ቲኦክራሲያዊ አስተዳደር በክርስትና ዘመን
“እንደ ወደደ እንደ አሳቡ . . . በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” — ኤፌሶን 1:9, 10
1, 2. (ሀ) ከ33 እዘአ ጀምሮ ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ የመሰብሰቡ ሥራ የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1914 ጀምሮ የሙሴንና የኤልያስን መንፈስ ያሳዩት እንዴት ነው?
“በሰማይ ያሉትን ነገሮች” የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው በ33 እዘአ ‘የአምላክ እስራኤል’ ሲወለድ ነው። (ገላትያ 6:16፤ ኢሳይያስ 43:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:9, 10) እውነተኛ ክርስቲያኖች (ኢየሱስ “ስንዴ” ብሎ የጠራቸው) ሰይጣን በዘራው “እንክርዳድ” ተውጠው ስለነበረ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በኋላ የመሰብሰቡ ሥራ አዝጋሚ ሆኖ ነበር። ሆኖም “የፍጻሜው ዘመን” እየቀረበ ሲመጣ እውነተኞቹ የአምላክ እስራኤሎች በዓለም መድረክ ላይ እንደገና ብቅ በማለት በ1919 በጠቅላላው የኢየሱስ ንብረት ላይ ተሾሙ።a— ማቴዎስ 13:24-30, 36-43፤ 24:45-47፤ ዳንኤል 12:4
2 እንደ ሙሴና ኤልያስ ሁሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አስገራሚ ሥራዎችን አከናውነዋል።b (ራእይ 11:5, 6) ተቃዋሚ በሆነ ዓለም ውስጥ የኤልያስን ዓይነት ድፍረት በማሳየት ከ1919 ጀምሮ ምሥራቹን ሰብከዋል። (ማቴዎስ 24:9-14) በተጨማሪም ሙሴ በጥንት ግብፃውያን ላይ የአምላክን መቅሰፍቶች እንዳመጣ ሁሉ ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ከ1922 ጀምሮ አውጀዋል። (ራእይ 15:1፤ 16:2-17) የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች በአሁኑ ጊዜ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም ኅብረተሰብ አስኳል ናቸው።
የአስተዳደር አካል ሥራውን ጀመረ
3. የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ በሚገባ የተደራጀ እንደነበረ ምን ነገሮች ያሳያሉ?
3 የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ከመጀመሪያው ጀምሮ የተደራጁ ነበሩ። የደቀ መዛሙርት ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በየአካባቢው ጉባኤዎች ይቋቋሙና ሽማግሌዎች ይሾሙ ነበር። (ቲቶ 1:5) ከ33 እዘአ በኋላ 12ቱ ሐዋርያት ሥልጣን ያለው ማዕከላዊ የአስተዳደር አካል ሆነው አገልግለዋል። በምስክርነቱ ሥራ ድፍረት የተሞላበት አመራር ሰጥተዋል። (ሥራ 4:33, 35, 37፤ 5:18, 29) ለችግረኞች ምግብ የሚከፋፈልበትን መንገድ አቀናጅተዋል፤ እንዲሁም በሰማርያ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት ሲደርሳቸው ተከታትለው እንዲረዷቸው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደዚያ ላኩ። (ሥራ 6:1-6፤ 8:6-8, 14-17) ቀድሞ አሳዳጅ የነበረው ጳውሎስ አሁን የኢየሱስ ተከታይ መሆኑን ለማሳወቅ በርናባስ ጳውሎስን ወደ እነሱ ይዞት ሄዷል። (ሥራ 9:27፤ ገላትያ 1:18, 19) ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ ከመሰከረ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በዚህ ረገድ የአምላክ ፈቃድ ምን መሆኑን መንፈስ ቅዱስ እንዴት እንዳመለከተው ለሐዋርያትና በይሁዳ ለሚገኙ ሌሎች ወንድሞች አብራርቷል።— ሥራ 11:1-18
4. ጴጥሮስን ለመግደል ምን ሙከራ ተደርጎ ነበር? ሕይወቱ የተረፈውስ እንዴት ነበር?
