አምላክን በመፍራት ጠቢብ ሁን!
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።”—ምሳሌ 9:10
1. ብዙዎች አምላክን መፍራት የሚለውን ሐሳብ መረዳት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?
ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ነው መባል እንደ ውዳሴ የሚቆጠርበት ጊዜ ነበር። አሁን አሁን ግን ብዙ ሰዎች አምላክን መፍራት የሚለው ሐሳብ ጊዜ ያለፈበትና ለመረዳት የሚያዳግት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘አምላክ ፍቅር ከሆነ፣ ለምን እፈራዋለሁ?’ በማለት ይጠይቁ ይሆናል። ለእነርሱ ፍርሃት ማለት የፈለጉትን ነገር እንዳያደርጉ የሚያግድ አሉታዊ ስሜት ነው። አምላካዊ ፍርሃት ከዚህ የሰፋ ትርጉም ያለው ሲሆን ቀጥለን እንደምንመለከተው ከስሜት ጋር የተያያዘ ነገር ብቻ አይደለም።
2, 3. ጤናማ አምላካዊ ፍርሃት ከምን ነገሮች ጋር ተዛማጅነት አለው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክን መፍራት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ባሕርያት መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 11:3) አምላካዊ ፍርሃት ለአምላክ ካለን ጥልቅ አክብሮት የተነሳ እርሱን ላለማሳዘን በውስጣችን የሚፈጠር ከፍተኛ ፍላጎት ነው። (መዝሙር 115:11) ይህም አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ትክክል መሆናቸውን ማመንና በጥብቅ መከተል እንዲሁም አምላክ ትክክል ወይም ስህተት ያላቸውን ነገሮች ተቀብሎ ከሰጠው መመሪያ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጨምራል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ዓይነቱን ጤናማ ፍርሃት “ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖረንና ከማንኛውም ዓይነት መጥፎ ድርጊት እንድንርቅ የሚያደርግ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው” ሲል ገልጾታል። የአምላክ ቃል “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ማለቱ የተገባ ነው።—ምሳሌ 9:10
3 በእርግጥም፣ አምላክን መፍራት የሰው ልጆችን የተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ይነካል። አምላክን መፍራት ከጥበብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከደስታ፣ ከሰላም፣ ከብልጽግና፣ ረጅም ዕድሜ ከማግኘት፣ ከተስፋና በአምላክ ከመታመን ጋር ተዛማጅነት አለው። (መዝሙር 2:11፤ ምሳሌ 1:7፤ 10:27፤ 14:26፤ 22:4፤ 23:17, 18፤ የሐዋርያት ሥራ 9:31) ከእምነትና ከፍቅርም ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። እንዲያውም ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና ሁሉ ይነካል። (ዘዳግም 10:12፤ ኢዮብ 6:14፤ ዕብራውያን 11:7) አምላክን መፍራት፣ በሰማይ የሚኖረው አባታችን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልንና መተላለፋችንን ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ ጽኑ እምነት ማሳደርን ይጨምራል። (መዝሙር 130:4) በአምላክ ፊት ሊሸበሩ የሚገባቸው ንስሐ የማይገቡ ክፉ አድራጊዎች ብቻ ናቸው።a—ዕብራውያን 10:26-31
ይሖዋን መፍራት መማር
4. ‘እግዚአብሔርን መፍራት እንድንማር’ ምን ሊረዳን ይችላል?
4 ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ለማድረግም ሆነ የአምላክን በረከቶች ለማግኘት አምላካዊ ፍርሃት ማዳበራችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ታዲያ በተገቢው መንገድ ‘እግዚአብሔርን መፍራትን መማር’ የምንችለው እንዴት ነው? (ዘዳግም 17:19 የ1954 ትርጉም) ቅዱሳን ጽሑፎች “ለትምህርታችን” የሚሆኑ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው የበርካታ ወንዶችንና ሴቶችን ታሪክ ይዘውልናል። (ሮሜ 15:4) አምላክን መፍራት ምን ማለት መሆኑን ለመረዳት እንድንችል ከእነዚህ ታሪኮች ውስጥ የጥንቷ የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ሕይወት መለስ ብለን እንቃኝ።
5. ዳዊት በጎችን ይጠብቅ የነበረ መሆኑ ይሖዋን መፍራት ያስተማረው እንዴት ነው?
