‘በናፍቆት መጠባበቅ’
“የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና።”—ሮሜ 8:19
1. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በነበሩበት ሁኔታ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
ዛሬ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከነበሩበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። በዚያን ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ ለመገንዘብ እንዲችሉ አንድ ትንቢት ረድቷቸዋል። (ዳንኤል 9:24–26) ይኸው ትንቢት ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ቢናገርም ክርስቲያኖች ከተማዋ የምትጠፋበትን ጊዜ አስቀድመው ለማወቅ የሚያስችላቸውን ፍንጭ የያዘ አልነበረም። (ዳንኤል 9:26, 27) በተመሳሳይም በ19ኛው መቶ ዘመን ቅን ልቦና የነበራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አንድ ትንቢት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል። በዳንኤል 4:25 ላይ የተጠቀሱትን “ሰባት ዘመናት” ‘ከአሕዛብ ዘመን’ ጋር በማያያዝ ክርስቶስ በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣን እንደሚቀበል ጠብቀዋል። (ሉቃስ 21:24፤ ሕዝቅኤል 21:25–27) የዳንኤል መጽሐፍ በርካታ ትንቢቶችን የያዘ ቢሆንም እንኳ ከእነዚህ ትንቢቶች ውስጥ የትኛውም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መላው የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት የሚደመሰስበትን ትክክለኛ ጊዜ ለማስላት አያስችሏቸውም። (ዳንኤል 2:31–44፤ 8:23–25፤ 11:36, 44, 45) ይሁን እንጂ የምንኖረው ‘በፍጻሜ ዘመን’ ስለሆነ ይህ ጥፋት በቅርቡ ይሆናል።—ዳንኤል 12:4a
በክርስቶስ መገኘት ጊዜ ነቅቶ መጠባበቅ
2, 3. (ሀ) ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ በተገኘበት ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳየው ዋነኛ ማረጋገጫ ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት ወቅት መትጋት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
2 እርግጥ ክርስቶስ በ1914 በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ ከመገኘቱ በፊት አንድ ትንቢት ክርስቲያኖችን በመጠባበቅ እንዲኖሩ አድርጓቸው ነበር። ሆኖም ክርስቶስ ስለ መገኘቱና ስለ ነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የሰጠው “ምልክት” ክንውኖችን የያዘ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የሚታዩት ደግሞ መገኘቱ ከጀመረ በኋላ ይሆናል። ጦርነትን፣ የምግብ እጥረትን፣ የመሬት መንቀጥቀጥን፣ ወረርሽኝ በሽታዎችን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ሥርዓት አልበኛነትን፣ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደትንና የመንግሥቱ ምሥራች በዓለም ዙሪያ መሰበክን የመሳሰሉ ክንውኖች ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ በተገኘበት ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳዩ ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው።—ማቴዎስ 24:3–14፤ ሉቃስ 21:10, 11
3 ሆኖም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው የመሰነባበቻ ምክር በአብዛኛው ‘ተጠንቀቁ፣ ትጉ፣ ንቁ’ የሚል ነበር። (ማርቆስ 13:33, 37፤ ሉቃስ 21:36) ነቅቶ ስለመጠባበቅ የተሰጡትን ምክሮች ጠቅላላ መልእክት በጥንቃቄ ማንበብ ክርስቶስ በዋነኛነት እየተናገረ የነበረው መገኘቱ የሚጀምርበትን ጊዜ የሚጠቁመውን ምልክት በትጋት ስለመጠበቅ ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ መገኘቱ ከጀመረ በኋላ ባለው ወቅት ሁሉ ንቁ ሆነው እንዲቀጥሉ ማዘዙ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖች ነቅተው ሊጠብቁት ይገባ የነበረው ነገር ምንድን ነው?
4. ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ለምን ዓላማ ያገለግላል?
4 ኢየሱስ ‘እነዚህ [ወደ አይሁድ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት የሚመሩ ክንውኖች] መቼ ይሆናሉ? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?’ በማለት ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ላይ ታላቁን ትንቢቱን ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3) በትንቢት የተነገረው ምልክት የክርስቶስን መገኘት ብቻ ሳይሆን ወደዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ የሚመሩ ክንውኖችንም ለማመልከት ጭምር ያገለግላል።
5. ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ተገኝቶ እያለም ገና ‘እንደሚመጣ’ ያመለከተው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ‘በሚገኝበት’ (በግሪክኛ፣ ፓሩሲያ) ጊዜ በኃይልና በክብር እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ የእሱን ‘መምጣት’ (ኤርኮማይ በተባለው የግሪክኛ ቃል እርባታ የተገለጸው) በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ . . . ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቊጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ [ክርስቶስ] በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። . . . ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። . . . ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”—ማቴዎስ 24:30, 32, 33, 42, 44፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው ለምንድን ነው?
