ዓይኖቻችሁ የሚመለከቱት ወዴት ነው?
“በሰማያት ዙፋን ላይ የተቀመጥክ ሆይ፣ ዓይኖቼን ወደ አንተ አነሳለሁ።”—መዝ. 123:1
1, 2. ምንጊዜም ወደ ይሖዋ መመልከት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ሲሆን በምድራችን ላይ እውነተኛ ሰላም የሚሰፍንበት ብሩሕ ቀን ከመምጣቱ በፊት ሕይወት ይበልጥ እየከበደ እንደሚሄድ እናውቃለን። (2 ጢሞ. 3:1) በመሆኑም ‘እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ዓይኖቼ የሚመለከቱት ወዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣው መልስ “ወደ ይሖዋ” የሚለው ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ይህ ከሁሉ የተሻለው መልስ ነው።
2 ወደ ይሖዋ መመልከት ምን ነገሮችን ይጨምራል? እንዲሁም የሕይወት ውጣ ውረዶች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ዓይናችን በእሱ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አንድ መዝሙራዊ፣ እርዳታ ለማግኘት ዓይናችንን አንስተን ወደ ይሖዋ የመመልከትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝሙር 123:1-4ን አንብብ።) እኛ ወደ ይሖዋ የምንመለከትበትን ሁኔታ አንድ አገልጋይ ወደ ጌታው ከሚመለከትበት ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ አገልጋይ ወደ ጌታው የሚመለከተው ምግብ እንዲሰጠውና ጥበቃ እንዲያደርግለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጌታው የሚፈልገውን ነገር ለማወቅና የጌታውን ፍላጎት ለመፈጸም ምንጊዜም ዓይኑ ወደ ጌታው መመልከት ይኖርበታል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለማወቅና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ በየዕለቱ የአምላክን ቃል መመርመር ያስፈልገናል። ይሖዋ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሞገሱን እንደሚያሳየን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—ኤፌ. 5:17
3. ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዳንመለከት ትኩረታችንን የሚከፋፍልብን ምን ሊሆን ይችላል?
3 ምንም እንኳ ሁልጊዜ ወደ ይሖዋ የመመልከትን አስፈላጊነት ብንገነዘብም አንዳንድ ጊዜ ትኩረታችን ሊከፋፈል ይችላል። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ማርታ ያጋጠማት ሁኔታ ይህ ነበር። ማርታ “በብዙ ሥራ ተጠምዳ ትባክን ነበር።” (ሉቃስ 10:40-42) እንደ እሷ ያለ ታማኝ ሰው ኢየሱስ አጠገቧ እያለ እንኳ ትኩረቷ ከተከፋፈለ እኛንማ እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥመን የሚችል መሆኑ ምን ያስገርማል? ታዲያ ትኩረታችን እንዲከፋፈል በማድረግ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዳንመለከት እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በዚህ ርዕስ ውስጥ የሌሎች ድርጊት ትኩረታችንን ሊከፋፍለው የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ምንጊዜም ወደ ይሖዋ መመልከት የምንችልበትን መንገድ እንመረምራለን።
አንድ ታማኝ ሰው ውድ የሆነ መብት አጣ
4. ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብቱን ማጣቱ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ሙሴ ምክርና መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ የሚመለከት ሰው ነበር። እንዲያውም “የማይታየውን አምላክ እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል” ተብሎለታል። (ዕብራውያን 11:24-27ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “ይሖዋ ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እስካሁን በእስራኤል ተነስቶ አያውቅም” ይላል። (ዘዳ. 34:10) ሙሴ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የቀረበ ዝምድና የነበረው ቢሆንም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብቱን አጥቷል። (ዘኁ. 20:12) ሙሴ እንዲደናቀፍ ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው?
5-7. እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ምን ችግር ተከሰተ? ሙሴስ በዚህ ወቅት ምን አደረገ?
