ለመለኮታዊ ሉዓላዊነት የቆሙ ክርስቲያን ምሥክሮች
‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት በስፋት መናገር አለባችሁ።’—1 ጴጥሮስ 2:9
1. በቅድመ ክርስትና ዘመን ስለ ይሖዋ ምን ውጤታማ የሆነ ምሥክርነት ተሰጥቶ ነበር?
በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ አያሌ ምሥክሮች ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ በድፍረት መሥክረዋል። (ዕብራውያን 11:4 እስከ 12:1) በእምነታቸው ጠንካሮች ስለነበሩ በድፍረት የይሖዋን ሕጎች ከመታዘዛቸውም በተጨማሪ በአምልኮ ረገድ አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኞች አልነበሩም። ለይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ከፍተኛ ምሥክርነት ሰጥተዋል።—መዝሙር 18:21–23፤ 47:1, 2
2. (ሀ) ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ማን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክር በመሆን ረገድ የእስራኤልን ብሔር የተኩት እነማን ናቸው? እንዴት እናውቃለን?
2 ከቅድመ ክርስትና በፊት ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ የላቀውና የመጨረሻው ምሥክር አጥማቂው ዮሐንስ ነበር። (ማቴዎስ 11:11) አጥማቂው ዮሐንስ የተመረጠውን ሰው መምጣት ለማወጅና ኢየሱስ ቃል የተገባለት መሲሕ መሆኑን ለማስታወቅ ልዩ መብት አግኝቷል። (ዮሐንስ 1:29–34) “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” የሆነው ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ የይሖዋ ምሥክር ነው። (ራእይ 3:14) ሥጋዊ እስራኤላውያን ኢየሱስን ስላልተቀበሉትና ይሖዋም እነሱን ስለተዋቸው የአምላክ እስራኤል የሆነውን አዲስ ሕዝብ ምሥክሩ እንዲሆን ሾመው። (ዮሐንስ 1:11, 12፤ ኢሳይያስ 42:8) እንዲህ በማለት ሲናገር ትንቢቱ የክርስቲያን ጉባኤ በሆነው ‘በአምላክ እስራኤል’ ላይ እንደሚሠራ ጠቁሟል፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።”—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ዘጸአት 19:5, 6፤ ኢሳይያስ 43:21፤ 60:2
3. የአምላክ እስራኤልና የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ተቀዳሚ ኃላፊነት ምንድን ነው?
3 የአምላክ እስራኤል ተቀዳሚ ኃላፊነት ስለ ይሖዋ ክብር በሕዝብ ፊት መመሥከር መሆኑን የጴጥሮስ ቃላት ያሳያሉ። በዘመናችን ይህን መንፈሳዊ ብሔር አምላክን በሕዝብ ፊት ከፍ ከፍ የሚያደርጉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ተባብረውታል። ሁሉም ሰው እንዲሰማቸው ጮክ ብለው “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” ይላሉ። (ራእይ 7:9, 10፤ ኢሳይያስ 60:8–10) የአምላክ እስራኤልና ጓደኞቻቸው ምሥክርነታቸውን መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? እምነትና ታዛዥነት በማሳየት ነው።
ሐሰተኛ ምሥክሮች
4. በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ሐሰተኛ ምሥክሮች የነበሩት ለምንድን ነው?
4 እምነትና ታዛዥነት አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እያከበሩ መኖርን ይጠይቃል። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች በተመለከተ በተናገረው ነገር የዚህ አስፈላጊነት ታይቷል። እነዚህ ሰዎች የሕጉ አስተማሪዎች በመሆን ‘በሙሴ ወንበር ተቀምጠው ነበር።’ እንዲያውም አረማውያንን ወደ ራሳቸው ሃይማኖት ለመለወጥ ሲሉ ሚስዮናውያንን ይልኩ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፣ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፣ ወዮላችሁ” ብሏቸዋል። እነዚህ ሃይማኖተኞች ትዕቢተኞች፣ ግብዞችና ፍቅር የሌላቸው ሐሰተኛ ምሥክሮች ነበሩ። (ማቴዎስ 23:1–12, 15) በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንዳንድ አይሁዳውያንን “እናንተ ከአባታቸሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትፈልጋላችሁ” ብሏቸው ነበር። የአምላክ ምርጥ ሕዝብ አባላት የሆኑትን ሰዎች እንደዚህ ሊላቸው የቻለው ለምን ነበር? ምክንያቱም ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ምሥክር የተናገረውን ቃል ስላልተቀበሉ ነው።—ዮሐንስ 8:41, 44, 47
5. ሕዝበ ክርስትና ስለ አምላክ የሰጠችው ምሥክርነት ሐሰት እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?