6. “ታላቂቱ ባቢሎን” የምትጠፋው እንዴት ይሆናል?
6 ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1914 ጀምሮ በንግሥና ላይ ቢሆንም ክፉ ሆነው ባገኛቸው ላይ የቅጣት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በተለያዩ ሥርዓቶችና ግለሰቦች ላይ ገና መፍረድ አለበት። (ከ2 ቆሮንቶስ 5:10 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ በቅርቡ ፖለቲካዊ መሪዎች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን “ታላቂቱ ባቢሎን” ለማጥፋት እንዲነሣሡ ሐሳቡን በአእምሯቸው ውስጥ ያስቀምጣል። (ራእይ 17:4, 5, 16, 17) ኢየሱስ ክርስቶስ “የዓመፅ ሰው” የተባሉትን ማለትም ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ዋነኛ ክፍል የሆነችውን የከሃዲዋን ሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት እንደሚያጠፋ ሐዋርያው ጳውሎስ ለይቶ ጠቅሷል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል።”—2 ተሰሎንቄ 2:3, 8
7. የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ምን ፍርድ ይሰጣል?
7 በቅርቡ ክርስቶስ ገና አሁንም በምድር ላይ ላሉት ወንድሞቹ ባደረጉት ነገር መሠረት በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል። እንዲህ እናነባለን:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። . . . ንጉሡም መልሶ [ለበጎቹ]:- እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። . . . እነዚያም [ፍየሎቹም] ወደ ዘላለም ቅጣት፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”—ማቴዎስ 25:31–46
8. ክርስቶስ አምላካዊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የቅጣት ፍርድ ለመስጠት የሚመጣበትን ሁኔታ ጳውሎስ የገለጸው እንዴት ነው?
8 ስለ በጎችና ፍየሎች የሚናገረው ምሳሌ እንደሚያሳየው ኢየሱስ አምላካዊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የመጨረሻ የፍርድ እርምጃ ይወስዳል። ጳውሎስ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ መሰል አማኞች እንዲህ ሲል ዋስትና ሰጥቷል:- “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ . . . ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ . . . እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፣ . . . ሲመጣ፣ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።” (2 ተሰሎንቄ 1:7–10) እነዚህ ሁሉ አስደናቂ ክንውኖች ከፊታችን ስላሉልን እምነት እንዳለን ልናሳይና የክርስቶስን መምጣት በናፍቆትና በትጋት ልንጠባበቅ አይገባንምን?
የክርስቶስን መገለጥ በናፍቆት መጠባበቅ
9, 10. አሁንም ገና ምድር ላይ የሚገኙ ቅቡዓን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በናፍቆት የሚጠባበቁት ለምንድን ነው?
9 ‘ኢየሱስ ከሰማይ የሚገለጠው’ ክፉዎችን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ለጻድቃን ሽልማት ለመስጠት ጭምር ነው። ከተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች ውስጥ ገና አሁንም በምድር ላይ ያሉት ቀሪዎች ክርስቶስ ከመገለጡ በፊት መከራ ይደርስባቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በክብራማው ሰማያዊ ተስፋቸው ይደሰታሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች “ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፣ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ” ሲል ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 4:13
10 እነዚህ ቅቡዓን ክርስቶስ ወደ ራሱ ‘እስኪሰበስባቸው’ ድረስ “የተፈተነ” እምነታቸው “ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፣ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ” ታማኝ ሆነው ለመቆየት ቆርጠዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:1፤ 1 ጴጥሮስ 1:7) እነዚህን በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች በተመለከተ እንዲህ ለማለት ይቻላል:- “ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ [ጸንቷል]። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ [“በናፍቆት፣” NW] ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጐድልባችሁም።”—1 ቆሮንቶስ 1:6, 7
11. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ እየተጠባበቁ ምን ያደርጋሉ?
