ስለ ይሖዋ ድርጅት ትክክለኛ ግንዛቤ አላችሁን?
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት።”—ኢሳይያስ 66:1
1, 2. (ሀ) ስለ ይሖዋ ድርጅት የትኞቹን ተጨባጭ ማስረጃዎች መጥቀስ ትችላለህ? (ለ) ይሖዋ የሚኖረው የት ነው?
ይሖዋ ድርጅት እንዳለው ታምናለህ? ከሆነ እንድታምን ያደረገህ ነገር ምንድን ነው? ምናልባትም እንደሚከተለው ብለህ ትመልስ ይሆናል:- ‘የመንግሥት አዳራሽ አለን። የሽማግሌዎች አካል ያለውና በሚገባ የተደራጀ ጉባኤ አለን። አግባብ ባለው መንገድ የተሾመ የወረዳ የበላይ ተመልካች በየጊዜው ይጎበኘናል። በሚገባ የተደራጁ የወረዳና የልዩ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎች እናደርጋለን። በአገራችን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ አለ። እነዚህና ሌሎቹም ነገሮች ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት እንዳለው የሚያረጋግጡ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው።’
2 እነዚህ ነገሮች አንድ ድርጅት እንዳለ ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ ግንዛቤያችን በምድር ባለው ነገር ላይ ብቻ የተወሰነ ከሆነ ስለ ይሖዋ ድርጅት የተሟላ ማስተዋል የለንም ማለት ነው። ይሖዋ ለኢሳይያስ የነገረው ምድር የእግሩ መቀመጫ ብቻ እንደሆነች ነው፤ ዙፋኑ ግን ሰማይ ነው። (ኢሳይያስ 66:1) ይሖዋ እዚህ ላይ የተናገረው ስለየትኛው “ሰማይ” ነው? በዙሪያችን ስላለው ከባቢ አየር ነው? ስለ ጠፈር ነው? ወይስ ስለሌላ ዓይነት ሕይወት? ኢሳይያስ ስለ ይሖዋ ‘ቅዱስና የክብር ማደሪያ’ ሲናገር መዝሙራዊው ደግሞ ሰማይ የአምላክ ‘ማደሪያ ቦታ’ መሆኑን ገልጿል። እንግዲያው በኢሳይያስ 66:1 ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው “ሰማይ” ይሖዋ ከሁሉ የላቀውን ወይም የመጨረሻውን ከፍተኛ ቦታ የያዘበትን መንፈሳዊ ዓለም የሚያመለክት ነው።—ኢሳይያስ 63:15፤ መዝሙር 33:13, 14
3. ጥርጣሬዎችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
3 እንግዲያው ስለ ይሖዋ ድርጅት ለመረዳትና ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ከፈለግን የሰማዩን ነገር መመልከት ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ለአንዳንዶች የሚከብዳቸው ነገር ይኼ ነው። የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት በዓይን የማይታይ በመሆኑ በእርግጥ መኖሩን እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዲያውም አንዳንዶች ‘እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን’ በሚል ጥርጣሬ ይዋጡ ይሆናል። ታዲያ እምነት ጥርጣሬን ሊያሸንፍ የሚችለው እንዴት ነው? ቁልፍ የሆኑት ሁለት መንገዶች ጥልቀት ባለው መንገድ የአምላክን ቃል በግል ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ በመገኘት ተሳትፎ ማድረግ ናቸው። በዚህ መንገድ የእውነት ብርሃን ያደረብንን ጥርጣሬ ለማሸነፍ ያስችለናል። ተመሳሳይ ጥርጣሬ አድሮባቸው የነበሩ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም ነበሩ። እስቲ እስራኤል ከሶርያ ንጉሥ ጥቃት በተሰነዘረባት ጊዜ የኤልሳዕ ሎሌ ምን እንደገጠመው እንመልከት።—ከዮሐንስ 20:24-29 ጋር አወዳድር፤ ያዕቆብ 1:5-8
የሰማይን ሠራዊት ያየው ሰው
4, 5. (ሀ) የኤልሳዕ ሎሌ የነበረበት ችግር ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለኤልሳዕ ጸሎት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
