የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?
“መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።”—ማቴዎስ 6:10
1. የአምላክ መንግሥት መምጣት ምን ማለት ይሆናል?
ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት ይምጣ ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምር የዚህ መንግሥት መምጣት ለብዙ ሺህ ዓመታት ከአምላክ አፈንግጦ የነበረውን የሰው አገዛዝ ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣ ያውቅ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ የአምላክ ፈቃድ በምድር ሁሉ ላይ ሆኖ ነበር ለማለት አይቻልም። (መዝሙር 147:19, 20) ይሁን እንጂ መንግሥቱ በሰማይ ከተቋቋመ በኋላ የአምላክ ፈቃድ በሁሉም ቦታ ይሆናል። ሰብዓዊ አገዛዝ በአምላክ አገዛዝ የሚተካበት አስደናቂ ጊዜ በጣም ቀርቧል።
2. ሰማያዊው መንግሥት ሥልጣኑን ከሰብዓዊው አገዛዝ በሚረከብበት ጊዜ ምን ነገር ይከሰታል?
2 ይህ የሽግግር ጊዜ ኢየሱስ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” በማለት የጠራው ወቅት ይሆናል። (ማቴዎስ 24:21) ይህ ወቅት የምን ያህል ጊዜ ርዝመት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ባይኖርም በዚህ ወቅት የሚደርሰው ጥፋት እስከ አሁን ድረስ በዓለም ላይ ከደረሱት ሁሉ የሚከፋ ይሆናል። ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ በምድር ላይ በሚኖሩ በአብዛኞቹ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ የሚፈጥር ነገር ይከሰታል። ይህም በጠቅላላ በሃሰት ሃይማኖት ላይ የሚደርሰው ጥፋት ነው። ሆኖም ይህ ክስተት የይሖዋ ምሥክሮች ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በጉጉት ሲጠባበቁት የነበረ ነገር ስለሆነ እነርሱን የሚያስደነግጥ አይሆንም። (ራእይ 17:1, 15-17፤ 18:1-24) የአምላክ መንግሥት መላውን የሰይጣን ሥርዓት በሚያደቅቅበት በአርማጌዶን የታላቁ መከራ ፍጻሜ ይሆናል።—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16
3. ኤርምያስ ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎች ወደፊት የሚገጥማቸውን ዕጣ የገለጸው እንዴት ነው?
3 በዚያን ወቅት ‘እግዚአብሔርን የማያውቁ’ እና ክርስቶስ ስለሚያስተዳድረው ስለ አምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሚናገረውን ‘ምሥራች የማይታዘዙ’ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “እነሆ፣ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፣ ጽኑም ዐውሎ ነፋስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይከማቹም አይቀበሩምም።”—ኤርምያስ 25:32, 33
ክፋት ይወገዳል
4. ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ማጥፋቱ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ አምላክ የሰው አገዛዝ መከራ እንደሚያስከትል ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ለማስገንዘብ ሲል ክፋትን ለብዙ ሺህ ዓመታት ታግሦ አሳልፏል። ለምሳሌ ያህል በ20ኛው መቶ ዘመን ብቻ ከ150 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት፣ በአብዮት እንቅስቃሴዎችና በሌሎች ሕዝባዊ ረብሻዎች መሞታቸውን አንድ ምንጭ ገልጿል። የሰው ልጅ አረመኔያዊ ተግባር በናዚ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አሰቃቂ በሆነ መንገድ የሞቱትን ጨምሮ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ባለቁበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በገሃድ ታይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተነበየው ጊዜያችን “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች . . . በክፋት እየባሱ” የሚሄዱበት ወቅት ሆኗል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ዛሬ የሥነ ምግባር ብልግና፣ ወንጀል፣ ዓመፅ፣ ሙስናና ለአምላክ የአቋም ደረጃዎች ንቀት ማሳየት በእጅጉ ተስፋፍተዋል። እንግዲያው ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ጥፋት ቢያመጣ ምንም የሚወቀስበት ምክንያት አይኖርም።
5, 6. በጥንቷ ከነዓን የነበረውን ክፋት ግለጽ።
5 በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ከዛሬ 3, 500 ዓመት በፊት በከነዓን ምድር ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኩሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋል” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 12:31) ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር “አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ [የ]ሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢአት ምክንያት” ነው በማለት ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 9:5) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኤች ሃሌይ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ለበኣል፣ ለአስታሮትና ለሌሎች ከነዓናውያን አማልክት የሚቀርበው አምልኮ መረን የለቀቁ የብልግና ድርጊቶችን ያቀፈ ነበር፤ ቤተ መቅደሶቻቸው የብልግና ማዕከሎች ነበሩ።”
