“ደፋርና ብርቱ ሁን”
“ደፋርና ብርቱ ሁን፤ . . . አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር [ነው]።”—ኢያሱ 1:7-9 NW
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ሄኖክና ኖኅ ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው?
በጥንት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ሴቶች እምነትና ድፍረት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
ከወጣቶች መካከል ድፍረት በማሳየት ረገድ አንተን የማረከህ የማን ምሳሌ ነው?
1, 2. (ሀ) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ ምን ያስፈልገናል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ድፍረት የፍርሃት፣ የመሸማቀቅና የወኔቢስነት ተቃራኒ ነው። አንድ ሰው ደፋር ነው ሲባል ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣልን ግለሰቡ ብርቱ፣ ልበ ሙሉ፣ ቆራጥ ሌላው ቀርቶ ምንም የማይፈራ እንደሆነ ሊሆን ይችላል። የሚገርመው ነገር፣ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግም ድፍረት ማሳየት የሚያስፈልገን ጊዜ አለ።
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ያጋጠማቸውን ፈታኝ ሁኔታ ያለ ምንም ፍርሃት በድፍረት ተወጥተዋል። ሌሎች ደግሞ በሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚደርሱ ነገሮች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ድፍረት አሳይተዋል። ድፍረት በማሳየት ረገድ ምሳሌ ከሚሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሰዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? ደፋሮች መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው?
ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ ድፍረት ያሳዩ የይሖዋ ምሥክሮች
3. ሄኖክ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች አስመልክቶ ምን ትንቢት ተናግሯል?
3 በኖኅ ዘመን ከተከሰተው የጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት ክፉ ሰዎች መካከል ሆኖ ስለ ይሖዋ መመሥከር ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ” የሚከተለውን ትንቢት በድፍረት ተናግሯል፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” (ይሁዳ 14, 15) ሄኖክ ከላይ ያለውን በተናገረበት ወቅት ሁኔታውን እንደተፈጸመ አድርጎ መግለጹ ትንቢቱ መፈጸሙ እንደማይቀር ያሳያል። በእርግጥም ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት ከምድረ ገጽ አስወግዷቸዋል።
4. ኖኅ ‘አካሄዱን ከአምላክ ጋር ያደረገው’ በምን ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው?
4 የጥፋት ውኃው የተከሰተው በ2370 ዓ.ዓ. ማለትም ሄኖክ ትንቢቱን ከተናገረ ከ650 ዓመታት በኋላ ነው። ኖኅ የተወለደው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ኖኅ ቤተሰብ መሥርቶ ልጆች ያፈራ ከመሆኑም ባሻገር ከልጆቹ ጋር ሆኖ መርከብ ሠርቷል። በዚህ ወቅት ክፉ መላእክት ሥጋ በመልበስ ቆንጆ የሆኑ ሴቶችን አግብተው ኔፊሊሞችን ወለዱ። ከዚህም በላይ የሰው ክፋት በምድር ላይ በመብዛቱ ምድር በዓመፅ ተሞላች። (ዘፍ. 6:1-5, 9, 11) ያም ሆኖ “የጽድቅ ሰባኪ የነበረው” ኖኅ በድፍረት በመመሥከር ‘አካሄዱን ከአምላክ ጋር አደረገ።’ (2 ጴጥሮስ 2:4, 5ን አንብብ።) እኛም በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እንዲህ ዓይነት ድፍረት ማሳየት ያስፈልገናል።
ድፍረትና እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል
5. ሙሴ ደፋርና የእምነት ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
5 ሙሴ እምነትና ድፍረት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው። (ዕብ. 11:24-27) አምላክ ከ1513 እስከ 1473 ዓ.ዓ. ባሉት ጊዜያት እስራኤላውያንን ከግብፅ በማውጣት በምድረ በዳ የመራቸው በሙሴ አማካኝነት ነው። ሙሴ መጀመሪያ ላይ ብቁ እንዳልሆነ ቢሰማውም በኋላ ግን የተሰጠውን ተልእኮ ተቀብሏል። (ዘፀ. 6:12) እሱና ወንድሙ አሮን አምባገነን በሆነው በግብፁ ፈርዖን ፊት በተደጋጋሚ ጊዜያት በመቅረብ ስለ አሥሩ መቅሰፍቶች በድፍረት ተናግረዋል፤ ይሖዋም በእነዚህ መቅሰፍቶች አማካኝነት የግብፅ ጣዖታት ከንቱ መሆናቸውን ያጋለጠ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር ነፃ አውጥቷል። (ዘፀ. ከምዕ. 7 እስከ 12) ሙሴ ደፋርና የእምነት ሰው መሆን የቻለው የአምላክ ድጋፍ ምንጊዜም ስላልተለየው ነው፤ በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ተመሳሳይ ድጋፍ ያደርግልናል።—ዘዳ. 33:27
6. በባለሥልጣናት ፊት በምንቀርብበት ወቅት በድፍረት መመሥከር እንድንችል የሚረዳን ምንድን ነው?