5 የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ሕዝቡን የሚፈራ፣ አምላካዊ ፍርሃት ግን የጎደለው በመሆኑ ይሖዋ ትቶታል። (1 ሳሙኤል 15:24-26) በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዳዊት በአኗኗሩም ሆነ ከይሖዋ ጋር በመሠረተው የቅርብ ዝምድና ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ዳዊት በልጅነቱ ብዙ ጊዜ የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:11) ዳዊት፣ በጎችን እየጠበቀ ከቤት ውጭ ያሳለፋቸው በርካታ ሌሊቶች ይሖዋን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድተውት መሆን አለበት። በእነዚህ ጊዜያት ዳዊት ሊመለከት የሚችለው ግዙፍ ከሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ በጣም ውስን የሆነውን ክፍል ብቻ ቢሆንም ያየው ነገር አምላክን ልናከብረው ይገባል የሚል ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አስችሎታል። በመሆኑም ቆየት ብሎ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?”—መዝሙር 8:3, 4
6. ዳዊት የይሖዋን ታላቅነት ሲገነዘብ ምን ተሰማው?
6 ዳዊት እጅግ ግዙፍ ከሆነው አጽናፈ ዓለም ጋር ራሱን ሲያነጻጽር ኢምንት መሆኑን በማወቁ እጅግ ተደንቋል። ሆኖም ይህን መገንዘቡ እንዲሸበር አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን እንዲያወድስና “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” እንዲል ገፋፍቶታል። (መዝሙር 19:1) ለይሖዋ ያለው ጥልቅ አክብሮት ይበልጥ ወደ እርሱ እንዲቀርብ እንዲሁም ፍጹም የሆነው መንገዱን ለመማርና በእርሱም ለመመላለስ እንዲነሳሳ አድርጎታል። ዳዊት “አንተ ታላቅ ነህና፤ ታምራትም ትሠራለህ፤ አንተ ብቻህን አምላክ ነህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ብሎ ሲዘምር ምን ዓይነት ስሜት አድሮበት ሊሆን እንደሚችል ገምት።—መዝሙር 86:10, 11
7. ዳዊት አምላክን መፍራቱ ከጎልያድ ጋር እንዲዋጋ የረዳው እንዴት ነው?
7 ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ምድር በወረሩ ጊዜ፣ ወደ ሦስት ሜትር የሚጠጋ ቁመት ያለው ጎልያድ የተባለ ጀግና ‘አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወዳለሁበት ይውረድ፣ እርሱ ካሸነፈኝ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን’ በማለት በእስራኤላውያን ላይ ተሳልቆ ነበር። (1 ሳሙኤል 17:4-10) ከዳዊት በቀር ሳኦልም ሆነ መላ ሠራዊቱ በፍርሃት ተሸበሩ። ዳዊት ከይሖዋ በቀር ማንም ሰው፣ ኃያላን የሚባሉ ሰዎችም እንኳ ሊፈሩ እንደማይገባቸው ያውቅ ነበር። በመሆኑም ዳዊት ጎልያድን እንዲህ አለው:- “እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። . . . እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ዳዊት በይሖዋ እርዳታ ግዙፉን ጎልያድን በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ገደለው።—1 ሳሙኤል 17:45-47
8. ፈሪሃ አምላክ ስለነበራቸው ሰዎች ከሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን እንማራለን?