11 ቅቡዓን ቀሪዎች እንዲህ ብሎ ከጻፈው ከጳውሎስ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ይሰማቸዋል:- “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።” (ሮሜ 8:18) እምነታቸው በጊዜ ስሌት መደገፍ አያስፈልገውም። በይሖዋ አገልግሎት በመጠመድ ጓደኞቻቸው ለሆኑት ለ“ሌሎች በጎች” ድንቅ ምሳሌ ሆነውላቸዋል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ቅቡዓን የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ቅርብ መሆኑን ስለሚያውቁ የሚከተለውን የጴጥሮስ ማሳሰቢያ ከልብ ይቀበላሉ:- “ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።”—1 ጴጥሮስ 1:13
“የፍጥረት ናፍቆት”
12, 13. ሰብዓዊ ፍጥረት ‘ለከንቱነት የተገዛው’ እንዴት ነው? ሌሎች በጎችስ የሚናፍቁት ምንን ነው?
12 ሌሎች በጎች በናፍቆት የሚጠባበቁት ነገር አላቸውን? በእርግጥ አላቸው። ይሖዋ በመንፈስ የተወለዱ “ልጆቹ” እንዲሆኑና በሰማያዊ መንግሥት ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው እንዲወርሱ’ የመረጣቸው ሰዎች ስላላቸው ክብራማ ተስፋ ከተናገረ በኋላ ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”—ሮሜ 8:14–21፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:10–12
13 በአዳም ኃጢአት ምክንያት ዘሮቹ በሙሉ በኃጢአትና በሞት ባርነት ሥር በመወለዳቸው ‘ለከንቱነት የተገዙ’ ሆነዋል። ራሳቸውን ከዚህ ባርነት ነፃ ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። (መዝሙር 49:7፤ ሮሜ 5:12, 21) ሌሎች በጎች ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ ለመውጣት’ ምንኛ ይናፍቃሉ! ሆኖም ይህ ከመሆኑ በፊት ይሖዋ በወሰናቸው ዘመናትና ወቅቶች መሠረት አንዳንድ ነገሮች መፈጸም አለባቸው።
14. ‘የአምላክ ልጆች መገለጥ’ ምን ነገር የሚጨምር ይሆናል? ይህ ‘የሰው ልጆችን ከጥፋት ባርነት ነፃ የሚያወጣውስ’ እንዴት ይሆናል?
14 በመጀመሪያ የተቀቡት ‘የአምላክ ልጆች’ ቀሪዎች ‘መገለጥ’ አለባቸው። ይህ ምንን ይጨምራል? አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ቅቡዓኑ ከክርስቶስ ጋር ለመንገሥ ‘መታተማቸውና’ ክብር መጎናጸፋቸው ለሌሎች በጎች ግልጽ ይሆናል። (ራእይ 7:2–4) በተጨማሪም ከሞት የተነሡት ‘የአምላክ ልጆች’ ከክርስቶስ ጋር በመሆን የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በማጥፋቱ እርምጃ ተካፋይ በመሆን ‘ይገለጣሉ።’ (ራእይ 2:26, 27፤ 19:14, 15) ከዚያም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች ለሰብዓዊው “ፍጥረት” የሚያድሉ ክህነታዊ መስመሮች በመሆን ‘ይገለጣሉ።’ ይህም የሰው ልጆችን ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ በማውጣት’ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። (ሮሜ 8:21፤ ራእይ 20:5፤ 22:1, 2) ሌሎች በጎች እነዚህን የመሳሰሉ ታላላቅ ተስፋዎች ከፊታቸው ተዘርግተውላቸው እያሉ “የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ” ‘በናፍቆት ቢጠባበቁ’ ያስደንቃል?—ሮሜ 8:19
የይሖዋ ትዕግሥት ለማዳን ነው
15. የተለያዩ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ይሖዋ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ መዘንጋት የሌለብን ነገር ምንድን ነው?
15 ይሖዋ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ የማይል አምላክ ነው። የተለያዩ ክንውኖችን የሚያስፈጽምበት የጊዜ ሰሌዳ ፍጹም ትክክል መሆኑ ይረጋገጣል። አንዳንድ ጊዜ ነገሮች እኛ በግል በጠበቅነው መንገድ አይከናወኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን። (ኢያሱ 23:14) አንዳንድ ሁኔታዎች ብዙዎች ይፈጸማሉ ብለው ከጠበቁት ጊዜ አልፈው እንዲሄዱ ይፈቅድ ይሆናል። ሆኖም መንገዶቹን ለመረዳትና ጥበቡን ለማድነቅ እንጣር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር?”—ሮሜ 11:33, 34
16. ከይሖዋ ትዕግሥት ተጠቃሚዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው?
