አስተዋይነት ይጠብቃችሁ
“ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል።”— ምሳሌ 2:11
1. አስተዋይነት ከምን ሊጠብቀን ይችላል?
ይሖዋ አስተዋዮች እንድትሆኑ ይፈልጋል። ለምን? ማስተዋል ከብዙ አደጋና ውድቀት እንደሚጠብቃችሁ ስለሚያውቅ ነው። ምሳሌ 2:10-19 እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፣ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል።” ማስተዋል የሚጋርዳችሁ ከምን ነገር ነው? “ከክፉ መንገድ፣” እንዲሁም የቀና አካሄድ ትተው በጠማማ መንገድ ከሚሄዱ ሰዎች ይጋርዳችኋል።
2. ማስተዋል ምንድን ነው? ክርስቲያኖች በተለይ ምን ዓይነት ማስተዋል እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ?
2 ማስተዋል ማለት አእምሮአችን አንዱን ነገር ከሌላው ነገር የሚለይበት ችሎታ መሆኑን ሳታስታውሱ አትቀሩም። ማስተዋል ያለው ሰው በተለያዩ ሐሳቦች ወይም ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ይገነዘባል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በተለይ በአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲኖረን እንፈልጋለን። ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናጠና ለመንፈሳዊ ማስተዋል ግንባታ የሚያስፈልገውን ድንጋይ ቆፍረን እንደምናወጣ ያህል ነው። በዚህ መንገድ የምንማረው ነገር ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።
3. መንፈሳዊ ማስተዋል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
3 አምላክ የእስራኤልን ንጉሥ ሰሎሞንን ምን በረከት እንደሚፈልግ በጠየቀው ጊዜ ወጣቱ ንጉሥ እንዲህ ብሏል:- “በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው።” ሰሎሞን ማስተዋል እንዲሰጠው ጠየቀ፣ ይሖዋም በጣም ከፍተኛ የሆነ የማስተዋል ችሎታ ሰጠው። (1 ነገሥት 3:9፤ 4:30) ማስተዋል እንድናገኝ መጸለይ ያስፈልገናል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ እውቀት በሚሰጡት “በታማኝና ልባም ባሪያ” በሚዘጋጁ ጽሑፎች ረዳትነት የአምላክን ቃል ማጥናት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህን ማድረግ ‘በማስተዋል ችሎታችን የበሰልን’ እንድንሆንና “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት [ወይም ለይተን ለማስተዋል]” የሚያስችለንን መንፈሳዊ ማስተዋል እንድናዳብር ይረዳናል።— 1 ቆሮንቶስ 14:20፤ ዕብራውያን 5:14
ማስተዋል የሚጠይቅ ለየት ያለ ጉዳይ
4. “ቀና” ዓይን መያዝ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ እኛን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
4 ትክክለኛ የሆነ ማስተዋል ካለን ከሚከተሉት የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት ጋር የሚስማማ ተግባር እንፈጽማለን:- “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም [ቁሳዊ ነገር] ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴዎስ 6:33) በተጨማሪም ኢየሱስ “የሰውነትህ መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ ጤናማ [“ቀና፣” NW ] በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 11:34) ዓይን ምሳሌያዊ መብራት ነው። “ቀና” ዓይን ወዲያ ወዲህ የማይቅበዘበዝ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ያተኮረ ነው። እንዲህ ያለ ዓይን ካለን አስተዋይ መሆንና በመንፈሳዊ ምንም ነገር ሳያደናቅፈን መራመድ እንችላለን።
5. በንግድ ጉዳዮች ረገድ ስለ ክርስቲያን ጉባኤ ዓላማ ምን ነገር ልንዘነጋ አይገባም?
