በመንፈስ ሰይፍ ሙስናን መዋጋት
“ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”—ኤፌሶን 4:24
ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የሮም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ከዚያ በፊት በዓለም የሥልጣን መድረክ ላይ ከታዩት ሰብዓዊ መስተዳድሮች ሁሉ እጅግ የላቀ ነበር። የሮማ የሕግ አነዳደፍ በጣም ስኬታማ ከመሆኑ የተነሳ እስካሁን ድረስ ለብዙ አገሮች ሕገ መንግሥት መሠረት ሆኖ ያገለግላል። ሮም ያን ያክል ስኬታማ የነበረች ብትሆንም የጦር ሠራዊቷ ግን አንድን መሰሪ ጠላት ማለትም ሙስናን ድል መንሳት ተስኖት ነበር። በመጨረሻም ሙስና የሮም ውድቀት እንዲፋጠን አድርጓል።
በሙስና በተጨማለቁት የሮም ባለሥልጣናት በደል ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስን የመረመረው የሮማው ገዥ ፊልክስ፣ ጳውሎስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት ተረድቶ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በእሱ ዘመን ከነበሩት በሙስና የተጨማለቁ ገዥዎች አንዱ የነበረው ፊልክስ ከእስር እንዳስፈታው ገንዘብ ይሰጠኛል በሚል ተስፋ የጳውሎስን ፍርድ አጓትቶበታል።—ሥራ 24:22-26
ጳውሎስ ለፊልክስ ጉቦ ከመስጠት ይልቅ “ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት” በግልጽ ነገረው። ፊልክስ አካሄዱን አልለወጠም፤ ጳውሎስ ደግሞ ጉቦ በመስጠት ሕጋዊ ከሆነው አሠራር ለማምለጥ ከመሞከር ይልቅ እዚያው በእስር መቆየትን መርጧል። ጳውሎስ የእውነትንና የሐቀኝነትን መልእክት ከመስበኩም በላይ ከዚያም ጋር ተስማምቶ ኖሯል። ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፣ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናል።”—ዕብራውያን 13:18
እንዲህ ዓይነቱ አቋም በዘመኑ ከነበረው የሥነ ምግባር ደረጃ ፈጽሞ የተለየ ነበር። የፊልክስ ወንድም ፖሎስ በጥንቱ ዓለም ከነበሩት እጅግ ባለጸጋ ሰዎች አንዱ የነበረ ሲሆን 45 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመተውን ሀብት ያከማቸው ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል በጉቦና በምዝበራ ነው። ይሁን እንጂ እሱ ያከማቸው ሀብት አንዳንድ ምግባረ ብልሹ የሆኑ የ20ኛው መቶ ዘመን መሪዎች ምሥጢራዊ በሆኑ የባንክ ሒሳቦች ከሸሸጉት በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ አይባልም። ዛሬ ያሉ መንግሥታት ከሙስና ጋር በሚደረገው ውጊያ ድል ተቀዳጅተዋል ብሎ የሚያስብ ካለ በጣም የዋህ ነው።
ሙስና ለረጅም ዘመን ሥር ሰድዶ የኖረ ነገር እስከሆነ ድረስ የሰው ልጅ ባሕርይ ክፍል እንደሆነ አድርገን መውሰድ ይኖርብናልን? ወይስ ሙስናን ለመግታት ማድረግ የሚቻል ነገር ይኖራል?
ሙስናን መግታት የሚቻለው እንዴት ነው?
