እምነት ለሥራ ያንቀሳቅሰናል!
“[የአብርሃም] እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?”—ያዕቆብ 2:22
1, 2. እምነት ካለን ምን እናደርጋለን?
ብዙ ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁንና እንዲሁ በቃል ብቻ የሚገለጽ እምነት እንደ አስከሬን በድን ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ የነበረው አብርሃም ‘ከሥራው ጋር አብሮ የሚያደርግ’ እምነት እንደነበረው ተናግሯል። (ያዕቆብ 2:17, 22) እንዲህ ያሉት ቃላት ለእኛ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?
2 እውነተኛ እምነት ካለን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንሰማቸውን ነገሮች አምነን በመቀበል ብቻ አንወሰንም። ንቁ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን እምነታችንን በተግባር እናሳያለን። አዎን፣ እምነት የአምላክን ቃል በሕይወታችን ሥራ ላይ እንድናውል የሚያነሳሳን ከመሆኑም ሌላ ለድርጊት ያንቀሳቅሰናል።
አድልዎና እምነት አብረው አይሄዱም
3, 4. እምነት ከሌሎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው?
3 በአምላክና በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ካለን አድሏዊነት አናሳይም። (ያዕቆብ 2:1-4) ያዕቆብ መልእክቱን ከጻፈላቸው መካከል አንዳንዶቹ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠበቀው ሁሉንም በእኩል ዓይን የማየት ባሕርይ አልነበራቸውም። (ሮሜ 2:11) በመሆኑም ያዕቆብ “በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ያለ አድልዎ ይዛችኋልን?” [NW] ሲል ጠይቋል። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያጌጠ ልብስ የለበሰ አንድ የማያምን ባለጠጋ ሰውና ‘ያደፈ ልብስ የለበሰ የማያምን ድሃ ሰው’ ወደ ስብሰባ ቢመጡ ለሁለቱም ጥሩ አቀባበል ሊደረግላቸው ሲገባ ለባለጠጋው ሰው የተለየ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ሀብታሞቹ “መልካም ሥፍራ” ይዘው እንዲቀመጡ ሲደረግ የማያምኑ ድሃ ሰዎች ግን እንዲቆሙ ወይም በሰው እግር አጠገብ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ይደረግ ነበር።
4 ይሖዋ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት ያዘጋጀው ለባለጠጎችም ለድሆችም ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:14) ለባለጠጎች የምናዳላ ከሆነ ‘እኛ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች እንድንሆን ስለ እኛ ድሃ ከሆነው’ ከክርስቶስ እምነት መራቃችን ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:9) በጥቅም ላይ የተመሠረተ መጥፎ ዝንባሌ በመያዝ ሰዎችን ማበላለጥ ፈጽሞ አይገባንም። አምላክ የማያዳላ ሆኖ ሳለ እኛ አድሏዊ ሆነን ብንገኝ ‘ክፉ አሳብ ያለን ዳኞች’ መሆናችን ነው። (ኢዮብ 34:19) አምላክን ለማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ አድሏዊነት እንድናሳይ ወይም ‘የራሳችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ሌሎችን እንድንክብ’ [NW] ለሚገጥመን ፈተና እጃችንን እንደማንሰጥ የተረጋገጠ ነው።—ይሁዳ 4, 16
5. አምላክ ‘በእምነት ባለጠጎች’ እንዲሆኑ የመረጠው እነማንን ነው? ብዙውን ጊዜ በቁሳዊ ነገሮች ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች ምን ያደርጋሉ?
