በዚህ አስጨናቂ ዓለም ውስጥ ሰላም ማግኘት ትችላለህ?
ሰላማዊ ሕይወት እየመራህ ነው? ብዙዎች ለዚህ ጥያቄ ‘አይደለም’ የሚል መልስ እንደሚሰጡ ግልጽ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት በጦርነት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በጎሳ ግጭት ወይም በሽብርተኝነት በሚታመሱ አካባቢዎች ነው። አንተ እንደነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ባትኖርም እንኳ ወንጀል፣ ሰዎች የሚያደርሱብህ ጥቃት እንዲሁም ከሥራ ባልደረቦችህ ወይም ከጎረቤቶችህ ጋር የሚፈጠር አለመግባባት ሰላም ይነሳህ ይሆናል። የቤተሰብ ሕይወትም ቢሆን በአብዛኛው ሰላም የሰፈነበት ከመሆን ይልቅ የጦርነት ቀጣና ሆኗል።
ብዙ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት ይመኛሉ። ስለሆነም የአንድ ሃይማኖት ተከታይ በመሆን፣ ለማሰላሰል የሚረዱ ዘዴዎችን በመማር አሊያም በዮጋ አማካኝነት ይህን ምኞታቸውን ለማሟላት ይጥራሉ። ሌሎች ደግሞ እረፍት ወስደው ወደ አንድ ቦታ በመሄድ፣ ተራራ በመውጣት ወይም ሰው የማይኖርባቸውን አካባቢዎችና የተፈጥሮ ፍልውኃዎችን በመጎብኘት ተፈጥሮ የሚሰጠውን ሰላም ለማግኘት ይሞክራሉ። እነዚህ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኙ ቢሰማቸውም ያገኙት ሰላም እውነተኛና ዘላቂ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድባቸውም።
ታዲያ እውነተኛ ሰላም ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? የሰላም ምንጭ፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” እሱ ስለሆነ ነው። (ሮም 15:33) በቅርቡ በሚመጣው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ሰላም ይበዛል።” (መዝሙር 72:7፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ ሰላም ሰዎች ከሚያደርጉት ከንቱ የሰላም ስምምነት ፈጽሞ የተለየ ነው። በአብዛኛው እንዲህ ያሉት ስምምነቶች ለአጭር ጊዜ ከሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ያለፉ አይደሉም። አምላክ የሚሰጠው ሰላም ግን ለጦርነትና ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ ያስወግዳል። እንዲያውም ማንም ሰው ጦርነትን አይማርም። (መዝሙር 46:8, 9) በመጨረሻም እውነተኛ ሰላም ይሰፍናል!
ይህ አስደሳች ተስፋ እንዳለ ሆኖ፣ በአሁኑ ጊዜም የተወሰነ ሰላም ለማግኘት እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም። በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ እየኖርክ ውስጣዊ ሰላም ልታገኝ የምትችልበት መንገድ አለ? የሚያስደስተው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ሰላም የምናገኝበትን መንገድ ይጠቁመናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ በ4ኛው ምዕራፍ ላይ የሰፈሩትን አንዳንድ መመሪያዎች እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ከቁጥር 4 እስከ 13 ያለውን ሐሳብ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
“የአምላክ ሰላም”
ፊልጵስዩስ 4:7 እንዲህ ይላል፦ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” ይህ ዓይነቱ ሰላም በማሰላሰል ወይም የባሕርይ ለውጥ በማድረግ የሚገኝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ የሚገኝ ነው። ይህ ሰላም ከፍተኛ ኃይል ያለው በመሆኑ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ” እንደሆነ ተገልጿል። ከጭንቀታችን፣ ውስን ከሆነው እውቀታችንም ሆነ ከማመዛዘን ችሎታችን ይበልጣል። በምንጨነቅበት ጊዜ መውጫ ቀዳዳው ሊጠፋን ይችላል፤ የአምላክ ሰላም ግን የሚያስጨንቁን ነገሮች ሁሉ አንድ ቀን እንደሚወገዱ በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ያደርገናል።
ይህንን ተስፋ መፈጸም የሚቻል ይመስልሃል? በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ ይሁንና “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል።” (ማርቆስ 10:27) በአምላክ መታመናችን ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ራሳችንን ለመቆጣጠር እንድንችል ይረዳናል። አንድ ትንሽ ልጅ ገበያ መሃል ከእናቱ ተነጥሎ ጠፋ እንበል። ይህ ልጅ ላጋጠመው ችግር መፍትሔው እናቱን ማግኘት ብቻ እንደሆነ ያውቃል፤ እሷን ካገኘ ሁሉም ነገር እንደሚስተካከል እርግጠኛ ነው። እናቱ ልጁን ስታገኘው በሁለት እጆቿ እቅፍ እንደምታደርገው ሁሉ አምላክም በምሳሌያዊ ሁኔታ እንዲሁ እንደሚያደርግልን ልንተማመን እንችላለን። እንድንረጋጋ አልፎ ተርፎም ጭንቀቶቻችንን እንድናስወግድ ይረዳናል።
በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች በጣም አስጨናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያሉም እንኳ የአምላክን ሰላም ማግኘት ችለዋል። ናዲን የተባለችውን ሴት ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ናዲን ልጇ ገና በማሕፀኗ ውስጥ እያለ ሞተባት። በጊዜው የተሰማትን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ስሜቴን አውጥቼ መናገር በጣም ይከብደኝ ነበር። በሁኔታው ያን ያህል እንዳልተጨነቅኩ ለማስመሰል ብሞክርም ውስጤ በጣም ተጎድቶ ነበር። በየቀኑ ማለት እችላለሁ ልቤን ለይሖዋ በማፍሰስ እንዲረዳኝ እማጸነው ነበር። የጸሎትን ኃይል በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። ‘አሁንስ ከአቅሜ በላይ ነው’ እስክል ድረስ በጣም ስጨነቅ ወደ አምላክ እጸልያለሁ፤ ከጸለይኩ በኋላ በውስጤ የመረጋጋትና የደኅንነት ስሜት እንዲሁም ሰላም ይሰማኛል።”
ልባችንንና አእምሯችንን ይጠብቃል
እስቲ ፊልጵስዩስ 4:7ን እንደገና እንመልከተው። ጥቅሱ የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅልን ይናገራል። አንድ ዘብ አንድን ሕንፃ ምድብ ቦታው ላይ ሆኖ እንደሚጠብቅ ሁሉ የአምላክ ሰላምም ቁሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርጎ የሚመለከተው የዚህ ዓለም ፍልስፍና፣ አላስፈላጊ ጭንቀትና ዓለማዊ አስተሳሰብ ወደ ውስጣችን እንዳይገባ አእምሯችንን ይጠብቅልናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
አስጨናቂ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ደስተኛና አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት ሀብት ማካበት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ባለሙያዎችን ካማከሩ በኋላ ያጠራቀሙትን ገንዘብ በአክስዮን ገበያ ላይ ለማዋል ይወስኑ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋቸው በእርግጥ ሰላም ያስገኝላቸዋል? ያስገኝላቸዋል ማለት አይቻልም። አክሲዮናቸውን ቢሸጡ ወይም ሌላ ቢገዙ አሊያም ባለበት ቢተዉት ይሻል እንደሆነ ለማረጋገጥ የአክሲዮን ዋጋ የደረሰበትን ደረጃ በየዕለቱ በስጋት ይከታተሉ ይሆናል። የአክሲዮን ገበያው ሲከስር ደግሞ የሚይዙት የሚጨብጡት ሊጠፋቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን ትርፍ ለሚያስገኝ ነገር ማዋልን አይከለክልም፤ ሆኖም የሚከተለውን ጥሩ ምክር ይለግሳል፦ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው። ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል።”—መክብብ 5:10, 12
ፊልጵስዩስ 4:7 የአምላክ ሰላም፣ “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት” ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅ ይናገራል። ‘በክርስቶስ ኢየሱስና በአምላክ ሰላም መካከል ምን ግንኙነት አለ?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ኢየሱስ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት ሕይወቱን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል። ኢየሱስ የሚጫወተውን ሚና መገንዘባችን ለአእምሯችንና ለልባችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ከኃጢአታችን ልባዊ ንስሐ ከገባንና በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ ለማግኘት ከለመንን አምላክ ይቅር ይለናል፤ ይህ ደግሞ የአእምሮና የልብ ሰላም እንድናገኝ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) የክርስቶስ መንግሥት እስከሚመጣ ድረስ ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ማጣጣም እንደማይቻል ስለምናውቅ ወደፊት የተሻለ ሕይወት የማናይ ይመስል ሁሉም ነገር እንዳይቀርብን አንፍጨረጨርም። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ከሁሉም ዓይነት ጭንቀት ነፃ እንሆናለን ማለት ባይቻልም ወደፊት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት እንደምናገኝ በሚናገረው እርግጠኛ ተስፋ መጽናናት እንችላለን።
የአምላክን ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
ታዲያ አምላክ የሚሰጠውን ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ፊልጵስዩስ 4:4, 5 የተወሰነ ፍንጭ ይሰጠናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ! ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ጌታ ቅርብ ነው።” ጳውሎስ ይህን የጻፈው ፍትሕ በጎደለው መንገድ ሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ነው። (ፊልጵስዩስ 1:13) ስለደረሰበት የፍትሕ መጓደል እያሰበ ከመቆዘም ይልቅ ሁልጊዜ በጌታ ደስ እንዲላቸው ክርስቲያን ባልንጀሮቹን አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ ደስተኛ መሆኑ የተመካው ባለበት ሁኔታ ላይ ሳይሆን ከአምላክ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ነበር። እኛም ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አምላክን በማገልገል ደስታ ማግኘትን መማር አለብን። ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነውና ፈቃዱን በተሟላ መንገድ በፈጸምን መጠን እሱን ማገልገል ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ይህ ደግሞ እርካታና ውስጣዊ ሰላም ይሰጠናል።
በተጨማሪም ምክንያታዊ እንድንሆን ተመክረናል። ምክንያታዊ ሰዎች ከሆንን ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ከራሳችን አንጠብቅም። ፍጹማን እንዳልሆን እንዲሁም በሁሉም ነገር ከሌሎች የተሻልን መሆን እንደማንችል እናውቃለን። ታዲያ ፍጹም ስለ መሆን ወይም ቢያንስ ከሁሉም ሰው የተሻልን ሆነን ስለ መገኘት በማሰብ ለምን እንቅልፍ አጥተን እናድራለን? ከሌሎችም ቢሆን ፍጽምና አንጠብቅም። እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ከያዝን ሰዎች በሚያበሳጩን ጊዜ ሰላማችንን እንጠብቃለን። “ምክንያታዊነት” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ገርነት” ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል። የግል ምርጫን በሚመለከቱ ጉዳዮች ረገድ ገርነት ማሳየታችን፣ እርባና በሌለው ብሎም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በሚያሻክርና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የእኛንም ውስጣዊ ሰላም በሚያደፈርስ ጭቅጭቅ ውስጥ እንዳንገባ ይረዳናል።
ፊልጵስዩስ 4:5 ላይ የሚገኘው “ጌታ ቅርብ ነው” የሚለው ዓረፍተ ነገር ያለቦታው የገባ ሊመስል ይችላል። አምላክ በቅርቡ ይህን አሮጌ ሥርዓት በመንግሥቱ በሚተዳደር አዲስ ሥርዓት እንደሚተካው ግልጽ ነው። ይሁንና አሁንም እንኳ አምላክ ወደ እሱ ለመቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ቅርብ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:27፤ ያዕቆብ 4:8) አምላክ ቅርብ መሆኑን መገንዘባችን ደስተኞችና ምክንያታዊ እንድንሆን አልፎ ተርፎም ቁጥር 6 እንደሚያጎላው በአሁኑ ጊዜ ስለሚያጋጥሙን ችግሮችም ሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ እንዳንጨነቅ ይረዳናል።
ቁጥር 6 እና 7ን ስንመለከት አምላክ የሚሰጠው ሰላም የጸሎት ውጤት እንደሆነ እንገነዘባለን። አንዳንዶች ማንኛውም ዓይነት ጸሎት የመረጋጋት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል አድርገው ስለሚያስቡ ጸሎትን ለማሰላሰል ከሚረዳ አንድ ዘዴ ለይተው አይመለከቱትም። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ ደስታውንም ሆነ ጭንቀቱን አፍቃሪ ለሆነው ወላጁ እንደሚያካፍለው ሁሉ ሰዎችም ይሖዋን የዚህን ያህል በቅርበት ሊያነጋግሩት እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። “ስለ ሁሉም ነገር” ለአምላክ መንገር እንደምንችል ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና እና የሚያረጋጋ ነው! በአእምሯችን ውስጥ ያለው ነገር ምንም ይሁን ምን ሌላው ቀርቶ ሚስጥራችንን እንኳ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን መንገር እንችላለን።
ቁጥር 8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሚያንጹ ነገሮችን እንድናስብ ያበረታታናል። ይሁንና የሚያንጹ ነገሮችን ማሰብ ብቻውን በቂ አይደለም። ቁጥር 9 እንደሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስን ግሩም ምክሮች በተግባር ማዋልም ይገባናል። እንዲህ ማድረጋችን ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን ያደርጋል። “ንጹሕ ሕሊና ምቹ ትራስ ነው” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ምንኛ እውነት ነው!
አዎን፣ አንተም ውስጣዊ ሰላም ማግኘት ትችላለህ! ይህ ሰላም የሚገኘው ከይሖዋ አምላክ ሲሆን ሰላሙን የሚሰጠውም ወደ እሱ ለሚቀርቡና መመሪያውን መከተል ለሚፈልጉ ሰዎች ነው። የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የእሱን አስተሳሰብ ማወቅ ትችላለህ። መመሪያዎቹን በተግባር ማዋል ሁልጊዜ ቀላል ነው ማለት አይደለም። ይሁንና ለዚህ ስትል ማንኛውንም ጥረት ብታደርግ የሚያስቆጭህ አይሆንም፤ ምክንያቱም ‘የሰላም አምላክ ከአንተ ጋር ይሆናል።’—ፊልጵስዩስ 4:9
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘የአምላክ ሰላም ልባችሁን ይጠብቃል።’—ፊልጵስዩስ 4:7
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ስለ ሁሉም ነገር” ለአምላክ መንገር እንደምንችል ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና እና የሚያረጋጋ ነው