ይሖዋ ስለ እናንተ ያስባል
“እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:7
1. ይሖዋ እና ሰይጣን ፍጹም ተቃራኒ የሆኑት በምንድን ነው?
ይሖዋ እና ሰይጣን ፈጽሞ ተቃራኒዎች ናቸው። አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ሲቀርብ በዲያብሎስ እየተጠላ ይሄዳል። በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት አንድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ (1970) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የሰይጣንን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲህ በማለት ይናገራል:- ‘የሰይጣን ሥራ የሚከሰውን ሰው ለማግኘት በምድር ላይ መዞር ነው፤ ዓላማው ጥሩ ምግባር ያላቸውን ሰዎች ለማጽናት በመላው ምድር ከሚመለከቱት “ከጌታ ዓይኖች” የተለየ ነው። (II ዜና xvi, 9) ሰይጣን፣ ሰዎች ጥሩነትን የሚያሳዩት በራስ ወዳድ መንፈስ ተነሳስተው ነው የሚል ክስ ያስነሳ ሲሆን አምላክ ከወሰነለት ገደብና ሥልጣን እንዲሁም ከእርሱ ቁጥጥር ሥር ሳይወጣ ይህ አባባሉ እውነት መሆኑን እንዲያረጋግጥ ተፈቅዶለታል።’ በእርግጥም በሁለቱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ!—ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7
2, 3. (ሀ) “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? በኢዮብ ላይ ከደረሰው ነገር የስሙን ትርጉም በግልጽ ማየት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን በምድር ላይ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮችን መክሰሱን እንዳላቆመ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
2 “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል “ሐሰተኛ ከሳሽ፣” “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ሰይጣን “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?” በማለት ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በራስ ወዳድነት መንፈስ ተነሳስቶ ነው የሚል ክስ እንደሰነዘረ የኢዮብ መጽሐፍ ይናገራል። (ኢዮብ 1:9) ኢዮብ ፈተናዎችና መከራዎች ቢፈራረቁበትም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረበ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዘገባ ያሳያል። (ኢዮብ 10:9, 12፤ 12:9, 10፤ 19:25፤ 27:5፤ 28:28) ከመከራው በኋላ አምላክን “መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ” ብሎታል።—ኢዮብ 42:5
3 ሰይጣን ከኢዮብ በኋላ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን መክሰሱን አቁሟልን? በጭራሽ። የራእይ መጽሐፍ ሰይጣን በዚህ በመጨረሻው ዘመን የክርስቶስን ቅቡዓን ወንድሞችና ታማኝ አጋሮቻቸውን መክሰሱን እንደቀጠለ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ ራእይ 12:10, 17) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ለሚያስብልን አምላክ ለይሖዋ ራሳችንን በማስገዛትና ከልብ በመነጨ ፍቅር ተነሳስተን እርሱን በማገልገል የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን የይሖዋን ልብ ደስ እናሰኛለን።—ምሳሌ 27:11
ይሖዋ ምንጊዜም እኛን መርዳት ይፈልጋል
4, 5. (ሀ) ከሰይጣን በተቃራኒ ይሖዋ ወደ ምድር የሚመለከተው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ በእኛ በኩል ምን እንድናደርግ ይጠበቅብናል?
4 ዲያብሎስ የሚከስሰውንና የሚውጠውን ለመፈለግ በምድር ላይ ይዞራል። (ኢዮብ 1:7, 9፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) በተቃራኒው ደግሞ ይሖዋ ብርታት የሚያሻቸው ሰዎችን ለመርዳት ይፈልጋል። ነቢዩ አናኒ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” በማለት ለንጉሥ አሳ ነግሮታል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ጥላቻን በተሞላው በሰይጣንና ፍቅራዊ እንክብካቤ በሚያደርገው በይሖዋ መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው!