8 እኛም ዳዊት ከተጋፈጠው ያልተናነሱ መሰናክሎች ወይም አስፈሪ ጠላቶች ይገጥሙን ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን? ዳዊትና ሌሎች የጥንት ታማኝ አገልጋዮች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም አምላክን በመፍራት ልንቋቋማቸው እንችላለን። አምላክን መፍራት የሰውን ፍርሃት ለማሸነፍ ይረዳል። የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው ነህምያ ተቃዋሚዎቻቸው ተጽዕኖ እያደረሱባቸው ለነበሩት እስራኤላውያን “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን እግዚአብሔርን አስቡ” ብሏቸዋል። (ነህምያ 4:14) ዳዊት፣ ነህምያና ሌሎች የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ በእርሱ እርዳታ ማከናወን ችለዋል። እኛም አምላክን በመፍራት እንዲሁ ማድረግ እንችላለን።
ችግሮችን በአምላካዊ ፍርሃት መቋቋም
9. ዳዊት አምላክን እንደሚፈራ ያሳየው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እያለ ነው?
9 ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ ይሖዋ ብዙ ድሎችን አጎናጽፎታል። ይሁንና ቅናት ያደረበት ሳኦል፣ በመጀመሪያ በስሜት ተነሳስቶ እርምጃ በመውሰድ ከዚያም መሠሪ ዘዴዎችን በመጠቀም በመጨረሻም ሠራዊት በማዝመት ዳዊትን ለመግደል ሞከረ። ምንም እንኳ ይሖዋ ለዳዊት ንጉሥ እንደሚሆን ያረጋገጠለት ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት በስደት መኖር፣ መዋጋትና እስከሚያነግሠው ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ነበረበት። ዳዊት በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ እውነተኛውን አምላክ እንደሚፈራ አሳይቷል።—1 ሳሙኤል 18:9, 11, 17፤ 24:2
10. ዳዊት ችግር በገጠመው ጊዜ አምላክን እንደሚፈራ ያሳየው እንዴት ነው?
10 በአንድ ወቅት ዳዊት፣ በንጉሥ አንኩስ ወደምትተዳደረውና የጎልያድ የትውልድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ጌት ተሰድዶ ነበር። (1 ሳሙኤል 21:10-15) በዚያም የንጉሡ አገልጋዮች የሕዝባቸው ጠላት እንደሆነ በመናገር ዳዊትን አጋለጡት። ዳዊት በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? የልቡን ግልጽልጽ አድርጎ ወደ ይሖዋ ጸለየ። (መዝሙር 56:1-4, 11-13) ዳዊት በፊቱ ከተደቀነው አደጋ ለማምለጥ እንደ አበደ ሰው መሆን አስፈልጎት የነበረ ቢሆንም ጥረቱን በመባረክ የተሳካ እንዲሆን ያደረገለት ይሖዋ መሆኑን ያውቅ ነበር። ዳዊት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመኑ በእርግጥም ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው እንደነበር ያሳያል።—መዝሙር 34:4-6, 9-11
11. ልክ እንደ ዳዊት እኛም በችግር ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ አምላካዊ ፍርሃት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ልክ እንደ ዳዊት እኛም፣ አምላክ ችግሮቻችንን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እንደሚሰጠን በገባው ቃል ላይ በመታመን እርሱን እንደምንፈራ ማሳየት እንችላለን። ዳዊት “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 37:5) ይህ ማለት ግን፣ ችግሮቻችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ በመጣል እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም። ዳዊት አምላክ እንዲረዳው ከጸለየ በኋላ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ አልተወውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በሰጠው ጉልበትና አእምሮ ተጠቅሞ ችግሩን ተወጥቷል። ያም ቢሆን ግን ዳዊት ጥረታችን ብቻውን ውጤት እንደማያስገኝ ተገንዝቧል፤ አምላክ ከእኛ ጋር መሆን አለበት። የቻልነውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ቀሪውን ለይሖዋ ልንተውለት ይገባል። እውነት ነው፣ ብዙውን ጊዜ በይሖዋ ከመታመን ያለፈ ነገር ማድረግ አንችል ይሆናል። በዚህ ጊዜ አምላክን በእርግጥ እንደምንፈራ ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። ዳዊት ከልብ በመነጨ ስሜት ተገፋፍቶ “እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም” በማለት የተናገራቸው ቃላት ያጽናኑናል።—መዝሙር 25:14
12. የምናቀርበውን ጸሎት በቁም ነገር ልንመለከተው የሚገባን ለምንድን ነው? ከየትኛውስ አመለካከት መራቅ አለብን?