6 እኛም እንደ ሙሴ ድፍረት ማሳየት ይገባናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በእኔ ምክንያት በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ ይህም ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ ምሥክር ይሆናል። ይሁን እንጂ አሳልፈው ሲሰጧችሁ እንዴት ብለን እንናገራለን? ምንስ ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋል፤ የምትናገሩት እናንተ ብቻ አይደላችሁም፤ የአባታችሁ መንፈስም በእናንተ ይናገራል።” (ማቴ. 10:18-20) በባለሥልጣናት ፊት በምንቀርብበት ወቅት የይሖዋ መንፈስ በአክብሮት ሆኖም እምነትና ድፍረት በሚንጸባረቅበት መንገድ ምሥክርነት እንድንሰጥ ያስችለናል።—ሉቃስ 12:11, 12ን አንብብ።
7. ኢያሱ ደፋርና ስኬታማ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
7 የሙሴ ተተኪ የሆነው ኢያሱ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማጥናቱ እምነቱ እንዲጠናከርና ይበልጥ ደፋር እንዲሆን ረድቶታል። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው በነበረበት ወቅት ማለትም በ1473 ዓ.ዓ. አምላክ ኢያሱን “ደፋርና ብርቱ ሁን” በማለት አበረታታው። ኢያሱ ከይሖዋ ሕግ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ከሆነ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን እንዲሁም በሚያደርገው ነገር ሁሉ ስኬታማ መሆን ይችላል። “አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ” የሚል ማበረታቻም አግኝቶ ነበር። (ኢያሱ 1:7-9 NW) እነዚህ ቃላት ኢያሱን በጣም አበረታተውት መሆን አለበት! በእርግጥም አምላክ ከእሱ ጋር ነበር፤ ምክንያቱም በ1467 ዓ.ዓ. ተስፋይቱን ምድር ለመቆጣጠር የፈጀበት ጊዜ ስድስት ዓመት ብቻ ነበር።
ቆራጥ አቋም የወሰዱ ሴቶች
8. እምነትና ድፍረት በማሳየት ረገድ ረዓብ ምን ምሳሌ ትታለች?
8 በታሪክ ዘመናት በርካታ ደፋር ሴቶች ከይሖዋ አምልኮ ጎን ለመቆም ቆራጥ አቋም ወስደዋል። ለምሳሌ በኢያሪኮ ከተማ ትኖር የነበረችው ጋለሞታይቷ ረዓብ፣ ድፍረት የሚጠይቅ ቢሆንም ኢያሱ የላካቸውን ሁለት ሰላዮች በመደበቅና የኢያሪኮ ንጉሥ መልእክተኞችን በተሳሳተ አቅጣጫ በመምራት በአምላክ ላይ እምነት እንዳላት አሳይታለች። በመሆኑም እስራኤላውያን ኢያሪኮን ሲቆጣጠሩ እሷና ቤተሰቦቿ በሕይወት ሊተርፉ ችለዋል። ረዓብ ትተዳደርበት የነበረውን የግልሙትና ሥራ እርግፍ አድርጋ በመተው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ሆነች፤ እንዲሁም የመሲሑ ቅድመ አያት የመሆን መብት አገኘች። (ኢያሱ 2:1-6፤ 6:22, 23፤ ማቴ. 1:1, 5) በእርግጥም እምነትና ድፍረት ማሳየቷ በእጅጉ ክሷታል!
9. ዲቦራ፣ ባርቅ እና ኢያዔል ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው?
