የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘው ብቸኛ መንገድ
“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ።”—ዮሐንስ 14:6
1, 2. ኢየሱስ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ከምን ነገር ጋር አመሳስሎታል? ምሳሌው እንዲያስተላልፍ የተፈለገው ነጥብስ ምንድን ነው?
ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ጠባብ ደጅ ባለው መንገድ መስሎታል። ኢየሱስ ወደ ሕይወት በሚወስደው በዚህ መንገድ ላይ መጓዝ ቀላል አለመሆኑን አበክሮ እንደገለጸ ልብ በሉ። “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ [ዘላለም] ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 7:13, 14
2 ይህ ምሳሌ እንዲያስተላልፍ የተፈለገው መልእክት ምን እንደሆነ ገብቷችኋል? ወደ ሕይወት የሚያደርሰው መንገድ ወይም ጎዳና አንድ ብቻ እንደሆነና ይህንን መንገድ ለማግኘትና ካገኘንም በኋላ ከዚህ መንገድ ሳንወጣ ለመቀጠል ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልገን አያመለክትም? ታዲያ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው ብቸኛ መንገድ ምንድን ነው?
የኢየሱስ ክርስቶስ ሚና
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ በእኛ መዳን ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል? (ለ) የሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ እንደሚችል አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸው መቼ ነበር?
3 የእሱ ሐዋርያ የነበረው ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች [ከኢየሱስ በስተቀር] ሌላ የለምና” በማለት በገለጸው መሠረት ኢየሱስ ከዚህ መንገድ ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው። (ሥራ 4:12) ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 6:23) ኢየሱስ ራሱ የዘላለም ሕይወት የሚገኝበት ብቸኛ መንገድ በእሱ በኩል መሆኑን ሲገልጽ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ብሏል።—ዮሐንስ 14:6
4 ስለዚህ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን መንገድ በመክፈት ረገድ ያለውን ሚና መቀበላችን ወሳኝ ነገር ነው። በመሆኑም እስቲ ኢየሱስ ያለውን ሚና ይበልጥ ጠለቅ ብለን እንመርምር። አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ የሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ እንደሚችል ይሖዋ አምላክ ያመለከተው መቼ እንደሆነ ታውቃላችሁ? አዳም ኃጢአት እንደሠራ ወዲያውኑ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች አዳኝ ሆኖ እንደሚሰጥ በመጀመሪያ የተተነበየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።
ተስፋ የተሰጠበት ዘር
5. ሔዋንን ያሳሳታትን እባብ ለይተን ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ አምላክ በምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም ተስፋ የተሰጠበት አዳኝ ማን መሆኑን አመልክቷል። ይህን ያደረገው ሔዋንን በማነጋገር ከተከለከለው ፍሬ እንድትበላና አምላክን እንዳትታዘዝ ባደረጋት ‘እባብ’ ላይ የፍርድ ቃል በተናገረ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-5) እርግጥ ይህ እባብ ቃል በቃል እባብ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ” ተብሎ የተገለጸው ይህ ኃያል የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር ነው። (ራእይ 12:9) ሰይጣን አነስተኛ ፍጥረት የሆነውን እባብ እንደ ቃል አቀባይ ተጠቅሞ ሔዋንን አሳታት። በመሆኑም አምላክ በሰይጣን ላይ ሲፈርድ እንዲህ አለ:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፣ እርሱ [የሴቲቱ ዘር] ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 3:15
6, 7. (ሀ) ‘ዘሩን’ ያስገኘችው ሴት ማን ናት? (ለ) ተስፋ የተሰጠበት ዘር ማን ነው? ምንስ ነገር ያከናውናል?