12 በመሆኑም ለአምላክ የምናቀርበውን ጸሎትም ይሁን ከእርሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በቁም ነገር መመልከት አለብን። ወደ ይሖዋ ስንቀርብ “መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን” ይኖርብናል። (ዕብራውያን 11:6፤ ያዕቆብ 1:5-8) አምላክ ሲረዳን ደግሞ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ‘ምስጋናችንን ልናቀርብለት’ ይገባል። (ቈላስይስ 3:15, 17) አንድ ተሞክሮ ያካበተ ቅቡዕ ክርስቲያን እንደሚከተለው በማለት የገለጻቸው ዓይነት ሰዎች መሆን አይኖርብንም:- ‘እነዚህ ሰዎች አምላክን በሰማይ ውስጥ እንዳለ የምግብ ቤት አስተናጋጅ አድርገው ይቆጥሩታል። የሆነ ነገር ሲፈልጉ እጃቸውን አጨብጭበው በመጥራት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ይሻሉ። የጠየቁትን ካገኙ በኋላ ግን ከአጠገባቸው ዞር እንዲልላቸው ይፈልጋሉ።’ ይህ ዓይነቱ አመለካከት አምላካዊ ፍርሃት የጎደለው ነው።
አምላካዊ ፍርሃት ሲቀንስ
13. ዳዊት ለአምላክ ሕግ ተገቢ አክብሮት ሳያሳይ የቀረው መቼ ነው?
13 ዳዊት፣ በችግር ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት የይሖዋን እርዳታ ማግኘቱ ለአምላክ የጠለቀ ፍርሃት እንዲያድርበት ከማድረጉም በላይ የመተማመን መንፈሱን አጠንክሮለታል። (መዝሙር 31:22-24) ሆኖም፣ ዳዊት በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ለአምላክ የነበረው ፍርሃት በመቀነሱ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርጎ ነበር። የመጀመሪያው፣ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ካደረገው ዝግጅት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ጊዜ ታቦቱ የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት በሌዋውያን ትከሻ ላይ ሆኖ ከመጓዝ ይልቅ በሠረገላ ተጭኖ ነበር። ሠረገላውን ይነዳ የነበረው ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ አስቦ በፈጸመው ‘የድፍረት’ ድርጊት ወዲያውኑ ተቀሠፈ። ዖዛ ትልቅ ኃጢአት የፈጸመ ቢሆንም እንኳ ዳዊት ለአምላክ ሕግ ተገቢውን አክብሮት ሳይሰጥ መቅረቱ ለዚህ አሳዛኝ ክስተት አስተዋጽኦ አድርጓል። አምላክን መፍራት ማለት እርሱ ያዘዛቸውን ነገሮች በእርሱ መንገድ መፈጸም ማለት ነው።—2 ሳሙኤል 6:2-9፤ ዘኍልቍ 4:15፤ 7:9
14. ዳዊት እስራኤላውያንን መቁጠሩ ምን ውጤት አስከተለ?
14 ቆየት ብሎም፣ ዳዊት በሰይጣን አነሳሽነት የእስራኤልን ጦረኞች ቆጠረ። (1 ዜና መዋዕል 21:1) ይህን ማድረጉ ለአምላክ የነበረው ፍርሃት ቀንሶ እንደነበር የሚያሳይ ሲሆን በውጤቱም 70,000 እስራኤላውያን ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። በዚህ ጊዜ ዳዊት በይሖዋ ፊት ንስሐ የገባ ቢሆንም እርሱም ሆነ ሕዝቡ ከፍተኛ ችግር ደርሶባቸዋል።—2 ሳሙኤል 24:1-16
15. ዳዊትን ወደ ጾታ ብልግና የመራው ምን ነበር?
