ጉባኤው ይሖዋን ያወድሰው
“ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጒባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ።” —ዕብራውያን 2:12
1, 2. የጉባኤ ዝግጅት በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ዋና ዓላማውስ ምንድን ነው?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ፣ የቤተሰብ ዝግጅት ሰዎች አጋር እንዲያገኙና የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንዲችሉ አስተዋጽኦ አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች ለየት ያለ ወዳጅነት ማግኘት እንዲችሉና የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሌላም ዝግጅት እንዳለ ይገልጻል። ይህ ዝግጅት የክርስቲያን ጉባኤ ነው። እርስ በርስ የሚቀራረብና የሚደጋገፍ ቤተሰብ ኖረህም አልኖረህ፣ አምላክ በጉባኤው በኩል ላደረገው ዝግጅት አመስጋኝ መሆን ትችላለህ፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርብሃል። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የምትሰበሰብ ከሆነ ጉባኤው የልብ ወዳጆች ለማግኘት እንደሚያስችል እንዲሁም የመረጋጋት ስሜት እንደሚያሳድር መመሥከር ትችላለህ።
2 የክርስቲያን ጉባኤ ሰዎች ተሰባስበው ከሚመሠርቱት ማኅበራዊ ቡድን የተለየ ነው። ጉባኤው አንድ ዓይነት አስተዳደግና የኑሮ ሁኔታ አሊያም በስፖርት ወይም በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ረገድ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚሰባሰቡበት ማኅበር ወይም ክበብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የጉባኤ ዝግጅት የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋ አምላክን ለማወደስ ነው። የመዝሙር መጽሐፍ ጎላ አድርጎ እንደሚያሳየው ከጥንት ጀምሮም የጉባኤ ዓላማ ይህ ነበር። መዝሙር 35:18 “በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ” ይላል። በተመሳሳይም በመዝሙር 107:31, 32 ላይ “እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት” የሚል ማበረታቻ ቀርቦልናል።
3. ጳውሎስ እንደተናገረው ጉባኤው ምን ሚና ይጫወታል?
3 ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔር ቤት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን [“ጉባኤ፣” NW] ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው’ ብሎ ሲናገር ጉባኤ ሌላም ጠቃሚ ሚና እንደሚጫወት መግለጹ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ጳውሎስ ስለ የትኛው ጉባኤ መናገሩ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት በየትኞቹ መንገዶች ነው? የጉባኤ ዝግጅት በአሁኑ ሕይወታችንም ሆነ በወደፊት ተስፋችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል በየትኞቹ መንገዶች እንደሚጠቀምበት እንመርምር።
4. “ጉባኤ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በብዛት የተሠራበት እንዴት ነው?
4 አብዛኛውን ጊዜ “ጉባኤ” ተብሎ የሚተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘መሰብሰብ’ ከሚል መሠረታዊ ቃል የመጣ ነው። (ዘዳግም 4:10፤ 9:10 የ1954 ትርጉም) መዝሙራዊው በሰማይ ስለሚገኙት መላእክት ሲናገር “ጉባኤ” በሚለው ቃል የተጠቀመ ሲሆን ይኸው ቃል የክፉዎችን ማኅበር ለማመልከትም ተሠርቶበታል። (መዝሙር 26:5 የታረመው የ1980 ትርጉም፤ 89:5-7) ይሁን እንጂ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ቃል የሚጠቀሙበት እስራኤላውያንን ለማመልከት ነው። አምላክ፣ ያዕቆብ “ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ” እንደሚሆን የጠቆመ ሲሆን ይህም ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘፍጥረት 28:3 የ1954 ትርጉም፤ 48:4 የ1954 ትርጉም) እስራኤላውያን ‘የእግዚአብሔር ጉባኤ’ እንዲሁም “የእውነተኛው አምላክ ጉባኤ” እንዲሆኑ ተጠርተው ወይም ተመርጠው ነበር።—ዘኍልቍ 20:4 የ1954 ትርጉም፤ ነህምያ 13:1 NW፤ ኢያሱ 8:35፤ ሚክያስ 2:5
5. አብዛኛውን ጊዜ “ጉባኤ” ተብሎ የሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምንድን ነው? ይህስ ቃል እንዴት ሊሠራበት ይችላል?