5 በተመሳሳይም ከኢየሱስ ዘመን በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ የሕዝበ ክርስትና አባላት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ ሲናገሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ ስላላደረጉ በኢየሱስ ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም። (ማቴዎስ 7:21–23፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1–3) ሕዝበ ክርስትና አያሌ ሚስዮናውያንን ልካለች፤ ከእነሱ ብዙዎቹም ቅን አመለካከት እንደነበራቸው አያጠራጥርም። ሆኖም እነዚህ ሚስዮናውያን ኃጢአተኞችን በሲኦል ውስጥ የሚያቃጥለውን ሥላሴ የሚሉትን አምላክ እንዲያመልኩ ሰዎችን አስተምረዋቸዋል፤ በተጨማሪም ወደ ክርስትና እምነት የለወጧቸው አብዛኞቹ ሰዎች ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሚጠቁም መረጃ የላቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ ሩዋንዳ የተባለችው አፍሪካዊቷ አገር ለሮማ ካቶሊክ ሚስዮናውያን ፍሬያማ መሬት ከሆነች ሰነባብታለች። ይህም ሆኖ በሩዋንዳ የሚገኙ ካቶሊኮች በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ በተካሄደው የጎሣ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ተካፍለዋል። በዚህ የሚስዮናዊ መስክ የተገኘው ፍሬ ሕዝበ ክርስትና እውነተኛ ክርስቲያናዊ ምሥክርነት እንዳልሰጠች ያሳያል።—ማቴዎስ 7:15–20
አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማክበር
6. ተገቢ ጠባይ ማሳየት ምሥክርነት በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው በምን በምን መንገዶች ነው?
6 ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የሚያሳዩት መጥፎ ጠባይ ‘በእውነት መንገድ’ ላይ ነቀፋ ያመጣል። (2 ጴጥሮስ 2:2) እውነተኛ ክርስቲያን ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖራል። አይሰርቅም፣ አይዋሽም፣ አያጭበረብርም ወይም የጾታ ብልግና አይፈጽምም። (ሮሜ 2:22) እንደሱው ሰብዓዊ ፍጡራን የሆኑትን ሰዎች በፍጹም አይገድልም። ክርስቲያን ባሎች ቤተሰባቸውን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ያስተዳድራሉ። ሚስቶች ይህን የበላይ ጥበቃ በአክብሮት ይደግፋሉ። ልጆች ከወላጆቻቸው ሥልጠና ስለሚያገኙ ኃላፊነት የሚሰማቸው ክርስቲያኖች ሆነው ያድጋሉ። (ኤፌሶን 5:21 እስከ 6:4) እርግጥ ሁላችንም ፍጹማን ያልሆንና ስሕተት የምንሠራ ሰዎች ነን። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ከመቀበሉም በላይ በተግባር ላይ ለማዋል ከልቡ ይጥራል። ይህም በሌሎች ዘንድ ስለሚስተዋል ጥሩ ምሥክርነት ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ቀደም ሲል እውነትን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች አንድ ክርስቲያን የሚያሳየውን ትክክለኛ ጠባይ ተመልክተው ይለወጣሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12, 15፤ 3:1
7. ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው መዋደዳቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
7 ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ሲናገር የክርስቲያን ጠባይ ዋነኛ ገጽታ የሆነውን ነገር ጠቁሟል። (ዮሐንስ 13:35) የሰይጣን ዓለም ‘በዓመፅ፣ በግፍ፣ በመመኘት፣ በክፋት፤ በቅናት፣ ነፍስ በመግደል፣ በክርክር፣ በተንኮል፣ በክፉ ጠባይ፣ በማንሾካሾክ፣ በሐሜት፣ አምላክን በመጥላት፣ ሰውን በማንገላታት፣ በትዕቢት፣ በትምክህተኛነት፣ ክፋትን በመፈላለግና ለወላጆች ባለመታዘዝ’ ተለይቶ ይታወቃል። (ሮሜ 1:29, 30) እንዲህ ዓይነቱ ተጽዕኖ በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ በፍቅር ተለይቶ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ድርጅት መኖሩ የአምላክ መንፈስ እየሠራ እንዳለ ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚመሠክር ጠንካራ ማረጋገጫ ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ድርጅት ናቸው።—1 ጴጥሮስ 2:17
የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናቸው
8, 9. (ሀ) መዝሙራዊው የአምላክን ሕግ ማጥናቱና በእርሱ ላይ ማሰላሰሉ ያበረታታው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና ማሰላሰላችን ለመመሥከር የሚያበረታታን በምን መንገዶች ነው?
