ጥሩ አርዓያም የማስጠንቀቂያ ምሳሌም ሊሆነን የሚችል ሰው
‘የያዕቆብ አምላክ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጐዳናውም እንሄዳለን።’—ኢሳ. 2:3
1, 2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት ዘገባዎች ጥቅም ማግኘት ይቻላል ቢባል አትስማማም? በአኗኗራቸውና በባሕርያቸው ልትመስላቸው የምትችል በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በአምላክ ቃል ውስጥ ተጠቅሰው ታገኛለህ። (ዕብ. 11:32-34) በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊታቸውንም ሆነ አመለካከታቸውን ልንኮርጅ የማይገባን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉ ወንዶችና ሴቶች እንዳሉም ሳታስተውል አልቀረህም።
2 የሚገርመው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ጥሩም መጥፎም ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ተራ እረኛ የነበረውንና በኋላም ኃያል ንጉሥ የሆነውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። ዳዊት እውነትን በመውደዱና በይሖዋ በመታመኑ ጥሩ አርዓያ ይሆነናል። ያም ሆኖ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር መፈጸምን፣ ኦርዮንን ማስገደልንና ጥበብ የጎደለው የሕዝብ ቆጠራ ማካሄድን የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ይሁንና በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ትኩረት የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ በሆነው በዳዊት ልጅ በንጉሥ ሰለሞን ላይ ነው። እስቲ በመጀመሪያ ጥሩ ምሳሌ የሆነባቸውን ሁለት መንገዶች እንመርምር።
‘የሰለሞን ጥበብ’
3. ሰለሞን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል የምንለው ለምንድን ነው?
3 ታላቁ ሰለሞን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ንጉሥ ሰለሞንን በመልካም ማንሳቱ ይህ ንጉሥ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን እንደሚችል ያሳያል። ኢየሱስ ተጠራጣሪ ለነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የደቡብ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለመጣች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትኮንነዋለች፤ ነገር ግን ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።” (ማቴ. 12:42) አዎን፣ ሰለሞን ጥበበኛ በመሆኑም ይታወቅ የነበረ ሲሆን እኛም ጥበብን እንድንፈልግ መክሮናል።
4, 5. ሰለሞን ጥበብ ያገኘው እንዴት ነው? እኛ ጥበብን የምናገኝበት መንገድ ከሰለሞን የሚለየውስ እንዴት ነው?
4 ሰለሞን በንግሥና ዘመኑ መጀመሪያ ላይ አምላክ በሕልም ተገልጦለት የፈለገውን እንዲጠይቅ ግብዣ አቀረበለት። እሱም ምንም ተሞክሮ እንደሌለው ስለተገነዘበ ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ። (1 ነገሥት 3:5-9ን አንብብ።) ሰለሞን ሀብትና ክብር ከመጠየቅ ይልቅ ጥበብ እንዲሰጠው መለመኑ አምላክን ስላስደሰተው “ጥበብና አስተዋይ ልቡና” ብቻ ሳይሆን ብልጽግናም ሰጠው። (1 ነገ. 3:10-14) የሰለሞን ጥበብ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የሳባ ንግሥት የእሱን ጥበብ በገዛ ዓይኗ ለማየት ረጅም ርቀት ተጉዛ መምጣቷን ኢየሱስ ጠቅሷል።—1 ነገ. 10:1, 4-9
5 እርግጥ ነው፣ እኛ በግለሰብ ደረጃ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበብ እናገኛለን ብለን አንጠብቅም። ሰለሞን ‘ጥበብን የሚሰጠው’ ይሖዋ እንደሆነ ቢናገርም “ጆሮህን ወደ ጥበብ [አቅና]፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል [መልስ]” በማለት ይህን አምላካዊ ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረግ እንደሚኖርብን ጠቁሟል። ጥበብን ከማግኘት ጋር በተያያዘ “ብትማጠን፣” “ብትፈልጋት” እና “ብትሻት” የሚሉ አባባሎችን መጠቀሙ ይህን ማድረግ ትጋት የሚጠይቅ መሆኑን ያሳያል። (ምሳሌ 2:1-6) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ጥበብን ማግኘት የሚቻል ነገር ነው።
6. ከጥበብ ጋር በተያያዘ ሰለሞን ከተወው ግሩም ምሳሌ ጥቅም እንዳገኘን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
