“በአምላክ ቤተ መቅደስ” እና በግሪክ ጣዖታት መካከል ስምምነት ሊኖር ይችላልን?
ወቅቱ በጋ ስለሆነ ቀኑ በጣም ይሞቃል፤ ፀሐዩ ከሚያንፀባርቁት ድንጋዮች ላይ እየነጠረ ሽቅብ ይጋረፋል። ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ ሙቀት በተራራው አናት ላይ ወደሚገኘው የጸሎት ቤት በመጓዝ ላይ ያሉትን የግሪክ ኦርቶዶክስ ምእመናን ቅንዓትና ቆራጥነት አልቀነሰውም።
በጣም ሩቅ ከሆነ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ድክም ያላቸው አንዲት አሮጊት እንደምንም እግራቸውን እየጎተቱ ሲጓዙ ትመለከታለህ። ትንሽ ከፍ ስትል ደግሞ እየተጋፉ የሚሄዱትን ሰዎች ቀድሞ ተራራውን ለመውጣት የሚፍጨረጨር ላብ በላብ የሆነ ሰው ትመለከታለህ። አንዲት ልጃገረድ ከፍተኛ ሕመምና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በፊቷ ላይ እየተነበበባት፣ ጉልበቷ ክፉኛ እየደማ በእምብርክኳ ተራራውን ስትወጣ ትመለከታለህ። ግባቸው ምንድን ነው? በዕለቱ የሚከበረው “ቅዱስ” ምስል ሲወጣ በዚያ ተገኝተው በፊቱ ለመጸለይ፣ ከተቻለም ምስሉን ለመንካትና ለመሳለም ነው።
በዓለም ዙሪያ “ቅዱሳን” በሚመለኩበት ሥፍራ ሁሉ እንዲህ ዓይነቱን ትእይንት መመልከት የተለመደ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻልበትን ትክክለኛ መንገድ እየተከተሉ እንዳሉና በዚህ ሁኔታ አምልኮታዊ ፍቅራቸውንና እምነታቸውን የገለጹ ሆኖ እንደሚሰማቸው ግልጽ ነው። የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነታችን (Our Orthodox Christian Faith) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እኛ [“የቅዱሳንን”] በዓል እናከብራለን፤ ለቅድስናቸውም ምስጋናና ክብር እናቀርባለን። . . . እንዲሁም ስለ እኛ ወደ አምላክ ጸሎትና ምልጃ እንዲያቀርቡና በሕይወታችን ውስጥ በሚያስፈልጉን ነገሮች ሁሉ እንዲረዱን እንለምናቸዋለን። . . . በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ለሚያስፈልጉን ነገሮች . . . ተአምር ሠሪ የሆኑ ቅዱሳን እንዲደርሱልን እንማጸናቸዋለን።” በተጨማሪም በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ቀኖና መሠረት “ቅዱሳን” ከአምላክ ጋር እንደሚያማልዱ ተደርገው ልመና ከመቅረቡም በላይ ከ“ቅዱሳን” ጋር ግንኙነት ላላቸው የተለያዩ ቅርሳ ቅርሶችና ለምስላቸው ከፍተኛ ክብር ይሰጣል።
አንድን እውነተኛ ክርስቲያን የሚያሳስበው መሠረታዊ ጉዳይ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ መሆን ይኖርበታል። (ዮሐንስ 4:24) ስለሆነም “ቅዱሳንን” ማምለክ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ የአምልኮ ሥርዓት ክፍል ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ አንዳንድ እውነታዎችን እንመርምር። እንዲህ ዓይነቱ ምርመራ አምላክን እሱ በሚቀበለው መንገድ ለመቅረብ ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው ማስተዋል የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል።
“ቅዱሳን” መመለክ የጀመሩት እንዴት ነው?
