረፍት ጊዜዎች ተጠቀምባቸው። በቤት ወይም ዘወትር በምታጠናበት ቦታ መጽሐፎችንና ለማጥናት የምትገለገልባቸውን ሌሎች ነገሮች በቀላሉ ማግኘት እንድትችል በደንብ አስተካክለህ አስቀምጣቸው። የምታጠናበት ሥፍራ ምቹ አድርግ፤ ነገር ግን እንቅልፍ እንቅልፍ እስኪልህ ድረስ የሚያንፈላስስ አይሁን። እንድታቀርበው የተሰጠህ ንግግር አለህን? በተቻለ መጠን ጽሑፉን ቀደም ብለህ ከዳር እስከ ዳር አንብበው። ከዚያም ዕረፍት በምታደርግበት ጊዜ ወይም ቀላል ሥራዎችን በምታከናውንበት ጊዜ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እንዲመጡ አድርግ።
ለጋራ ጥቅም ሲባል ጊዜን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ሌሎች ሰዎች ሊተባበሩህ ይችላሉ። ለምሳሌ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በምታከናውንበት ጊዜ አንድ ሰው ቀለል ያለ መልዕክት ያለው ጽሑፍ ሊያነብልህ ይችላል፤ ወይም ሻይ በምታቀራርብለት ጊዜ እንዲያነብልህ ማድረግ ትችላለህ። በቤት ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ በአንድ የተወሰነ ሰዓት ላይ የግል ጥናት ለማካሄድ ጸጥ ለማለት ሊወስኑ አይችሉምን? አንዳንድ ጊዜ “በቅርቡ ካነበብከው ምን ነጥብ አግኝተሃል?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ውይይት ልትከፍትና ጓደኞችህ ያገኙትን እውቀት እንዲያካፍሉህ ማድረግ ትችል ይሆናል።
በጥናት ፕሮግራምህ ላይ አዳዲስ ዕቅዶችን በማውጣት መጠቀም ትፈልጋለህን? ብዙዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሌሎች በመናገር ለሚያሳልፉት ሰዓት ግብ እንደሚያወጡ ሁሉ ይሄን ያህል ጊዜ በማጥናት አሳልፋለሁ ብለህ ግብ ልታወጣ ትችላለህ። አንዲት የሙሉ ጊዜ (አቅኚ) አስፋፊ በአንድ ወር ውስጥ በትንሹ ይሄን ያህል ሰዓት በጥናት አሳልፋለሁ የሚል ግብ አወጣች። ወዳወጣችው የሰዓት ግብ እየተቃረበች መምጣቷን ስትመለከት ተደሰተች። ሌሎች ደግሞ ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፉትን ጊዜ በመገደብ ለጥናት የሚሆን ጊዜ ማትረፍ ችለዋል። ብዙዎች ለተወሰነ ጊዜ የሚከተሉትን እንደ መንፈስ ፍሬዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሥረ መሠረት ወይም የማስተማር ችሎታ የሚሉትን የመሰሉ የጥናት ርዕሶችን በመምረጥ ያጠናሉ። አንዳንዶች ደግሞ በእስራኤላውያን ነገሥታትና በነቢያቶች መካከል ወይም በሐዋሪያት ሥራና በጳውሎስ ደብዳቤዎች መካከል ያሉትን የጊዜ ዝምድናዎች የሚያሳዩትን ሰንጠረዦች የመሰሉ የዘመን አቆጣጠር ሰንጠረዦችን መሥራት ያስደስታቸዋል።
ወጣቶች ሆይ፣ ይበልጥ ጠንካራ እምነት እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁን? በሚቀጥለው የትምህርት ቤት የዕረፍት ጊዜያችሁ ጥልቀት ባለው መንገድ በደንብ የምታነቡትን አንድ ጽሑፍ ለምን አትመርጡም? አንዲት የተጠመቀች የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ መርጣ አነበበች። አንድ ምዕራፍ አንብባ በጨረሰች ቁጥር ያገኘችውን እውቀት በአንድ ማስታወሻ ደብተር ላይ በአጭር በአጭሩ ጠቅለል አድርጋ ታሰፍር ነበር። ያደረገችው ጥናት ትዕግሥቷን የሚፈታተንና ካሰበችው የበለጠ ጊዜን የወሰደ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፉን በሙሉ አንብባ ስትጨርስ በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እውነተኝነት እጅግ ተገረመች።
አዲስ እውቀት ለማግኘት ምን ጊዜም ጉጉት ይኑርህ