5 አንዳንዶች ዓይናቸውን ቀና ከማድረግ ይልቅ አጓጊ መስለው በሚታዩ የንግድ ሥራዎች የተነሳ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ከተዋል። ነገር ግን የክርስቲያን ጉባኤ “የእውነት አምድና መሠረት” መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) የአንድ ሕንፃ ዓምዶች ሕንፃውን ደግፈው ለማቆም እንደሚያገለግሉ ሁሉ ጉባኤም አምላክ የገለጸውን እውነት ለመደገፍ እንጂ የማንንም የንግድ ድርጅት ለመደገፍ የቆመ አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የተቋቋሙት የንግድ ጉዳዮችን፣ ሸቀጦችን ወይም አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ የሚያገለግሉ ቦታዎች እንዲሆኑ ተብሎ አይደለም። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ግላዊ የንግድ ጉዳዮችን ከማካሄድ መቆጠብ አለብን። ማስተዋል የመንግሥት አዳራሾች፣ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናቶችና የይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎች መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ለመተያየት እንዲችሉና መንፈሳዊ ውይይት እንዲያደርጉ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። መንፈሳዊ ግንኙነታችንን ማንኛውንም ዓይነት የንግድ ጉዳይ ማስፋፊያ ወይም ማስተዋወቂያ አድርገን ብንጠቀምበት ይህን ማድረጋችን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች አድናቆት የጎደለን መሆኑን አያሳይምን? የጉባኤ ትውውቆችና ግንኙነቶች በምንም መንገድ የገንዘብ ትርፍ ማግኛ ሆነው ማገልገል የለባቸውም።
6. የጉባኤ ስብሰባዎች በሚካሄዱበት ቦታ የንግድ ሸቀጦችንም ሆነ አገልግሎቶችን መሸጥ ወይም ማስተዋወቅ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
6 አንዳንዶች ቲኦክራሲያዊ ትውውቃቸውንና ግንኙነታቸውን የጤና ወይም የውበት መጠበቂያ ሸቀጦችን፣ የቫይታሚን ተዋጽኦዎችን፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን፣ የግንባታ ዕቃዎችን፣ የጉዞ ዝግጅቶችን፣ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችንና መሣሪያዎችን የመሳሰሉትን ነገሮች ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ የጉባኤ ስብሰባዎች የንግድ ሸቀጦች ወይም አገልግሎቶች ማስተዋወቂያና መሸጫ ቦታዎች አይደሉም። ኢየሱስ “ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም:- ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።” ይህ የኢየሱስ እርምጃ ትዝ ካለን መሠረታዊ ሥርዓቱን ማስተዋል አይቸግረንም።— ዮሐንስ 2:15, 16
ገንዘብን በንግድ ሥራ ላይ ማዋልን በተመለከተስ?
7. ገንዘብን በንግድ ሥራ ላይ ስናውል አስተዋዮችና ጠንቃቆች መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?
7 ገንዘባችንን በንግድ ሥራ ላይ ለማዋል በምናስብበት ጊዜም አስተዋይነትና ጥንቃቄ ያስፈልገናል። አንድ ሰው “ትርፍ እንደምታገኝበት ሙሉ ዋስትና እሰጥሃለሁ።” “ምንም የምትከስረው ነገር አይኖርም። እንደማተርፍ የተረጋገጠ ነው” እንደሚሉ ያሉ ተስፋዎችን እየሰጠ ገንዘብ እንድታበድሩት ቢጠይቃችሁ ጠንቀቅ በሉ። አንድ ሰው እንዲህ ያለ የማረጋገጫ ቃል ከሰጠ ትክክለኛ አስተሳሰብ የለውም ወይም ከእውነታው የራቀ አመለካከት አለው ማለት ነው፤ ምክንያቱም ገንዘብ ንግድ ላይ ሲውል ስለሚገኘው ውጤት እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ የለም። እንዲያውም ስለሌላው ደንታ የሌላቸው አንዳንድ አታላይ ግለሰቦች የጉባኤውን አባላት እስከማጭበርበር ደርሰዋል። ይህ ሁኔታ ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ሾልከው የገቡትንና ‘ይገባናል የማንለውን የአምላክ ቸርነት ለሴሰኝነት ምክንያት አድርገው የተጠቀሙበትን’ ከአምላክ የራቁ ሰዎች ያስታውሰናል። እነዚህ ሰዎች ዋናተኞችን አቁስለው ሊገድሉ እንደሚችሉ ከውኃ በታች ያሉ ስለታም አለቶች ናቸው። (ይሁዳ 4, 12 NW) እርግጥ፣ ስግብግብ አታላዮች ያላቸው ፍላጎት ከከሃዲዎች ይለያል፤ ቢሆንም ሁለቱም ቢሆኑ የጉባኤውን አባላት ለመዋጥ የተዘጋጁ ናቸው።
8. አትራፊ ከሚመስሉ አንዳንድ ንግዶች ጋር በተያያዘ ምን ተከስቷል?