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በክርስቶስ ደም የነጹትንና ወደፊት ከክርስቶስ ጋር ወራሾች በመሆን ለአምላክ አገልግሎት የተለዩትን ክርስቲያኖች በሙሉ “ቅዱሳን” በማለት ይጠሯቸዋል። (ሥራ 9:32፤ 2 ቆሮንቶስ 1:1፤ 13:13)a በጉባኤ ውስጥ የነበሩ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ታዋቂ ሰዎችም ሆኑ ተራ ሰዎች ሁሉም እዚህ ምድር ላይ እያሉ “ቅዱሳን” በመባል ተገልጸዋል። ከመሞታቸው በፊትም ቢሆን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚታወቁት በቅዱሳንነታቸው ነው።
ሆኖም የክህደት ክርስትና ብቅ ማለት ከጀመረበት ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ በኋላ ግን የነበረው ዝንባሌ ክርስትና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት እንዲያገኝና አረማውያን በቀላሉ የሚቀበሉት ሃይማኖት እንዲሆን ለማድረግ መጣር ነበር። እነዚህ አረማውያን በርካታ አማልክትን ያመልኩ የነበረ ሲሆን አዲሱ ሃይማኖት ደግሞ በአንድ አምላክ ብቻ የተወሰነ ነበር። ስለዚህ በተለያዩ የጥንት አማልክት፣ እንደ አምላክ በሚመለኩና ገድል ሠርተዋል የሚል አፈ ታሪክ በሚነገርላቸው ሰዎች ቦታ “ቅዱሳን” እንዲተኩ ማድረግ አዲሱ ሃይማኖት ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል አንድ አማራጭ ሆነ። ኤክሊዚያስቲኪ ኢስቶሪያ (ግሪክኛ) የተባለው መጽሐፍ ይህን አስመልክቶ አስተያየቱን ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የሚለወጡ ሰዎች ከፍተኛ ባለ ገድል ናቸው ብለው ያምኑባቸው የነበሩ ሰዎችን ተግባር ከሰማዕታት ተግባር ጋር ማዛመድና ዱሮ ለባለ ገድሎቹ ይሰጡት የነበረውን ክብር አሁን ለሰማዕታቱ መስጠት ቀላል ነበር። . . . ሆኖም ለቅዱሳን እንዲህ ዓይነቱን ክብር የመስጠቱ ተግባር ብዙውን ጊዜ የለየለት የጣዖት አምልኮ ነበር።”
አንድ ሌላ መጽሐፍ “ቅዱሳን” በሕዝበ ክርስትና ውስጥ መመለክ የጀመሩት እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ለግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ክብር እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ የአረማውያን ሃይማኖት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበረው በቂ ማስረጃ እናገኛለን። ሰዎች ወደ ክርስትና እምነት ከመለወጣቸው በፊት ለጥንቷ ግሪክ አማልክት ይሰጡ የነበሩት ባሕርያት አሁን ለቅዱሳን ተሰጥተዋል። . . . አዲሱ ሃይማኖት ገና ከጅምሩ አንስቶ ተከታዮቹ የፀሐይ አምላክ የሆነውን (ፎበስ አፖሎን) በነቢዩ ኤልያስ ሲተኩ እንመለከታለን፤ ይህንንም ያደረጉት የዚህ አምላክ የጥንት ቤተ መቅደስ ወይም ቅዱስ ሥፍራ ፍርስራሽ በሚገኝበት ቦታ ላይ ወይም አጠገቡ ቤተ ክርስቲያኖችን በመሥራት ነው፤ የጥንት ግሪካውያን የብርሃን ምንጭ ነው በማለት ፎበስ አፖሎን ያመልኩበት በነበረው ቦታ ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ በኮረብቶችና በተራሮች አናት ላይ ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል። . . . ሌላው ቀርቶ ራሷን ድንግል ማርያምን ድንግል አምላክ ከሆነችው ከአቴና ጋር አንድ አድርገው ያዩአታል። ስለዚህ ምንም እንኳ የአቴና ጣዖት ቢጠፋም ወደ አዲሱ እምነት የተለወጠው ጣዖት አምላኪ ቅር የሚሰኝበት ነገር የለም።”— ኔኦቴሮን ኢንካይክሎፔዲኮን ሌክሲኮን (New Encyclopedic Dictionary) ጥራዝ 1 ገጽ 270-1
ለምሳሌ ያክል አራተኛ መቶ ዘመን ሊያበቃ አካባቢ በአቴንስ የነበረውን ሁኔታ መርምር። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ገና አረማውያን ነበሩ። በጣም ቅዱስ ከሚባሉት የአምልኮ ሥርዓቶቻቸው አንዱ የኤሊዩሲስ ምስጢራዊ አምልኮb ሲሆን ይህም ከአቴንስ ሰሜን ምዕራብ 23 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኤሊዩሲስ ከተማ በየካቲት ወር በየዓመቱ በሁለት ደረጃ ተከፍሎ ይከናወናል። እነዚህን ምስጢራዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ለማከናወን አረማዊ አቴናውያን ቅዱስ መንገድ (ሃይኢራ ሆዶስ) መከተል አለባቸው። የከተማዋ መሪዎች አማራጭ የአምልኮ ሥፍራ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ብልሃት ተጠቅመዋል። አረማውያንን ለመሳብና ከምስጢራዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ለመከልከል በዚሁ መንገድ ከአቴንስ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የዳፍኒ ገዳም ተሠራ። የገዳሙ ቤተ ክርስቲያን የታነጸው በጥንቱ ቤተ መቅደስ መሠረት ላይ ሲሆን ይህ ቤተ መቅደስ የግሪክ አምላክ ለሆነው ለዳፍኔዮስ ወይም ለፒቲኦስ አፖሎ የተሠራ ነበር።
