በጸጋው ነፃ ወጥታችኋል
“በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም።”—ሮም 6:14
1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች ሮም 5:12ን በተደጋጋሚ የሚጠቀሙበት ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች በደንብ የሚያውቋቸውንና ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለመዘርዘር አሰብክ እንበል። መጀመሪያ ከምትጽፋቸው ጥቅሶች አንዱ ሮም 5:12 ይሆን? “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” የሚለውን ጥቅስ ምን ያህል ጊዜ እንደጠቀስከው እስቲ ቆም ብለህ አስብ።
2 ይህ ጥቅስ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህ መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 3, 5 እና 6ን ለልጆችህ ወይም ለሌሎች ስታስጠና ሮም 5:12ን ማንበብህ አይቀርም፤ እነዚህ ምዕራፎች አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ፣ ስለ ቤዛውና የሞቱ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ የሚያብራሩ ናቸው። ይሁንና ሮም 5:12 በይሖዋ ዘንድ ካለህ አቋም፣ ከአኗኗርህ እንዲሁም ከወደፊት ተስፋህ ጋር እንደሚያያዝስ አስበህ ታውቃለህ?
3. ከኃጢአት ጋር በተያያዘ ልንዘነጋው የማይገባው ሐቅ የትኛው ነው?
3 ሁላችንም ኃጢአተኞች መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም። በየዕለቱ ስህተቶች እንሠራለን። ሆኖም አምላክ፣ አፈር መሆናችንን እንደሚያውቅና ምሕረት ሊያሳየን እንደሚፈልግ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 103:13, 14) ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ “ኃጢአታችንን ይቅር በለን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ሉቃስ 11:2-4) በመሆኑም አምላክ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ፣ ስለሠራናቸው ስህተቶች እያሰብን የምንብሰለሰልበት ምንም ምክንያት የለም። ያም ቢሆን አምላክ፣ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ስላደረገው ዝግጅት ማሰባችን ይጠቅመናል።
በጸጋ የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል
4, 5. (ሀ) ሮም 5:12ን ለመረዳት የሚያግዘን ሐሳብ የት እናገኛለን? (ለ) ሮም 3:24 ላይ የሚገኘው “ጸጋ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም 5:12 ዙሪያ በተለይ ደግሞ በምዕራፍ 6 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ምዕራፎች ይሖዋ፣ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ስላደረገው ዝግጅት ያስገነዝቡናል። በምዕራፍ 3 ላይ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ . . . ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (ሮም 3:23, 24) ጳውሎስ “ጸጋ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “ሰጪው ብድራት እንዲመለስለት ሳያስብ በነፃ የሚያደርገውን ውለታ” ያመለክታል። ተቀባዩ ‘ይገባኛል’ ወይም ‘የደከምኩበት ነው’ ብሎ የሚጠይቀው ነገር አይደለም።
5 ጆን ፓርክኸርስት የተባሉ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[ይህ የግሪክኛ ቃል] ከአምላክ ወይም ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ሲሠራበት፣ የሰውን ዘር ለመዋጀትና ለማዳን ሲሉ የሰጡትን ይገባናል የማይባልና ነፃ የሆነ ስጦታ ወይም ያሳዩትን ደግነት ያመለክታል።” በመሆኑም ይህ ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ጸጋ” (ይኸውም ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ) ተብሎ መተርጎሙ ተስማሚ ነው። ይሁንና አምላክ ይህን ጸጋ ያሳየን እንዴት ነው? ጸጋው ከተስፋችንና ከአምላክ ጋር ከመሠረትነው ዝምድና ጋር ምን ግንኙነት አለው? መልሱን እስቲ እንመልከት።
6. የሰው ልጆች ከአምላክ ጸጋ ምን ጥቅም ያገኛሉ?
6 ኃጢአትና ሞት “ወደ ዓለም” እንዲገባ ምክንያት የሆነው “አንድ ሰው” ሲሆን እሱም አዳም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው በደል የተነሳ ሞት” እንደነገሠ የሚናገረው ለዚህ ነው። ጳውሎስ “የአምላክን የተትረፈረፈ ጸጋ” ማግኘት የሚቻለው “በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት” እንደሆነ ተናግሯል። (ሮም 5:12, 15, 17) ይህ ጸጋ የሰውን ዘር በሙሉ ጠቅሟል። ጳውሎስ “በአንዱ ሰው [በኢየሱስ] መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ብሏል። በመሆኑም የአምላክ ጸጋ “በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት” ያስገኛል።—ሮም 5:19, 21
7. የቤዛው ዝግጅት የአምላክ ደግነት መግለጫና ይገባናል የማንለው ስጦታ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ፣ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ቤዛውን እንዲከፍል የማድረግ ግዴታ አልነበረበትም። ይሖዋና ኢየሱስ፣ ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች በቤዛው አማካኝነት ይቅርታ ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት ያደረጉት የሰው ልጆች ይህን ለማግኘት የሚበቁ ወይም የሚገባቸው ስለሆኑ አይደለም። በመሆኑም የኃጢአት ይቅርታ እና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘታችን ይገባናል የማንለው ደግነት ወይም ጸጋ ነው። እንግዲያው የአምላክን የደግነት ስጦታ ይኸውም ጸጋውን ከፍ አድርገን ልንመለከተውና ይህንንም በአኗኗራችን ልናሳይ ይገባል።
ለአምላክ ጸጋ አድናቆት ይኑራችሁ
8. አንዳንዶች ኃጢአት መፈጸምን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው?
8 ከአዳም ኃጢአትን ስለወረስን ስህተትና መጥፎ ነገር ብሎም ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ በውስጣችን አለ። ያም ቢሆን የይሖዋን ጸጋ፣ ኃጢአት ለመሥራት ሰበብ ልናደርገው አይገባም፤ ‘አምላክ እንደ ኃጢአት የሚቆጥረውን መጥፎ ድርጊት ብፈጽምም እንኳ መጨነቅ አያስፈልገኝም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ይቅር ይለኛል’ ብለን ማሰብ ተገቢ አይሆንም። የሚያሳዝነው፣ ሐዋርያት በሕይወት እያሉም እንኳ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው። (ይሁዳ 4ን አንብብ።) እኛ እንዲህ ብለን አንናገር ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያለው የተሳሳተ አመለካከት በውስጣችን ሊኖር አሊያም እያቆጠቆጠ ሊሆን ይችላል።
9, 10. ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የወጡት እንዴት ነው?
9 ‘አምላክ እኮ ያለሁበትን ሁኔታ ይረዳልኛል። መጥፎ ድርጊት ብፈጽምም ይቅር ይለኛል’ የሚል ዓይነት አመለካከትን ማስወገድ እንዳለብን ጳውሎስ አበክሮ ገልጿል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስ እንደገለጸው ክርስቲያኖች ‘ለኃጢአት ሞተዋል።’ (ሮም 6:1, 2ን አንብብ።) ይሁንና ክርስቲያኖች በምድር ላይ በሕይወት እየኖሩም እንኳ ‘ለኃጢአት ሞተዋል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
10 ጳውሎስና በእሱ ዘመን የኖሩ ሌሎች ሰዎች ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አምላክ ዝግጅት አድርጓል። በመሆኑም ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሏቸዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ቀብቷቸዋል እንዲሁም መንፈሳዊ ልጆቹ እንዲሆኑ ጠርቷቸዋል። በዚህም ምክንያት በሰማይ የመኖር ተስፋ አግኝተዋል። በታማኝነት ከጸኑ ደግሞ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመኖርና ከእሱ ጋር የመግዛት መብት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት ያሉ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ ‘ለኃጢአት እንደሞቱ’ ገልጿል። ጳውሎስ፣ ሰው ሆኖ የሞተውንና ከሞት ከተነሳ በኋላ የማይሞት ሕይወት ተላብሶ በሰማይ የሚኖረውን የኢየሱስን ምሳሌ ጠቅሷል። ሞት በኢየሱስ ላይ ጌታ መሆኑ አብቅቷል። ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች “ለኃጢአት [እንደሞቱ] ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ [እንደሚኖሩ]” አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። (ሮም 6:9, 11) ቀድሞ የነበራቸው ሕይወት ተለውጧል። ከዚህ በኋላ የኃጢአት ምኞታቸው እንዲመራቸው ወይም እንዲቆጣጠራቸው አይፈቅዱም። ለቀድሞ ሕይወታቸው ሞተዋል።
11. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ‘ለኃጢአት ሞተዋል’ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?