8 በቅን ልቦና የተነሳሱ ክርስቲያኖችም እንኳ አትራፊ ናቸው ስለሚባሉ የንግድ ሥራዎች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መረጃ በመለዋወጥ እነርሱም ሆኑ የእነርሱን ምሳሌ የተከተሉ በንግድ ሥራ ላይ ያዋሉትን ገንዘብ አጥተዋል። በዚህ የተነሣ በርካታ ክርስቲያኖች ጉባኤ ውስጥ የነበራቸውን መብት አጥተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ያበለጽጋሉ የተባሉ የንግድ ውጥኖች መሠረተ ቢስና የማጭበርበሪያ ውጥኖች ሲሆኑ ትርፍ የሚያገኘው ወዲያው ከአካባቢው የሚሰወረው አጭበርባሪ ብቻ ነው። አስተዋይነት እንዲህ ካለው ሁኔታ እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
9. ገንዘብን በንግድ ሥራ ላይ ስለማዋል የሚቀርቡልንን ሐሳቦች ለማመዛዘን የማስተዋል ችሎታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ማስተዋል ስውር የሆነን ነገር ለመረዳት መቻልን የሚያመለክት ትርጉም አለው። ገንዘብን በንግድ ሥራ ላይ ስለማዋል የሚቀርቡልንን ሐሳቦች ለማመዛዘን ከፈለግን ይህ ችሎታ ያስፈልገናል። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ስለሚተማመኑ መንፈሳዊ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የእምነት ባልደረቦቻቸውን ገንዘብ አደጋ ላይ በሚጥል ሥራ ውስጥ አይገቡም ብለው አንዳንዶች ያስባሉ። ይሁን እንጂ አንድ ነጋዴ ክርስቲያን መሆኑ ብቻ በንግድ ጉዳዮች ከሌሎች እንደሚልቅ ወይም የንግድ ድርጅቱ አትራፊ እንደሚሆን ዋስትና አይሰጥም።
10. አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚነግዱበትን ገንዘብ ከእምነት ባልደረቦቻቸው መበደር የሚፈልጉት ለምንድን ነው? በዚህ መንገድ ገንዘብን በንግድ ሥራ ላይ ማዋል ምን ሊያስከትል ይችላል?
10 አንዳንድ ክርስቲያኖች አደገኛ ለሆነ ንግዳቸው ከታወቁ አበዳሪ ድርጅቶች ብድር ለማግኘት ባለመቻላቸው ከወንድሞችና እህቶች ብድር ለማግኘት ይፈልጋሉ። ብዙዎችም ገንዘባቸውን ሥራ ላይ በማዋላቸው ብቻ ሳይወጡና ሳይወርዱ፣ በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት የሚችሉ እየመሰላቸው ተታልለዋል። አንዳንዶች ደግሞ ንግድ ውስጥ የሚገቡት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማመንም ብቻ ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ማራኪ መስለው ለመታየት ሲሉ ቢሆንም በዚህ የተነሳ ዕድሜ ልካቸውን ያጠራቀሙትን ጥሪት አጥተዋል! አንድ ክርስቲያን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 25 በመቶ ትርፍ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጎ በርካታ ገንዘብ በንግድ ሥራ ላይ አዋለ። ገንዘቡን ሥራ ላይ ያዋለበት ድርጅት ከስሮ በመዘጋቱ ገንዘቡን በሙሉ አጣ። የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እየገዛ በትርፍ የሚሸጥ አንድ ሌላ ክርስቲያን ደግሞ ከጉባኤ አባላት በጣም በርካታ የሆነ ገንዘብ ይበደራል። ከመጠን በላይ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ እንደሚያስገኝላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ በመክሰሩ ምክንያት የተበደረው ገንዘብ በሙሉ ጠፍቶ ቀረ።
አንድ የንግድ ሥራ በሚከስርበት ጊዜ
11. ስግብግብነትንና የገንዘብን ፍቅር በተመለከተ ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል?