4 የሶርያ ንጉሥ ኤልሳዕን ለመያዝ በሌሊት ወደ ዶታይን ግዙፍ ሠራዊት ላከ። የኤልሳዕ ሎሌ ንፋስ ለመቀበል ሳይሆን አይቀርም በማለዳ ተነስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኘው ቤታቸው አናት ላይ በወጣ ጊዜ አንድ የሚያስደነግጥ ነገር ተመለከተ! በፈረሶችና በጦር ሠረገላዎች የታጀበው የሶሪያውያን ሠራዊት የአምላክን ነቢይ ለመያዝ እየተጠባበቀ ከተማዋን ከብቧታል። ሎሌውም “ጌታዬ፣ ሆይ ወዮ! ምን እናደርጋለን?” ሲል ወደ ኤልሳዕ ጮኸ። ኤልሳዕ ምንም ሳይረበሽ ተማምኖ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” ሲል መለሰለት። ሎሌው ‘የት አሉ? ለእኔ አይታዩኝም’ ብሎ ሳይገረም አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ እኛም ሰማያዊውን ሠራዊት በማስተዋል ዓይናችን የማየት ተመሳሳይ ችግር ይገጥመን ይሆናል።—2 ነገሥት 6:8-16፤ ኤፌሶን 1:18
5 ኤልሳዕ የሎሌው ዓይን እንዲከፈት ጸለየ። ከዚያስ ምን ሆነ? “እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይን ገለጠ፣ አየም፤ እነሆም፣ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።” (2 ነገሥት 6:17) አዎን፣ የአምላክን አገልጋይ ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ ያለውን የሰማይ ሠራዊት ማለትም መላእክታዊ ኃይል ተመለከተ። አሁን ኤልሳዕ ለምን እንደዚያ ዓይነት ትምክህት እንዳሳየ ሎሌው ሊገባው ይችላል።
6. ስለ ይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ጥልቅ ማስተዋል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
6 የኤልሳዕ አገልጋይ እንደገጠመው እኛስ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ማስተዋል ይሳነናልን? ማየት የሚቀናን የነገሮቹን ሰብዓዊ ገጽታ ብቻ ማለትም በእኛ ወይም በአንዳንድ አገሮች እንዳለው በሥራችን ላይ ስጋት የሚፈጥሩትን ሁኔታዎች ብቻ ነውን? ከሆነስ የእውቀት ብርሃናችንን የሚጨምርልን ልዩ ነገር ይገለጥልናል ብለን መጠበቅ እንችላለን? የለም እንዲህ ያለ ነገር አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም እኛ የኤልሳዕ ሎሌ ያልነበረውን ነገር አግኝተናል። ብዙ ራእይዎችን ያካተተውንና ምሉዕ መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን አግኝተናል። ይህ መጽሐፍ ስለ ሰማያዊው ድርጅት ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል። ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ቃል አስተሳሰባችንና አኗኗራችን ለማቅናት እንደ መመሪያ ሆነው የሚያገለግሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይሰጠናል። ይሁን እንጂ ማስተዋል ለማግኘትና ለይሖዋ ዝግጅት አድናቆት ለመኮትኮት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህንንም ማድረግ የምንችለው ጸሎትና ማሰላሰል የታከለበት የግል ጥናት በማድረግ ነው።—ሮሜ 12:12፤ ፊልጵስዩስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15-17
ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት የሚደረግ ጥናት
7. (ሀ) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን በግል በማጥናት ረገድ ምን ችግር ይኖርባቸው ይሆናል? (ለ) ለግል ጥናት የምናደርገው ጥረት አያስቆጭም የምንለው ለምንድን ነው?