11 በዛሬው ጊዜ ስለምንኖር ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይቻላል? ክርስቲያን ከመሆናችን በፊት፣ ድርጊታችን በአምላክ ፊት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ ባለማወቃችን ብዙ ጊዜ ኃጢአት እንሠራ ነበር። “ለርኩሰትና ለክፋት ባሪያዎች” የሆንን ያህል ነበር። በሌላ አባባል “የኃጢአት ባሪያዎች” ነበርን ማለት ይቻላል። (ሮም 6:19, 20) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስናውቅ ግን በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ አደረግን፤ ከዚያም ራሳችንን ለአምላክ ወስነን ተጠመቅን። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለአምላክ ትምህርቶችና መሥፈርቶች ‘ከልብ የመታዘዝ’ ፍላጎት አለን። ጳውሎስ እንዳለው ‘ከኃጢአት ነፃ ወጥተን የጽድቅ ባሪያዎች ሆነናል።’ (ሮም 6:17, 18) በመሆኑም እኛም ‘ለኃጢአት ሞተናል’ ሊባል ይችላል።
12. እያንዳንዳችን ምን ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል?
12 ጳውሎስ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ አንጻር ራስህን ገምግም፦ “ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።” (ሮም 6:12) ፍጽምና የጎደለው ሰውነታችን እንድናደርግ የሚገፋፋንን ነገሮች በሙሉ የምናደርግ ከሆነ ‘ኃጢአት በሰውነታችን ላይ መንገሡን እንዲቀጥል እየፈቀድን ነው’ ሊባል ይችላል። ኃጢአት እንዲነግሥብን ‘መፍቀድ’ ወይም አለመፍቀድ በእኛ ላይ የተመካ ነው፤ በመሆኑም ሊያሳስበን የሚገባው ጥያቄ ‘የልባችን ፍላጎት ምንድን ነው?’ የሚለው ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ፍጽምና የጎደለው ሰውነቴ ወይም አእምሮዬ ወደተሳሳተ አቅጣጫ እንዲመራኝ በመፍቀድ መጥፎ ድርጊት የምፈጽምበት ጊዜ አለ? ወይስ ለኃጢአት ሞቻለሁ? በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ እየኖርኩ ነው?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ፣ አምላክ እኛን ይቅር በማለት ላሳየን ጸጋ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንን የሚያሳይ ነው።
በትግሉ ልታሸንፍ ትችላለህ
13. የኃጢአት ድርጊቶችን ማስወገድ እንደምንችል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
13 የይሖዋ ሕዝቦች ስለ አምላክ ከማወቃቸው፣ ለእሱ ፍቅር ከማዳበራቸውና እሱን ማገልገል ከመጀመራቸው በፊት ‘ያፈሯቸው የነበሩትን ፍሬዎች’ አስወግደዋል። ቀድሞ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ‘አሁን ያፍሩባቸዋል’፤ ደግሞም “የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነው።” (ሮም 6:21) ይሖዋን ሲያውቁ ግን አኗኗራቸውን ቀየሩ። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከጻፈላቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ነበራቸው። አንዳንዶቹ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ሌቦች፣ ሰካራሞች እና እንደነዚህ ያሉትን ኃጢአቶች የሚፈጽሙ ሰዎች ነበሩ። ይሁንና ‘ታጥበው ነጽተዋል’ እንዲሁም ‘ተቀድሰዋል።’ (1 ቆሮ. 6:9-11) የሮም ጉባኤ አባላት የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “ሰውነታችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ሰውነታችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለአምላክ አቅርቡ።” (ሮም 6:13) ጳውሎስ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች ምንጊዜም መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ከጠበቁ ከአምላክ ጸጋ ጥቅም ማግኘታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበር።
14, 15. ‘ከልብ መታዘዝን’ በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
14 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የአንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የቀድሞ ሕይወት በቆሮንቶስ ከነበሩት ክርስቲያኖች ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እነዚህ ክርስቲያኖችም ተለውጠዋል። ቀድሞ ይከተሉት የነበረውን የኃጢአት ጎዳና የተዉ ከመሆኑም ሌላ ‘ታጥበው ነጽተዋል።’ አንተስ ከዚህ በፊት የነበረህ ሕይወት ምንም ይሁን ምን፣ በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ዘንድ ያለህ አቋም ምን ይመስላል? የአምላክን ጸጋ እና ይቅርታውን ካገኘህ በኋላ ‘ሰውነትህን ለኃጢአት ማቅረብህን’ ለመተው ቆርጠሃል? ‘ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገረ ሰው አድርገህ ራስህን እያቀረብክ’ ነው?
