ክርስቲያኖችና የሰው ዘር ዓለም
“በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ።”—ቆላስይስ 4:5
1. ኢየሱስ ተከታዮቹንና ዓለምን በሚመለከት ምን ብሏል?
ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ አባቱ ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱን በሚመለከት እንዲህ አለ:- “እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።” በመቀጠልም “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:14, 15) ክርስቲያኖች በገዳማት ተገልለው በመኖር ከዓለም በአካል ይለያሉ ማለት አልነበረም። ይልቁንም ክርስቶስ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቹ’ እንዲሆኑ ‘ወደ ዓለም ልኳቸዋል።’ (ዮሐንስ 17:18፤ ሥራ 1:8) ያም ቢሆን ግን “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን በክርስቶስ ስም ምክንያት በእነርሱ ላይ ጥላቻን መቆስቆሱ ስለማይቀር አምላክ እንዲጠብቃቸው ጸልዮአል።—ዮሐንስ 12:31፤ ማቴዎስ 24:9
2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለዓለም ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት አለው?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ዓለም” (በግሪክኛ ኮስሞስ) የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ‘በክፉው የተያዘውን’ ኃጢአተኛ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ክርስቲያኖች ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ በመሆናቸውና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለዓለም እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመፈጸማቸው አንዳንድ ጊዜ ከዓለም ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የሻከረ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ዮሐንስ 3:1, 13) ይሁን እንጂ ኮስሞስ የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጠቅላላውን ሰብዓዊ ቤተሰብም ለማመልከት ተሠርቶበታል። ኢየሱስ ዓለም የሚለውን ቃል በዚህ መንገድ በመጠቀም ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” (ዮሐንስ 3:16, 17፤ 2 ቆሮንቶስ 5:19፤ 1 ዮሐንስ 4:14) በመሆኑም ይሖዋ በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ውስጥ የሚንጸባረቁትን ነገሮች ቢጠላም ‘ንስሐ የሚገቡ’ ሁሉ ይድኑ ዘንድ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ለሰው ዘር ያለውን ፍቅር አሳይቷል። (2 ጴጥሮስ 3:9፤ ምሳሌ 6:16-19) አምላኪዎቹም ቢሆኑ ይሖዋ ለዓለም ያለውን ሚዛናዊ አመለካከት ሊከተሉ ይገባል።
የኢየሱስ ምሳሌ
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ገዥ መሆንን በሚመለከት ምን ዓይነት አቋም ነበረው? (ለ) ኢየሱስ ለሰው ዘር ዓለም የነበረው አመለካከት ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ጴንጤናዊው ጲላጦስን “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) ኢየሱስ ከእነዚህ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ቀደም ሲል ሰይጣን በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ልስጥህ በማለት ያቀረበለትን ግብዣ አልቀበልም ከማለቱም ሌላ አይሁዳውያን ንጉሥ ሊያደርጉት በፈለጉ ጊዜ ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል። (ሉቃስ 4:5-8፤ ዮሐንስ 6:14, 15) ይሁንና ኢየሱስ ለሰው ዘር ዓለም ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። ሐዋርያው ማቴዎስ የዘገበው የሚከተለው ሐሳብ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል:- “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” በፍቅር ተገፋፍቶ በሚኖሩበት ከተማና መንደር እየሄደ ሰብኳል። አስተምሯቸዋል፣ ከሕመማቸውም ፈውሷቸዋል። (ማቴዎስ 9:36) ከእርሱ ለመማር የመጡት ሰዎች ስለሚያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ነገርም አጥብቆ ያስብ ነበር። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ:- ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው።” (ማቴዎስ 15:32) እንዴት ያለ ፍቅራዊ አሳቢነት ነው!
4 አይሁዳውያን ለሳምራውያን የከረረ ስሜታዊ ጥላቻ ነበራቸው፤ ኢየሱስ ግን ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ከመወያየቱም ሌላ በአንድ የሰማርያ ከተማ ሁለት ቀን ቆይቶ ሰፊ ምሥክርነት ሰጥቷል። (ዮሐንስ 4:5-42) አምላክ የላከው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ቢሆንም ኢየሱስ አልፎ አልፎ ሌሎች አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ላሳዩትም እምነት ምላሽ ይሰጥ ነበር። (ማቴዎስ 8:5-13፤ 15:21-28) አዎን፣ ኢየሱስ ‘ከዓለም ክፍል ሳይሆኑ’ ለሰው ዘር ዓለም ማለትም ለሰዎች ፍቅር ማሳየት እንደሚቻል በተጨባጭ አሳይቷል። እኛስ በምንኖርበት፣ በምንሠራበት ወይም በምንገበያይበት አካባቢ ላሉ ሰዎች ተመሳሳይ ርኅራኄ እናሳያለንን? ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ብቻ ሳይሆን አቅማችን የሚፈቅድልን ሆኖ ሲገኝ በሌሎች ችግሮቻቸው ረገድም ለደህንነታቸው እንደምናስብ እናሳያለንን? ኢየሱስ እንደዚያ አድርጓል፤ ይህንን ማድረጉ ደግሞ ሰዎችን ስለ መንግሥቱ ማስተማር የሚችልበት አጋጣሚ ከፍቶለታል። ኢየሱስ እንዳደረገው ቃል በቃል ተዓምራት ማከናወን እንደማንችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ያላቸውን ስሜታዊ ጥላቻ በማርገብ በኩል ደግነት ብዙውን ጊዜ ከተዓምር የማይተናነስ ነገር ያከናውናል።
ጳውሎስ “በውጭ” ላሉት ሰዎች የነበረው አመለካከት
5, 6. ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በውጭ ላሉ’ አይሁዳውያን ምን ዝንባሌ ነበረው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ በተለያዩ ደብዳቤዎቹ ውስጥ “በውጭ” ስላሉ ሰዎች ማለትም ክርስቲያን ስላልሆኑ አይሁዶችና አሕዛብ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 5:12፤ 1 ተሰሎንቄ 4:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:7) ለእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ምን አመለካከት ነበረው? ‘በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ያድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆኗል።’ (1 ቆሮንቶስ 9:20-22) ወደ አንድ ከተማ እንደደረሰ መጀመሪያ ለመስበክ የሚሄደው በአካባቢው ወደሚገኙት አይሁዳውያን ነበር። አቀራረቡስ እንዴት ነበር? መሲሑ እንደመጣ፣ መሥዋዕታዊ ሞት እንደሞተና ትንሣኤ እንዳገኘ የሚገልጹ አሳማኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን በጥበብና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ያቀርብ ነበር።—ሥራ 13:5, 14-16, 43፤ 17:1-3, 10
6 በዚህ መንገድ ጳውሎስ አይሁዳውያን ስለ ሕጉና ስለ ነቢያት መጻሕፍት የነበራቸውን እውቀት መሠረት አድርጎ በመጠቀም ስለ መሲሑና ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯቸዋል። አንዳንዶችንም ለማሳመን ችሏል። (ሥራ 14:1፤ 17:4) የአይሁድ መሪዎች ይቃወሙት የነበረ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ለአይሁዳውያን ልባዊ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል:- “ወንድሞች ሆይ፣ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና።”—ሮሜ 10:1, 2
አይሁዳዊ ያልሆኑ አማኞችን መርዳት
7. ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ብዙ ሰዎች ጳውሎስ ለሰበከው ምሥራች ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
7 ወደ ይሁዲነት የተለወጡ የሚባሉት ሰዎች በትውልድ አይሁዳዊ ያልሆኑና ተገርዘው የአይሁድ እምነት ተከታይ ሆነው የነበሩ ሰዎች ናቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በሮም፣ በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ፣ በኢትዮጵያና በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ይገኙ ነበር። እንዲያውም ከፍልስጤም ምድር ውጭ አይሁዳውያን በሰፈሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ይገኙ ነበር ለማለት ይቻላል። (ሥራ 2:8-10፤ 6:5፤ 8:27፤ 13:14, 43፤ ከማቴዎስ 23:15 ጋር አወዳድር።) ከብዙዎቹ የአይሁድ ገዥዎች በተለየ መልኩ ወደ ይሁዲነት የተለወጡት ሰዎች ትዕቢተኞች አልነበሩም፤ ደግሞም እነርሱ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ሊኩራሩ አይችሉም ነበር። (ማቴዎስ 3:9፤ ዮሐንስ 8:33) ከዚህ ይልቅ አረማዊ አማልክትን ትተው በትሕትና ወደ ይሖዋ ዞር በማለት ስለ እርሱና ስለ ሕጉ መጠነኛ እውቀት ቀስመዋል። በተጨማሪም መሲሕ ይመጣል የሚለውን የአይሁዳውያን ተስፋ ተቀብለዋል። ብዙዎቹ እውነትን የሚፈልጉና ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በመሆናቸው ተጨማሪ ለውጦችን በማድረግ ለሐዋርያው ጳውሎስ የስብከት መልእክት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ። (ሥራ 13:42, 43) በአንድ ወቅት አረማዊ አማልክትን ያመልክ የነበረ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው ክርስትናን ሲቀበል እነዚያን አማልክት በማምለክ ላይ ላሉ ሌሎች አሕዛብ ለመመሥከር የሚያስችል ጥሩ ብቃት ይኖረዋል።
8, 9. (ሀ) ወደ ይሁዲነት ከተለወጡት ሰዎች በተጨማሪ ወደ አይሁዳውያን ሃይማኖት ተስበው የነበሩት ሌሎች የአሕዛብ ወገኖች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አምላክን የሚፈሩ ብዙ ያልተገረዙ ሰዎች ለምሥራቹ ምን ምላሽ ሰጥተዋል?
8 ከተገረዙትና ወደ ይሁዲነት ከተለወጡት ሰዎች ሌላ፣ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችም ወደ አይሁድ ሃይማኖት ተስበው ነበር። ከእነዚህም መካከል ክርስቲያን ለመሆን የመጀመሪያ ሰው የነበረው ቆርኔሌዎስ ሲሆን ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው ባይሆንም “እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ” ሰው ነበር። (ሥራ 10:2) ፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንደነዚህ ያሉት አሕዛብ ብዙውን ጊዜ ‘አምላክን የሚፈሩ ሰዎች’ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ይህ ሕጋዊ ስያሜ ባይሆንም ተስማሚ አጠራር ነው። በዚያ ዘመን የነበሩት ብዙ አሕዛብ ሙሉ በሙሉ ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ የተዘጋጁ ባይሆኑም እንኳ (በተለይ ለወንዶቹ ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸው መገረዝ አለባችሁ የሚለው ጥያቄ ነበር) ለአንድ አምላክ ብቻ የሚቀርበው ያልተወሳሰበ የአይሁዳውያን የምኩራብ አምልኮና በሕይወታቸው ውስጥ የሚከተሏቸው የግብረገብ ደንቦች ይማርኳቸው ነበር። አንዳንዶቹ በምኩራቦች ተገኝተው ከሚሰሟቸው ጸሎቶችና በግሪክኛው ትርጉም ከሚነበብላቸው የቅዱሳን ጽሑፎች ሐሳብ ብዙ ትምህርት ይቀስሙ ነበር።”
9 ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሿ እስያና በግሪክ ምኩራቦች ሲሰብክ አምላክን የሚፈሩ ብዙ ሰዎች አግኝቷል። በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በምኩራብ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 13:16, 26) ጳውሎስ በተሰሎንቄ በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ ለሦስት ሰንበት ያህል ከሰበከ በኋላ “ከእነርሱም [ከአይሁዳውያን] አንዳንዶቹ ተረድተው [ክርስቲያን ሆነው]፣ ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፣ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ” ሲል ሉቃስ ጽፏል። (ሥራ 17:4) አንዳንዶቹ ግሪካውያን አምላክን የሚፈሩ ያልተገረዙ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እንደነዚህ ያሉት ብዙ አሕዛብ ከአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ጋር ይተባበሩ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ።