6 ሰይጣን በጠላትነት የሚመለከታት ይህች “ሴት” ማን ናት? “የቀድሞውን እባብ” ማንነት ያሳወቀን ራእይ ምዕራፍ 12 እንደሆነ ሁሉ አሁንም የሴቲቱን ማንነት ያሳውቀናል። በቁጥር 1 ላይ “ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት” ሴት እንደሆነች ተገልጿል። ይህች ሴት የምታመለክተው ታማኝ መላእክትን ያቀፈውን የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ሲሆን ሴቲቱ የወለደችው “ወንድ ልጅ” ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለትን የአምላክ መንግሥት ያመለክታል።—ራእይ 12:1-5
7 ታዲያ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰውና የሰይጣንን ‘ራስ’ ቀጥቅጦ የሚገድለው ይህ የሴቲቱ “ዘር” ወይም ልጅ ማን ነው? አምላክ ከአንዲት ድንግል በተአምር እንዲወለድ ከሰማይ የላከውና ሰው የሆነው ኢየሱስ ነው። (ማቴዎስ 1:18-23፤ ዮሐንስ 6:38) የራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 12 እንደሚያመለክተው ይህ ዘር፣ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን የተነሣ ሰማያዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን አዝማች ሆኖ ሰይጣንን ድል በማድረግ ራእይ 12:10 በሚለው መሠረት “የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን” እንዲሆን ያደርጋል።
8. (ሀ) አምላክ ከመጀመሪያ ዓላማው ጋር ግንኙነት ያለው ምን አዲስ ነገር አዘጋጅቷል? (ለ) የአምላክ አዲስ መንግሥት ከእነማን የተውጣጣ ነው?
8 ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረው መንግሥት የሰው ልጅ በምድር የዘላለም ሕይወት አግኝቶ በደስታ እንዲኖር አምላክ ባወጣው የመጀመሪያ ዓላማ ላይ የገባ አዲስ ዝግጅት ነው። ሰይጣን እንዳመፀ ይሖዋ ወዲያው በክፋት ምክንያት የመጡትን መጥፎ ነገሮች በሙሉ በዚህ አዲስ ንጉሣዊ መስተዳድር አማካኝነት ለማስወገድ ዝግጅት አደረገ። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከእርሱ ጋር በዚህ መንግሥት አገዛዝ የሚካፈሉ እንደሚኖሩ አመልክቷል። (ሉቃስ 22:28-30) ከሰው ልጆች መካከል ተመርጠው ከእርሱ ጋር በሰማያዊው መንግሥት አስተዳደር የሚካፈሉና የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ደረጃ ክፍሎች የሚሆኑ ሌሎች ሰዎች ይኖራሉ። (ገላትያ 3:16, 29) መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ከሚገኙት ኃጢአተኛ የሰው ልጆች መካከል ተዋጅተው ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የሚሆኑት ብዛታቸው 144,000 እንደሚሆኑ ይገልጻል።—ራእይ 14:1-3
9. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ መገኘት ያስፈለገው ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ የሰይጣንን ሥራዎች ያፈረሰው እንዴት ነበር?
9 ይህ መንግሥት መግዛት ከመጀመሩ በፊት ግን ዋነኛው የሴቲቱ ዘር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት ነበረበት። ለምን? “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ” [ወይም እንዲሽር] ይሖዋ አምላክ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። (1 ዮሐንስ 3:8) ከሰይጣን ሥራዎች አንዱ አዳም ኃጢአት እንዲሠራ መገፋፋት ሲሆን ይህም በአዳም ልጆች ሁሉ ላይ የኃጢአትና የሞት ኩነኔ አስከትሏል። (ሮሜ 5:12) ኢየሱስ የገዛ ራሱን ሕይወት ቤዛ አድርጎ በመስጠት ይህን የሰይጣን ሥራ አፍርሷል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሰው ልጅ ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነጻ ሊወጣ የሚያስችለውን መሠረት ከመጣሉም በላይ የዘላለም ሕይወትን መንገድ ከፍቷል።—ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 3:24፤ ኤፌሶን 1:7
ቤዛው ያስገኘው ጥቅም
10. ኢየሱስና አዳም የሚመሳሰሉት እንዴት ነበር?
10 የኢየሱስ ሕይወት ወደ አንዲት ሴት ማሕፀን እንዲዛወር የተደረገው ከሰማይ ስለነበረ አንዳችም የአዳም ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኖ ሊወለድ ችሏል። በመሆኑም በምድር ላይ ዘላለም የመኖር ችሎታና አቅም ነበረው። አዳምም በተመሳሳይ የተፈጠረው ፍጹም ሰው ሆኖ ስለነበረ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ በእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በአእምሮው ይዞ ነበር:- “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም [ኢየሱስ ክርስቶስ] ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:45, 47
11. (ሀ) አዳምና ኢየሱስ በሰው ልጆች ላይ ምን አስከትለዋል? (ለ) የኢየሱስን መሥዋዕት እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
11 እስከ ዛሬ ምድርን ከረገጡ ሰዎች ሁሉ ፍጹም በነበሩት በእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል ያለውን ንጽጽር መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ራሱን ‘ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ’ አድርጎ እንደሰጠ ከተናገረው ሐሳብ ለማስተዋል እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:6 NW) ኢየሱስ ተመጣጣኝ የሆነው ከማን ጋር ነው? ፍጹም ከሆነው አዳም ጋር ነዋ! የመጀመሪያው አዳም ኃጢአት በመላው ሰብዓዊ ዘር ላይ የሞት ኩነኔ አስከትሏል። “የኋለኛው አዳም” ያቀረበው መሥዋዕት ደግሞ ከኃጢአትና ከሞት ነጻ የምንወጣበትን መንገድ ስለከፈተ ለዘላለም መኖር እንችላለን። የኢየሱስ መሥዋዕት ምንኛ ውድ ነገር ነው! ሐዋርያው ጴጥሮስ መዳን ያገኘነው “በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ” እንዳልሆነ ገልጿል። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ “ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ብሏል።—1 ጴጥሮስ 1:18, 19
12. መጽሐፍ ቅዱስ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ የተጫነው የሞት ኩነኔ የሚሻርበትን መንገድ የሚገልጸው እንዴት ነው?