4 ከዚያም በአስተዳደር አካሉ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። ጴጥሮስ ታሰረና በመላእክታዊ ጣልቃ ገብነት ሕይወቱ ሊተርፍ ቻለ። (ሥራ 12:3-11) አሁን ከ12ቱ ሐዋርያት ሌላ አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከፍተኛ ኃላፊነት ተቀበለ። ጴጥሮስ ከእስር ቤት ሲለቀቅ በዮሐንስ ማርቆስ እናት ቤት ተሰብስበው ለነበሩት “ይህን ለያዕቆብ [ለኢየሱስ ግማሽ ወንድም] እና ለወንድሞች ንገሩ” አላቸው።— ሥራ 12:17
5. ያዕቆብ በሰማዕትነት ከተገደለ በኋላ የአስተዳደር አካል ይዘት የተለወጠው እንዴት ነበር?
5 ከሃዲ ሐዋርያ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ራሱን በገደለበት ወቅት “ሹመቱን” በአገልግሎት ከኢየሱስ ጋር ለነበረና የኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ ላየ ለሌላ ሰው መስጠት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ተችሎ ነበር። ይሁን እንጂ የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ ሲገደል ከ12ቱ እንደ አንዱ በመሆን የተካው ሰው አልነበረም። (ሥራ 1:20-26፤ 12:1, 2) ምንም እንኳ ያዕቆብን በቀጥታ የተካው ሰው ባይኖርም ስለ አስተዳደር አካሉ የተሰጠው ቅዱስ ጽሑፋዊ መግለጫ የአስተዳደር አካሉ ቁጥር እንደጨመረ ያሳያል። የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑ አሕዛብ ለሙሴ ሕግ መገዛት አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል ክርክር በተነሳ ጊዜ ጉዳዩ ውሳኔ እንዲያገኝ በኢየሩሳሌም ወደነበሩት “ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም” ተላከ። (ሥራ 15:2, 6, 20, 22, 23፤ 16:4) አሁን በአስተዳደር አካል ላይ “ሽማግሌዎች” የተጨመሩት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የሚገልጸው ነገር የለም፤ ግን አንድ ግልጽ የሆነ ጥቅም ነበረው። የያዕቆብ መሞትና የጴጥሮስ መታሰር ሌሎች ሐዋርያትም አንድ ቀን ሊታሰሩ ወይም ሊገደሉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነበር። የአስተዳደር አካሉን አሠራር ጠንቅቀው የሚያውቁ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች መኖራቸው እንዲህ ያለ ድንገተኛ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ በበላይነት የማስተዳደሩ ሥራ ሥርዓት ባለው መንገድ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ያደርጋል።
6. ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ አባላቱ ከዚያች ከተማ ቢለቁም የአስተዳደር አካል በኢየሩሳሌም ሥራውን የቀጠለው እንዴት ነበር?
6 በ56 እዘአ ገደማ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ለያዕቆብ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን “ሽማግሌዎችም ሁሉ” በዚያ እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሥራ 21:18) በዚህ ስብሰባ ላይ ሐዋርያት እንደነበሩ ያልተጠቀሰው ለምንድን ነው? አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ነገር የለም። ይሁን እንጂ “የቀሩት ሐዋርያት በተሸረበባቸው የግድያ ሴራ ሕይወታቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ በመውደቁ ከይሁዳ ወጥተው ነበር። ያም ሆኖ ግን መልእክታቸውን ለሌሎች ለማዳረስ ሲሉ በክርስቶስ ኃይል በየአገሩ ዞረዋል” ሲል ታሪክ ጸሐፊው ዩሲቢየስ ከ66 እዘአ ጥቂት ቀደም ብሎ ዘግቧል። (ዩሲቢየስ መጽሐፍ 3, 5 ጥራዝ 2) እርግጥ ነው፣ የዩሲቢየስ ቃላት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ጽሑፍ ክፍል አይደሉም፤ ሆኖም እነዚህ ቃላት በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ዘገባ ጋር ይስማማሉ። ለምሳሌ ያክል በ62 እዘአ ጴጥሮስ ከኢየሩሳሌም ርቃ በምትገኘው በባቢሎን ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:13) ያም ሆኖ ግን በ56 እዘአ፣ እንዲያውም እስከ 66 እዘአ ድረስ በኢየሩሳሌም የአስተዳደር አካል እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም።
በአሁኑ ጊዜ ያለው አስተዳደር
7. በዛሬው ጊዜ ያለው የአስተዳደር አካል ይዘት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የአስተዳደር አካል ጋር ሲወዳደር ምን የጎላ ልዩነት አለ?