6 ‘መለኮታዊውን ጥበብ ከፍ አድርጎ በመመልከት ረገድ የሰለሞንን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አደርጋለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። የኢኮኖሚው አለመረጋጋት ብዙዎች በገንዘብና በሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል፤ አሊያም ምን መማር እንዳለባቸውና እስከምን ድረስ መማር እንዳለባቸው በሚያደርጉት ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። አንተና ቤተሰብህስ በዚህ ረገድ እንዴት ናችሁ? የምታደርጉት ምርጫ መለኮታዊውን ጥበብ ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱና ይህን ጥበብ ለማግኘት እንደምትጓጉ ያሳያል? ጥበብን የበለጠ ለማግኘት ቅድሚያ በምትሰጧቸው ነገሮች ወይም በግቦቻችሁ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባችሁ ይሆን? በእርግጥም ጥበብን ለማግኘት ጥረት የምታደርጉና ያገኛችሁትን ጥበብ በሕይወታችሁ ውስጥ የምትጠቀሙበት ከሆነ ዘላቂ ጥቅም ታገኛላችሁ። ሰለሞን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በዚያን ጊዜ ጽድቅን፣ ፍትሕን፣ ሚዛናዊነትን፣ መልካሙንም መንገድ ሁሉ ትገነዘባለህ።”—ምሳሌ 2:9
እውነተኛውን አምልኮ ከፍ ከፍ ማድረጉ ሰላም አስገኝቷል
7. ታላቁ የአምላክ ቤተ መቅደስ ሊሠራ የቻለው እንዴት ነው?
7 ሰለሞን፣ ከሙሴ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን የማደሪያ ድንኳን እጹብ ድንቅ በሆነ ቤተ መቅደስ ለመተካት በግዛቱ መጀመሪያ ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። (1 ነገ. 6:1) ይህ ሕንፃ የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተብሎ ቢጠራም ቤተ መቅደስ የመሥራቱን ሐሳብ ያመነጨው እሱ አይደለም፤ እንዲሁም ድንቅ ንድፍ አውጪ ወይም ሀብቱን ለዚህ ሥራ የሰጠ ታላቅ ሰው ተብሎ የመታወቅ ፍላጎትም አልነበረውም። እንዲያውም ቤተ መቅደሱን የመሥራት ሐሳብ በመጀመሪያ ያቀረበው ዳዊት ነው፤ በዚያ ላይ አምላክ የቤተ መቅደሱንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን ንድፍ የሰጠው ለዳዊት ነው። በተጨማሪም ዳዊት ሥራውን ለመደገፍ ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። (2 ሳሙ. 7:2, 12, 13፤ 1 ዜና 22:14-16) ያም ቢሆን ሰባት ዓመት ተኩል የፈጀውን የግንባታ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው ለሰለሞን ነበር።—1 ነገ. 6:37, 38፤ 7:51
8, 9. (ሀ) መልካም ሥራዎችን በጽናት በመሥራት ረገድ ሰለሞን ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? (ለ) ሰለሞን እውነተኛውን አምልኮ ከፍ ከፍ ማድረጉ ምን ውጤት አስገኝቷል?
8 በእርግጥም ሰለሞን መልካም ሥራዎችን በጽናት በመሥራትና በተገቢው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቅቆ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደዚያ በሚገባበት ወቅት ሰለሞን በሕዝቡ ፊት ጸሎት አቅርቦ ነበር። ለይሖዋ ያቀረበው ጸሎት በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወዳልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ።” (1 ነገ. 8:6, 29) እስራኤላውያንም ሆኑ የሌላ አገር ሰዎች የአምላክ ስም በሚጠራበት በዚህ ስፍራ መጸለይ ይችሉ ነበር።—1 ነገ. 8:30, 41-43, 60
9 ሰለሞን እውነተኛውን አምልኮ ከፍ ከፍ ማድረጉ ምን ውጤት አስገኝቷል? የቤተ መቅደሱ የምረቃ በዓል ሲያበቃ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች “እግዚአብሔር ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት” አደረጉ። (1 ነገ. 8:65, 66) እንዲያውም ለ40 ዓመታት የቆየው የሰለሞን አገዛዝ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት በመሆኑ ይታወቅ ነበር። (1 ነገሥት 4:20, 21, 25ን አንብብ።) መዝሙር 72 በሰለሞን ዘመን የነበረውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ በታላቁ ሰለሞን በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ወቅት ስለምናገኛቸው በረከቶች ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል።—መዝ. 72, 6-8, 16
የማስጠንቀቂያ ምሳሌም ይሆነናል
10. ሰለሞን ስለፈጸማቸው ስህተቶች ሲነሳ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?
