የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
አንድ ሳምራዊ መልካም ባልንጀራ ሆኖ ተገኘ
በኢየሱስ ዘመን በአይሁዳውያንና በአሕዛብ መካከል ግልጽ ጥላቻ ነበር። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ የአይሁዳውያን ሚሽና እስራኤላውያን ሴቶች አይሁዳዊ ያልሆኑ ሴቶችን በአዋላጅነት እንዳይረዱ የሚከለክል ሕግ አውጥቶ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ሌላ ተጨማሪ አሕዛብ ወደ ዓለም እንዲመጣ መርዳት ስለሚሆን ነው።—አቦዳህ ዛራህ 2:1
ከአሕዛብ ይልቅ ሳምራውያን በሃይማኖትም ሆነ በዘር ከአይሁዳውያን ጋር ይበልጥ ይዛመዱ ነበር። ሆኖም እነሱም ጭምር እንደ ባዕድ ይቆጠሩ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ “አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም” ሲል ጽፏል። (ዮሐንስ 4:9) ታልሙድ “አንድ ሳምራዊ ለአንድ አይሁዳዊ የሚሰጠው ቁራሽ ዳቦ ከአሳማ ሥጋ ይበልጥ የረከሰ ነው” ሲል ያስተምራል። እንዲያውም አንዳንድ አይሁዳውያን “ሳምራዊ” የሚለውን ቃል ለማላገጫና ለማዋረጃ ይጠቀሙበት ነበር።—ዮሐንስ 8:48
ከዚህ ሁኔታ አንፃር ኢየሱስ የአይሁድን ሕግ ጠንቅቆ ያውቅ ለነበረ ሰው የተናገራቸው ቃላት ከፍተኛ ትምህርት ያዘሉ ነበሩ። ሰውየው ወደ ኢየሱስ ቀረበና እንዲህ ሲል ጠየቀው:- “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ኢየሱስ ጥያቄውን ሲመልስ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ’ እና ‘ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ በማለት ወደሚያዘው የሙሴ ሕግ ላይ እንዲያተኩር አደረገ። ከዚህ በመቀጠል ሕግ አዋቂው “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። (ሉቃስ 10:25-29፤ ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 6:5) እንደ ፈሪሳውያን አባባል ከሆነ “ባልንጀራ” የሚለው ቃል የሚያገለግለው የአይሁዳውያንን ወግ ለሚጠብቁ ብቻ እንጂ ለአሕዛብና ለሳምራውያን አልነበረም። ይህ የሕግ አዋቂ ኢየሱስ ይህንን አመለካከት ይደግፋል ብሎ አስቦ ከነበረ ጨርሶ ያልጠበቀው መልስ ሊያገኝ ነው።
ሩኅሩኅ ሳምራዊ
ኢየሱስ የሰውየውን ጥያቄ የመለሰው አንድ ምሳሌ በመናገር ነበር።a እንዲህ አለ:- “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ።” በኢየሩሳሌምና በኢያሪኮ መካከል ያለው ርቀት ወደ 23 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ነበር። እነዚህን ሁለት ከተማዎች የሚያገናኘው መንገድ ጠመዝማዛ ከመሆኑም በላይ ትላልቅ ሾጣጣ አለቶች ነበሩት፤ ይህ ደግሞ ለመደበቅ፣ ለመዝረፍና ለማምለጥ ለሌቦች በጣም ምቹ ነው። በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው መንገደኛ በመጨረሻ ላይ “በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።”—ሉቃስ 10:30
ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ።” (ሉቃስ 10:31, 32) ካህናትና ሌዋውያን ባልንጀራን ስለመውደድ የሚናገረውን ሕግ ጨምሮ የሕጉ አስተማሪዎች ነበሩ። (ዘሌዋውያን 10:8-11፤ ዘዳግም 33:1, 10) በእርግጥም ከማንኛውም ሰው ይበልጥ የተጎዳውን መንገደኛ ለመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይገባ ነበር።
ኢየሱስ ምሳሌውን በመቀጠል “አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ” አለ። ስለ አንድ ሳምራዊ መጠቀሱ የሕግ አዋቂው ጉጉት እንዲጨምር ሳያደርግ እንደማይቀር እሙን ነው። ኢየሱስ ስለዚህ ዘር ተስፋፍቶ የነበረውን አሉታዊ አመለካከት መደገፉን ይገልጽ ይሆን? ከዚህ በተቃራኒ ሳምራዊው አደጋ የደረሰበትን መንገደኛ ሲመለከት “አዘነለት።” ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፣ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም።b በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና:- ጠብቀው፣ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው።”—ሉቃስ 10:33-35
እዚህ ላይ ኢየሱስ ሰውየውን እንዲህ ሲል ጠየቀው:- “እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” ሕግ አዋቂው መልሱን ቢያውቀውም “ሳምራዊው” ለማለት ፈቃደኛ የሆነ አይመስልም። ከዚህ ይልቅ “ምሕረት ያደረገለት” ሲል መለሰ። ከዚያም በመቀጠል ኢየሱስ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” አለው።—ሉቃስ 10:36, 37
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ለኢየሱስ ጥያቄ ያቀረበለት ሰው ጥረቱ ‘ራሱን ለማጽደቅ’ ነበር። (ሉቃስ 10:29) ምናልባትም የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ ስለሚከተል ኢየሱስ ያወድሰኛል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ተመፃዳቂ ግለሰብ “የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የያዘውን ሐቅ መቀበል አስፈልጎታል።—ምሳሌ 21:2
ትክክል የሆነውን ነገር ከልቡ የሚሠራ ሰው የአምላክን ሕግ መታዘዝ ብቻ ሳይሆን ባሕርያቱንም መኮረጅ እንዳለበት የኢየሱስ ምሳሌ ያሳያል። (ኤፌሶን 5:1) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም’ በማለት ይገልጽልናል። (ሥራ 10:34) በዚህ ረገድ አምላክን እየመሰልን ነውን? ኢየሱስ የተናገረው ስሜት የሚነካ ምሳሌ ለሰዎች የምናሳየው ወዳጃዊ ስሜት ብሔራዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ድንበሮችን አልፎ መሄድ እንዳለበት ያሳያል። በእርግጥም ክርስቲያኖች ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ዘር ወይም ብሔር ላላቸው እንዲሁም ለእምነት ጓደኞቻቸው ብቻ ሳይሆን “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።—ገላትያ 6:10
የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመከተል ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርጉት ለእምነት ጓደኞቻቸው ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮች ላልሆኑ ሰዎች ጭምር ነው።c ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲኖራቸው በመርዳት በየዓመቱ በድምሩ ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ። የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ስለሆነ ለእያንዳንዱ ሰው የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ እየጣሩ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4፤ ሥራ 10:35
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ምሳሌ ማለት አብዛኛውን ጊዜ አጭር የሆነ ልብ ወለድ ትረካ ሲሆን ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ ትምህርት ይገኝበታል።
b በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አንዳንድ የእንግዳ ማረፊያዎች መጠለያ ብቻ ሳይሆን ምግብና ሌሎች መስተንግዶዎችም ያቀርቡ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ በአእምሮው ይዞት የነበረው ይህን ዓይነቱን ማረፊያ ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል በሉቃስ 2:7 ላይ “በእንግዶችም ማደሪያ” ተብሎ ከተገለጸው የተለየ ስለሆነ ነው።
c ለምሳሌ ያህል የታኅሣሥ 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-8 እና የጥር 15, 1998ን ከገጽ 3-7 ተመልከት።