የፍቅር፣ የእምነትና የታዛዥነት ሕያው ማስረጃ
ቀኑ ግንቦት 16, 2005 ሲሆን የማለዳው አየር ነፋሻማና ፀሐያማ ነበር። ቦታው በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው ዋችታወር ፋርምስ ነው። ጎህ ከመቅደዱ በፊት የጣለው ዝናብ በግቢው ውስጥ ለሚገኘው ሳርና አበባ ውበት ጨምሮለታል። አንዲት ዳክዬና ስምንት ጫጩቶቿ በኩሬው ዳርቻ ላይ በዝግታ ይንሳፈፋሉ። ጎብኚዎቹ የሚያዩት ውበት በጣም ማርኳቸዋል። የአካባቢውን ጸጥታ ላለማደፍረስ የሰጉ ይመስል በለሆሳስ ይነጋገሩ ነበር።
እነዚህ ጎብኚዎች በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ 48 አገራት የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ይሁን እንጂ እዚህ የመጡት የአካባቢውን ገጽታ ለመቃኘት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዎልኪል በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ግቢ በቀይ ጡብ በቅርቡ በተጨመረው ሰፊ ሕንጻ ውስጥ ምን እንደሚከናወን ለማወቅ ጓጉተው ነው። እንግዶቹ ወደ ሕንጻው ሲገቡ፣ ውስጡ እንደውጪው ሰጥ እረጭ ያለ ባይሆንም እንኳ በአድናቆት እንዲዋጡ የሚያደርግ ሌላ ነገር ገጠማቸው።
ጎብኚዎቹ ሰገነት ላይ ቆመው ውስብስቦቹን የማተሚያ ማሽኖች ቁልቁል ይመለከቱ ጀመር። አምስት ግዙፍ የማተሚያ ማሽኖች 6 ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚያህል ስፋት ባለው ጠንካራ የኮንክሪት ወለል ላይ ተተክለዋል። እዚህ ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጽሐፎችና መጽሔቶች ይታተማሉ። እያንዳንዳቸው 1,700 ኪሎ ግራም የሚመዝኑት ግዙፍ የወረቀት ጥቅልሎች በፍጥነት እንደሚሽከረከር የመኪና ጎማ ይሾራሉ። ይህ 23 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ወረቀት እየተተረተረ በማተሚያ መሣሪያዎቹ ውስጥ አልፎ ለመውጣት የሚወስድበት ጊዜ 25 ደቂቃ ብቻ ነው። ማሽኑ በዚህ ደቂቃ ውስጥ ወረቀቱ ላይ አትሞ ቀለሙን በማድረቅ ለመተጣጠፍ ምቹ በሚሆን መንገድ ያቀዘቅዘዋል። በዚህ ሁኔታ የተዘጋጁት መጽሔቶች ከፍ ብሎ በተዘጋጀ ማስተላለፊያ ውስጥ በፍጥነት በመጓዝ ወደየጉባኤው ለመላክ ወደሚታሸጉበት ክፍል ይሄዳሉ። ሌሎች የማተሚያ ማሽኖች ደግሞ የአንድን መጽሐፍ የተለያዩ ገጾች በሰፊ ወረቀት ላይ ያትማሉ፤ የታተሙትም ወረቀቶች ወደ መጠረዣ ክፍል እስከሚላኩ ድረስ እስከ ጣሪያ በሚደርስ ግዙፍ ማስቀመጫ ውስጥ በፍጥነት ይከማቻሉ። ይህ ሥራ ምንም ዝንፍ ሳይል በተቀናጀ መልኩ የሚከናወነው በኮምፒውተር በመታገዝ ነው።
ጎብኚዎቹ የሕትመት ክፍሉን ለቀው ወደ ጥረዛ ክፍል አመሩ። እዚህ ክፍል ውስጥ ያሉት ማሽኖች በየቀኑ 50,000 የሚያህሉ ጠንካራ ሽፋን ያላቸው መጻሕፍትንና ዴሉክስ መጽሐፍ ቅዱሶችን ያትማሉ። ቀደም ሲል በሰፊ ወረቀት ላይ የታተሙት የመጽሐፍ ክፍሎች በገጽ ቅደም ተከተላቸው ተጣጥፈው ይጠረዙና ጠርዛቸው ተስተካክሎ ይቆረጣል። መጽሐፎቹ ሽፋን ከለበሱ በኋላ በየካርቶኑ ይገባሉ። ከዚያም ማሽኖቹ ካርቶኖቹን እያሸጉና ምልክት እያደረጉ ለማንቀሳቀስ አመቺ በሆነ የእንጨት ማስቀመጫ ላይ ይደረድሯቸዋል። ከዚህም በላይ ስስ ሽፋን ያላቸው መጻሕፍት በሚዘጋጁበት ስፍራ በቀን እስከ 100,000 ቅጂዎች ተጠርዘው ይታሸጋሉ። በዚህም ስፍራ ቢሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማተም በሚያስገርም ፍጥነት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሞተሮች፣ መቀበያዎች፣ ማርሾች፣ የሚሽከረከሩ ነገሮችና ቀበቶዎች ያሉት እጅግ ውስብስብ ማሽን ይገኛል።