5 “ጉባኤ” ተብሎ የተተረጎመው ኤክሌሲያ የሚለው የግሪክኛ ቃል “መውጣት” እና “መጥራት” የሚል ትርጉም ካላቸው ሁለት የግሪክኛ ቃላት የመጣ ነው። ይህ ቃል ሃይማኖታዊ ላልሆነ ዓላማ የተሰበሰቡ ሰዎችንም ሊያመለክት ይችላል፤ ድሜጥሮስ በኤፌሶን ከተማ በጳውሎስ ላይ ሁከት ለማስነሳት ያሰባሰበውን “ጉባኤ” እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። (የሐዋርያት ሥራ 19:32, 39, 41) መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን ቃል ብዙውን ጊዜ የሚጠቀምበት የክርስቲያን ጉባኤን ለማመልከት ነው። እንደ አማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ያሉ አንዳንድ ትርጉሞች “ጉባኤ” የሚለውን ቃል “ቤተ ክርስቲያን” ብለው ቢተረጉሙትም ዚ ኢምፔሪያል ባይብል ዲክሽነሪ፣ ቃሉ “ክርስቲያኖች ለሕዝባዊ አምልኮ የሚሰበሰቡበትን ሕንፃ ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም” ብሏል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ጉባኤ” የሚለው ቃል ቢያንስ በአራት መንገዶች የተሠራበት መሆኑ ያስገርማል።
ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈው የአምላክ ጉባኤ
6. ዳዊትና ኢየሱስ በጉባኤ መካከል ምን አድርገዋል?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በመዝሙር 22:22 ላይ ዳዊት የተናገረው ሐሳብ በኢየሱስ ላይ እንዴት እንደተፈጸመ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “‘ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤ በጒባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ።’ ስለዚህ [ኢየሱስ] በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ እግዚአብሔርን ለማገልገል . . . ነው።” (ዕብራውያን 2:12, 17) ዳዊት በጥንቷ እስራኤል ጉባኤ መካከል አምላክን አወድሶታል። (መዝሙር 40:9) ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ አምላክን “በጉባኤም መካከል” እንዳወደሰው ሲናገር ስለ የትኛው ጉባኤ መግለጹ ነበር?
7. “ጉባኤ” የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በዋነኝነት የተሠራበት እንዴት ነው?
7 በዕብራውያን 2:12, 17 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ትልቅ ትርጉም አለው። ይህ ጥቅስ፣ ክርስቶስ የአምላክን ስም ለወንድሞቹ የተናገረበት ጉባኤ አባል እንደነበረ ያሳያል። እነዚህ ወንድሞቹ እነማን ነበሩ? ‘የአብርሃም ዘር’ አባላትና “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” እንዲሁም በመንፈስ የተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች ናቸው። (ዕብራውያን 2:16 እስከ 3:1፤ ማቴዎስ 25:40) ከዚህ ለመመልከት እንደሚቻለው፣ “ጉባኤ” የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በዋነኝነት የተሠራበት በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ተከታዮችን በጥቅሉ ለማመልከት ነው። እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ 144,000 ክርስቲያኖች ‘ስማቸው በሰማይ የተጻፈው የበኲራት ማኀበር’ ወይም ጉባኤ ናቸው።—ዕብራውያን 12:23
8. ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ እንደሚቋቋም አስቀድሞ ያመለከተው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ ይህ የክርስቲያን “ጉባኤ” እንደሚቋቋም ተናግሮ ነበር። ከመሞቱ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከሐዋርያቱ ለአንዱ እንዲህ ብሎት ነበር:- “አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን [“ጉባኤዬን፣” NW] እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም።” (ማቴዎስ 16:18) ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ አስቀድሞ የተነገረለት ዐለት ኢየሱስ እንደሆነ በትክክል ተረድተው ነበር። ጴጥሮስ፣ ዐለት በሆነው በክርስቶስ ላይ የመንፈሳዊ ቤት “ሕያዋን ድንጋዮች” ሆነው የሚገነቡት ሰዎች፣ የጠራቸውን አምላክ ‘ታላቅ ሥራ እንዲያውጁ እግዚአብሔር ለራሱ የለያቸው ሕዝብ’ እንደሆኑ ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:4-9፤ መዝሙር 118:22፤ ኢሳይያስ 8:14፤ 1 ቆሮንቶስ 10:1-4
9. የአምላክ ጉባኤ መቋቋም የጀመረው መቼ ነበር?
9 ይሖዋ ‘ለራሱ የለየው ይህ ሕዝብ’ የክርስቲያን ጉባኤ ሆኖ መቋቋም የጀመረው መቼ ነበር? በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው በነበሩት ደቀ መዛሙርት ላይ አምላክ መንፈስ ቅዱስን ባፈሰሰበት ወቅት ነበር። በዚያኑ ዕለት ጴጥሮስ ለአይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ሰዎች ግሩም ንግግር አቀረበ። ብዙዎች በኢየሱስ ሞት ልባቸው በመነካቱ ንስሐ ገብተው ተጠመቁ። ይህ ታሪካዊ ዘገባ እንደሚገልጸው እንዲህ ያደረጉት ሦስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ፤ በዚህ መንገድ አዲስ የተቋቋመውና እድገት እያደረገ ያለው የአምላክ ጉባኤ አባላት ሆኑ። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 14, 37-47) ቁጥራቸው እያደገ የሚሄድ አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች፣ ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ ጉባኤ መሆናቸው እንደቀረ በመገንዘባቸው አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ አባላት ይጨምሩ ነበር። መንፈሳዊ ‘የአምላክ እስራኤል’ የሆኑት የተቀቡ ክርስቲያኖች በሥጋዊ እስራኤላውያን ምትክ የእውነተኛው አምላክ ጉባኤ ሆኑ።—ገላትያ 6:16፤ የሐዋርያት ሥራ 20:28
10. ኢየሱስ ከአምላክ ጉባኤ ጋር ያለው ዝምድና ምን ይመስላል?
10 መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ በኢየሱስና በቅቡዓን መካከል ልዩነት እንዳለ ይገልጻል፤ ለዚህም ‘ስለ ክርስቶስ እና ስለ ቤተ ክርስቲያን’ የሚለውን ሐረግ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ኢየሱስ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው የዚህ ጉባኤ ራስ ነው። አምላክ፣ ኢየሱስን “በቤተ ክርስቲያንም፣ [“በጉባኤም፣” NW] በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው። እርሷም . . . አካሉ ናት” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (ኤፌሶን 1:22, 23፤ 5:23, 32፤ ቈላስይስ 1:18, 24) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የቀሩት የዚህ ጉባኤ አባላት የሆኑ ቅቡዓን በጣም ጥቂት ናቸው። የእነዚህ ቅቡዓን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወዳቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በኤፌሶን 5:25 ላይ የሚገኘው “ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ” የሚለው ሐሳብ ኢየሱስ ለቅቡዓኑ ያለውን ስሜት ይገልጻል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ቅቡዓኑም ለአምላክ “የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመስክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” በማቅረቡ ሥራ የተጠመዱ በመሆናቸው ይወዳቸዋል።—ዕብራውያን 13:15
“ጉባኤ” የሚለው ቃል የተሠራባቸው ሌሎች መንገዶች
11. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት “ጉባኤ” የሚለውን ቃል ምንን ለማመልከትም ይጠቀሙበታል?
11 አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል ‘በአምላክ ጉባኤ’ ውስጥ የታቀፉትን የ144,000 ቅቡዓን አባላት በሙሉ ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። ለአብነት ያህል፣ ጳውሎስ ለተወሰኑ ክርስቲያኖች “ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን [“ጉባኤ፣” NW] መሰናክል አትሁኑ” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:32) በጥንቷ ቆሮንቶስ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽም ይህ ለአንዳንዶች እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ግለሰብ የፈጸመው ድርጊት በዚያን ጊዜም ሆነ በዘመናችን የኖሩትን ሁሉንም ግሪኮች፣ አይሁዶች ወይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሊያሰናክል ይችላል? ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። በመሆኑም በዚህ ጥቅስ ላይ ‘የአምላክ ጉባኤ’ የሚለው አባባል የተሠራበት በተወሰነ ወቅት የኖሩትን ክርስቲያኖች ለማመልከት ይመስላል። በዚህ መሠረት አንድ ሰው አምላክ ጉባኤውን እንደሚመራው፣ እንደሚደግፈው ወይም እንደሚባርከው ሊናገር ይችላል፤ ይህንንም ሲል በየትኛውም ቦታ የሚገኙ በአንድ ወቅት የኖሩ ክርስቲያኖችን በሙሉ ማመልከቱ ነው። ወይም በዛሬው ጊዜ በአምላክ ጉባኤ ማለትም በመላው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረት ውስጥ ስለሚታየው ደስታና ሰላም ልንናገር እንችላለን።
12. መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል በምን ሌላ መንገድ ተጠቅሞበታል?
12 መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት ሦስተኛው መንገድ ደግሞ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖችን በአጠቃላይ ለማመልከት ነው። የአምላክ ቃል “በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን [“ጉባኤ፣” NW] በሰላም መኖር ጀመረች” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 9:31) ሰፊ ቦታ በሚሸፍነው በዚህ አካባቢ ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡባቸው በርካታ ቡድኖች ነበሩ፤ ሆኖም በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ባሉት በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙት ክርስቲያኖች በሙሉ እንደ አንድ “ጉባኤ” ተደርገው ተገልጸዋል። እንዲያውም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለትና ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከተጠመቁት ሰዎች አንጻር በኢየሩሳሌም አካባቢ አዘውትረው ይሰበሰቡ የነበሩት ክርስቲያኖች ከአንድ ቡድን በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 2:41, 46, 47፤ 4:4፤ 6:1, 7) ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ በ44 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በይሁዳ የገዛ ሲሆን ከ1 ተሰሎንቄ 2:14 በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ቢያንስ እስከ 50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በይሁዳ በርካታ ጉባኤዎች ነበሩ። በመሆኑም ሄሮድስ “አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን [“የጉባኤ፣” NW] አባላትን እያሳደደ ያስጨንቅ” እንደነበር የሚገልጸው ዘገባ በኢየሩሳሌም የሚሰበሰቡ ከአንድ በላይ ጉባኤዎች እንደነበሩ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 12:1
13. መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት አራተኛ መንገድ ምንድን ነው?
13 “ጉባኤ” የሚለው ቃል የተሠራበት አራተኛው መንገድ በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት ነው፤ ቃሉ አንድ ጉባኤን፣ ለምሳሌ በአንድ ቤት ውስጥ የሚሰበሰቡ ክርስቲያኖችን ሊያመለክት የሚችል ሲሆን በዚህ መንገድ ደግሞ ብዙ ጊዜ ይሠራበታል። ጳውሎስ ‘በገላትያ ስላሉት አብያተ ክርስቲያናት’ ወይም ጉባኤዎች ጠቅሷል። በዚህ ሰፊ የሮም ግዛት ውስጥ በርካታ ጉባኤዎች ነበሩ። ጳውሎስ ስለ ገላትያ ሲናገር “አብያተ ክርስቲያናት” ወይም ጉባኤዎች የሚለውን ብዙ ቁጥር የተጠቀመው ሁለት ጊዜ ሲሆን ይህ አገላለጽ በአንጾኪያ፣ በደርቤን፣ በልስጥራንና በኢቆኒዮን የሚገኙትን ጉባኤዎች ያካትታል። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ይሾሙ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 16:1፤ ገላትያ 1:2፤ የሐዋርያት ሥራ 14:19-23) በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት እነዚህ ሁሉ ‘የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት’ ወይም ጉባኤዎች ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 11:16፤ 2 ተሰሎንቄ 1:4
14. በተወሰኑ ጥቅሶች ላይ “ጉባኤ” የሚለው ቃል ከተሠራበት መንገድ አንጻር ምን ብለን መደምደም እንችላለን?
14 አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚኖሩት ተሰብሳቢዎች ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ የሚሰበሰቡት በግለሰቦች ቤት ውስጥ ነበር። ያም ቢሆን ግን “ጉባኤ” የሚለው ቃል እነዚህን አነስተኛ ቡድኖችም ለማመልከት ይሠራል። በአቂላና በጵርስቅላ፣ በንምፉን እንዲሁም በፊልሞና ቤት ውስጥ የሚሰበሰቡ ጉባኤዎች እንደነበሩ እናውቃለን። (ሮሜ 16:3-5፤ ቈላስይስ 4:15፤ ፊልሞና 2) ይህ ደግሞ፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና አዘውትረው በግለሰቦች ቤት ውስጥ የሚሰበሰቡ ጉባኤዎችን ሊያበረታታቸው ይገባል። ይሖዋ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ እንደነዚህ ያሉ አነስተኛ ጉባኤዎችን እንደ ሌሎቹ ጉባኤዎች አድርጎ ይመለከታቸው ነበር፤ በዛሬው ጊዜ ስላሉት አነስተኛ ጉባኤዎችም ተመሳሳይ አመለካከት እንዳለውና በመንፈሱ አማካኝነት እንደሚባርካቸው ጥርጥር የለውም።
ጉባኤዎች ይሖዋን ያወድሳሉ
15. ጥንት በነበሩት አንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ምን ማድረግ ችለው ነበር?
15 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በመዝሙር 22:22 ፍጻሜ መሠረት ኢየሱስ አምላክን በጉባኤ መካከል አወድሶታል። (ዕብራውያን 2:12) ታማኝ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ተበረታትተዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ ልጆችና የክርስቶስ ወንድሞች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ በተቀቡበት ወቅት፣ የአምላክ መንፈስ በአንዳንዶች ላይ ለየት ባለ መንገድ ይሠራ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተአምራዊ ስጦታዎችን ተቀብለዋል። ይህ ስጦታ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ጥበብ ወይም እውቀት የተሞላበት ንግግር የማቅረብ ችሎታ፣ የመፈወስ ኃይል፣ ትንቢት የመናገር አሊያም እነርሱ ራሳቸው እንኳ በማያውቁት ቋንቋ የመናገር ችሎታ ይገኙበታል።—1 ቆሮንቶስ 12:4-11
16. ተአምር ለመፈጸም የሚያስችሉ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከነበሯቸው ዓላማዎች አንዱ ምን ነበር?
16 ጳውሎስ በልሳን የመናገር ችሎታን በተመለከተ “በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 14:15) ጳውሎስ ከሚናገረው ነገር ሌሎች ትምህርት እንዲያገኙ ሐሳቡን መረዳታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ዓላማው በጉባኤው መካከል ይሖዋን ማወደስ ነበር። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ያላቸውን ሌሎች ክርስቲያኖች “ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ” በማለት ያሳሰባቸው ሲሆን ይህንንም ሲል ስጦታዎቻቸውን የሚያካፍሏቸውን ጉባኤዎች ማመልከቱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:4, 5, 12, 23) ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ጳውሎስ ስለ እነዚህ ጉባኤዎች ያስብ ነበር፤ በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች አምላክን ለማወደስ አጋጣሚ እንዳላቸውም ያውቅ ነበር።
17. በዛሬው ጊዜ ያሉትን ጉባኤዎች በተመለከተ ምን ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን?
17 ይሖዋ ጉባኤውን መርዳቱንና በእርሱ መጠቀሙን አላቋረጠም። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚገኘውን በርካታ አባላት ያሉት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን እየባረከ ነው። የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኙት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይህንን ያሳያል። (ሉቃስ 12:42) ይሖዋ መላውን ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት እየባረከው ነው። ከዚህም በላይ በተግባራችንና በምንሰጣቸው የሚያንጹ መንፈሳዊ ሐሳቦች አማካኝነት ፈጣሪያችንን የምናወድስባቸውን ጉባኤዎችም ይባርካል። በሌሎች ጊዜያት ማለትም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በማንሆንበት ጊዜም አምላክን ማወደስ እንድንችል በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ትምህርትና ሥልጠና እናገኛለን።
18, 19. በየትኛውም ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ለአምላክ ያደሩ ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ ይፈልጋሉ?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ በመቄዶንያ በምትገኘው በፊልጵስዩስ ከተማ በነበረው ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያኖች “ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ [እጸልያለሁ]” ብሏቸው እንደነበረ አስታውስ። ይህም በኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነትና ድንቅ ስለሆነው ተስፋቸው ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች መናገርን ይጨምር ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:9-11፤ 3:8-11) በመሆኑም ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን “ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል።—ዕብራውያን 13:15
19 ኢየሱስ እንዳደረገው “በጒባኤም መካከል” አምላክን በማወደስ ትደሰታለህ? በአሁኑ ጊዜ አምላክን በማያውቁትና በማያወድሱት ሰዎች መካከልስ ይሖዋን በከንፈሮችህ ታወድሰዋለህ? (ዕብራውያን 2:12፤ ሮሜ 15:9-11) በግለሰብ ደረጃ ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሚመካው ጉባኤያችን በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ባለን አመለካከት ላይ ነው። ይሖዋ ጉባኤያችንን እንዴት እንደሚመራውና እንደሚጠቀምበት እንዲሁም የጉባኤ ዝግጅት በዛሬው ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።
ታስታውሳለህ?
• ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈው ‘የአምላክ ጉባኤ’ ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?
• መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤ” የሚለውን ቃል በየትኞቹ ሌሎች ሦስት መንገዶችም ይጠቀምበታል?
• ዳዊት፣ ኢየሱስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በጉባኤው ውስጥ ምን ማድረግ ፈልገው ነበር? ይህስ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የየትኛው ጉባኤ መሠረት ነበር?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቡድን የሚሰበሰቡት ክርስቲያኖች ‘የአምላክ ጉባኤዎች’ ነበሩ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤኒን እንዳሉት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በታላቅ ጉባኤ መካከል ይሖዋን ማወደስ እንችላለን