8 አንድ ክርስቲያን ጥሩ በሆነ መንገድ እንዲመሠክር ከተፈለገ የይሖዋን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅና መውደድ እንዲሁም የዓለምን ርኩሰት ከልቡ መጥላት ይኖርበታል። (መዝሙር 97:10) ዓለም በጣም በሚያሳስት መልኩ የራሱን አስተሳሰብና መንፈስ ስለሚያራምድ የዓለምን መንፈስ መቋቋም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 2:1–3፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16) ትክክለኛ የአእምሮ ዝንባሌ ለመያዝ ሊረዳን የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ቋሚና ዓላማ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ነው። የመዝሙር 119 ጸሐፊ ለይሖዋ ሕግ ያለውን ፍቅር በተደጋጋሚ ጊዜያት ገልጿል። ሕጉን “ቀኑን ሁሉ” ማለትም ያለማቋረጥ ያነብበውና በእርሱ ላይ ያሰላስል ነበር። (መዝሙር 119:92, 93, 97–105) በዚህም ምክንያት “ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፤ ሕግህን ግን ወደድሁ” ብሎ ሊጽፍ ችሏል። ከዚህ በላይ በውስጡ ያደረበት የጠለቀ ፍቅር ለተግባር አነሳስቶታል። “ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” ብሏል።—መዝሙር 119:163, 164
9 በተመሳሳይም እኛም ዘወትር የአምላክን ቃል ማጥናታችንና በእርሱ ላይ ማሰላሰላችን ልባችን እንዲነካና ዘወትር እንዲያውም ‘በቀን ሰባት ጊዜ እርሱን እንድናወድሰው’ ይኸውም ስለ ይሖዋ እንድንመሠክር ይገፋፋናል። (ሮሜ 10:10) ከዚህ ጋር በመስማማት የመጀመሪያው መዝሙር ጸሐፊ ዘወትር የይሖዋን ቃላት የሚያሰላስል ሰው “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ብሏል። (መዝሙር 1:3) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ብሎ ሲጽፍ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል ጠቁሟል፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
10. በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ግልጽ የሆነው ነገር ምንድን ነው?
10 በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የእውነተኛ አምላኪዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሄዱ የይሖዋ በረከት እንዳለበት ያሳያል። ያላንዳች ጥርጥር እነዚህ ለመለኮታዊ ሉዓላዊነት የሚመሠክሩ ሰዎች በቡድን ደረጃ በልባቸው ውስጥ ለይሖዋ ሕግ ፍቅር ኮትኩተዋል። እንደ መዝሙራዊው ሁሉ ሕጉን ለመታዘዝና ስለ ይሖዋ ክብር ‘ቀንና ሌሊት’ በታማኝነት ለመመሥከር ተነሳስተዋል።—ራእይ 7:15
ይሖዋ ያደረጋቸው ታላላቅ ተአምራት
11, 12. ኢየሱስና ሐዋርያት የፈጸሟቸው ተአምራት ምን አከናውነዋል?