ዝንፍ እንደማይል ሰዓት በጥሩ ሁኔታ ሥራውን የሚያከናውነው ይህ የማተሚያ ማሽን የዘመናችን ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ቀጥሎ እንደምናየው ደግሞ ማሽኑ የይሖዋ ሕዝቦች ላላቸው ፍቅር፣ እምነትና ታዛዥነት ሕያው ማስረጃ ነው። ይሁንና የሕትመት ሥራው ከብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደ ዎልኪል መዛወር ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ሁሉንም ሥራ አንድ ላይ በማከናወን የሕትመቱንና ጽሑፎችን ወደየጉባኤዎች የመላኩን ሥራ ለማቀላጠፍ ሲባል ነው። ለብዙ ዓመታት መጻሕፍት የሚታተሙትና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚላኩት ከብሩክሊን ሲሆን መጽሔቶች ደግሞ ከዎልኪል ነበር። እነዚህን ሁለት ክፍሎች ወደ አንድ ቦታ ማምጣቱ የሰው ኃይል ከመቆጠቡም በላይ ለዚህ ሥራ ተብሎ የሚደረገውን መዋጮ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ በቡሩክሊን ያሉት የማተሚያ መሣሪያዎች በማርጀታቸው ማን ሮላንድ ሊት ማን የሚባሉ ሁለት አዳዲስ ማተሚያ ማሽኖች ከጀርመን ታዝዘው ነበር። አዳዲሶቹ ማሽኖች በጣም ግዙፍ ስለሆኑ ብሩክሊን ያለው የማተሚያ ክፍል አይበቃቸውም።
ይሖዋ ሥራውን ይደግፋል
ምንጊዜም ቢሆን ጽሑፎች የሚታተሙት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማስፋፋት ነው። የሕትመቱን ሥራ ይሖዋ እየባረከው እንደሆነ ገና ከጅምሩ ታይቷል። ከ1879 እስከ 1922 መጽሐፎች የሚታተሙት በንግድ ማተሚያ ቤቶች ውስጥ ነበር። በ1922 በኒው ዮርክ 18 ኮንኮርድ አውራ ጎዳና የሚገኝ ባለ ስድስት ፎቅ ሕንጻ በመከራየት መጽሐፍ ለማተም የሚያስፈልጉ ማሽኖች ተገዙ። በዚህ ጊዜ አንዳንዶች፣ ወንድሞች ሥራውን ማከናወን መቻላቸውን ተጠራጥረው ነበር።
እንዲህ ዓይነቱ ጥርጣሬ ከነበራቸው ሰዎች መካከል ቀድሞ አብዛኞቹን መጽሐፎቻችንን ሲያትም የነበረ ድርጅት ፕሬዚዳንት ይገኙበታል። እኚህ ሰው በኮንኮርድ አውራ ጎዳና የሚገኘውን የሕትመት ክፍል ከጎበኙ በኋላ እንደሚከተለው ብለው ነበር:- “ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው የሕትመት መሣሪያዎች በእጃችሁ ቢገኙም መሣሪያዎቹን ማንቀሳቀስ የሚችል ሰው በመካከላችሁ የለም። ምናለ በሉኝ፣ ይህን ማሽን በስድስት ወራት ውስጥ እንክትክቱን አውጥታችሁ ታስቀምጡታላችሁ፤ የዚያን ጊዜ ሥራውን ማከናወን የሚገባቸው ልምድ ያላቸውና በሙያው የተካኑ ሰዎች እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ።”
በዚያን ጊዜ የሕትመት ክፍል የበላይ ተመልካች የነበረው ሮበርት ማርቲን የተሰማውን ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- “እኚህ ሰው የተናገሩት ነገር ምክንያታዊ ነበር፤ ይሁንና የሰጡት ሐሳብ ጌታን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም፤ እርሱ ደግሞ ዘወትር ከእኛ ጋር ነው። . . . ብዙም ሳይቆይ መጻሕፍት ማተም ጀመርን።” በቀጣዮቹ 80 ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ማተሚያ ማሽኖች ተጠቅመው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎችን ለሕትመት አብቅተዋል።