7 ከ33 እዘአ ጀምሮ በኢየሩሳሌም ላይ መከራ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የአስተዳደር አካሉ ያቀፈው አይሁድ ክርስቲያኖችን እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ጳውሎስ በ56 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣበት ወቅት በዚያ የሚገኙ ብዙ አይሁድ ክርስቲያኖች ‘የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን’ እምነት ከመያዝ ይልቅ “[ለሙሴ] ሕግ የሚቀኑ” እንደነበሩ ተገንዝቧል።c (ያዕቆብ 2:1፤ ሥራ 21:20-25) እነዚህ አይሁዶች ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰው የአስተዳደር አካል አባል በመሆን ሊሠራ ይችላል ቢባሉ ይህን ለመቀበል ይከብዳቸው የነበረ ይመስላል። ሆኖም አሁን ያለው የአስተዳደር አካል ይዘት ፈጽሞ የተለየ ነው። በዛሬው ጊዜ ያለው የአስተዳደር አካል አይሁዳዊ ያልሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ሲሆን ይሖዋም የሚሰጡትን አመራር በእጅጉ ባርኮታል።— ኤፌሶን 2:11-15
8, 9. በዘመናችን ባለው የአስተዳደር አካል ውስጥ ምን ለውጦች ተከስተዋል?
8 የፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከተቋቋመበት ከ1884 አንስቶ እስከ 1972 ድረስ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሲሆን የአስተዳደር አካሉ ደግሞ ከማኅበሩ የዲሬክተሮች ቦርድ ጋር ተቀራርቦ ይሠራ ነበር። በእነዚህ ዓመታት የተገኘው በረከት ይሖዋ ይህን አሠራር እንደተቀበለው የሚያሳይ ነው። በ1972 እና በ1975 መካከል የአስተዳደር አካሉ አባላት ቁጥር ወደ 18 ከፍ ብሏል። ከተጨማሪዎቹ አባላት መካከል አንዳንዶቹ የፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዲሬክተሮች ሲሆኑ የአባላቱን ቁጥር የጨመረው ይህ የአስተዳደር አካል ተጨማሪ ሥልጣን እንዲያገኝ መደረጉ አሠራሩ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አሠራር ጋር ይበልጥ እንዲመሳሰል አድርጎታል።
9 ከ1975 ጀምሮ ከእነዚህ ከአሥራ ስምንቶቹ ግለሰቦች መካከል በርካታዎቹ ምድራዊ ሕይወታቸውን ጨርሰዋል። ዓለምን ድል አድርገው ‘ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ ዙፋኑ ተቀምጠዋል።’ (ራእይ 3:21) በ1994 አባል የሆነውን ወንድም ጨምሮ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የአስተዳደር አካሉ በአሁኑ ጊዜ አሥር አባላት አሉት። አብዛኞቹ በእድሜ በጣም ገፍተዋል። ሆኖም እነዚህ ቅቡዓን ወንድሞች የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ጥሩ ድጋፍ በማግኘት ላይ ናቸው። ይህን ድጋፍ እያገኙ ያሉት ከየት ነው? በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮች በመጠኑ በመቃኘት ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን።
ለአምላክ እስራኤል የተደረገ ድጋፍ
10. በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ በይሖዋ አገልግሎት ከቅቡዓን ጋር የተባበሩት እነማን ናቸው? ይህስ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?
