የይሖዋን ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህ?
“መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ።”—ኢሳ. 30:21
1, 2. ሰይጣን ምን ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል? የአምላክ ቃል የሚረዳን እንዴት ነው?
የተሳሳተ የመንገድ ምልክት አንድ መንገደኛ አቅጣጫውን እንዲስት የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ አደገኛ ሊሆን ይችላል። አንድ መጥፎ ሰው መንገደኞችን ለማሳሳት ሲል የመንገዱን ምልክት ሆን ብሎ እንደቀየረው አንድ ጓደኛህ ነገረህ እንበል። እንዲህ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ አትወስድም?
2 ሰይጣን እኛን ለማሳሳት ቆርጦ የተነሳ ክፉ ጠላት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ራእይ 12:9) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተመለከትናቸው መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ነው፤ የሰይጣን ዓላማ ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ስተን እንድንወጣ ማድረግ ነው። (ማቴ. 7:13, 14) ደስ የሚለው ነገር አሳቢ የሆነው አምላካችን፣ ሰይጣን ያስቀመጣቸውን አሳሳች ‘የመንገድ ምልክቶች’ እንዳንከተል ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። ሰይጣን መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸውን ሦስት ተጨማሪ መንገዶች እስቲ እንመልከት። የአምላክ ቃል በተሳሳተ መንገድ እንዳንጓዝ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እየመረመርን ስንሄድ ይሖዋ ከኋላችን ሆኖ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” በማለት ትክክለኛውን አቅጣጫ እንደሚመራን አድርገን ማሰብ እንችላለን። (ኢሳ. 30:21) ይሖዋ የሚሰጠንን ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች በጥልቀት መመርመራችን ማስጠንቀቂያዎቹን ሰምተን እርምጃ ለመውሰድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።
‘ሐሰተኛ አስተማሪዎችን’ አትከተል
3, 4. (ሀ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች ልክ እንደ ደረቅ የውኃ ጉድጓድ የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ የሚመጡት ከየት ነው? ዓላማቸውስ ምንድን ነው?
3 በረሃማ በሆነ አካባቢ እየተጓዝክ እንደሆነ አድርገህ አስብ። ከርቀት አንድ የውኃ ጉድጓድ ስላየህ ጥምህን የሚያረካ ውኃ እንደምታገኝ ተስፋ በማድረግ ወደዚያ አቀናህ። ይሁንና እዚያ ስትደርስ ጉድጓዱ ደረቅ ሆኖ ብታገኘው ምን ይሰማሃል? ወሽመጥህ ቁርጥ እንደሚል የታወቀ ነው! ሐሰተኛ አስተማሪዎችም ልክ እንደ ደረቅ የውኃ ጉድጓድ ናቸው። የእውነትን ውኃ ለማግኘት ወደ እነሱ የሚሄድ ማንኛውም ሰው ያሰበው ነገር ሳይሆን በመቅረቱ በእጅጉ ማዘኑ አይቀርም። ይሖዋ፣ በሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ አማካኝነት ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30ን እና 2 ጴጥሮስ 2:1-3ን አንብብ።) እነዚህ አስተማሪዎች እነማን ናቸው? ጳውሎስና ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የጻፉት ዘገባ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ከየት እንደሚመጡና ሥራቸውን የሚያከናውኑት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል።
4 ጳውሎስ፣ ለኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች “ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል . . . ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ” ብሏቸው ነበር። ጴጥሮስ ደግሞ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ “በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ” በማለት ጽፎላቸዋል። ታዲያ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሚመጡት ከየት ነው? እነዚህ አስተማሪዎች ከጉባኤው ውስጥ ሊነሱ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ከሃዲዎች ናቸው።a ዓላማቸው ምንድን ነው? ከሃዲዎች ምናልባትም በአንድ ወቅት ይወዱት የነበረውን ድርጅት ትተው በመሄድ ብቻ አይወሰኑም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እንደገለጸው ዓላማቸው “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ” ነው። ጳውሎስ “ደቀ መዛሙርቱን” እንዳለ ልብ በል። ከሃዲዎች ከድርጅቱ ወጥተው የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ከማፍራት ይልቅ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት መውሰድ ይፈልጋሉ። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ልክ እንደ “ነጣቂ ተኩላዎች” የዋህ የሆኑትን የጉባኤ አባላት ለመዋጥ ይኸውም እምነታቸውን ለማጥፋትና ከእውነት እንዲርቁ ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው።—ማቴ. 7:15፤ 2 ጢሞ. 2:18
5. ሐሰተኛ አስተማሪዎች የትኞቹን ዘዴዎች ይጠቀማሉ?