ጥቅምት 5, 2002 በተደረገው የፔንስልቬንያ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከናወነው ሕትመት ወደ ዎልኪል እንዲዛወር የቀረበውን ሐሳብ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ማጽደቁን የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። በየካቲት 2004 ርክክብ የሚደረግባቸው ሁለት አዳዲስ ማተሚያ ማሽኖችም እንዲሠሩ ታዘዘ። ወንድሞች ማሽኖቹን ለመረከብ በቀራቸው የ1 ዓመት ከ3 ወር ጊዜ ውስጥ የሕትመት ክፍሉን ንድፍ በማውጣትና የማስፋፋቱን ሥራ በማከናወን ዝግጅት ማድረግ ነበረባቸው። አዲሱን የመጠረዣ ማሽን የመገጣጠሙና የጽሑፍ መላኪያ ክፍሉን የማደራጀቱ ሥራ ደግሞ በቀጣዮቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ መጠናቀቅ ነበረበት። ምናልባት አንዳንዶች ይህ ሁሉ ሥራ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ መከናወን መቻሉን ተጠራጥረው ይሆናል፤ በእርግጥም ደግሞ ሁኔታው ፈጽሞ የሚቻል አይመስልም ነበር። ያም ሆኖ ግን ወንድሞች በይሖዋ እርዳታ ሥራውን ማጠናቀቅ እንደሚችሉ እርግጠኞች ነበሩ።
“ደስ የሚያሰኝ የትብብር መንፈስ”
የይሖዋ ሕዝቦች ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንደሚያቀርቡ በመተማመን ወንድሞች ፕሮጀክቱን ጀመሩ። (መዝሙር 110:3) ይህ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት የቤቴል የግንባታ ክፍሎች ካላቸው የሰው ኃይል በላይ በመሆኑ ሌሎች ሠራተኞች ያስፈልጉ ነበር። ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ሙያው ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ከአንድ ሳምንት እስከ ሦስት ወር ለሚደርሱ ጊዜያት በጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኝነት ለማገልገል ከዩናይትድ ስቴትስና ከካናዳ ወደ ስፍራው ተጓዙ። ከዚህም ሌላ ዓለም አቀፍ አገልጋዮች እንዲሁም በፈቃደኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ ወንድሞች በፕሮጀክቱ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር። የአካባቢው የሕንጻ ሥራ ኮሚቴዎችም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ብዙዎቹ በዎልኪል ፕሮጀክት ለመካፈል ከፍተኛ የጉዞ ወጪ ማውጣትና ለበርካታ ጊዜያት ከሰብዓዊ ሥራቸው መቅረት አስፈልጓቸዋል። ያም ሆኖ እነዚህን መሥዋዕትነቶች ለመክፈል ፈቃደኞች ነበሩ። ለእነዚህ በርካታ ተጨማሪ ፈቃደኛ ሠራተኞች ማረፊያና ምግብ ማዘጋጀት ማስፈለጉ ለቤቴል ቤተሰብ አባላት ፕሮጀክቱን ለመደገፍ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ከብሩክሊን፣ ከፓተርሰንና ከዎልኪል የተውጣጡ 535 ቤቴላውያን በሳምንቱ ቀናት ከሚያከናውኑት ሥራ በተጨማሪ ቅዳሜን በፕሮጀክቱ ላይ ለማሳለፍ ፈቃደኞች ነበሩ። የይሖዋ ሕዝቦች ለዚህ ታሪካዊ ክንውን ከፍተኛ ምላሽ ሊሰጡ የቻሉት ይሖዋ ፕሮጀክቱን ይደግፍ ስለነበር ነው።
ሌሎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ለአብነት ያህል፣ ወንድሞች የዘጠኝ ዓመት ልጅ ከሆነችው ኤቢ ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር። የጻፈችው እንዲህ ይላል:- “ግሩም የሆኑ መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ስለምታከናውኑት ሥራ ሁሉ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በቅርቡ ሳልጎበኛችሁ አልቀርም። አባባ በሚቀጥለው ዓመት እንሄዳለን ብሎኛል! ማንነቴን ማወቅ እንድትችሉ ባጅ አደርጋለሁ። አዲሱን የሕትመት መሣሪያ የሚያግዝ 20 የአሜሪካን ዶላር ልኬላችኋለሁ! ወላጆቼ የሰጡኝን ይህን የኪስ ገንዘብ ለእናንተ ለወንድሞቼ መስጠት እፈልጋለሁ።”
አንዲት እህት ደግሞ እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች:- “እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እንኳ የሠራኋቸውን የሹራብ ኮፍያዎች እባካችሁ ተቀበሉኝ። እነዚህን ኮፍያዎች በዎልኪል ፕሮጀክት እየተካፈሉ ላሉት ወንድሞች እንድትሰጡልኝ እፈልጋለሁ። የአየር ትንበያን ይዞ የሚወጣው ዓመታዊ መጽሐፍ ክረምቱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገልጻል። ጸሐፊዎቹ ትክክል ይሁኑ አይሁኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ይሁንና በዎልኪል ያለው አብዛኛው ሥራ ከቤት ውጪ እንደሚከናወን ስለማውቅ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዳይበርዳቸው ስል እነዚህን ኮፍያዎች ልኬላችኋለሁ። ወንድሞች ለግንባታው የሚፈልጉት ዓይነት ሙያ ባይኖረኝም ሹራብ መሥራት ግን እችላለሁ፤ ስለዚህ በምችለው ለመርዳት ወሰንኩ።” ከደብዳቤው ጋር 106 የሹራብ ኮፍያዎች ነበሩ!
ሥራው በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ተጠናቀቀ። የሕትመት ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ጆን ላርሰን እንደሚከተለው ብሏል:- “ደስ የሚያሰኝ የትብብር መንፈስ ይታይ ነበር። ይሖዋ ሥራውን እንደባረከው ማን ሊጠራጠር ይችላል? የፕሮጀክቱ ሂደት እጅግ ፈጣን ነበር። ግንቦት 2003 ወንድሞች የሕንጻውን መሠረት ሲገነቡ ጭቃ ውስጥ ቆሜ ያየሁበትን ቀን አስታውሳለሁ። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እዚያው ቦታ ላይ ቆሜ የሕትመት ሥራው ሲካሄድ ተመልክቻለሁ።”
የውሰና ፕሮግራም
ሌሎች ሦስት መኖሪያ ሕንጻዎችን ጨምሮ የአዲሱ የሕትመት ክፍል የውሰና ፕሮግራም በግንቦት 16, 2005 ተከናወነ። በብሩክሊን፣ በፓተርሰንና በካናዳ የቤቴል ቤቶች የሚገኙ ወንድሞች ፕሮግራሙን በቀጥታ በቪዲዮ ተከታትለዋል። በድምሩ 6,049 የሚያህሉ ወንድሞችና እህቶች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ ሲሆን በመክፈቻው ላይ የሕትመት ሥራውን ታሪክ በአጭሩ አቅርቧል። የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ጆን ላርሰን እና ጆን ኪኮት በቃለ ምልልስና በቪዲዮ በመታገዝ የዩናይትድ ስቴትስን የግንባታና የሕትመት ሥራ ታሪክ ከልሰዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጆን ባር የሕትመት ክፍሉና ሦስቱ የመኖሪያ ሕንጻዎች ለይሖዋ አምላክ የተወሰኑበትን የመደምደሚያ ንግግር አቅርቧል።
በቀጣዩ ሳምንት በፓተርሰንና በብሩክሊን የሚኖሩ ቤቴላውያን አዳዲሶቹን ሕንጻዎች እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጎላቸው ነበር። በወቅቱ በድምሩ 5,920 የሚያህሉ ሰዎች ስፍራውን ጎብኝተዋል።
ለማተሚያዎቹ ያለን አመለካከት ምንድን ነው?