5 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ገና ሲና ተራራ እንኳ ሳይደርሱ አንድ ከባድ ችግር ተከሰተ። ሕዝቡ ውኃ በማጣቱ ማማረርና በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመረ። ሁኔታው በጣም እየተባባሰ ከመሄዱ የተነሳ ሙሴ “ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻለኛል? ትንሽ ቆይተው እኮ ይወግሩኛል!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። (ዘፀ. 17:4) ይሖዋም ግልጽ መመሪያዎችን ሰጠው። በትሩን ወስዶ በኮሬብ የሚገኘውን ዓለት ሲመታው ውኃ ከውስጡ እየተንዶለዶለ እንደሚወጣ ነገረው። ዘገባው “ሙሴም የእስራኤል ሽማግሌዎች እያዩ እንደተባለው አደረገ” ይላል። እስራኤላውያን እስኪበቃቸው ድረስ የጠጡ ሲሆን ችግሩም በዚህ መንገድ ተፈታ።—ዘፀ. 17:5, 6
6 በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ ሲቀጥል እንዲህ ይላል፦ “[ሙሴ] እስራኤላውያን ስለተጣሉትና ‘ለመሆኑ ይሖዋ በመካከላችን አለ ወይስ የለም?’ በማለት ይሖዋን ስለተፈታተኑት የቦታውን ስም ማሳህ እና መሪባ አለው።” (ዘፀ. 17:7) “ማሳህ” እና “መሪባ” የሚሉት ቃላት “ፈተና” እና “ጠብ” የሚል ትርጉም ስላላቸው ቦታው እንዲህ ያለ ስያሜ የተሰጠው መሆኑ ተገቢ ነው።
7 ይሖዋ በመሪባ ስለተከሰተው ነገር ምን ተሰማው? እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር በሙሴ ላይ እንደተነሳ ዓመፅ ብቻ ሳይሆን በራሱ አምላክነት ላይ እንደተነሳ ግድድር አድርጎ ቆጥሮታል። (መዝሙር 95:8, 9ን አንብብ።) እስራኤላውያን ከባድ ስህተት እንደፈጸሙ ግልጽ ነበር። በዚህ ወቅት ሙሴ ወደ ይሖዋ በመመልከት እንዲሁም እሱ የሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ በመከተል ተገቢውን እርምጃ ወስዷል።
8. እስራኤላውያን ለ40 ዓመት በምድረ በዳ ያደረጉትን ጉዞ ሊያጠናቅቁ በተቃረቡበት ወቅት ምን ችግር ተከሰተ?
8 ይሁንና ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ እስራኤላውያን በምድረ በዳ የሚያደርጉትን ጉዞ ሊያጠናቅቁ በተቃረቡበት ወቅትም ተመሳሳይ ችግር አጋጠመ። በዚህ ጊዜስ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? በዚህ ጊዜም ቢሆን እስራኤላውያን የሚገኙት መሪባ የሚል ስያሜ በተሰጠው ስፍራ ነበር። ሆኖም ይሄኛው መሪባ በተስፋይቱ ምድር ድንበር አካባቢ ያለና በቃዴስ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ቀደም ሲል ከተጠቀሰው መሪባ የተለየ ቦታ ነው።a እስራኤላውያን አሁንም ውኃ በማጣታቸው ማማረር ጀመሩ። (ዘኁ. 20:1-5) በዚህ ጊዜ ግን ሙሴ ከባድ ስህተት ፈጸመ።
9. ሙሴ ምን መመሪያ ተሰጠው? እሱ ግን ምን አደረገ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
9 ሙሴ ለተነሳው ዓመፅ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? አሁንም ቢሆን መመሪያ ለማግኘት ዓይኖቹ የተመለከቱት ወደ ይሖዋ ነበር። ሆኖም በዚህ ወቅት ይሖዋ ዓለቱን እንዲመታ አላዘዘውም። ከዚህ ይልቅ በትሩን እንዲወስድ፣ ሕዝቡን በዓለቱ ፊት እንዲሰበስብና ዓለቱን እንዲናገረው መመሪያ ሰጠው። (ዘኁ. 20:6-8) ሙሴ ግን ዓለቱን ከመናገር ይልቅ እዚያ በተሰበሰቡት ሰዎች ላይ “እናንተ ዓመፀኞች ስሙ! ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?” ብሎ በመጮኽ ንዴቱን ገለጸ። ከዚያም ዓለቱን ከአንዴም ሁለት ጊዜ መታው።—ዘኁ. 20:10, 11
10. ይሖዋ በሙሴ ድርጊት ምን ተሰማው?