5 ይሖዋ እኛን የሚመለከተን ስህተታችንንና ጉድለታችንን ለመለቃቀም አይደለም። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 130:3) መልሱ በፊቱ ሊቆም የሚችል ማንም የለም የሚል ነው። (መክብብ 7:20) በፍጹም ልብ ወደ ይሖዋ ብንቀርብ እኛን ለመኮነን ሳይሆን ጥረታችንን ተመልክቶ እኛን ለመርዳትና ምህረት እንዲያደርግልን ወደ እርሱ የምናቀርበውን ልመና ለመስማት ዓይኖቹን ወደ እኛ ይመልሳል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፣ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 3:12
6. በዳዊት ላይ የደረሰው ሁኔታ ለእኛ መጽናኛ የሚሆነው እንዴት ነው? ምንስ ማስጠንቀቂያ ይዟል?
6 ዳዊት ፍጽምና የጎደለው ከመሆኑም በላይ ከባድ ኃጢአት ሰርቶ ነበር። (2 ሳሙኤል 12:7-9) ሆኖም የልቡን ግልጽልጽ አድርጎ ለይሖዋ በመናገር በጸሎት ወደ እርሱ ቀረበ። (መዝሙር 51:1-12፤ በመዝሙሩ አናት ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት።) ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ካስከተለበት መዘዝ ነፃ ባይሆንም እንኳ ይሖዋ ጸሎቱን ሰምቶ ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙኤል 12:10-14) ይህ ዘገባ ለእኛ ማጽናኛና ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። ከልብ ንስሐ ከገባን ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለን ማወቃችን የሚያጽናናን ቢሆንም እንኳ ኃጢአት መሥራት ብዙውን ጊዜ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል ማወቁም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። (ገላትያ 6:7-9) ወደ ይሖዋ ተጠግተን መኖር የምንፈልግ ከሆነ እርሱን ከሚያሳዝን ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል።—መዝሙር 97:10
ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ራሱ ይስባል
7. ይሖዋ የሚመለከተው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? ወደ እርሱ የሚስባቸውስ እንዴት ነው?
7 ዳዊት በአንድ መዝሙር ላይ “እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፣ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 138:6) በተመሳሳይም አንድ ሌላ መዝሙር “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤ በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ . . . ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ” ይላል። (መዝሙር 113:5-7) አዎን፣ ሁሉን ቻይ የሆነው የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ በምድር ላይ ያሉትን ለመመልከት ራሱን ዝቅ ያደርጋል። ዓይኖቹም “የተዋረዱትን፣” “ችግረኞችን፣” ‘ስለ ተሠራው ርኩሰት ሁሉ የሚያለቅሱና የሚተክዙ’ ሰዎችን ይመለከታሉ። (ሕዝቅኤል 9:4) በልጁ አማካኝነት እነዚህን ሰዎች ወደ እርሱ ይስባቸዋል። ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም . . . ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 6:44, 65
8, 9. (ሀ) ሁላችንም ወደ ኢየሱስ መቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የቤዛውን ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
8 ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኛ ሆነው የተወለዱና ከአምላክ የራቁ በመሆናቸው ወደ ኢየሱስ መቅረብና በቤዛው መሥዋዕት ላይ እምነት ማሳደር ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 3:36) ከአምላክ ጋር እርቅ መፍጠር ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) አምላክ ኃጢአተኛ ሰዎች ከእርሱ ጋር ሰላም መፍጠር የሚችሉበትን መንገድ እንዲያዘጋጅ እስኪጠይቁት ድረስ አልጠበቀም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። . . . ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፣ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 5:8, 10
