ይሖዋ ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ ነው
“ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።”—ዕብ. 11:6
1, 2. (ሀ) በፍቅርና በእምነት መካከል ምን ተያያዥነት አለ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ይሖዋ “አስቀድሞ ስለወደደን” እኛም እንወደዋለን። (1 ዮሐ. 4:19) ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይበት አንዱ መንገድ የሚባርካቸው መሆኑ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ በሄደ መጠን አምላክ መኖሩንና ለሚወዳቸው ወሮታ ከፋይ መሆኑን ይበልጥ እርግጠኛ ስለምንሆን እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል።—ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።
2 ወሮታ ከፋይ መሆን የይሖዋ ማንነትና የመንገዶቹ አቢይ ገጽታ ነው። አምላክ ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ መሆኑን እርግጠኞች ካልሆንን እምነታችን ሙሉ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም “እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው።” (ዕብ. 11:1) በእርግጥም እምነት ማለት ይሖዋ ቃል የገባቸው በረከቶች መፈጸማቸው እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ መተማመን ነው። ይሁንና ወሮታ እንደምናገኝ ተስፋ ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ጥንትም ሆነ ዛሬ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ከፋይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚባርክ ቃል ገብቷል
3. ይሖዋ በሚልክያስ 3:10 ላይ ምን ቃል ገብቶልናል?
3 ይሖዋ አምላክ፣ ለታማኝ አገልጋዮቹ ወሮታ ለመክፈል ራሱን ግዳጅ ውስጥ ያስገባ ሲሆን በረከቱን ለማግኘት እንድንጥርም ጋብዞናል። እንዲህ ብሏል፦ “የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣ እስቲ . . . ፈትኑኝ።” (ሚል. 3:10) ይሖዋ እንድንፈትነው ያቀረበውን ግብዣ በመቀበል አድናቆታችንንና አመስጋኝነታችንን እናሳያለን።
4. ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ በሰጠው ማረጋገጫ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የአምላክን መንግሥት ካስቀደሙ ይሖዋ እንደሚደግፋቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:33ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ማረጋገጫ የሰጠው ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በመፈጸም ረገድ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት አምላክ ስለሆነ ነው። አምላክ የተናገረውን ነገር ምንጊዜም እንደሚፈጸም ኢየሱስ ያውቃል። (ኢሳ. 55:11) እኛም በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት እንዳለን ካሳየን እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዕብ. 13:5) ይሖዋ የገባው ይህ ቃል፣ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ካስቀደምን ይሖዋ እንደሚባርከን በተናገረው ሐሳብ እንድንተማመን ያደርገናል።
5. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ እምነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
5 በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” በማለት ጠይቆት ነበር። (ማቴ. 19:27) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ይህን ጥያቄ በማቅረቡ ተግሣጽ ከመስጠት ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ ለከፈሉት መሥዋዕት ወሮታ እንደሚያገኙ ተናገረ። ታማኝ ሐዋርያቱን ጨምሮ ሌሎች ተከታዮቹ ከእሱ ጋር በሰማይ ይገዛሉ። ይሁንና በዚህ ዘመንም ቢሆን የሚያገኙት ወሮታ አለ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።” (ማቴ. 19:29) ደቀ መዛሙርቱ በሕይወታቸው ውስጥ መሥዋዕት ካደረጉት ከየትኛውም ነገር እጅግ የላቀ በረከት ያገኛሉ። መንፈሳዊ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶች ወይም ልጆች ማግኘታችን ለመንግሥቱ ስንል ከተውነው ከማንኛውም ነገር አይበልጥም?
“ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ”
6. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ እንደሚከፍል ቃል መግባቱ ምን ጥቅም አለው?
6 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ እንደሚከፍል ቃል መግባቱ፣ አገልጋዮቹ ንጹሕ አቋማቸውን የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ለመጽናት ይረዳቸዋል። የይሖዋ አምላክ ታማኝ አገልጋዮች አሁን ከሚያገኟቸው የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶች በተጨማሪ ወደፊት የላቁ በረከቶችን እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ። (1 ጢሞ. 4:8) በእርግጥም ይሖዋ “ከልብ [ለሚፈልጉት] ወሮታ ከፋይ መሆኑን” እርግጠኛ መሆናችን በእምነት ጸንተን ለመኖር ይረዳናል።—ዕብ. 11:6
7. ተስፋችን እንደ መልሕቅ የሚሆንልን እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።” (ማቴ. 5:12) በሰማይ ሽልማት የሚያገኙት የአምላክ አገልጋዮችም ሆኑ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ‘ሐሴት ለማድረግና በደስታ ለመፈንጠዝ’ የሚያበቃ ምክንያት አላቸው። (መዝ. 37:11፤ ሉቃስ 18:30) ሽልማታችን በሰማይ መኖርም ይሁን በምድር “አስተማማኝና ጽኑ” የሆነው ተስፋችን “ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ” ይሆንልናል። (ዕብ. 6:17-20) መልሕቅ፣ ኃይለኛ ማዕበል በሚነሳበት ወቅት አንድን መርከብ አጥብቆ እንደሚይዘው ሁሉ ሽልማት እንደምናገኝ ያለን የተረጋገጠ ተስፋም ስሜታችንና አስተሳሰባችን እንዲረጋጋ እንዲሁም መንፈሳዊነታችን እንዳይናጋ ይረዳናል። ተስፋችን፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በጽናት ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል።
8. ተስፋችን ጭንቀታችንን ለማቅለል የሚረዳን እንዴት ነው?
8 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችን በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥመንን ጭንቀት ያቀልልናል። ሕመምን እንደሚያስታግስ ቅባት ሁሉ አምላክ የገባው ቃልም የተጨነቀ ልባችንን ያረጋጋልናል። ይሖዋ ‘እንደሚደግፈን’ ተማምነን ‘ሸክማችንን በእሱ ላይ መጣል’ መቻላችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! (መዝ. 55:22) አምላክ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ” እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (ኤፌ. 3:20) እስቲ አስበው፤ ይሖዋ የሚያደርግልን “አብልጦ” ወይም “እጅግ አብልጦ” ብቻ ሳይሆን ከምናስበው ሁሉ “በላይ እጅግ አብልጦ” ነው!
9. ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
9 ሽልማታችንን ማግኘት ከፈለግን በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ማሳደር እንዲሁም መመሪያዎቹን መታዘዝ ይኖርብናል። ሙሴ የእስራኤልን ብሔር እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ [ይባርክሃል]፤ . . . ይህ የሚሆነው ግን የአምላክህን የይሖዋን ቃል በትኩረት የምትሰማና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዛት በሙሉ በጥንቃቄ የምትፈጽም ከሆነ ነው። አምላክህ ይሖዋ በገባልህ ቃል መሠረት ይባርክሃል።” (ዘዳ. 15:4-6) ይሖዋ፣ በታማኝነት እስካገለገልከው ድረስ እንደሚባርክህ ሙሉ በሙሉ ትተማመናለህ? ይህን ለማድረግ በቂ ምክንያት አለህ።
ይሖዋ ወሮታቸውን ከፍሏቸዋል
10, 11. ይሖዋ ዮሴፍን የባረከው እንዴት ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለእኛ ጥቅም ነው። አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደባረካቸው የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን ይዟል። (ሮም 15:4) የዮሴፍ ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ወንድሞቹ በባርነት ወደ ግብፅ የሸጡት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ የጌታው ሚስት የሐሰት ውንጀላ ስለሰነዘረችበት ወኅኒ ወረደ። ይህ መሆኑ ታዲያ ከአምላክ እንዲርቅ አድርጎት ይሆን? በፍጹም! “ይሖዋ ከዮሴፍ አልተለየም፤ እንደወትሮው ሁሉ ለእሱ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላለም።” እንዲሁም ‘ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ያሳካለት ነበር።’ (ዘፍ. 39:21-23) ዮሴፍም በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ አምላኩን በታማኝነት ይጠባበቅ ነበር።
11 ዓመታት ካለፉ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን ከእስር ቤት ያስወጣው ሲሆን ባሪያ ለነበረው ለዚህ ሰው በግብፅ ምድር ላይ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን ሰጠው። (ዘፍ. 41:1, 37-43) ዮሴፍ፣ ሚስቱ ሁለት ወንዶች ልጆች ስትወልድለት “‘አምላክ የደረሰብኝን ችግር ሁሉና የአባቴን ቤት በሙሉ እንድረሳ አደረገኝ’ በማለት ለበኩር ልጁ ምናሴ የሚል ስም አወጣለት። ሁለተኛውን ልጁን ደግሞ ‘መከራዬን ባየሁበት ምድር አምላክ ፍሬያማ አደረገኝ’ በማለት ኤፍሬም የሚል ስም አወጣለት።” (ዘፍ. 41:51, 52) ዮሴፍ ለአምላክ ታማኝ በመሆኑ ይሖዋ ወሮታውን ከፍሎታል፤ በዚህም ምክንያት ዮሴፍ የእስራኤላውያንንም ሆነ የግብፃውያንን ሕይወት ማትረፍ ችሏል። ዮሴፍ ወሮታውን የከፈለውና የባረከው ይሖዋ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።—ዘፍ. 45:5-9
12. ኢየሱስ ፈተና ሲያጋጥመው ታማኝ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?
12 በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ የእምነት ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ምንጊዜም ለአምላክ ታዛዥ ነበር፤ በመሆኑም ወሮታውን አግኝቷል። ፈተናዎቹን ለመቋቋም የረዳው ምን ነበር? የአምላክ ቃል “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል፣ የሚደርስበትን ውርደት ከምንም ሳይቆጥር በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል” ይላል። (ዕብ. 12:2) ኢየሱስ የአምላክን ስም ማስቀደስ መቻሉ እንዳስደሰተው ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ የአባቱን ሞገስ እንዲሁም በርካታ አስደናቂ መብቶች በማግኘት ተባርኳል። መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል” ይላል። በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ደግሞ “አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን።—ፊልጵ. 2:9
ይሖዋ የምናከናውነውን ሥራ አይረሳም
13, 14. ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናከናውነውን ነገር እንዴት ይመለከተዋል?
13 ይሖዋ፣ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ማንኛውንም ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በራስ ያለመተማመን ስሜት ሊያድርብን እንደሚችል ያውቃል። ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ቢያስጨንቁን አሊያም የጤና ወይም የስሜት መቃወስ ቅዱስ አገልግሎታችንን ቢገድቡብን ይሖዋ ይራራልናል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ለእሱ ታማኝ ለመሆን ሲሉ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ዕብራውያን 6:10, 11ን አንብብ።
14 በተጨማሪም ‘ጸሎት ሰሚ የሆነው’ አምላክ የሚያሳስቡንን ነገሮች ስንነግረው እንደሚሰማን በመተማመን ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። (መዝ. 65:2) “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሚያስፈልገንን ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ አትረፍርፎ ይሰጠናል፤ ይህን የሚያደርገውም በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 1:3 ግርጌ) ለሌሎች ርኅራኄ ስናሳይ የይሖዋን ልብ እናስደስታለን። “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።” (ምሳሌ 19:17፤ ማቴ. 6:3, 4) በመሆኑም ራሳችንን ሳንቆጥብ በችግር ላይ ያሉትን የምንረዳ ከሆነ ይሖዋ ያደረግነውን መልካም ነገር ለእሱ እንደማበደር ይቆጥረዋል። ለደግነታችን ወሮታውን እንደሚከፍለን ቃል ገብቷል።
አሁንና ወደፊት የምናገኘው ሽልማት
15. በጉጉት የምትጠባበቀው ሽልማት ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
15 በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ብሎ የተናገረው የጳውሎስ ዓይነት ተስፋ አላቸው፦ “የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤ ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ . . . ይህን እንደ ሽልማት አድርጎ ይሰጠኛል።” (2 ጢሞ. 4:7, 8) የአንተ ተስፋ ከዚህ የተለየ ከሆነ ሽልማትህ ያነሰ ነው ማለት አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር በጉጉት ይጠባበቃሉ። በዚያም “በብዙ [ሰላም] እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—ዮሐ. 10:16፤ መዝ. 37:11
16. በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ ምን ማጽናኛ እናገኛለን?
16 አንዳንድ ጊዜ፣ ያን ያህል የሚጠቅም ነገር እያከናወንን እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ የምናደርገው ጥረት ይሖዋን የሚያስደስት መሆኑን የምንጠራጠርበት ጊዜ ይኖራል። እንዲያውም ሽልማት የሚገባን እንዳልሆንን ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ እንደሆነና ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ’ አንዘንጋ። (1 ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ።) አንድ ሰው ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርበው በእምነትና በፍቅር ተነሳስቶ እስከሆነ ድረስ ግለሰቡ መሥዋዕቱ ትንሽ እንደሆነ ቢሰማውም እንኳ ይሖዋ ወሮታውን ይከፍለዋል።—ማር. 12:41-44
17. በአሁኑ ጊዜ ያገኘናቸው አንዳንድ ሽልማቶች የትኞቹ ናቸው?
17 የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበበትና በጨለማ በተዋጠው በመጨረሻው ቀን ውስጥም እንኳ ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ ነው። እውነተኛ አገልጋዮቹ በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ሐሴት እንዲያደርጉና የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ እያደረገ ነው። (ኢሳ. 54:13) ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞችና እህቶች በተሞላ ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ እንድንታቀፍ በማድረግ ወሮታ ከፍሎናል። (ማር. 10:29, 30) ከዚህም ሌላ አምላክን ከልባቸው የሚፈልጉ ሁሉ የአእምሮ ሰላም፣ እርካታና ደስታ ስላላቸው ወደር የሌለው ሽልማት እያገኙ ነው።—ፊልጵ. 4:4-7
18, 19. የይሖዋ አገልጋዮች ከእሱ ስለሚያገኙት ወሮታ ምን ይሰማቸዋል?
18 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ይሖዋ አስደናቂ ሽልማት እንደሚሰጥ መመሥከር ይችላሉ። ለምሳሌ በጀርመን የምትኖረው ቢያንካ እንዲህ ብላለች፦ “በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ ስለሚሰጠኝ እርዳታ እንዲሁም በየዕለቱ ከጎኔ ስለሚሆን ይሖዋን እጅግ ላመሰግነው እወዳለሁ። ዓለም ምስቅልቅሉ የወጣ ከመሆኑም ሌላ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለውም። ይሁንና ከይሖዋ ጋር አብሬ ስሠራ በእሱ እቅፍ ውስጥ እንዳለሁ ስለሚሰማኝ ስጋት አያድርብኝም። እሱን ለማገልገል ብዬ መሥዋዕትነት ስከፍል ወሮታውን መቶ እጥፍ አድርጎ ይመልስልኛል።”
19 ፖላ የተባሉትን በካናዳ የሚኖሩ እህትም እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እኚህ የ70 ዓመት አረጋዊት ስፓይና ቢፊዳ የተባለ የአከርካሪ በሽታ ያለባቸው ሲሆን ሕመሙ እንቅስቃሴያቸውን በጣም ይገድበዋል። እህት ፖላ እንዲህ ብለዋል፦ “እንቅስቃሴዬ የተገደበ መሆኑ አገልግሎቴን አይገድበውም። በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ በስልክና መደበኛ ባልሆነ መንገድ እመሠክራለሁ። ጥቅሶችና ከጽሑፎቻችን የተወሰዱ ሐሳቦችን በማስታወሻ ላይ እጽፋለሁ፤ የጻፍኩትን ሐሳብ ባነበብኩ ቁጥር እበረታታለሁ። ማስታወሻዬን ‘የብርታቴ ምንጭ’ ብዬ እጠራዋለሁ። ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ካተኮርን፣ ለጊዜው ተስፋ ብንቆርጥም በዚህ ስሜት አንዋጥም። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ነው።” አንተ ያለህበት ሁኔታ ከቢያንካም ሆነ ከፖላ የተለየ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ ለአንተና ለምትቀርባቸው ሰዎች ወሮታ የከፈለባቸው አንዳንድ መንገዶች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሽልማት የሰጠህና ወደፊት ደግሞ ወሮታ የሚከፍልህ እንዴት እንደሆነ ማሰላሰልህ እንደሚያስደስትህ የታወቀ ነው!
20. ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገላችንን ከቀጠልን ምን እንደምናገኝ መጠበቅ እንችላለን?
20 ለይሖዋ የልብህን አውጥተህ በግልጽ የምታቀርበው ጸሎት “ትልቅ ወሮታ” እንደሚያስገኝ ፈጽሞ አትዘንጋ። ‘የአምላክን ፈቃድ ከፈጸምክ የተስፋው ቃል ሲፈጸም እንደምታይ’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 10:35, 36) እንግዲያው እምነታችንን ማጠናከራችንን እና ለይሖዋ እንደምናደርገው በማሰብ በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችንን እንቀጥል። ሽልማታችንን የምናገኘው ከይሖዋ ዘንድ እንደሆነ በማሰብ ይህን ማድረግ እንችላለን።—ቆላስይስ 3:23, 24ን አንብብ።