5 ያዕቆብ እውነተኞቹ ባለጠጎች እነማን መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ለሁሉም ሰዎች ያለ አድልዎ ፍቅር ስለማሳየት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ያዕቆብ 2:5-9) አምላክ ‘በእምነት ባለጠጎችና የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የመረጠው ድሆችን ነው።’ ይህ የሆነበት ምክንያት ባብዛኛው ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት እነርሱ በመሆናቸው ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29) በጥቅሉ ሲታይ በቁሳዊ ነገሮች ባለጠጋ የሆኑ ሰዎች በዕዳ፣ በደሞዝ እንዲሁም በሌሎች ሕጋዊ ነገሮች ረገድ ሌሎችን ይጨቁናሉ። ክርስቶስን ይሳደባሉ፤ በስሙም ስለተጠራን ያሳድዱናል። ይሁን እንጂ ባልንጀራን መውደድን ማለትም ለሃብታሙም ለድሃውም እኩል ፍቅር ማሳየትን የሚጠይቀውን ‘የንጉሥ ሕግ’ ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ማቴዎስ 22:37-40) አምላክ እንዲህ እንድናደርግ ስለሚፈልግብን አድሏዊ መሆን ‘ኃጢአት’ ነው።
“ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል”
6. ሌሎችን በምሕረት ዓይን የማንመለከት ከሆነ ሕግ ተላላፊዎች የምንሆነው እንዴት ነው?
6 ምሕረት የለሽ አድሏዊነት የምናሳይ ከሆነ ሕግ ተላላፊዎች እንሆናለን። (ያዕቆብ 2:10-13) በዚህ ረገድ የተሳሳተ እርምጃ በመውሰዳችን በሁሉም የአምላክ ሕጎች ረገድ በደለኛ እንሆናለን። ምንዝር ያልፈጸሙ እስራኤላውያን ሌብነት ቢፈጽሙ የሙሴን ሕግ መተላለፋቸው ነበር። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ፍርድ የሚሰጠን ‘በነፃ ሰዎች ሕግ’ ነው፤ እነዚህ ነፃ ሰዎች ሕጉ በልባቸው ጽላት የተጻፈላቸውና በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት መንፈሳዊ እስራኤላውያን ናቸው።—ኤርምያስ 31:31-33
7. አድሏዊነት ማሳየታቸውን የገፉበት ሰዎች ከአምላክ ምሕረት እናገኛለን ብለው መጠበቅ የማይችሉት ለምንድን ነው?
7 እምነት አለን እያልን በአድሏዊነታችን ከገፋንበት ለአደጋ ተጋልጠናል። ፍቅርና ምሕረት የለሽ የሆኑ ሰዎች የሚሰጣቸውም ፍርድ ምሕረት የሌለበት ይሆናል። (ማቴዎስ 7:1, 2) ያዕቆብ “ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል” [የ1980 ትርጉም] ብሏል። ከሌሎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ሁሉ ምሕረት በማሳየት የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ አመራር የምንከተል ከሆነ በፍርድ ፊት ስንቀርብ አንወገዝም። ከዚህ ይልቅ ምሕረት እናገኝና ጥብቅ የሆነን ፍትሕ ወይም ከባድ ፍርድ በድል አድራጊነት ልንወጣ እንችላለን።
እምነት መልካም ሥራዎችን ያፈራል
8. እምነት አለኝ የሚል ሆኖም እምነቱን በሥራ የማይገልጽ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
8 እምነት፣ አፍቃሪዎችና መሐሪዎች እንድንሆን ከማስቻሉም ሌላ ሌሎች መልካም ሥራዎችን ያፈራል። (ያዕቆብ 2:14-26) እርግጥ ነው፣ በቃል ብቻ የሚገለጽ ከሥራ የተለየ እምነት ሊያድነን አይችልም። የሕጉን ትእዛዝ በመፈጸም በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም ማግኘት እንደማንችል እሙን ነው። (ሮሜ 4:2-5) ያዕቆብ እየተናገረ ያለው በእምነትና በፍቅር ተገፋፍተን ስለምንሠራቸው ሥራዎች እንጂ በሕጉ ውስጥ ስለሰፈሩ ሥራዎች አይደለም። እነዚህ ባሕርያት ካሉን ለተቸገረው የእምነት ወንድማችን የደግነት ምኞታችንን በመግለጽ ብቻ አንወሰንም። የታረዙ ወይም የተራቡ ወንድሞቻችንን ወይም እህቶቻችንን በቁሳዊ ነገር እንደግፋቸዋለን። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- ‘ለተቸገረው ወንድማችሁ “በደህና ሂድ፣ እሳት ሙቅ፣ ጥገብም” ብትሉት ለሰውነት ግን የሚያስፈልገውን ባትሰጡት ምን ይጠቅመዋል?’ ምንም አይጠቅመውም። (ኢዮብ 31:16-22) እንዲህ ያለው “እምነት” ሙት ነው!
