መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ከሰዎች ጋር መቀራረብ የሚያስጠላው አንድ የፓንክ ሮክ እንቅስቃሴ አራማጅ፣ ሰዎችን ለመውደድና ለመርዳት እንዲነሳሳ ያደረገው ምንድን ነው? በሜክሲኮ የሚኖር አንድ ሰው ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗሩን እንዲለውጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? አንድ ታዋቂ ጃፓናዊ የብስክሌት ተወዳዳሪ በውድድር መካፈሉን አቁሞ አምላክን ማገልገል የጀመረው ለምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።
‘ሥርዓት የሌለኝ፣ እብሪተኛና ቁጡ ሰው ነበርኩ።’—ዴነስ ኦቤርን
የትውልድ ዘመን፦ 1958
የትውልድ አገር፦ እንግሊዝ
የኋላ ታሪክ፦ የፓንክ ሮክ እንቅስቃሴ አራማጅ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ በአባቴ በኩል አየርላንዳዊ ስሆን በልጅነቴ የአየርላንድ ካቶሊክ ተከታይ ነበርኩ። ብዙውን ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምሄደው ብቻዬን ስለሆነ ወደዚያ መሄድ አያስደስተኝም ነበር። ያም ሆኖ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥማት ነበረኝ። አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት አዘውትሬ እጸልይ የነበረ ሲሆን ማታ ማታ አልጋ ውስጥ ሆኜ ጸሎቱ ምን ትርጉም እንዳለው አስብ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ጸሎቱ የያዘውን እያንዳንዱን ሐሳብ ለየብቻ እነጣጥልና ምን ትርጉም እንዳለው ለመገመት እሞክር ነበር።
በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል አጋማሽ ላይ ሳለሁ የራስተፈሪያን እንቅስቃሴ አባል ሆንኩ። እንዲሁም እንደ ፀረ ናዚ ባሉ የፖለቲካ ንቅናቄዎች ውስጥ የመግባት ፍላጎት ነበረኝ። ይሁን እንጂ የፓንክ ሮክ እንቅስቃሴ የሚያራምደው የዓመፀኝነት መንፈስ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረብኝ መጣ። ዕፅ እወስድ የነበረ ሲሆን በተለይ ማሪዋና በየቀኑ አጨስ ነበር ማለት ይቻላል። “ለምንም ነገር መጨነቅ አያስፈልግም” የሚለው ዝንባሌ ስለተጠናወተኝ ጠጪና ለራሴ ሕይወትም ሆነ ለሌሎች ደንታ የሌለኝ ሰው ሆንኩ። ከሰዎች ጋር መቀራረብ በጣም ያስጠላኝ ስለነበር የሚናገሩት ነገር ስሜት እስካልሰጠኝ ድረስ ማንንም አላዋራም ነበር። ፎቶ ለመነሳት እንኳ ፈቃደኛ አልነበርኩም። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ሥርዓት የሌለኝ፣ እብሪተኛና ቁጡ ሰው እንደነበርኩ ይሰማኛል። ደግና ለጋስ የምሆነው ለምቀርባቸው ሰዎች ብቻ ነበር።
ሃያ ዓመት ገደማ ሲሆነኝ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት አደረብኝ። እስር ቤት በገባበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብብ ከነበረ ዕፅ የሚያዘዋውር አንድ ጓደኛዬ ጋር ስለ ሃይማኖት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ሰይጣን በዓለም ላይ ስለሚጫወተው ሚና ረዘም ያለ ውይይት እናደርግ ነበር። እኔም መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቼ በግሌ ማጥናት ጀመርኩ። እኔና ጓደኛዬ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በግላችን አንብበን እንገናኛለን፤ ከዚያም ባነበብነው ነገር ላይ እንወያይና አንድ መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። ለብዙ ወራት እንዲህ አደረግን።