7 ተማሪዎች እያሉ ማጥናት ይጠሉ ለነበሩ ወይም እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ላልነበራቸው ብዙ ሰዎች የግል ጥናት ማድረግ ሁልጊዜ አስደሳች ይሆንላቸዋል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ በማስተዋል ዓይናችን ስለ ይሖዋ ድርጅት ለመረዳትና ጥሩ ግንዛቤ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ የማጥናት ፍላጎታችንን መኮትኮት ይገባናል። ምንም ዝግጅት ሳይደረግ ጥሩ ምግብ ማግኘት ትችላለህን? አንድ ጣፋጭ ምግብ ማዘጋጀት ብዙ ድካም እንደሚጠይቅ ማንኛውም የወጥ ቤት ሠራተኛ ሊነግርህ ይችላል። ይሁንና ምግቡ በግማሽ ሰዓት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተበልቶ ሊያልቅ ይችላል። በአንጻሩ ግን ከግል ጥናት የሚገኙት ጥቅሞች በሕይወታችን በሙሉ ሊያገለግሉን ይችላሉ። ምን ያህል ዕድገት እያደረግን እንዳለን ስንመለከት የግል ጥናት የሚወደድ ነገር ሊሆንልን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለራሳችንና ለትምህርታችን ሁልጊዜ መጠንቀቅ እንደሚገባንና ለሕዝብ በማንበብ እንድንተጋ መናገሩ ተገቢ ነበር። የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ቢኖርብንም ዘላለማዊ ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 4:13-16
8. የምሳሌ መጽሐፍ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል?
8 አንድ በጥንት ዘመን የኖረ ጠቢብ ሰው ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”—ምሳሌ 2:1-5
9. (ሀ) ወርቅ ያለው ዋጋ ‘የአምላክን እውቀት’ ከማግኘት ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? (ለ) ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የሚያስፈልጉን መገልገያ መሣሪያዎች ምንድን ናቸው?
9 ኃላፊነቱ የወደቀው በማን ላይ እንደሆነ አስተዋልክ? ‘አንተ’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ሐሳብ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። እንዲሁም ‘እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት’ የሚለውን ሐረግ ልብ በል። በቦሊቪያ፣ በሜክሲኮ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም አገሮች ለበርካታ መቶ ዘመናት ብርና ወርቅ ቆፍረው ሲያወጡ የኖሩትን የማዕድን ሠራተኞች አስብ። ውድ የሆኑ ማዕድኖች የሚያገኙባቸውን ዓለቶች ያለመታከት በአካፋና ዶማ ሲቆፍሩ ኖረዋል። ለወርቅ ከፍተኛ ግምት ከመስጠታቸው የተነሣ በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የማዕድን ማውጫ ቦታ ወርቅ ለማግኘት ብቻ ወደታች ጥልቀታቸው እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር የሚደርስና ወደጎን 591 ኪሎ ሜትር ርቀት ያላቸውን ዋሻዎች ቆፍረዋል። ይሁንና ወርቅ ሊበላ ወይስ ሊጠጣ ይችላልን? ጭልጥ ያለ በረሃ ላይ በረሃብ ወይም በጥም ልትሞት ብትደርስ ወርቅ ሕይወትህን ሊያቆይልህ ይችላልን? በጭራሽ። የወርቅ ዋጋ ሰዎች ራሳቸው የተመኑት ነገር ሲሆን የዓለም አቀፉ ገበያ በዋዠቀ ቁጥር ዋጋው ከዕለት ወደ ዕለት ይቀያየራል። የሆነ ሆኖ ሰዎች ሕይወታቸውን ሳይቀር ሠውተውለታል። ታዲያ መንፈሳዊውን ወርቅ ማለትም ‘የአምላክን እውቀት’ ለማግኘት ምን ያህል ጥረት ማድረግ ይገባል? እስቲ አስበው የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ስለሆነው አምላክ፣ ስለ ድርጅቱና ስለ ዓላማው ማወቅ ትችላለህ። በዚህ ረገድ መንፈሳዊ ዶማና አካፋ ልንጠቀም እንችላለን። እነዚህ የይሖዋን ቃል ለመቆፈርና ትርጉሙን ለማስተዋል የሚያስችሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ናቸው።—ኢዮብ 28:12-19
ማስተዋል ለማግኘት መቆፈር
10. ዳንኤል በራእይ የተመለከተው ነገር ምን ነበር?
