የአምላክ ቃል መንገዳችሁን እንዲያበራላችሁ ፍቀዱ
‘ሕግህ . . . ለመንገዴ ብርሃን ነው።’—መዝሙር 119:105
1, 2. የይሖዋ ቃል ለመንገዳችን ብርሃን የሚሆንልን ምን ካደረግን ነው?
እኛ ፈቃደኞች እስከሆንን ድረስ የይሖዋ ቃል ለመንገዳችን ያበራልናል። ከእንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ብርሃን ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በጽሑፍ የሠፈረውን የአምላክ ቃል በትጋት ማጥናትና ምክሩን በሥራ ማዋል ይኖርብናል። እኛም እንደ መዝሙራዊው “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ልንል የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—መዝሙር 119:105
2 አሁን ደግሞ መዝሙር 119:89-176ን እንመርምር። በ11 አንቀጾች በተዘጋጁት በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ብዙ ትምህርት ይገኛል። ይህ ትምህርት ወደ ዘላለም ሕይወት በሚያመራው መንገድ ላይ ጸንተን እንድንቀጥል ይረዳናል።—ማቴዎስ 7:13, 14
የአምላክን ቃል መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?
3. መዝሙር 119:89, 90 በአምላክ ቃል ላይ መታመን እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው?
3 የአምላክን ቃል መውደድ የተረጋጋ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖረን ያስችለናል። (መዝሙር 119:89-96) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። . . . ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:89, 90) በአምላክ ቃል ማለትም ‘በሰማያት ሥርዐት’ አማካኝነት በሰማይ ላይ ያሉ ግዑዝ አካላት ከምኅዋራቸው ዝንፍ ሳይሉ የሚጓዙ ሲሆን ምድርም ለዘላለም እንድትኖር በጥብቅ ተመሥርታለች። (ኢዮብ 38:31-33፤ መዝሙር 104:5) ከይሖዋ አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ ላይ እምነት ማሳደር እንችላለን፤ አምላክ የሚናገረው ነገር ዓላማው ‘እንዲፈጸም’ ያደርጋል።—ኢሳይያስ 55:8-11
4. መከራ የሚደርስባቸው የአምላክ አገልጋዮች ለቃሉ ፍቅር ማሳደራቸው እንዴት ይጠቅማቸዋል?
4 መዝሙራዊው ‘የአምላክ ሕግ ደስታው ባይሆን ኖሮ በመከራው ወቅት በጠፋ ነበር።’ (መዝሙር 119:92) ስደት ያደረሱበት የሌላ አገር ሰዎች አልነበሩም። እርሱን የጠሉት ሕግ ይጥሱ የነበሩት እስራኤላውያን ናቸው። (ዘሌዋውያን 19:17) ይሁንና ብርታት ይሰጠው የነበረውን የአምላክን ሕግ ይወድ ስለነበር ለተጽዕኗቸው አልተሸነፈም። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ በእርሱ ላይ ጥፋት ለማግኘት ይጠባበቁ ለነበሩ “ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ” ተጋልጦ ነበር። በዚህ ረገድ “ታላላቅ ሐዋርያት” የሚባሉትም ሳይኖሩበት አይቀሩም። (2 ቆሮንቶስ 11:5, 12-14, 26) ሆኖም ጳውሎስ ለአምላክ ቃል ፍቅር ስለነበረው በመንፈሳዊ መቆም ችሏል። በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ፍቅር ስላለንና መመሪያውን በተግባር ስለምናውል ወንድሞቻችንን እንወድዳለን። (1 ዮሐንስ 3:15) ሌላው ቀርቶ ከዓለም የሚደርስብን ጥላቻ እንኳ የአምላክን ትእዛዛት እንድንረሳ አያደርገንም። ይሖዋን ለዘላለም በደስታ የምናገለግልበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅን ከወንድሞቻችን ጋር በፍቅር ተሳስረን ፈቃዱን ማድረጋችንን እንቀጥላለን።—መዝሙር 119:93
5. ንጉሥ አሳ ይሖዋን የፈለገው እንዴት ነው?
5 ለይሖዋ ያደርን መሆናችንን በመግለጽ እኛም እንደ መዝሙራዊው “እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ ሕግህንም ፈልጌአለሁና” ብለን እንጸልይ ይሆናል። (መዝሙር 119:94) ንጉሥ አሳ አምላክን የፈለገ ከመሆኑም ሌላ ከይሁዳ ምድር ክህደትን አስወግዷል። በአሳ የንግሥና ዘመን በ15ኛው ዓመት (963 ከክርስቶስ ልደት በፊት) በተደረገ ታላቅ ስብሰባ ላይ የይሁዳ ነዋሪዎች “እግዚአብሔርን . . . ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ።” ይሖዋም “ተገኘላቸው” እንዲሁም “በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው።” (2 ዜና መዋዕል 15:10-15) ከክርስቲያን ጉባኤ የራቁ ሰዎች ሁሉ ይህ ምሳሌ አምላክን በአዲስ መልክ እንዲፈልጉ ሊያበረታታቸው ይገባል። ከሕዝቦቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያደሱትን ሰዎች ይባርካቸዋል፤ ደግሞም ይጠብቃቸዋል።
6. ከመንፈሳዊ ጉዳት የሚጠብቀን ምን ዓይነት አካሄድ ነው?
6 የይሖዋ ቃል ከመንፈሳዊ ጉዳት የሚጠብቀንን ጥበብ ሊሰጠን ይችላል። (መዝሙር 119:97-104) የአምላክ ትእዛዛት ከጠላቶቻችን የበለጠ ጥበበኞች ያደርጉናል። ማሳሰቢያዎቹን ማክበራችን ማስተዋል ይሰጠናል፤ እንዲሁም ‘መመሪያውን ተከትለን መሄዳችን ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ያደርገናል።’ (መዝሙር 119:98-100) የይሖዋ ቃል ‘ለአፋችን ከማር ወለላ ይልቅ የሚጥመን’ ከሆነ “የሐሰትን መንገድ ሁሉ” ከመጥላትም አልፎ እንርቃለን። (መዝሙር 119:103, 104) ይህም በዚህ በመጨረሻ ዘመን ትዕቢተኛ፣ ጨካኝና አምላክን የማይፈሩ ሰዎች ሲያጋጥሙን መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስብን ጥበቃ ይሆነናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ለእግራችን መብራት
7, 8. ከመዝሙር 119:105 ጋር በሚስማማ መንገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
7 የአምላክ ቃል ምንጊዜም የማይጠፋ የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ ነው። (መዝሙር 119:105-112) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆን የእነርሱ አጋሮች የሆንን “ሌሎች በጎች” “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብለን እንናገራለን። (ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 119:105) በመንፈሳዊ ተደናቅፈን እንዳንወድቅ የአምላክ ቃል መንገዳችንን እንደሚያበራልን መብራት ነው። (ምሳሌ 6:23) ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ የይሖዋ ቃል ለእግራችን መብራት እንዲሆንልን መፍቀድ ይኖርብናል።
8 እኛም መዝሙር 119ን እንዳቀናበረው ሰው ጽኑ አቋም ሊኖረን ይገባል። ከአምላክ መመሪያ ላለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። ለይሖዋ “የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ” ብሏል። (መዝሙር 119:106) አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግን ፈጽሞ አቅልለን መመልከት የለብንም።
9, 10. ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ግለሰቦች ‘መመሪያውን ሊተላለፉ’ እንደሚችሉ እንዴት ማወቅ እንችላለን? ይሁንና ይህ እንዳይደርስብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
9 መዝሙራዊው ‘የአምላክን መመሪያ አልተላለፈም፤’ ሆኖም ራሱን ለይሖዋ በወሰነ አንድ ሰው ላይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊደርስ ይችላል። (መዝሙር 119:110) ንጉሥ ሰሎሞን ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር አባልና መጀመሪያ ላይ ከመለኮታዊ ጥበብ ጋር የሚስማማ እርምጃ የወሰደ ሰው ቢሆንም በኋላ ግን አቅጣጫውን ስቷል። የሐሰት አማልክትን እንዲያመልክ በማድረግ ‘ባዕዳን ሴቶች ወደ ኀጢአት መርተውታል።’—ነህምያ 13:26፤ 1 ነገሥት 11:1-6
10 ‘አዳኙ’ ሰይጣን ብዙ ወጥመዶች ይዘረጋል። (መዝሙር 91:3) ለምሳሌ ያህል፣ በፊት የአምልኮ ባልንጀራችን የነበረ ሰው መንፈሳዊ ብርሃን ካለበት መንገድ ስተን ወጥተን በጨለማ ወደተዋጠ የክህደት ጎዳና እንድንገባ ለማድረግ ይሞክር ይሆናል። በትያጥሮን በነበሩ ክርስቲያኖች መካከል ‘ኤልዛቤል’ ተብለው የተጠሩ ሴቶች የነበሩ ሲሆን ይህ መጠሪያ ሌሎች ጣዖት እንዲያመልኩና እንዲሴስኑ የሚያስተምሩ የሴቶችን ቡድን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ርኩሰት ፈጽሞ አልታገሰም፤ እኛም ዝም ብለን ማለፍ አይኖርብንም። (ራእይ 2:18-22፤ ይሁዳ 3, 4) ስለዚህ ከመመሪያው ስተን ላለመውጣትና በመለኮታዊ ብርሃን ውስጥ ለመቀጠል የይሖዋን እርዳታ በጸሎት እንጠይቅ።—መዝሙር 119:111, 112
ከአምላክ ቃል ማበረታቻ ማግኘት
11. በመዝሙር 119:119 መሠረት አምላክ ለክፉዎች ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
11 ከሥርዓቱ የማንወጣ ከሆነ አምላክ ብርታት ይሰጠናል። (መዝሙር 119:113-120) ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ለብ ያሉ ክርስቲያን ነን ባዮችን እንደማይቀበል ሁሉ እኛም “መንታ ልብ ያላቸውን” አንቀበልም። (መዝሙር 119:113፤ ራእይ 3:16) ይሖዋን በሙሉ ልባችን ስለምናገለግል ‘መጠጊያችን’ ከመሆኑም በተጨማሪ ደግፎ ይይዘናል። መሰሪና ከንቱ መንገድ ስለሚከተሉ ‘ከሥርዐቱ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ ያስወግዳቸዋል።’ (መዝሙር 119:114, 117, 118፤ ምሳሌ 3:32) እንደ ብርና ወርቅ ካሉ ውድ ማዕድናት እንደሚወጣው ቆሻሻ ሁሉ እንዲህ ያሉትን ክፉ ሰዎች እንደ “ጥራጊ” ይቆጥራቸዋል። (መዝሙር 119:119፤ ምሳሌ 17:3) የሚወገድ የቆሻሻ ክምር ውስጥ ከክፉዎች ጋር መገኘት ስለማንፈልግ ምንጊዜም አምላክ ለሚሰጠን ማሳሰቢያዎች ፍቅር ይኑረን!
12. ይሖዋን መፍራት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 መዝሙራዊው “ሥጋዬ አንተን [ይሖዋን] በመፍራት ይንቀጠቀጣል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:120) እንደ አገልጋዮቹ ቆጥሮ እንዲደግፈን ከፈለግን አምላክ የሚጠላውን ነገር በማስወገድ ለእርሱ ጤናማ ፍርሃት እንዳለን ማሳየታችን የግድ አስፈላጊ ነው። ኢዮብ ለይሖዋ ያለው አክብሮታዊ ፍርሃት የጽድቅ ጎዳና እንዲከተል አድርጎታል። (ኢዮብ 1:1፤ 23:15) በጽናት ማሳለፍ ያለብን ነገር ምንም ይሁን ምን አምላካዊ ፍርሃት የእርሱን ሞገስ ከሚያስገኝልን ጎዳና ሳንወጣ እንድንቀጥል ያስችለናል። ለመጽናት ግን በእምነት ልባዊ ጸሎት ማቅረብ አስፈላጊ ነው።—ያዕቆብ 5:15
በእምነት ጸልዩ
13-15. (ሀ) ጸሎታችን መልስ እንደሚያገኝ እምነት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ምን ብለን እንደምንጸልይ ግራ ከገባን ምን ዓይነት እርዳታ አለልን? (ሐ) መዝሙር 119:121-128 ስንጸልይ ከሚያጋጥመን ‘በቃላት ሊገለጥ የማይችል መቃተት’ ጋር ምን ዝምድና እንዳለው ግለጽ።
13 አምላክ ለእኛ ብሎ እርምጃ እንደሚወስድ በማመን መጸለይ እንችላለን። (መዝሙር 119:121-128) እንደ መዝሙራዊው ሁሉ እኛም ጸሎታችን መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኞች ነን። ለምን? የአምላክን ትእዛዛት “ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ” ስለምንወድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ‘የአምላክ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው እንላለን።’—መዝሙር 119:127, 128
14 በእምነት ስለምንጸልይና መመሪያውን በጥንቃቄ ስለምናከብር ይሖዋ ልመናችንን ይሰማል። (መዝሙር 65:2) ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ያጋጠሙን ችግሮች ግራ የሚያጋቡ ከመሆናቸው የተነሳ ምን ብለን እንደምንጸልይ ቢጠፋንስ? በዚህ ጊዜ “መንፈስ . . . በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል።” (ሮሜ 8:26, 27) በእነዚህ ጊዜያት አምላክ በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች የእኛን ስሜት እንደሚገልጹ አድርጎ ይቆጥርልናል።
15 ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በቃላት ሊገለጥ የማይችል መቃተታችንን’ ሊገልጹ የሚችሉ ብዙ ጸሎቶችና ሐሳቦች ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 119:121-128ን ተመልከት። እዚህ ላይ አንዳንድ ነገሮች የተገለጹበት መንገድ እኛ ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ሌሎች ችግር እንዳያደርሱብን የምንሰጋ ከሆነ መዝሙራዊው እንዳደረገው እኛም አምላክ እንዲረዳን መጠየቅ እንችላለን። (ቁጥር 121-123) በጣም አስቸጋሪ የሆነ ውሳኔ ተደቅኖብናል እንበል። በዚህ ጊዜ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች አስታውሰን በሥራ ለማዋል መንፈሱ እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን። (ቁጥር 124, 125) ‘የሐሰትን መንገድ ሁሉ የምንጠላ’ ቢሆንም እንኳ ሕጉን እንድንጥስ ለሚያጋጥመን ፈተና እንዳንሸነፍ አምላክ እንዲረዳን መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። (ቁጥር 126-128) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነብ ከሆነ ይሖዋን በጸሎት በምንማጸንበት ጊዜ እንደዚህ ያሉ ጠቃሚ ጥቅሶች ትዝ ሊሉን ይችላሉ።
ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች እርዳታ ማግኘት
16, 17. (ሀ) የአምላክ ማሳሰቢያ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ለማሳሰቢያዎቹስ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) ሌሎች እኛን እንዴት ይመለከቱን ይሆናል? ይሁንና ትልቅ ቦታ የሚይዘው ነገር ምንድን ነው?
16 አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማና ሞገሱን እንዲሰጠን ከፈለግን ማሳሰቢያዎቹን መታዘዝ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:129-136) ዝንጉ ስለሆንን የይሖዋ ትምህርትና መመሪያ ትዝ እንዲለን የሚያስችሉን ድንቅ የሆኑት ማሳሰቢያዎቹ ያስፈልጉናል። እርግጥ ነው፣ የአምላክን ቃል በአዲስ መልክ እንድንረዳ ለሚያስችለን መንፈሳዊ ብርሃን አመስጋኞች ነን። (መዝሙር 119:129, 130) ሌሎች የይሖዋን ሕግ በመጣሳቸው ‘እንባችን እንደ ውሃ የሚፈስ’ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ‘በእኛ ላይ ፊቱን በማብራት’ ሞገሱን ስለሚያሳየንም አመስጋኞች ነን።—መዝሙር 119:135, 136፤ ዘኁልቁ 6:25
17 ከጽድቅ ማሳሰቢያዎቹ ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ በአምላክ ዘንድ ተወዳጅ ሆነን እንደምንቀጥል እርግጠኞች ነን። (መዝሙር 119:137-144) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የጽድቅ ማሳሰቢያዎቹን እንድናውቅ የማድረግና ልናከብራቸው የሚገቡ መመሪያዎች አድርጎ የመስጠት መብት እንዳለው እንገነዘባለን። (መዝሙር 119:138) መዝሙራዊው የአምላክን መመሪያዎች የሚያከብር ሰው ሆኖ ሳለ “እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ” ያለው ለምንድን ነው? (መዝሙር 119:141) እንዲህ ሲል ጠላቶቹ ለእርሱ ያላቸውን አመለካከት እየጠቀሰ እንደነበረ መረዳት እንችላለን። ለጽድቅ ጥብቅ አቋም ካለን ሌሎች በንቀት ይመለከቱን ይሆናል። ይሁንና ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ይሖዋ ከጽድቅ ማሳሰቢያዎቹ ጋር ተስማምተን ስለምንኖር በጥሩ ዓይን የሚያየን መሆኑን ነው።
ጥበቃና ሰላም ማግኘት
18, 19. የአምላክን ማሳሰቢያዎች መከተላችን ምን ያስገኝልናል?
18 የአምላክን ማሳሰቢያዎች ማክበራችን ወደ እርሱ እንድንቀርብ ያደርገናል። (መዝሙር 119:145-152) ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ትኩረት ስለምንሰጥ በሙሉ ልባችን እርሱን ለመጥራት ነፃነት ያለን ከመሆኑም ሌላ ይሰማናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። “ጎሕ ሳይቀድ” ከእንቅልፋችን ነቅተን እንዲረዳን እንጮኽ ይሆናል። ይህ ለመጸለይ የሚያስችል በጣም ምቹ ሰዓት ነው! (መዝሙር 119:145-147) በተጨማሪም፣ ከብልግና ስለምንርቅና ቃሉ እውነት መሆኑን እንደ ኢየሱስ ስለምንቀበል አምላክ ቅርባችን ነው። (መዝሙር 119:150, 151፤ ዮሐንስ 17:17) ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና በዚህ በችግር በሚታመስ ዓለም ውስጥ ብርታት የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ ታላቁን የአርማጌዶን ጦርነት በሕይወት እንድናልፍ ያስችለናል።—ራእይ 7:9, 14፤ 16:13-16
19 ለአምላክ ቃል ከፍተኛ አክብሮት ስላለን አስተማማኝ ጥበቃ አግኝተናል። (መዝሙር 119:153-160) ከክፉዎች በተለየ መልኩ ከይሖዋ ማሳሰቢያ ወይም ‘ከምስክሩ ዘወር አላልንም።’ የአምላክን መመሪያዎች ስለምንወድ ፍቅራዊ ደግነቱ ጥበቃ ያስገኝልናል። (መዝሙር 119:157-159) ይሖዋ በአንዳንድ ሁኔታዎች ረገድ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግብን ትዝ እንዲለን ማሳሰቢያዎቹ የማስታወስ ችሎታችንን ያነቃቁልናል። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ መመሪያዎች አመራር የሚሰጡን ሲሆን እኛም ፈጣሪያችን እንዲህ የማድረግ መብት እንዳለው ምንም ሳናቅማማ እንቀበላለን። ‘የአምላክ ቃል በሙሉ እውነት’ መሆኑንና አካሄዳችንን በራሳችን ማቅናት እንደማንችል ስለምንገነዘብ አምላክ የሚሰጠንን መመሪያ በደስታ እንቀበላለን።—መዝሙር 119:160፤ ኤርምያስ 10:23
20. “ብዙ ሰላም” ያለን ለምንድን ነው?
20 ለይሖዋ ሕግ ያለን ፍቅር ብዙ ሰላም ያስገኝልናል። (መዝሙር 119:161-168) ስደት አቻ የሌለውን ‘የእግዚአብሔርን ሰላም’ ሊነጥቀን አይችልም። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የይሖዋን ፍርድ በጣም የምናደንቅ ከመሆኑ የተነሳ “በቀን ሰባት ጊዜ” ይህም ማለት ብዙ ጊዜ እናመሰግነዋለን። (መዝሙር 119:161-164) መዝሙራዊው “ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:165) በግለሰብ ደረጃ የይሖዋን ሕግ የምንወድና የምናከብር ከሆነ አንድ ሰው ባደረገው ነገር ወይም በሌላ በማንኛውም ጉዳይ አንሰናከልም።
21. በጉባኤ ውስጥ ችግሮች ቢከሰቱ መሰናከል እንደሌለብን የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?
21 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ብዙ ግለሰቦች ማንኛውም ነገር ለዘለቄታው እንዲያሰናክላቸው አልፈቀዱም። ለምሳሌ ያህል፣ ዲዮጥራጢስ መጥፎ ባሕርይ የነበረው ቢሆንም እንኳ ክርስቲያኑ ጋይዮስ በእርሱ ከመደናቀፍ ይልቅ ‘በእውነት መመላለሱን’ ቀጥሏል። (3 ዮሐንስ 1-3, 9, 10) ጳውሎስ፣ በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበረ ሳይሆን አይቀርም ኤዎድያን እና ሲንጤኪን የተባሉትን ክርስቲያን ሴቶች “በጌታ አንድ ልብ እንዲኖራቸው” አሳስቧቸዋል። በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግር እንዲፈቱ እርዳታ እንዳገኙና ከዚያም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንደቀጠሉ መገመት እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:2, 3) ስለዚህ በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ችግር ቢከሰት መሰናከል አይኖርብንም። ‘መንገዳችን ሁሉ በፊቱ ግልጽ’ መሆኑን በማስታወስ የይሖዋን ሥርዓት ለማክበር ከፍተኛ ትኩረት እንስጥ። (መዝሙር 119:168፤ ምሳሌ 15:3) እንዲህ ካደረግን ‘ሰላማችንን’ ለዘለቄታው የሚወስድብን አንዳች ነገር አይኖርም።
22. (ሀ) አምላክን የምንታዘዝ ከሆነ ምን ዓይነት መብት ማግኘት እንችላለን? (ለ) ከክርስቲያን ጉባኤ ለራቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
22 ይሖዋን ምንጊዜም የምንታዘዝ ከሆነ እርሱን ማወደሳችንን የመቀጠል መብት እናገኛለን። (መዝሙር 119:169-176) አምላክ ካወጣቸው ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን በመኖር መንፈሳዊ ጥበቃ የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ ‘ከንፈሮቻችን የይሖዋን ምስጋና ማፍለቃቸውን ይቀጥላሉ።’ (መዝሙር 119:169-171, 174) ይህ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ማግኘት የምንችለው ከሁሉ የላቀ መብት ነው። መዝሙራዊው በሕይወት መኖርና ይሖዋን ማመስገን ፈልጓል፤ ሆኖም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ‘እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዞ’ ነበር። (መዝሙር 119:175, 176) ከክርስቲያን ጉባኤ የጠፉ አንዳንዶች አሁንም አምላክን የሚወዱና እርሱን ማመስገን የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም እንደገና መንፈሳዊ ጥበቃ እንዲያገኙና ከሕዝቡ ጋር ሆነው ይሖዋን ከማመስገን የሚመጣውን ደስታ እንዲቀምሱ እነርሱን ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።—ዕብራውያን 13:15፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
ለመንገዳችን የሚሆን ዘላቂ ብርሃን
23, 24. ከመዝሙር 119 ምን ጥቅሞች አግኝተሃል?
23 መዝሙር 119 በብዙ መንገዶች ሊጠቅመን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ‘በእግዚአብሔር ሕግ በመሄድ’ መሆኑን ስለሚገልጽ በአምላክ ላይ ይበልጥ እንድንመካ ሊያደርገን ይችላል። (መዝሙር 119:1) መዝሙራዊው ‘የአምላክ ቃል በሙሉ እውነት’ መሆኑን አስታውሶናል። (መዝሙር 119:160) ይህ በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል በሙሉ ያለንን አድናቆት ሊያሳድግልን እንደሚገባ የተረጋገጠ ነው። በመዝሙር 119 ላይ ማሰላሰላችን ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ለማጥናት ሊያነሳሳን ይገባል። መዝሙራዊው አምላክን “ሥርዐትህን አስተምረኝ” ሲል ደጋግሞ ተማጽኗል። (መዝሙር 119:12, 68, 135) እንዲሁም “በትእዛዛትህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ” ሲል ለምኗል። (መዝሙር 119:66) እኛም ተመሳሳይ ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል።
24 መለኮታዊ ትምህርት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት ያስችለናል። መዝሙራዊው የአምላክ አገልጋይ እንደሆነ ደጋግሞ ተናግሯል። እንዲያውም ይሖዋን “እኔ የአንተ ነኝ” በማለት አንጀት የሚበላ አባባል ተጠቅሟል። (መዝሙር 119:17, 65, 94, 122, 125፤ ሮሜ 14:8) ከምሥክሮቹ እንደ አንዱ ተቆጥሮ ይሖዋን ማገልገልና ማወደስ ትልቅ ክብር ነው! (መዝሙር 119:7) የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን አምላክን በደስታ እያገለገልከው ነው? እንግዲያው ምንጊዜም በቃሉ የምትታመንና ቃሉ መንገድህን እንዲያበራልህ የምትፈቅድ ከሆነ በዚህ ታላቅ ሥራ ስትካፈል የይሖዋ ድጋፍና በረከት እንደማይለይህ እርግጠኛ ሁን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ለአምላክ ቃል ፍቅር ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
• የአምላክ ቃል ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው?
• ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች እርዳታ የምናገኘው በምን መንገዶች ነው?
• የይሖዋ ሕዝቦች ጥበቃና ሰላም ያላቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ቃል የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ ነው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን ማሳሰቢያዎች የምንወድ ከሆነ እንደ “ጥራጊ” አይቆጥረንም
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነብ ከሆነ በምንጸልይበት ወቅት ጠቃሚ ሐሳቦች ወዲያውኑ ትዝ ሊሉን ይችላሉ