9 ኢያሱ በ1450 ዓ.ዓ. ከሞተ በኋላ በእስራኤል ፍትሕን ለማስፈን መሳፍንቶች ያስተዳድሩ ነበር። የከነዓን ንጉሥ የነበረው ኢያቢስ እስራኤላውያን ለ20 ዓመታት ሲጨቁን ነበር፤ በዚህ ጊዜ መስፍኑ ባርቅ እርምጃ እንዲወስድ አምላክ በነቢይቱ ዲቦራ አማካኝነት ነገረው። ባርቅ 10,000 የሚያህሉ ሰዎችን በታቦር ተራራ ላይ በማሰባሰብ ለውጊያ ተዘጋጀ፤ የኢያቢስ ሠራዊት ዋና አዛዥ የነበረው ሲሣራ ደግሞ 900 የጦር ሠረገሎችን አስከትሎ ወደ ቂሶን ሸለቆ ወረደ። እስራኤላውያን ወደ ሸለቆው እየወረዱ ሳሉ አምላክ የሲሣራ ሠራዊት የሰፈረበትን ቦታ በጎርፍ በማጥለቅለቁ የሲሣራ ሠረገሎች ማጥ ውስጥ ተዘፍቀው መንቀሳቀስ ተሳናቸው። በጦርነቱ ወቅት “የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ”፤ በመሆኑም የባርቅ ወታደሮች ድል ተቀዳጁ። ለመሸሸግ ወደ ኢያዔል ድንኳን የሄደው ሲሣራም ተኝቶ ሳለ በኢያዔል እጅ ተገደለ። ዲቦራ አስቀድማ እንደተናገረችው ለተገኘው ድል ‘ክብር’ የተሰጠው ለኢያዔል ነበር። ዲቦራ፣ ባርቅ እና ኢያዔል ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዳቸው እስራኤል “ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።” (መሳ. 4:1-9, 14-22፤ 5:20, 21, 31) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሌሎች በርካታ ወንዶችና ሴቶችም ተመሳሳይ እምነትና ድፍረት አሳይተዋል።
በአንደበታችን ሌሎችን ማበረታታት እንችላለን
10. የምንናገረው ነገር ወንድሞቻችንን ሊያበረታታ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?
10 የምንናገረው ነገር የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሊያበረታታቸው ይችላል። በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ላይ ንጉሥ ዳዊት ልጁን ሰለሞንን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እንግዲህ በል በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋር ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም።” (1 ዜና 28:20) ሰለሞን ብርታት በማግኘቱ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ገንብቷል።
11. አንዲት እስራኤላዊት ልጅ በድፍረት የተናገረችው ነገር የአንድን ሰው ሕይወት የቀየረው እንዴት ነው?
11 በአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አንዲት እስራኤላዊት ልጅ በድፍረት የተናገረችው ነገር በለምጽ ለተያዘ ሰው መዳን ምክንያት ሆኗል። ይህች ልጅ በወራሪ ጦር በመማረኳ የሠራዊት አለቃ የሆነው የለምጻሙ የንዕማን ሚስት አገልጋይ ሆና ነበር። ይሖዋ በኤልሳዕ በኩል ስላደረገው ተአምር ታውቅ ስለነበር ንዕማን ወደ እስራኤል ቢሄድ የአምላክ ነቢይ ሊፈውሰው እንደሚችል ለባለቤቱ ነገረቻት። ንዕማንም ወደ እስራኤል በመሄድ በተአምር ከለምጹ የተፈወሰ ከመሆኑም በላይ የይሖዋ አምላኪ መሆን ችሏል። (2 ነገ. 5:1-3, 10-17) አንተም እንደዚህች ልጅ ይሖዋን የምትወድ ወጣት ከሆንክ ለአስተማሪዎችህ፣ አብረውህ ለሚማሩትና ለሌሎች ሰዎች መመሥከር እንድትችል አምላክ ድፍረቱን ይሰጥሃል።
12. ንጉሥ ሕዝቅያስ የተናገረው ነገር በሕዝቡ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?