9 ሐዋርያው ዮሐንስ “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም” ብሎ በመጻፍ አምላክ ሰዎችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እርምጃ መውሰዱን የሚገልጸውን ውድ እውነት አስረግጦ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ቅድሚያውን የወሰዱት ሰዎች ሳይሆኑ አምላክ ራሱ ነው። “ኃጢአተኞች” ብቻ ሳይሆን ‘ጠላቶቹ’ ለሆንነው ለሰው ልጆች እንዲህ ያለ ከፍተኛ ፍቅር ወደሚያሳየን አምላክ ለመቅረብ ይበልጥ አትገፋፋም?—ዮሐንስ 3:16
ይሖዋን መፈለግ ይኖርብናል
10, 11. (ሀ) ይሖዋን ለመፈለግ ምን ማድረግ አለብን? (ለ) የሰይጣንን ዓለም እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
10 እርግጥ ነው ይሖዋ ወደ እርሱ እንድንቀርብ አያስገድደንም። ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ ባለመሆኑ እርሱን ፈልገን ማግኘት’ ይገባናል። (ሥራ 17:26, 27) ይሖዋ እንድንገዛለት እኛን የመጠየቅ መብት እንዳለው ማወቅ ይገባናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፣ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፣ ልባችሁን አጥሩ” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:7, 8) ሰይጣንን በመቃወም ከይሖዋ ጎን መቆማችንን ለማሳየት ፈጽሞ ማቅማማት አይገባንም።
11 ይህም ክፉ ከሆነው የሰይጣን ዓለም ርቀን እንድንኖር ይጠብቅብናል። ያዕቆብ በመጨመር “ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:4) በተቃራኒው የይሖዋ ወዳጆች ስንሆን የሰይጣን ዓለም ይጠላናል ብለን መጠበቅ ይገባናል።—ዮሐንስ 15:19፤ 1 ዮሐንስ 3:13
12. (ሀ) ዳዊት ምን የሚያጽናኑ ቃላት ጽፏል? (ለ) ይሖዋ በነቢዩ ዓዛርያስ አማካኝነት ምን ማስጠንቀቂያ ተናግሯል?
12 ከሰይጣን ዓለም ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ በጸሎት ወደ ይሖዋ ቀርበን እንዲረዳን መጠየቅ ይኖርብናል። የይሖዋን የማዳን እጅ በተደጋጋሚ የተመለከተው ዳዊት እንዲህ የሚል የሚያጽናና ቃል ጽፎልናል:- “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።” (መዝሙር 145:18-20) ይህ መዝሙር በግለሰብ ደረጃ ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ ሊያድነን እንደሚችልና ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ደግሞ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ እንደሚያድናቸው ያሳያል። (ራእይ 7:14) እኛ ወደ ይሖዋ ከቀረብን እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል። ነቢዩ ዓዛርያስ ‘በአምላክ መንፈስ’ ተመርቶ “እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብተተዉት ግን ይተዋችኋል” በማለት እንደ አንድ መሠረታዊ እውነት አድርገን ልንወስደው የምንችለውን ሃሳብ ተናግሯል።—2 ዜና መዋዕል 15:1, 2
ይሖዋ እውን ሊሆንልን ይገባል
13. ይሖዋ ለእኛ እውን እንደሆነልን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” በማለት ስለ ሙሴ ጽፏል። (ዕብራውያን 11:27) ሙሴ ይሖዋን ቃል በቃል አይቶት እንደማያውቅ የታወቀ ነው። (ዘጸአት 33:20) ሆኖም ይሖዋ ለእርሱ እውን ከመሆኑ የተነሳ እርሱን ያየው ያህል ነበር። በተመሳሳይም ኢዮብ ከደረሰበት መከራ በኋላ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ መከራ እንዲደርስባቸው ቢፈቅድም ፈጽሞ የማይተዋቸው አምላክ መሆኑን በእምነት ዓይኑ ጥርት አድርጎ ማየት ችሎ ነበር። (ኢዮብ 42:5) ሔኖክና ኖኅም ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር’ እንዳደረጉ ተነግሮላቸዋል። አምላክን ለማስደሰት በመፈለግና እርሱን በመታዘዝ ይህን አድርገዋል። (ዘፍጥረት 5:22-24፤ ዘፍጥረት 6:9, 22፤ ዕብራውያን 11:5, 7) ይሖዋ ለሔኖክ፣ ለኖኅ፣ ለኢዮብ እና ለሙሴ እውን እንደነበረው ሁሉ ለእኛም እውን ከሆነልን በመንገዳችን ሁሉ እርሱን ‘እናውቀዋለን’፤ ‘እርሱም ጎዳናችንን ያቀናልናል።’—ምሳሌ 3:5, 6