ባነበብነው ነገር ላይ ተመሥርተን ከደረስንባቸው መደምደሚያዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ የምንኖረው በዚህ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ነው፤ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ አለባቸው፤ በፖለቲካ ውስጥ መካፈልም ሆነ የዓለም ክፍል መሆን የለባቸውም እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የሥነ ምግባር መመሪያ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነና አንድ እውነተኛ ሃይማኖት መኖር እንዳለበት በግልጽ መረዳት ችለን ነበር። ሆኖም ጥያቄው ‘እውነተኛው ሃይማኖት የቱ ነው?’ የሚለው ነው። ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የሚያካሂዱትን የሃይማኖት ሥርዓትና በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት ስንመለከት ሥራቸው ኢየሱስ ካደረገው ነገር ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም እንደሆነ ተገነዘብን። አምላክ በእነዚህ ሃይማኖቶች እንደማይጠቀም ስለተገነዘብን እምብዛም ከማይታወቁ ሃይማኖቶች መካከል አንዳንዶቹ ምን እንደሚያስተምሩ ለመመርመር ወሰንን።
የእነዚህ ሃይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ሰዎችን በርካታ ጥያቄዎች እንጠይቃቸው ነበር። ለምናቀርብላቸው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እናውቅ ስለነበር እነሱ የሚሰጡት መልስ ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችል ነበር። ከእነሱ ጋር ውይይት ካደረግን በኋላ ‘እነዚህ ሰዎች እውነተኛውን ሃይማኖት የሚወክሉ ከሆነ እባክህ ከእነሱ ጋር እንደገና እንድገናኝ ልቤን አነሳሳልኝ’ እያልኩ ሁልጊዜ ወደ አምላክ እጸልይ ነበር። ይሁን እንጂ ለወራት ያህል እንዲህ ዓይነት ውይይቶችን ያደረግን ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለጥያቄዎቻችን መልስ ሊሰጠን የቻለ አንድም ቡድን አላገኘሁም፤ እንዲሁም ከእነሱ መካከል ከማናቸውም ጋር እንደገና የመገናኘት ፍላጎት አልነበረኝም።
በመጨረሻ እኔና ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘን። ከዚያም ሁልጊዜ ሌሎችን የምንጠይቃቸውን ጥያቄዎች ጠየቅናቸው፤ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው መልስ ሰጡን። የሰጡን መልስ ቀደም ሲል ካወቅነው ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነበር። በመሆኑም ስለ ማጨስና ዕፅ ስለመውሰድ አምላክ ያለውን አመለካከት ጨምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ያላገኘንላቸው ሌሎች ጥያቄዎችን ጠየቅናቸው። አሁንም የአምላክን ቃል ተጠቅመው መልስ ሰጡን። ከዚያም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረግ አንድ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተስማማን።
በስብሰባው ላይ መገኘት ከባድ ሆኖብኝ ነበር። እዚያ የነበሩ ሰዎች ጥሩ አለባበስና ወዳጃዊ የሆነ አቀራረብ ነበራቸው፤ እኔ ግን ከሰዎች ጋር መቀራረብ በጣም ስለሚያስጠላኝ እነዚህ ሰዎች ቀርበው እንዲያነጋግሩኝ አልፈለግኩም። አንዳንዶቹ ያነጋገሩኝ በጥሩ መንፈስ እንዳልሆነ ስላሰብኩ ከዚያ በኋላ ወደ ስብሰባ መሄድ አስጠላኝ። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ እንደማደርገው ‘እነዚህ ሰዎች እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ከሆነ እንደገና ከእነሱ ጋር የመገናኘት ፍላጎት እንዲኖረኝ እርዳኝ’ ብዬ ወደ አምላክ ጸለይኩ፤ ከዚያ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ እንደሌለብኝ ሳውቅ ይህን ልማድ ለማቆም ምንም አልተቸገርኩም። ትልቅ ፈተና የሆነብኝ ሲጋራ ማቆም ነበር። ብዙ ጊዜ ለማቆም ብሞክርም አልተሳካልኝም። ሌሎች በቀላሉ ሲጋራ ማጨስ እንዳቆሙና ልማዱ እንዳላገረሸባቸው ስሰማ ችግሬን ለይሖዋ ነገርኩት። በኋላም በይሖዋ እርዳታ ማጨሴን አቆምኩ። ለይሖዋ የሚሰማንን ሁሉ በግልጽ መናገር ያለውን ጥቅም ተገንዝቤያለሁ።
በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድም ትልቅ ማተካከያ ማድረግ ነበረብኝ። በመንግሥት አዳራሽ በሚደረግ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገኝ ፀጉሬን ወደ ላይ አቁሜውና ወደ ሰማያዊ ያደላ ደማቅ አረንጓዴ ቀለም አልፎ አልፎ ተቀብቼው ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ደማቅ ብርቱካንማ ቀለም ተቀባሁ። ጂንስ ሱሪና መፈክሮች ያሉበት የቆዳ ጃኬት እለብስ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ በደግነት ሊያስረዱኝ ቢሞክሩም አለባበሴን ማስተካከል እንዳለብኝ አልተሰማኝም። ይሁን እንጂ በ1 ዮሐንስ 2:15-17 ላይ በሚገኘው “ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ። ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም” በሚለው ጥቅስ ላይ ቆም ብዬ አሰብኩ። አለባበሴና የፀጉር አያያዜ ይህን ዓለም እንደምወድ የሚያሳይ እንደሆነና ለአምላክ ያለኝን ፍቅር ለማሳየት ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተረዳሁ። በመሆኑም ለውጥ አደረግሁ።
ከጊዜ በኋላ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንድገኝ የሚፈልጉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንዳልሆኑ ተገነዘብኩ። አምላክ በስብሰባዎች ላይ እንድገኝ የሚፈልግ መሆኑን በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ መረዳት ቻልኩ። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርኩ በኋላ በዚያ ከማገኛቸው ሰዎች ጋር በደንብ ተዋወቅሁ፤ ከዚያም ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ስል ተጠመቅሁ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ይሖዋ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችለንን አጋጣሚ እንደከፈተልን ማወቄ ልቤን በእጅጉ ነክቶታል። የአምላክ ርኅራኄና የሚያደርግልን እንክብካቤ እሱን ለመምሰል እንድጥር ብሎም የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ እንድከተል አነሳስቶኛል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ማንነቴ ሳይለወጥ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር እንደምችል ተምሬያለሁ። ለሌሎች አሳቢና አፍቃሪ ሰው ለመሆን ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ከባለቤቴና ከልጄ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርይ ለማንጸባረቅ ጥረት አደርጋለሁ። በተጨማሪም ለመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ በጥልቅ አስባለሁ። ክርስቶስን መከተሌ በሰዎች ዘንድ አክብሮት እንዳተርፍ፣ ለራሴ ያለኝ አመለካከት ከፍ እንዲል እንዲሁም ለሌሎች ፍቅር ማሳየት እንድችል ረድቶኛል።
“የያዙኝ በአክብሮት ነበር።”—ጓዋዳሉፔ ቪላሪል
የትውልድ ዘመን፦ 1964
የትውልድ አገር፦ ሜክሲኮ