5 ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በምን መንገድ ነው? የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ተንኮል የሞላባቸው ናቸው። ከሃዲዎች ጉባኤውን የሚበክሉ ሐሳቦችን “በስውር ያስገባሉ።” ሥራቸውን የሚያካሂዱት እንደ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በድብቅ ሲሆን የክህደት ሐሳቦችን በረቀቀ መንገድ ያስፋፋሉ። የሐሰት ሰነዶችን እውነተኛ አስመስሎ በማዘጋጀት ረገድ እንደተዋጣለት ባለሙያ፣ ከሃዲዎችም “አስመሳይ ቃላት” በመናገር ወይም የሐሰት የመከራከሪያ ነጥቦች በማቅረብ ራሳቸው የፈጠሯቸውን ሐሳቦች እንደ እውነት አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። የራሳቸውን ሐሳብ በሚደግፍ መልኩ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጣመም’ ‘አታላይ የሆኑ ትምህርቶቻቸውን’ ያስፋፋሉ። (2 ጴጥ. 2:1, 3, 13፤ 3:16) ከሃዲዎች ስለ እኛ እንደማያስቡ ግልጽ ነው። እነሱን መከተል ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው ጎዳና እንድንወጣ ከማድረግ ውጪ የሚያስገኘው ጥቅም የለም።
6. መጽሐፍ ቅዱስ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን አስመልክቶ ምን ግልጽ ምክር ሰጥቶናል?
6 ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዳያታልሉን ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለከሃዲዎች ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት የሚሰጠው ምክር ምንም የማያሻማ ነው። (ሮም 16:17ን እና 2 ዮሐንስ 9-11ን አንብብ።) የአምላክ ቃል “ከእነሱ ራቁ” ይላል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ሐረግ “ከእነሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ” እንዲሁም “ፈጽሞ ወደ እነሱ አትቅረቡ” በማለት አስቀምጠውታል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ምክር ግራ የሚያጋባ ነገር የለውም። አንድ ሐኪም፣ ገዳይ የሆነ ተላላፊ በሽታ ከያዘው ሰው እንድትርቅ ነገረህ እንበል። ሐኪሙ ምን ማለቱ እንደሆነ ስለምታውቅ ማሳሰቢያውን ሰምተህ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደምታደርግ ጥርጥር የለውም። ከሃዲዎች ተላላፊ በሽታ እንዳለበት ሰው ናቸው፤ የክህደት ትምህርታቸውን በማስፋፋት ሌሎችንም ለመበከል ይጥራሉ። (1 ጢሞ. 6:3, 4) ታላቁ ሐኪም የሆነው ይሖዋ ከከሃዲዎች እንድንርቅ አስጠንቅቆናል። ይህን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እናውቃለን፤ ይሁንና በሁሉም መስኮች የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ ሰምተን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል?
7, 8. (ሀ) ከሐሰተኛ አስተማሪዎች መራቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ፈጽሞ ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ያደረግኸው ለምንድን ነው?
7 ከሐሰተኛ አስተማሪዎች መራቅ ሲባል ምን ማለት ነው? በቤታችን አንቀበላቸውም ወይም ሰላም አንላቸውም። ከዚህም ሌላ ጽሑፎቻቸውን አናነብም፣ እነሱ የሚቀርቡባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አንመለከትም፣ ድረ ገጻቸውን አንቃኝም ወይም በእነሱ ድረ ገጽ (ብሎግ) ላይ አስተያየታችንን አናሰፍርም። እንዲህ ያለ ጠንካራ አቋም የምንወስደው ለምንድን ነው? ፍቅር ስላለን ነው። “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ስለምንወድ እውነት ከሆነው ቃሉ ጋር የሚጋጩ የተጣመሙ ትምህርቶችን ለመስማት ፈቃደኞች አንሆንም። (መዝ. 31:5፤ ዮሐ. 17:17) በተጨማሪም አስደናቂ እውነቶችን ያስተማረንን የይሖዋን ድርጅት እንወደዋለን፤ የይሖዋ ድርጅት ካስተማረን እውነቶች መካከል የይሖዋ ስምና ትርጉሙ፣ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ፣ ሙታን ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም የትንሣኤ ተስፋ ይገኙበታል። እነዚህንና ሌሎች ውድ እውነቶችን መጀመሪያ ባወቅህበት ጊዜ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ታስታውሳለህ? ታዲያ የይሖዋን ድርጅት የሚያጥላላ ነገር የሚናገር ሰው እነዚህን እውነቶች እንድታውቅ በረዳህ ድርጅት ላይ ቅሬታ እንዲያድርብህ እንዲያደርግ ለምን ትፈቅዳለህ?—ዮሐ. 6:66-69