14. ከይሖዋ ጋር ‘መጣበቅ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
14 እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ደፍ ላይ ቆመው ሳለ ሙሴ እንዲህ በማለት መከራቸው:- “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ተከተሉ፣ እርሱንም ፍሩ፣ ትእዛዙንም ጠብቁ፣ ቃሉንም ስሙ፣ እርሱንም አምልኩ፣ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።” (ዘዳግም 13:4) ይሖዋን መከተል፣ መፍራት፣ መታዘዝና ከእርሱ ጋር መጣበቅ ነበረባቸው። እዚህ ላይ “መጣበቅ” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል በማስመልከት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲናገሩ “[የዕብራይስጡ] ቃል በጣም መቀራረብንና በቅርብ ወዳጅነት መፍጠርን ያመለክታል” ብለዋል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው [“ወዳጃቸው፣” የ1980 ትርጉም ] ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 25:14) ይሖዋ ለእኛም እውን ሆኖ የሚታየንና ለእርሱ ካለን ፍቅር የተነሳ እርሱን ላለማሳዘን የምንፈራው ከሆነ እኛም ከእርሱ ጋር ውድና የቅርብ ዝምድና ልንመሠርት እንችላለን።—መዝሙር 19:9-14
ይሖዋ እንደሚያስብልህ ሆኖ ይሰማሃል?
15, 16. (ሀ) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደሚያስብ ከመዝሙር 34 መገንዘብ የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ያደረገልንን ጥሩ ነገር ለማስታወስ የምንቸገር ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች መካከል አንዱ አምላካችን ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስብ መሆኑን እንድንዘነጋ ማድረግ ነው። የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት በጣም አደገኛ ሁኔታ ገጥሞት በነበረበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር የይሖዋ ጥበቃ እንዳልተለየው ያውቅ ነበር። በጌት ንጉሥ በአንኩስ ፊት ያበደ ሰው መስሎ በመቅረቡ ተባርሮ በወጣ ጊዜ የሚከተሉትን የእምነት መግለጫዎች የያዘ አንድ ውብ መዝሙር ተቀኝቶ ነበር:- “እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፣ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፣ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል። እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።”—መዝሙር 34:3, 4, 7, 8, 18, 19፤ 1 ሳሙኤል 21:10-15
16 በይሖዋ የማዳን ኃይል ትታመናለህ? የመላእክቱ ጥበቃ እንዳለህ ይሰማሃል? ይሖዋ ጥሩ አምላክ እንደሆነ በግልህ ቀምሰኸዋል? ይሖዋ ጥሩነቱን እንዳሳየህ ሆኖ የተሰማህ መቼ ነው? እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። በአገልግሎት ላይ እያለህ ደክሞህ ከዚህ በላይ መሥራት አልችልም ብለህ አስበህ ሳለ የመጨረሻውን ቤት ለማንኳኳት የሚያስችል ብርታት ባገኘህበት ወቅት ይሆን? ምናልባት ከቤቱ ባለቤት ጋር አስደሳች ውይይት አድርገህ ይሆናል። የሚያስፈልግህን ብርታት ስለሰጠህና ስለባረከህ ሳትረሳ ይሖዋን አመስግነኸዋል? (2 ቆሮንቶስ 4:7) በሌላው በኩል ደግሞ ይሖዋ ያደረገልህን ጥሩ ነገሮች ለማስታወስ ትቸገር ይሆናል። ከሳምንት፣ ከወር፣ ከዓመት ወይም ከዚያ በላይ ወደኋላ ተመልሰህ ለማስታወስ ብትሞክርም ትዝ የሚልህ ምንም አይኖር ይሆናል። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብና እንዴት እየመራህ እንዳለ ለማወቅ ለምን ልባዊ ጥረት አታደርግም? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ክርስቲያኖችን ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ምን ያህል እንደተንከባከበህ ስታውቅ በጣም ትገረማለህ!—መዝሙር 73:28
ይሖዋን መፈለጋችሁን ቀጥሉ
17. ይሖዋን ሳያቋርጡ ለመፈለግ ምን ያስፈልጋል?
