በሪኢንካርኔሽን ማመን ይኖርብሃልን?
የግሪኩ ፈላስፋ ፕላቶ በፍቅር መያዝን ከሪኢንካርኔሽን ትምህርት ጋር አዛምዶታል። ሥጋ ከሞተ በኋላ የማትሞተው ነፍስ ወደ “ላይኛው ዓለም” ትጓዛለች ብሎ ያምን ነበር። እዚያም ለተወሰነ ጊዜ የማትታይ አካል ሆና ወደፊት ወደ ምንነት እንደምትለወጥ እያሰበች ትቆያለች። ከዚያም ወደ ሌላ አካል ስትገባ የላይኛውን ዓለም እያሰበች ያንን መናፈቅ ትጀምራለች። እንደ ፕላቶ አባባል ከሆነ ሰዎች ፍቅር የሚይዛቸው ከዚህ በፊት ያዩትን ትንሽ ትንሽ ትዝ የሚላቸውን ዓይነት ማራኪ ውበት በሚወዱት ሰው ላይ ስለሚያዩ ነው።
ምንጩንና መሠረቱን መረዳት
የሪኢንካርኔሽን ትምህርት ከነፍስ አለመሞት ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ሪኢንካርኔሽን የመነጨው እንዲህ ዓይነት እምነት ካላቸው ሕዝቦች ወይም ብሔራት መሆን ይኖርበታል። አንዳንዶች ከዚህ በመነሣት ይህ ትምህርት የመነጨው ከጥንቷ ግብጽ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከጥንቷ ባቢሎን እንደመጣ ያምናሉ። ካህናቱ የባቢሎናውያን ሃይማኖት በሰዎች ዘንድ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠው ሲሉ ነፍስ በሌላ መልኩ ትኖራለች የሚለውን ትምህርት አስፋፍተዋል። በዚህ መንገድ ሃይማኖታዊ ገድል እንደፈጸሙ አድርገው የሚያዩአቸውን ሰዎች ከረጅም ጊዜ በፊት የኖሩ ስመጥር አባቶች ነፍስ ናቸው ብለው ማስተማር ችለው ነበር።
ይሁን እንጂ የሪኢንካርኔሽን ትምህርት ይበልጥ የዳበረው ሕንድ ውስጥ ነው። የሂንዱ ሃይማኖታዊ ጠበብት በሰው ልጆች ላይ ከተፈራረቁት ዓለም አቀፍ ችግሮችና ስቃዮች ጋር ሲተናነቁ ኖረዋል። ‘እነዚህ ነገሮች ጻድቅ ፈጣሪ አለ ከሚለው ጽንሰ ሐሳብ ጋር እንዴት ይጣጣማሉ?’ ሲሉም ጠይቀዋል። በአምላክ ጻድቅነትና በዓለም ውስጥ በሚከሰቱት ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም የእርስ በርስ መበላለጥ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስታረቅ ሞክረዋል። ከዚያም ‘ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል’ የሚል መሠረታዊ ሐሳብ የተከተለና “የካርማ ሕግ” በመባል የሚታወቅ የምክንያትና የውጤት ሕግ ደነገጉ። በአንደኛው ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙ በጎ ወይም እኩይ ተግባሮች በሚቀጥለው ሕይወት ውስጥ ሽልማት አለዚያም ቅጣት እንደሚያስከትሉ የሚገልጽ ዝርዝር ‘መግለጫ’ አወጡ።
ባጭር አነጋገር “ካርማ” ማለት “ድርጊት” ማለት ነው። አንድ የሂንዱ እምነት ተከታይ ጥሩ ካርማ አለው የሚባለው ከማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ደንቦች ጋር ተስማምቶ ሲኖር ሲሆን ይህን ሳያደርግ ሲቀር ደግሞ ካርማው መጥፎ ነው ይባላል። ድርጊቱ ወይም ካርማው ወደፊት እንደገና በሚወለድባቸው ተከታታይ ሕይወቶች ውስጥ የሚኖረውን ሁኔታ ይወስናል። ፈላስፋው ኒኪላነንዳ እንዲህ ይላሉ:- “የእያንዳንዱ ሰው አካላዊ ባሕርይ የሚወሰነው በዘር ውርስ ቢሆንም አንድ ሰው የሚወለደው ባሕርይውን ከሚገልጽ መረጃ ጋር ነው፤ ይህም ባብዛኛው የሚወሰነው በቀደመው ሕይወቱ ውስጥ ባደረገው ነገር ነው። በዚህ መንገድ አንድ ሰው የራሱን ዕድል ይነድፋል፤ ዕጣ ፋንታውን ያዘጋጃል።” ይሁን እንጂ የመጨረሻው ግብ ከዚህ ከሕይወት ወደ ሕይወት የመሻገር ዑደት ነፃ ወጥቶ የመጨረሻ እውነታ ወደ ሆነው ወደ ብራሕማ መቀላቀል ነው። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ባሕርይና ልዩ የሆነ የሂንዱ እውቀት ለማግኘት መጣጣርን እንደሚጠይቅ ይታመናል።
