መንፈሳዊ ሰው በመሆን እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!
“በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ገላ. 5:16
1, 2. አንድ ወንድም ከመንፈሳዊነቱ ጋር በተያያዘ ምን ተገነዘበ? ከዚያስ ምን እርምጃ ወሰደ?
ሮበርት የተጠመቀው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ነበር፤ ሆኖም እውነትን በቁም ነገር አልያዘውም። እንዲህ ብሏል፦ “ምንም መጥፎ ነገር ባልሠራም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው በዘልማድ ነበር። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የምገኝ ከመሆኑም ሌላ በዓመት ውስጥ ለተወሰኑ ወራት ረዳት አቅኚ ሆኜ ስለማገለግል ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያለኝ እመስል ነበር። ሆኖም የሚጎድለኝ ነገር ነበር።”
2 ሮበርት የጎደለው ነገር ምን እንደሆነ የተገነዘበው ካገባ በኋላ ነው። ከባለቤቱ ጋር በትርፍ ጊዜያቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ይጠያየቁ ነበር። ባለቤቱ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ስላላት ጥያቄዎቹን ለመመለስ አልተቸገረችም፤ ሮበርት ግን በተደጋጋሚ የጥያቄዎቹን መልስ አለማወቁ ያሳፍረው ጀመር። እንዲህ ብሏል፦ “ምንም ነገር እንደማላውቅ ተሰማኝ። ‘የቤተሰብ ራስ እንደመሆኔ መጠን ባለቤቴን በመንፈሳዊ ነገሮች መምራት እንድችል አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ’ ብዬ አሰብኩ።” ከዚያም ሮበርት መንፈሳዊ አቋሙን ለማስተካከል እርምጃ ወሰደ። እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ማጥናት ጀመርኩ፤ አዘውትሬ በትጋት ሳጠና ትምህርቶቹ ያላቸው ተያያዥነት ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በደንብ ገባኝ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሠረትኩ።”
3. (ሀ) ሮበርት ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ሮበርት ካጋጠመው ነገር ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። መጠነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይኖረን፣ አዘውትረን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንገኝ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት እንካፈል ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች ብቻ መንፈሳዊ ሰው መሆናችንን አያሳዩም። በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ስናደርግ ቆይተን ይሆናል፤ ይሁንና ራሳችንን ስንገመግም በመንፈሳዊነታችን ረገድ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ልንገነዘብ እንችላለን። (ፊልጵ. 3:16) እድገት ማድረጋችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ጥያቄዎችን እንመረምራለን፦ (1) መንፈሳዊነታችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መገምገም የምንችለው እንዴት ነው? (2) መንፈሳዊ ሰው ለመሆንና በዚህ ረገድ እድገት ማድረጋችንን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል? (3) በመንፈሳዊ ጠንካራ መሆናችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
ራሳችንን መገምገም
4. በኤፌሶን 4:23, 24 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?
4 የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን ስንል መላ ሕይወታችንን የሚነካ ትልቅ ለውጥ አድርገናል። ከተጠመቅን በኋላም ቢሆን ለውጥ ማድረጋችንን አላቆምንም። መጽሐፍ ቅዱስ “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌ. 4:23, 24) ማናችንም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ለውጥ ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል። ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ የኖሩ ክርስቲያኖችም መንፈሳዊነታቸው ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።—ፊልጵ. 3:12, 13
5. ራሳችንን ለመገምገም የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?
5 መንፈሳዊነታችንን ማሳደግና ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ይዘን መቀጠል እንድንችል ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። ወጣትም ሆንን አዋቂ እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘መንፈሳዊ አስተሳሰብ በማዳበር ረገድ ማሻሻያ እያደረግኩ እንደሆነ ይሰማኛል? ክርስቶስን ይበልጥ እየመሰልኩ ነው? ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያለኝ አመለካከት እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ ስገኝ የማሳየው ምግባር ስለ መንፈሳዊ አቋሜ ምን ይናገራል? ንግግሬ በሕይወቴ ውስጥ ለማግኘት ስለምመኘው ነገር ምን ያሳያል? የጥናት ልማዴ፣ አለባበሴና አጋጌጤ እንዲሁም ሌሎች ሲመክሩኝ የምሰጠው ምላሽ ስለ እኔ ምን ይጠቁማል? ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ ስፈተን ምን እርምጃ እወስዳለሁ? መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች አልፌ ጎልማሳ ክርስቲያን ወደ መሆን ደረጃ ደርሻለሁ?’ (ኤፌ. 4:13) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ በመንፈሳዊ ምን ያህል እድገት እንዳደረግን ለመገምገም ያስችለናል።
6. መንፈሳዊነታችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ለመገምገም የሚረዳን ሌላው ነገር ምንድን ነው?
