በረከት ወይም መርገም ዛሬ ለምንኖረው የሚሆኑ ምሳሌዎች
“ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባቸው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው፤የተጻፈውም በዘመናት መጨረሻ ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ነው።”—1 ቆሮንቶስ 10:11 የ1980 ትርጉም
1. አንድ ሰው አንድን ዕቃ እንደሚመረምር ሁሉ ምን ምርመራ ማድረግ ይኖርብናል?
አንድ ከብረት የተሠራ ዕቃ ከላይ ቀለም ቢቀባም ውስጥ ውስጡን በዝገት መበላት ሊጀምር ይችላል። ዝገቱ ከላይ እስኪታይ ድረስ ጥቂት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። በተመሳሳይም የአንድ ሰው ዝንባሌና ምኞት ከባድ መዘዞችን ከማስከተሉ ወይም ደግሞ በሌሎች ሰዎች ከመታወቁ ከረጅም ጊዜ በፊት መበላሸት ጀምሮ ሊሆን ይችላል። አንድ ዕቃ ዝጎ እንደሆነና እንዳልሆነ መመልከታችን ጥበብ እንደሆነ ሁሉ ልባችንን በጥብቅ መመርመራችንና ወቅታዊ ጥገና ማድረጋችን ክርስቲያናዊ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያስችለናል። በሌላ አነጋገር የአምላክን በረከቶች ልናገኝና ከመለኮታዊ መርገሞች ልንጠበቅ እንችላለን። አንዳንዶች ለጥንቷ እስራኤል የተነገሩት በረከቶችና መርገሞች የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ከፊታቸው ለተደቀነባቸው ሰዎች ምንም ትርጉም የላቸውም ብለው ያስቡ ይሆናል። (ኢያሱ 8:34, 35፤ ማቴዎስ 13:49, 50፤ 24:3) ሆኖም ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ላይ እንደተገለጸው በእስራኤላውያን ላይ ስለደረሱት ሁኔታዎች ከሚናገሩት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ከፍተኛ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን።
2. እስራኤላውያን በምድረ በዳ ስላጋጠሟቸው ነገሮች 1 ቆሮንቶስ 10:5, 6 ምን ይላል?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ ይመራቸው የነበሩትን እስራኤላውያን ክርስቶስ ከሚመራቸው ክርስቲያኖች ጋር አወዳድሯል። (1 ቆሮንቶስ 10:1-4) የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት ይችሉ የነበረ ቢሆንም “እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፣ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።” ስለሆነም ጳውሎስ ክርስቲያን ጓደኞቹን “እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:5, 6፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የተለያየ ምኞት የሚያድገው በልብ ውስጥ ስለሆነ ጳውሎስ የጠቀሳቸውን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ልብ ልንላቸው ይገባል።
ጣዖት አምልኮን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
3.እስራኤላውያን ከወርቁ ጥጃ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ኃጢአት የሠሩት እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ በመጀመሪያ ያስጠነቀቀው “ሕዝ[ቡ]ም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ” በማለት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:7፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እስራኤላውያን ወደ ግብፃውያን አካሄድ ዞር በማለት የወርቅ ጥጃ በመሥራት ጣዖት እንዳመለኩ የሚገልጽ ነው። (ዘጸአት ምዕራፍ 32) ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ እንዲህ በማለት በተናገረበት ወቅት የችግሩን ዋነኛ መንስኤ ጠቁሟል፦ “አባቶቻችን (የአምላክ ወኪል የነበረውን ሙሴን) ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤ አሮንንም፦ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት። በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፣ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው።” (ሥራ 7:39-41) ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ወደ ጣዖት አምልኮ የመራቸው ‘በልባቸው’ ውስጥ ያደረው የተሳሳተ ምኞት እንደነበር አስተውሉ። “ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ።” ከዚህም በላይ “በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው።” ሙዚቃ፣ ዘፈን፣ ጭፈራ፣ መብልና መጠጥ ነበር። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የጣዖት አምልኮው የሚያታልልና የሚያስደስት ነበር።
4, 5. ከየትኞቹ የጣዖት አምልኮ ድርጊቶች መታቀብ ይኖርብናል?