12 መጽሐፍ ቅዱስ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ የተጫነው የሞት ኩነኔ የሚሻርበትን መንገድ ውብ አድርጎ ሲገልጸው እንዲህ ይላል:- “እንግዲህ በአንድ [በአዳም] በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ [እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ባሳየው የአቋም ጽናት] ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ [በኢየሱስ] መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።”—ሮሜ 5:18, 19
አስደናቂ ተስፋ
13. ብዙዎች ለዘላለም መኖር እንደማይፈልጉ የሚናገሩት ለምንድን ነው?
13 አምላክ ያደረገልን ይህ ዝግጅት እጅግ በጣም ሊያስደስተን ይገባል! አዳኝ ስለተዘጋጀልን ደስ ብሏችኋል? በአንድ ትልቅ የአሜሪካ ከተማ የሚታተም አንድ ጋዜጣ ሰዎችን “የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያጓጓችኋልን? የሚል ጥያቄ በመጠየቅ ባደረገው አንድ ጥናት ላይ ለጥያቄው ምላሽ ከሰጡት ሰዎች መካከል 67.4 በመቶ የሚሆኑት “የለም አያጓጓንም” ሲሉ መመለሳቸው የሚያስደንቅ ነው። ለዘላለም ለመኖር አንፈልግም ያሉት ለምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያለው ኑሮ ከብዙ ችግሮች ጋር በመቆራኘቱ እንደሚሆን ግልጽ ነው። አንደኛው ሰው “የ200 ዓመት ሽማግሌ ሆኜ መታየት አልፈልግም” ብለዋል።
14. ለዘላለም መኖር ሙሉ በሙሉ አስደሳች የሚሆነው ለምንድን ነው?
14 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሰዎች በበሽታ፣ በእርጅናና በሌሎች አሳዛኝ ችግሮች በሚሰቃዩበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም ስለ መኖር አይደለም። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ገዥ እንደመሆኑ እነዚህን በሰይጣን ምክንያት የመጡትን ችግሮች በሙሉ ይሽራል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት የአምላክ መንግሥት የዚህን ዓለም ጨቋኝ መንግሥታት በሙሉ “ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች።” (ዳንኤል 2:44) በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ተከታዮቹን ላስተማረው ጸሎት ምላሽ እንዲሆን የአምላክ “ፈቃድ” ‘በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ይሆናል።’ (ማቴዎስ 6:9, 10) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ምድር ከማንኛውም ክፋት ሙሉ በሙሉ ከፀዳች በኋላ የኢየሱስ ቤዛ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ መዋል ይጀምራሉ። አዎን፣ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹም ጤና ያገኛሉ!
15, 16. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ምን ሁኔታዎች ይኖራሉ?