16 ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፣ ይህን እየጠበቃችሁ [የአሮጌዎቹ “ሰማያት” እና “ምድር” መጥፋትና አምላክ ተስፋ በሰጠባቸው “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” መተካት] ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም [በመጨረሻ] በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ።” ይሖዋ በመታገሡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “እንደ ሌባ” ሆኖ ከሚመጣው “የይሖዋ ቀን” ለመዳን አጋጣሚውን በማግኘት ላይ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:9–15) በተጨማሪም ትዕግሥቱ እያንዳንዳችን ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን እንድንፈጽም’ በማስቻል ላይ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:12) ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ተቀባይነት እንድናገኝና ‘በሰው ልጅ ፊት ለመቆም’ እንድንችል ከፈለግን ‘ለራሳችን መጠንቀቅና’ ‘ዘወትር ንቁ መሆን’ እንደሚያስፈልገን ተናግሯል።—ሉቃስ 21:34–36፤ ማቴዎስ 25:31–33
በጽናት መጠባበቃችሁን ቀጥሉ
17. ልብ ልንላቸው የሚገቡ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት የትኞቹ ናቸው?
17 ጳውሎስ መንፈሳዊ ወንድሞቹ ዓይናቸውን ‘በሚታዩ ነገሮች ላይ ሳይሆን በማይታዩ ነገሮች’ ላይ እንዲተክሉ አሳስቧቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:16–18) ከፊታቸው የተዘረጋውን በሰማይ የሚያገኙትን ሽልማት በተመለከተ ምንም ነገር እይታቸውን እንዲያደበዝዝባቸው አልፈለገም። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን የሌሎች በጎች ክፍል በፊታችን የተዘረጋው አስደናቂ ተስፋ ዘወትር ከአእምሮአችን አይጥፋ፤ እንዲሁም በፍጹም ተስፋ አንቁረጥ። ‘በትዕግሥት መጠባበቃችንን በመቀጠል’ “ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ . . . እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ” መካከል አለመሆናችንን እናስመስክር።—ሮሜ 8:25፤ ዕብራውያን 10:39
18. ዘመናትንና ወቅቶችን በትምክህት በይሖዋ እጅ ላይ ልንተዋቸው የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ዘመናትንና ወቅቶችን በትምክህት በይሖዋ እጅ ላይ ልንተዋቸው እንችላለን። የሰጠን ተስፋዎች ባወጣው የጊዜ ፕሮግራም መሠረት ይፈጸማሉ እንጂ ‘አይዘገዩም።’ (ዕንባቆም 2:3) እስከዚያ ድርስ ግን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ማሳሰቢያ ለእኛ ተጨማሪ ትርጉም ይኖረዋል። እንዲህ ብሏል:- “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፣ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፣ . . . የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፣ አገልግሎትህን ፈጽም።”—2 ጢሞቴዎስ 4:1-5
19. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው? ለምንስ?
19 የራሳችንም ሆነ የጎረቤቶቻችን ሕይወት በአደጋ ላይ ይገኛል። ጳውሎስ “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው። ከፊታችን የሚጠብቁንን አስደሳች ክንውኖች በናፍቆት እየተጠባበቅን ሕዝቦቹ የመንግሥቱን ምሥራች የሚሰብኩበት ይሖዋ የወሰነው ዘመንና ወቅት ገና አለማብቃቱን ፈጽሞ አንዘንጋ። ሥራው ይሖዋ እስከሚፈልገው ደረጃ ድረስ መሠራት አለበት። “በዚያን ጊዜም” ኢየሱስ እንዳለው “መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10ና 11 ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
◻ የጊዜ ስሌቶችን በተመለከተ ያለንበት ሁኔታ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያኖች በክርስቶስ መገኘት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ‘መትጋት’ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
◻ ሰብዓዊ ፍጥረት ‘የአምላክ ልጆችን መገለጥ’ በናፍቆት የሚጠባበቀው ለምንድን ነው?
◻ ዘመናትንና ወቅቶችን በትምክህት በይሖዋ እጅ ላይ ልንተዋቸው የምንችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች የክርስቶስን መምጣት እየተጠባበቁ ነቅተው ሊኖሩ ይገባል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅቡዓን ቀሪዎች እምነታቸውን በጊዜ ስሌቶች ላይ መሠረት ሳያደርጉ በይሖዋ አገልግሎት ይጠመዳሉ