ወንድም ባር ባቀረበው የውሰና ንግግር ላይ እንደገለጸው ማተሚያው እጅግ የሚያስገርም ቢሆንም በጣም አስደናቂ ያደረገው ግን ከሰዎች ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው። የምናትማቸው ጽሑፎች በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
አዳዲሶቹ ማሽኖች እያንዳንዳቸው በአንድ ሰዓት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትራክቶችን ማተም ይችላሉ! ይሁንና አንዷ ትራክት ብቻ በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ልታመጣ ትችላለች። ለምሳሌ ያህል፣ በ1921 በደቡብ አፍሪካ የባቡር ሃዲድ ጥገና ቡድን አባሎች አንድን የሃዲድ መስመር እየጠገኑ ነበር። ከሠራተኞቹ መካከል ክርስቲያን የተባለ ሰው አንድ ወረቀት ሃዲድ ስር ተወሽቆ ተመለከተ። ወረቀቱ ከትራክቶቻችን ውስጥ አንደኛው ነበር። ክርስቲያን ወረቀቱን በጉጉት አነበበው። ከዚያም በአድናቆት ተሞልቶ እየሮጠ ወደ አማቹ ሄደና:- “እውነትን አገኘሁ!” ሲል ነገረው። ብዙም ሳይቆዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ደብዳቤ ጻፉ። የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮም ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ላከላቸው። አሁን እነዚህ ሁለት ሰዎች አጥንተው በመጠመቅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማካፈል ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሳቢያ ብዙዎች እውነትን ሊቀበሉ በቅተዋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከመቶ የሚበልጡ የልጅ ልጆቻቸው ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው አንድ ሰው ከሃዲድ ሥር ባገኛት አንዲት ትራክት የተነሳ ነው!
ወንድም ባር እንደገለጸው የምናትማቸው ጽሑፎች ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡ፣ በእውነት እንዲኖሩና የጋለ ቅንዓት እንዲያሳዩ እንዲሁም የወንድማማች ኅብረታችን አንድነት እንዲጠበቅ ያደርጋሉ። ሁላችንም የምናሰራጫቸው እነዚህ ጽሑፎች ከሁሉም በላይ አምላካችንን ይሖዋን ያስከብራሉ!
ይሖዋ ማተሚያውን እንዴት ይመለከተዋል?
ከዚህም በላይ ወንድም ባር፣ ይሖዋ የሕትመት ሥራው ለሚከናወንባቸው መሣሪያዎች ምን አመለካከት እንዳለው ላንድ አፍታ ቆም ብለው እንዲያስቡበት አድማጮቹን ጠይቆ ነበር። ይሖዋ ምሥራቹ እንዲሰበክ ያለው ዓላማ ፍጻሜውን ማግኘቱ የተመካው በሕትመቱ ሥራ ላይ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እርሱ ድንጋዮች እንኳ ምሥራቹን እንዲናገሩ ማድረግ ይችላል! (ሉቃስ 19:40) በተጨማሪም የማሽኖቹ ውስብስብነት፣ መጠን፣ ፍጥነት አሊያም የመሥራት አቅም ይሖዋን አያስደንቀውም። ለምን? እርሱ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ነው! (መዝሙር 147:10, 11) ይሖዋ ጽሑፎችን ለማምረት ሰዎች ያልደረሱበትን እንዲያውም ጭራሽ ሊያስቡት የማይችሉትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ መጠቀም ይችላል። ታዲያ ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ምንን ነው? በዚህ የሕትመት ሥራ አማካኝነት የሕዝቦቹን ግሩም ባሕርያት ማለትም ፍቅራቸውን፣ እምነታቸውንና ታዛዥነታቸውን እንደሚመለከት ግልጽ ነው።