10 ሰለሞን የተከተለው ጎዳና የማስጠንቀቂያ ምሳሌም ሊሆነን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? ሰለሞን ስለፈጸማቸው ስህተቶች ሲነሳ በመጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው የባዕድ አገር ሚስቶችና ቁባቶች የነበሩት መሆኑ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ . . . በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።” (1 ነገ. 11:1-6) አንተ ግን እንዲህ ዓይነቱን የሞኝነት አካሄድ ላለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረግህ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ከሰለሞን ሕይወት የምናገኘው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይህ ብቻ ነው? እስቲ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸውን አንዳንድ የሕይወቱን ገጽታዎች እንመርምር፤ እንዲሁም ከዚህ ምን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።
11. ስለ ሰለሞን የመጀመሪያ ጋብቻ ከሚናገረው ዘገባ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?
11 ሰለሞን የገዛው ለ40 ዓመታት ነው። (2 ዜና 9:30) ታዲያ በ1 ነገሥት 14:21 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ትችላለህ? (ጥቅሱን አንብብ።) ይህ ጥቅስ እንደሚያስገነዝበን በሰለሞን ፋንታ የተተካው ልጁ ሮብዓም ሲነግሥ 41 ዓመቱ ነበር፤ “እናቱ [ደግሞ] ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።” ይህ ምን ማለት ነው? ሰለሞን ንጉሥ ከመሆኑ በፊት፣ ጣዖት አምላኪና የእስራኤላውያን ጠላት ከሆነ ብሔር ሚስት አግብቶ ነበር ማለት ነው። (መሳ. 10:6፤ 2 ሳሙ. 10:6) ሚስቱስ የአገሯን አማልክት ታመልክ ነበር? በአንድ ወቅት ጣዖት አምላኪ የነበረች ቢሆንም እንደ ረዓብና ሩት ሁሉ እሷም የቀድሞ እምነቷን እርግፍ አድርጋ በመተው እውነተኛውን አምልኮ ተቀብላ ይሆናል። (ሩት 1:16፤ 4:13-17፤ ማቴ. 1:5, 6) ያም ቢሆን ሰለሞን ይሖዋን የማያመልኩ አሞናውያን አማቾችና ዘመዶች እንደሚኖሩት ምንም ጥርጥር የለውም።
12, 13. ሰለሞን በግዛቱ መጀመሪያ ላይ ምን ከባድ ስህተት ሠርቶ ነበር? ምንስ ሰበብ አቅርቦ ሊሆን ይችላል?
12 ሰለሞን፣ ንጉሥ ከሆነ በኋላ ሁኔታው እየተባባሰ ሄደ። ምክንያቱም ‘የግብፅ ንጉሥ የፈርዖን ወዳጅ እንደሆነና የፈርዖንንም ልጅ እንዳገባ ከዚያም በዳዊት ከተማ እንዳስቀመጣት’ የአምላክ ቃል ይናገራል። (1 ነገ. 3:1) ይህቺ ግብፃዊ ሴት እንደ ሩት እውነተኛውን አምልኮ ተቀብላ ይሆን? ይህን እንዳደረገች የሚጠቁም ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ሰለሞን ከዳዊት ከተማ ውጪ ለእሷ (ለግብፃዊ አገልጋዮቿም ጭምር ሊሆን ይችላል) ቤት እንደሠራ ዘገባው ይናገራል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? የሐሰት አምላኪ የሆነ ሰው በቃል ኪዳኑ ታቦት አቅራቢያ መኖሩ ተገቢ ባለመሆኑ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ዜና 8:11
13 ሰለሞን ግብፃዊቷን ልዕልት ማግባቱ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተሰምቶት ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሊሆን ይችላል? ከብዙ ዓመታት በፊት አምላክ አረማዊ ከሆኑት ከከነዓናውያን ጋር ጋብቻ እንዳይመሠርቱ እስራኤላውያንን ከልክሏቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹን ብሔራት በስም ጠቅሶ ነበር። (ዘፀ. 34:11-16) ሰለሞን ‘ግብፃውያን በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም’ ብሎ አስቦ ይሆን? ያም ቢሆን እንዲህ ያለው ሰበብ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል? በእርግጥም ሰለሞን እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተሉ ይሖዋ የጠቀሰውን አንድ ግልጽ የሆነ አደጋ ማለትም እስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት ጋር መጋባታቸው ይሖዋን ትተው የሐሰት አማልክትን እንዲያመልኩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ እንዳለ የሚያሳይ ነው።—ዘዳግም 7:1-4ን አንብብ።
14. የሰለሞንን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ልብ ማለታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
14 የሰለሞን አካሄድ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው እንዴት ነው? አንዲት እህት ጋብቻ “በጌታ ብቻ ይሁን” በማለት አምላክ የሰጠውን መመሪያ ችላ በማለት የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመሯ አንዳንድ ሰበቦችን ለማቅረብ ትሞክር ይሆናል። (1 ቆሮ. 7:39) በተመሳሳይም አንዳንዶች በሌሎች ጉዳዮች ረገድ አጥጋቢ የሚመስሉ ምክንያቶችን ያቀርቡ ይሆናል፤ ለምሳሌ አንድ ተማሪ ከትምህርት ሰዓት ውጪ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በክበቦች ውስጥ ለመሳተፍ ወይም አንድ ወንድም ለግብር ሲል ገቢውን አሳንሶ ለመናገር ሰበብ ያቀርብ ይሆናል፤ አሊያም ስላደረገው ነገር ሲጠየቅ ኀፍረቱን ለመሸፋፈን ሲል ይዋሽ ይሆናል። እንግዲያው ከሰለሞን ታሪክ አንድ የምናገኘው ትምህርት አለ፦ ሰለሞን የአምላክን ሕግ ላለመጠበቅ ሰበብ እንዳቀረበ ሁሉ እኛም ካልተጠነቀቅን ተመሳሳይ አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል።
15. ይሖዋ ለሰለሞን ምሕረት ያሳየው እንዴት ነው? ይሁንና ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?
15 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰለሞን የባዕድ አገር ልዕልት ካገባ በኋላ አምላክ፣ ሰለሞን የጠየቀውን ጥበብ ብቻ ሳይሆን ሀብትም ጭምር እንደሰጠው መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። (1 ነገ. 3:10-13) ሰለሞን የአምላክን መመሪያዎች ችላ ቢልም ይሖዋ ወዲያውኑ ከንግሥናው እንደሻረው ወይም ከባድ ተግሣጽ እንደሰጠው የሚጠቁም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ይህም ይሖዋ ከአፈር የተሠራንና ፍጽምና የጎደለን መሆናችንን የሚገነዘብ አምላክ እንደሆነ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐቅ ጋር ይስማማል። (መዝ. 103:10, 13, 14) ይሁንና አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፦ የምናደርጋቸው ነገሮች ወዲያውኑም ይሁን ውሎ አድሮ መዘዝ ማስከተላቸው አይቀርም።
በጣም ብዙ ሚስቶችን አገባ!
16. ሰለሞን ብዙ ሚስቶች ማግባቱ ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?
16 ንጉሥ ሰለሞን በማሕልየ መሓልይ ላይ ከ60 ንግሥቶችና ከ80 ቁባቶች ይበልጥ ውብ ስለሆነች አንዲት ልጃገረድ በአድናቆት ተናግሯል። (ማሕ. 6:1, 8-10) እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሴቶች የሰለሞን ሚስቶችና ቁባቶች ከሆኑ ሰለሞን ይህን በተናገረበት ወቅት በርካታ ሚስቶችና ቁባቶች ነበሩት ማለት ነው። ከእነዚህ ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ሌላው ቀርቶ ሁሉም እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ቢሆኑ እንኳ አንድ የእስራኤል ንጉሥ ‘ልቡ እንዳይስት ብዙ ሚስቶችን ማግባት እንደሌለበት’ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ሰለሞን ተላልፏል። (ዘዳ. 17:17) እርግጥ ነው፣ በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ሞገሱን አልነፈገውም። እንዲያውም አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ እንዲጽፍ በማድረግ ሰለሞንን ባርኮታል።
17. የትኛውን እውነታ መዘንጋት አይኖርብንም?
17 ሰለሞን የይሖዋን ሞገስ አለማጣቱ የአምላክን መመሪያ ችላ እያለ ከቅጣት ማምለጥ ይችል እንደነበር ወይም እኛ እንዲህ ማድረግ እንደምንችል የሚጠቁም ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሁኔታ፣ አምላክ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ እንደሚታገሥ የሚያሳይ ነው። አንድ የአምላክ አገልጋይ የይሖዋን መመሪያ ችላ ሲል ወዲያውኑ የዘራውን አለማጨዱ የሚፈጽመው ድርጊት ውሎ አድሮ መጥፎ ውጤት አያስከትልበትም ማለት አይደለም። ሰለሞን “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል” ብሎ እንደጻፈ ልብ በል። አክሎም “እግዚአብሔርን የሚያከብሩ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው ዐውቃለሁ” ብሏል።—መክ. 8:11, 12
18. በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑ በሰለሞን ሕይወት የታየው እንዴት ነው?