6 መንፈሳዊነታችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ለመገምገም የሌሎች እርዳታም ሊያስፈልገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ዓለማዊ ሰው፣ አምላክን የሚያሳዝን ነገር እየፈጸመ መሆኑን ማስተዋል አይችልም። በሌላ በኩል ግን መንፈሳዊ የሆነ ሰው፣ የአምላክን አስተሳሰብ የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር ሥጋዊ አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን ይገነዘባል። (1 ቆሮ. 2:14-16፤ 3:1-3) የክርስቶስ አስተሳሰብ ያላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ አንድ ሰው ሥጋዊ አስተሳሰብ ማዳበር እንደጀመረ የሚያሳዩ ምልክቶችን ማስተዋል ይችላሉ። ታዲያ በዚህ ረገድ ምክር ቢሰጡን ምክሩን ተቀብለን ተግባራዊ እናደርጋለን? እንዲህ ማድረጋችን መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር እንደምንፈልግ ያሳያል።—መክ. 7:5, 9
መንፈሳዊነታችንን ማጠናከር
7. መንፈሳዊ አስተሳሰብ ለመያዝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብቻ በቂ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
7 መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ለመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል። በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰለሞን ስለ ይሖዋ መንገዶች ጥልቅ እውቀት ነበረው። እንዲያውም እሱ የተናገራቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካትተዋል። ውሎ አድሮ ግን ሰለሞን መንፈሳዊነቱን ያጣ ሲሆን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት አጓድሏል። (1 ነገ. 4:29, 30፤ 11:4-6) ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ባለፈ ሌላ ምን የሚያስፈልገን ነገር አለ? መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል። (ቆላ. 2:6, 7) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
8, 9. (ሀ) ጽኑ የሆነ መንፈሳዊ አቋም ለማዳበር ምን ይረዳናል? (ለ) የምናጠናበትና የምናሰላስልበት ዓላማ ምን መሆን አለበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
8 ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች “ወደ ጉልምስና ለመድረስ [እንዲጣጣሩ]” አበረታቷቸዋል። (ዕብ. 6:1) በዛሬው ጊዜስ የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ ከሚረዱን ጠቃሚ እርምጃዎች አንዱ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ነው። ይህን መጽሐፍ አጥንተን መጨረሳችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ እንዴት በሥራ ላይ ልናውላቸው እንደምንችል ለማስተዋል ይረዳናል። ይህን መጽሐፍ አጥንተን ከሆነ ደግሞ በእምነት ጸንተን ለመኖር የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን ማጥናት እንችላለን። (ቆላ. 1:23) ከዚህም ሌላ ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ለማስተዋል እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለይ ያስፈልገናል።
9 የምናጠናበትና የምናሰላስልበት ዓላማ፣ ይሖዋን የማስደሰትና ሕጎቹን የመታዘዝ ልባዊ ፍላጎት ማዳበር መሆን እንዳለበት ልንዘነጋ አይገባም። (መዝ. 40:8፤ 119:97) በተጨማሪም መንፈሳዊ እድገታችንን ሊገቱ ከሚችሉ ነገሮች ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—ቲቶ 2:11, 12
10. ወጣቶች መንፈሳዊነታቸውን ለማጠናከር ምን ይረዳቸዋል?
10 ወጣቶች፣ ግልጽ የሆኑ መንፈሳዊ ግቦች አሏችሁ? በቤቴል የሚያገለግል አንድ ወንድም በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት የጥምቀት እጩዎችን የማነጋገር ልማድ አለው። አብዛኞቹ የጥምቀት እጩዎች ወጣቶች ናቸው። ይህ ወንድም እነዚህን ወጣቶች ምን መንፈሳዊ ግብ እንዳላቸው ይጠይቃቸዋል። ብዙዎቹ ወጣቶች የሚሰጡት መልስ ግልጽ የሆኑ መንፈሳዊ ግቦች እንዳሏቸው የሚያሳይ ነው፤ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል አሊያም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዶ የማገልገል ግብ እንዳላቸው ይናገራሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህ ወንድም፣ ላነሳው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚቸገሩ ወጣቶች ያጋጥሙታል። እነዚህ ወጣቶች ግልጽ የሆነ መንፈሳዊ ግብ ሊኖራቸው እንደሚገባ ከልባቸው አላመኑበት ይሆን? አንተም ወጣት ከሆንክ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው ወላጆቼ እንዲህ እንዳደርግ ስለሚጠብቁብኝ ብቻ ነው? ከአምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት ለመመሥረትና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት እያደረግኩ ነው?’ እርግጥ ነው፣ መንፈሳዊ ግብ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ወጣቶች ብቻ አይደሉም። የይሖዋ አገልጋዮች የሆንን ሁሉ መንፈሳዊ ግብ ማውጣታችን መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል።—መክ. 12:1, 13
11. (ሀ) መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የማንን ምሳሌ መከተል እንችላለን?