9. እምነት እንዳለን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
9 ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በተወሰነ መጠን እንተባበር ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እምነት እንዳለን ሊያረጋግጡልን የሚችሉት በሙሉ ልብ የምናከናውናቸው ሥራዎች ብቻ ናቸው። የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ትተን አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ ማመናችን መልካም ነው። ይሁንና እምነት ማለት አንድ ነገር ትክክል መሆኑን መቀበል ማለት ብቻ አይደለም። “አጋንንት ደግሞ ያምናሉ” ጥፋት እንደሚጠብቃቸውም ስለሚያውቁ በፍርሃት “ይንቀጠቀጣሉ።” በእርግጥ እምነት ካለን፣ ይህ እምነት የምሥራቹን መስበክን እንዲሁም ለተቸገሩ የእምነት ወንድሞቻችን ምግብና ልብስ መስጠትን ለመሳሰሉት ሥራዎች ያንቀሳቅሰናል። ያዕቆብ “አንተ ከንቱ [በአምላክ ትክክለኛ እውቀት ያልተሞላህ] ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?” ሲል ጠይቋል። አዎን፣ እምነት በሥራ ሊደገፍ ይገባዋል።
10. አብርሃም ‘የሚያምኑ ሁሉ አባት ነው’ የተባለው ለምንድን ነው?
10 አምላካዊ አክብሮት የነበረው የዕብራውያን አባት አብርሃም እምነቱ ለሥራ አንቀሳቅሶታል። “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” የሆነው አብርሃም ‘ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ ጸድቋል።’ (ሮሜ 4:11, 12፤ ዘፍጥረት 22:1-14) አምላክ በእርሱ በኩል አንድ ዘር እንደሚያመጣ የገባውን የተስፋ ቃል ይስሐቅን ከሞት በማስነሣት ለመፈጸም ስለመቻሉ አብርሃም እምነት አንሶት ቢሆን ኖሮስ? አብርሃም ፈጽሞ ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ አይነሣም ነበር። (ዕብራውያን 11:19) አብርሃም የታዛዥነት ሥራ በመሥራቱ ምክንያት ‘እምነቱ ፍጹም’ ወይም ምሉዕ ሆኗል። በዚህ መንገድ “መጽሐፍም [ዘፍጥረት 15:6]:- አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ።” አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ አብርሃም ጻድቅ ስለመሆኑ አምላክ ቀደም ሲል የተናገረውን ቃል የሚያረጋግጥ ነበር። የእምነት ሥራ በመሥራት ለአምላክ ያለውን ፍቅር ከማሳየቱም ሌላ ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ለመባልም በቅቷል።
11. ረዓብ እምነት እንዳላት የሚያሳይ ምን ነገር አድርጋለች?
11 አብርሃም “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ” እንደሚጸድቅ አረጋግጧል። በኢያሪኮ የነበረችው የጋለሞታይቱ ረዓብ ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር። ‘[እስራኤላውያን] መልእክተኞቹን በእንግድነት ተቀብላ’ ከከነዓናውያን ጠላቶቻቸው ያመልጡ ዘንድ ‘በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ ጸድቃለች።’ እስራኤላውያኑን ሰላዮች ከማግኘቷም በፊት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ ተገንዝባ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላም የተናገረቻቸው ቃላትና የዝሙት አዳሪነት ሥራዋን መተዋ እምነት እንዳላት የሚያሳይ ነበር። (ኢያሱ 2:9-11፤ ዕብራውያን 11:31) ያዕቆብ በሥራ ስለተገለጸ እምነት ከሚያስረዳው ከዚህ ሁለተኛ ምሳሌው ቀጥሎ እንዲህ ብሏል:- “ከነፍስ [“ከመንፈስ፣” NW] የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” አንድ ሰው ሲሞት በውስጡ ሕያው የሚያደርግ ኃይል ወይም “መንፈስ” ስለማይኖረው አንዳች ነገር ማከናወን አይችልም። በቃል ብቻ የሚገለጽ እምነትም ልክ እንደሞተ ሰው አካል በድንና ከንቱ ነው። ይሁንና እውነተኛ እምነት ካለን ለአምላካዊ ሥራ ያነሳሳናል።
አንደበትህን ተቆጣጠር!
12. በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
12 መናገርና ማስተማርም እምነት እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጥንቃቄ ይጠይቃል። (ያዕቆብ 3:1-4) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ አስተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፣ በአምላክም ፊት ከፍተኛ ተጠያቂነት አለባቸው። በመሆኑም በትሕትና ውስጣዊ ዝንባሌዎቻቸውንና ብቃቶቻቸውን መመርመር ይገባቸዋል። እነዚህ ወንዶች እውቀትና ችሎታ ብቻ ሳይሆን ለአምላክና ለእምነት ወንድሞቻቸው ጥልቅ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል። (ሮሜ 12:3, 16፤ 1 ቆሮንቶስ 13:3, 4) ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክር በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። አንድ ሽማግሌ የተሳሳተ ትምህርት በመስጠቱ ምክንያት በሌሎች ላይ ችግር ቢደርስ አምላክ በክርስቶስ በኩል ከባድ ፍርድ ይፈርድበታል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ትሑቶች፣ በትጋት የሚያጠኑ፣ የአምላክን ቃል በታማኝነት የሚከተሉ ሊሆኑ ይገባል።
13. በቃል የምንሰናከለው ለምንድን ነው?
13 የተዋጣላቸውን አስተማሪዎች ጨምሮ ሁላችንም ብንሆን ባለፍጽምና ምክንያት “በብዙ ነገር እንሰናከላለን።” በቃል መሰናከል በተደጋጋሚ ከሚፈጸሙትና ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉት ድክመቶች መካከል አንዱ ነው። ያዕቆብ “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ብሏል። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም በሆነ መንገድ አንደበታችንን መቆጣጠር አንችልም። ይህን መቆጣጠር የምንችል ቢሆን ኖሮ ሌሎች የሰውነታችንን ብልቶች ሁሉ መቆጣጠር በቻልን ነበር። ልጓም ፈረሱን ወደፈለግንበት አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችለን ሲሆን በትንሽ መቅዘፊያ አማካኝነትም በዓውሎ ንፋስ የሚገፋውን ትልቅ መርከብ እንደ መሪው ፈቃድ ማሽከርከር ይቻላል።
14. ያዕቆብ አንደበታችንን ለመቆጣጠር ጥረት የማድረጉን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
14 አንደበትን መቆጣጠር ልባዊ ጥረት እንደሚጠይቅ ማንኛችንም አንክድም። (ያዕቆብ 3:5-12) ልጓም ከፈረስ እንዲሁም መቅዘፊያ ከመርከብ ጋር ሲወዳደሩ ትናንሽ ነገሮች ናቸው። እንዲሁም አንደበት ከሰው አካል ጋር ሲወዳደር ትንሽ ነገር ቢሆንም “በታላላቅ ነገሮች ይመካል።” ቅዱሳን ጽሑፎች ጉራ መንዛት አምላክን የሚያሳዝን ነገር መሆኑን በግልጽ ስለሚናገሩ ከዚህ ነገር ለመራቅ እንድንችል የእርሱን እርዳታ ለማግኘት እንጣር። (መዝሙር 12:3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 4:7) አንድን ጫካ በእሳት ለማያያዝ የሚያስፈልገው አንድ ብልጭታ ብቻ መሆኑን በማስታወስ የሚያስቆጣ ነገር ሲገጥመን አንደበታችንን እንግታ። ያዕቆብ እንደጠቆመው “አንደበት” ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትል የሚችል “እሳት ነው።” (ምሳሌ 18:21) እንዲያውም ያልተገራ አንደበት “ዓመፀኛ ዓለም ሆኗል”! የዚህ አምላካዊ አክብሮት የሌለው ዓለም ክፉ ባሕርያት በሙሉ ካልተገራ አንደበት ጋር የተያያዙ ናቸው። እንደ ስም ማጥፋትና የሐሰት ትምህርት ላሉት ጎጂ ነገሮችም ምክንያቱ ያልተገራ ምላስ ነው። (ዘሌዋውያን 19:16፤ 2 ጴጥሮስ 2:1) አንተ ምን ይመስልሃል? እምነታችን አንደበታችንን ለመቆጣጠር ጠንክረን እንድንሠራ ሊያነሳሳን አይገባምን?
15. ያልተገታ አንደበት ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?
15 ያልተገታ አንደበት ፈጽሞ ‘ሊያዋርደን’ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ደጋግመን ስንዋሽ ብንገኝ ውሸታም የሚል ስም እናተርፋለን። ይሁንና ያልተገታ አንደበት ‘የፍጥረትን ሩጫ የሚያቃጥለው’ እንዴት ነው? ሕይወትን ውስብስብ በማድረግ ነው። በአንድ ያልተገታ አንደበት ምክንያት መላው ጉባኤ ሊታመስ ይችላል። ያዕቆብ ስለ ሄኖም ሸለቆ ስለ “ገሃነም” ጠቅሷል። በአንድ ወቅት ልጆችን መሥዋዕት ለማድረግ ይጠቀሙበት የነበረው ይህ ቦታ የኢየሩሳሌም ቆሻሻ በእሳት የሚቃጠልበት ቆሻሻ መጣያ ሆኖ ነበር። (ኤርምያስ 7:31) በመሆኑም ገሃነም ጨርሶ መጥፋትን ያመለክታል። ያልተገራ ምላስ የገሃነምን አውዳሚ ኃይል የተዋሰ ያክል ነው። አንደበታችንን የማንገታ ከሆነ ራሳችን የጫርነው እሳት ለእኛው ሊተርፈን ይችላል። (ማቴዎስ 5:22) ሌላውን ሰው ነውረኛ ስድብ በመሳደባችን ምክንያት ከጉባኤ ልንወገድም እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 5:11-13
16. ያልተገራ አንደበት ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት በማሰብ ምን ማድረግ ይገባናል?
16 የአምላክን ቃል ስታነብ ሰዎች እንስሳትን እንዲገዙ ይሖዋ መደንገጉን ሳታስተውል አልቀረህም። (ዘፍጥረት 1:28) ሁሉንም ዓይነት ፍጥረታት ለማዳ ማድረግ ተችሏል። ለምሳሌ ያህል ጭልፊቶች ሥልጠና ተሰጥቷቸው ለአደን አገልግሎት ውለዋል። ያዕቆብ ‘በመሬት የሚሳቡ’ [የ1980 ትርጉም] ብሎ የጠቀሳቸው ነገሮች እባቦችን በማላመድ ትርዒት የሚያሳዩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን እባቦች ሊጨምር ይችላል። (መዝሙር 58:4, 5) የሰው ልጅ ዓሣ ነባሪዎችን ሳይቀር መቆጣጠር ይችላል፤ ነገር ግን ፍጽምና የሌለን በመሆናችን ምላሳችንን ሙሉ በሙሉ መግራት አንችልም። ያም ሆነ ይህ የዘለፋ፣ ሌሎችን የሚያቆስል ወይም ስማቸውን የሚያጎድፍ ነገር ከመናገር መቆጠብ ይገባናል። ያልተገራ አንደበት የሚገድል መርዝ የሞላበት አደገኛ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 3:13) ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ምላስ ተወስደው ከአምላክ መራቃቸው የሚያሳዝን ነበር። እንግዲያው ከሐዲዎች በቃልም ይሁን በጽሑፍ የሚያስተላልፉት መርዘኛ ሐሳብ እንዲወስደን ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም።—1 ጢሞቴዎስ 1:18-20፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3
17, 18. በያዕቆብ 3:9-12 ላይ አንደበትን በሁለት ዓይነት መንገድ መጠቀምን በሚመለከት ምን ተገልጿል? በዚህ ረገድስ ምን ማድረግ ይገባናል?