10 ይሖዋ በሙሴ ላይ በጣም ተቆጣ። (ዘዳ. 1:37፤ 3:26) ይሖዋ እንዲህ የተቆጣው ለምንድን ነው? ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ የተለያዩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዱ ምክንያት ሙሴ የተሰጠውን አዲስ መመሪያ ሳይከተል መቅረቱ ሊሆን ይችላል።
11. ሙሴ ዓለቱን መምታቱ ይሖዋ ያከናወነው ነገር ተአምር እንዳይመስል አድርጎ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ በሙሴ ላይ የተቆጣበት ሌላም ምክንያት ሊኖር ይችላል። በመጀመሪያው መሪባ አካባቢ የሚገኙት ዓለቶች ጠንካራ ጥቁር ድንጋዮች ናቸው። አንድ ሰው ጥቁር ድንጋይን የፈለገውን ያህል በኃይል ቢመታ ድንጋዩ ውኃ ያፈልቃል ብሎ የሚጠብቅ ማንም ሰው የለም። በሁለተኛው መሪባ አካባቢ ያሉት ዓለቶች ግን ከዚህ በጣም የተለዩ ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ያን ያህል ጥንካሬ የሌላቸው በሃ ድንጋዮች ናቸው። በሃ ድንጋይ በባሕርይው ውስጡ ክፍት ስለሆነ ይህ ድንጋይ ያለባቸው አካባቢዎች አብዛኛውን ጊዜ የተጠራቀመ የከርሰ ምድር ውኃ ይኖራቸዋል፤ በመሆኑም ሰዎች እነዚህን ድንጋዮች በመቦርቦር ውኃ ማውጣት ይችላሉ። ምናልባትም ሙሴ እንዲህ ያለውን ጥንካሬ የሌለው ዓለት ሁለት ጊዜ መምታቱ፣ ውኃው የፈለቀው በይሖዋ እርዳታ ሳይሆን በተፈጥሯዊ መንገድ ነው ለሚል ትችት አጋልጦት ይሆን? ሙሴ ዓለቱን ከመናገር ይልቅ መምታቱ፣ ተአምር የሆነው ነገር ተአምር እንዳይመስል አድርጎ ይሆን?b ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።
ሙሴ ያመፀው እንዴት ነው?
12. ይሖዋ በሙሴና በአሮን ላይ የተቆጣበት ሌላኛው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?
12 ይሖዋ በሙሴም ሆነ በአሮን ላይ የተቆጣበት ሌላም ምክንያት ሊኖር ይችላል። ሙሴ ሕዝቡን “ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?” እንዳላቸው ልብ በል። ሙሴ “አለብን” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ራሱንና አሮንን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። ሙሴ የተጠቀመበት አገላለጽ የተአምሩ እውነተኛ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው። በመዝሙር 106:32, 33 ላይ ያለው ሐሳብም ይህን የሚደግፍ ይመስላል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በመሪባ ውኃ አጠገብ አምላክን አስቆጡት፤ በእነሱም የተነሳ ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። መንፈሱን አስመረሩት፤ እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።”c (ዘኁ. 27:14) ሙሴ ያደረገው ነገር ይሖዋ የሚገባውን ክብር እንዳያገኝ አድርጓል። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ‘ሁለታችሁም በሰጠሁት ትእዛዝ ላይ ዓምፃችኋል’ ብሏቸዋል። (ዘኁ. 20:24) ይህ በእርግጥም በጣም ከባድ ኃጢአት ነው!