11 አደገኛ በሆኑ ንግዶች ላይ ገንዘባቸውን ያዋሉ ክርስቲያኖች ያወጧቸው የንግድ እቅዶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው ምክንያት ከፍተኛ ብስጭት ከማትረፋቸውም በላይ አንዳንዶቹ መንፈሳዊነታቸውን ጭምር እስከ ማጣት ደርሰዋል። ማስተዋል እንዲጠብቃቸው አለማድረጋቸው የልብ ቁስለትና ምሬት አስከትሎባቸዋል። ስግብግብነት ለብዙ ግለሰቦች ወጥመድ ሆኖባቸዋል። ጳውሎስ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን . . . መመኘት [“ስግብግብነት፣” NW ] በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 5:3) በተጨማሪም እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።”— 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
12. ክርስቲያኖች አንድ ላይ የሚነግዱ ከሆነ በተለይ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
12 አንድ ክርስቲያን የገንዘብ ፍቅር ካደረበት በራሱ ላይ ብዙ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ፈሪሳውያን ገንዘብ ወዳዶች ነበሩ፤ ይህም በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ የብዙ ሰዎች ባሕርይ ነው። (ሉቃስ 16:14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) በአንጻሩ ደግሞ የአንድ ክርስቲያን አኗኗር ‘ገንዘብን ከመውደድ የራቀ’ መሆን ይገባዋል። (ዕብራውያን 13:5) እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች አብረው ሊነግዱ ወይም ሊገበያዩ ይችላሉ። አብረው በሚነግዱበትና በሚገበያዩበት ጊዜ ግን የሚያደርጉት ውይይትና ድርድር ከጉባኤ ጉዳዮች መለየት ይኖርበታል። እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድማማቾች እንኳን የሚያደርጓቸውን ንግድ ነክ ውሎች ሁልጊዜ ጽሑፍ ላይ ማስፈር እንደሚኖርባቸው አትዘንጉ። በዚህ ረገድ በየካቲት 8, 1983 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ገጽ 13 እስከ 15 ላይ የወጣው “በጽሑፍ ላይ አስፍሩት!” የሚለው ርዕስ በጣም ጠቃሚ ነው።
13. ምሳሌ 22:7 ከንግድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?
13 ምሳሌ 22:7 “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” በማለት ይነግረናል። አብዛኛውን ጊዜ ራሳችን ባሪያ ብንሆን ወይም ወንድማችንን ባሪያ ብናደርግ ተገቢ አይሆንም። አንድ ሰው ሊነግድበት ፈልጎ ገንዘብ እንድናበድረው ቢጠይቀን ገንዘቡን መልሶ ለመክፈል የሚያስችል አቅም እንዳለውና እንደሌለው ማመዛዘን ጥሩ ይሆናል። በታማኝነቱና እምነት የሚጣልበት በመሆኑ የታወቀ ነውን? እርግጥ፣ ብዙ የንግድ ውጥኖች አክሣሪ በመሆናቸው ያበደርነው ገንዘብ ሳይመለስ ሊቀር እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። ውል መፈራረማችን ብቻውን ገንዘባችንን ለማግኘታችን ዋስትና ሊሆን አይችልም። በእርግጥም አንድ ሰው ያለ የሌለ ገንዘቡን ሊያከስረው በሚችል አንድ ዓይነት ንግድ ላይ ቢያውል ሞኝነት ይሆንበታል።
14. ለአንድ የእምነት ባልደረባችን ገንዘብ አበድረነው ቢሆንና ንግዱ ቢከስርበት የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
14 ለአንድ ክርስቲያን ገንዘባችንን እንዲነግድበት አበድረነው ከነበረና ምንም ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ሳይፈጽም የጀመረው ንግድ ቢከስርበት የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። ኪሣራ የደረሰው ገንዘቡን የተበደረው የእምነት ባልደረባችን በሠራው ስህተት ምክንያት ካልሆነ በደል ተፈጽሞብናል ለማለት እንችላለንን? አንችልም፤ ምክንያቱም ብድር የሰጠነው ወደንና ፈቅደን ከመሆኑም በላይ ምናልባት ወለድ ስንቀበለው ቆይተን ይሆናል፤ ደግሞም ምንም ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አልተፈጸመብንም። ተበዳሪው ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ስላልፈጸመ በእሱ ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የምንችልበት ምክንያት የለንም። ሐቀኛ የሆነ ክርስቲያን ባልደረባችን በጥሩ እቅድ የጀመረው ንግድ ስለ ከሰረበት ብቻ ለፍርድ ቤት ከስሬአለሁ የሚል መግለጫ እንዲሰጥ ቢገደድ ምን ጥቅም ይገኛል?— 1 ቆሮንቶስ 6:1
15. አንድ ንግድ እንደ ከሰረ ቢገለጽ ምን ነገሮች መጤን ይኖርባቸዋል?
