ይሖዋ ከልብ የምናደርገውን ጥረት ይባርካል
“ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ።”
“ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም።”
“ስምህ ማን ነው?”
“ያዕቆብ”
“ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።”—ዘፍጥረት 32:26-28
ይህ ትኩረት የሚስብ የቃላት ምልልስ የተደረገው የ97 ዓመቱ ያዕቆብ አካላዊ ብቃቱን ያሳየበትን ከባድ ትግል ካደረገ በኋላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ ስፖርተኛ እንደሆነ አድርጎ ባይገልጸውም አንድ ሌሊት ሙሉ ከመልአክ ጋር ሲታገል አድሯል። የታገለው ለምን ነበር? ይሖዋ ለቅድመ አያቱ የሰጠው ተስፋ ማለትም ውርሻው በጣም ስላሳሰበው ነበር።
ከብዙ ዓመታት በፊት ወንድሙ ኤሳው በአንድ ሳህን ምስር ወጥ ብኩርናውን አሳልፎ ሰጥቶት ነበር። አሁን ኤሳው 400 ሰዎችን አስከትሎ ወደ እሱ እየገሰገሰ እንዳለ ሰማ። ፍርሃት የገባው ያዕቆብ ቤተሰቡ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር የሚገኘውን ምድር እንደሚወርስ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም እንዲያረጋግጥለት በጸሎት ጠየቀ። ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ ወሳኝ እርምጃዎችንም ወሰደ። እየቀረበ ወዳለው ኤሳው ጠቀም ያለ እጅ መንሻ ላከ። ከዚያም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ለሁለት በመክፈል እንዲሁም ሚስቶቹና ልጆቹ የያቦቅን ወንዝ እንዲሻገሩ በማድረግ የመከላከያ ስልት ቀየሰ። ከዚህ በኋላ ደግሞ ከብርቱ ጥረትና እንባ ጋር ‘በፊቱ ሞገስን ለማግኘት’ ከአንድ መልአክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ሲታገል አደረ።—ሆሴዕ 12:4 አ.መ.ት፤ ዘፍጥረት 32:1-32
ያዕቆብ ከሁሉ አብልጦ ይወዳት የነበረችው ሁለተኛ ሚስቱ ራሔል የተወችውን ምሳሌ ደግሞ ተመልከት። ይሖዋ ያዕቆብን ለመባረክ ቃል እንደገባ በሚገባ ታውቅ ነበር። የያዕቆብ የመጀመሪያ ሚስት የሆነችው ልያ አራት ልጆችን ስትወልድ እሷ ግን መካን ነበረች። (ዘፍጥረት 29:31-35) ራሔል በደረሰባት ሁኔታ ቁጭ ብላ ከመቆዘም ይልቅ ይሖዋን ደጋግማ በጸሎት ትለምንና ከጸሎቷ ጋር የሚስማሙ እርምጃዎችን ትወስድ ነበር። ቅድመ አያቷ ሣራ በአጋር እንዳደረገችው ራሔልም ‘ከሷ የሚወለዱት ልጆች ለራስዋ እንዲሆኑላት’ አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው። ባላ ዳንና ንፍታሌም የተባሉ ሁለት ልጆች ከያዕቆብ ወለደች። ራሔል ንፍታሌም ሲወለድ “ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፣ አሸነፍሁም!” በማለት ልጅ ለማግኘት የነበራትን ከፍተኛ ምኞት ገልጻለች።a በኋላም ራሔል ዮሴፍና ብንያም የተባሉ ልጆችን በመውለድ ተባርካለች።—ዘፍጥረት 30:1-8፤ 35:24
ይሖዋ ያዕቆብና ራሔል ያሳዩትን ጥረት የባረከው ለምንድን ነው? የይሖዋን ፈቃድ በማስቀደማቸውና ውርሻቸውን ከፍ አድርገው በመመልከታቸው ነው። አምላክ እንዲባርካቸው ልባዊ ጸሎት ያቀረቡ ሲሆን ከእሱ ፈቃድና ካቀረቡት ልመና ጋር የሚስማሙ እርምጃዎችንም ወስደዋል።
ዛሬም ቢሆን ብዙዎች ልክ እንደ ያዕቆብና እንደ ራሔል የይሖዋን በረከት ለማግኘት ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከራሳቸው ተሞክሮ ሊናገሩ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ጥረቶቻቸው በእንባ፣ በተስፋ መቁረጥና በብስጭት የተሞሉ ናቸው። ኤልዛቤት የተባለች አንዲት ክርስቲያን እናት ለረጅም ጊዜ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከቀረች በኋላ በድጋሚ መሰብሰብ ለመጀመር ምን ያህል ጥረት እንደጠየቀባት ታስታውሳለች። አምስት ትናንሽ ወንዶች ልጆችና የማያምን ባል የነበራት ሲሆን በአቅራቢያዋ ወዳለው የመንግሥት አዳራሽ ለመሄድ 30 ኪሎ ሜትር በመኪና መጓዝ ነበረባት። እነዚህ ሁኔታዎች በስብሰባ ላይ መገኘትን ፈታኝ አድርገውባት ነበር። “አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ራስን መገሰጽ የሚጠይቅ ቢሆንም ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ጠቃሚ እንደሆነ አውቅ ነበር። ልጆቼ ሊከተሉት የሚገባው የሕይወት መንገድ ይህ መሆኑን እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።” ይሖዋ ያደረገችውን ጥረት ባርኮላታል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ሦስት ልጆቿ ውስጥ ሁለቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ልጆችዋ ባደረጉት መንፈሳዊ እድገት በመደሰት “በመንፈሳዊ ከእኔ የላቀ እድገት አድርገዋል” በማለት ተናግራለች። ልባዊ ጥረት በማድረጓ ምንኛ ተባርካለች!