10 በ1884 ከአምላክ እስራኤል ጋር ተባብረው የነበሩት ሁሉም ማለት ይቻላል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። ሆኖም ቀስ በቀስ ሌላ ቡድን ብቅ ማለት ጀመረ፤ ከዚያም በ1935 ይህ ቡድን በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሱትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚያመለክት ታወቀ። እነዚህ ሰዎች ምድራዊ ተስፋ ስላላቸው ይሖዋ በክርስቶስ ለመጠቅለል ያሰበውን ‘በምድር ያለውን ነገር’ ያመለክታሉ። (ኤፌሶን 1:10) ኢየሱስ ስለ በጎች በረት በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሱትን “ሌሎች በጎች” ያመለክታሉ። (ዮሐንስ 10:16) ከ1935 ጀምሮ ሌሎች በጎች ወደ ይሖዋ ድርጅት በመጉረፍ ላይ ናቸው። ‘ወደ ቤታቸው እንደሚበሩ ርግቦችና እንደ ደመና በርረው እየመጡ’ ነው። (ኢሳይያስ 60:8) የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱና የቅቡዓን ክፍል የሆኑት ብዙዎች እየሞቱ ምድራዊ ሕይወታቸውን በመጨረሳቸው ቁጥራቸው እየቀነሰ በመሄዱ ብቃት ያላቸው ሌሎች በጎች በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መጥቷል። ይህ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
11. ቀድሞ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ተወስነው የነበሩ በኋላ ግን ለሌሎች በጎችም የተሰጡት መብቶች የትኞቹ ናቸው?
11 የይሖዋን ክብር በሰፊው ማወጅ የአምላክ “ቅዱስ ሕዝብ” ተቀዳሚ ግዴታ ሆኖ ቆይቷል። ጳውሎስ በቤተ መቅደስ እንደሚቀርብ መሥዋዕት አድርጎ የገለጸው ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ “የንጉሥ ካህናት” ለሚሆኑት ሰዎች የመስበክና የማስተማር ተልእኮ ሰጥቷል። (ዘጸአት 19:5, 6፤ 1 ጴጥሮስ 2:4, 9፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 13:15, 16) ሆኖም የነሐሴ 1, 1932 መጠበቂያ ግንብ በኢዮናዳብ የተመሰሉት ሰዎች በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ በቀጥታ አበረታትቷል። እርግጥ ነው፣ ብዙዎቹ የሌሎች በጎች አባላት ቀደም ብሎም በዚህ ሥራ መሳተፍ ጀምረው ነበር። በዛሬው ጊዜ እነዚህ ሌሎች በጎች ‘በመቅደሱ ሌሊትና ቀን [ለአምላክ] የሚያቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት’ ዋነኛ ክፍል በማድረግ የስብከቱን ሥራ በአብዛኛው እያከናወኑ ያሉት እነሱ ናቸው። (ራእይ 7:15) በተመሳሳይም ቀደም ባለው ዘመናዊ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ፤ እነዚህ የጉባኤ ሽማግሌዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ እጅ ውስጥ ያሉ “ከዋክብት” ተደርገው ተገልጸዋል። (ራእይ 1:16, 20) ሆኖም የግንቦት 1, 1937 መጠበቂያ ግንብ ብቃት ያላቸው ሌሎች በጎች የቡድን አገልጋይ (ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች) ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ አስታወቀ። ቅቡዓን ወንዶች ቢኖሩም እንኳ ይህን ኃላፊነት መሸከም የማይችሉ ከሆነ ሌሎች በጎች በዚህ ኃላፊነት ሊያገለግሉ ይችላሉ። ዛሬ ያሉት ሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች ማለት ይቻላል የሌሎች በጎች ክፍል ናቸው።
12. ብቃት ያላቸው ሌሎች በጎች ድርጅታዊ የሆኑ ከባድ ኃላፊነቶችን እንዲቀበሉ የተደረገው የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች በመከተል ነው?