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ታማኝ ክርስቲያን ምሥክሮች ተአምራትን ማድረግ እንዲችሉ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል፤ ይህም የመሠከሩት ነገር እውነት እንደ ነበር ጠንካራ ማረጋገጫ ሆኗል። አጥማቂው ዮሐንስ በወኅኒ ቤት ውስጥ ሳለ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ” ብለው እንዲጠይቁት ደቀ መዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ ላካቸው። ኢየሱስ እኔ ነኝ ወይም አይደለሁም ብሎ መልስ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለ፦ “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ፣ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው።” (ማቴዎስ 11:3–6) እነዚህ ተአምራት “የሚመጣው” የተባለው በእርግጥም ኢየሱስ እንደ ነበረ ለዮሐንስ መሥክረዋል።—ሥራ 2:22
12 በተመሳሳይም አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የታመሙ ሰዎችን ፈውሰዋል፤ እንዲያውም የሞቱ ሰዎችን አስነስተዋል። (ሥራ 5:15, 16፤ 20:9–12) እነዚህ ተአምራቶች አምላክ ራሱ ስለ እነሱ የሰጠው ምሥክርነት ነበሩ ማለት ይቻላል። (ዕብራውያን 2:4) በተጨማሪም እነዚህ ሥራዎች ይሖዋ ሁሉን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንዳለው አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን ለመግደል የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑ እሙን ነው። (ዮሐንስ 14:30፤ ዕብራውያን 2:14) ሆኖም ጴጥሮስ ዶርቃ የተባለችውን ታማኝ ሴት ከሞት ሲያስነሣት ድርጊቱን መፈጸም የሚችለው በይሖዋ ኃይል ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም ሕይወትን መልሶ መስጠት የሚችለው እርሱ ብቻ ነው።—መዝሙር 16:10፤ 36:9፤ ሥራ 2:25-27
13. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ተአምራት አሁንም ቢሆን ስለ ይሖዋ ኃይል የሚመሠክሩት በምን መንገድ ነው? (ለ) የትንቢቶች መፈጸም የይሖዋን አምላክነት በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተው እንዴት ነው?
13 በአሁኑ ወቅት እነዚህ ተአምራታዊ ሥራዎች አይፈጸሙም። የታቀደላቸውን ዓላማ አከናውነዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ያም ሆኖ ግን ብዙ ተመልካቾች የመሠከሩላቸው ተአምራት አሁንም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው እናገኛለን። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች እነዚህን ታሪካዊ ዘገባዎች ለሌሎች ሰዎች ሲያሳውቁ ተአምራቱ በአሁኑ ጊዜም ስለ ይሖዋ ኃይል ውጤታማ ምሥክርነት ይሰጣሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:3–6) በተጨማሪም ይሖዋ ትክክለኛ ትንቢት መናገሩ እውነተኛ አምላክ ለመሆኑ ጉልህ ማረጋገጫ እንደሚሆን በኢሳይያስ ዘመን ጠቁሟል። (ኢሳይያስ 46:8–11) በአሁኑ ወቅት በክርስቲያን ጉባኤ ላይ የተፈጸሙትን በርካታ ትንቢቶች ጨምሮ ሌሎች በመንፈስ አነሣሽነት የተነገሩ ብዙ ትንቢቶች እየተፈጸሙ ነው። (ኢሳይያስ 60:8–10፤ ዳንኤል 12:6–12፤ ሚልክያስ 3:17, 18፤ ማቴዎስ 24:9፤ ራእይ 11:1–13) የእነዚህ ትንቢቶች መፈጸም “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ እንደምንኖር በትክክል ከማመልከቱም በላይ ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
14. ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን ጉልህ በሆነ መንገድ የሚመሠክረው በምን በምን መንገዶች ነው?
14 ይሖዋ አሁንም ቢሆን ለሕዝቦቹ ታላላቅና አስገራሚ ነገሮችን ያደርግላቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ እየጨመረ የሚሄደው ብርሃን በይሖዋ መንፈስ መሪነት የተገኘ ነው። (መዝሙር 86:10፤ ራእይ 4:5, 6) በዓለም ዙሪያ ሪፖርት የተደረገው ከፍተኛ ጭማሪ ይሖዋ ‘በዘመኑ እያፋጠነው እንዳለ’ ያሳያል። (ኢሳይያስ 60:22) በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የይሖዋ ሕዝቦች በተለያዩ አገሮች መራራ ተቃውሞ እያጋጠማቸው በድፍረት ሊጸኑ የቻሉት መንፈስ ቅዱስ ስላበረታቸው ነው። (መዝሙር 18:1, 2, 17, 18፤ 2 ቆሮንቶስ 1:8–10) አዎን፣ ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ራሱ ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን ጉልህ በሆነ መንገድ ይመሠክራል።—ዘካርያስ 4:6
ምሥራቹ መሰበክ ይኖርበታል
15. በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ምን ሰፊ ምሥክርነት መሰጠት ነበረበት?