13. ይሖዋ በሙሴ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ተገቢና ፍትሐዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
13 ሙሴና አሮን በይሖዋ ሕዝብ መካከል የተሾሙ መሪዎች እንደመሆናቸው መጠን የበለጠ ተጠያቂነት ነበረባቸው። (ሉቃስ 12:48) ቀደም ሲል ይሖዋ እስራኤላውያን በእሱ ላይ ስላመፁ አንድ ትውልድ በሙሉ ወደ ከነአን ምድር እንዳይገባ ከልክሎ ነበር። (ዘኁ. 14:26-30, 34) በመሆኑም ይሖዋ፣ ሙሴ ለፈጸመው የዓመፅ ድርጊትም ተመሳሳይ ፍርድ መስጠቱ ተገቢና ፍትሐዊ ነው። እንደ ሌሎቹ ዓመፀኞች ሁሉ ሙሴም ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከልክሏል።
የችግሩ መንስኤ
14, 15. ሙሴ እንዲያምፅ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
14 ሙሴን እንዲህ ዓይነት የዓመፀኝነት ድርጊት ወደመፈጸም የመራው ምንድን ነው? እስቲ መዝሙር 106:32, 33ን በድጋሚ እንመልከት፦ “በመሪባ ውኃ አጠገብ አምላክን አስቆጡት፤ በእነሱም የተነሳ ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። መንፈሱን አስመረሩት፤ እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።” እስራኤላውያን ያስቆጡት ይሖዋን ቢሆንም የተመረረው ግን ሙሴ ነበር። ራሱን መግዛት አለመቻሉ፣ ውጤቱን ሳያመዛዝን እንዲናገር አድርጎታል።
15 ሙሴ የሌሎች ድርጊት እንቅፋት እንዲሆንበት መፍቀዱ ዓይኑ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዳይመለከት አድርጎታል። ሙሴ መጀመሪያ ላይ ያጋጠመውን ችግር ተገቢ በሆነ መንገድ ፈቶት ነበር። (ዘፀ. 7:6) ሆኖም ዓመፀኛ ከሆኑት እስራኤላውያን ጋር ለአሥርተ ዓመታት አብሮ ማሳለፉ እንዲዝልና ትዕግሥቱ እንዲሟጠጥ አድርጎት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ሙሴ ይሖዋን እንዴት ማክበር እንደሚችል ከማሰብ ይልቅ በራሱ ስሜት ላይ ብቻ አተኩሮ ይሆን?
16. ሙሴ የሠራውን ስህተት ትኩረት ሰጥተን ልናስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?
16 እንደ ሙሴ ያለ ታማኝ ነቢይ ትኩረቱ ሊከፋፈልና ሊደናቀፍ ከቻለ እኛም ተመሳሳይ ስህተት ልንሠራ የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ልክ እንደ ሙሴ እኛም በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ ተስፋይቱ ምድር ማለትም ይሖዋ ቃል ወደገባልን አዲስ ዓለም ልንገባ ተቃርበናል። (2 ጴጥ. 3:13) ማናችንም ብንሆን ይህ ልዩ መብት እንዲያመልጠን አንፈልግም። ሆኖም ይህን ግባችንን ማሳካት የምንችለው ዓይናችን ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዲመለከት የምናደርግ ማለትም ዘወትር የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የምንጣጣር ከሆነ ነው። (1 ዮሐ. 2:17) ሙሴ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት እናገኛለን?
የሌሎች ድርጊት ትኩረታችሁን እንዳይከፋፍለው ተጠንቀቁ
17. የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመን ራሳችንን መግዛት እንድንችል ምን ይረዳናል?