የአረማውያን አማልክት ከ“ቅዱሳን” አምልኮ ጋር መዋሃዳቸውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ የግሪክ ደሴት ከሆነችው ከኪቲራ ማግኘት ይቻላል። በደሴቲቷ ከሚገኙት ተራራዎች በአንዱ አናት ላይ ሁለት አነስተኛ የባይዛንታይን የጸሎት ቤቶች አሉ፤ ከእነዚህ አንደኛው የ“ቅዱስ” ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህ ቦታ ከ3,500 ዓመት ገደማ በፊት የሚኖዋ ቅዱስ የአምልኮ ሥፍራ እንደነበረ ከምድር ተቆፍረው የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በስድስተኛው ወይም በሰባተኛው መቶ ዘመን ገደማ “ክርስቲያኖች” በዚሁ ቅዱስ ሥፍራ ላይ የ“ቅዱስ” ጊዮርጊስን የጸሎት ቤት ሠሩ። ይህ ቦታ የተመረጠው እንዲሁ ባጋጣሚ አይደለም፤ ይህ ከሌሎች ላቅ ያለ እድገት የነበረው የሚኖዋ የሃይማኖት ማዕከል በኤጂያ ባሕር የሚያልፉ መርከቦች በቀላሉ ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ላይ ጉብ ብሎ ይገኛል። ሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖች በዚያ ቦታ የተሠሩት እመቤታችን ማርያምን እና “ቅዱስ” ጊዮርጊስን ለማስደሰት ሲሆን ሁለቱም የሚከበሩት “የባሕረተኞች ጠባቂ” ተደርጎ ይመለክ የነበረው “ቅዱስ” ኒኮላስ ይከበርበት በነበረው ቀን ነው። አንድ ጋዜጣ ይህን ግኝት አስመልክቶ ሲዘግብ “የሚኖዋ ካህን ልክ ጥንት ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም [የግሪክ ኦርቶዶክስ] ቄስ” ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም “ወደ ተራራው ይወጣል!” ብሏል።
አረማዊ የግሪክ ሃይማኖት በክህደት ክርስትና ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሲገልጹ አንዲት የታሪክ ተመራማሪ እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርገው ተናግረዋል:- “በታወቁ እምነቶች ረገድ የክርስትና ሃይማኖት አረማዊ መሠረት ብዙውን ጊዜ ምንም ሳይለወጥ እንዳለ ይቀጥላል፤ ይህ ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልማድ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል መሆኑን ያረጋግጣል።”
‘የምናውቀውን እናመልካለን’
ኢየሱስ “እኛ . . . ለምናውቀው እንሰግዳለን። . . . በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” ሲል ለሳምራዊቷ ሴት ነግሯታል። (ዮሐንስ 4:22, 23) በእውነት ማምለክ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ልብ በል! ስለዚህ ያለ ትክክለኛ እውቀትና ለእውነት ጥልቅ ፍቅር ሳይኖር አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ አይቻልም። እውነተኛው የክርስትና ሃይማኖት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ወግና ከአረማዊ ሃይማኖት በተወረሰ ልማድ ላይ ሳይሆን በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊያመልኩት ሲሞክሩ ይሖዋ እንዴት እንደሚሰማው እናውቃለን። ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ የግሪክ ከተማ በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? . . . ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” ሲል ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:15, 16) ቤተ መቅደሱን ከጣዖት ጋር ለማስማማት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አምላክን አያስደስተውም።
ከዚህም በላይ ከአምላክ ጋር ያማልዱናል በሚል ወደ “ቅዱሳን” መጸለይን ቅዱሳን ጽሑፎች ጨርሶ አይደግፉትም። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት መመሪያ ስለሰጣቸው ጸሎት መቅረብ ያለበት ለአብ ብቻ መሆኑን በናሙና ጸሎቱ ላይ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ሲል ገልጿል።— ዮሐንስ 14:6, 14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5
ጸሎቶቻችንን በእርግጥ አምላክ እንዲሰማልን የምንፈልግ ከሆነ ቃሉ በሚሰጠን መመሪያ መሠረት ወደ እሱ መቅረብ ይኖርብናል። ጳውሎስም ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበትን ብቸኛ መንገድ ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”— ሮሜ 8:34፤ ዕብራውያን 7:25
‘በመንፈስና በእውነት ማምለክ’