ወንድም ባር ይህ እንዴት የፍቅር መግለጫ እንደሚሆን በምሳሌ አብራርቶ ነበር። አንዲት ልጅ ለወላጆቿ ኬክ ጋገረች እንበል። ወላጆቿ በሁኔታው እንደሚደሰቱ ምንም አያጠራጥርም። አዎን፣ የኬኩ ጥራት ምንም ይሁን ምን ወላጆቿ ይበልጥ የሚደሰቱት ልጃቸው በደግነት ተነሳስታ ባሳየቻቸው ፍቅር ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ አዲሱን ማተሚያ ሲያይ በዋነኝነት የሚደነቀው ሕዝቦቹ ለስሙ ባሳዩት ፍቅር እንጂ ሕንጻው ባለው ውበትና በማሽኖቹ ውስብስብነት አይደለም።—ዕብራውያን 6:10
ከዚህም በላይ ይሖዋ ኖኅ የሠራውን መርከብ የእምነቱ መግለጫ አድርጎ እንደተመለከተለት ሁሉ ማተሚያውንም እምነት እንዳለን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አድርጎ ያየዋል። በምን ላይ ያለንን እምነት? ኖኅ፣ ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው እንደሚፈጸም እምነት ነበረው። እኛም በመጨረሻው ዘመን እንደምንኖር፣ ምሥራቹ በምድር ላይ ሊታወጅ የሚገባው ከሁሉ የላቀ መልእክት እንደሆነና ሰዎች መልእክቱን መስማታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የሰዎችን ሕይወት እንደሚያድን እናውቃለን።—ሮሜ 10:13, 14
ከዚህም በላይ ይሖዋ የሕትመቱን ሥራ የታዛዥነታችን ማስረጃ አድርጎ እንደሚመለከተው የተረጋገጠ ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው የእርሱ ፈቃድ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ እንዲሰበክ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ማተሚያ በምድር ዙሪያ ከሚገኙ ሌሎች ማተሚያዎች ጋር ተዳምሮ የተሰጠንን ተልእኮ እንድንወጣ ይረዳናል።
አዎን በገንዘብ መዋጮው፣ በግንባታውና አዲሱ ማተሚያ ሥራውን እንዲጀምር በማድረግ ረገድ የታየው የፍቅር፣ የእምነትና የታዛዥነት መንፈስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች እውነትን ለመስበክ በሚያደርጉት ቅንዓት የታከለበት እንቅስቃሴ ላይም ይታያል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በዩናይትድ ስቴትስ ከሕትመቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የታየው እድገት
1920:- በ35 መርትል ጎዳና፣ ብሩክሊን የመጀመሪያውን ተሽከርካሪ የማተሚያ ማሽን በመጠቀም መጽሔቶች ይታተሙ ጀመረ።
1922:- የሕትመት ክፍሉ በ18 ኮንኮርድ ጎዳና ወደሚገኝ ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻ ተዛወረ። ከዚህ ዓመት አንስቶ መጽሐፍ መታተም ጀመረ።
1927:- የሕትመት ክፍሉ 117 አዳምስ ጎዳና ላይ ወደተገነባው አዲስ ሕንጻ ተዛወረ።
1949:- በሕንጻው ላይ ዘጠኝ ፎቅ በመጨመሩ የሕትመት ክፍሉ በእጥፍ አደገ።
1956:- በ77 ሳንድስ ጎዳና አዲስ ሕንጻ ሲገነባ በአዳምስ ጎዳና የነበረው የሕትመት ክፍል በእጥፍ አደገ።
1967:- ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንጻ መገንባቱ ከመጀመሪያው ሕንጻ አሥር እጥፍ የሚበልጥ ውስጥ ለውስጥ የተያያዘ የሕትመት ክፍል እንዲኖር አስችሏል።
1973:- መጽሔቶችን ማተምን ተቀዳሚ ዓላማው ያደረገ አጋዥ የሕትመት ክፍል በዎልኪል ተቋቋመ።
2004:- በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚከናወነው የሕትመት፣ የጥረዛና የጽሑፍ መላኪያ ክፍሎች በዎልኪል በሚገኘው ሕንጻ ተጠቃለሉ።