የኢየሱስ ተአምራት—እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ተረት?
“ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።”—ማቴዎስ 14:25
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በሠራቸው ተአምራት ማመንን በእግዚአብሔር ከማመን የማይተናነስ ዋጋ ይሰጡታል። የወንጌል ጸሐፊዎቹ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ 35 የሚያክሉ የኢየሱስን ተአምራት ይገልጻሉ። ሆኖም ዘገባዎቹ ኢየሱስ ከሰብዓዊ ችሎታ በላይ የሆኑ ሌሎች ብዙ ገድሎችን እንደፈጸመ ይጠ ቁማሉ።—ማቴዎስ 9:35፤ ሉቃስ 9:11
እነዚህ ተአምራት ሰዎችን ለማዝናናት የተፈጸሙ አልነበሩም። ኢየሱስ የአምላክ ልጅና ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ እንደሆነ ለተናገረው ነገር ማረጋገጫ ነበሩ። (ዮሐንስ 14:11) ሙሴ በባርነት ሥር ለነበረው የእስራኤል ሕዝብ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ተአምራዊ ምልክቶችን አከናውኖ ነበር። (ዘጸአት 4:1–9) ልክ እንደዚሁ ከሙሴ እንደሚበልጥ የተተነበየለት መሲሑ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች እንደሚፈጽም የሚጠበቅ ነው። (ዘዳግም 18:15) ይህም በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ [ለአይሁዶች] የተገለጠ ሰው ነበረ” ብሎ ኢየሱስን ይገልጸዋል።—ሥራ 2:22
ባለፉት ዘመናት የነበሩ ሰዎች ኢየሱስን እንደ ተአምር ሠሪ አድርጎ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በጥቅሉ ያለ አንዳች ጥርጥር ይቀበሉት ነበር። ነገር ግን ቅርብ በሆኑት አሥርተ ዓመታት የወንጌል ዘገባዎች ከአቃቂረኞች የተለያየ ትችት እየደረሰባቸው ነው። ሎይድ ግራሃም ዲሴፕሽን ኤንድ ሚዝ ኦቭ ዘ ባይብል በተባለው መጽሐፋቸው ኢየሱስ በውኃ ላይ ስለ መሄዱ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ በእርግጥ ተፈጽሟል ብሎ ማመን መደናቆር ቢሆንም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእርግጥ ተፈጽሟል ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ዓለማችን ምን እንደነካው መገረም አይገባንም። ከእንዲህ ዓይነቱ ድንቁርና ምን የተሻለ ዓለም ትጠብቃላችሁ?”
የማይቻል ነውን?
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ትችቶች ምክንያታዊ አይደሉም። ተአምር ማለት “በሚታወቁ የተፈጥሮ ሕግጋት ሊብራራ የማይችል አንድ የተፈጸመ ነገር ነው” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ፍቺ ሰጥቷል። በዚህ ማብራሪያ መሠረት ባለ ቀለም ቴሌቪዥን፣ በተወሰነ ርቀት ውስጥ የሚሠራ ሽቦ አልባ ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስ አነስተኛ ኮምፒውተር ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ብቻ እንደ ተአምር ተደርጎ በታየ ነበር! አንድን ነገር በጊዜው ባለው ሳይንሳዊ እውቀት ተመርኩዘን ማብራራት ስላልቻልን ብቻ በጭፍንነት ይህ የማይቻል ነው ማለቱ ምክንያታዊ ነውን?