17 የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ራሳችሁን መግዛት እንዳያቅታችሁ ተጠንቀቁ። በተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ችግር በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ “ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።” (ገላ. 6:9፤ 2 ተሰ. 3:13) ትዕግሥታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ወይም በባሕርይ አለመጣጣም ምክንያት ከአንድ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ስንጋጭ አንደበታችንን ወይም ቁጣችንን ለመቆጣጠር እንሞክራለን? (ምሳሌ 10:19፤ 17:27፤ ማቴ. 5:22) ሌሎች የሚያበሳጭ ነገር ሲፈጽሙብን “ለቁጣው” ማለትም ለይሖዋ ቁጣ “ዕድል [መስጠት]” ይኖርብናል። (ሮም 12:17-21ን አንብብ።) ምንጊዜም ወደ ይሖዋ የምንመለከት ከሆነ እሱ ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው ሰዓት እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቅ ለቁጣው ዕድል እንሰጣለን፤ በዚህ መንገድ ለይሖዋ ተገቢውን አክብሮት እናሳያለን። ከዚህ በተቃራኒ ራሳችን በሆነ መንገድ ለመበቀል መሞከራችን ለይሖዋ አክብሮት እንደማጣት ይቆጠራል።
18. መመሪያዎችን ስለመከተል ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
18 አዳዲስ መመሪያዎችን በጥንቃቄ ተከተሉ። ይሖዋ የሚሰጠንን አዳዲስ መመሪያዎች በታማኝነት እንፈጽማለን? ከሆነ ነገሮችን ሁልጊዜ በለመድነው መንገድ ለመሥራት አንሞክርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን ማንኛውንም አዲስ መመሪያ ለመከተል ፈጣኖች እንሆናለን። (ዕብ. 13:17) በተጨማሪም ‘ከተጻፈው ላለማለፍ’ እንጠነቀቃለን። (1 ቆሮ. 4:6) በዚህ መንገድ ዓይናችን ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዲመለከት እናደርጋለን።
19. የሌሎች ስህተት ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና እንዳያበላሽብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
19 የሌሎች ስህተት ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና እንዲያበላሽባችሁ አትፍቀዱ። ምሳሌያዊ ዓይናችን ምንጊዜም በይሖዋ ላይ እንዲያተኩር የምናደርግ ከሆነ የሌሎች ድርጊት እንዲያስመርረን ወይም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና እንዲያበላሽብን አንፈቅድም። በተለይ ደግሞ እንደ ሙሴ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የተወሰነ ኃላፊነት ካለን እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ሁላችንም ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተን መሥራት’ ያለብን ቢሆንም ይሖዋ በእያንዳንዳችን ላይ የሚፈርደው ድርቅ ባለ አንድ መሥፈርት ላይ ተመሥርቶ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (ፊልጵ. 2:12) የበለጠ ኃላፊነት በተሰጠን መጠን ተጠያቂነታችንም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። (ሉቃስ 12:48) ይሖዋን ከልባችን የምንወድ ከሆነ ግን ምንም ነገር ሊያደናቅፈን ወይም ከእሱ ፍቅር ሊለየን አይችልም።—መዝ. 119:165፤ ሮም 8:37-39
20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
20 በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ዓይናችንን ምንጊዜም ‘በሰማያት ዙፋን ላይ ወደተቀመጠው’ በማንሳት የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናድርግ። የሌሎች ድርጊት ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ዝምድና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ፈጽሞ አንፍቀድ። በሙሴ ላይ የደረሰው ነገር እንዲህ ማድረጋችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝበናል። በዙሪያችን ባሉት ሰዎች አለፍጽምና ከመመረር ይልቅ ‘ሞገስ እስኪያሳየን ድረስ ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ ለመመልከት’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝ. 123:1, 2
a ይሄኛው መሪባ በረፊዲም አቅራቢያ ካለው መሪባ የተለየ ነው። የመጀመሪያው መሪባ የተጠቀሰው ከማሳህ ጋር ሲሆን ሁለተኛው መሪባ ግን ከቃዴስ ጋር ነው። ሆኖም ሁለቱም ቦታዎች መሪባ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው በዚያ በተከሰተው ጠብ ምክንያት ነው።—አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተጨማሪ መረጃ ለ3 ሥር የሚገኘውን ካርታ ተመልከት።
b ጆን ቤክ የተባሉ ፕሮፌሰር ይህን ዘገባ አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ የአይሁዳውያን ወግ እንደሚለው ዓመፀኞቹ ሙሴን እንዲህ ብለው ተችተውት ነበር፦ ‘ሙሴ የዚህን ዓለት ባሕርይ ያውቃል! ተአምር የመፈጸም ኃይል እንዳለው ማሳየት ከፈለገ ለምን ከሌላኛው ዓለት ውኃ አያወጣም?’” እርግጥ ነው፣ ይህ የአይሁዳውያን ወግ የሚለው ነው።
c የጥቅምት 15, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።