በመሆኑም የሪኢንካርኔሽን ትምህርት መሠረት ያደረገው ነፍስ አትሞትም የሚለውን መሠረተ ትምህርት ሲሆን በዚያ ላይ ደግሞ በካርማ ሕግ አማካኝነት ሌሎች ነገሮችን ጨምሯል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ነጥቦች በተመለከተ ምን እንደሚል እንመልከት።
ነፍስ አትሞትምን?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ዳኛ ወደ ሆነውና በመንፈስ አነሳሽነት ወደ ተጻፈው የአምላክ ቃል ዘወር እንበል። በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማለትም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ‘የነፍስን’ ትክክለኛ ትርጉም እናገኛለን። የመጀመሪያውን ሰው የአዳምን አፈጣጠር በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር። ባፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7 1879 ትርጉም) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ነፍስ በሰው ውስጥ ያለች ነገር ሳትሆን ሰው ራሱ ነፍስ ነው። እዚህ ላይ ነፍስ ለማለት የተሠራበት የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ የሚል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 700 የሚያክል ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን የሚጨበጥና ግዑዝ የሆነን ነገር እንጂ አንድም ጊዜ ቢሆን ከሰው የተለየና የማይጨበጥ ነገር ለማመልከት አልተሠራበትም።— ኢዮብ 6:7፤ መዝሙር 35:13፤ 107:9፤ 119:28
ሰው ሲሞት ነፍስ ምን ትሆናለች? አዳም ሲሞት ምን እንደተፈጸመ ልብ በል። ኃጢአት በሠራ ጊዜ አምላክ “ወደ ወጣህበት መሬት [ትመለሳለህ]፤ . . . አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ሲል ነግሮታል። (ዘፍጥረት 3:19) ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስብ። አምላክ አዳምን ከምድር አፈር ሳይፈጥረው በፊት አዳም ሕልውና አልነበረውም። አዳም ከሞተም በኋላ የሚመለሰው ወደ ቀድሞው ያለመኖር ሁኔታው ነው።
በአጭሩ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። በመክብብ 9:5, 10 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”
ይህ ማለት ሙታን ምንም ነገር ሊያደርጉም ሆነ ምንም ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው አይችልም ማለት ነው። ሐሳባቸው ሁሉ ይጠፋል የሚያስታውሱትም ነገር አይኖርም። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “ባለቆች ማዳን በማይችሉት በሰው አትታመኑ። መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል። በዚያን ቀን ትምክሕቱ ሁሉ ይጠፋል።”— መዝሙር 146:3, 4 የ1879 ትርጉም
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያረጋግጠው ሰው ሲሞት ነፍስ ትሞታለች እንጂ ወደ ሌላ አካል አትዛወርም። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ሲል ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 18:4, 20፤ ሥራ 3:23፤ ራእይ 16:3) በመሆኑም የሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ ዋነኛ መሠረት የሆነው ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለውም። ያለዚህ ትምህርት ደግሞ የሪኢንካርኔሽን ሐሳብ ሊጸና አይችልም። በዓለም ላይ ስለምናየውስ ስቃይ ምን ማለት ይቻላል?