8 ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምንም አሉ ምን እኛ እነሱን አንከተልም! እንደነዚህ ወዳሉ የደረቁ የውኃ ጉድጓዶች በመሄድ የምንታለልበት ምን ምክንያት አለ? ይህን ብናደርግ የጠበቅነው ሳይሆን በመቅረቱ ከማዘን ሌላ ምንም የምናተርፈው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኞች ሆነን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ የይሖዋ ድርጅት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ንጹሕና መንፈስን የሚያድስ የእውነት ውኃ አማካኝነት ለረጅም ጊዜ ጥማችንን ሲያረካልን ቆይቷል።—ኢሳ. 55:1-3፤ ማቴ. 24:45-47
‘የፈጠራ ወሬዎችን’ አትከተል
9, 10. ጳውሎስ ‘የፈጠራ ወሬዎችን’ አስመልክቶ ለጢሞቴዎስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል? ጳውሎስ ይህን ሲል በአእምሮው ምን ይዞ ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
9 አንዳንድ ጊዜ አንድ የመንገድ ምልክት እንደተነካካና ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንደሚያመለክት በቀላሉ መለየት ይቻል ይሆናል። በሌሎች ጊዜያት ግን ይህን ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ሰይጣን ከሚያሳድርብን መጥፎ ተጽዕኖዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ አንዳንዶቹ ተጽዕኖዎች ግልጽ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ስውር ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው መሰሪ ዘዴዎች መካከል ‘የፈጠራ ወሬዎች’ እንደሚገኙበት አሳስቦናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:3, 4ን አንብብ።) አቅጣጫችንን ስተን ወደ ሕይወት ከሚመራው ጎዳና እንዳንወጣ የፈጠራ ወሬዎች ምን እንደሆኑና ለእነዚህ ነገሮች ትኩረት ከመስጠት መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።
10 ጳውሎስ ስለ ፈጠራ ወሬዎች የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሚገኘው ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ነው፤ ይህ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች፣ የጉባኤውን ንጽሕና የመጠበቅ እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቹ ታማኝነታቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ የመርዳት አደራ ተጥሎበት ነበር። (1 ጢሞ. 1:18, 19) ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ልብ ወለድን፣ ተረትን ወይም የሐሰት ወሬን ሊያመለክት ይችላል። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው ይህ ቃል “ከእውነታ ፈጽሞ የራቀ (ሃይማኖታዊ) ታሪክን” ያመለክታል። ጳውሎስ ከላይ ያለውን ሲጽፍ ቀልብ በሚስቡ ተረቶች ወይም በሚያስደምሙ አፈ ታሪኮች አማካኝነት የሚሰራጩ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል።b እንዲህ ያሉት የፈጠራ ወሬዎች፣ ትርጉም ወደሌለው ምርምር የሚመሩ “እርባና ቢስ ጥያቄዎችን” ከማስከተል ውጪ ምንም የሚፈይዱት ነገር የለም። የፈጠራ ወሬዎች፣ ቀንደኛ አታላይ የሆነው ሰይጣን የሚጠቀምባቸው የተንኮል ዘዴዎች ናቸው፤ ሰይጣን የዋህ የሆኑ ሰዎች አቅጣጫቸውን እንዲስቱ ለማድረግ በሃይማኖታዊ ውሸቶችና አምላክ የለሾች በሚያስፋፏቸው ተረቶች ይጠቀማል። ጳውሎስ የሰጠው ምክር ግልጽ ነው፦ ለፈጠራ ወሬዎች ጆሯችሁን አትስጡ!
11. ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት ተጠቅሞ ሰዎችን በማሳሳት ረገድ የተዋጣለት እንዴት ነው? የትኛውን ማስጠንቀቂያ መስማታችን እንዳንታለል ይጠብቀናል?
