የአንባብያን ጥያቄዎች
ይሖዋ በቤዛዊ መሥዋዕቱ አማካኝነት ኃጢአትን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ሆኖ ሳለ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሽማግሌዎች መናዘዝ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
ከዳዊትና ከቤርሳቤህ ታሪክ ማየት እንደሚቻለው ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ከባድ ቢሆንም እንኳ ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ምክንያት ይሖዋ ይቅር ብሎታል። ነቢዩ ናታን ቀርቦ ባነጋገረው ጊዜ ዳዊት ያለምንም ማንገራገር “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ኃጢአቱን ተናዝዟል።—2 ሳሙኤል 12:13
ይሁን እንጂ ይሖዋ ከልቡ ንስሐ የገባን ኃጢአተኛ ይቅር ከማለቱም በላይ ስህተት የፈጸመው ግለሰብ በመንፈሳዊ እንዲያገግም ለመርዳት ፍቅራዊ ዝግጅቶችን ያደርጋል። በዚህ ረገድ ዳዊት እርዳታ የተደረገለት በነቢዩ ናታን በኩል ነበር። በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሽማግሌዎች አሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ [በመንፈሳዊ] የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።”—ያዕቆብ 5:14, 15
ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ኃጢአት በመፈጸሙ ምክንያት ጸጸት የሚያብከነክነውን ሰው ለማጽናናት ማድረግ የሚችሏቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እሱን ቀርበው በሚረዱበት ጊዜ ይሖዋን ለመምሰል ይጣጣራሉ። ጠንከር ያለ ተግሣጽ መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ሸካራ ቃላትን ከመናገር ይቆጠባሉ። ከዚህ ይልቅ ሩኅሩኅ በመሆን ግለሰቡ በወቅቱ በሚያስፈልገው ነገር ላይ ያተኩራሉ። የአምላክን ቃል በመጠቀም ስህተት የፈጸመውን ክርስቲያን አስተሳሰብ ለማስተካከል በትዕግሥት ይጣጣራሉ። (ገላትያ 6:1) ግለሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ኃጢአቱን ባይናዘዝ እንኳ ናታን ቀርቦ ባነጋገረው ጊዜ ዳዊት እንዳደረገው ሽማግሌዎች ሲያነጋግሩት ንስሐ ለመግባት ይነሳሳ ይሆናል። በዚህ መንገድ ሽማግሌዎች የሚሰጡት ድጋፍ ስህተት የፈጸመው ክርስቲያን ያንን ኃጢአት ከመድገም እንዲርቅ እንዲሁም ልቡ የደነደነ ልማደኛ ኃጢአተኛ መሆን ከሚያስከትለው መዘዝ እንዲጠበቅ ይረዳዋል።—ዕብራውያን 10:26-31
አንድ ሰው አንገቱን እንዲደፋ ያደረገውን ኃጢአት ተናዝዞ ይቅር እንዲባል መጠየቅ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ውስጣዊ ጥንካሬ ይጠይቃል። እስቲ ለጥቂት ጊዜ ሌላውን አማራጭ አስብ። የሠራውን ከባድ ኃጢአት በጉባኤው ለሚገኙ ሽማግሌዎች ሳይናገር የቀረ አንድ ሰው “በውስጤ ፈጽሞ የማይጠፋ ከባድ ሥቃይ ይሰማኝ ነበር። በስብከቱ ሥራ ላይ የማደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ አደረግሁ። ሆኖም ጸጸቱ ሊወጣልኝ አልቻለም” ብሏል። በጸሎት ለአምላክ መናዘዝ ብቻ በቂ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ሆኖም ንጉሥ ዳዊት እንዳጋጠመው ያለ ስሜት ተሰምቶት ስለነበር ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (መዝሙር 51:8, 11) ይሖዋ በሽማግሌዎች አማካኝነት የሚሰጠውን ፍቅራዊ እርዳታ ማግኘቱ ምንኛ የተሻለ ነው!