15 በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ፍጻሜውን ያገኛል:- “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጉብዝናውም ዘመን ይመለሳል።” (ኢዮብ 33:25) ሌላም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል:- “የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6
16 እስቲ አስቡት! ዕድሜያችን 80ም ይሁን 800 ወይም ከዚያ የሚበልጥ ሰውነታችን ፍጹም ጤነኛ ሆኖ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ መሠረት “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” በዚያን ጊዜ ይህም ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል:- “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4
17. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች ምን ነገሮችን ያከናውናሉ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
17 ፈጣሪ ገደብ የለሽ እውቀት የማከማቸትና የመማር አቅም እንዲኖረው አድርጎ የፈጠረውን አስደናቂውን አንጎላችንን በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ እርሱ በመጀመሪያ ባቀደለት መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። እንዴት ያሉ አስደናቂ ነገሮች ልንሠራ እንደምንችል ገምቱ! ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች እንኳን ከምድር ጎተራ ውስጥ ካወጧቸው ንጥረ ነገሮች ተንቀሳቃሽ ቴሌፎኖችን፣ የድምፅ ማጉያዎችን፣ ሰዓቶችን፣ ፔጀሮችን፣ ኮምፒዩተሮችን፣ አውሮፕላኖችን፣ አዎን፣ በዙሪያችን የምናያቸውን አስደናቂ ነገሮች በሙሉ ሊሠሩ ችለዋል። አንዳቸውም ቢሆኑ ከምድር ውጭ ከሚገኙ የጽንፈ ዓለሙ ክፍሎች በመጡ ንጥረ ነገሮች የተሠሩ አይደሉም። በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ በዕድሜ ውስንነት ስለማንገደብ ልንሠራ የምንችላቸው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ስፍር ቁጥር አይኖራቸውም!—ኢሳይያስ 65:21-25
18. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት በፍጹም አሰልቺ የማይሆነው ለምንድን ነው?
18 በተጨማሪም ሕይወት አሰልቺ አይሆንም። ሌላው ቢቀር እስከ አሁን ድረስ በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት የበላን ብንሆንም ከአሁን በኋላ ምግብ የሚባል አልቀምስም አንልም። ሰብዓዊ ፍጽምና በምናገኝበት ጊዜ ደግሞ ገነቲቱ ምድር በምታፈራልን ጣፋጭ ምርቶች ከአሁኑ የበለጠ እንደሰታለን። (ኢሳይያስ 25:6) ከዚህም በላይ የምድርን በርካታ እንስሳት በመንከባከብ፣ በጣም ውብ የሆኑትን ተራሮች፣ ወንዞች፣ ሸለቆዎችና የፀሐይ መጥለቅ በማየት ለዘላለም እንደሰታለን። በእርግጥም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር አሰልቺ አይሆንም!—መዝሙር 145:16
የአምላክን ብቃቶች ማሟላት
19. የአምላክን የሕይወት ስጦታ ለማግኘት የሚፈልጉ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶች ይኖራሉ ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ታዲያ ይህ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ታላቅ ስጦታ እንዲሁ የሚገኝ ይመስልሃል? ይህን ለማግኘት እንድንችል አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ቢኖር ምክንያታዊ አይሆንም? አዎን፣ በእርግጥ ምክንያታዊ ነው። አምላክ እንዲህ ያለውን ስጦታ እጃችንን አጣምረን ቁጭ እንዳልን አይወረውርልንም። ስጦታውን ዘርግቶልናል፣ ለማግኘት ግን እጃችንን መዘርጋት ይኖርብናል። አዎን፣ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። እንግዲያውስ አንተም ኢየሱስን እንደጠየቀው ወጣት ባለጠጋ “የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ወይም የጥያቄውን አቀራረብ ለወጥ አድርገህ የፊልጵስዩስ እስር ቤት ዘበኛ የነበረው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስን እንደጠየቀው “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ትል ይሆናል።—ማቴዎስ 19:16፤ ሥራ 16:30
20. የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነው አንደኛው ብቃት ምንድን ነው?
20 ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ ምሽት ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት አንደኛውን አስፈላጊ ብቃት ጠቅሷል። እንዲህ አለ:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ስላስቻለን ስለ ይሖዋ እንዲሁም ለእኛ ሲል ስለ ሞተው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናውቅ መጠየቁ ምክንያታዊ አይደለም? ሆኖም እንዲህ የመሰለውን እውቀት ከማግኘት የበለጠ ነገር ይጠይቃል።
21. እምነት በማሳየት ረገድ የሚፈለግብንን ብቃት እያሟላን መሆኑን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
21 መጽሐፍ ቅዱስ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ይላል። ከዚያም በመቀጠል “በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ይላል። (ዮሐንስ 3:36) በሕይወትህ ላይ ለውጥ በማድረግና ሕይወትህን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በማስማማት ይህን ልታሳይ ትችላለህ። ቀደም ሲል ስትከተለው የነበረውን መጥፎ አካሄድ መተውና አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ መውሰድ አለብህ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ያዘዘውን ማድረግ ይኖርብሃል:- “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ . . . ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።”—ሥራ 3:19
22. የኢየሱስን ፈለግ መከተል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድን ያካትታል?