6 ሃሌይ፣ አርኪኦሎጂስቶች ከእንዲህ ዓይነቶቹ በርካታ ቦታዎች በአንዱ “ለበኣል መሥዋዕት ሆነው በቀረቡ ሕፃናት አፅም የተሞሉ በርካታ ማሰሮዎች” ማግኘታቸውን በመግለጽ የእነዚህ ሰዎች ክፋት ምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ አመልክተዋል። እንዲህ ሲሉም ተናግረዋል:- “አካባቢው እንዳለ በሕፃናት መካነ መቃብር ተሞልቷል። . . . ከነዓናውያን የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑት በአማልክቶቻቸው ፊት የጾታ ብልግና በመፈጸምና የበኩር ልጆቻቸውን አርደው ለእነዚሁ አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። የከነዓን ምድር በጠቅላላ ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሆኖ ነበር። . . . እንዲህ ያለ አጸያፊ ድርጊትና የጭካኔ ተግባር ይፈጽም የነበረ ኅብረተሰብ እንዳለ የመቀጠል መብት ይኖረዋልን? . . . የከነዓናውያንን ከተሞች ፍርስራሽ ቆፍረው ጥናት ያደረጉ አርኪኦሎጂስቶች አምላክ ለምን ከዚያ ቀደም ብሎ እንዳላጠፋቸው በጣም ይገርማቸዋል።”
ምድርን መውረስ
7, 8. አምላክ ይህችን ምድር የሚያጸዳት እንዴት ነው?
7 አምላክ ከነዓንን እንዳጸዳ ሁሉ በቅርቡ መላውን ምድር አጽድቶ ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ይሰጣቸዋል። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) በተጨማሪም መዝሙራዊው ሲናገር “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” ብሏል። (መዝሙር 37:10, 11) እንዲሁም ሰይጣን “አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ” ይወገዳል። (ራእይ 20:1-3) አዎን፣ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17
8 ኢየሱስ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚፈልጉ ሰዎች ወደፊት የሚያገኙትን ታላቅ ተስፋ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5) ኢየሱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለውን በመዝሙር 37:29 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ መናገሩ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የይሖዋ ፈቃድ እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌ . . . ፈጥሬአለሁ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ።”—ኤርምያስ 27:5
እጹብ ድንቅ የሆነ አዲስ ዓለም
9. የአምላክ መንግሥት ምን ዓይነት ዓለም ያጎናጽፈናል?
9 ከአርማጌዶን በኋላ የአምላክ መንግሥት “ጽድቅ የሚኖርባትን” ድንቅ የሆነች “አዲስ ምድር” ያመጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13) የአርማጌዶን ተራፊዎች ከዚህ ጨቋኝ ከሆነ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መላቀቃቸው ምንኛ ግልግል ይሆንላቸዋል! ግሩም የሆኑ በረከቶችና ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው በሰማያዊው መንግሥት አገዛዝ ሥር ወደሚገኘው ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም ሲገቡ ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!—ራእይ 7:9-17
10. በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምን መጥፎ ነገሮች ይወገዳሉ?
10 ጦርነት፣ ወንጀል፣ ረሃብ ሌላው ቀርቶ የሚተናኮሉ እንስሳት እንኳ በዚያ የሚኖሩ ሰዎችን አያስፈሯቸውም። “የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ [ከሕዝቤ] ጋር እጋባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ . . . የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፣ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ።” “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። . . . ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሕዝቅኤል 34:25-28፤ ሚክያስ 4:3, 4
11. አካላዊ ሕመሞች እንደሚወገዱ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
11 ህመም፣ ሐዘን ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳን ሳይቀር ይወገዳሉ። “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም፣ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።” (ኢሳይያስ 33:24) “[እግዚአብሔር] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና . . . እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ።” (ራእይ 21:4, 5) ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ በአምላክ ኃይል እነዚህን ነገሮች የማድረግ ችሎታ እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ድጋፍ በመታገዝ በመላው የአገሪቱ ክፍል በመጓዝ አንካሶችንና የታመሙ ሰዎችን ፈውሷል።—ማቴዎስ 15:30, 31
12. ሙታን ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው?