15 ማናችንም ብንሆን ይህን ማድረግ ከፈለግን በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይፈጽሟቸው የነበሩ ከባድ ኃጢአቶችን ከመፈጸም መራቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። የአምላክን ጸጋ እንደተቀበልንና ‘ኃጢአት በእኛ ላይ ጌታ እንዳልሆነ’ መናገር የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ከከባድ ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች እንደ ቀላል ከሚመለከቷቸው ኃጢአቶችም ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ አምላክን ‘ከልብ ለመታዘዝ’ ቆርጠናል?—ሮም 6:14, 17
16. የክርስትና ሕይወት ከባድ ኃጢአቶችን ከማስወገድ ያለፈ ነገርን ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ከባድ ኃጢአቶች እየፈጸመ እንዳልነበረ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ያም ቢሆን ኃጢአተኛ መሆኑን ገልጿል። ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ። ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው።” (ሮም 7:14, 15) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ እንደ ኃጢአት አድርጎ የሚቆጥራቸው ሌሎች ነገሮች ነበሩ፤ እንዲህ ያሉትን ኃጢአቶች ለማስወገድ እየታገለ ነበር። (ሮም 7:21-23ን አንብብ።) እኛም ‘ከልብ ለመታዘዝ’ ጥረት በማድረግ የጳውሎስን ምሳሌ እንከተል።
17. ሐቀኛ ለመሆን የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?
17 እስቲ ስለ ሐቀኝነት እናንሳ። ማንኛውም ክርስቲያን ሐቀኛ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። (ምሳሌ 14:5ን እና ኤፌሶን 4:25ን አንብብ።) “የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን ነው። ሐናንያ እና ሚስቱም ሕይወታቸውን ያጡት ስለዋሹ ነው። እነዚህን ግለሰቦች መምሰል ስለማንፈልግ ከውሸት እንርቃለን። (ዮሐ. 8:44፤ ሥራ 5:1-11) ይሁንና ሐቀኝነት ሲባል ከውሸት መራቅ ማለት ብቻ አይደለም። ለአምላክ ጸጋ ከልባችን አመስጋኞች ከሆንን በሌሎች መንገዶችም ሐቀኞች ለመሆን እንጥራለን።
18, 19. ሐቀኛ መሆን ሲባል ከውሸት ከመራቅ ያለፈ ነገርን ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው?