“አዲስ ኪዳን” በተጻፈበት የጥንቱ የግሪክኛ ቋንቋ “ተአምር” ለሚለው ቃል የሚጠቀምበት “ኃይል” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ያለውን ዳይናሚስ የሚለውን ቃል መሆኑ ሌላው የምንመረምረው መረጃ ነው። በተጨማሪም ይህ ቃል “አስገራሚ ሥራዎች” ወይም ‘ዓቅም’ ተብሎ ተተርጉሟል። (ሉቃስ 6:19፤ 1 ቆሮንቶስ 12:10 አዓት ፤ ማቴዎስ 25:15) መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ተአምራት “የእግዚአብሔርን ታላቅ ኀይል” የሚያሳዩ እንደሆኑ ይገልጻል። (ሉቃስ 9:43 የ1980 ትርጉም) እንደዚህ ያሉ ሥራዎች ‘ብዙ ኃይል’ ላለው ሁሉን ማድረግ ለሚችል አምላክ የሚሳኑ ይሆናሉን?—ኢሳይያስ 40:26
የሐቀኝነታቸው ማስረጃ
በአራቱ ወንጌሎች ላይ የሚደረገው ጠለቅ ያለ ምርምር ለተዓማኒነታቸው ተጨማሪ ማስረጃ ያስገኛል። ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር እነዚህ ዘገባዎች ከተረቶችና ከአፈ ታሪኮች በጣም የተለዩ ናቸው። ለምሳሌ እሱ ከሞተ በኋላ ባሉት መቶ ዓመታት ስለ ኢየሱስ የተሰራጩትን የውሸት ታሪኮች ተመልከት። “የቶማስ ወንጌል” የተባለው አዋልድ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይናገራል “ይህ ኢየሱስ የተባለው ልጅ አምስት ዓመቱ በነበረ ጊዜ . . . መንደሩን አቋርጦ ሲሄድ አንድ ወጣት ሮጦ ትከሻውን መታው። ኢየሱስ በቁጣ ነደደና ‘ካለህበት ቦታ ንቅንቅ አትልም’ አለው። ልጁ ወዲያው ወደቀና ሞተ።” የታሪኩን መንፈስ ምንነት ማለትም ተፈጥሮ የተወራ ተረት መሆኑን መለየት አያስቸግርም። ከዚህም በላይ እዚህ ላይ የተገለጸው ግብታዊው ብስጩ ልጅ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ጋር አይመሳሰልም።—ከሉቃስ 2:51, 52 ጋር አነጻጽር።
አሁን ደግሞ ያልተዛቡትን የወንጌል ዘገባዎች ተመልከት። ዘገባዎቹ ከማጋነንም ሆነ ከልብ ወለዳዊ ባሕርይ የጸዱ ናቸው። ኢየሱስ ተአምራትን የፈጸመው እውነተኛ ችግር ላለባቸው አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት እንጂ በግብታዊነት ተነሳስቶ አይደለም። (ማርቆስ 10:46–52) መቼም ቢሆን ኢየሱስ ራሱን ለመጥቀም ሲል በራሱ ኃይል ተጠቅሞ አያውቅም። (ማቴዎስ 4:2–4) እንዲሁም ጉራውን ለመንዛት ፈጽሞ አልተጠቀመበትም። እንዲያውም ለማወቅ ጉጉ የነበረው ንጉስ ሄሮድስ ኢየሱስ ተአምራዊ ‘ምልክት’ እንዲፈጽምለት በፈለገ ጊዜ ኢየሱስ “አንድ ስንኳ አልመለሰለትም።”—ሉቃስ 23:8, 9
በተጨማሪም የኢየሱስ ተአምራት ከምትሃት አዋቂዎች፣ ከአስማተኞችና ከእምነት ፈዋሾች ሥራ ጉልህ ልዩነት አላቸው። አስገራሚ ሥራዎቹ ሁልጊዜ አምላክን ክብር የሚያቀዳጁ ነበሩ። (ዮሐንስ 9:3፤ 11:1–4) ተአምራቱ በስሜት የሚከናወኑ የተለመዱ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች፣ አስማታዊ ድግምቶች፣ ዓይን ሚስቡ ትርዒቶች፣ አታላይና የአፍዝ አደንግዝ ድርጊቶች አልነበሩም። “መምህር ሆይ! እባክህ እንዳይ አድርገኝ” ብሎ ከለመነው በርጢሜዎስ ከተባለ አንድ ዓይነ ስውር ለማኝ ጋር ባጋጣሚ በተገናኘ ጊዜ ኢየሱስ ጣጣ ሳያበዛ “‘በል ሂድ እምነትህ አድኖሃል’ አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ።”—ማርቆስ 10:46–52 የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ አስገራሚ ሥራዎቹን የፈጸመው ያለ ምንም ድጋፍ በተለይም የመድረክ ቅንብር ወይም የማታለያ የመድረክ መብራቶችን ሳይጠቀም እንደሆነ የወንጌል ዘገባዎች ያሳያሉ። ተአምራቱ ብዙውን ጊዜ አያሌ የዓይን ምሥክሮች በተሰበሰቡበት በግልጽ የተፈጸሙ ነበሩ። (ማርቆስ 5:24–29፤ ሉቃስ 7:11–15) በዘመናችን ያሉት የእምነት ፈዋሾች ለመፈወስ የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ሰውዬው እምነት ይጎለዋል የሚል ሰበብ ቢያቀርቡም ኢየሱስ ግን ለመፈወስ ያደረገው ጥረት በዚህ ሳቢያ ሳይሳካ የቀረበት አንድም ጊዜ የለም። ማቴዎስ 8:16 (በ1954 እትም 8:17) “የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ” ይላል።