የክህደት ክርስትና አረማውያን የሐሰት አምልኮአቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉና የኢየሱስ ክርስቶስን የእውነት ትምህርት እንዲከተሉ ግፊት ለማሳደር መንፈሳዊ ጥንካሬም ሆነ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድጋፍ የለውም። ሰዎችን ወደ ሃይማኖቱ ለመለወጥ፣ ለሥልጣንና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት ከነበረው ጥማት የተነሳ የአረማውያንን እምነት እንዳለ ተቀብሏል። ከዚህም የተነሳ በአምላክና በክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ጥሩ ክርስቲያኖች ከማፍራት ይልቅ ለአምላክ መንግሥት ብቁ ያልሆኑ አስመሳይ ክርስቲያኖች የሆኑ ‘እንክርዳዶችን’ አፍርቷል።— ማቴዎስ 13:24-30
ሆኖም በዚህ የመጨረሻ ዘመን እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም በይሖዋ አመራር ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ከዚህ በፊት የነበራቸው ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አኗኗራቸውን በተቻለ መጠን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ለማስማማት ይጥራሉ። አምላክን እንዴት “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ እንደሚቻል የበለጠ ለማወቅ ከፈለግህ በምትኖርበት አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግራቸው። በማመዛዘን ችሎታህና በትክክለኛ የአምላክ ቃል እውቀት ላይ የተመሠረተ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት ለአምላክ ማቅረብ እንድትችል ሊረዱህ ዝግጁዎች ናቸው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደግሞ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- ‘እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔር እውቀት እንድታድጉ ስለ እናንተ መጸለያችንን አላቋረጥንም።’— ሮሜ 12:1, 2፤ ቆላስይስ 1:9, 10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሐጊኦስ የሚለውን ግሪክኛ ቃል በእንግሊዝኛ “ሆሊ ዋን” ብለው ሲተረጉሙት ሌሎች ደግሞ “ሴይንት” ብለው ይተረጉሙታል።
b ታላቁ የኤሊዩሲስ በዓል በአቴንስና በኤሊዩሲስ ከተሞች በየዓመቱ በመስከረም ወር ይከበር ነበር።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ፓርቴኖን ለተለያየ አገልግሎት
“ክርስቲያኑ” ንጉሠ ነገሥት ቲኦዶሲስ ዳግማዊ (በ438 እዘአ) የአቴንስ ከተማ ከአረማውያን አምልኮና ምሥጢራዊ ከሆኑ ሥርዓቶች እንድትጸዳ እንዲሁም ቤተ መቅደሶቻቸው እንዲዘጉ ትእዛዝ ወጣ። ከዚያ በኋላ ቤተ መቅደሶቹ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት መለወጥ ይችሉ ነበር። አንድን የአረማውያን ቤተ መቅደስ ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ለመለወጥ የሚያስፈልግ ነገር ቢኖር መስቀል እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነበር!
ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ከተለወጡት ቤተ መቅደሶች መካከል የመጀመሪያው የፓርቴኖን ቤተ መቅደስ ነበር። ፓርቴኖን “ለክርስቲያን” ቤተ መቅደስነት ተስማሚ እንዲሆን አንዳንድ እድሳት ተደረገለት። ከ869 እዘአ ጀምሮ የአቴንስ ካቴድራል ሆኖ አገልግሏል። ቀደም ሲል “የቅዱስ ጥበብ” ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይከበር ነበር። ይህም የቤተ መቅደሱ የመጀመሪያ “ባለቤት” የሆነችው አቴና የጥበብ ሴት አምላክ እንደነበረች ለማስታወስ ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ቆየት ብሎ “የእመቤታችን አቴና” ቤተ መቅደስ ሆነ። ይህ ቤተ መቅደስ ለስምንት መቶ ዓመታት ለኦርቶዶክስ ካገለገለ በኋላ የአቴንስ ቅድስተ ማርያም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆነ። በዚህ መልክ በፓርቴኖን ቤተ መቅደስ ላይ የሚደረገው ሃይማኖታዊ “መፈራረቅ” በ15ኛው መቶ ዘመን ኦቶማን ቱርኮች ወደ መስጊድነት እስከለወጡበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል።
ዛሬ ያለችው ፓርቴኖን ማለትም የግሪክ የጥበብ ሴት አምላክ የነበረችው የአቴና ፓርቴኖስ (“ድንግል”) ጥንታዊ የዶሪክ ቤተ መቅደስ የግሪክን ድንቅ የሕንፃ ሥራ ጥበብ ስለሚያንጸባርቅ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ይጎበኙታል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንቷ አቴንስ አረማውያን አማራጭ የአምልኮ ሥፍራ የሆነው የዳፍኒ ገዳም