ሙስናን በመግታት ረገድ አማራጭ የሌለው የመጀመሪያ እርምጃ ሙስና ሌሎችን እያቆረቆዘ ይሉኝታ ቢስ የሆኑ ሰዎችን የሚያበለጽግ አደገኛና ጎጂ ነገር መሆኑን መገንዘብ ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ መሻሻል እንደተደረገ አይካድም። የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ፎሊ እንዲህ ብለዋል:- “ጉቦኝነት ምን ያህል ኪሳራ እንደሚያስከትል ሁላችንም እናውቀዋለን። ጉቦ ጥሩ መስተዳደርን ያዳክማል፣ የኢኮኖሚ አቅምን ያዳሽቃል፣ እድገትን ያቀጭጫል፣ የንግድ እንቅስቃሴን ያዛባል እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ዜጎችን ለከፍተኛ ችግር ይዳርጋል።” ብዙዎች በእሳቸው አባባል ይስማማሉ። ታኅሣሥ 17, 1997, 34 የሚሆኑ ታላላቅ አገሮች “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሙስና ጋር በሚደረገው ውጊያ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት” ተደርጎ የተነደፈውን “ጉቦኝነትን የሚመለከተውን ዓለም አቀፍ ስምምነት” ፈርመዋል። ስምምነቱ “በብሔራት መካከል የሚደረግ የንግድ ግንኙነት ለመመሥረት ወይም እንዳይቋረጥ ለማድረግ ሲባል ለአንድ የውጭ አገር የመንግሥት ባለሥልጣን ጉቦ መስጠትም ሆነ ለመስጠት ሐሳብ ማቅረብ ወይም ቃል መግባት ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል።”
ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች የንግድ ኮንትራቶችን ለማሸነፍ የሚሰጥ ጉቦ የሙስና ጥቂት ክፍል ብቻ ነው። ሙስናን ከናካቴው ለማስወገድ፣ ይበልጥ አዳጋች የሆነ ሁለተኛ ደረጃ እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል። ይህም የልብ ለውጥ እንዲያውም የብዙ ሰዎች የልብ ለውጥ ማድረግ ነው። በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች ጉቦኝነትንና ሙስናን መጥላት መቻል አለባቸው። ጉቦኝነት ሊወገድ የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አንዳንድ ሰዎች መንግሥታት “ዜጎቻቸው ሁለገብ የሆነ በጎ ምግባር እንዲያሳዩ ማበረታታት” አለባቸው የሚል ስሜት እንዳላቸው ኒውስዊክ መጽሔት ዘግቧል። በተመሳሳይ ትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ አንድ የፀረ ሙስና ቡድን ደጋፊዎቹ በሥራ ቦታ “‘እርስ በርስ የመደጋገፍ መንፈስ’ እንዲያስፋፉ” ሐሳብ አቅርቧል።
ከሙስና ጋር የሚደረገው ውጊያ ሥነ ምግባርን የሚመለከት ጉዳይ ስለሆነ እንዲያው ሕግ በማርቀቅ ወይም ሕግ በሚያስከትለው የቅጣት “ሰይፍ” ማስፈራሪያ ብቻ ድል ማድረግ አይቻልም። (ሮሜ 13:4, 5) በሰዎች ልብ ውስጥ የበጎ ምግባርና የታማኝነት ዘር መተከል አለበት። በተሻለ ሁኔታ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመንፈስ ሰይፍ’ ሲል የገለጸውን የአምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ያስፈልጋል።—ኤፌሶን 6:17
መጽሐፍ ቅዱስ ሙስናን ያወግዛል
ሐዋርያው ጳውሎስ ሙስናን አቅልሎ ያልተመለከተው ለምን ነበር? ‘በፍርድ የማያዳላውን፣ መማለጃም የማይቀበለውን’ አምላክ ፈቃድ ለመፈጸም ይፈልግ ስለነበር ነው። (ዘዳግም 10:17) በተጨማሪም ጳውሎስ በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኘውን ቀጥተኛ መመሪያ እንዳስታወሰ ምንም አያጠራጥርም:- “ፊት አይተህ አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፣ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል።” (ዘዳግም 16:19) በተመሳሳይ ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ሙስናን እንደሚጠላ ከመገንዘቡም በላይ ‘ቀኛቸው መማለጃ ከተሞላች’ ኃጢአተኞች ጋር እንዳይቆጥረው ለምኗል።—መዝሙር 26:10
አምላክን በቅንነት የሚያመልኩ ሰዎች ሙስናን የሚጠሉበት ተጨማሪ ምክንያቶች አሏቸው። ሰሎሞን “ንጉሥ በፍትህ አገሩን ያጸናል፤ ለጉቦ የሚስገበገብ ግን ያፈርሰዋል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 29:4 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) በተለይ ከከፍተኛው ባለሥልጣን አንስቶ እስከ ተራው ግለሰብ ድረስ ፍትህ መጠበቃቸው አገርን የሚያጸና ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ሙስና አገርን ያደኸያል። ኒውስዊክ “ሁሉም ሰው በሙስና ከሚገኘው ትርፍ ለመቋደስ በሚፈልግበትና ማግኛ ዘዴውንም በሚያውቅበት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚው ይወድቃል” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው።