11 ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገን በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ካስተዋልን በኋላ፣ ዛሬ ነገ ሳንል ለውጥ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። መንፈሳዊ ሰው መሆን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። እንዲያውም የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። (ሮም 8:6-8) በመንፈሳዊ መጎልመስ አለብን ሲባል ግን ፍጹም መሆን አለብን ማለት አይደለም። የይሖዋ መንፈስ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። ያም ቢሆን እኛም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የበላይ አካል አባል የነበረው ወንድም ጆን ባር ሉቃስ 13:24ን ሲያብራራ “ብዙዎች በጠባቡ በር መግባት የሚያቅታቸው [መንፈሳዊ ሰው ለመሆን] ብርቱ ተጋድሎ ስለማያደርጉ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። ከያዕቆብ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ያዕቆብ በረከቱን እስኪያገኝ ድረስ ከመልአኩ ጋር መታገሉን አላቆመም። (ዘፍ. 32:26-28) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች ሊሆን ቢችልም ልክ እንደ ልብ ወለድ መጻሕፍት አዝናኝ እንዲሆንልን መጠበቅ የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ በውስጡ ያሉትን ጠቃሚ መንፈሳዊ ዕንቁዎች ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
12, 13. (ሀ) “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) ከሐዋርያው ጴጥሮስ ምሳሌ እንዲሁም ከሰጠው ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሐ) መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር ምን ማድረግ እንችላለን? (“መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር ልንወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
12 መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር የምንጥር ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን እርዳታ በአስተሳሰባችን ይበልጥ ክርስቶስን እየመሰልን እንድንሄድ ያደርገናል። (ሮም 15:5) ከዚህም ሌላ፣ ሥጋዊ ምኞቶችን እንድናስወግድና አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል። (ገላ. 5:16, 22, 23) ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የመስጠት ወይም በሥጋዊ ምኞቶች ላይ የማተኮር አዝማሚያ እንዳለን ብናስተውልስ? ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን ሳናቋርጥ ከለመንነው አስተሳሰባችንን ማስተካከልና ተገቢ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር እንድንችል ይረዳናል። (ሉቃስ 11:13) የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ እናስታውስ። ጴጥሮስ ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የማይጠበቁ ነገሮችን ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ማቴ. 16:22, 23፤ ሉቃስ 22:34, 54-62፤ ገላ. 2:11-14) ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጠም። ጴጥሮስ በይሖዋ እርዳታ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበር ችሏል። እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።
13 ጴጥሮስ ልናዳብራቸው የሚገቡ ባሕርያትን በዝርዝር ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:5-8ን አንብብ።) ራስን መግዛትን፣ ጽናትን፣ ወንድማዊ መዋደድንና የመሳሰሉትን ባሕርያት ለማዳበር “ልባዊ ጥረት” ማድረጋችን መንፈሳዊ አመለካከት ያለን ሰዎች በመሆን ረገድ እድገት እያደረግን ለመሄድ ያስችለናል። እንግዲያው ‘መንፈሳዊነቴን ለማጠናከር በዛሬው ዕለት የትኛውን ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረግ እችላለሁ?’ እያልን በየዕለቱ ራሳችንን እንጠይቅ።
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ
14. መንፈሳዊ አስተሳሰብ መያዛችን በዕለታዊ ሕይወታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
14 የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበራችን በንግግራችን፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት በሚኖረን ምግባር እንዲሁም በየዕለቱ በምናደርገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን እንደምንጥር የሚያሳዩ ይሆናሉ። መንፈሳዊ ሰዎች ስለሆንን፣ ከሰማዩ አባታችን ጋር ያለንን ዝምድና ምንም ነገር እንዲያበላሽብን አንፈቅድም። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ በምንፈተንበት ጊዜ ፈተናውን ለመወጣት ያስችለናል። ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለን እናስባለን፦ ‘ከጉዳዩ ጋር የሚያያዙት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? ክርስቶስ በእኔ ቦታ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ውሳኔ ያደርግ ነበር? ይሖዋን የሚያስደስተው ምን ዓይነት ውሳኔ ነው?’ ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት እንደነዚህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ የማሰብ ልማድ ሊኖረን ይገባል። እስቲ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንመለከታለን።
15, 16. የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ማዳበራችን (ሀ) በትዳር ጓደኛ ምርጫ ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ከጓደኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ሊጠቅመን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
15 የትዳር ጓደኛ ምርጫ። ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በ2 ቆሮንቶስ 6:14, 15 ላይ እናገኛለን። (ጥቅሱን አንብብ።) ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ መንፈሳዊ ሰው ከዓለማዊ ሰው ጋር ኅብረት ሊኖረው እንደማይችል በግልጽ ያሳያል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በትዳር ጓደኛ ምርጫ ረገድ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?