17 ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና እያደር እየጠበቀ መሄድ ይኖርበታል። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ ለማወቅ በእኛ በኩል ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” ለመገንዘብ መጸለይና የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ማግኘት ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 2:10፤ ሉቃስ 11:13) መንፈሳዊ ምግብ “በጊዜው” በመስጠት አእምሯችንን የሚመግብልን “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠው መመሪያም ያስፈልገናል። (ማቴዎስ 24:45) ይሖዋ በዚህ የመገናኛ መሥመር አማካኝነት ቃሉን በየዕለቱ እንድናነብ፣ አዘውትረን በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝና ‘በመንግሥቱ ወንጌል’ የስብከት ሥራ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንድናደርግ ይመክረናል። (ማቴዎስ 24:14) እንዲህ ካደረግን የሚያስብልንን አምላክ ይሖዋን መፈለጋችንን እንዳላቋረጥን እናሳያለን።
18, 19. (ሀ) ምን ለማድረግ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል? (ለ) ሰይጣንን በጽናት የምንቃወምና ሳናቋርጥ ይሖዋን የምንፈልግ ከሆነ የምንባረከው እንዴት ነው?
18 ሰይጣን በአራቱም ማዕዘናት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስደት፣ ተቃውሞና ተጽዕኖ ለማምጣት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ሰላማችንን ለማደፍረስና በአምላክ ፊት ያለንን ጥሩ አቋም ለማበላሸት ይጥራል። በአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊነት ላይ በተነሳው ግድድር ከይሖዋ ጎን የሚቆሙ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን ለመፈለግና ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት በአጭር ለመቅጨት ይፈልጋል። ሆኖም ከክፉው እንደሚያድነን እርግጠኞች በመሆን ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ለመቆም ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጸንተን እንኑር። የአምላክ ቃል እንዲመራን የምንፈቅድና በሚታየው ድርጅቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የምናደርግ ከሆነ ሁልጊዜ የእርሱን ድጋፍ እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 41:8-13
19 ስለዚህ ሁላችንም እኛን ሁልጊዜ ‘ለማጽናትና ለማበርታት’ የሚፈልገውን ውድ አምላካችንን ይሖዋን ሳናቋርጥ በመፈለግ ሰይጣንንና መሠሪ ዘዴዎቹን በጽናት እንቃወም። (1 ጴጥሮስ 5:8-11) እንዲህ ካደረግን ‘ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እየተጠባበቅን በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችንን እንጠብቃለን።’—ይሁዳ 21
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ስሙ ለእርሱ የሚስማማ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
• ይሖዋ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን የሚያይበት መንገድ ከዲያብሎስ የሚለየው እንዴት ነው?
• አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በቤዛው ማመን ያለበት ለምንድን ነው?
• ከይሖዋ ጋር ‘መጣበቅ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋን ሳናቋርጥ መፈለግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ መከራ ቢደርስበትም የይሖዋ እንክብካቤ እንዳልተለየው አውቋል
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ በክርስቲያን ስብሰባ ላይ አዘውትሮ መገኘትና በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ይሖዋ የሚያስብልን መሆኑን እንድናስታውስ ይረዳናል