11 የዋህ የሆኑ ሰዎች መንገዳቸውን እንዲስቱ ሊያደርጓቸው የሚችሉ አንዳንድ የፈጠራ ወሬዎች የትኞቹ ናቸው? ‘የፈጠራ ወሬዎች’ የሚለው አገላለጽ መሠረታዊ ትርጉም ‘እውነትን ከመስማት ጆሯችንን እንድንመልስ’ ሊያደርገን የሚችልን ማንኛውም ሃይማኖታዊ ውሸት ወይም ተረት ሊያመለክት ይችላል። (2 ጢሞ. 4:3, 4) “የብርሃን መልአክ” መስሎ የሚቀርበው ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት ተጠቅሞ ሰዎችን በማሳሳት ረገድ ተዋጥቶለታል። (2 ቆሮ. 11:14) ሕዝበ ክርስትና፣ እንደ ሥላሴና ገሃነመ እሳት እንዲሁም ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ያሉ በአፈ ታሪክና በውሸት የተሞሉ ትምህርቶችን የክርስትና ትምህርቶች እንደሆኑ አድርጋ ታስተምራለች። በተጨማሪም ሕዝበ ክርስትና እንደ ፋሲካና ገና ያሉ በዓላት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጋለች፤ ብዙ ሰዎች እነዚህ በዓላት አምላክን የሚያስደስቱ እንደሆኑ ቢሰማቸውም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዓላቱ ከአረማዊ አምልኮ የመነጩ ናቸው። “ራሳችሁን ለዩ” እንዲሁም “ርኩስ የሆነውንም ነገር መንካት አቁሙ” የሚለውን አምላክ የሰጠንን ማስጠንቀቂያ ሰምተን እርምጃ መውሰዳችን በፈጠራ ወሬዎች እንዳንታለል ይጠብቀናል።—2 ቆሮ. 6:14-17
12, 13. (ሀ) ሰይጣን የትኞቹን ውሸቶች ያስፋፋል? ይሁንና እነዚህን ውሸቶች አስመልክቶ እውነታው ምንድን ነው? (ለ) በሰይጣን የፈጠራ ወሬዎች እንዳንታለል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 ሰይጣን፣ ጠንቃቆች ካልሆንን ሊያሳስቱን የሚችሉ ሌሎች ውሸቶችንም ያስፋፋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር የለም፤ ማንኛውም ነገር ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል። ይህ የሚወሰነው በአንተ ስሜት ነው። የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛው ዓለም እንዲህ ያለውን አመለካከት ያስፋፋሉ። የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በተመለከተ እንዲህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት መያዝ ማንኛውንም የሥነ ምግባር ደንብ ወደ ጎን ገሸሽ እንድናደርግ ጫና ሊያሳድርብን ይችላል። እውነቱን ለመናገር ግን የሥነ ምግባር መመሪያ በእጅጉ የሚያስፈልገን ሲሆን ይህንንም ማሟላት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (ኤር. 10:23) አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ውስጥ እጁን አያስገባም። ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከማሰብ ይልቅ ስለ ዛሬው ሕይወታቸው ብቻ እንዲያስቡ የሚያበረታታው ይህ ዓይነቱ አመለካከት “ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። (2 ጴጥ. 1:8) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ሲሆን ይህን ቀን በተስፋ ልንጠብቀው ይገባል። (ማቴ. 24:44) አምላክ በግለሰብ ደረጃ ስለ አንተ አያስብም። ይህን የሰይጣን ውሸት ማመናችን አምላክ በፍጹም ሊወደን እንደማይችል በማሰብ ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል። እውነታው ግን ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ የሚወዳቸው ከመሆኑም ሌላ ውድ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ማቴ. 10:29-31
13 የሰይጣን ዓለም አስተሳሰብና ዝንባሌ ላይ ላዩን ሲታይ እውነት ሊመስል ስለሚችል እንዲህ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ አለብን። ሰይጣን በማታለል የተካነ እንደሆነ አስታውስ። ሰይጣን ‘በብልሃት በፈጠረው ተረት’ እንዳንታለል በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክርና ማሳሰቢያ ሰምተን ተግባራዊ ማድረግ አለብን።—2 ጴጥ. 1:16
‘ሰይጣንን አትከተል’
14. ጳውሎስ በዕድሜ ላልገፉ አንዳንድ መበለቶች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? ሁላችንም ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ያለብን ለምንድን ነው?
14 “ሰይጣንን ለመከተል የሚፈልግ በዚህ በኩል ይሂድ” የሚል የመንገድ ምልክት ቢኖር ከመካከላችን እንዲህ ያለውን ምልክት ተከትሎ የሚሄድ ማን ይኖራል? የሚገርመው ግን ጳውሎስ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንኳ “ሰይጣንን ለመከተል ዘወር” ሊሉ የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች በመጥቀስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (1 ጢሞቴዎስ 5:11-15ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ‘በዕድሜ ላልገፉ’ አንዳንድ “መበለቶች” ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሁላችንም ይሠራል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚያ ክርስቲያን ሴቶች ሰይጣንን እየተከተሉ እንደሆነ አላሰቡ ይሆናል፤ ድርጊታቸው ግን ይህን ከማድረግ ተለይቶ አይታይም። እኛም ሳይታወቀን ሰይጣንን እንዳንከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል? እስቲ ጳውሎስ ሐሜትን አስመልክቶ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እንመልከት።
15. የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው? ጳውሎስ፣ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ለይቶ የገለጻቸው እንዴት ነው?
15 የሰይጣን ዓላማ ስለ እምነታችን እንዳንናገር ይኸውም ምሥራቹን መስበካችንን እንድናቆም ማድረግ ነው። (ራእይ 12:17) ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል ጊዜያችንን በሚያባክኑ ወይም በመካከላችን መከፋፈል በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እንድንጠመድ ሊያደርገን ይሞክራል። ጳውሎስ የሰይጣንን ዘዴዎች የገለጻቸው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። “ሥራ መፍታትን ይማራሉ እንዲሁም በየቤቱ ይዞራሉ።” ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት በዚህ ዘመን አላስፈላጊ የሆኑ አልፎ ተርፎም ከእውነት የራቁ ኢ-ሜይሎችን ወይም የስልክ መልእክቶችን በመላክ የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ጊዜ በቀላሉ ልናባክን እንችላለን። “ሐሜተኞች።” ሐሜት፣ ስም ወደ ማጥፋት ሊያመራ የሚችል ሲሆን ይህም ብዙውን ጊዜ ጠብ ይፈጥራል። (ምሳሌ 26:20) በተንኮል ተነስተው የሌሎችን ስም የሚያጠፉ ሰዎች አወቁትም አላወቁት የሰይጣን ዲያብሎስን ምሳሌ እየኮረጁ ነው።c “በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ።” በሰዎች ሕይወት ገብተን እንዲህ አድርጉ ወይም እንዲህ አታድርጉ የማለት መብት የለንም። እንዲህ ያለው ፍሬ ቢስና ችግር የሚፈጥር ተግባር አምላክ የሰጠንን የስብከት ሥራ እንዳናከናውን ሊያዘናጋን ይችላል። የይሖዋን ሥራ በቅንዓት ማከናወናችንን ካቆምን ሰይጣንን መከተላችን የማይቀር ነው። መሃል ሰፋሪ መሆን አንችልም።—ማቴ. 12:30
16. የትኛውን ምክር መከተላችን “ሰይጣንን ለመከተል ዘወር” እንዳንል ጥበቃ ይሆንልናል?
16 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሰምተን ተግባራዊ ማድረጋችን “ሰይጣንን ለመከተል ዘወር” ከማለት ይጠብቀናል። ጳውሎስ ከሰጣቸው ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ምክሮች ውስጥ አንዳንዶቹን እንመልከት። “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮ. 15:58) ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን ሥራ ፈት እንዳንሆንና ጊዜ ወደሚያባክኑ ነገሮች ዘወር እንዳንል ጥበቃ ይሆንልናል። (ማቴ. 6:33) “የሚያንጽ” ነገር ተናገሩ። (ኤፌ. 4:29) ሐሜትን ላለመስማትም ሆነ ላለማሰራጨት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።d የእምነት ባልንጀሮቻችሁን አትጠራጠሯቸው፤ እንዲሁም ለእነሱ አክብሮት አዳብሩ። እንዲህ ካደረግን የምንናገረው ነገር የሚያንጽ እንጂ የሚያፈርስ አይሆንም። “በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት [ተጣጣሩ]።” (1 ተሰ. 4:11) ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ እንደምታስቡ አሳዩ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በግል ጉዳያቸው ላለመግባትና ክብራቸውን የሚነካ ነገር ላለማድረግ ተጠንቀቁ። በተጨማሪም ሰዎች የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ በሚኖርባቸው ጉዳዮች ረገድ የእኛን አመለካከት በእነሱ ላይ መጫን እንደሌለብን እናስታውስ።—ገላ. 6:5