በዘመናችን ያሉ እጅግ ብዙ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በአሁኑ ጊዜ ‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’ ሆነዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ፕሮግራምህን መለስ ብለህ በማጤን አንዳንድ ማስተካከያዎችን ብታደርግና ልባዊ ጥረቶችን ብታደርግም በሳምንት ውስጥ የምትከተለው የሥራ ፕሮግራም እምብዛም ለውጥ አይታይበት ይሆናል። ሆኖም ጥልቀት ያለው የእውነት እውቀት ለማግኘትና በየጊዜው ከሚገለጹት የአምላክ ዓላማዎች ጋር እኩል ለመራመድ የምታደርገው የማያቋርጥ ትጋት ለውጥ ሊያመጣልህ ይችላል።
የአጠናን ዘዴያቸውን ያሻሻሉ ወንድሞችና እህቶች ለድካማቸው ያገኙትን ዋጋ መስማቱ የሚያበረታታ ነው። አንድ ክርስቲያን ጥልቅ የሆነ የእውነት እውቀትን በመሻት ረገድ አዎንታዊ አመለካከት እያጣ መምጣቱን በመገንዘብ ትርፍ ጊዜውን ይበልጥ ለግል ጥናት ማዋል እንዲችል ሕይወቱን በፕሮግራም መምራት ጀመረ። “ከዚህ በፊት አግኝቼው የማላውቀውን ደስታ ሰጠኝ” በማለት ይናገራል። “መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በመለኮታዊ መሪነት እንደሆነ ያለኝ ትምክህት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየጎለበተ በመምጣቱ ስለ እምነቴ ለሌሎች ከልብ ፈንቅሎ በሚወጣ የጋለ ስሜት መናገር ቻልኩ። እያንዳንዱ ቀን በተገባደደ ቁጥር በሚገባ እንደተመገብሁ፣ መንፈሳዊ ጤንነትና እርካታ እንዳገኘሁ ይሰማኛል።”
ብዙ ጉባኤዎችን የሚጎበኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ሌሎች ጥቅሞችን ዘርዝሯል፦ “በግል ጥናት የሚተጉ ወንድሞችና እህቶች በጥቅሉ ለሌሎች የሚናገሩትን ነገር ሕያውና በሰዎች ልብ ላይ ሊቀረጽ በሚችልበት መንገድ ያቀርቡታል። ከሌሎች ሰዎች ጋር የተሻለ ወዳጃዊ ዝምድና ይኖራቸዋል፤ ሌሎች ለሚያቀርቧቸው አፍራሽ አስተያየቶችም በቀላሉ እጃቸውን አይሰጡም። በመስክ አገልግሎት ሲሰማሩም አቀራረባቸውን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ ይለዋውጣሉ፤ እንዲሁም የሰዎቹን ፍላጎት በንቃት ይከታተላሉ።”
ቀጥሎ የተናገረውን ነጥብ አንዳንዶች የራሳቸውን የአጠናን ዘዴ በሚመረምሩበት ጊዜ በአእምሮአቸው ሊይዙት ይፈልጉ ይሆናል። “ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶች በሚደረጉባቸው ስብሰባዎች ላይ ብዙዎች ሐሳብ ሲሰጡ በቀጥታ ከጽሑፉ ላይ ማንበብ ይቀናቸዋል። ትምህርቱ በፊት ከነበራቸው እውቀት ጋር ወይም ከሕይወታቸው ጋር እንዴት ሊዛመድ እንደሚችል ቢያሰላስሉበት ኖሮ ይበልጥ ይጠቀሙ ነበር።” በዚህ ረገድ ማሻሻል ያለብህ ነገር እንዳለ ይሰማሃልን?
ነቢዩ ዳንኤል ለ90 ዓመታት ከኖረም በኋላ የይሖዋን መንገዶች ሙሉ በሙሉ አንደተረዳ ሆኖ አልተሰማውም። በመጨረሻዎቹ የሕይወቱ ዓመታት ላይ ስለ አንድ ሙሉ በሙሉ ሊጨበጥለት ስላልቻለ ጉዳይ “ጌታዬ ሆይ፣ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድር ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። (ዳንኤል 12:8) ይህ ስለ አምላክ እውነት የበለጠ ለማወቅ የነበረው እስከ መጨረሻው የዘለቀው ጉጉት ብዙ አስገራሚ ክንውኖች በተካሄዱበት የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከፍተኛ የአቋም ጽናት ለመያዝ አስችሎታል።—ዳንኤል 7:8, 16, 19, 20
ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች የእሱ ምሥክሮች እንደመሆናቸው መጠን ጸንተው በመቆም ረገድ ያለባቸው ኃላፊነት ከዳንኤል የሚያንስ አይደለም። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነህ መቀጠል እንድትችል እውቀት ለማግኘት ከምን ጊዜውም የበለጠ ጉጉት ይደርብህ። በየሳምንቱ፣ በየወሩ ወይም በየዓመቱ በምታወጣው የግል ጥናት ፕሮግራምህ ላይ አንድ ወይም ሁለት አዲስ ገጽታዎችን ለመጨመር ጥረት አድርግ። የምታደርገውን ማንኛውንም አነስተኛ ጥረት አምላክ አንዴት እንደሚባርከው ተመልከት። አዎን፣ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህና በሚያስገኝልህ በረከቶች ተደሰት።—መዝሙር 107:43 አዓት