እንዲያው ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ ባይወድቅም እንኳ ፍትህ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ሙስና ያለአንዳች ቁጥጥር እየተስፋፋ እንዳለ ሲመለከቱ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይሰማቸዋል። (መዝሙር 73:3, 13) በተጨማሪም በተፈጥሮአችን ውስጣዊ የፍትሕ ፍላጎት እንዲኖረን ያደረገውን ፈጣሪያችንን መበደል ነው። ከዚህ በፊት ይሖዋ ዓይን ያወጣ ሙስናን ለማስወገድ ጣልቃ የገባበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ያህል የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችን ለጠላቶቻቸው አሳልፎ የሚሰጥበትን ምክንያት በግልጽ ነግሯቸዋል።
አምላክ በነቢዩ ሚክያስ በኩል እንዲህ ብሏቸዋል:- “ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፣ እባካችሁ ይህን ስሙ። አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፣ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፣ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ . . . ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፣ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች።” ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሙስና ሮምን ውስጥ ውስጧን እንደቦረቦራት ሁሉ በእስራኤል የነበረውንም ኅብረተሰብ ለጥፋት ዳርጓል። ሚክያስ እነዚህን ቃላት ከጻፈ ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በኋላ አምላክ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ መሠረት ኢየሩሳሌም ፈራርሳ ወና ሆናለች።—ሚክያስ 3:9, 11, 12
ማንም ሰው ወይም ብሔር ከሙስና መላቀቅ አይችልም ማለት ግን አይደለም። አምላክ ክፉዎች አካሄዳቸውን እንዲተዉና አስተሳሰባቸውን እንዲቀይሩ ያበረታታቸዋል። (ኢሳይያስ 55:7) ሁላችንም የስስትን ባሕርይ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ባሕርይ፣ ሙስናን ደግሞ በጽድቅ እንድንተካ ይፈልግብናል። ይሖዋ “ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል” ሲል ያሳስበናል።—ምሳሌ 14:31
በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሙስናን በተሳካ ሁኔታ መዋጋት
አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዲያደርግ ምን ነገር ሊገፋፋው ይችላል? ጳውሎስ የፈሪሳዊነትን ሕይወት እርግፍ አድርጎ እንዲተውና ቆራጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ እንዲሆን የገፋፋው ኃይል ሌሎች ሰዎችም በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ ሊገፋፋቸው ይችላል። ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው’ ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 4:12) በዛሬው ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊው እውነት በሙስና በጣም ተዘፍቀው በነበሩ ሰዎች መካከል እንኳ ሳይቀር ሐቀኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ነው። አንድ ምሳሌ ተመልከት።
የምሥራቅ አውሮፓ ተወላጅ የሆነው አሌክሳንደር የውትድርና አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ማጭበርበር፣ ዝርፊያና ጉቦኝነት የሚያካሂድ የአንድ የወንጀለኞች ቡድን አባል ሆነ።a “የእኔ ምድብ ሀብታም ከሆኑ ነጋዴዎች ለደኅንነታችሁ ጥበቃ ነው እያልኩ ገንዘብ መቀበል ነበር” ሲል ይገልጻል። “አንድ ነጋዴ አንዴ በእኔ እንዲተማመን ካደረግሁት በኋላ ሌሎች የቡድናችን አባላት ጥቃት እንደሚፈጽሙበት ይዝቱበታል። በዚህ ጊዜ እኔ ከፍተኛ ዋጋ በመጠየቅ ለጉዳዩ መፍትሄ እንደማስገኝ ሆኜ እቀርባለሁ። ‘ደንበኞቼ’ የችግሩ መንስዔ እኔ ራሴ ሆኜ እያለሁ የገጠሟቸውን ችግሮች እንዲወጡ ስለረዳኋቸው ያመሰግኑኛል። ነገሩ በጣም ሊያስገርም ቢችልም ይህ የምወደው ሥራ ነበር።
“ገንዘቡም ሆነ የአኗኗር ዘይቤው ከመጠን በላይ ያስደስተኝ ነበር። በጣም ውድ መኪና ነበረኝ፣ በጣም ቆንጆ አፓርታማ ውስጥ እኖር ነበር፣ እንዲሁም የፈለግሁትን ነገር ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ነበረኝ። ሰዎች ይፈሩኝ ነበር፤ ይህ ደግሞ የማን አለብኝነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርግ ነበር። ማንም ጫፌን ሊነካኝ እንደማይችልና ከሕግም በላይ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። ከፖሊስ ጋር ምንም ዓይነት ችግር ቢፈጠር ወይ የሕጉን ማምለጫ አሳምሮ የሚያውቅ ጎበዝ ጠበቃ በማቆም አሊያም ለሚመለከተው ሰው ጉቦ በመስጠት መፍትሄ ማግኘት ይቻል ነበር።
“ይሁን እንጂ በሙስና በሚተዳደሩ ሰዎች መካከል እርስ በርስ መተማመን የሚባል ነገር የለም ለማለት ይቻላል። ከቡድናችን አባል አንዱ እኔን ስለጠላኝ በቡድኑ ውስጥ ተቀባይነት እያጣሁ መጣሁ። ወዲያውኑ በጣም የምታምረውን መኪናዬን፣ ገንዘቤንና ቅንጦት የምትወደውን ሴት ጓደኛዬን አጣሁ። ይባስ ብሎም ክፉኛ ተደበደብኩ። ይህ አሳዛኝ ገጠመኝ ስለ ሕይወት ዓላማ በቁም ነገር እንዳስብ አደረገኝ።
