ነጠላነትንና ትዳርን አስመልክቶ የተሰጠ ጥበብ ያዘለ ምክር
“ይህን እያልኩ ያለሁት . . . ተስማሚ የሆነውን ነገር እንድታደርጉና ልባችሁ ሳይከፈል ዘወትር ጌታን እንድታገለግሉ ላነሳሳችሁ ብዬ ነው።”—1 ቆሮ. 7:35
1, 2. አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነጠላነትና ስለ ትዳር የሚሰጠውን ምክር መመርመር ያለበት ለምንድን ነው?
በሕይወታችን ውስጥ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለንን ግንኙነት ያህል በደስታ የሚያስፈነድቀን፣ የሚያበሳጨን ወይም የሚያስጨንቀን ነገር ጥቂት ነው። እነዚህን ስሜቶች በአግባቡ ለማስተናገድ ያለን ፍላጎት መለኮታዊ መመሪያ እንድንሻ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት ቢሆንም ይህን ለማድረግ የሚገፋፉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። አንድ ክርስቲያን ነጠላ ሆኖ ለመኖር የሚፈልግ ቢሆንም ቤተሰቡ አሊያም ጓደኞቹ እንዲያገባ ጫና እያሳደሩበት እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ሌሎች ደግሞ ማግባት ቢፈልጉም ተስማሚ የትዳር አጋር አላገኙ ይሆናል። አንዳንዶች ባል ወይም ሚስት መሆን ለሚያስከትለው ኃላፊነት ራሳቸውን ለማዘጋጀት መመሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ሊሰማቸው ይችላል። በተጨማሪም ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል።
2 እነዚህ ጉዳዮች ደስታችንን ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድናም ይነኩብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ምዕራፍ 7 ላይ ስለ ነጠላነትና ስለ ትዳር መመሪያ ሰጥቷል። ይህን ያደረገበትን ዓላማ ሲገልጽ አንባቢዎቹን “ተስማሚ የሆነውን ነገር እንድታደርጉና ልባችሁ ሳይከፈል ዘወትር ጌታን እንድታገለግሉ ላነሳሳችሁ ብዬ ነው” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 7:35) ነጠላም ሆንክ ያገባህ ክርስቲያን አንተም ጳውሎስ በእነዚህ አስፈላጊ ጉዳዮች ረገድ የሰጠውን ምክር በምትመረምርበት ጊዜ ያለህበትን ሁኔታ ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።
በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ ከባድ ውሳኔ
3, 4. (ሀ) ሰዎች አንድ ጓደኛቸው ወይም ዘመዳቸው ባለማግባቱ ከልክ በላይ መጨነቃቸው አንዳንድ ጊዜ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ የሰጠው ምክር አንድ ሰው ጋብቻን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው የሚረዳው እንዴት ነው?
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ ሁሉ በዛሬው ጊዜም በብዙ ባሕሎች ውስጥ ማግባት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። አንድ ሰው ሳያገባ የተወሰነ ዕድሜ ካለፈው ሁኔታው ያሳሰባቸው ወዳጆችም ሆኑ ዘመዶች ለዚህ ሰው ምክር መስጠት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ግለሰቡ በቁም ነገር የትዳር ጓደኛ መፈለግ እንዳለበት የሚጠቁም ነገር ይናገሩ ይሆናል። እንዲሁም ለትዳር ይመጥነዋል የሚሉትን ሰው ጠቆም ሊያደርጉት ይችላሉ። እንዲያውም ሁለቱን ሰዎች ለማገናኘት ብልሃት ይፈጥሩ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉ ድርጊቶች አንዳንድ ጊዜ ኀፍረትና የስሜት መጎዳት የሚያስከትሉ ከመሆኑም ሌላ በግለሰቦች መካከል ያለው ወዳጅነት እንዲበላሽ ያደርጋሉ።
4 ጳውሎስ፣ ሌሎች እንዲያገቡም ሆነ ነጠላ ሆነው እንዲኖሩ ጫና አላደረገባቸውም። (1 ቆሮ. 7:7) እሱ በነጠላነት ይሖዋን በማገልገሉ ደስተኛ የነበረ ቢሆንም የሌሎችን የማግባት መብት አልተጋፋም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ለማግባት ወይም በነጠላነት ለመኖር የመወሰን መብት አላቸው። እንዲያገቡም ሆነ ነጠላ ሆነው እንዲኖሩ ሌሎች ጫና ሊያሳድሩባቸው አይገባም።
ነጠላነትን ስኬታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
5, 6. ጳውሎስ ነጠላነትን ያበረታታው ለምንድን ነው?