የኋላ ታሪክ፦ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ይከተል የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በሜክሲኮ፣ ሶኖራ ግዛት በምትገኘውና በከፍተኛ ድህነት በተጠቃችው ኤርሞሲኦ በተባለች ከተማ ውስጥ ነበር፤ በቤተሰባችን ውስጥ ሰባት ልጆች ነበርን። አባቴ ልጅ እያለሁ ስለሞተ እናቴ እኛን ለማሳደግ ጠንክራ መሥራት ነበረባት። ለጫማ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረን ብዙውን ጊዜ የምሄደው በባዶ እግሬ ነበር። ቤተሰቤን ለመርዳት ስል ገና በልጅነቴ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። እንደ ብዙዎቹ ቤተሰቦች ሁሉ እኛም በጠባብ ቤት ውስጥ ተጨናንቀን እንኖር ነበር።
እናቴ አብዛኛውን ጊዜ ቀን ቀን ቤት ውስጥ ስለማትውል የሚጠብቀን ሰው አልነበረም። በ6 ዓመቴ አንድ የ15 ዓመት ወጣት በፆታ ያስነውረኝ ጀመር። ይህ ልጅ የሚያደርስብኝ የፆታ ጥቃት ለረጅም ጊዜ ቀጠለ። ይህ ደግሞ ከፆታ ጋር በተያያዘ በጣም ግራ እንድጋባ አደረገኝ። አንድ ወንድ ከሌላ ወንድ ጋር በፆታዊ ፍላጎት መሳሳቡ ተፈጥሯዊ እንደሆነ ይሰማኝ ጀመር። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከሐኪሞችና ከቄሶች ምክር ለማግኘት ሞከርኩ፤ እነሱም ስሜቴ ተፈጥሯዊ እንደሆነና ምንም ችግር እንደሌለብኝ ይነግሩኝ ነበር።
አሥራ አራት ዓመት ሲሆነኝ ሁሉም ሰው ግብረ ሰዶማዊ መሆኔን እንዲያውቅ ለማድረግ ወሰንኩ። ቀጣዮቹን 11 ዓመታት በዚህ ሁኔታ ያሳለፍኩ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከብዙ ወንዶች ጋር አብሬ ኖሬያለሁ። ከጊዜ በኋላ የፀጉር ሥራ ሥልጠና በመውሰድ አንድ የውበት ሳሎን ከፍቼ መሥራት ጀመርኩ። ሆኖም ደስተኛ አልነበርኩም። ሥቃይ ያለበት ሕይወት እመራ የነበረ ከመሆኑም በላይ እምነት የጣልኩባቸው ብዙ ሰዎች ክደውኛል። የማደርገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር። ‘ጥሩና እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን?’ እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።
በዚህ ጊዜ ስለ እህቴ ሁኔታ ማሰብ ጀመርኩ። እህቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጥንታ ተጠምቃ ነበር። እየተማረች ስላለችው ነገር ትነግረኝ የነበረ ቢሆንም ትኩረት ሰጥቼ አላዳምጣትም ነበር። ያም ሆኖ በአኗኗሯም ሆነ በትዳር ሕይወቷ እደነቅ ነበር። ከባሏ ጋር በጣም እንደሚዋደዱና እንደሚከባበሩ ማየት ችዬ ነበር። አንዳቸው ሌላውን የሚይዙት በደግነት ነው። ከጊዜ በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ጀመር። መጀመሪያ ላይ ሳጠና ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም። በኋላ ግን ሁኔታው ተለወጠ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋብዘውኝ ሄድኩ። በዚያ ያጋጠመኝ ሁኔታ ለእኔ አዲስ ነበር። ብዙ ሰዎች የሚያሾፉብኝ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ አላደረጉም። በደግነት የተቀበሉኝ ከመሆኑም በላይ የያዙኝ በአክብሮት ነበር። ይህም ልቤን ነካው።
በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘቴ ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረኝ ጥሩ አመለካከት ይበልጥ እንዲጎለብት አድርጓል። በስብሰባው ላይ ብዙ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ልክ እንደ እህቴ እውነተኛና ቅን እንደሆኑ ለማስተዋል ቻልኩ። ‘ለረጅም ጊዜ ስፈልጋቸው የነበርኩት ጥሩና እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ ሰዎች እነዚህ ይሆኑ እንዴ?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ለሚጠየቁት ጥያቄ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ የሚሰጡበት መንገድ ያስገርመኝ እንደነበር ሁሉ ፍቅራቸውና አንድነታቸውም እጅግ አስደነቀኝ። በሕይወታቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ተገነዘብኩ። እንደ እነሱ ለመሆን ብዙ ለውጦችን ማድረግ እንዳለብኝም ተረዳሁ።
እርግጥ ነው፣ ነገረ ሥራዬ ሁሉ እንደ ሴት ስለነበር ከአባጨጓሬነት ወደ ቢራቢሮነት የመለወጥን ያህል ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ነበረብኝ። በአነጋገሬ፣ በአኳኋኔ፣ በአለባበሴ፣ በፀጉር አያያዜና በጓደኛ ምርጫዬ ረገድ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገኝ ነበር። የቀድሞ ጓደኞቼ “እንዲህ የምታደርገው ምን ሆነህ ነው? እንደበፊቱ ብትሆን የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ቢቀርብህ ይሻላል። ምን ጎደለኝ ብለህ ነው?” እያሉ ያሾፉብኝ ጀመር። ይሁን እንጂ ከሁሉ የበለጠ የከበደኝ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗሬን እርግፍ አድርጎ መተው ነበር።
ያም ሆኖ በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ ያለው ሐሳብ ልቤን በጥልቅ ስለነካው ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ እንደምችል ተገነዘብኩ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም? አትታለሉ። ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ . . . የአምላክን መንግሥት አይወርሱም። አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችሁ ተጠርታችኋል።” ይሖዋ በዚያ ጊዜ የነበሩ ሰዎችን እንዲለወጡ እንደረዳቸው ሁሉ እኔንም ረድቶኛል። ለውጥ ለማድረግ ለተወሰኑ ዓመታት ከፍተኛ ትግል ማድረግ ነበረብኝ፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ያስተማሩኝ ነገርና ያሳዩኝ ፍቅር በዚህ ረገድ በእጅጉ ረድቶኛል።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ከቀድሞ አኗኗሬ ሙሉ በሙሉ ተላቅቄያለሁ። በአሁኑ ወቅት ባለትዳር ስሆን እኔና ባለቤቴ ልጃችንን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እያስተማርነው ነው። ከቀድሞ አኗኗሬ ከተላቀቅኩ ረጅም ጊዜ ያለፈ ሲሆን በርካታ መንፈሳዊ በረከቶችንና መብቶችን አግኝቻለሁ። በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲያውቁ እየረዳሁ ነው። እናቴ ባደረግኳቸው ለውጦች በጣም ስለተደሰተች እሷም መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀብላ አሁን የተጠመቀች ክርስቲያን ሆናለች። በተጨማሪም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር የነበራት ታናሽ እህቴ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።
የቀድሞ አኗኗሬን ያውቁ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ሕይወቴ እንደተሻሻለ እየተገነዘቡ ነው። እኔ ግን ከእነዚህ ለውጦች በስተጀርባ ያለው ማን እንደሆነ አውቃለሁ። ቀደም ሲል የባለሙያ እርዳታ ለማግኘት ብሞክርም ያገኘሁት መጥፎ ምክር ብቻ ነበር። ይሁንና እውነተኛ እርዳታ ያገኘሁት ከይሖዋ ነው። ምንም እንደማልረባ ቢሰማኝም አምላክ እኔን ከቁም ነገር ቆጥሮ በፍቅርና በትዕግሥት ይዞኛል። ጥበበኛ፣ አፍቃሪና አስደናቂ የሆነው አምላክ እኔን ከቁም ነገር መቁጠሩ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንድነሳሳ አድርጎኛል።
“ብቸኝነት፣ ባዶነትና እርካታ የማጣት ስሜት ይሰማኝ ነበር።”—ካዙሂሮ ኩኒሞቼ
የትውልድ ዘመን፦ 1951
የትውልድ አገር፦ ጃፓን