15 ንግዳቸው የከሰረባቸው ሰዎች ራሳቸውን ከዕዳ ነጻ ለማውጣት ሲሉ ከስረናል የሚል መግለጫ የሚሰጡበት ጊዜ አለ። ክርስቲያኖች ግን የገቡትን ዕዳ የመክፈል የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ሕጉ ከአንዳንድ ዕዳዎች ነጻ ቢያወጣቸውም አበዳሪዎቻቸው የሚቀበሏቸው ከሆነ የተሰረዘላቸውን ዕዳ ለመክፈል ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ተበዳሪው የወንድሙን ገንዘብ ካከሰረ በኋላ በአንጻራዊ ሁኔታ በተንደላቀቀ ሁኔታ የሚኖር ከሆነስ? ወይም ተበዳሪው ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ ቢያገኝም ለወንድሙ የመክፈል ሞራላዊ ግዴታውን ችላ ቢልስ? እንዲህ ባለው ሁኔታ ግለሰቡ በጉባኤው ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ተመድቦ ለመሥራት ያለው ብቃት አጠያያቂ ይሆናል።— 1 ጢሞቴዎስ 3:3, 8፤ መስከረም 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-1 ተመልከት።
ማጭበርበር ካለበትስ?
16. የንግድ ማጭበርበር እንደተፈጸመብን ከተሰማን ምን እርምጃዎች ልንወስድ እንችላለን?
16 አስተዋይነት ሁሉም ዓይነት ንግዶች አትራፊዎች አለመሆናቸውን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ሆኖም የማጭበርበር ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነስ? ማጭበርበር ማለት “ሆን ብሎ በማታለል፣ በማሳሳት፣ ወይም እውነቱን በማጣመም አንድ ሰው ንብረቱን ወይም ሕጋዊ መብቱን እንዲያጣ ማድረግ” ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልደረባዬ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሞብኛል ብሎ በሚያስብበት ጊዜ መወሰድ የሚኖርባቸውን እርምጃዎች ዘርዝሯል። በማቴዎስ 18:15-17 መሠረት ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው ባይሰማህ ግን፣ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፣ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፣ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” ኢየሱስ ወረድ ብሎ ከተናገረው ምሳሌ ለመረዳት እንደምንችለው ማጭበርበርን ጨምሮ ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዩችን የሚመለከቱ ኃጢአቶች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ይካተታሉ።—ማቴዎስ 18:23-35
17, 18. ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ቢያጭበረብረን ማስተዋል ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
17 በንግድ ጉዳዮች ማጭበርበር ተፈጽሟል የሚያሰኝ ምክንያት ወይም ማስረጃ ካልኖረ በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የተገለጹትን እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አይኖርም። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው አጭበርብሮን ከሆነስ? አስተዋይነት ጉባኤውን የሚያስነቅፍ እርምጃ ከመውሰድ ሊጠብቀን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልደረቦቹ አንድን ወንድም በፍርድ ቤት ከመክሰስ ይልቅ ቢበደሉ ወይም ቢጭበረበሩ የተሻለ እንደሚሆን መክሯል።— 1 ቆሮንቶስ 6:7
18 እውነተኛ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን በርያሱስ እንደሚባለው ጠንቋይ ‘አጭበርባሪዎችና አታላዮች’ አይደሉም። (ሥራ 13:6-12) ስለዚህ የእምነት ባልደረቦቻችን ተካፋይ በሆኑባቸው የንግድ ሥራዎች ምክንያት ገንዘባችንን በምንከስርበት ጊዜ አስተዋዮች መሆን ያስፈልገናል። ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የምናስብ ከሆነ እርምጃችን በራሳችን ላይ፣ በሌላው ግለሰብ ወይም ግለሰቦች ላይ፣ በጉባኤውና በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ማገናዘብ ይኖርብናል። ካሣ ለማግኘት ጥረት ማድረጋችንን ብንቀጥል ግን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ሌሎች ንብረቶቻችንን በከንቱ ማባከን ሊሆንብን ይችላል። እንዲያውም ጠበቆችንና ሌሎች የሕግ ሰዎችን ከማበልጸግ በስተቀር የምናገኘው ፋይዳ ላይኖር ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ባሉት በጣም አስፈላጊ ባልሆኑ ጉዳዮች በመዋጣቸው ምክንያት ቲኦክራሲያዊ መብቶቻቸውን እስከማጣት መድረሳቸው በእጅጉ ያሳዝናል። በዚህ መንገድ ሐሳባችን መከፋፈሉ ሰይጣንን እንደሚያስደስተው የታወቀ ነው፤ እኛ ግን የይሖዋን ልብ ማስደሰት እንፈልጋለን። (ምሳሌ 27:11) በሌላ በኩል ደግሞ የደረሰብንን ኪሣራ ተቀብለን ዝም ማለታችን እኛንም ሆነ ሽማግሌዎችን ከብዙ ድካምና ጊዜ ማባከን ሊያድን ይችላል። እንዲህ ማድረጋችን የጉባኤውን ሰላም እንዲጠበቅ ከማድረጉም በተጨማሪ የመንግሥቱን ጉዳዮች በማስቀደም እንድንቀጥል ያስችለናል።