15 በሌላም ወቅት እንዲሁ፣ ዳዊት ለአምላክ ያለው ፍርሃት መቀነሱ ከኦርዮን ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽም አድርጎታል። ዳዊት ማመንዘር፣ ሌላው ቀርቶ የሌላውን ሚስት መመኘት እንኳ ስህተት መሆኑን ያውቅ ነበር። (ዘፀአት 20:14, 17) ችግሩ የጀመረው ቤርሳቤህ ገላዋን ስትታጠብ በተመለከተ ጊዜ ነበር። ለአምላክ ያለው ጤናማ ፍርሃት ዓይኑን ወዲያውኑ እንዲመልስና ትኩረቱን በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይገባ ነበር። ሆኖም ዳዊት ይህን ከማድረግ ይልቅ ስሜቱ ለአምላክ ያለውን ፍርሃት እስኪሸፍንበት ድረስ ‘መመልከቱን’ ቀጠለ። (ማቴዎስ 5:28፤ 2 ሳሙኤል 11:1-4) ዳዊት ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ጥብቅ ዝምድና መላ አኗኗሩን እንደሚነካ ዘንግቶ ነበር።—መዝሙር 139:1-7
16. ዳዊት ኃጢአት በመሥራቱ ምን ደርሶበታል?
16 ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በፈጸመው ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ሳቢያ ቤርሳቤህ ወንድ ልጅ ጸነሰች። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ነቢዩ ናታንን በመላክ የዳዊት ኃጢአት እንዲጋለጥ አደረገ። ዳዊትም ወደ አእምሮው በመመለስ በድጋሚ ለይሖዋ ያለውን ፍርሃት ማደስና ንስሐ መግባት ቻለ። ይሖዋ እንዳይጥለውና ቅዱስ መንፈሱን እንዳይወስድበት ተማጸነ። (መዝሙር 51:7, 11) ይሖዋ ዳዊትን ይቅርታ ያደረገለትና የሚደርስበትን ቅጣት ያቀለለት ቢሆንም የፈጸመው መጥፎ ምግባር ካመጣበት ችግር ግን ሙሉ በሙሉ አልጋረደውም። ልጁ የሞተበት ሲሆን ቤተሰቡ ላይ ሥቃይና መከራ ደርሷል። በእርግጥም፣ ለአምላክ ያለን ፍርሃት እንዲቀንስ መፍቀድ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል!—2 ሳሙኤል 12:10-14፤ 13:10-14፤ 15:14
17. ኃጢአት መፈጸም የሚያስከትለውን አሳዛኝ ውጤት በምሳሌ አስረዳ።
17 በተመሳሳይም፣ በዛሬው ጊዜ በሥነ ምግባር ረገድ አምላካዊ ፍርሃትን ሳያሳዩ መቅረት ከፍተኛና ዘላቂ የሆነ ችግር እያስከተለ ይገኛል። አንዲት ወጣት፣ ክርስቲያን የሆነው ባሏ በሌላ አገር ይሠራ በነበረበት ወቅት ለእርሷ ያለውን ታማኝነት ማጉደሉን ስታውቅ ምን እንደተሰማት ገምት። በድንጋጤና በሐዘን በመዋጧ ፊቷን በእጆቿ በመሸፈን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ባለቤቷ በእርሷ ዘንድ የነበረውን አመኔታና ክብር መልሶ ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ይወስድበት ይሆን? እውነተኛ አምላካዊ ፍርሃት ይህን ከመሰለው አሳዛኝ ሁኔታ ይጠብቀናል።—1 ቆሮንቶስ 6:18
አምላካዊ ፍርሃት ከኃጢአት ይጠብቀናል
18. የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው? ይህን ከግብ ለማድረስ የትኞቹን ነገሮች ይጠቀማል?