የኋላ ታሪክ፦ ታዋቂ የብስክሌት ተወዳዳሪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት በጃፓን፣ ሺዙካ ግዛት ውስጥ በምትገኝና ብዙም እንቅስቃሴ በሌለባት በአንዲት የወደብ ከተማ ሲሆን ስምንት አባላት ያሉት ቤተሰባችን በአንድ አነስተኛ ቤት ውስጥ ይኖር ነበር። አባቴ የብስክሌት መሸጫ ሱቅ ነበረው። ከልጅነቴ ጀምሮ የብስክሌት ውድድሮች ወደሚካሄድባቸው ቦታዎች ይወስደኝ ስለነበር ለዚህ ስፖርት ፍቅር አደረብኝ። በመሆኑም አባቴ ፕሮፌሽናል የብስክሌት ተወዳዳሪ እንድሆን ነገሮችን ማመቻቸት ጀመረ። ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በትጋት ያሠለጥነኝ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ በየዓመቱ በሚካሄደው ብሔራዊ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በብስክሌት ውድድር አሸንፌያለሁ። ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የመማር አጋጣሚ አግኝቼ የነበረ ቢሆንም በቀጥታ ወደ ብስክሌት ውድድር ማሠልጠኛ ተቋም ለመግባት ወሰንኩ። በ19 ዓመቴ ፕሮፌሽናል የብስክሌት ተወዳዳሪ ሆንኩ።
በዚህ ወቅት ዋነኛው ግቤ በጃፓን ውስጥ አንቱ የተባለ የብስክሌት ተወዳዳሪ መሆን ነበር። ቤተሰቤ አስተማማኝና የተደላደለ ሕይወት እንዲመራ በማሰብ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለማግኘት እቅድ አወጣሁ። ቀን ከሌት ልምምድ ማድረግ ጀመርኩ። ልምምድ ወይም ውድድር ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ የተወለድኩት ለብስክሌት ውድድር እንደሆነና ምንም ሆነ ምን እጅ መስጠት እንደሌለብኝ ለራሴ ደጋግሜ እናገር ነበር። ያደረግኩትም ይህንኑ ሲሆን ልፋቴም ከንቱ አልቀረም። ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮፌሽናል ውድድር ላይ ከሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድሬ አንደኛ ወጣሁ። በሚቀጥለው ዓመት የጃፓንን ቁጥር አንድ የብስክሌት ጋላቢ ለመለየት በሚካሄደው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ብቃት አገኘሁ። በዚህ ውድድር ላይ ስድስት ጊዜ ሁለተኛ ወጥቻለሁ።
ሁልጊዜ ከተሸላሚዎች ተርታ ስለማልጠፋ የቶካይ ብርቱ እግሮች በሚል ቅጽል ስም እታወቅ ነበር፤ ቶካይ በጃፓን የሚገኝ የአንድ አካባቢ ስም ነው። ደግሞም ጎበዝ ተፎካካሪ ነበርኩ። በውድድር ጊዜ ደፋርና ምንም የማይበግረኝ ስለነበርኩ ሌሎች ይፈሩኝ ጀመር። የማገኘው ገቢ እያደገ በመሄዱ ደስ ያለኝን ነገር ሁሉ መግዛት ቻልኩ። አንድ ትልቅ ቤት የገዛሁ ሲሆን ቤቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚረዱ ዘመናዊ ማሽኖች የሞሉበት ክፍል ነበረው። ቤት የሚገዛ ገንዘብ አውጥቼ አንድ የውጭ አገር መኪና ገዛሁ። የወደፊቱ ሕይወቴን አስተማማኝ ለማድረግ ስል የማይንቀሳቀስ ንብረት እና አክሲዮን መግዛት ጀመርኩ።
ያም ሆኖ ብቸኝነት፣ ባዶነትና እርካታ የማጣት ስሜት ይሰማኝ ነበር። በዚህ ጊዜ ባለ ትዳርና የልጆች አባት ነበርኩ፤ ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰቤን የምይዘው በትዕግሥት ስላልነበረ በጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር በባለቤቴና በልጆቼ ላይ እጮኽ ነበር። እነሱም ስሜቴ ጥሩ ይሁን አይሁን ለማወቅ ሁልጊዜ በጭንቀት ተውጠው ዓይን ዓይኔን ይመለከቱኝ ጀመር።