አስተዋይነትና ውሳኔ ማድረግ
19. ከባድ የሆኑ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ መንፈሳዊ ማስተዋልና ጸሎት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
19 በንግድ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ውሳኔ ማድረግ በጣም ከባድ ውጥረት የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። ሆኖም መንፈሳዊ ማስተዋል ነገሮችን እንድናመዛዝንና ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ከዚህም በላይ በጸሎት አማካኝነት የይሖዋን እርዳታ መጠየቃችን ‘የእግዚአብሔርን ሰላም’ ያስገኝልናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይህ ሰላም ከይሖዋ ጋር ያለን በጣም የተቀራረበ ዝምድና የሚያስገኘው መረጋጋትና ጸጥታ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰላም ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንኳን ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ሊረዳን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው።
20. የንግድ ጉዳዮችንና ጉባኤን በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
20 በንግድ ጉዳዮች ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችና ውዝግቦች የራሳችንንም ሆነ የጉባኤውን ሰላም እንዲያውኩ ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የክርስቲያን ጉባኤ እኛን በመንፈሳዊ ለመርዳት የሚንቀሳቀስ እንጂ የንግድ ጉዳዮች ማስፋፊያ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልገናል። በማንኛውም ጊዜ የንግድ ጉዳዮች ከጉባኤ እንቅስቃሴዎች መለየት አለባቸው። ማንኛውንም ንግድ ስንጀምር አስተዋዮችና ጥንቁቆች መሆን ይገባናል። ምን ጊዜም ቢሆን የመንግሥቱን ጉዳዮች እያስቀደምን ስለ ንግድ ጉዳዮች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንያዝ። መሰል አማኞችን የሚነካ አንድ ንግድ ቢከስር ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ የሚበጀውን ለማድረግ እንጣር።
21. የማስተዋል ችሎታችንን ልንጠቀምና ከፊልጵስዩስ 1:9-11 ጋር የሚስማማ ነገር ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
21 ከገንዘብ ጋር ለተያያዙና ይህን ያህል አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች ከመጠን በላይ ከመጨነቅ ይልቅ ሁላችንም ልባችንን ወደ ማስተዋል እናዘንብል፣ አምላክ መመሪያ እንዲሰጠን በጸሎት እንጠይቀው፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ፍላጎቶች እናስቀድም። ጳውሎስ ካቀረበው ጸሎት ጋር በመስማማት ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማረጋገጥ እንድንችል ፍቅራችን በትክክለኛ እውቀትና በተሟላ ማስተዋል ይብዛ።’ ሌሎችንም ሆነ ራሳችንን ከማደናቀፍ እንቆጠብ። ንጉሡ ክርስቶስ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ሆኖ በሚገዛበት በዚህ ዘመን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች መንፈሳዊ አስተዋይነታችንን እናሳይ። እንዲሁም የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ ለሆነው ‘ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በጽድቅ ፍሬዎች የተሞላን እንሁን።’— ፊልጵስዩስ 1:9-11
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ማስተዋል ምንድን ነው?
◻ በተለይ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በሚያከናውኑት ንግድ ነክ ጉዳይ ረገድ ማስተዋል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የእምነት ባልደረባችን ያጭበረበረን መስሎ ከተሰማን ማስተዋል እንዴት ሊረዳን ይችላል?
◻ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ማስተዋል ምን ሚና መጫወት አለበት?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማስተዋል አስቀድመን መንግሥቱን መፈለጋችንን እንድንቀጥል ኢየሱስ የሰጠንን ምክር በሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የንግድ ስምምነት ስታደርጉ ምንጊዜም በጽሑፍ አስፍሩት