ከልብ የሚደረግ ጥረትን ይሖዋ ይባርካል
ከልብ ጥረት ማድረግና ጠንክሮ መሥራት በረከት ያስገኛል። አንድን ሥራ ወይም ኃላፊነት ለመወጣት ተጨማሪ ጥረት ባደረግን መጠን የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እርካታ እናገኛለን። ይሖዋ የፈጠረንም እንደዚያ አድርጎ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 3:13፤ 5:18, 19) ይሖዋ እንዲባርከን ከፈለግን ግን ጥረታችን ዓላማውን የሳተ መሆን የለበትም። ለምሳሌ ያህል፣ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በሁለተኛ ደረጃ እንድናስቀምጥ የሚያደርግን አኗኗር ይሖዋ ይባርክልናል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነውን? ራሱን ለአምላክ የወሰነ አንድ ክርስቲያን እምነት በሚገነቡና መመሪያ በሚሰጥባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ እንዳይገኝ የሚያደርግ ሥራ ቢይዝ ወይም የደረጃ ዕድገት ቢቀበል የይሖዋን ሞገስ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ ሊያደርግ ይችላልን?—ዕብራውያን 10:23-25
አንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራ የሚሠራው ወይም ቁሳዊ ብልጽግና ለማግኘት የሚጥረው መንፈሳዊ ጉዳዮችን ችላ ብሎ ከሆነ ዕድሜውን ሙሉ ጠንክሮ ቢሠራም ‘ደስተኛ’ ላይሆን ይችላል። ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ ዓላማውን የሳተ ጥረት የሚያስከትለውን ውጤት ገልጿል። ‘በእሾህ መካከል የተዘራውን’ ዘር አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፣ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፣ የማያፈራም ይሆናል” ብሏል። (ማቴዎስ 13:22) ጳውሎስም ስለዚሁ ወጥመድ ካስጠነቀቀ በኋላ ቁሳዊ ሃብትን የሚያሳድዱ ሰዎች “በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” በማለት አክሎ ተናግሯል። እንዲህ ካለው መንፈሳዊ ውድቀት ሊያስከትል ከሚችል ጎዳና መራቅ የሚቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስ በመቀጠል ‘ከዚህ ሽሹ . . . ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ አታድርጉ’ በማለት ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 11, 17
በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ እንገኝ ወይም ይሖዋን የቱንም ያህል ለረጅም ዓመት እናገልግል ሁላችንም ልባዊ ጥረት በማድረግ ረገድ ያዕቆብና ራሔል ያሳዩትን ምሳሌ በመኮረጅ ልንጠቀም እንችላለን። የገጠሟቸው ሁኔታዎች የቱንም ያህል አስፈሪና ተስፋ አስቆራጭ ሊሆኑ ቢችሉም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ መንፈሳዊ ውርሻቸውን ላፍታም ቢሆን አልዘነጉም። ዛሬም ካሉብን ውጥረቶችና ችግሮች የተነሳ በፍርሃት ልንርድ፣ ተስፋ ልንቆርጥ አልፎ ተርፎም በጭንቀት ልንዋጥ እንችላለን። ፈተናው የሚደርስብን እጃችንን ሰጥተን ትግሉን እንድናቆምና የሰይጣን ጥቃት ሰለባ እንድንሆን ለማድረግ ነው። ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ከእነዚህም መካከል መዝናኛን ወይም ጨዋታን፣ ስፖርትን ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን እንዲሁም ሰብዓዊ ሥራዎችን ወይም ቁሳዊ ብልጽግናን እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። አብዛኛውን ጊዜ ሊጨበጡ የማይችሉ የሚያጓጉ ተስፋዎችን ያቀርብልናል። ተታልለው ወይም ተስበው እነዚህን ነገሮች ማሳደድ የጀመሩ ብዙውን ጊዜ መጨረሻቸው ብስጭት ነው። በጥንት ጊዜ እንደነበሩት ያዕቆብና ራሔል እኛም በብርቱ በመታገል የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች እንቋቋም።
‘ሁኔታው ተስፋ የለውም፤ ከአሁን በኋላ ምንም ብፍጨረጨር ለውጥ አላመጣም’ በሚል ስሜት መሸነፋችንን አምነን ስንቀበል መመልከትን የመሰለ ዲያብሎስን የሚያስደስተው ነገር የለም። እንግዲያው ‘የሚወደኝ የለም፤ ይሖዋ ጨርሶ ረስቶኛል’ ብለን በማሰብ ውድቀታችንን ሊያፋጥን የሚችል መንፈስ እንዳናዳብር መጠንቀቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ለእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ መንበርከክ ራስን መጉዳት ነው። እንዲህ ያለ አስተሳሰብ መያዛችን እጃችንን እንደሰጠንና ይሖዋ አንድ ነገር እስኪያደርግልን ድረስ መታገላችንን እንዳቆምን የሚያሳይ ይሆን? ይሖዋ የሚባርከው ከልብ የምናደርገውን ጥረት እንደሆነ አስታውስ።
የይሖዋን በረከት ለማግኘት መታገላችሁን ቀጥሉ
መንፈሳዊ ደህንነታችን በእጅጉ የተመካው ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን የሚመለከቱ ሁለት መሠረታዊ እውነታዎችን በመገንዘባችን ላይ ነው። (1) ችግር፣ ሕመም ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ የሚደርስብን እኛ ብቻ አይደለንም፣ (2) ይሖዋ እንዲረዳቸውና እንዲባርካቸው ከልብ የሚለምኑትን ሰዎች ጸሎት ይሰማል።—ዘጸአት 3:7-10፤ ያዕቆብ 4:8, 10፤ 1 ጴጥሮስ 5:8, 9
ሁኔታዎችህ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆኑ ወይም አቅምህ የቱንም ያህል ውስን እንደሆነ ቢሰማህ ‘ቶሎ የሚከበን ኃጢአት’ ተብሎ ለተገለጸው ለእምነት ማጣት እጅህን መስጠት አይኖርብህም። (ዕብራውያን 12:1) በረከት እስክታገኝ ድረስ መታገልህን ቀጥል። በረከት ለማግኘት አንድ ሌሊት ሙሉ የታገለውን አረጋዊውን ያዕቆብ በማስታወስ ትዕግሥተኛ ሁን። በክረምት ዘሩን ከዘራ በኋላ መከሩ እስኪደርስ እንደሚጠባበቅ ገበሬ መንፈሳዊ እንቅስቃሴህ የቱንም ያህል አነስተኛ ቢሆን ይሖዋ እስኪባርከው ድረስ በትዕግሥት ተጠባበቅ። (ያዕቆብ 5:7, 8) “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ” የሚሉትን የመዝሙራዊው ቃላት ሁልጊዜ አስታውስ። (መዝሙር 126:5፤ ገላትያ 6:9) ጸንተህ ቁም፤ እንደ ሌሎች ሁሉ አንተም መታገልህን ቀጥል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሕጉ ቃል ኪዳን ከመሰጠቱ በፊት ከሚስት ሌላ ቁባት የማግባት ልማድ የነበረ ሲሆን ሕጉ ከተሰጠ በኋላም ተቀባይነት አግኝቶ በሕጉ ውስጥ ተካትቶ ነበር። አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ ያቋቋመውን አንድ ወንድ ከአንድ ሴት ጋር የሚለውን የጋብቻ ሥርዓት መሲሁ ከመገለጡ በፊት ተግባራዊ ማድረግ አልፈለገም። እንዲያውም የቁባቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል ሕግ አውጥቷል። ቁባት ማግባት የእስራኤል ሕዝብ በፍጥነት ማደግ ይችል ዘንድ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል።