ደስታ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
ከጥቂት ዓመታት በፊት በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በታላቋ ብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ ሰዎች “የደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ጥያቄው ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት ጥሩ ጤንነት ወሳኝ ነገር እንደሆነ ሲናገሩ 79 በመቶዎቹ አስደሳች ትዳር ወይም ጥሩ የትዳር ጓደኛ፣ 62 በመቶዎቹ ልጅ ወልዶ ማሳደግ እንዲሁም 51 በመቶ የሚያህሉት ደግሞ አርኪ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ብዙዎች ገንዘብ ደስታን እንደማያስገኝ ሲነገር የሚሰሙ ቢሆንም እንኳ መጠይቁ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ገንዘብ ደስታ ያስገኛል ብለው ያምናሉ። ይሁንና ይህ ሐቅ ምን ያሳያል?
በመጀመሪያ፣ በገንዘብና በደስታ መካከል አለ ስለሚባለው ግንኙነት እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመጨረሻ ሀብታም በሆኑ አንድ መቶ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት ሀብታሞቹ ከአጠቃላዩ ሕዝብ የተለየ ደስታ እንደሌላቸው አስገንዝቧል። ከዚህም በላይ የአእምሮ ጤና ሕክምና ጠበብት እንደሚናገሩት በዩናይትድ ስቴትስ ብዙዎች ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ቁሳዊ ሀብታቸውን በሁለት እጥፍ ገደማ ቢያሳድጉም ከበፊቱ የተሻለ ደስታ አላገኙም። እንዲያውም አንድ ዘገባ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “በእነዚሁ ዓመታት የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። ራሳቸውን የሚያጠፉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ አድጓል። ፍቺ በእጥፍ ጨምሯል።” በገንዘብና በደስታ መካከል ያለውን ዝምድና በሚመለከት በ50 አገሮች በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ገንዘብ ደስታን ሊገዛ አይችልም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
እስቲ ደግሞ ጥሩ ጤንነት፣ ደስታ የሰፈነበት ትዳርና አርኪ ሥራ ከደስታ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንመልከት። ደስተኛ ለመሆን እነዚህ ነገሮች የግድ አስፈላጊ ቢሆኑ ኖሮ ጥሩ ጤንነትና ስኬታማ ትዳር የሌላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን ይውጣቸው ነበር? ልጅ ያልወለዱ ባልና ሚስቶች እንዲሁም አርኪ ሥራ የሌላቸው ወንዶችና ሴቶችስ ምን ይሆኑ ነበር? እነዚህ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ደስተኛ መሆን አይችሉም ማለት ነው? ጥሩ ጤንነትና ደስታ የሰፈነበት ትዳር ያላቸው ሰዎች ሁኔታቸው ቢለወጥ አላቸው የሚባለው ደስታ ዘላቂነት ይኖረዋል?
ደስታን የምንፈልገው ከትክክለኛ ምንጭ ነው?
ደስተኛ መሆን የማይፈልግ ሰው የለም። የሰው ልጆች ፈጣሪ “ደስተኛ አምላክ” ስለተባለና ሰውም በአምላክ መልክ ስለተፈጠረ ይህ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ ዘፍጥረት 1:26, 27) በመሆኑም ሰዎች ደስተኛ ለመሆን መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ ነው። ይሁን እንጂ፣ ብዙ ሰዎች ደስታን ማግኘት አሸዋን ከመጨበጥ ተለይቶ እንደማይታይ ይሰማቸዋል። ሁለቱም በቀላሉ ያመልጣሉ።
ይህ ሊሆን የቻለው አንዳንዶች ደስታ ለማግኘት ከልክ ያለፈ ጥረት በማድረጋቸው ይሆን? የማኅበራዊ ኑሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤሪክ ሆፈር እንደዚያ ይሰማቸዋል። ይህን በሚመለከት “ለደስታ ማጣት ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ደስታ ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ነው” ብለዋል። ደስታን ተገቢ ካልሆነ ምንጭ ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ይህ አባባል እውነት ከመሆኑም በላይ ተስፋ መቁረጣችንና ለሐዘን መዳረጋችን የማይቀር ነው። ሀብታም ለመሆን መጣጣር፣ ዝና ወይም ታዋቂነት ለማትረፍ መሯሯጥ፣ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊው ወይም በኢኮኖሚው መስክ አንድ ዓይነት ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር አሊያም በግል ጥቅም እንዲሁም በቅጽበታዊ ደስታ ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት አንዳቸውም ቢሆኑ ደስታ አያስገኙም። አንዳንዶች “ደስተኛ ለመሆን የምናደርገውን ጥረት ካቆምን ደስተኛ መሆን እንችላለን” በማለት በምጸት ከተናገሩት ደራሲ ጋር መስማማታቸው ምንም አያስደንቅም!
በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ጥናት ከአሥር ሰዎች መካከል አራቱ ጥሩ በማድረግና ሌሎችን በመርዳት ደስታ ይገኛል ብለው እንደሚያምኑ ጨምሮ አመልክቷል። እንዲሁም ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ ደስተኛ በመሆን ረገድ ሃይማኖታዊ እምነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ ደስታ ለማግኘት በእርግጥ ምን እንደሚያስፈልግ በጥልቀት መመርመራችን አስፈላጊ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንድናደርግ ይረዳናል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች የደስታ ቁልፉ ገንዘብ፣ ደስታ የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት ወይም አርኪ ሥራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተስ በዚህ ትስማማለህ?