18 ሰይጣን፣ የዓለም የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በፍጥነት እንዲያሽቆለቁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህን የሚያደርገው በዋነኝነት የእውነተኛ ክርስቲያኖችን አቋም ለማበላሸት ሲል ነው። እንዲህ ለማድረግ ከልባችንና ከአእምሯችን ጋር በቀጥታ የተያያዙትን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን በተለይም ደግሞ ዓይናችንንና ጆሯችንን እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። (ኤፌሶን 4:17-19) የብልግና ምስሎችም ሆኑ አነጋገሮች ወይም ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች ቢያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?
19. አንድ ክርስቲያን አምላክን መፍራቱ የደረሰበትን ፈተና እንዲቋቋም የረዳው እንዴት ነው?
19 የጉባኤ ሽማግሌ፣ የልጆች አባትና ሐኪም የሆነው አንድሬb ያጋጠመውን ሁኔታ ተመልከት። በአውሮፓ የሚኖረው አንድሬ በሆስፒታል ውስጥ የሌሊት ተረኛ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ ሴት የሥራ ባልደረቦቹ የጻፏቸውን አብሯቸው እንዲተኛ የሚጠይቁ በልብ ሥዕሎች ያጌጡ ወረቀቶችን ትራሱ ላይ ተለጥፈው ያገኝ ነበር። ሆኖም አንድሬ እነዚህን ማባበያዎች በፍጹም አልተቀበለም። ከዚህም በላይ ይህን ለመሰለው ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ራሱን ላለማጋለጥ ሲል ሥራውን ለቅቆ በሌላ ቦታ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። አምላክን መፍራት ወደር የማይገኝለት ጥበብና በረከት ያስገኛል። በአሁኑ ወቅት አንድሬ በአካባቢው በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ግማሽ ቀን በማገልገል ላይ ይገኛል።
20, 21. (ሀ) አምላክን መፍራት ኃጢአት እንዳንሠራ የሚጠብቀን እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?
20 መጥፎ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል አንድ ሰው ማድረግ የሌለበትን እንዲያደርግ ሊያነሳሳው የሚችል ሲሆን ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለውን ውድ ዝምድና ወደማጣት ይመራዋል። (ያዕቆብ 1:14, 15) በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይሖዋን የምንፈራ ከሆነ የሥነ ምግባር አቋማችንን እንድናላላ ከሚያደርጉን ሰዎች፣ ቦታዎች፣ ድርጊቶችና መዝናኛዎች እንርቃለን። (ምሳሌ 22:3) ምንም ዓይነት አሳፋሪ ሁኔታ ይድረስብን ወይም የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ይጠይቅብን፣ እነዚህን ነገሮች የአምላክን ሞገስ ከማግኘት ጋር ስናወዳድራቸው እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። (ማቴዎስ 5:29, 30) አምላክን መፍራት፣ ለወሲባዊ ምስሎችም ይሁን እነዚህን ለመሳሰሉ ከሥነ ምግባር ውጭ ለሆኑ ነገሮች ሆነ ብለን ራሳችንን ከማጋለጥ እንድንቆጠብና ‘ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቻችንን እንድንመልስ’ ሊገፋፋን ይገባል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ‘ሕያው አድርጎ’ እንደሚያቆየንና የምንፈልገውንም ሁሉ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝሙር 84:11፤ 119:37
21 በእርግጥም፣ ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ማዳበር ጥበብን ያስገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነው። (መዝሙር 34:9) ይህ ጉዳይ በቀጣዩ ርዕስ ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው በጥር 8, 1998 (እንግሊዝኛ) የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- አፍቃሪውን አምላክ ልትፈራው የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ስሙ ተቀይሯል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• አምላካዊ ፍርሃት የትኞቹን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ያጠቃልላል?
• አምላካዊ ፍርሃት የሰውን ፍርሃት ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
• ለጸሎት ተገቢ አመለካከት እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን?
• አምላክን መፍራት ከኃጢአት የሚጠብቀን እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት የይሖዋን የእጅ ሥራዎች መመልከቱ አምላክን መፍራት አስተምሮታል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ፈታኝ የሆነ ሁኔታ በድንገት ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?