17. (ሀ) ይሖዋ ልንከተላቸው የማይገቡ ነገሮችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ የሰጠን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ እንድንከተለው የሚፈልገውን መንገድ በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
17 ይሖዋ ልንከተላቸው የማይገቡ ነገሮችን በግልጽ ስለነገረን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዚህና ባለፈው ርዕስ ላይ የተወያየንባቸውን ማስጠንቀቂያዎች የሰጠን ለእኛ ባለው ታላቅ ፍቅር ተነሳስቶ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ሰይጣን ያስቀመጣቸውን የተሳሳቱ ‘የመንገድ ምልክቶች’ በመከተል ለመከራና ለሐዘን እንዳንዳረግ ይሖዋ ሊጠብቀን ይፈልጋል። አምላካችን እንድንከተለው የሚፈልገው ጎዳና ቀጭን ቢሆንም ከሁሉ ወደተሻለው ቦታ ይኸውም ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራናል። (ማቴ. 7:14) እንግዲያው “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚለውን የይሖዋን ማሳሰቢያ ለመስማት ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጸንተን እንቀጥል።—ኢሳ. 30:21
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ክህደት” ሲባል ከእውነተኛው አምልኮ ማፈንገጥ፣ መገንጠል፣ ተጻራሪ አቋም መያዝ፣ ማመፅ እንዲሁም ትቶ መሄድ ማለት ነው።
b ለምሳሌ ያህል፣ በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አካባቢ የተጻፈው መጽሐፈ ጦቢት (ጦቢያስ) የተባለው የአዋልድ መጽሐፍ በጳውሎስ ዘመን ይታወቅ የነበረ ሲሆን መጽሐፉ በአጉል እምነት እንዲሁም እንደ እውነት ተደርገው በቀረቡ ስለ አስማትና ጥንቆላ የሚናገሩ ታሪኮች የተሞላ ነው።—ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 122ን ተመልከት።
c “ዲያብሎስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያቦሎስ ሲሆን “ስም አጥፊ” ማለት ነው። ይኸው ቃል፣ ዋነኛ ስም አጥፊ የሆነው የሰይጣን ሌላ መጠሪያ ሆኖ አገልግሏል።—ዮሐ. 8:44፤ ራእይ 12:9, 10
መልስህ ምንድን ነው?
ከዚህ በታች ባሉት ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን ማስጠንቀቂያዎች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ላባ መበተን
ሐሜትን ማሰራጨት የሚያስከትለውን መዘዝ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ አንድ የቆየ የአይሁዳውያን ተረት አለ። ይህ ተረት በተለያዩ መንገዶች የሚነገር ቢሆንም ፍሬ ሐሳቡ ግን የሚከተለው ነው፦
አንድ ግለሰብ የከተማውን ጠቢብ ሰው ስም የሚያጠፋ ወሬ በከተማው ውስጥ አሰራጨ። ከጊዜ በኋላ ግን ሐሜተኛው ግለሰብ ስህተት እንደሠራ ስለተገነዘበ ወደ ጠቢቡ ሰው በመሄድ ይቅርታ እንዲያደርግለት ጠየቀው፤ እንዲሁም ለበደሉ ካሳ እንዲሆን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸ። ጠቢቡ ሰውም፣ ሐሜተኛው የላባ ትራስ ወስዶ እንዲቀደውና ላባውን እንዲበትነው ነገረው። ሐሜተኛው በነገሩ ግራ ቢጋባም የተባለውን ካደረገ በኋላ ወደ ጠቢቡ ሰው ተመለሰ።
ከዚያም “አሁንስ ይቅርታ አደረግህልኝ?” በማለት ጠቢቡን ሰው ጠየቀው።
ጠቢቡ ሰውም “መጀመሪያ ላባዎቹን በሙሉ ሰብስበህ አምጣ” በማለት መለሰለት።
“እንዴ፣ እንዴት አድርጌ? ላባዎቹን እኮ ነፋሱ ወስዷቸዋል” በማለት ሐሜተኛው ተናገረ።
በዚህ ጊዜ ጠቢቡ ሰው “የተናገርከው ነገር ያደረሰውን ጉዳት ማስተካከልም ላባዎቹን የመሰብሰብ ያህል ከባድ ነው” አለው።
ትምህርቱ ግልጽ ነው። የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም እንደሚባለው አንድ ሰው የተናገረው ነገር ያደረሰውን ጉዳት ማስተካከል የማይቻል ነገር ሊሆን ይችላል። እንግዲያው ሐሜት ለማሰራጨት ስንፈተን እንዲህ ማድረግ ላባ እንደመበተን መሆኑን ማስታወሳችን የጥበብ እርምጃ ነው።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች፣ ከሃዲዎችን ቤታቸው ሊጋብዟቸው የሚችሉት እንዴት ነው?