10 እስቲ ስለ ይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት አንዳንድ እውቀት ለማግኘት እንድንችል ትንሽ መንፈሳዊ ቁፋሮ እናካሂድ። ቁልፍ የሆነውን ነጥብ ለማስተዋል እንድንችል ዳንኤል በዘመናት የሸመገለው በዙፋን ላይ ተቀምጦ የተመለከተበትን ራእይ እንውሰድ። ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፣ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፣ የራሱም ጠጉር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበር። ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበር። መንኮራኩሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፣ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር። ፍርድም ሆነ፣ መጻሕፍትም ተገለጡ።” (ዳንኤል 7:9, 10) ይሖዋን የሚያገለግሉት እነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ ፍጥረታት እነማን ናቸው? እንደ “ዶማና” “አካፋ” የሚያገለግሉት በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ኅዳግ ላይ ያሉት ተጨማሪ መግለጫዎች እንደ መዝሙር 68:17 እና ዕብራውያን 1:14 ወዳሉት ጥቅሶች ይመሩናል። አዎን ይሖዋን የሚያገለግሉት እነዚህ ፍጥረታት መላእክት ናቸው!
11. ዳንኤል ያየው ራእይ ኤልሳዕ የተናገራቸውን ቃላት እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?
11 ዳንኤል በአምላክ መመሪያ ሥር ያሉትን የታመኑ መላእክት በሙሉ እንዳየ አይገልጽም። ከእነርሱ ሌላ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ይኖሩ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ኤልሳዕ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉ” ሊል የቻለው ለምን እንደሆነ ሊገባን ይችላል። የሶርያው ንጉሥ ያሰለፈው ሠራዊት በከሃዲዎቹ መላእክት ማለትም በአጋንንት የሚደገፍ ቢሆንም የይሖዋ ሰማያዊ ሠራዊት በቁጥር እጅግ የሚበልጥ ነው!—መዝሙር 34:7፤ 91:11
12. ስለ መላእክት ብዙ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
12 ምናልባት ስለ እነዚህ መላእክት ተጨማሪ ነገር ማለትም ይሖዋን በማገልገል ስለሚጫወቱት ሚና ማወቅ ትፈልግ ይሆናል። መልአክ የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ “መልእክተኛ” ማለትም ስለሆነ ሥራቸው መላላክ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ሥራቸው ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ሌላ ምን ነገር እንደሚያከናውኑ ለማወቅ ከፈለግህ ግን መቆፈር ይኖርብሃል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ካለህ “መላእክት” [Angels] የሚለውን ርዕስ አውጥተህ ልታጠና ወይም ደግሞ ስለ መላእክት የሚያብራሩ የቆዩ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችን ልትመረምር ትችላለህ። በሰማይ ስላሉት ስለ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች በምታገኘው እውቀት ትገረማለህ። እንዲሁም ምን ያህል እገዛ እንደሚያደርጉ ትገነዘባለህ። (ራእይ 14:6, 7) ይሁን እንጂ በአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ውስጥ ለየት ላለ ዓላማ የተሰለፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት አሉ።
ኢሳይያስ የተመለከተው ነገር
13, 14. ኢሳይያስ በራእይ ምን ነገር ተመልክቷል? ይህስ የነካው እንዴት ነው?
13 እስቲ አሁን ደግሞ ኢሳይያስ ያየውን ራእይ በሚመለከት ጥቂት ቁፈራ እናድርግ። ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 7 ስታነብ እጅግ ትገረማለህ። ይሖዋ “በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ” “ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው” እንዳየ ኢሳይያስ ተናግሯል። የይሖዋን ክብር እያወጁና ቅድስናውን ከፍ ከፍ አድርገው እየተናገሩ ነበር። ይህን ዘገባ ማንበብህ ራሱ ሊነካህ ይገባል። የኢሳይያስ ምላሽ ምን ነበር? “እኔም:- ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፣ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝቦች መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊት ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቼአለሁና [ሲኦል እንደገባ ሆኛለሁና] ወዮልኝ! አልሁ።” ኢሳይያስ ባየው ራእይ በጥልቅ ተነክቶ ነበር! አንተስ?