18 መዋሸት ሲባል እውነት ያልሆነ ነገር መናገር ማለት ነው። ይሁንና ይሖዋ፣ ከሕዝቡ የሚጠብቀው ከውሸት እንዲርቁ ብቻ አይደለም። የጥንቶቹን እስራኤላውያን “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” በማለት አሳስቧቸዋል። ከዚያም ቅድስና ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ሲገልጽ “አትስረቁ፤ አታታሉ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አትፈጽሙ” ብሏቸዋል። (ዘሌ. 19:2, 11) የሚያሳዝነው ግን ውሸት ላለመናገር የሚጠነቀቅ ሰውም እንኳ ሌሎችን ሊያታልል ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ሊፈጽም ይችላል።
19 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በነጋታው “የሐኪም” ቀጠሮ ስላለው ሥራ እንደማይገባ ወይም በጊዜ መውጣት እንደሚኖርበት ለአለቃው ወይም ለሥራ ባልደረቦቹ ነገራቸው እንበል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን “የሐኪም” ቀጠሮ እንዳለበት የተናገረው፣ መድኃኒት መግዛት ስለፈለገ ወይም ሐኪም ቤት ደረስ ብሎ የሚከፍለው ነገር ስላለው ሊሆን ይችላል። ከሥራ የቀረበት ዋነኛ ምክንያት፣ የእረፍት ጊዜውን ቀደም ብሎ መጀመር አሊያም ከቤተሰቡ ጋር መንሸራሸር ስለፈለገ ነው። ይህ ሰው “የሐኪም” ቀጠሮ እንዳለው መናገሩ በተወሰነ መጠን እውነት ቢሆንም ሐቀኛ ነበር ሊባል ይችላል? ወይስ ሌሎችን እያታለለ ነው? አንዳንዶች፣ ሌሎችን ሆን ብለው የሚያታልሉባቸው ተመሳሳይ ሁኔታዎች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ይህን የሚያደርጉት ከቅጣት ለማምለጥ አሊያም የፈለጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ሊሆን ይችላል። እንዲህ የሚያደርግ ሰው ውሸት ባይናገርም እንኳ “አታታሉ” የሚለውን የአምላክ መመሪያ ተከትሏል ሊባል ይችላል? “የአካል ክፍሎቻችሁን ቅዱስ ሥራ ለመሥራት የጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ” የሚለውን በሮም 6:19 ላይ የሚገኘውን ጥቅስም እናስታውስ።
20, 21. የአምላክ ጸጋ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
20 ዋናው ነጥብ ይህ ነው፦ ለአምላክ ጸጋ ያለን አድናቆት ምንዝርንና ስካርን ወይም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይፈጽሟቸው የነበሩ ሌሎች ኃጢአቶችን ከማስወገድ ያለፈ ነገር እንድናደርግ ይገፋፋናል። ለአምላክ ጸጋ አድናቆት ካለን ከፆታ ብልግና ብቻ ሳይሆን ወራዳ ከሆኑ መዝናኛዎች በሙሉ እንርቃለን። የአካል ክፍሎቻችንን የጽድቅ ባሪያዎች አድርገን ለማቅረብ እንድንችል፣ ከስካር በመራቅ ብቻ ከመወሰን ይልቅ ሞቅ እስኪለን ድረስ ከመጠጣትም እንቆጠባለን። እንዲህ ያሉትን መጥፎ ድርጊቶች ማስወገድ ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም በትግሉ ማሸነፍ እንችላለን።
21 ግባችን ከከባድ ኃጢአቶችም ሆነ ቀለል ተደርገው ከሚታዩ መጥፎ ድርጊቶች መራቅ ነው። እርግጥ ከእነዚህ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ መራቅ አንችልም። ያም ቢሆን እንደ ጳውሎስ ይህን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። ጳውሎስ ወንድሞቹን “ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሮም 6:12፤ 7:18-20) ከማንኛውም ዓይነት ኃጢአት ለመራቅ ስንታገል በክርስቶስ በኩል ለተገለጠው የአምላክ ጸጋ ልባዊ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።
22. ለአምላክ ጸጋ አድናቆት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች ምን ሽልማት ያገኛሉ?
22 አምላክ በጸጋው ኃጢአታችንን ይቅር ብሎናል፤ ወደፊትም እንዲህ ያደርግልናል። ለዚህ ዝግጅት ያለን አድናቆት፣ ሌሎች እንደ ቀላል ኃጢአት የሚመለከቷቸውን ነገሮች ለማስወገድ ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይገባል። ጳውሎስ ይህን ካደረግን የምናገኘውን ሽልማት እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “አሁን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ የአምላክ ባሪያዎች ስለሆናችሁ በቅድስና ጎዳና ፍሬ እያፈራችሁ ነው፤ የዚህም መጨረሻ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:22