“ከጥቂት ወራት በፊት እናቴ የይሖዋ ምሥክር ሆና ስለነበር የእነሱን ጽሑፍ ማንበብ ጀመርኩ። በምሳሌ 4:14, 15 ላይ የሚገኘው ጥቅስ በጥልቅ እንዳስብ አደረገኝ:- ‘በኀጥኣን መንገድ አትግባ፣ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። ከእርስዋ ራቅ፣ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም።’ እንደነዚህ የመሳሰሉት ጥቅሶች የወንጀለኛነት ሕይወት መምራት የሚፈልጉ ሰዎች እውን የሆነ የወደፊት ተስፋ እንደሌላቸው እንድገነዘብ አደረጉኝ። በትክክለኛው መንገድ እንዲመራኝ በመጠየቅ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመርኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጠናሁና በመጨረሻም ሕይወቴን ለአምላክ ወሰንኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሐቀኝነት ስኖር ቆይቻለሁ።
“እርግጥ የሐቀኝነትን መስፈርቶች አሟልቶ መኖር ከበፊቱ በጣም ያነሰ ገቢ ማግኘት ማለት ሆኖብኛል። ይሁን እንጂ አሁን እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ስለምመራ ተስፋ እንዳለኝ ይሰማኛል። የቀድሞ አኗኗሬም ሆነ ያን ጊዜ የነበረኝ ውድ ነገር ሁሉ ልጆች እንደሚሠሩት የዕቃ ዕቃ ቤት በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ ሊፈርስ የሚችል መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። ቀድሞ ሕሊናዬ ደንዝዞ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናቴ ምክንያት በጥቃቅን ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ሐቀኝነት የጎደለው ነገር እንዳደርግ ስፈተን ሕሊናዬ ይወጋኛል። ከመዝሙር 37:3 ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር እየጣርኩ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- ‘በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ፣ በምድርም ተቀመጥ፣ ታምነህም ተሰማራ።’ ”
‘ጉቦን የሚጠላ በሕይወት ይኖራል’
አሌክሳንደር እንደተገነዘበው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አንድ ሰው ሙስናን እንዲያሸንፍ ሊያነሳሳው ይችላል። እሱ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከገለጸው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ለውጥ አድርጓል:- “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጐደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።” (ኤፌሶን 4:22-25, 28) የሰው ዘር ሕልውና እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ በማድረግ ላይ የተመካ ነው።
ስግብግብነትና ሙስና ካልተገቱ በቀር ለሮም አገዛዝ መውደቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ሁሉ ምድርንም ሊያጠፉ ይችላሉ። ደስ የሚለው ግን የሰው ልጆች ፈጣሪ እነዚህ ነገሮች እንዲሁ እንዲቀጥሉ የመተው ዓላማ የሌለው መሆኑ ነው። ‘ምድርን የሚያጠፉትን ለማጥፋት’ ወስኗል። (ራእይ 11:18) በተጨማሪም ይሖዋ ከሙስና ነፃ የሆነ ዓለም ለማየት ለሚናፍቁ ሰዎች በቅርቡ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።—2 ጴጥሮስ 3:13
በዛሬው ጊዜ የሐቀኝነት መስፈርቶችን ጠብቆ መኖር ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም የኋላ ኋላ ‘ስስታም ሰው ቤተሰቡን ችግር ላይ እንደሚጥል፣ ጉቦን የሚጠላ ግን በሕይወት እንደሚኖር’ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶናል።b (ምሳሌ 15:27) በአሁኑ ጊዜ ሙስናን የማንቀበል ከሆነ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን ለአምላክ የምናቀርበው ጸሎት ልባዊ መሆኑን እናሳያለን።—ማቴዎስ 6:10
ሁላችንም የአምላክ መንግሥት እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ሙስናን አቅልለን ባለማየት ወይም በሙስና ባለመካፈል ‘ጽድቅን መዝራት’ እንችላለን። (ሆሴዕ 10:12) ይህን ካደረግን ሕይወታችንም ጭምር በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ላለው ኃይል ማስረጃ ይሆናል። የመንፈስ ሰይፍ ሙስናን ድል ማድረግ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሙ ተቀይሯል።
b እርግጥ፣ በጉቦና በጉርሻ መካከል ልዩነት አለ። ጉቦ የሚሰጠው ከፍትሕ ለመሸሽ ወይም ሐቀኝነት ለጎደላቸው ድርጊቶች ሲሆን ጉርሻ ግን ለአንድ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጥ የአድናቆት መግለጫ ነው። ይህ ጉዳይ በጥቅምት 1, 1986 የመጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እትም “የአንባብያን ጥያቄዎች” ላይ ተብራርቷል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ “አዲሱን ሰው” ማዳበርና ከሙስና መራቅ እንችላለን