‘በማያምኑት’ መካከል መስበክ
10. ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንም እውቀት ላልነበራቸው አሕዛብ የሰበከላቸው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
10 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ‘የማያምኑ’ የሚለው ቃል ባጠቃላይ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉትን ሰዎች ሊያመለክት ይችላል። ብዙውን ጊዜ አረማዊ የሆኑ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ሮሜ 15:31፤ 1 ቆሮንቶስ 14:22, 23፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 6:14) በአቴንስ ውስጥ ብዙዎቹ የማያምኑ ሰዎች የግሪክን ፍልስፍና የተማሩና ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንም የሚያውቁት ነገር የሌላቸው ሰዎች ነበሩ። ይህ ሁኔታ ጳውሎስ ለእነርሱ ከመመሥከር ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታልን? አላደረገውም፤ ነገር ግን አቀራረቡን ለሁኔታው እንደሚስማማ አድርጎ አስተካክሏል። የአቴና ሰዎች ጨርሶ የማያውቋቸውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በቀጥታ ሳይጠቅስ በጥበብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች አስተላልፏል። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና በአንዳንድ የጥንት ኢስጦይክ ባለ ቅኔዎች ሐሳብ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በዘዴ አስረድቷቸዋል። ከዚያም ለሁሉም የሰው ዘር አንድ እውነተኛ አምላክ እንዳለ ገልጾ ይህ አምላክ ከሞት በተነሣው ሰው እጅ በጽድቅ እንደሚፈርድ ተናገረ። በዚህ መንገድ ጳውሎስ ለአቴና ሰዎች በጥበብ ስለ ክርስቶስ ሰብኮላቸዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? አብዛኞቹ እዚያው ፊቱ ቢያሾፉበትም ወይም ቢጠራጠሩም “አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።”—ሥራ 17:18, 21-34
11. ቆሮንቶስ ምን ዓይነት ከተማ ነበረች? ጳውሎስ በዚያ ያከናወነው ስብከትስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
11 በቆሮንቶስ በርከት ያሉ አይሁዳውያን ስለነበሩ ጳውሎስ አገልግሎቱን የጀመረው በምኩራብ ውስጥ በመስበክ ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ በተቃወሙ ጊዜ ጳውሎስ ወደ አሕዛብ ሄደ። (ሥራ 18:1-16) ይህ ሕዝብ ደግሞ ብልሹ የሆነ አኗኗር ያለው ነበር! ቆሮንቶስ ግር ግር የሚበዛባትና ብዙ ድብልቅ ሕዝብ የሚኖርባት የንግድ ከተማ ስትሆን በግሪካውያኑና በሮማውያኑ ዓለም በሙሉ የምትታወቀው ልቅ በሆነ አኗኗር ነበር። እንዲያውም “ቆሮንቶሳዊ መሆን” ማለት የብልግና ጎዳናን መከተል ማለት ነው። ይሁንና ክርስቶስ ለጳውሎስ ተገልጦለት “አትፍራ፣ ነገር ግን ተናገር . . . በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና” ያለው አይሁዳውያን ስብከቱን አንቀበልም ካሉ በኋላ ነው። (ሥራ 18:9, 10) ልክ እንዳለውም ምንም እንኳ ከተቋቋመው ጉባኤ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል “ቆሮንቶሳዊ” አኗኗር ይከተሉ የነበሩ ቢሆንም ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ማቋቋም ችሏል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
ዛሬ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እንዲድኑ መጣር
12, 13. (ሀ) ዛሬ ያለው የአገልግሎት ክልል በጳውሎስ ዘመን ከነበረው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ለረጅም ጊዜ በቆዩባቸው ወይም ብዙ ሰዎች በሃይማኖት ድርጅት ግራ በተጋቡባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ምን ዓይነት አመለካከት እንይዛለን?