22 የዘላለም ሕይወት ልናገኝ የምንችለው በኢየሱስ በማመን መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። (ዮሐንስ 6:40፤ 14:6) በኢየሱስ እንደምናምን የምናሳየው ‘ፍለጋውን በቅርብ በመከተል ነው።’ (1 ጴጥሮስ 2:21) የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ መከተል ምን ነገሮችን ይጨምራል? ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ” ብሎ ነበር። (ዕብራውያን 10:7) ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በመስማማትና ራሳችሁን ለይሖዋ በመወሰን ኢየሱስን መምሰል አስፈላጊ ነው። ይህን ካደረግን በኋላ ውሳኔያችንን ለሕዝብ ለማሳየት ኢየሱስ ራሱ እንዳደረገው በውኃ መጠመቅ ያስፈልጋል። (ሉቃስ 3:21, 22) እነዚህን እርምጃዎች መውሰዱ ምክንያታዊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) የክርስቶስ ፍቅር ግድ የሚለን በምን መንገድ ነው? ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን እንዲሰጥ ፍቅር ገፋፍቶታል። ታዲያ ይህ በእሱ በማመን ለፍቅሩ ምላሽ እንድንሰጥ ሊገፋፋን አይገባም? አዎን፣ ሌሎችን ለመርዳት ራሱን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ትቶት ያለፈውን ፍቅራዊ ምሳሌ እንድንከተል ሊገፋፋን ይገባል። ኢየሱስ የኖረው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ነበር፤ እኛም ለራሳችን መኖርን በማቆም እንዲህ ማድረግ አለብን።
23. (ሀ) ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች ወደ ምን መጨመር አለባቸው? (ለ) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች ምን ይፈለጋል?
23 ሆኖም ጉዳዩ እዚህ ላይ አያበቃም። መጽሐፍ ቅዱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 3,000 የሚያክሉ ሰዎች በተጠመቁ ጊዜ እንደ “ተጨመሩ” ይናገራል። ወዴት ተጨመሩ? ሉቃስ እንደሚገልጽልን “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።” (ሥራ 2:41, 42) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትና ለኅብረት ይገናኙ ስለነበር የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሆነው ወይም ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተጨምረው ነበር። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ መመሪያዎችን ለማግኘት ዘወትር በስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር። (ዕብራውያን 10:25) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው የሚሰበሰቡ ሲሆን እናንተም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንድትገኙ ያበረታቷችኋል።
24. ‘እውነተኛው ሕይወት’ ምንድን ነው? ይህ ሕይወት ሊጨበጥ የሚችለውስ እንዴትና መቼ ነው?
24 በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ወደ ሕይወት የሚያደርስ ጠባብ መንገድ በመከተል ላይ ናቸው። በዚህ ጠባብ መንገድ ላይ ለመቆየት ጥረት ያስፈልጋል! (ማቴዎስ 7:13, 14) ጳውሎስ “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ” ሲል በሰጠው ልባዊ ምክር ላይ ይህን አመልክቷል። ‘እውነተኛውን ሕይወት ለመያዝ’ ይህንን ውጊያ መጋፈጥ አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ይህ እውነተኛ ሕይወት በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣብን የሕመም፣ የመቃተትና የሥቃይ ሕይወት አይደለም። እውነተኛው ሕይወት ይህ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ በቅርቡ ይሖዋ አምላክንና ልጁን ለሚወዱ ሁሉ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች በሚዳረሱበት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘው ሕይወት ነው። ሁላችንም የዘላለም ሕይወትን ማለትም በአምላክ አስደናቂ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘውን “እውነተኛውን ሕይወት” ለማግኘት ከሚመርጡት መካከል እንሁን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሱት እባቡ፣ ሴቲቱና ዘሩ እነማን ናቸው?
◻ ኢየሱስ ከአዳም ጋር የሚመጣጠነው እንዴት ነው? ቤዛውስ ምን ነገር እንዲቻል አድርጓል?
◻ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ያስደስተኛል የምትለው ምን ነገር በጉጉት ልትጠባበቅ ትችላለህ?
◻ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የትኞቹን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርብናል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣት ለሆኑትም ሆነ በዕድሜ ለገፉት መጨረሻ የሌለው ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ በወሰነው ጊዜ ያረጁ ሰዎች የወጣትነት ጉልበታቸውን መልሰው ያገኛሉ