5 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለነጠላነት አዎንታዊ አመለካከት እንደነበረው በግልጽ ይታያል። (1 ቆሮንቶስ 7:8ን አንብብ።) ጳውሎስ ነጠላ የነበረ ቢሆንም እንደ ሕዝበ ክርስትና ባሕታውያን ባገቡ ሰዎች ላይ ራሱን ለማመጻደቅ አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው፣ ነጠላ የሆኑ በርካታ የምሥራቹ ሰባኪዎች ባለማግባታቸው የሚያገኙትን ጥቅም ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህ ጥቅም ምንድን ነው?
6 አብዛኛውን ጊዜ ነጠላ የሆነ ክርስቲያን፣ አንድ ያገባ ክርስቲያን ሊከብዱት የሚችሉትን ከይሖዋ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶች ለመቀበል ነፃነት አለው። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” የመሆን ልዩ መብት አግኝቷል። (ሮም 11:13) የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13 እስከ የሐዋርያት ሥራ 20ን በማንበብ ጳውሎስና ሚስዮናውያን ባልደረቦቹ ባልተሰበከባቸው ክልሎች ሲሰብኩና በተለያዩ ቦታዎች ጉባኤዎችን ሲያቋቁሙ በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ። ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን በአሁኑ ወቅት ብዙዎች የማያጋጥሟቸውን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቁሟል። (2 ቆሮ. 11:23-27, 32, 33) ሆኖም ብዙ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት ያገኘው ደስታ ካጋጠመው ችግር ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ተሰምቶታል። (1 ተሰ. 1:2-7, 9፤ 2:19) ጳውሎስ አግብቶ ወይም ቤተሰብ መሥርቶ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማከናወን ይችል ነበር? አይችል ይሆናል።
7. ያላገቡ ክርስቲያኖች ያላቸውን አጋጣሚ የመንግሥቱን ምሥራች ለማስፋፋት እንዴት እንደተጠቀሙበት የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
7 በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ያላቸውን አጋጣሚ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ይጠቀሙበታል። በቦሊቪያ የሚገኙት ሣራና ሊምባኒያ የተባሉ ነጠላ እህቶች ምሥራቹ ለብዙ ዓመታት ወዳልተሰበከበት አንድ መንደር ሄደው በዚያ መኖር ጀመሩ። በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም፤ እነዚህ እህቶች ይህን ሁኔታ እንደ ከባድ ችግር ተመልክተውት ነበር? እንዲህ ብለዋል፦ “በዚህ አካባቢ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን የለም፤ በመሆኑም ሰዎቹ ትኩረታቸውን የሚከፋፍል ነገር ስለሌለ ትርፍ ጊዜያቸውን በዋነኝነት የሚያሳልፉት በማንበብ ነው።” አንዳንድ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚያነቧቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ለአቅኚዎቹ አሳዩአቸው፤ እነዚህ ጽሑፎች መታተም ካቆሙ ረጅም ጊዜ አልፏል። እህቶች በየቤቱ ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ያገኙ ስለነበር ክልሉን ለመሸፈን ተቸግረው ነበር። አንዲት በዕድሜ የገፉ ሴት “የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ጋ መምጣት ከቻሉ መጨረሻው በጣም ቀርቧል ማለት ነው” አሏቸው። ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ የመንደሩ ነዋሪዎች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ።
8, 9. (ሀ) ጳውሎስ ነጠላነት የተሻለ እንደሆነ የተናገረው ከምን አንጻር ነው? (ለ) ያላገቡ ክርስቲያኖች ምን አጋጣሚዎች አሏቸው?