ሰዎች ስቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው ስቃይ ዋነኛው ምክንያት ሁላችንም ከኃጢአተኛው አዳም አለፍጽምና መውረሳችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ይላል። (ሮሜ 5:12) ሁላችንም ከአዳም የተወለድን እንደመሆናችን መጠን እንታመማለን፣ እናረጃለን እንዲሁም እንሞታለን።— መዝሙር 41:1, 3፤ ፊልጵስዩስ 2:25-27
ከዚህ በተጨማሪ የማይለዋወጠው የአምላክ የሥነ ምግባር ሕግ እንዲህ ይላል:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።” (ገላትያ 6:7, 8) በመሆኑም የሴሰኝነት አኗኗር ለስሜት ቀውስ፣ ላልተፈለገ እርግዝና እና በፆታ ለሚተላለፉ በሽታዎች ሊዳርግ ይችላል። “[በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ] ከሚከሰቱት ለሞት የሚያደርሱ የካንሰር በሽታዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ዋነኛ መንስኤያቸው ሲጋራ ማጨስ ነው ሊባል የሚችል ሲሆን ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ የችግሩ ሰለባ የሚሆኑት ከአኗኗራቸው የተነሣ በተለይ ደግሞ ከአመጋገብ ልማድና ከጥንቃቄ ጉድለት እንደሆነ” ሳይንቲፊክ አሜሪካ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። አንዳንዶቹ ስቃይ የሚያስከትሉ አደጋዎች የሚደርሱት የሰው ልጅ የምድርን ሀብት አላግባብ በመጠቀሙ ነው።— ከራእይ 11:18 ጋር አወዳድር።
አዎን፣ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው አብዛኛው ሰቆቃ ተጠያቂው የሰው ልጅ ራሱ ነው። ይሁን እንጂ ነፍስ ሟች በመሆኗ ‘ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል’ የሚለውን ሕግ በመጠቀም በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ከካርማ ማለትም በቀድሞ ሕይወት ተፈጽመዋል ከሚባሉት ድርጊቶች ጋር ማዛመድ አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ “የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቆአልና” ይላል። (ሮሜ 6:7, 23) በመሆኑም የኃጢአት ውጤት ከሞት በኋላ ወዳለው ሕይወት አይሻገርም።
ሰይጣን ዲያብሎስም ብዙ ስቃይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። እንዲያውም ይህንን ዓለም የሚቆጣጠረው ሰይጣን ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደተናገረው ደቀ መዛሙርቱ ‘በሁሉም ዘንድ ስለ ስሙ የተጠሉ’ ይሆናሉ። (ማቴዎስ 10:22) በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ከክፉዎች የበለጠ ችግር ይደርስባቸዋል።
ባለንበት ዓለም ባልታወቀ ምክንያት አንዳንድ ነገሮች ይከሰታሉ። ፈጣን የሆነው ሯጭ ተደናቅፎ ከሩጫው ሊወጣ ይችላል። ኃያል የሆነው ሠራዊት በደካማዎቹ ድል ሊደረግ ይችላል። ጠቢብ የሆነው ሰው ጥሩ ሥራ ማግኘት ሊያቅተውና በዚህም ምክንያት ሊራብ ይችላል። ንግድ የማካሄድ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች በሁኔታዎች አስገዳጅነት እውቀታቸውን ለመጠቀም ሳይችሉ ይቀሩና በድህነት ሊወድቁ ይችላሉ። አዋቂ የሆኑ ሰዎች የባለ ሥልጣናት ቁጣ ሊነድባቸውና በፊታቸው ሞገስ ሊያጡ ይችላሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው? ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ጊዜና አጋጣሚ ሁሉን ስለሚያገናኛቸው ነው’ ሲል መልስ ይሰጣል።— መክብብ 9:11
የሂንዱ ሃይማኖታዊ ጠበብት የሰው ልጅ ስቃይ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማብራራት ከመሞከራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ስቃይና መከራ የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ሆነው ኖረዋል። ይሁን እንጂ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይኖራልን? መጽሐፍ ቅዱስ ለሙታን ምን ተስፋ ይዟል?