14 ታዲያ ኢሳይያስ እንዲህ ባለው አስደናቂ ራእይ ፊት ሊቆም የቻለው እንዴት ነው? ከሱራፌልም አንዱ እንደደረሰለትና “በደልህም ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ” እንዳለው ገልጿል። (ኢሳይያስ 6:7) ኢሳይያስ በአምላክ ምሕረት ላይ ትምክህት በማሳደር ይሖዋ የሚናገረውን በትኩረት ማዳመጥ ይችል ነበር። ታዲያ አሁን ስለ እነዚህ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት ተጨማሪ እውቀት ማግኘት አትፈልግም? እንግዲያው ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ቆፍር። ልትጠቀምባቸው ከምትችላቸው መሣሪያዎች አንዱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ሲሆን ተጨማሪ ማብራሪያ የያዙ ብዙ ጽሑፎችን ይጠቁምሃል።
ሕዝቅኤል ምን ነገር ተመልክቷል?
15. የሕዝቅኤል ራእይ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚጠቁመው ነገር ምንድን ነው?
15 አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ዓይነት መንፈሳዊ ፍጥረት ዘወር እንበል። ሕዝቅኤል ገና በባቢሎን ምርኮኛ ሆኖ ሳለ አንድ ቀስቃሽ ራእይ የማየት መብት አግኝቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስህን ሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 አውጣና የመጀመሪያዎቹን ሦስት ቁጥሮች ተመልከት። ዘገባው የሚጀምረው እንዴት ነው? ‘ከዕለታት አንድ ቀን በሩቅ አገር የሚኖር . . .’ ብሎ ነው? የለም፤ ይህ አፈታሪካዊ መቼት ያለው ተረት አይደለም። ቁጥር 1 እንዲህ ይላል:- “በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፣ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።” ከዚህ ቁጥር ምን ነገር አስተዋልክ? ትክክለኛውን ጊዜና ቦታ ለይቶ ይጠቅሳል። በዝርዝር የተጠቀሰው ሁኔታ ጊዜው ንጉሥ ዮአኪን ከታሰረ ከአምስት ዓመታት በኋላ ማለትም 613 ከዘአበ መሆኑን ያመለክታል።
16. ሕዝቅኤል ምን ነገር ተመልክቷል?
16 የይሖዋ እጅ በሕዝቅኤል ላይ ሆነ። እርሱም ይሖዋ ዓይኖች የሞሉባቸው በጣም ትላልቅ መንኮራኩሮች ባሉት ሰፊ ሰማያዊ ሠረገላ ላይ በዙፋኑ ተቀምጦ የሚያሳይ አስፈሪ ራእይ ተመለከተ። ይበልጥ ትኩረታችንን የሚስበው በእያንዳንዱ መንኮራኩር አጠገብ ቆመው ስለነበሩት አራት እንስሳት የተገለጸው ነገር ነው። “መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፣ ሰውም ይመስሉ ነበር። ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት፣ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። . . . የፊታቸውም አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፣ ለአራቱም በስተቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፣ በስተግራቸውም እንደ ላም [“በሬ” የ1980 ትርጉም ] ፊት ነበራቸው፣ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።”—ሕዝቅኤል 1:5, 6, 10
17. የኪሩቦቹ አራት ፊቶች የሚያመለክቱት ምንድን ነው?
17 እነዚህ አራት ሕያዋን ፍጥረታት ምንድን ናቸው? ሕዝቅኤል ራሱ ኪሩቤል እንደሆኑ ይነግረናል። (ሕዝቅኤል 10:1-3, 14) አራት ፊት ያላቸውስ ለምንድን ነው? የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን አራት ታላላቅ ባሕርያት ለመወከል ነው። የንስሩ ፊት አርቆ አሳቢነት የሚንጸባረቅበትን ጥበብ ለማመልከት የቆመ ነው። (ኢዮብ 39:27-29) የበሬውስ ፊት ምን ያመለክታል? አንድ ተዋጊ በሬ በአንገቱና በትከሻው ላይ ከፍተኛ ኃይል ስላለው አንድን ፈረስ ከነጋላቢው ወደ አየር ሊያስፈነጥራቸው ይችላል። በሬ በእርግጥም ገደብ የሌለውን የይሖዋን ኃይል የሚያመለክት ምሳሌ ነው። አንበሳው በድፍረት የሚሰጥን ፍትሕ ለማመልከት አገልግሏል። በመጨረሻም የሰው ፊት የሚመስለው ገጽታ የአምላክን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነው ቢባል ተገቢ ነው። ምክንያቱም በማስተዋል ችሎታው ተጠቅሞ ይህን ባሕርይ ለማንጸባረቅ የሚችለው ብቸኛ ምድራዊ ፍጥረት ሰው ነው።—ማቴዎስ 22:37, 39፤ 1 ዮሐንስ 4:8
18. ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ሰማያዊው ድርጅት ያለንን ግንዛቤ ያሳደገልን እንዴት ነው?