17 በአምላክ ላይ ያለን እምነት እንዲሁም እርሱን ለማስደሰት መፈለጋችን ከክህደት የሚጠብቀን ከመሆኑም በላይ ምላሳችንንም በሁለት ዓይነት መንገድ ከመጠቀም እንድንቆጠብ ይረዳናል። ያዕቆብ ምላሳቸውን በሁለት ዓይነት መንገድ ስለሚጠቀሙ ስለአንዳንዶች ሲናገር ‘በእርሱ አባታችንን ይሖዋን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ አምላክ ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን’ ብሏል። (ዘፍጥረት 1:26) ይሖዋ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ” የሚሰጥ በመሆኑ አባታችን ነው። (ሥራ 17:24, 25) ከዚህም ሌላ በመንፈሳዊ ሁኔታ የቅቡዓን ክርስቲያኖች አባት ነው። በአእምሮአዊና ሥነ ምግባራዊ ባሕርያት ረገድ ሁላችንም የተፈጠርነው “እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፤” ይህም ከእንስሳት የተለየን የሚያደርጉንን የፍቅር፣ የፍትሕና የጥበብ ባሕርያት ያካትታል። እንግዲያው በይሖዋ ላይ እምነት ካለን እንዴት ልንመላለስ ይገባናል?
18 ሰዎችን የምንረግም ከሆነ ክፉ እንዲደርስባቸው እንለምናለን ወይም እንመኛለን ማለት ነው። እኛ ሌሎች ሰዎች ክፉ እንዲደርስባቸው የመለመን መለኮታዊ ሥልጣን የተሰጠን ነቢያት አይደለንም። በመሆኑም ይህን የመሰለ ነገር ከአፋችን መውጣቱ በውስጣችን ጥላቻ እንዳለ የሚያሳይ ስለሆነ አምላክን መባረካችን ትርጉም አይኖረውም። ከአንድ አፍ “በረከትና መርገም” መውጣታቸው ተገቢ አይደለም። (ሉቃስ 6:27, 28፤ ሮሜ 12:14, 17-21፤ ይሁዳ 9) በስብሰባዎች ላይ ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር ስንዘምር ከቆየን በኋላ የእምነት ወንድሞቻችንን ብናማ ምንኛ ኃጢአት ይሆናል! ከአንድ ምንጭ የሚጣፍጥና የሚመር ውኃ ሊፈልቅ አይችልም። ‘በለስ ወይራን ወይም ወይን በለስን ልታፈራ እንደማትችል’ ሁሉ ጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊያመነጭ አይችልም። መልካም ነገር ልንናገር የሚገባን ሰዎች ዘወትር ሸካራ ቃላት የምንሰነዝር ከሆነ አንድ መንፈሳዊ ችግር አለ ማለት ነው። እንዲህ ያለ ልማድ ተጠናውቶን ከሆነ በዚህ መልክ መናገራችንን ለማቆም ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልይ።—መዝሙር 39:1
ከላይኛው ጥበብ ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላለሱ
19. በሰማያዊ ጥበብ የምንመራ መሆናችን ሌሎችን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
19 ሁላችንም የምንናገረውና የምናደርገው ነገር እምነት ካላቸው ሰዎች የሚጠበቅ ዓይነት እንዲሆን ጥበብ ያስፈልገናል። (ያዕቆብ 3:13-18) ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ካለን ሰማያዊውን ጥበብ ማለትም እውቀትን በትክክል የመጠቀም ችሎታ ይሰጠናል። (ምሳሌ 9:10፤ ዕብራውያን 5:14) የአምላክ ቃል እንዴት ‘የጥበብ የዋህነት ማሳየት’ እንደምንችል ያስተምረናል። የዋሆች ከሆንን ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን እንጥራለን። (1 ቆሮንቶስ 8:1, 2) ከእምነት መሰሎቻቸው ሁሉ የላቁ አስተማሪዎች እንደሆኑ በማሰብ የሚኩራሩ ካሉ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግን የሚያወግዘውን ‘ክርስቲያናዊ እውነት እየዋሹ’ ነው ማለት ነው። (ገላትያ 5:26) ‘ጥበባቸው’ “የምድር” ማለትም ከአምላክ የራቀውን ኃጢአተኛ የሰው ዘር ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ነው። የሥጋዊ ዝንባሌ ውጤት በመሆኑ “የሥጋ” [“የእንስሳት፣” NW] ነው። “የአጋንንትም” ነው፤ ምክንያቱም ክፉ መናፍስት ኩሩዎች ናቸው! (1 ጢሞቴዎስ 3:6) እንግዲያው እንደ ስም ማጥፋትና አድሏዊነት ያሉት ‘ክፉ ነገሮች’ እንዲያቆጠቁጡ በር የሚከፍት ምንም ነገር ላለማድረግ በጥበብና በትሕትና እንመላለስ።
20. ሰማያዊውን ጥበብ እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
20 ‘ላይኛው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹህ ነው፤’ በመሆኑም በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ያደርገናል። (2 ቆሮንቶስ 7:11) “ታራቂ” [“ሰላም ወዳድ፣” የ1980 ትርጉም] ስለሆነ ሰላምን ለማስፈን እንድንጥር ይገፋፋናል። (ዕብራውያን 12:14) ሰማያዊው ጥበብ ቀኖናዊና አስቸጋሪ ሳይሆን “ገር” ሰዎች እንድንሆን ያደርገናል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ላይኛው ጥበብ “እሺ ባይ” በመሆኑ መለኮታዊውን ትምህርት መታዘዝንና ከይሖዋ ድርጅት ጋር መተባበርን ያበረታታል። (ሮሜ 6:17) እንዲሁም ላይኛው ጥበብ መሐሪዎችና ርኅሩኆች እንድንሆን ይረዳናል። (ይሁዳ 22, 23) “በጎ ፍሬ” የሞላበት በመሆኑ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን እንዲሁም ከበጎነት፣ ከጽድቅና ከእውነት ጋር የሚስማማ ሥራ መሥራትን ያበረታታል። (ኤፌሶን 5:9) ሰላም እንዲሰፍን የምንጥር በመሆናችን ደግሞ በሰላማዊ ሁኔታ ሥር የሚያብበውን ‘የጽድቅ ፍሬ’ እናፈራለን።
21. በያዕቆብ 2:1 እስከ 3:18 ላይ በተገለጸው ሐሳብ መሠረት በአምላክ ላይ ያለን እምነት የትኞቹን ሥራዎች እንድንሠራ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል?
21 እንግዲያው እምነት ለሥራ እንደሚያንቀሳቅሰን ግልጽ ነው። የማናዳላ፣ መሐሪዎችና በመልካም ሥራ የምንተጋ እንድንሆን ያስችለናል። እምነት አንደበታችንን እንድንቆጣጠርና ከሰማያዊው ጥበብ ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንመላለስ ይረዳናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ደብዳቤ የምናገኘው ትምህርት በዚህ ብቻ አያበቃም። ያዕቆብ በይሖዋ ላይ እምነት ካላቸው ሰዎች የሚጠበቀውን እንድናደርግ ሊረዳን የሚችል ሌላም ምክር ሰጥቷል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አድሏዊነት ማሳየት ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?
◻ እምነትና ሥራ የሚዛመዱት እንዴት ነው?
◻ አንደበትን መቆጣጠር ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ሰማያዊው ጥበብ ምን ይመስላል?