ምሁሩ አርተር ፒርሰን “ሜኒ ኢንፎሊብል ፕሩፍስ” ዘ ኤቪደንስስ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ክርስቶስ ተአምራት ሲናገሩ “ብዛታቸው፣ ዛሬ ነገ ሳይል የተፈጸሙ መሆናቸውና ሙሉ በሙሉ ፈውስ የሚያስገኙ ተአምራት መፈጸሙ እንዲሁም ሙታንን እንኳ ለማስነሳት ሲሞክር አንድም ጊዜ ሙከራው መና አለመቅረቱ በእነዚህ ተአምራትና በአሁኑም ሆነ በሌላ በየትኛውም ትውልድ በተፈጸሙ አስመሳይ ድንቆች መካከል ይህ ነው የማይባል ልዩነት አምጥቷል።”
ዓለማዊ ድጋፍ
ምሁሩ አርተር ፒርሰን “በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለተጠቀሱት ተአምራት እውነተኝነት ጠላቶቹ አፋቸውን ከመያዛቸው የበለጠ የሚያስደንቅ ማስረጃ የለም” በማለት የወንጌል ዘገባዎችን የሚደግፍ ሌላ ማሳመኛ ነጥብ አቅርበዋል። የአይሁድ አለቆች ኢየሱስን ለመቃወም ጠንካራ የልብ ፍላጎት ቢኖራቸውም ተአምራቱ በሰፊው ስለ ታወቁ ተቃዋሚዎቹ ሊያስተባብሏቸው አልደፈሩም። ማድረግ የቻሉት እነዚህ ገድሎች በአጋንንታዊ ኃይል እንደተፈጸሙ መናገር ብቻ ነበር። (ማቴዎስ 12:22–24) ኢየሱስ ከሞተ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የአይሁዱ ታልሙድ ጸሐፊዎች ተአምራዊ ኃይል እንደነበረው ማመናቸውን ቀጥለው ነበር። ጁዊሽ ኤክስፕሬሽንስ ኦን ጂሰስ የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው “የአስማት ሥራዎችን እንደሚፈጽም” ሰው አድርገው በመመልከት አንቀበልም አሉት። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ተረት ናቸው እንዲሉ የሚያስችላቸው ትንሽ ፍንጭ እንኳ ቢኖር ኖሮ እንዲህ ዓይነት አስተያየት ይሰጡ ነበርን?
ሌላኛው ማረጋገጫ የመነጨው ከአራተኛው መቶ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ዩሴቢዬስ ነው። ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ቸርች ፍሮም ክራይስት ቱ ኮንስታንቲን በተባለው መጽሐፉ ለንጉሠ ነገሥቱ ክርስትናን የሚደግፍ ደብዳቤ ስለላከ ኳዋድሬተስ ስለሚባል አንድ ሰው ይጠቅሳል። ኳድሬተስ እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ “የመድኃኒታችን ሥራዎች እውነት እንደነበሩ ምንጊዜም ማየት ይቻላል። ተፈውሰውና ከሞት ተነስተው የነበሩት ሰዎች ሲፈወሱና ከሞት ሲነሱ ብቻ ለቅጽበት የታዩ ሳይሆኑ ምንግዜም እነሱን ማየት ይቻላል። መድኃኒታችን ከእኛ ጋር በነበረበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከተለየን ከረጅም ጊዜ በኋላም ቢሆን እነርሱን ማየት ይቻላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ እኔ እሳካለሁበት ጊዜ ድረስ በሕይወት ቆይተዋል።” ዊሊያም ባርክሌይ የተባሉት ምሁር “እሱ እስከኖረበት ጊዜ ድረስ ትክክለኛ እማኝ ሊሆኑ የቻሉ ተአምር የተሰራባቸው ሰዎች እንዳሉ ኳድሬተስ መናገሩ ነው። ይህ እውነት ባይሆን ኖሮ ለሮም መንግሥት የዚህን ውሸተኝነት ከማጋለጥ የሚቀል ምንም ነገር አይኖርም ነበር” ብለዋል።
በኢየሱስ ተአምራት ማመን ምክንያታዊ፣ ግልጽና ከማስረጃው ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነው። የሆነ ሆኖ የኢየሱስ ተአምራት ለዘመናችን ምንም ጥቅም የሌላቸው ታሪኮች አይደሉም። ዕብራውያን 13:8 “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው” በማለት ያስታውሰናል። አዎን፣ ዛሬ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ከፈጸማቸው በእጅጉ የሚልቁ ተአምራታዊ ኃይሎች መፈጸም በሚችልበት ሰማያት ውስጥ ይኖራል። ከዚህም በላይ ስለ ተአምራቱ የሚናገሩት የወንጌል ታሪኮች (1) ላለንበት ጊዜ የሚሠሩ ትምህርቶችን ለክርስቲያኖች ያስተምራሉ (2) አስደናቂ የሆኑትን የኢየሱስን ባሕርያት ገጽታ ያሳያሉ እንዲሁም (3) ከዚህ የላቁ አስገራሚ ነገሮች ወደሚፈጸሙበት በቅርቡ ወደሚመጣው ጊዜ ትኩረታችንን ይስባሉ!
የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እነዚህን ነጥቦች ግልጽ ለማድረግ በሦስት ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ያነጣጥራል።