የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
አንዲት ልባም ሴት ጥፋት እንዳይደርስ ተከላከለች
አንዲት አስተዋይ ሴት አንድን የማይረባ ሰው አግብታ ነበር። ይህ አቢጋኤልንና ናባልን የሚገልጽ ሁኔታ ነው። አቢጋኤል “እጅግ የተዋበች አስተዋይ ሴት” ነበረች። ናባል ግን “መልካም ጠባይ የጎደለው ባለጌ ሰው ነበር።” (1 ሳሙኤል 25:3 የ1980 ትርጉም) የማይጣጣም ሁኔታ ስላላቸው ስለ እነዚህ ባልና ሚስት በግልጽ የሚናገረው ትዕይንት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ በማይረሳ መንገድ ሰፍሯል። እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ከቁም ነገር ያልተቆጠረ ውለታ
ጊዜው 11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። ዳዊት የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ ተቀብቶ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሆኖ ከመግዛት ይልቅ ከቦታ ቦታ የሚንከራተት ሰው ሆነ። በዙፋን ላይ የነበረው ንጉሥ ሳኦል እርሱን ለመግደል ቆርጦ ተነስቷል። በዚህም ምክንያት ዳዊት ስደተኛ ሆኖ ለመኖር ተገደደ። ከጊዜ በኋላ እርሱና 600 የሚሆኑት ግብረ አበሮቹ ከይሁዳ በስተ ደቡብና በሲና ምድረ በዳ አካባቢ በሚገኘው ፋራን በሚባል ምድረ በዳ መደበቂያ ቦታ አገኙ።— 1 ሳሙኤል 23:13፤ 25:1
እዚያ ይኖሩ በነበረበት ወቅት ናባል የሚባል ሰው አገልጋይ የሆኑ እረኞችን አገኙ። ይህ የካሌብ ዝርያ የሆነ ሀብታም ሰው 3,000 በጎችና 1,000 ፍየሎች ነበሩት። ከኬብሮን በስተ ሰሜንና ምናልባትም ከፋራን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ራቅ ብሎ በሚገኘው ቀርሜሎስ በሚባለው ከተማ በጎቹን ይሸልታል።a ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በጫካ ውስጥ አድፍጠው የሚመጡ ሌቦችን በመከላከል የናባልን እረኞች ረድተዋቸዋል።— 1 ሳሙኤል 25:14-16
በቀርሜሎስ በጎች የሚሸለቱበት ወቅት ጀምሮ ነበር። የአጨዳ ጊዜ ለገበሬዎች ትልቅ የደስታ ወቅት እንደሆነ ሁሉ ይህ ጊዜም ለእነርሱ የደስታ ወቅት ነበር። በተጨማሪም ይህ ጊዜ የበግ ባለ ሀብቶች አገልግሎት ለሰጧቸው ሰዎች ወሮታ በመክፈል ከፍተኛ ልግስና የሚያሳዩበት ወቅት ነው። ስለዚህ ዳዊት በጎቹን በመጠበቅ ላደረገው አገልግሎት ብድራት እንዲከፍለው አሥር ሰዎችን ወደ ቀርሜሎስ ከተማ ልኮ ምግብ እንዲልክለት ናባልን መጠየቁ የማይገባውን ለማግኘት በማን አለብኝነት የሚመራ ሰው መሆኑ አልነበረም።— 1 ሳሙኤል 25:4-9
ናባል የሰጠው ምላሽ ግን ስቁንቁን መሆኑን የሚያሳይ ነበር። “ዳዊት ማን ነው?” በማለት በንቀት መለሰ። ከዚያም ዳዊትም ሆነ ግብረ አበሮቹ ከጌቶቻቸው የከዱ ባሪያዎች እንደሆኑ በመግለጽ “እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን?” በማለት ጠየቀ። ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች “ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው።” ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች ለጦርነት ተሰለፉ።— 1 ሳሙኤል 25:10-13
አቢጋኤል ያሳየችው ማስተዋል
ናባል የተናገራቸው የዘለፋ ቃላት ሚስቱ ወደሆነችው ወደ አቢጋኤል ጆሮ ደረሱ። ለናባል አማላጅና አስታራቂ ሆና ስትሠራ ይህ የመጀመሪያዋ ጊዜ ላይሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ አቢጋኤል ፈጥና እርምጃ ወስዳለች። ለናባል ሳትነግረው አምስት በጎችና ብዙ ምግብ ይዛ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ምድረ በዳ ሄደች።— 1 ሳሙኤል 25:18-20