12 ከዚህ የሚበልጥ ነገርም አድርጓል። የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል። ትሑት የሆኑ ሰዎች ይህንን ሲመለከቱ ምን ምላሽ ሰጡ? ኢየሱስ አንዲት የ12 ዓመት ልጅን ከሞት ባስነሳ ጊዜ ወላጆቿ “ታላቅ መገረም ተገረሙ።” (ማርቆስ 5:42) ኢየሱስ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን’ በሚነሱበት ወቅት በንጉሣዊ አገዛዝ ሥር በመላው ምድር ላይ ለሚያደርገው ነገር ይህ አንድ ሌላ ምሳሌ ነው። (ሥራ 24:15) ሙታን ደረጃ በደረጃ ተነስተው ከሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ጋር ዳግመኛ ሲገናኙ የሚኖረውን ደስታ አስብ! ‘ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በሚያውቁ ሰዎች እንድትሞላ’ በመንግሥቱ የበላይ ተቆጣጣሪነት ታላቅ የትምህርት መርሐ ግብር እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳይያስ 11:9
የይሖዋ ሉዓላዊነት ይረጋገጣል
13. የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛነት የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
13 በመንግሥቱ የሺህ ዓመት አገዛዝ ማብቂያ ላይ ሰብዓዊው ቤተሰብ አእምሯዊና አካላዊ ፍጽምና ያገኛል። ምድር ዓለም አቀፍ የኤደን የአትክልት ቦታ ማለትም ገነት ትሆናለች። ሰላም፣ ደስታና ፀጥታ የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ ምድር አፍቃሪ በሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ትሞላለች። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያደረገ አንድም የመንግሥት አገዛዝ አልተነሳም። በዚያን ወቅት፣ አስከፊ በሆነው ባለፈው የሰው ልጅ የብዙ ሺህ ዓመታት አገዛዝና ድንቅ በሆነው የአንድ ሺህ ዓመት የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ መካከል የሚኖረው ልዩነት ሰማይና ምድር ይሆናል! አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚኖረው አገዛዝ በሁሉም ዘርፍ የላቀ መሆኑ ይታያል። የአምላክ የመግዛት መብት ማለትም ሉዓላዊነቱ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል።
14. በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ዓመፀኞች ምን ይደርስባቸዋል?
14 በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ይሖዋ ፍጹም የሆኑት የሰው ልጆች በነፃ ምርጫቸው ተጠቅመው ማገልገል የሚፈልጉትን እንዲመርጡ ይፈቅድላቸዋል። ‘ሰይጣን ከእስራቱ እንደሚፈታ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የሰው ልጆችን ለማሳት እንደገና ሙከራ ያደርጋል። አንዳንዶች ከአምላክ አገዛዝ ማፈንገጥ ይመርጣሉ። ይሖዋ ‘መከራ ዳግም እንዳይነሳ’ ለማድረግ ሰይጣንን፣ አጋንንቱንና በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ዓመፀኛ ያጠፋል። በዚያን ጊዜ ለዘላለም እንዲጠፋ የተደረጉት ሰዎች በቂ ጊዜ አልተሰጣቸውም ወይም የተሳሳተ አካሄድ የተከተሉት ፍጽምና ስለጎደላቸው ነው ብሎ ሊከራከር የሚችል ማንም ሰው አይኖርም። አዳምና ሔዋን የአምላክን የጽድቅ ሕግ ሆነ ብለው ለመጣስ ከመምረጣቸው በፊት እንደነበሩት ፍጹም ይሆናሉ።—ራእይ 20:7-10፤ ናሆም 1:9
15. ታማኝ የሆኑት ከይሖዋ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ይመሠርታሉ?
15 በሌላው በኩል ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ ይመርጣሉ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ዓመፀኛ የሆኑት ሁሉ ስለሚጠፉ ጻድቃን የመጨረሻውን የታማኝነት ፈተና አልፈው በይሖዋ ፊት ይቆማሉ። ከዚያም ይሖዋ እነዚህን ታማኝ ሰዎች እንደ ወንድና ሴት ልጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ስለሆነም አዳምና ሔዋን ከማመፃቸው በፊት ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዓይነት ዝምድና ይመሠርታሉ። በዚህም መንገድ ሮሜ 8:21 ፍጻሜውን ያገኛል:- “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ [የሰው ዘር] ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” ነቢዩ ኢሳይያስም “[አምላክ] ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” በማለት ተንብዮአል።—ኢሳይያስ 25:8
የዘላለም ሕይወት ተስፋ