በኋላ ላይ ግን ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ይህ ደግሞ ብዙ ለውጥ አስከተለ። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንደምትፈልግ ስትነግረኝ በቤተሰብ አንድ ላይ እንድንሄድ ወሰንኩ። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ቤቴ ድረስ መጥቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያስጀመረኝን ዕለት እስካሁን አልረሳውም። በዚያ ምሽት የተማርኩት ነገር ልቤን በጥልቅ ነካው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ኤፌሶን 5:5ን ማንበቤ ልቤን ምን ያህል በጥልቅ እንደነካው ፈጽሞ አልረሳውም። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ሴሰኛ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ማለትም ጣዖት አምላኪ የሆነ ማንኛውም ሰው በክርስቶስና በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ የለውም።” የብስክሌት ውድድር ከቁማር ጋር የተያያዘ እንደሆነና የስግብግብነትን መንፈስ እንደሚያበረታታ ተገነዘብኩ። በዚህ ጊዜ ሕሊናዬ መረበሽ ጀመረ። ይሖዋ አምላክን ማስደሰት ከፈለግሁ ውድድሩን እርግፍ አድርጌ መተው እንዳለብኝ ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ይህን ውሳኔ ማድረግ በጣም ከብዶኝ ነበር።
ከመቼውም ይበልጥ የረካሁበትን የውድድር ዓመት ገና መጨረሴ ስለነበር ተጨማሪ ስኬቶችን ለማግኘት ቋምጬ ነበር። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የአእምሮ ሰላምና መረጋጋት እንዳስገኘልኝ ተገነዘብኩ፤ ይህ ደግሞ ውድድሮችን የማሸነፍ መንፈስ ከሚፈጥርብኝ ስሜት በእጅጉ የተለየ ነው! ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ የተወዳደርኩት ሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም እንኳ ለመወዳደር የነበረኝ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አልከሰመም ነበር። እንዲሁም ቤተሰቤን በምን ገቢ መደገፍ እንደምችል ግራ ገብቶኝ ነበር። ወደፊትም ሆነ ወደኋላ መሄድ የማልችልበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቴ አንሶ ዘመዶቼ በአዲሱ እምነቴ የተነሳ በጣም ያስቸግሩኝ ጀመር። አባቴም ክፉኛ ተበሳጨብኝ። በሁለት ሐሳብ ከመወጠሬ ብዛት የጨጓራ አልሰር ያዘኝ።
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የረዳኝ ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት መቀጠሌና የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች መሄድ አለማቋረጤ ነው። እያደር እምነቴ እየጠነከረ ሄደ። ይሖዋ ጸሎቴን እንዲሰማልኝ እንዲሁም ጸሎት ሰሚ አምላክ መሆኑን እንዳስተውል እንዲረዳኝ ለመንኩት። ባለቤቴ ደስተኛ ለመሆን የግድ ትልቅ ቤት ውስጥ መኖር እንደማያስፈልጋት ስትነግረኝ ጭንቀቴ ቀነሰልኝ። ቀስ በቀስ እድገት አደረግኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ በማቴዎስ 6:33 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በእርግጥ እውነት እንደሆነ በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።” ኢየሱስ “እነዚህም ነገሮች ሁሉ” በማለት የጠቀሳቸውን ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አጥተን አናውቅም። አሁን የማገኘው ገቢ ተወዳዳሪ በነበርኩበት ጊዜ የማገኘው ገንዘብ አንድ ሠላሳኛ ቢሆንም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን ለመደገፍ ምንም አጥቼ አላውቅም።
ከምንም በላይ ደግሞ ከእምነት አጋሮቼ ጋር ስሠራና ይሖዋን ሳመልክ ከዚህ ቀደም ያልነበረኝን ደስታና እርካታ አገኛለሁ። ጊዜው ሳይታወቀኝ ይነጉዳል። የቤተሰቤ ሕይወትም በእጅጉ ተሻሽሏል። ሦስቱም ወንዶች ልጆቼ ከባለቤቶቻቸው ጋር በመሆን ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው።