ምሕረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
“ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ።”—ገላትያ 6:10
1, 2. ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረው ምሳሌ ስለ ምሕረት ምን ያስተምረናል?
አንድ የሕግ አዋቂ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገር “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የሚከተለውን ምሳሌ ነገረው:- “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቁልቁል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ አለፈ። ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ ቀርቦም ቁስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለ ቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጪ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።” ቀጥሎም ኢየሱስ ለሕግ አዋቂው እንዲህ ሲል ጠየቀው:- “ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ አዋቂውም “የራራለት [“ምሕረት ያደረገለት፣” የ1954 ትርጉም] ነዋ” ሲል መለሰ።—ሉቃስ 10:25, 29-37ሀ
2 ሳምራዊው ጉዳት ለደረሰበት ሰው ያደረገለት እንክብካቤ የምሕረትን ትክክለኛ ትርጉም በግልጽ ያሳያል! ሳምራዊው በሐዘኔታና በርኅራኄ ስሜት ተነሳስቶ ለተጎዳው ሰው የሚያስፈልገውን እርዳታ አድርጎለታል። ከዚህም በላይ ሳምራዊው ችግር የደረሰበትን ሰው አያውቀውም። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የባሕል ልዩነት ምሕረት ላለማሳየት ምክንያት አይሆንም። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ ለሕግ አዋቂው ከነገረው በኋላ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” ሲል መከረው። (ሉቃስ 10:37ለ) እኛም ይህን ምክር ልብ ማለትና ለሌሎች ምሕረት ለማሳየት መጣር ይኖርብናል። ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ምሕረት ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
‘አንድ ወንድም የሚለብሰው ልብስ ቢያጣ’
3, 4. በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላሉት ምሕረት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ “ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” ብሏል። (ገላትያ 6:10) በመሆኑም በመጀመሪያ ለእምነት አጋሮቻችን ምሕረት ማሳየት የምንችልባቸውን በርካታ መንገዶች እንመልከት።
4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እውነተኛ ክርስቲያኖችን አንዳቸው ለሌላው ምሕረት እንዲያሳዩ ሲያሳስባቸው “ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 2:13) በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምሕረት ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ይጠቁመናል። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብ 1:27 እንዲህ ይላል:- “በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኵሰት ራስን መጠበቅ ነው።” በተጨማሪም ያዕቆብ 2:15, 16 እንደሚከተለው ይላል:- “አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ ‘በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ’ ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?”
5, 6. በጉባኤያችን ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምሕረት ማሳየት ከምንችልባቸው በርካታ መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
5 ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትና የተቸገሩትን መርዳት የእውነተኛ ሃይማኖት አንዱ ገጽታ ነው። አምልኳችን ለሌሎች መልካም ምኞታችንን በቃላት ብቻ ከመግለጽ የበለጠ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። የርኅራኄ ስሜት በከባድ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንድናደርግላቸው ያነሳሳናል። (1 ዮሐንስ 3:17, 18) አዎን፣ ለታመመ ሰው ምግብ ማዘጋጀት፣ አረጋውያንን የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማገዝ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመኪናችን ወደ ስብሰባ ማምጣትና ለሚገባቸው የገንዘብ እርዳታ ከማድረግ አለመሰሰት ለሌሎች ምሕረት ከምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።—ዘዳግም 15:7-10
6 ይሁንና እያደገ በሚሄደው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች በመንፈሳዊ መርዳት ቁሳዊ ልግስና ከማድረግ የበለጠ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው” በማለት ያሳስበናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) “አሮጊቶች . . . በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ” እንዲሆኑ ተበረታተዋል። (ቲቶ 2:3) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ‘ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ መሆን’ እንዳለባቸው ይገልጻል።—ኢሳይያስ 32:2
7. በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ ይኖሩ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ምሕረት ስለማሳየት ምን እንማራለን?
7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች መበለቶችን፣ ወላጅ አልባ ልጆችን እንዲሁም ድጋፍና ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻቸውን ከመርዳት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ላሉ አማኞች አልፎ አልፎ እርዳታ ይልኩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ አጋቦስ “በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን” ትንቢት በተናገረ ጊዜ በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት “እያንዳንዳቸው ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ የሚኖሩትን ወንድሞች ለመርዳት ወሰኑ።” እርዳታውንም “በበርናባስና በሳውል እጅ” በዚያ ለሚገኙ ሽማግሌዎች ላኩ። (የሐዋርያት ሥራ 11:28-30) በዛሬው ጊዜስ? “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደ አውሎ ነፋስ፣ የምድር መናወጥ ወይም ሱናሚ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚጎዱ ወንድሞችን ለመርዳት የእርዳታ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ይህን ዝግጅት ለመደገፍ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን በፈቃደኝነት መስጠታችን ለሌሎች ምሕረት የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው።
‘አድልዎ የምታደርጉ ከሆነ’
8. አድልዎ ምሕረት እንዳናሳይ እንቅፋት የሚሆነው እንዴት ነው?
8 ያዕቆብ ምሕረትን እና “ክቡር ሕግ” የተባለውን ፍቅርን እንዳናሳይ እንቅፋት ስለሚሆን አንድ ባሕርይ ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው፤ በሕግም ፊት እንደ ሕግ ተላላፊዎች ትቈጠራላችሁ።” (ያዕቆብ 2:8, 9) ሀብታም ወይም ታዋቂ ለሆኑ ሰዎች ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠት “የድኾችን ጩኸት” ችላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። (ምሳሌ 21:13) አድልዎ ምሕረት እንዳናደርግ እንቅፋት ይሆንብናል። በመሆኑም ሌሎችን በእኩል ዓይን በመመልከት ምሕረት እናሳያለን።
9. ለሚገባቸው ሰዎች የተለየ ትኩረት መስጠት ስህተት ያልሆነው ለምንድን ነው?
9 አድልዎ አናደርግም ሲባል የተለየ ትኩረት የምንሰጣቸው ሰዎች ከነጭራሹ አይኖሩም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የነበረውን አፍሮዲጡን አስመልክቶ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች አክብሯቸው” ብሏል። ለምን? “እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበር” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 2:25, 29, 30) አፍሮዲጡ በታማኝነት በማገልገሉ በሌሎች ዘንድ ሊመሰገን ይገባው ነበር። ከዚህም በላይ 1 ጢሞቴዎስ 5:17 እንዲህ ይላል:- “ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ የሚያስተዳድሩ፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች ዕጥፍ ክብር ይገባቸዋል።” ግሩም መንፈሳዊ ባሕርያት ያሉት ሰውም አድናቆት ሊቸረው ይገባል። እነዚህን ለመሰሉ ሰዎች የተለየ ትኩረት መስጠት አድልዎ ነው ሊባል አይችልም።
‘ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ምሕረት የሞላባት ናት’
10. አንደበታችንን መቆጣጠር ያለብን ለምንድን ነው?
10 ያዕቆብ አንደበትን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርስዋም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ።” ያዕቆብ ከዚህ ጋር አያይዞ የሚከተለውን ብሏል:- “መራራ ቅንአትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኵራት አይሰማችሁ፤ እውነትንም አትካዱ። እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ከምድር ከሥጋና ከአጋንንት ናት። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይገኛሉ። ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።”—ያዕቆብ 3:8-10ሀ, 14-17
11. በአንደበት አጠቃቀማችን ረገድ ምሕረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 በመሆኑም አንደበታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ‘ምሕረት የሞላበትን’ ጥበብ የምናንጸባርቅ መሆን አለመሆናችንን ያሳያል። ቅናት ስላደረብን ወይም ከሌሎች ጋር መስማማት ስላልቻልን ብቻ ስለራሳችን በጉራ የምንናገር፣ የምንዋሽ አሊያም ጎጂ ሐሜት የምናሠራጭ ከሆነስ? መዝሙር 94:4 “ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጕራ ይነዛሉ” ይላል። በተጨማሪም ጎጂ ሐሜት የአንድን ንጹሕ ሰው መልካም ስም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያጎድፍ ይችላል! (መዝሙር 64:2-4) ከዚህም በላይ ‘ውሸትን የሚዘከዝክ ሐሰተኛ ምስክር’ ምን ያህል ከባድ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አስብ። (ምሳሌ 14:5፤ 1 ነገሥት 21:7-13) ያዕቆብ አንደበትን ያለአግባብ ስለ መጠቀም ከተናገረ በኋላ “ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም” ብሏል። (ያዕቆብ 3:10ለ) እውነተኛ ምሕረት አንደበታችንን ንጹሕ፣ ሰላማዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንድንጠቀምበት ግድ ይለናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል።” (ማቴዎስ 12:36) በአንደበት አጠቃቀማችን ረገድ ምሕረት ማሳየታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
‘የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ’
12, 13. (ሀ) ብዙ ዕዳ ስለነበረበት አገልጋይ የሚናገረው ምሳሌ ስለ ምሕረት ምን ያስተምረናል? (ለ) ወንድማችንን “ሰባ ሰባት ጊዜ” ይቅር ልንለው ይገባል ሲባል ምን ማለት ነው?
12 ኢየሱስ፣ ከጌታው 60,000,000 ዲናር ስለተበደረ አገልጋይ የተናገረው ምሳሌ ምሕረት ማሳየት የሚቻልበትን ሌላ መንገድ ይጠቁማል። አገልጋዩ ዕዳውን ለመክፈል ገንዘብ ስላልነበረው ምሕረት እንዲደረግለት ጌታውን ለመነ። ጌታውም “አዘነለትና ማረው።” ይሁንና አገልጋዩ ሲወጣ 100 ዲናር የተበደረውን ሌላ አገልጋይ አገኘና በጭካኔ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው። ጌታው የሆነውን ነገር ሲሰማ ምሕረት ያደረገለትን ባሪያ አስጠርቶ እንዲህ አለው:- “አንተ ክፉ አገልጋይ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?” ከዚያም ጌታው ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም “እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል” አለ።—ማቴዎስ 18:23-35
13 ይህ ምሳሌ ምሕረት ማሳየት ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆንን እንደሚጨምር በግልጽ ያሳያል! ይሖዋ ያለብንን ከባድ የኃጢአት ዕዳ ይቅር ብሎልናል። ታዲያ እኛስ ‘የበደሉንን ይቅር ማለት’ አይገባንም? (ማቴዎስ 6:14, 15) ኢየሱስ ይቅር ስላላለው አገልጋይ የሚተርከውን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ሲል ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት [“ሰባ ሰባት ጊዜ፣” NW] እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ሲል መለሰለት። (ማቴዎስ 18:21, 22) አዎን፣ መሐሪ ሰው “ሰባ ሰባት ጊዜ” ይኸውም ምንጊዜም ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።
14. በማቴዎስ 7:1-4 መሠረት በየዕለቱ ምሕረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ምሕረት ማሳየት ስለሚቻልበት ሌላ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበትም ዐይነት ይፈረድባችኋል፤ . . . በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን፣ ‘ዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ ማለት እንዴት ትችላለህ?” (ማቴዎስ 7:1-4) ስለሆነም በሌሎች ላይ ለመፍረድ ሳንቸኩል ወይም ነቃፊ ሳንሆን ድክመታቸውን እየቻልን በየዕለቱ ምሕረት ማሳየት እንችላለን።
‘ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ’
15. ምሕረት የምናሳየው ለእምነት ባልንጀሮቻችን ብቻ ያልሆነው ለምንድን ነው?