16. የዘላለም ሕይወት ሽልማትን በጉጉት መጠባበቅ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ታማኝ የሆኑ ሰዎች ወደፊት አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል! አምላክ የተትረፈረፉ መንፈሳዊና ቁሳዊ በረከቶችን ለዘላለም ያፈስስላቸዋል። መዝሙራዊው “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” በማለት ሁኔታውን በትክክል ገልጾታል። (መዝሙር 145:16) ይሖዋ ምድራዊ ክፍል የሆኑት ሰዎች ይህንን በገነት ውስጥ የመኖርን ተስፋ በእርሱ ላይ ያላቸው እምነት ክፍል አድርገው እንዲይዙት ያበረታታቸዋል። ይበልጥ አንገብጋቢው ጉዳይ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ግድድር ቢሆንም እንኳ አምላክ ምንም ዓይነት ሽልማት ከፊታቸው ሳያስቀምጥ ሰዎች እንዲሁ እንዲያገለግሉት አይጠብቅባቸውም። ለአምላክ ታማኝ መሆንና ለዘላለም የመኖር ተስፋ አንድ ክርስቲያን በአምላክ ላይ እምነት ማሳደሩ አስፈላጊ የሆነውን ያህል እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው። “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።”—ዕብራውያን 11:6
17. ኢየሱስ ተስፋችንን ለማግኘት ብለን መጽናታችን ስህተት አለመሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) እዚህ ላይ ኢየሱስ አምላክንና ዓላማዎቹን ማወቅን ይህ እውቀት ከሚያስገኘው ሽልማት ጋር አያይዞታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክፉ አድራጊ ኢየሱስ በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ እንዲያስበው ሲጠይቀው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። (ሉቃስ 23:43) እዚህ ላይ ኢየሱስ ሰውየውን ሽልማት ባታገኝም እንኳ ማመን ይኖርብሃል አላለውም። ይሖዋ አገልጋዮቹ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸውና በዚህ ዓለም ላይ የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሟቸው ይህ ተስፋ አጽንቶ እንዲያቆማቸው እንደሚፈልግ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሽልማትን መጠባበቅ በክርስትና ጎዳና ጸንቶ ለመቀጠል ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል።
የመንግሥቱ የወደፊት ዕጣ
18, 19. በሺው ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ ንጉሡና መንግሥቱ ምን ይሆናሉ?
18 መንግሥቱ ይሖዋ ምድርንና በላይዋ ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ወደ ፍጽምና ለማድረስና ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የሚጠቀምበት ሁለተኛ ደረጃ መስተዳድር እንደመሆኑ መጠን ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስና ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚያገለግሉት 144, 000ዎቹ ከሺው ዓመት ግዛት በኋላ ምን ሚና ይኖራቸዋል? “በኋላም፣ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፣ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።”—1 ቆሮንቶስ 15:24, 25
19 ክርስቶስ መንግሥቱን ለአምላክ አሳልፎ የሚሰጥ ከሆነ መንግሥቱ ለዘላለም እንደሚኖር የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የምንረዳቸው እንዴት ነው? መንግሥቱ ያከናወናቸው ነገሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ። ክርስቶስ የአምላክ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ በተጫወተው ሚና የተነሳ ለዘላለም ይከበራል። ሆኖም በዚያን ወቅት ኃጢአትና ሞት ሙሉ በሙሉ ስለሚወገዱና የሰው ልጆችም አንዴ ስለተቤዡ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የመቤዠት ሚና አይኖረውም። የመንግሥቱ የሺህ ዓመት አገዛዝም ሥራውን ሙሉ በሙሉ ስለሚፈጽም በዚያን ጊዜ በይሖዋና ታዛዥ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል የሚሆን ሁለተኛ ደረጃ መስተዳድር አያስፈልግም። ስለዚህ ‘እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆናል።’—1 ቆሮንቶስ 15:28
20. የወደፊቱ ጊዜ ለክርስቶስና ለ144, 000ዎቹ ምን እንደያዘላቸው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
20 የሺው ዓመት ግዛት ከተፈጸመ በኋላ ክርስቶስና የእርሱ ተባባሪ ገዥዎች ወደፊት ምን ሚና ይኖራቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ይሖዋ በመላው ፍጥረታቱ ላይ በርካታ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይሖዋ ለንጉሡና አብረውት ነገሥታትና ካህናት ሆነው ለሚያገለግሉት እንዲሁም ግርማ ሞገስ ለተላበሰው ለመላው ዓጽናፈ ዓለም ያለውን ዓላማ በሕይወት ኖረን ማወቅ እንችል ዘንድ ዛሬ የይሖዋን ሉዓላዊነት የምንደግፍና ለዘላለም ሕይወት የምንበቃ ያድርገን!
ለክለሳ የሚሆኑ ነጥቦች
• በቅርቡ በአገዛዝ ረገድ ምን ለውጥ እንመለከታለን?
• አምላክ በክፉዎችና በጻድቃን ላይ የሚፈርደው እንዴት ነው?
• በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ሁኔታዎች ይኖራሉ?
• የይሖዋ ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሳሉ ’
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታማኞች ከይሖዋ ጋር ትክክለኛ ዝምድና ይመሠርታሉ