15 ይሖዋ በአሕዛብ ፊት እንዲመሠክሩለት እስራኤላውያንን ሾሟቸው ነበር። (ኢሳይያስ 43:10) ሆኖም እስራኤላውያን ወዳልሆኑ ሰዎች ሄደው እንዲሰብኩ መለኮታዊ ትእዛዝ የተቀበሉት ጥቂት እስራኤላውያን ብቻ ነበሩ፤ ይህም አብዛኛውን ጊዜ የተደረገው የይሖዋን ፍርዶች ለማወጅ ሲባል ነበር። (ኤርምያስ 1:5፤ ዮናስ 1:1, 2) ይሁንና ይሖዋ አንድ ቀን በከፍተኛ ደረጃ ትኩረቱን በአሕዛብ ላይ እንደሚያደርግ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶች ይጠቁማሉ፤ በእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ መሠረት በመንፈሳዊ የአምላክ እስራኤል አማካኝነት በአሕዛብ ላይ ትኩረት እያደረገ ነው። (ኢሳይያስ 2:2–4፤ 62:2) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተከታዮቹን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ኢየሱስ ‘ከእስራኤል ቤት በጠፉት በጎች’ ላይ ያተኮረ ቢሆንም ተከታዮቹ ወደ ‘አሕዛብ ሁሉ’ እንዲያውም ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ተልከው ነበር። (ማቴዎስ 15:24፤ ሥራ 1:8) ክርስቲያኖች የሚሰጡትን ምሥክርነት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት ያስፈልጋል።
16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የትኛውን ተልእኮ ፈጽሟል? እስከ ምን ድረስ?
16 ጳውሎስ ይህን በሚገባ እንደተረዳ አሳይቷል። በ61 እዘአ ምሥራቹ ‘በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው’ ለማለት ችሎ ነበር። ምሥራቹ የተሰበከው ለአንድ ብሔር ወይም ‘በመላእክት አምልኮ’ ይሳተፍ እንደ ነበረው ቡድን ላለ ለአንድ የሃይማኖት ቡድን ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በግልጽ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው።” (ቆላስይስ 1:6, 23፤ 2:13, 14, 16–18) በዚህ መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአምላክ እስራኤል አባላት ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራቸውን የእርሱን በጎነት እንዲናገሩ’ የተሰጣቸውን ተልእኮ ፈጽመዋል።
17. ማቴዎስ 24:14 በከፍተኛ ደረጃ መፈጸሙን የቀጠለው እንዴት ነው?
17 ይሁንና የመጀመሪያው መቶ ዘመን የስብከት ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ለሚከናወነው ስብከት ቅምሻ ብቻ የሚሆን ነበር። ኢየሱስ በተለይ የእኛን ዘመን አስቀድሞ በመመልከት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) ይህ ትንቢት ሲፈጸም ቆይቷልን? አዎን፣ ሲፈጸም ቆይቷል። የምሥራቹ ስብከት በ1919 ከነበረበት አነስተኛ ጅምር ተነሥቶ በአሁኑ ወቅት ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ተስፋፍቷል። ቀዝቃዛ በሆነው አርክቲክ አቅራቢያ ባሉ ክልሎችና በጣም ሞቃታማ በሆነው በሐሩር ክልል በሚገኙ አገሮች ውስጥ ምሥክርነቱ ተሰጥቷል። በትላልቆቹ አህጉሮች ምሥክርነቱ የተሰጠ ከመሆኑም በላይ ራቅ ባሉ ደሴቶች ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች ምሥክርነቱ እንዲዳረስ ለማድረግ ተጥሯል። በቦስኒያ እና በሄርዞጎቪና የሚካሄደው ጦርነት ዓይነት ከፍተኛ ብጥብጥ ባሉባቸው ቦታዎችም እንኳ ምሥራቹ መሰበኩን ቀጥሏል። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ የተሰጠው ምሥክርነት “በመላው ዓለም” ፍሬ በማፍራት ላይ ነው። ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በግልጽ እየታወጀ ነው። ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ እስራኤል ቀሪዎች “ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ” ተሰበሰቡ። በሁለተኛ ደረጃ በሚልዮን የሚቆጠሩት “እጅግ ብዙ ሰዎች” “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” መምጣት ጀመሩ። (ራእይ 5:9፤ 7:9) ማቴዎስ 24:14 በከፍተኛ ደረጃ መፈጸሙን ቀጥሏል።