15 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የያዕቆብ መጽሐፍ የሚናገረው ለእምነት ባልንጀሮች ምሕረት ስለማሳየት ቢሆንም፣ ምሕረት የምናሳየው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ ነው ማለት አይደለም። መዝሙር 145:9 “[ይሖዋ] ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው” ይላል። በተጨማሪም ‘አምላክን እንድንመስል’ እንዲሁም ‘ለሰው ሁሉ፣ መልካም እንድናደርግ’ ተመክረናል። (ኤፌሶን 5:1፤ ገላትያ 6:10) “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር” ባንወድም ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎች ለሚደርስባቸው ችግር ደንታ ቢሶች አይደለንም።—1 ዮሐንስ 2:15
16. ለሌሎች ምሕረት የምናሳይበትን መንገድ የሚወስኑት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
16 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ባልታሰበ “አጋጣሚ” ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወይም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የቻልነውን ያህል ለመርዳት ምንጊዜም ፈቃደኞች ነን። (መክብብ 9:11 NW) እርግጥ ነው፣ ምን ያህል መርዳት እንችላለን የሚለውን የሚወስነው ሁኔታችን ነው። (ምሳሌ 3:27) ለሌሎች ቁሳዊ እርዳታ ስንሰጥ ልግስናችን ስንፍናን የሚያበረታታ እንዳይሆን እንጠነቀቃለን። (ምሳሌ 20:1, 4፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10-12) በመሆኑም እውነተኛ ምሕረት የርኅራኄ ወይም የሐዘኔታ ስሜት ማሳየትን ብሎም ምክንያታዊ መሆንን ይጨምራል።
17. ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ምሕረት ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?
17 ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ምሕረት የምናሳይበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማካፈል ነው። ለምን? ምክንያቱም አብዛኛው የሰው ዘር በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እየዳከረ ነው። ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታም ሆነ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውነተኛ ተስፋ የላቸውም። በመሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው” ይታያሉ። (ማቴዎስ 9:36) የአምላክ ቃል የያዘው መልእክት ግን ‘ለእግራቸው መብራት’ በመሆን በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም ይረዳቸዋል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ስለሚገልጽ ‘ለመንገዳቸው ብርሃን’ በመሆን ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቅላቸዋል። (መዝሙር 119:105) ይህንን ግሩም እውነት በጣም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማካፈል ምንኛ ታላቅ መብት ነው! ‘ታላቁ መከራ’ እየተቃረበ ከመሆኑ አንጻር፣ የመንግሥቱን ወንጌል በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት የምንካፈልበት ጊዜ አሁን ነው። (ማቴዎስ 24:3-8, 21, 22, 36-41፤ 28:19, 20) የዚህን ያህል ምሕረት የሚንጸባረቅበት ሥራ የለም።
“በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ”
18, 19. በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ምሕረትን ይበልጥ ለማሳየት መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ “በውስጥ ያለውን ምጽዋት [“የምሕረት ስጦታ፣” NW] አድርጋችሁ ስጡ” ብሏል። (ሉቃስ 11:41) አንድ መልካም ድርጊት እውነተኛ ምሕረት ነው እንዲባል ከውስጥ የመነጨ ማለትም በፍቅርና በፈቃደኝነት የተደረገ መሆን ይኖርበታል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) በጭካኔና በራስ ወዳድነት በተሞላ እንዲሁም ስለ ሌሎች ሥቃይና ችግር ደንታ ቢስ በሆነ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ምሕረት ማግኘት ምንኛ የሚያጽናና ነው!
19 እንግዲያው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለሌሎች ምሕረት ለማሳየት እንጣር። ምሕረት እያሳየን በሄድን መጠን ይበልጥ አምላክን እንመስላለን። ይህም በእርግጥ ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት ለመምራት ያስችለናል።—ማቴዎስ 5:7
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• በተለይ ለእምነት አጋሮቻችን ምሕረት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምሕረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች መልካም ማድረግ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳምራዊው ምሕረት አሳይቷል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ምሕረት የሚያሳዩባቸው በርካታ መንገዶች አሉ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ምሕረት ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማካፈል ነው