18 ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ እንድንረዳ የሚያስችሉን ሌሎች ራእይዎችም አሉ። ከእነዚህም መካከል በመጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የዮሐንስ ራእይዎች ይገኙበታል። እርሱም እንደ ሕዝቅኤል ይሖዋ በክብራማ ዙፋን ላይ ተቀምጦና በኪሩቤል ተከቦ ተመልክቷል። ኪሩቦቹ ምን ያደርጋሉ? “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ” በማለት በኢሳይያስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን የሱራፌሎች አዋጅ ያስተጋባሉ። (ራእይ 4:6-8) ከዚህም በተጨማሪ ዮሐንስ ከዙፋኑ አጠገብ አንድ በግ ተመልክቷል። ይህ ማንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል? የአምላክ በግ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።—ራእይ 5:13, 14
19. በዚህ ጥናት አማካኝነት ስለ ይሖዋ ድርጅት ምን ነገር ተረድተሃል?
19 እንግዲያው ከእነዚህ ራእይዎች የተገነዘብነው ነገር ምንድን ነው? ሰማያዊው ድርጅት በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን ይሖዋ አምላክን ማዕከል ያደረገ መሆኑንና ከእርሱም ጋር ቃል ወይም ሎጎስ የሆነው በጉ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለ ተመልክተናል። ከዚያም ሱራፌሎችንና ኪሩቤልን ያቀፈ የመላእክት ሰማያዊ ሠራዊት እንዳለ ተመልክተናል። እነዚህ የይሖዋን ዓላማ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሰው ግዙፍና አንድነት ያለው ድርጅት አካል ናቸው። ከዓላማዎቹ አንዱ ደግሞ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ መስበክ ነው።—ማርቆስ 13:10፤ ዮሐንስ 1:1-3፤ ራእይ 14:6, 7
20. በሚቀጥለው ርዕስ የትኛው ጥያቄ መልስ ያገኛል?
20 በመጨረሻም ወደ ምድር መለስ ስንል የሉዓላዊውን ጌታ ፈቃድ እንዴት መፈጸም እንደሚችሉ በየመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ የሚማሩትን የይሖዋ ምሥክሮች እናገኛለን። በእርግጥም ከሰይጣንና የእውነት ጠላት ከሆኑት ወገኖች ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት እንደሚበልጡ መገንዘብ ችለናል። ሰማያዊው ድርጅት ከመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ጋር ያለው ተዛምዶ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ገና አሁንም መልስ ማግኘት ይኖርበታል። በሚቀጥለው ርዕስ ይህም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ስለ ይሖዋ ድርጅት ጥሩ ግንዛቤ እንድናገኝ ምን ነገር መረዳት ይኖርብናል?
◻ የኤልሳዕ ሎሌ ምን ዓይነት ሁኔታ ገጥሞት ነበር? ነቢዩ ያበረታታውስ እንዴት ነው?
◻ ለግል ጥናት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን ዓይነት መሆን አለበት?
◻ ዳንኤል፣ ኢሳይያስና ሕዝቅኤል ስለ ሰማያዊው ድርጅት ዝርዝር ሁኔታዎችን የገለጹት እንዴት ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግል ጥናት የሚያስገኘው ጥቅም በደንብ የተዘጋጀ ምግብ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች እጅግ የላቀ ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰማይ ሠራዊት መታየታቸው ይሖዋ ለኤልሳዕ ጸሎት የሰጠው መልስ ነበር