18. ምሥራቹ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በመሰበኩ እየተከናወኑ ያሉት አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
18 ምሥራቹ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እየተሰበከ መሆኑ ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘት መጀመሩን ያረጋግጣል። (ማቴዎስ 24:3) በተጨማሪም ይህ ስብከት ሰዎችን የሰው ልጆች ብቸኛና እውነተኛ ተስፋ ወደ ሆነችው ወደ ይሖዋ መንግሥት ስለሚመራ “የምድሪቱ መከር” የሚታጨድበት ዋነኛ መንገድ ነው። (ራእይ 14:15, 16) ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የሚሳተፉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቻ ስለሆኑ ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች ለይቶ ለማወቅ ይረዳል። (ሚልክያስ 3:18) በዚህ መንገድ ለሚሰብኩትም ሆነ ለስብከቱ አዎንታዊ ምላሽ ለሚያሳዩ ሰዎች መዳን ያስገኝላቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ከሁሉም በላይ ግን ምሥራቹን መስበክ ሥራው እንዲሠራ ያዘዘው፣ ሥራውን የሚሠሩትን የሚደግፋቸውና ፍሬያማ እንዲሆን የሚያደርገው ይሖዋ አምላክ እንዲወደስና እንዲከበር ያደርጋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7
19. በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ቁርጥ ውሳኔ እንዲይዙ ይበረታታሉ?
19 ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” ለማለት መገፋፋቱ አያስደንቅም። (1 ቆሮንቶስ 9:16) በአሁኑ ወቅት ያሉት ክርስቲያኖችም እንደዚሁ ይሰማቸዋል። “የአምላክ የሥራ ባልደረባ” ሆኖ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ዓለም ውስጥ የእውነትን ብርሃን ማብራት ታላቅ መብትና ከባድ ኃላፊነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:9 አዓት ፤ ኢሳይያስ 60:2, 3) በ1919 አነስተኛ ጅምር የነበረው ይህ ሥራ አሁን በጣም አስደናቂ ደረጃ ላይ ደርሷል። ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ክርስቲያኖች የመዳንን መልእክት ለሌሎች ለማድረስ ከአንድ ቢልዮን በላይ ሰዓት በሚያሳልፉበት ወቅት ለመለኮታዊ ሉዓላዊነት ይመሠክራሉ። የይሖዋን ስም በሚያስቀድሰው በዚህ ሥራ ላይ ተካፋይ መሆን ምንኛ ያስደስታል! በ1996 የአገልግሎት ዓመት ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዳይቀንስ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ከዚህ ይልቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ “ቃሉን በጥድፊያ ስሜት ስበክ” የሚሉትን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የተናገራቸውን ቃላት እንታዘዛለን። (2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት) ይህን ስናደርግ ይሖዋ ጥረቶቻችን መባረኩን እንዲቀጥል በሙሉ ልባችን እንጸልያለን።መሆኑን የሚያረጋግጠው በምን መንገድ ነው?
ታስታውሳለህን?
◻ ለአሕዛብ “ምሥክሮች” በመሆን ረገድ እስራኤልን የተኩት እነማን ናቸው?
◻ ክርስቲያናዊ ጠባይ ለመመሥከሩ ተግባር አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በእርሱ ላይ ማሰላሰል ለክርስቲያን ምሥክሮች በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን የሚያረጋግጠው በምን መንገድ ነው?
◻ ምሥራቹ መሰበኩ ምን ነገር እንዲከናወን አድርጓል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአሁኑ ወቅት ምሥራቹ በአንድ ቦታ ብቻ ከመወሰን ይልቅ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በመታወጅ ላይ ነው