8 እርግጥ ነው፣ ያገቡ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ አስቸጋሪ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ምሥራቹን በመስበክ ግሩም ውጤቶችን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ነጠላ የሆኑ አቅኚዎች ሊሸከሟቸው የሚችሉ አንዳንድ ኃላፊነቶች፣ ላገቡ ወይም ልጆች ላሏቸው ክርስቲያኖች ከባድ ሊሆኑባቸው ይችላሉ። ጳውሎስ ለጉባኤዎቹ ደብዳቤውን ሲጽፍ ምሥራቹን በማስፋፋት ረገድ ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ያውቅ ነበር። ሌሎችም እንደ እሱ በዚህ ሥራ በመካፈል ደስታ እንዲያገኙ ፈልጎ ነበር። ጳውሎስ ነጠላ ሆኖ ይሖዋን ማገልገል የተሻለ እንደሆነ የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው።
9 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት ያላገባች እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አንዳንዶች ያላገቡ ሰዎች ደስተኛ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ዘላቂ ደስታ ማግኘቱ የተመካው ከይሖዋ ጋር ባለው ወዳጅነት ላይ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ። ነጠላነት መሥዋዕትነት መክፈል የሚጠይቅ ቢሆንም ከተጠቀምንበት ግሩም ስጦታ ነው።” ደስተኛ መሆንን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ነጠላነት ደስተኛ ለመሆን አጋጣሚ ይከፍታል እንጂ እንቅፋት አይሆንም። ይሖዋ ነጠላ ወይም ባለትዳር ሳይል ሁሉንም ሰው በጥልቅ እንደሚወድ አውቃለሁ።” በአሁኑ ጊዜ ይህች እህት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዳ በደስታ እያገለገለች ነው። አንተም ነጠላ ከሆንክ ያለህን ነፃነት ተጠቅመህ ሌሎችን ስለ እውነት በማስተማሩ ሥራ የምታደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ ማሳደግ ትችላለህ? እንዲህ ካደረግህ ነጠላነት ለአንተም ከይሖዋ ያገኘኸው በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ሊሆንልህ ይችላል።
ለማግባት የሚፈልጉ ነጠላ ክርስቲያኖች
10, 11. ይሖዋ ለማግባት እየፈለጉ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ያላገኙ ክርስቲያኖችን የሚደግፋቸው እንዴት ነው?
10 በርካታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ለተወሰነ ጊዜ ነጠላ ሆነው ከቆዩ በኋላ የትዳር አጋር ለማግኘት ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ መመሪያ እንደሚያሻቸው ስለሚገነዘቡም ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እንዲረዳቸው ይሖዋን ይጠይቃሉ።—1 ቆሮንቶስ 7:36ን አንብብ።
11 እንደ አንተው ይሖዋን በሙሉ ነፍሷ ለማገልገል የምትፈልግ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የምትሻ ከሆነ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (ፊልጵ. 4:6, 7) የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ምንም ያህል ረጅም ጊዜ መጠበቅ ቢኖርብህ ተስፋ አትቁረጥ። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን እንደሚረዳህ እምነት ይኑርህ፤ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ስሜታዊ ድጋፍ በመስጠት ይረዳሃል።—ዕብ. 13:6
12. አንድ ክርስቲያን ለጋብቻ የቀረበለትን ጥያቄ በጥንቃቄ ማመዛዘን ያለበት ለምንድን ነው?
12 ለማግባት ፍላጎት ያለው አንድ ክርስቲያን አጠያያቂ መንፈሳዊ አቋም ካለው ሌላው ቀርቶ ከማያምን ሰው የጋብቻ ጥያቄ ሊቀርብለት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ፣ የማይሆን የትዳር ጓደኛ መምረጥ የሚያስከትለው ሥቃይ አንድ ሰው ነጠላ በመሆኑ ከሚሰማው ስሜት የባሰ እንደሚሆን አስታውስ። አንድ ጊዜ ካገባህ ደግሞ፣ ከፋም ለማም ከትዳር አጋርህ ጋር የዕድሜ ልክ ጥምረት ትመሠርታለህ። (1 ቆሮ. 7:27) ለማግባት ካለህ ጉጉት የተነሳ፣ በኋላ ላይ የሚያስቆጭህ ውሳኔ እንዳታደርግ ተጠንቀቅ።—1 ቆሮንቶስ 7:39ን አንብብ።
ለማግባት ስታስቡ እውነታውን ለመቀበል ተዘጋጁ
13-15. የሚጠናኑ ሰዎች በትዳር ውስጥ መከራ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የትኞቹን ጉዳዮች አስቀድመው ሊወያዩባቸው ይገባል?
13 ጳውሎስ ይሖዋን በነጠላነት ማገልገል የተሻለ እንደሆነ ቢገልጽም ለማግባት የወሰኑ ሰዎችን አልነቀፈም። እንዲያውም በመንፈስ መሪነት የሰጠው ምክር ባለትዳሮች ስለ ጋብቻ ሕይወት ሐቁን እንዲገነዘቡና ጥምረታቸውን ዘላቂ ለማድረግ እንዲጥሩ ይረዳቸዋል።
14 አንዳንድ ጥንዶች ከትዳር ለማግኘት በሚጠብቋቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ሁለት ሰዎች በሚጠናኑበት ወቅት በመካከላቸው ያለው ፍቅር ልዩ እንደሆነና ይህ ፍቅራቸው ለትዳራቸው መሳካት ዋስትና እንደሚሆን ይሰማቸው ይሆናል። ትዳርን የሚጀምሩት እንዲህ ያለ በእውነታው ላይ ያልተመሠረተ አመለካከት ይዘው ሲሆን ምንም ነገር ደስታቸውን ሊያጠፋባቸው እንደማይችል ያስባሉ። እንዲህ ያለው አመለካከት ከእውነታው ጨርሶ የራቀ ነው። በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለው የፍቅር ስሜት አስደሳች ቢሆንም ይህ ብቻ ሙሽሮቹ በጋብቻ ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን መከራዎች ለመቋቋም እንዲዘጋጁ አይረዳቸውም።—1 ቆሮንቶስ 7:28ን አንብብ።a
15 በርካታ አዳዲስ ተጋቢዎች በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ የትዳር ጓደኛቸው ከእነሱ የተለየ አስተሳሰብ እንዳለው ሲገነዘቡ ይገረማሉ፤ አልፎ ተርፎም ያዝናሉ። ለምሳሌ ገንዘባቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙ፣ ትርፍ ጊዜያቸውን የት እንደሚያሳልፉ፣ የት እንደሚኖሩ፣ ቤተሰቦቻቸውን በየስንት ጊዜው እንደሚጠይቁ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ ላይስማሙ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንዳቸው ሌላውን የሚያበሳጭ ባሕርይ ይኖራቸዋል። በሚጠናኑበት ወቅት እነዚህን ነገሮች አቅልለው ይመለከቷቸው ይሆናል፤ በኋላ ላይ ግን እነዚህ ሁኔታዎች በትዳር ውስጥ ከባድ ውጥረት ይፈጥራሉ። ለመጋባት የሚያስቡ ሁለት ሰዎች የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ከመጋባታቸው በፊት መፍታታቸው የጥበብ እርምጃ ነው።
16. ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት እንደሚወጡ ተወያይተው መስማማት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
16 ባልና ሚስት ትዳራቸው የሰመረና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተባብረው ለመፍታት መጣር አለባቸው። ለልጆቻቸው እንዴት ተግሣጽ እንደሚሰጡ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን እንዴት እንደሚንከባከቡ ተወያይተው ሊስማሙ ይገባል። በቤተሰባቸው ውስጥ የሚከሰቱት ችግሮች የሚፈጥሩት ውጥረት እንዲያራርቃቸው መፍቀድ የለባቸውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ችግሮችን መፍታትና የማይወገዱትን ችግሮች ደግሞ ችለው በደስታ አብረው መኖር ይችላሉ።—1 ቆሮ. 7:10, 11
17. ያገቡ ሰዎች በየትኞቹ ነገሮች ረገድ “ስለ ዓለም ነገር” እንደሚጨነቁ መጠበቅ ይኖርባቸዋል?