12 ይህን ዓይነቱን ከባድ ኃላፊነት ለሌሎች በጎች መስጠት ስህተት ነውን? ስህተት አይደለም፤ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ጥንት የተፈጸመ ሁኔታ አለ። እምነታቸውን የለወጡ የውጭ አገር ሰዎች (መጻተኞች) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ከፍ ያሉ የኃላፊነት ቦታዎችን ይዘው ነበር። (2 ሳሙኤል 23:37, 39፤ ኤርምያስ 38:7-9) ከባቢሎን ግዞት በኋላ ብቃት ያላቸው ናታኒሞች (እስራኤላውያን ያልሆኑ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች) ቀድሞ ለሌዋውያን ብቻ ይሰጥ የነበረውን በቤተ መቅደስ ውስጥ የማገልገል መብት አግኝተዋል። (ዕዝራ 8:15-20፤ ነህምያ 7:60) በተጨማሪም ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ አብሮ የታየው ሙሴ ምድያማዊው ዮቶር የሰጠውን ጥሩ ምክር ተቀብሏል። በኋላም ሙሴ የዮቶርን ልጅ ኦባብን በምድረ በዳ እንዲመራቸው ጠይቆታል።— ዘጸአት 18:5, 17-24፤ ዘኁልቁ 10:29
13. ብቃት ላላቸው ሌሎች በጎች ኃላፊነቶችን በትህትና በመስጠት ረገድ ቅቡዓን የማንን ግሩም ምሳሌ አንጸባርቀዋል?
13 በምድረ በዳ ያሳለፏቸው 40 ዓመታት እየተገባደዱ ሲሄዱ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደማይገባ ስላወቀ በእሱ ቦታ የሚተካ ሰው እንዲያዘጋጅ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (ዘኁልቁ 27:15-17) ይሖዋ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ኢያሱን እንዲሾመው ነገረው፤ ምንም እንኳ ሙሴ ገና ብርቱ የነበረና እስራኤላውያንን መምራቱን ወዲያው የማያቆም ቢሆንም የተባለውን አድርጓል። (ዘዳግም 3:28፤ 34:5-7, 9) ቅቡዓንም ተመሳሳይ በሆነ የትህትና መንፈስ የሌሎች በጎች ክፍል ለሆኑ ብቃት ያላቸው ወንዶች ተጨማሪ ኃላፊነቶችን በመስጠት ላይ ናቸው።
14. ሌሎች በጎች በድርጅቱ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እየጨመረ እንደሚሄድ የትኞቹ ትንቢቶች ይጠቁማሉ?
14 ሌሎች በጎች በድርጅቱ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እየጨመረ መሄዱ ትንቢታዊ ፍጻሜ ጭምር አለው። እስራኤላዊ ያልሆነ ፍልስጤማዊ “እንደ አለቃ” እንደሚሆን ዘካርያስ ትንቢት ተናግሯል። (ዘካርያስ 9:6, 7) እዚህ ላይ አለቃ የተባሉት የነገድ መሪዎች ነበሩ፤ ስለዚህ ዘካርያስ ቀድሞ የእስራኤል ጠላት የነበረ ሰው እውነተኛውን አምልኮ ተቀብሎ በተስፋይቱ ምድር ውስጥ እንደ ነገድ አለቃ ይሆናል ማለቱ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የአምላክ እስራኤልን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፣ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፣ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል።” (ኢሳይያስ 61:5, 6) “መጻተኞች” እና “ሌሎች ወገኖች” የተባሉት ሌሎች በጎች ናቸው። እድሜያቸው እየገፋ ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች ምድራዊ ሕይወታቸውን ጨርሰው በክብራማው የይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ‘የአምላካችን አገልጋዮች’ በመሆን ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ ‘የይሖዋ ካህናት’ ሆነው ለማገልገል ወደ ሰማይ በሚሄዱበት ጊዜ ሌሎች በጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥራውን እንዲረከቡ ኃላፊነት እየተሰጣቸው ነው።— 1 ቆሮንቶስ 15:50-57፤ ራእይ 4:4, 9-11፤ 5:9, 10
‘የሚመጣው ትውልድ’
15. በዚህ የፍጻሜ ዘመን ‘ዕድሜያቸው የገፋው’ የትኞቹ የክርስቲያኖች ቡድን አባላት ናቸው? ‘የሚመጣው ትውልድ’ የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው እነማንን ነው?
