ልጆቻችሁን አስተምሩ
የጳውሎስ የእህት ልጅ የአጎቱን ሕይወት አተረፈ
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የኢየሱስ ተከታይ የሆኑ ዘመዶች እንደነበሩት ታውቃለህ?a— መጽሐፍ ቅዱስ፣ እህቱና የእህቱ ልጅ የኢየሱስ ተከታዮች እንደነበሩ ይጠቁማል። የአጎቱን ማለትም የጳውሎስን ሕይወት ከሞት ያተረፈው ይህ ልጅ ነበር! የዚህ ልጅም ሆነ የእናቱ ስም ማን እንደሆነ አይታወቅም፤ ይሁንና ይህ ልጅ ያደረገው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። ምን እንዳደረገ ማወቅ ትፈልጋለህ?—
ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን አጠናቆ ኢየሩሳሌም መድረሱ ሲሆን ወቅቱ 56 ዓ.ም. ነው። ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ተይዞ ለፍርድ ሊቀርብ ነው። ይሁንና ጠላቶቹ ጳውሎስ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ አልፈለጉም። ከዚህ ይልቅ እንዲሞት ፈልገው ነበር! በመሆኑም ጳውሎስን መንገድ ላይ ጠብቀው እንዲገድሉት 40 ገደማ ሰዎችን አሰባሰቡ።
የጳውሎስ የእህቱ ልጅ ይህን ዕቅዳቸውን በሆነ መንገድ ሰማ። በዚህ ጊዜ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— ወደ ጳውሎስ በመሄድ ስለ ጉዳዩ ነገረው። ወዲያውኑም ጳውሎስ ከመኮንኖቹ አንዱን ጠርቶ “ይህ ወጣት ለሠራዊቱ ሻለቃ የሚነግረው ነገር ስላለው ወደ እሱ ውሰደው” አለው። መኮንኑም ወደ ሻለቃ ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ከወሰደው በኋላ ልጁ በጣም አስፈላጊ መልእክት ሊነግረው እንደሚፈልግ ገለጸለት። ቀላውዴዎስም የጳውሎስን የእህት ልጅ ለብቻው ወሰደው፤ ከዚያም ልጁ ሁሉንም ነገር ነገረው።
ቀላውዴዎስ የጳውሎስን የእህት ልጅ “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም እንዳታወራ” በማለት አስጠነቀቀው። ከዚያም ከመኮንኖቹ መካከል ሁለቱን ጠርቶ ጳውሎስን በማጀብ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ 200 ወታደሮች፣ 70 ፈረሰኞችና ጦር የያዙ 200 ሰዎች እንዲያዘጋጁ ነገራቸው። የዚያን ዕለት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ 470ዎቹ ሰዎች ጳውሎስን ይዘው ጉዞ የጀመሩ ሲሆን ቂሳርያ ለሚገኘው ለሮማዊው አገረ ገዥ ለፊሊክስ በደህና አስረከቡት። ቀላውዴዎስ ለፊሊክስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጳውሎስን ለመግደል ስለተጠነሰሰው ሴራ ገልጾ ነበር።
በመሆኑም አይሁዶች በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ በሕግ ፊት ለማቅረብ ቂሳርያ ወደሚገኘው ፍርድ ቤት መሄድ ግድ ሆነባቸው። ጳውሎስ ጥፋተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ጳውሎስ ያለ ምንም ምክንያት ለሁለት ዓመት ታሰረ። በመሆኑም ሮም በሚገኘው ፍርድ ቤት ለመዳኘት ይግባኝ ጠየቀ፤ በጥያቄው መሠረትም ጳውሎስ ወደዚያ ተላከ።—የሐዋርያት ሥራ 23:16 እስከ 24:27፤ 25:8-12
ስለ ጳውሎስ የእህት ልጅ ከሚናገረው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?— ሌሎች ሊያውቁት የሚገባቸውን ትክክለኛ ነገር ለማሳወቅ ድፍረት እንደሚጠይቅና እንዲህ ማድረጋችን የሰዎችን ሕይወት ሊታደግ እንደሚችል እንማራለን። ኢየሱስ ጠላቶቹ ‘ሊገድሉት እንደሚፈልጉ’ ቢያውቅም ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት መናገሩን አላቆመም። ኢየሱስ እኛም እንዲሁ እንድናደርግ አዞናል። ታዲያ ይህን ትእዛዝ እንፈጽማለን? የጳውሎስ የእህት ልጅ የነበረው ዓይነት ድፍረት ካለን ትእዛዙን እንፈጽማለን።—ዮሐንስ 7:1፤ 15:13፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:18-20
ጳውሎስ ለወጣቱ ጓደኛው ለጢሞቴዎስ እንደሚከተለው በማለት መክሮታል፦ “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ። በእነዚህ ነገሮች ጽና፤ ምክንያቱም ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) የጳውሎስ የእህቱ ልጅም አጎቱ የሰጠውን እንዲህ ያለ ማበረታቻ በተግባር አውሎ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። አንተስ ይህን ማበረታቻ በተግባር ታውላለህ?
a ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ የተደረገው ቆም ብለህ ጥያቄውን ለልጆቹ እንድታቀርብላቸው ለማስታወስ ተብሎ ነው።