4 የግብፅ አምሳያ የሆነው የሰይጣን ዓለም ልክ እንደዚሁ መዝናኛን ያመልካል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 11:8) የፊልም ተዋንያንን፣ ዘፋኞችን፣ ኮከብ ስፖርተኞችን እንዲሁም ዳንሳቸውን፣ ሙዚቃቸውንም ሆነ እነርሱ ስለ ደስታና ስለ መዝናኛ ያላቸውን አመለካከት እንደ ጣዖት ያመልካሉ። ብዙዎች ይሖዋን እናመልካለን እያሉም እንኳን በመዝናኛ ሙሉ በሙሉ ለመዋጥ ተፈትነዋል። አንድ ክርስቲያን መጥፎ ድርጊት በመፈጸሙ ምክንያት የግድ ተግሣጽ መስጠት በሚያስፈልግበት ወቅት ብዙውን ጊዜ መንፈሳዊነቱ ሊዳከም የቻለው የአልኮል መጠጦችን በመጠጣቱ፣ በዳንስና ወደ ጣዖት አምልኮ በሚጠጋ አንድ ዓይነት መዝናኛ በመካፈሉ እንደሆነ ተደርሶበታል። (ዘጸአት 32:5, 6, 17, 18) አንዳንድ መዝናኛ ጠቃሚና አስደሳች ነው። ሆኖም በዛሬው ጊዜ አብዛኛው ዓለማዊ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ፊልም ወይም ቪዲዮ መጥፎ ሥጋዊ ምኞት የሚቀሰቅስ ነው።
5 እውነተኛ ክርስቲያኖች ለጣዖት አምልኮ አይሸነፉም። (2 ቆሮንቶስ 6:16፤ 1 ዮሐንስ 5:21) ሁላችንም የጣዖት አምልኮ ለሚንጸባረቅበት መዝናኛ ሱሰኛ ከመሆንና በዓለማዊ መንገድ መዝናናት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች እንጠንቀቅ። ለዓለማዊ ተጽዕኖዎች ከተንበረከክን ጎጂ ምኞቶችና ዝንባሌዎች በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እያየሉ ይሄዳሉ። እነዚህን ነገሮች ካላስተካከልናቸው ከጊዜ በኋላ በሰይጣን ሥርዓት ‘ምድረ በዳ ውስጥ ወድቀን’ እንቀራለን።
6. መዝናኛን በተመለከተ ምን አዎንታዊ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልገን ይችላል?
6 ሙሴ የወርቁ ጥጃ በተመለከተ እንዳደረገው ሁሉ “ታማኝና ልባም ባሪያ”ም “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ!” በማለት ላይ ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ጎን የተሰለፍን መሆናችንን የሚያሳይ አዎንታዊ እርምጃ መውሰዳችን ሕይወት አድን ተግባር ሊሆን ይችላል። የሙሴ ነገድ የሆነው የሌዊ ነገድ ወራዳ ተጽዕኖዎችን ለማስወገድ ወዲያውኑ እርምጃ ወስዷል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ዘጸአት 32:26-28) ስለዚህ የመዝናኛ፣ የሙዚቃ፣ የቪዲዮና የመሳሰሉት ነገሮች ምርጫህን በጥንቃቄ መርምር። የመዝናኛ ምርጫህ በአንድ ዓይነት ሁኔታ አቋምን የሚያበላሽ ሆኖ ካገኘኸው ከይሖዋ ጎን መቆምህን የሚያሳይ እርምጃ ውሰድ። በጸሎት አማካኝነት በአምላክ በመታመን በመዝናኛና በሙዚቃ ምርጫህ ረገድ ለውጦችን አድርግ፤ ሙሴ የወርቁን ጥጃ እንዳስወገደው ሁሉ በመንፈሳዊ የሚጎዳህን ነገር አጥፋ።—ዘጸአት 32:20፤ ዘዳግም 9:21
7. ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
7 የልብ ዝገትን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ወደ አእምሯችንና ወደ ልባችን ጠልቀው እንዲገቡ በመፍቀድ ነው። (ሮሜ 12:1, 2) እርግጥ ነው፣ ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይኖርብናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ምንም ተሳትፎ ሳያደርጉ በስብሰባ ላይ መገኘት የዛገውን የብረት ክፍል ቀለም ከመቀባት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ለጊዜው ፊታችን እንዲፈካ ቢያደርግም ውስጥ የተደበቀውን ችግር አያስወግድም። ከዚህ ይልቅ አስቀድመን በመዘጋጀት፣ በማሰላሰልና በስብሰባዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በምሳሌያዊ ልባችን ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉትን የሚያዝጉ ነገሮች ፍግፍግ አድርገን ልናስወግድ እንችላለን። ይህም የአምላክን ቃል አጥብቀን ለመከተል፣ በእምነታችን ላይ የሚመጡትን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ለማግኘትና ‘በሁሉም ነገር ጤነኞች እንድንሆን’ ይረዳናል።—ያዕቆብ 1:3, 4፤ ምሳሌ 15:28
ዝሙትን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