15 ቅቡዓን ቀሪዎች ሌሎች በጎችን ለተጨማሪ ኃላፊነቶች ሲያሠለጥኑ ቆይተዋል። መዝሙር 71:18 እንዲህ ይላል:- “እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፣ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፣ አቤቱ፣ አትተወኝ።” የታኅሣሥ 15, 1948 መጠበቂያ ግንብ ይህን ጥቅስ በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጥ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባላት በእርግጥም በእድሜ እንደገፉ አመልክቷል። ቅቡዓን “በመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት ብርሃን የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቁና አንድ አዲስ ትውልድ እንደሚያዩ” ገልጿል። ይህ በተለይ የሚያመለክተው እነማንን ነው? መጠበቂያ ግንቡ “ኢየሱስ ‘ሌሎች በጎቹ’ እንደሆኑ አድርጎ እንደጠራቸው” ይናገራል። ‘የሚመጣው ትውልድ’ የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው በሰማያዊው መንግሥት በሚመራው አዲስ ምድራዊ አስተዳደር ሥር የሚኖሩትን ሰዎች ነው።
16. እነዚህ ‘የሚመጣው ትውልድ’ የተባሉት ምን በረከቶችን በጉጉት ይጠባበቃሉ?
16 ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የሚመጣው ትውልድ’ ተብለው ከተጠሩት ወንድሞቻቸው የሚለዩትና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ክብር የሚጎናጸፉት መቼ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። ሆኖም እነዚህ ቅቡዓን ይህ ጊዜ በጣም እንደቀረበ እርግጠኞች ናቸው። ኢየሱስ ስለ “ፍጻሜው ዘመን” በተናገረው ታላቅ ትንቢት ውስጥ የተነገሩት ነገሮች ከ1914 ጀምሮ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ ይህም የዚህ ዓለም ጥፋት ቅርብ እንደሆነ ያሳያል። (ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ ማርቆስ 13:4-20፤ ሉቃስ 21:7-24) ‘ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀለትን መንግሥት [ምድራዊ ግዛት]’ ለሚወርሰው ‘ለሚመጣው ትውልድ’ ይሖዋ በቅርቡ አዲስ ዓለም ያመጣል። (ማቴዎስ 25:34) ገነት ተመልሳ እንደምትመጣና በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን ከሐዴስ እንደሚወጡ በማሰብ ልባቸው በደስታ ይሞላል። (ራእይ 20:13) ከሞት የሚነሱትን ሰዎች ለመቀበል ቅቡዓን በዚያ ይገኛሉን? በ1925 የግንቦት 1 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “አምላክ እንዲህ ያደርጋል ወይም እንዲህ አያደርግም እያልን የየራሳችንን ግምት መስጠት አይኖርብንም። . . . ነገር ግን የጥንት ጻድቃን [በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ታማኝ ምስክሮች] ከመነሳታቸው በፊት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት [ቅቡዓን ክርስቲያኖች] ክብር ይጎናጸፋሉ ወደሚል መደምደሚያ እንደርሳለን።” መጠበቂያ ግንብ 17-110 ስለዚሁ ጉዳይ ማለትም ሙታን ሲነሱ ለመቀበል ከቅቡዓን መካከል የተወሰኑት ምድር ላይ መቆየት ያስፈልጋቸው እንደሆነ ሲያብራራ “ይህ አስፈላጊ አይሆንም” ብሏል።d
17. ቅቡዓን በቡድን ደረጃ በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የትኞቹን አስደናቂ መብቶች ይካፈላሉ?
17 እርግጥ ነው፣ በእያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያን ላይ ምን እንደሚደርስ አናውቅም። ሆኖም ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ጊዜ ሙሴና ኤልያስ አብረው መታየታቸው ኢየሱስ ፍርዱን በሚያስፈጽምበትና ‘ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ለማስረከብ’ በክብር በሚመጣበት ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም አብረውት መሆን እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታል። በተጨማሪም ኢየሱስ በአርማጌዶን ‘አሕዛብን በብረት በትር በሚገዛበት’ ጊዜ ‘ድል የነሱት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አብረውት እንደሚገዙ ቃል መግባቱን እናስታውሳለን። ኢየሱስ በክብር በሚመጣበት ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ በመፍረድ’ አብረውት ይቀመጣሉ። ከኢየሱስ ጋር በመሆን ‘ሰይጣንን ከእግራቸው በታች ይቀጠቅጡታል።’— ማቴዎስ 16:27 እስከ 17:9፤ 19:28፤ ራእይ 2:26, 27፤ 16:14, 16፤ ሮሜ 16:20፤ ዘፍጥረት 3:15፤ መዝሙር 2:9፤ 2 ተሰሎንቄ 1:9, 10
18. (ሀ) ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች በክርስቶስ የመሰብሰቡ’ ሥራ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? (ለ) ‘በምድር ያሉትን ነገሮች በክርስቶስ የመሰብሰቡን’ ሥራ በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?
18 ይሖዋ ነገሮችን እያስተዳደረ ካለበት መንገድ ጋር በመስማማት ‘ነገሮችን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል’ ደረጃ በደረጃ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው። ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ በተመለከተ ያለው ዓላማ ወደ ፍጻሜው ቀርቧል። ‘ለበጉ ሰርግ’ 144,000ዎቹ በጠቅላላ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የሚሆኑበት ጊዜ ቀርቧል። ስለዚህ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ ለረጅም ጊዜ የቆዩ የጎለመሱ ወንድሞች ‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ በመወከል ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ከባድ ኃላፊነቶችን በመቀበል ላይ ናቸው። የምንኖረው ምንኛ አስደሳች በሆነ ወቅት ነው! የይሖዋ ዓላማ ወደ ፍጻሜው ሲገሰግስ ማየት እንዴት ያስደስታል! (ኤፌሶን 1:9, 10፤ 3:10-12፤ ራእይ 14:1፤ 19:7, 9) ለንጉሡ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመገዛት ለታላቁ የአጽናፈ ዓለም ገዥ ለይሖዋ አምላክ ክብር ሁለቱም ቡድኖች “በአንድ እረኛ” ስር እንደ “አንድ መንጋ” ሆነው አንድ ላይ ሲያገለግሉ ሌሎች በጎች ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን በመርዳታቸው ምንኛ ይደሰታሉ!— ዮሐንስ 10:16፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b ለምሳሌ ያክል በምስልና በድምፅ ተቀርጾ የቀረበው “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ከ1914 ጀምሮ በመላው የምዕራቡ ዓለም በተመልካቾች ጢም ብለው በሞሉ የቲያትር ቤት አዳራሾች ሲታይ ቆይቷል።
c አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለሕጉ ይቀኑ የነበረው ለምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 1163-4 ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአምላክ ድርጅት ወደፊት ሲገፋ የነበረው እንዴት ነው?
◻ በዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ በአስተዳደር አካል ውስጥ ምን ለውጦች ተደርገዋል?
◻ ሌሎች በጎች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲይዙ ማድረጉ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለው?
◻ ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ እና ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ በክርስቶስ ሲሰበሰቡ የቆዩት እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያዎቹ አባላት በኢየሩሳሌም ባልነበሩበት ጊዜም እንኳ በዚያ የነበረው የአስተዳደር አካል ሥራ አልተቋረጠም
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የጎለመሱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለይሖዋ ሕዝቦች በረከት ሆነው ቆይተዋል
ሲ ቲ ራስል 1884-1916
ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 1916-42
ኤን ኤች ኖር 1942-77
ኤፍ ደብልዩ ፍራንዝ 1977-92
ኤም ጂ ሄንሼል 1992-