16 ጓደኝነት። በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ስለዚህ ጉዳይ ይናገራል። (ጥቅሱን አንብብ።) መንፈሳዊ የሆነ ሰው፣ መንፈሳዊነቱ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት አይመሠርትም። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ስለምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች እናስብ። ለምሳሌ፣ ከማኅበራዊ ድረ ገጾች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው? ወይም ደግሞ ከማታውቃቸው ሰዎች ጋር ኢንተርኔት ላይ ጌም እንድትጫወት ግብዣ ቢቀርብልህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
17-19. መንፈሳዊ አመለካከት መያዛችን (ሀ) እርባና ቢስ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ከመካፈል እንድንቆጠብ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ግቦች በማውጣት ረገድ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሐ) አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችለን እንዴት ነው?
17 መንፈሳዊ እድገት እንዳናደርግ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች። ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጠው ማሳሰቢያ በዚህ ረገድ ይጠቅመናል። (ዕብራውያን 6:1ን አንብብ።) ልንርቃቸው የሚገቡት ‘የሞቱ ሥራዎች’ ምንድን ናቸው? ለመንፈሳዊ እድገታችን አስተዋጽኦ የማያደርጉ እርባና ቢስ የሆኑ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ‘በሞቱ ሥራዎች’ ውስጥ ይካተታሉ። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን፤ ለምሳሌ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይነሱብን ይሆናል፦ ‘በዚህ እንቅስቃሴ መሳተፍ በሥጋ ሥራዎች እንድካፈል ያደርገኛል? በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛሉ በሚባሉ የንግድ ሥራዎች ላይ ብሰማራ ተገቢ ነው? የለውጥ አራማጆች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች መካፈል የሌለብኝ ለምንድን ነው?’
18 መንፈሳዊ ግቦች። ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ የተናገረው ሐሳብ ምን ዓይነት ግቦች ልናወጣ እንደሚገባ ግልጽ መመሪያ ይሰጠናል። (ማቴ. 6:33) መንፈሳዊ ሰው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጋል። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሯችን መያዛችን እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳናል፦ ‘ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ግብ ባወጣ ይሻላል? የቀረበልኝን የሥራ አጋጣሚ ልቀበል?’
19 አለመግባባት። ጳውሎስ በሮም ለነበረው ጉባኤ የሰጠው ምክር አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚረዳን እንዴት ነው? (ሮም 12:18) የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት እናደርጋለን። ታዲያ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ምን እርምጃ እንወስዳለን? የሌሎችን አመለካከት ለመቀበል እንቸገራለን? ወይስ ‘ሰላም ፈጣሪዎች’ ነን?—ያዕ. 3:18
20. መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠል የምትፈልገው ለምንድን ነው?
20 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰላችን፣ መንፈሳዊ ሰው መሆናችንን የሚያሳዩ ውሳኔዎች ለማድረግ እንዴት እንደሚረዳን የሚጠቁሙ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልክተናል። መንፈሳዊ አስተሳሰብ ማዳበራችን የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳችና አርኪ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ከመሠረትኩ በኋላ የተሻልኩ ባልና አባት መሆን ችያለሁ። በሕይወቴም እርካታና ደስታ አግኝቻለሁ።” እኛም ለመንፈሳዊ እድገታችን ትኩረት ከሰጠን እንዲህ ያሉ በረከቶችን ማጣጣም እንችላለን። መንፈሳዊ ሰው ከሆንን በአሁኑ ጊዜ እርካታ ያለው ሕይወት መምራት፣ ወደፊት ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:19