12 የታሰበባቸው ቃላት መናገር በመከራ ውስጥ ያለን ሰው ሊያበረታታ ይችላል። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የአሦር ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ በዘመተ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በርቱ፤ ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ታዲያ ይህ ንግግር በሕዝቡ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳደረ? ሕዝቡ “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል” እንደተበረታታ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ዜና 32:7, 8) ተቃዋሚዎች ስደት ሲያደርሱብን እንዲህ ያሉ የሚያንጹ ቃላትን መስማታችን ለሁላችንም ትልቅ ማበረታቻ ይሰጠናል።
13. የንጉሥ አክዓብ ቤት አዛዥ የሆነው አብድዩ ድፍረት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
13 አንዳንድ ጊዜ ድፍረት የሚገለጸው በንግግር ብቻ ላይሆን ይችላል። በአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የንጉሥ አክዓብ ቤት አዛዥ የሆነው አብድዩ፣ በክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል እንዳይገደሉ ሲል በድፍረት መቶ የይሖዋ ነቢያትን ወስዶ “አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ” ነበር። (1 ነገ. 18:4) ፈሪሃ አምላክ እንደነበረው እንደ አብድዩ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የሚመለከት መረጃ ለአሳዳጆች ባለመስጠት ወንድሞቻቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተከላክለዋል።
አስቴር—ደፋሯ ንግሥት
14, 15. ንግሥት አስቴር እምነትና ድፍረት ያሳየችው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
14 ክፉ የሆነው ሐማ በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ላይ በመላው የፋርስ ግዛቶች በሚገኙ አይሁዳውያን ላይ የጠነሰሰውን የዘር ማጥፋት ሴራ ለማክሸፍ ንግሥት አስቴር ታላቅ እምነትና ድፍረት አሳይታለች። አይሁዳውያን ይህን ሲሰሙ ማዘናቸውና መጾማቸው ምናልባትም መጸለያቸው ምንም አያስገርምም። (አስ. 4:1-3) ንግሥት አስቴርም ብትሆን በጣም ተጨንቃለች። የአጎቷ ልጅ የሆነው መርዶክዮስ የጅምላ ጭፍጨፋው እንዲካሄድ የሚያዘውን ደብዳቤ ቅጂ የላከላት ከመሆኑም በላይ ወደ ንጉሡ በመግባት ወገኖቿን ይታደግ ዘንድ እንድትለምነው አጥብቆ ነገራት። ይሁን እንጂ ሳይጠራ ወደ ንጉሡ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደል ነበር።—አስ. 4:4-11
15 ያም ሆኖ መርዶክዮስ አስቴርን ‘አንቺ ዝም ብትዪ መዳን ከሌላ ቦታ ይመጣል። ሆኖም ንግሥት የሆንሽው ለዚህ ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?’ አላት። አስቴርም ሕዝቡን በሱሳ እንዲሰበስብና ስለ እሷ እንዲጾሙ ለመርዶክዮስ ነገረችው። በተጨማሪም እንዲህ አለችው፦ “እናንተ እንደምታደርጉት ሁሉ [እኔም እጾማለሁ]፤ ይህ ከተፈጸመ በኋላ ግን ነገሩ ምንም እንኳ ከሕግ ውጭ ቢሆንም፣ ወደ ንጉሡ ዘንድ እሄዳለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።” (አስ. 4:12-17) በስሟ የተሰየመው መጽሐፍ እንደሚያሳየው አስቴር ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዷ አምላክ ሕዝቡን ታድጓል። በዘመናችንም ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ታማኝ አጋሮቻቸው በመከራ ጊዜ ተመሳሳይ ድፍረት ያሳያሉ፤ ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክም ምንጊዜም ከጎናቸው ነው።—መዝሙር 65:2ን እና 118:6ን አንብብ።
“አይዟችሁ!”
16. በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወጣቶች ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ “ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው” ነበር። “በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በማስተዋል ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር።” (ሉቃስ 2:41-50) ኢየሱስ ልጅ ቢሆንም በቤተ መቅደሱ የሚገኙ በዕድሜ ትልልቅ የነበሩ መምህራንን መጠየቁ እምነትና ድፍረት እንደነበረው ያሳያል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸው ‘ስለ ተስፋቸው ለሚጠይቃቸው ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት’ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት ይረዳቸዋል።—1 ጴጥ. 3:15
17. ኢየሱስ “አይዟችሁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ያበረታታቸው ለምንድን ነው? እኛስ ደፋሮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
17 ኢየሱስ ‘አይዟችሁ’ በማለት ሌሎችን ያበረታታ ነበር። (ማቴ. 9:2, 22) በአንድ ወቅትም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት እየቀረበ ነው፤ እንዲያውም ደርሷል፤ ይሁንና አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም። እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ. 16:32, 33) እንደ ጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ ዓለም እኛንም ይጠላናል፤ ሆኖም ከዓለም ጋር መመሳሰል አንፈልግም። ድፍረት በማሳየት ረገድ የአምላክ ልጅ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ከዚህ ዓለም እድፍ ለመራቅ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ኢየሱስ ዓለምን አሸንፏል፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።—ዮሐ. 17:16፤ ያዕ. 1:27
“አይዞህ፣ አትፍራ!”
18, 19. ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትና ድፍረት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት ተቋቁሟል። በአንድ ወቅት የሮም ወታደሮች ደርሰው ባያስጥሉት ኖሮ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አይሁዳውያን ሊዘነጣጥሉት ተዘጋጅተው ነበር። በዚያን ዕለት፣ ሌሊት ላይ “ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለው፦ ‘አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ የተሟላ ምሥክርነት እንደሰጠህ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።’” (ሥራ 23:11) ጳውሎስም እንደተባለው አድርጓል።
19 ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኘውን ጉባኤ ለመበከል ጥረት ያደርጉ የነበሩትን “ምርጥ ሐዋርያት” ያለምንም ፍርሃት በድፍረት ገሥጿቸዋል። (2 ቆሮ. 11:5፤ 12:11) ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች በተለየ እውነተኛ ሐዋርያ ለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ ይችል ነበር፤ ለምሳሌ የደረሰበት እስርና ግርፋት፣ ያደረጋቸው አደገኛ ጉዞዎች ብሎም ሌሎች አስፈሪ ሁኔታዎችን መጋፈጡ እንዲሁም መራቡ፣ መጠማቱ፣ እንቅልፍ ማጣቱና ለእምነት ባልንጀሮቹ መጨነቁ ለዚህ ማስረጃ ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:23-28ን አንብብ።) እንዴት ያለ የእምነትና የድፍረት ምሳሌ ነው! ጳውሎስ ይህን ሁሉ መጋፈጥ የቻለው አምላክ በሰጠው ብርታት ነው።
20, 21. (ሀ) ምንጊዜም ደፋሮች መሆን እንደሚያስፈልገን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር። (ለ) ድፍረት ማሳየት የሚያስፈልገን በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው? ስለ ምን ነገርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
20 ከባድ ፈተና የሚያጋጥማቸው ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ያም ሆኖ ሁሉም ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ውጣ ውረዶች ለማሸነፍ ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸዋል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በብራዚል የሚኖር አንድ ወጣት የወረበሎች ቡድን አባል ነበር። ይህ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ተገነዘበ፤ ሆኖም ከዚህ ቡድን የሚወጣ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ይገደል ነበር። ጉዳዩን አስመልክቶ ከጸለየ በኋላ ከቡድኑ መውጣት የፈለገበትን ምክንያት ጥቅሶችን በመጠቀም ለመሪያቸው አስረዳው። ይህ ወጣት ከዚህ ቡድን በሰላም መለያየት የቻለ ሲሆን አሁን የመንግሥቱ አስፋፊ ሆኗል።
21 ምሥራቹን ለመስበክ ድፍረት ያስፈልጋል። ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ይህን ባሕርይ ማዳበር ይኖርባቸዋል። ሠራተኞች ደግሞ በሁሉም የአውራጃ ስብሰባ ቀናት መገኘት እንዲችሉ ከመሥሪያ ቤታቸው ፈቃድ ለመጠየቅ ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ረገድ እንዘርዝር ብንል ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን። የሚያጋጥመን ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ‘በእምነት የምናቀርበውን ጸሎት’ ይሰማል። (ያዕ. 5:15) መንፈስ ቅዱሱን በመስጠት “ደፋርና ብርቱ” እንደሚያደርገንም እርግጠኞች መሆን እንችላለን!
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄኖክ ፈሪሃ አምላክ በሌላቸው ሰዎች መካከል በድፍረት ሰብኳል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢያኤል ደፋርና ብርቱ ነበረች