18 ሰለሞን፣ ራሱ ከጻፈው ከዚህ መለኮታዊ እውነት ጋር ተስማምቶ ቢኖር እንዴት ጥሩ ነበር! እርግጥ ነው፣ ሰለሞን ብዙ መልካም ነገሮችን አከናውኗል፤ አምላክም በእጅጉ ባርኮታል። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በስህተት ላይ ስህተት መፈጸም ጀመረ። በዚህም ምክንያት መጥፎ ድርጊት መፈጸምን ልማድ እያደረገ ሄደ። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት “አትታለሉ፦ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ብሎ መናገሩ ምንኛ ትክክል ነው! (ገላ. 6:7) ሰለሞን የአምላክን መመሪያዎች ችላ ማለቱ የኋላ ኋላ አሳዛኝ ውጤት አስከትሎበታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ንጉሥ ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን ማለትም ሞዓባውያትን፣ አሞናውያትን፣ ኤዶማውያትን፣ ሲዶናውያትን፣ ኬጢያውያትን አፈቀረ።” (1 ነገ. 11:1) ከእነዚህ ሴቶች መካከል ብዙዎቹ የሐሰት አማልክትን ማምለካቸውን ሳይቀጥሉ አልቀረም፤ ሰለሞንም ቢሆን ከዚህ ማምለጥ አልቻለም። ከትክክለኛው ጎዳና በመውጣቱ የታጋሹ አምላካችንን የይሖዋን ሞገስ አጥቷል።—1 ነገሥት 11:4-8ን አንብብ።
ጥሩም መጥፎም አርዓያ ከሆነው ንጉሥ ትምህርት ማግኘት
19. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል? አብራራ።
19 ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” (ሮም 15:4) ቀደም ብሎ ከተጻፉት ነገሮች መካከል ጥሩ ምሳሌ ስለሚሆኑና አስደናቂ እምነት ስላሳዩ ወንዶችና ሴቶች የሚናገሩት ዘገባዎች ይገኙበታል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን እላለሁ? ምክንያቱም ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት እንዲሁም ስለ ሳሙኤልና ስለ ሌሎቹ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል፤ እነዚህ ሰዎች በእምነት መንግሥታትን በውጊያ ድል ነስተዋል፣ ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር ፈጽመዋል፣ የተስፋ ቃል አግኝተዋል፣ . . . ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል።” (ዕብ. 11:32-34) በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ሰዎችን ፈለግ በመከተል እነሱ ከተዉት ምሳሌ ጥቅም ማግኘት እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል።
20, 21. በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ ያደረከው ለምንድን ነው?
20 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የማስጠንቀቂያ ምሳሌም ይዘዋል። ከእነዚህ ዘገባዎች መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት የይሖዋን ሞገስ ስላገኙና የእሱ አገልጋይ ስለነበሩ ሰዎች የሚያወሱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች መቼና እንዴት ከትክክለኛው መንገድ እንደወጡ እንዲሁም ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ የሚሆኑት በምን መንገድ እንደሆነ እንገነዘባለን። አንዳንዶቹ ቀስ በቀስ የተሳሳተ ዝንባሌና አመለካከት እንዳዳበሩ፣ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ መጥፎ ውጤት እንዳስከተለባቸው መመልከት እንችላለን። ታዲያ ከእነዚህ ዘገባዎች ትምህርት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን በመጠየቅ ነው፦ ‘እነዚህ ሰዎች ይህን ዝንባሌ ሊያዳብሩ የቻሉት እንዴት ነው? እንዲህ ያለው ሁኔታ በእኔ ላይ ሊደርስ ይችላል? ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ እንዳይደርስ በዘገባዎቹ ውስጥ የሚገኙት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች የሚጠቅሙኝ እንዴት ነው?’
21 በእርግጥም፣ እነዚህን ምሳሌዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።”—1 ቆሮ. 10:11
እስካሁን ምን ተረዳህ?
• በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥሩም መጥፎም ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች እናገኛለን የምንለው ለምንድን ነው?
• ሰለሞን መጥፎ ድርጊት መፈጸምን ልማድ እያደረገ የሄደው እንዴት ነው?
• ከሰለሞን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰለሞን ከአምላክ ያገኘውን ጥበብ በሕይወቱ ውስጥ ተጠቅሞበታል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሰለሞን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት እየሆነህ ነው?