ሰላም የሰፈነበት የወደፊት ጊዜ
ፈጣሪ በቅርብ ጊዜ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውን የአሁኑን የዓለም ኅብረተሰብ ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ ዳንኤል 2:44) በዚያን ጊዜ ጻድቅ የሆነ አዲስ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ በሌላ አባባል “አዲስ ምድር” እውን ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያን ጊዜ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም። (ኢሳይያስ 33:24) ሞት የሚያስከትለው ሰቆቃ እንኳ አይኖርም፤ ምክንያቱም አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”— ራእይ 21:4
አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ነዋሪዎች በተመለከተ መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ከዚህም በላይ ገሮች “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”— መዝሙር 37:11
በፊተኛው ርዕስ ውስጥ የተጠቀሰው ሙካንድባይ ስለ አምላክ ድንቅ ተስፋ ሳያውቅ በሞት አንቀላፍቷል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ” ተስፋ ስለሚሰጥ አምላክን ሳያውቁ በሞት ያሸለቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነሥተው ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ አላቸው።— ሥራ 24:15፤ ሉቃስ 23:43
እዚህ ላይ የተሠራበት “ትንሣኤ” የሚለው ቃል አናስታሲስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “ዳግመኛ መነሣት” ማለት ነው። በመሆኑም ትንሣኤ የግለሰቡን አኗኗር እንደገና ማስጀመር ማለት ነው።
የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው አምላክ ለጥበቡ ዳርቻ የለውም። (ኢዮብ 12:13) የሙታንን የቀድሞ አኗኗር ለማስታወስ ምንም አይቸገርም። (ከኢሳይያስ 40:26 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ፍቅሩ ብዙ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) በመሆኑም ፍጹም የሆነውን የማስታወስ ችሎታውን ሙታንን ከዚያ ቀደም በሠሩት ኃጢአት ለመቅጣት ሳይሆን ከመሞታቸው በፊት የነበራቸውን ሁለንታናዊ ባሕርይ እንደገና በማላበስ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለሕይወት እንዲበቁ ለማድረግ ሊጠቀምበት ይችላል።
እንደ ሙካንድባይ ላሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትንሣኤ ማለት ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደገና የሚገናኙበት አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በሕይወት ላሉት ሰዎች ምን ትርጉም እንደሚኖረው እስቲ አስብ። ለምሳሌ ያህል ስለ አምላክና ስለ ዓላማው ግሩም የሆነውን እውነት ያወቀውን የሙካንድባይን ልጅ ሁኔታ እንውሰድ። አባቱ ዙሪያውን በክፋትና ስቃይ በታጠረና መጨረሻ በሌለው እንደገና የመወለድ ሽክርክሪት ውስጥ እንዳልሆነ ማወቁ ምን ያህል አጽናንቶት ይሆን! አባቱ በሞት አንቀላፍቶ ትንሣኤ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረውን ነገር ለአባቱ ማካፈል የሚችልበት ቀን እንደሚመጣ ሲያስብ ምንኛ ይደሰት ይሆን!
“ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ የአምላክ ፈቃድ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ካሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የምትችለው እንዴት እንደሆነ የምትማርበት ጊዜ አሁን ነው።— ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ጊዜና አጋጣሚ ሁሉን ያገናኟቸዋል።’—መክብብ 9:11
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ ባሕርይና የካርማ ሕግ
የአምላክ ባሕርይና የካርማ ሕግ “የካርማ ሕግ” ይላሉ ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ “የማይሻርና ልንሸሸው የማንችለው ሕግ ነው። በመሆኑም አምላክ ምንም ጣልቃ መግባት አያስፈልገውም። አንዴ ሕጉን ከደነገገ በኋላ እጁን እንዳወጣ ያክል ነው።” ጋንዲ ይህንን ማብራሪያ ለመቀበል ከብዷቸዋል።
በሌላ በኩል ግን የትንሣኤ ተስፋ አምላክ ለፍጥረታቱ በጥልቅ እንደሚያስብ ያሳያል። አንድን ሞቶ የነበረ ሰው ወደ ሕይወት መልሶ ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖር ማድረግ አምላክ ስለዚያ ሰው እያንዳንዱን ነገር እንዲያስታውስ የሚጠይቅ ነው። በእርግጥም አምላክ ስለ እያንዳንዳችን ያስባል።— 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሂንዱ የሕይወት ሽክርክሪት
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ቃል ስለ ትንሣኤ ያስተምራል