12 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ‘ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን ምክንያት ይሆናል።’ (ቲቶ 2:11 NW) ምሥራቹ የሚሰበክበት ክልል ሁሉንም አህጉሮችና አብዛኛዎቹን የባሕር ደሴቶች የሚሸፍን ሆኗል። በእርግጥም ልክ እንደ ጳውሎስ ዘመን ዛሬም “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶቻችን የምንሰብከው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ለብዙ መቶ ዘመናት በቆዩባቸው አገሮች ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት አይሁዶች የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አባሎችም በሃይማኖታዊ ወጎች የተጠላለፉ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ ግን ጥሩ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ፈልገን በማግኘት ባላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ መገንባት በመቻላችን ደስ ይለናል። አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው የሚቃወሙንና የሚያሳድዱን ቢሆንም እንኳ እነዚህን ሰዎች በሚያቃልል መንገድ አናያቸውም ወይም በንቀት አንናገራቸውም። ከዚህ ይልቅ ግን ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ትክክለኛ እውቀት ባይኖራቸውም ‘ለአምላክ የሚቀኑ’ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንገነዘባለን። ልክ እንደ ኢየሱስና ጳውሎስ ለሰዎች እውነተኛ ፍቅር እናሳያለን፤ እንዲድኑም ከልባችን እንመኛለን።—ሮሜ 10:2
13 ብዙዎቻችን በምንሰብክበት ጊዜ በአንድ የሃይማኖት ድርጅት ግራ የተጋቡ ግለሰቦች እናገኛለን። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሰዎች አምላክን የሚፈሩ፣ በመጠኑም ቢሆን በአምላክ የሚያምኑና ቀና ጎዳና ተከትለው ለመኖር የሚጥሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ጠማማና እያደር አምላክ የለሽ እየሆነ በሚሄድ ትውልድ መካከል ትንሽም ቢሆን በአምላክ ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ለማግኘት በመቻላችን ልንደሰት አይገባም? እነዚህን ሰዎችስ ግብዝነትና ሐሰት ወደሌለበት አምልኮ ለመምራት አንጓጓም?—ፊልጵስዩስ 2:15
14, 15. ምሥራቹን የምንሰብክበት ሰፊ መስክ የተገኘው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ስለ መረቡ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ በስብከቱ ሥራ የሚሸፈን እጅግ ሰፊ ክልል እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:47-49) የሰኔ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ስለዚህ ምሳሌ ሲያብራራ በገጽ 20 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑ ሰዎች ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ የአምላክን ቃል በመተርጎም፣ በመገልበጥና በማሠራጨት ረገድ ከፍተኛ የሥራ ድርሻ አበርክተዋል። በኋለኞቹ ዘመናትም ሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ የሩቅ አገሮች ቋንቋዎች የተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራትን አቋቁማለች ወይም ደግፋለች። በተጨማሪም አብያተ ክርስቲያናት የዳቦ ክርስቲያኖችን ለማፍራት ሐኪሞችና አስተማሪዎች ሆነው የሚሠሩ ሚስዮናውያንን ወደ ተለያዩ አገሮች ልከዋል። እነርሱም የአምላክ ሞገስ የሌላቸውን ብዙ መጥፎ ዓሦች ቢሰበስቡና የተበላሸውን ክርስትና ቢያስፋፉም ሌላው ቢቀር ክርስቲያን ያልነበሩትን ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አስተዋውቀዋል።”
15 ሕዝበ ክርስትና ሰዎችን ለመለወጥ ያደረገችው እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ የነበረው በተለይ በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በአንዳንድ የባሕር ደሴቶች ነበር። በጊዜያችንም በእነዚህ አካባቢዎች ብዙ ገር ሰዎችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን አዎንታዊ አመለካከት ከያዝን እንዲሁም ጳውሎስ ወደ ይሁዲነት ለተለወጡት ሰዎች የነበረው ዓይነት ፍቅር ለእነዚህ ትሑት ሰዎች ካዳበርን ገና ብዙ መልካም ውጤቶች ማግኘታችንን ልንቀጥል እንችላለን። የእኛ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች “ደጋፊዎች” ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። ሁልጊዜ ሄደን ስናነጋግራቸው ደስ ይላቸዋል። አንዳንዶቹ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጥንተዋል እንዲሁም ስብሰባዎቻችን ላይ በተለይ ደግሞ በዓመታዊ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ የመንግሥቱ ምሥራች ሊሰበክበት የሚገባ እጅግ ሰፊ መስክ እንዳለ አይጠቁመንም?