17 በ1 ቆሮንቶስ 7:32-34 ላይ ጳውሎስ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ሌላ ሐቅ ተናግሯል። (ጥቅሱን አንብብ።) ያገቡ ሰዎች “ስለ ዓለም ነገር” ይኸውም ስለ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሌሎች ሰብዓዊ ነገሮች ‘መጨነቃቸው’ የግድ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ወንድም ነጠላ በነበረበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜውንና ጉልበቱን በአገልግሎት ላይ ያሳልፍ ይሆናል። ካገባ በኋላ ግን ጊዜውንና ጉልበቱን ለአገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሚስቱን ለመንከባከብና እሷን ደስ ለማሰኘትም ማዋል እንዳለበት ይገነዘባል። ሚስትም ብትሆን ለባሏ እንዲሁ ማድረግ ይኖርባታል። ይሖዋ ባለትዳሮች እንዲህ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል። ትዳር የሰመረ እንዲሆን ባልና ሚስት ቀደም ሲል ለእሱ አገልግሎት ያውሉት ከነበረው ጊዜና ጉልበት የተወሰነውን ለትዳር ጓደኛቸው መስጠት እንዳለባቸው ያውቃል።
18. አንዳንዶች ካገቡ በኋላ ከሌሎች ጋር በሚያሳልፉት ጊዜ ረገድ ምን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል?
18 ጳውሎስ የተናገረው ነገር ሌላም ትምህርት ይዟል። ባለትዳሮች አንዳቸው ሌላውን ለማስደሰት ሲሉ ለአምላክ አገልግሎት ያውሉት የነበረውን ጊዜና ጉልበት መቀነስ ካስፈለጋቸው ነጠላ በነበሩበት ወቅት ከሌሎች ሰዎች ጋር ያሳልፉት የነበረውን ጊዜስ መቀነስ አይኖርባቸውም? አንድ ባል ከጓደኞቹ ጋር በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዱ ሚስቱ ምን እንዲሰማት ሊያደርግ ይችላል? ወይም ደግሞ አንዲት ሚስት ከጓደኞቿ ጋር በምታከናውነው አንድ ዓይነት የጊዜ ማሳለፊያ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታጠፋ ቢሆን ባለቤቷ ምን ሊሰማው ይችላል? ችላ የተባለው የትዳር ጓደኛ ብቸኝነት ሊሰማው፣ ደስታ ሊርቀውና እንደማይወደድ ሊያስብ ይችላል። ያገቡ ሰዎች ትዳራቸውን ለማጠናከር የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሊወገድ ይችላል።—ኤፌ. 5:31
ይሖዋ በሥነ ምግባር ንጹሕ እንድንሆን ይፈልጋል
19, 20. (ሀ) ያገቡ ሰዎች የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ባለትዳሮች ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የሚቆዩ ከሆነ ራሳቸውን ለየትኛው አደጋ ያጋልጣሉ?