8-10. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 10:8 ላይ የተጠቀሰው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ምንድን ነው? (ለ) በማቴዎስ 5:27, 28 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሊሠራባቸው የሚችለው እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ ቀጥሎ በጠቀሰው ምሳሌ ላይ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን” የሚል ምክር ተሰጥቶናል።a (1 ቆሮንቶስ 10:8) ሐዋርያው የጠቀሰው እስራኤላውያን ለሐሰት አማልክት የሰገዱበትንና ‘ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዘሩበትን’ ጊዜ ነው። (ዘኁልቁ 25:1-9) የጾታ ብልግና መፈጸም ሕይወት ያሳጣል! የብልግና ሐሳቦችንና ምኞቶችን አለመቆጣጠር ልብ “እንዲዝግ” የመፍቀድ ያህል ይቆጠራል። ኢየሱስ “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ብሏል።—ማቴዎስ 5:27, 28
9 ከኖኅ የውኃ ጥፋት በፊት የነበሩት ዓመፀኛ መላእክት በነበራቸው ወራዳ አስተሳሰብ ምክንያት የደረሰባቸው ነገር ‘ሴትን በምኞት መመልከት’ የሚያስከትለውን መዘዝ ያሳያል። (ዘፍጥረት 6:1, 2) በተጨማሪም በንጉሥ ዳዊት ሕይወት ውስጥ ከተከሰቱት አሳዛኝ ሁኔታዎች ሁሉ የከፋው አንዲትን ሴት ተገቢ ባልሆነ መንገድ መመልከቱን በመቀጠሉ የተከሰተው ሁኔታ እንደሆነ አስታውስ። (2 ሳሙኤል 11:1-4) ከዚህ በተቃራኒ ባለትዳር የነበረው ጻድቁ ኢዮብ ‘ቆንጆይቱን ላለመመልከት ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር፤’ በዚህ መንገድ ከሥነ ምግባር ብልግና በመቆጠብ ንጹሕ አቋም ጠባቂ መሆኑን አስመስክሯል። (ኢዮብ 31:1-3, 6-11) ዓይን የልብ መስኮት ነው ሊባል ይችላል። በተጨማሪም ብዙ ክፉ ነገሮች የሚመነጩት ከመጥፎ ልብ ነው።—ማርቆስ 7:20-23
10 የኢየሱስን ምክር የምንከተል ከሆነ የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ሥዕሎችን በመመልከት ወይም አንድን ሌላ ክርስቲያን፣ የሥራ ባልደረባን ወይም ማንኛውንም ሰው በተመለከተ የብልግና ሐሳቦች በአእምሯችን እንዲመላለሱ በመፍቀድ ለተሳሳቱ ሐሳቦች ቦታ አንሰጥም። እንዲያው ከላይ ከላይ በመጥረግ ብቻ ዝገትን ከብረት ላይ ማስለቀቅ አይቻልም። ስለዚህ የብልግና ሐሳቦችንና ዝንባሌዎችን አነስተኛ እንደሆኑ ነገሮች አድርገህ በመመልከት ችላ አትበላቸው። የብልግና ዝንባሌዎችን ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃዎችን ውሰድ። (ከማቴዎስ 5:29, 30 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስ የእምነት ጓደኞቹን እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል፦ “በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።” አዎን፣ እንደ ጾታ ብልግና ባሉት ነገሮች ምክንያት “የእግዚአብሔር ቁጣ” የመርገም መግለጫ ሆኖ “ይመጣል።” ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች አኳያ የአካል ክፍሎቻችንን ‘መግደል’ ይኖርብናል።—ቆላስይስ 3:5, 6
በዓመፀኝነት መንፈስ ማማረርን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
11, 12. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 10:9 ላይ ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል? እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሰው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የጳውሎስ ማስጠንቀቂያ እኛን የሚነካን እንዴት ነው?
11 ጳውሎስ በመቀጠል “ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 10:9) እስራኤላውያን በኤዶም አቅራቢያ በሚገኝ ምድረ በዳ በሚጓዙበት ወቅት “በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፣ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ [በተአምር የተሰጣቸውን መና] ተጸየፈ ብለው ተናገሩ።” (ዘኁልቁ 21:4, 5) እስቲ አስበው! እነዚያ እስራኤላውያን ዝግጅቶቹን በመናቅ ‘በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ቃል ተናገሩ’!
12 እስራኤላውያን በማጉረምረማቸው የይሖዋን ትዕግሥት ፈትነዋል። ይሖዋ በመካከላቸው ብዙ መርዛማ እባቦችን ልኮ አያሌ ሰዎች በእባብ ተነድፈው ስለሞቱ ቅጣት ቀምሰዋል። ሕዝቡ ንስሐ ገብተው ሙሴ ስለ እነርሱ ከማለደ በኋላ መቅሰፍቱ ተከለከለ። (ዘኁልቁ 21:6-9) በእነርሱ ላይ የደረሰው ይህ ሁኔታ በተለይ በአምላክና በቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶቹ ላይ የዓመፀኝነትና የማማረር መንፈስ እንዳናሳይ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል።
ማጉረምረምን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
13. አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 10 የሚያስጠነቅቀን ከምንድን ነው? ጳውሎስ በአእምሮው ይዞት የነበረው የትኛውን ዓመፅ ነው?
13 ጳውሎስ በምድረ በዳ የነበሩትን እስራኤላውያን በተመለከተ የመጨረሻውን ምሳሌ ሲጠቅስ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐራጒሩ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:10) ቆሬ፣ ዳታን፣ አቤሮንና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ቲኦክራሲያዊ ያልሆነ አቋም በያዙበትና የሙሴንና የአሮንን ሥልጣን በተቃወሙበት ወቅት ዓመፅ ፈነዳ። (ዘኁልቁ 16:1-3) ዓመፀኞቹ ከጠፉ በኋላ እስራኤላውያን ማጉረምረም ጀመሩ። ይህን ያደረጉት በዓመፀኞቹ ላይ የደረሰው ጥፋት ተገቢ አይደለም ብለው ስላሰቡ ነው። ዘኁልቁ 16:41 “እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ” በማለት ስለ ሁኔታው ይገልጻል። በዚያን ወቅት ፍትሕ የተደረገበትን መንገድ በመንቀፋቸው ምክንያት 14,700 እስራኤላውያን በመለኮታዊ መቅሰፍት ጠፉ።—ዘኁልቁ 16:49
14, 15. (ሀ) ወደ ጉባኤው ሾልከው የገቡት “ኃጢአተኞች” ከፈጸሟቸው ኃጢአቶች አንዱ ምን ነበር? (ለ) ቆሬን ካጋጠመው ሁኔታ ምን መማር ይቻላል?
14 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው የገቡ “አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች” ሐሰተኛ አስተማሪዎችና አጉረምራሚዎች ሆነው ነበር። እነዚህ “ጌትነትን የሚንቁና ክብር ያላቸውን” ማለትም በዚያን ጊዜ በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ የበላይ ጥበቃ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩትን ቅቡዓን ‘የሚሳደቡ’ ሰዎች ነበሩ። በተጨማሪም ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ በአምላክ ላይ ያመፁ ከሃዲዎችን በተመለከተ “እነዚህ ሰዎች ስለ ሕይወት ዕጣቸው የሚያጉረመርሙና የሚያማርሩ ናቸው፣ የራሳቸውን ምኞት ይከተላሉ” ብሏል። (ይሁዳ 3, 4, 8, 16) በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ግለሰቦች በመንፈሳዊ የሚያዝግ አመለካከት በልባቸው ውስጥ እንዲያድግ ስለፈቀዱ አጉረምራሚዎች ሆነዋል። ብዙውን ጊዜ በጉባኤው ውስጥ በበላይ ጠባቂነት ቦታ የሚያገለግሉት ሰዎች ባለባቸው አለፍጽምና ላይ ስለሚያተኩሩ በእነርሱ ላይ ማጉረምረም ይጀምራሉ። አጉረምራሚነታቸው ሌላው ቀርቶ ‘የታማኙን ባሪያ’ ጽሑፎች እስከ መተቸት ይደርሳል።
15 አንድን ቅዱስ ጹሑፋዊ ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በቅን ልቦና ጥያቄዎችን ማቅረብ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጓደኞቻችን ጋር ሆነን ወደ መተቸት የሚመራ አፍራሽ አመለካከት ብናዳብርስ? ራሳችንን እንዲህ በማለት ብንጠይቅ ጥሩ ነው፦ ‘ይህ ማጉረምረም ምን ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል? ከማጉረምረም ይልቅ ጥበብ ለማግኘት በትሕትና መጸለይ ከሁሉ የተሻለ አይደለምን?’ (ያዕቆብ 1:5-8፤ ይሁዳ 17-21) በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ያመፁት ቆሬና ደጋፊዎቹ አመለካከታቸው ተገቢ እንደሆነ ስለተሰማቸው ዝንባሌዎቻቸውን ሳይመረምሩ ቀርተው ይሆናል። ሆኖም ፈጽሞ ተሳስተዋል። በቆሬና በሌሎች ዓመፀኞች ላይ በደረሰው ጥፋት ያጉረመረሙት እስራኤላውያንም ትክክለኛ አመለካከት እንዳላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ያሉት ምሳሌዎች ውስጣዊ ዝንባሌያችንን እንድንመረምር፣ የማጉረምረም ወይም የማማረርን መንፈስ እንድናስወግድ እንዲገፋፉንና ይሖዋ እንዲያጠራን ራሳችንን እንድናቀርብ እንዲያደርጉን መፍቀድ ምንኛ ጥበብ ነው!—መዝሙር 17:1-3
ትምህርት መውሰድና በረከቶቹን ማግኘት
16. በ1 ቆሮንቶስ 10:11, 12 ላይ ያለው ምክር የያዘው ሐሳብ ምንድን ነው?
16 ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት እንዲህ የሚል ጥብቅ ምክር በመስጠት የማስጠንቀቂያ መልእክቶቹን ዝርዝር አጠቃልሏል፦ “ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባቸው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው፤ የተጻፈውም በዘመናት መጨረሻ ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ነው። ስለዚህ የቆመ የሚመስለው ሰው፣ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1 ቆሮንቶስ 10:11, 12 የ1980 ትርጉም) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለንን ቦታ አቅልለን አንመልከተው።
17. በልባችን ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ እንዳለ ከተሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ብረት የመዛግ ባሕርይ እንዳለው ሁሉ የኃጢአተኛው የአዳም ዝርያዎች የሆንን በሙሉ የክፋት ዝንባሌ ወርሰናል። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 5:12) ስለሆነም በልባችን ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ እንዳለ ከተሰማን ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ቁርጥ ያለ እርምጃ እንውሰድ። ብረት እርጥበት ላዘለ አየርና የሚያዝግ ኬሚካል ላለበት አካባቢ ሲጋለጥ የዝገቱ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይፋጠናል። እኛም ለሰይጣን ዓለም “አየር” ከመጋለጥ መቆጠብ ይኖርብናል። ይህም የረከሰ መዝናኛውን፣ በየትኛውም ስፍራ የተስፋፋውን የሥነ ምግባር ብልግናና አፍራሽ ዝንባሌ ይጨምራል።—ኤፌሶን 2:1, 2
18. የሰው ልጆችን መጥፎ ዝንባሌዎች በተመለከተ ይሖዋ ምን አድርጓል?
18 ይሖዋ ሰዎች የወረሷቸውን የተሳሳቱ ዝንባሌዎች ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት አድርጎላቸዋል። በእርሱ የሚያምኑ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አንድያ ልጁን ሰጥቶናል። (ዮሐንስ 3:16) የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ ከተከተልንና ክርስቶስ መሰል ባሕርይ ካንጸባረቅን ለሌሎች ሰዎች በረከት እንሆናለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) በተጨማሪም መርገሞችን ሳይሆን መለኮታዊ በረከቶችን እናገኛለን።
19. ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችን ስንመረምር ምን ጥቅሞችን ልናገኝ እንችላለን?
19 እኛ በዛሬው ጊዜ የምንኖር ሰዎች በጥንት ዘመን እንደነበሩት እስራኤላውያን ለስሕተት የተጋለጥን ብንሆንም መመሪያ የሚሆነን የተሟላ የአምላክ ቃል አለን። ይህን መጽሐፍ ስናነብ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላደረጋቸው ነገሮችም ሆነ ‘የክብሩ ነጸብራቅና የባሕሪው ትክክለኛ ምሳሌ’ በሆነው በኢየሱስ ምሳሌነት ስለ ታዩት ባሕርያቱ እንማራለን። (ዕብራውያን 1:1-3፤ ዮሐንስ 14:9, 10) በጸሎትና ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት በማጥናት “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ሊኖረን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) ፈተናና ሌሎች እምነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ሲያጋጥሙን የጥንት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች በተለይም ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን የላቀ ምሳሌ ብንመረምር ልንጠቀም እንችላለን። እንዲህ ካደረግን መለኮታዊ መርገሞች አይደርሱብንም። ከዚህ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን ሞገስ ወደፊት ደግሞ ዘላለማዊ በረከቶቹን እናገኛለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሐምሌ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ጳውሎስ ጣዖት አምላኪዎች እንዳንሆን የሰጠንን ምክር ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ሐዋርያው ዝሙትን በተመለከተ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
◻ ከማጉረምረምና ከማማረር መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ከመርገሞች ይልቅ መለኮታዊ በረከቶችን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መለኮታዊ በረከቶችን ለማግኘት ከፈለግን ከጣዖት አምልኮ መራቅ አለብን
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዝገት መወገድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ከልባችን ውስጥ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ለማስወገድ አዎንታዊ እርምጃ እንውሰድ