16, 17. (ሀ) ምሥራቹን ለምን ዓይነት ሰዎች እናዳርሳለን? (ለ) ለተለያዩ ዓይነት ሰዎች በመስበክ የጳውሎስን ምሳሌ የምንከተለው እንዴት ነው?
16 ከዚህም በተጨማሪ በትውልድ አገራቸው አለዚያም ደግሞ ወደ ምዕራባውያን አገሮች መጥተው የምናገኛቸውን ከሕዝበ ክርስትና ውጭ ያሉትን ሰዎች እንዴት ልናያቸው ይገባል? ለሃይማኖት ጀርባቸውን ሰጥተው አምላክ የለሽ የሆኑትን ወይም ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሚመለከትስ ምን ለማለት ይቻላል? ከዚህም ሌላ ዛሬ የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮችን ባጨናነቁት የራስ አገዝ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ዘመናዊ ፍልስፍናና ስሙ የገነነውን የስነ ልቦና ምርምር እንደ ሃይማኖት አድርገው የያዙት ሰዎችስ? እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ሊመለሱ እንደማይችሉ በማሰብ ችላ ልንላቸው ይገባልን? የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ እንደዚያ አናደርግም።
17 ጳውሎስ በአቴና ሲሰብክ ከአድማጮቹ ጋር የፍልስፍና ሙግት አልገጠመም። ይሁንና ግን የሚያቀርባቸው ሐሳቦች ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ እንዲሆኑ በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግልጽና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አቅርቦላቸዋል። በተመሳሳይም ዛሬ የምንሰብክላቸው ሰዎች በያዟቸው ሃይማኖቶች ወይም ፍልስፍናዎች ረገድ ኤክስፐርቶች መሆን አያስፈልገንም። ይሁን እንጂ ምሥክርነታችን ውጤታማ እንዲሆን አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው በማስተካከል “ከሁሉ ጋር . . . እንደ እነርሱ” እንሆናለን። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ዘመኑን እየዋጃችሁ፣ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።”—ቆላስይስ 4:5, 6፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
18. ምን ኃላፊነት አለብን? ምን ነገርስ መርሳት የለብንም?
18 ልክ እንደ ኢየሱስና እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛም ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅር እናሳይ። በተለይ የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል ከልባችን እንጣጣር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚመለከት “ከዓለም አይደሉም” እንዳለ ፈጽሞ አትዘንጉ። (ዮሐንስ 17:16) ይህ አባባል ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።
ለክለሳ ያህል
◻ ኢየሱስ ለዓለም የነበረውን ሚዛናዊ አመለካከት ግለጽ።
◻ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡት ሰዎች የሰበከው እንዴት ነው?
◻ ጳውሎስ አምላክን የሚፈሩ ሰዎችንና የማያምኑትን ሰዎች ያነጋገረው እንዴት ነው?
◻ በስብከት ሥራችን “ከሁሉ ጋር . . . እንደ እነርሱ” መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ክርስቲያኖች ለጎረቤቶቻቸው ደግነትን የሚያንጸባርቅ ነገር በማድረግ ብዙውን ጊዜ ስሜታዊ ጥላቻን ማርገብ ይችላሉ