19 የይሖዋ አገልጋዮች ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አንዳንዶች በዚህ ረገድ ችግር እንዳያጋጥማቸው ሲሉ ለማግባት ወስነዋል። ይሁንና ማግባት በራሱ ሥነ ምግባራዊ ብልግና ላለመፈጸም ጥበቃ ያስገኛል ማለት አይደለም። በጥንት ዘመን በግንብ በታጠረ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት ከቅጥሩ እስካልወጡ ድረስ ብቻ ነበር። አንድ ሰው ሽፍቶችና ወንበዴዎች ባሉበት ጊዜ ከከተማው ቢወጣ ሊዘረፍ ወይም ሊገደል ይችላል። በተመሳሳይም ያገቡ ሰዎች ከሥነ ምግባር ብልግና ሊጠበቁ የሚችሉት የጋብቻ መሥራች የሆነው አምላክ ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ያወጣውን ገደብ እስካከበሩ ድረስ ብቻ ነው።
20 ጳውሎስ፣ ይሖዋ ያወጣውን ገደብ በ1 ቆሮንቶስ 7:2-5 ላይ ገልጾታል። ከአንድ ያገባ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት የመፈጸም መብት ያላት ሚስቱ ብቻ ናት፤ በተመሳሳይም ከአንዲት ያገባች ሴት ጋር የፆታ ግንኙነት የመፈጸም መብት ያለው ባሏ ብቻ ነው። እያንዳንዳቸው ለትዳር ጓደኛቸው ‘የሚገባውን’ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፤ በሌላ አባባል የትዳር ጓደኛቸው ያለውን የፆታ ግንኙነት የመፈጸም መብት ማክበር አለባቸው። ይሁንና አንዳንድ ባልና ሚስቶች ለየብቻቸው እረፍት በመውጣት ወይም በሥራቸው ምክንያት ተራርቀው በመኖር ለረጅም ጊዜ ይለያያሉ፤ በዚህም የተነሳ አንዳቸው ለሌላው ‘የሚገባውን’ ይከለክላሉ። አንድ ሰው ‘ራሱን መግዛት አቅቶት’ ለሰይጣን ተጽዕኖ ቢሸነፍና ምንዝር ቢፈጽም ምን ያህል አሳዛኝ እንደሚሆን አስበው። ይሖዋ ትዳራቸውን አደጋ ላይ ሳይጥሉ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚጥሩ የቤተሰብ ራሶችን ይባርካቸዋል።—መዝ. 37:25
የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መታዘዝ የሚያስገኘው ጥቅም
21. (ሀ) ነጠላ ሆኖ ከመኖር ወይም ከማግባት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች ማድረግ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘው ምክር ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?
21 አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚያደርጋቸው በጣም ከባድ ውሳኔዎች መካከል ነጠላ ሆኖ ከመኖር ወይም ከማግባት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች ይገኙበታል። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ብዙ ጊዜ ለችግር መንስኤ የሚሆነው አለፍጽምና ሲሆን ይህም በሁላችንም ውስጥ ያለ ነገር ነው። በዚህም ምክንያት የይሖዋን ሞገስና በረከት ያገኙ ሰዎችም እንኳ ያገቡም ሆኑ ያላገቡ አንዳንድ ጊዜ አሳዛኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ ካደረግህ እንዲህ ያሉ ችግሮችን መቀነስ ትችላለህ። ነጠላም ሆንክ ባለትዳር በይሖዋ ዓይን ‘መልካም ማድረግ’ ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 7:37, 38ን አንብብ።) ልትደርስባቸው ከምትችላቸው ግቦች ሁሉ የላቀው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ነው። የአምላክን ሞገስ ካገኘህ እሱ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ። በዚያን ጊዜ በወንዶችና በሴቶች መካከል ካለው ግንኙነት ጋር በተያያዘ በዛሬው ጊዜ በስፋት የሚታዩት ችግሮችና ተጽዕኖዎች ይወገዳሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ከአንቀጽ 16-19 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ማንም ሰው ሌሎች እንዲያገቡ መገፋፋት የሌለበት ለምንድን ነው?
• ይሖዋን በነጠላነት የምታገለግል ከሆነ ጊዜህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?
• የሚጠናኑ ሰዎች በትዳር ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ራሳቸውን ማዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?
• ማግባት በራሱ ሥነ ምግባራዊ ብልግና ላለመፈጸም ጥበቃ አያስገኝም የምንለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ያላገቡ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን ተጠቅመው አገልግሎታቸውን የሚያሰፉ ከሆነ ደስተኞች ይሆናሉ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ካገቡ በኋላ የትኞቹን ማስተካከያዎች ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?