አቢጋኤል ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፊቱ ወድቃ እጅ ነሳች። “በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጥል እለምናለሁ” አለች። “አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጎልማሶች ይሰጥ።” አክላም “ይህ [የናባል ሁኔታ] ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ” ላይ አይሁን በማለት ተናገረች። እዚህ ላይ “ዕንቅፋት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የሕሊና ጸጸትን ያመለክታል። በዚህም የተነሳ አቢጋኤል የኋላ ኋላ ጸጸት ውስጥ ሊከተው የሚችል የችኮላ ድርጊት እንዳይፈጽም ዳዊትን አስጠነቀቀችው።— 1 ሳሙኤል 25:23-31
ዳዊት የአቢጋኤልን ቃል ሰማ። “ወደ ደም እንዳልሄድ፣ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፣ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ” በማለት ተናገራት። “እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ [“በቅጥሩ ላይ የሚሸና ማንኛውም ሰው፣” NW] ባልቀረውም ነበር።”b— 1 ሳሙኤል 25:32-34
ከዚህ የምናገኘው ትምህርት
አምላክን የምትወድ አንዲት ሴት አስፈላጊ ከሆነ በራሷ አነሳሽነት አንድ እርምጃ ብትወስድ በምንም ዓይነት መንገድ ስህተት ነው ሊባል እንደማይችል ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያሳያል። አቢጋኤል ከባሏ ማለትም ከናባል ፈቃድ ውጪ እርምጃ ወስዳለች። መጽሐፍ ቅዱስም ያደረገችውን ነገር ስህተት እንደሆነ አድርጎ አይናገርም። በተቃራኒው ግን ልባምና አስተዋይ ሴት በማለት ይክባታል። አቢጋኤል በዚህ አስጊ በሆነ ወቅት ቀዳሚ ሆና እርምጃ በመውሰዷ ብዙ ሕይወት አዳነች።
አንዲት ሚስት አምላካዊ የተገዥነት መንፈስ ማሳየት ቢኖርባትም ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ከባሏ የተለየ አቋም ልትወስድ ትችላለች። እርግጥ ነው “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ” ለማሳየት መጣጣር ይኖርባታል፤ እንዲሁም እልኸኛ፣ ኩሩ ወይም ዓመፀኛ በመሆን ራሷ በራሷ እርምጃ መውሰድ አይኖርባትም። (1 ጴጥሮስ 3:4) ይሁን እንጂ አምላካዊ አክብሮት ያላት አንዲት ሚስት ጥበብ የጎደለው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት የሚያስጥስ እንደሆነ የምታውቀውን ማንኛውንም ነገር እንድታደርግ እንደተገደደች ሆኖ ሊሰማት አይገባም። እውነት ነው አቢጋኤልን አስመልክቶ የሚናገረው ዘገባ መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን እንደ ባሪያ አድርጎ ይገልጻቸዋል የሚል አመለካከት ያላቸውን ሰዎች የሚቃወም ጠንካራ ማስረጃ ያቀርባል።
በተጨማሪም ይህ ዘገባ ራስን ስለ መግዛት ያስተምረናል። አንዳንድ ጊዜ ዳዊት ይህን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ምንም እንኳ አመቺ ጊዜ አግኝቶ የነበረና የሳኦል መሞት ለዳዊት ሰላም የሚያመጣ መሆኑን ቢያውቅም በደም በቀል ተነሳስቶ ንጉሥ ሳኦልን ለመግደል እምቢ ብሏል። (1 ሳሙኤል 24:2-7) በአንፃሩ ደግሞ ናባል የዘለፋ ስድብ በሰነዘረበት ጊዜ ዳዊት ባልተጠበቀ መንገድ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ጦር መዟል። “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን” ላለመመለስ ለሚጣጣሩ ክርስቲያኖች ይህ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ነው። በማንኛውም ጊዜ ሁሉ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር መከተል ይኖርባቸዋል።— ሮሜ 12:17-19
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የፋራን ምድረ በዳ እስከ ሰሜናዊው ቤርሳቤህ ድረስ እንደሚዘልቅ የታወቀ ነው። ይህ የምድር ክፍል ከፍተኛ ስፋት ያለው የግጦሽ መሬትን ያካተተ ነው።
b “በቅጥሩ ላይ የሚሸና ማንኛውም ሰው” የሚለው ሐረግ ወንዶችን ለማመልከት የሚሠራበት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። ንቀት ያዘለ ንግግር እንደሆነ ከዚህ ለመረዳት ይቻላል።—ከ1 ነገሥት 14:10 (NW) ጋር አወዳድር።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቢጋኤል ለዳዊት ስጦታ አመጣች