የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ውሳኔዬን አብዝቶ ባርኮልኛል
በተመደበልን ክልል ውስጥ በነበሩት ቤቶች በር ሥር ትራክቶችን አስገብተን የጨረስነው ጎህ ሊቀድ ሲል ነበር። ጊዜው 1939 ሲሆን ሌሊት ከእንቅልፋችን ተነስተን ከአንድ ሰዓት በላይ በመኪና ከተጓዝን በኋላ በደቡብ ምዕራብ ሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወደምትገኘው ጆፕሊን የተባለች አነስተኛ ከተማ ደረስን። ድምፃችንን አጥፍተን ክልላችንን ከሸፈንን በኋላ በፍጥነት ወደ መኪናችን ገባን። ከዚያም በሌሎች መኪኖች ከመጡት ወንድሞች ጋር ወደተቀጣጠርንበት ቦታ ሄደን እነሱ እስኪመጡ ድረስ እንጠብቅ ጀመር። ይሁንና ገና ጎህ ሳይቀድ አገልግሎት የወጣነው እንዲሁም ክልሉን በፍጥነት ለቀን የሄድነው ለምን እንደሆነ ሳይገርማችሁ አይቀርም። ምክንያቱን በኋላ እነግራችኋለሁ።
የተወለድኩት በ1934 ነው፤ ወላጆቼ ፍሬድ እና ኤድና እኔ ከመወለዴ ከ20 ዓመት በፊት ጀምሮ ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች) ነበሩ። ወላጆቼ ለአምላክ የማደር ባሕርይ በውስጤ እንዲቀረጽ አድርገው ስላሳደጉኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ቤተሰባችን የሚኖረው በደቡብ ምሥራቅ ካንሳስ በምትገኝ ፓርሰንስ የምትባል አንዲት አነስተኛ ከተማ ውስጥ ሲሆን ጉባኤያችንም የሚገኘው እዚያው ከተማ ውስጥ ነበር። የጉባኤያችን አባላት በሙሉ ማለት ይቻላል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። ቤተሰባችን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና የአምላክን ቃል እውነት ለሌሎች በመስበክ ረገድ ጥሩ ልማድ ነበረው። አብዛኛውን ጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላን የምናሳልፈው አሁን የአደባባይ ምሥክርነት ብለን በምንጠራው አገልግሎት በመካፈል ማለትም መንገድ ላይ በማገልገል ነበር። እርግጥ ይህ አንዳንድ ጊዜ አድካሚ ነው፤ ያም ቢሆን ሁልጊዜ አገልግሎት ስንጨርስ አባባ አይስ ክሬም ስለሚጋብዘን ደስ ይለን ነበር።
ጉባኤያችን አነስተኛ ቢሆንም በርካታ ትናንሽ ከተሞችንና በአቅራቢያችን ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የእርሻ ቦታዎችን የሚጨምር ሰፊ ክልል ነበረው። አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ገበሬዎች ለምናበረክትላቸው ጽሑፍ አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ ፋንታ የጓሮ አትክልት፣ እንቁላል ወይም ዶሮ ይሰጡን ነበር። አባባ ጽሑፎቹን የሚወስደው አስተዋጽኦ አድርጎ ስለሆነ በጽሑፎቹ ምትክ የሚሰጡን ነገሮች የምግብ አቅርቦታችንን ለመደጎም ይረዱን ነበር።
የስብከት ዘመቻዎች
ወላጆቼ በስብከቱ ሥራ ላይ የሚጠቀሙበት አንድ የሸክላ ማጫወቻ ነበራቸው። ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ መሣሪያውን መጠቀም አልችልም ነበር፤ ሆኖም አባባና እማማ ተመላልሶ መጠየቅ በሚያደርጉበትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚመሩበት ጊዜ የወንድም ራዘርፎርድን ንግግሮች ሲያጫውቱ እነሱን መርዳት ያስደስተኝ ነበር።
አባባ የ1936 ሞዴል ፎርድ መኪናችን ጣሪያ ላይ ትልቅ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ገጠመለት፤ እንዲህ ያሉት መኪኖች ባለ ድምፅ ማጉያ መኪና ይባሉ ነበር። ይህ መኪና የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አብዛኛውን ጊዜ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ መጀመሪያ ላይ ሙዚቃ እናጫውታለን፤ ከዚያም የተቀዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እናሰማለን። ንግግሩ ሲያልቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ጽሑፍ እናበረክታለን።
አንድ ቀን አባባ መኪናውን ይዞ ቼሪቬል በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ወዳለ አንድ መናፈሻ ሄደ፤ ብዙ ሰዎች እሁድ እሁድ ዘና ለማለት ወደዚህ መናፈሻ ይሄዱ ነበር። ሆኖም ፖሊሶች መጥተው፣ መናፈሻው ውስጥ ንግግር ማሰማት ክልክል እንደሆነና እንዲህ ማድረግ የሚፈቀደው ከግቢው ውጭ እንደሆነ ለአባባ ነገሩት። አባባም ምንም ሳይከራከር መኪናውን ከመናፈሻው አጠገብ ወዳለው መንገድ ወስደው፤ ከዚያም መናፈሻው ውስጥ ያሉት ሰዎች መልእክቱን መስማት እንዲችሉ ፊቱን ወደ መናፈሻው አዙሮ አቆመውና ንግግሩን ማጫወቱን ቀጠለ። እንዲህ ባሉ ወቅቶች ከአባባና ከታላቅ ወንድሜ ከጄሪ ጋር መሆን በጣም ያስደስተኝ ነበር።
በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ ከባድ ተቃውሞ ያለባቸውን ክልሎች በፍጥነት ለመሸፈን ልዩ በሆኑ ዘመቻዎች እንካፈል ነበር። ጎህ ሳይቀድ እንወጣና (በጆፕሊን፣ ሚዙሪ እንዳደረግነው) ድምፃችንን አጥፍተን ትራክቶችን ወይም ቡክሌቶችን በእያንዳንዱ በር ሥር እናስገባለን። ክልላችንን ስንጨርስ፣ አብረውን ከተሰማሩት መካከል በፖሊስ ተይዞ የታሰረ ሰው መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ከከተማዋ ውጭ እንገናኛለን።
በዚያ ዘመን፣ የማስታወቂያ ሰልፍ ተብሎ በሚጠራ አስደሳች የአገልግሎት ዘርፍም እንካፈል ነበር። የአምላክን መንግሥት ለማስታወቅ፣ የተለያየ መልእክት የተጻፈባቸው ሰሌዳዎችን አንግበን በከተማ መሃል በሰልፍ እንጓዝ ነበር። በአንድ ወቅት በከተማችን በተደረገ እንዲህ ያለ ሰልፍ ላይ ወንድሞች “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” የሚል ሰሌዳ አንግበው እንደተጓዙ አስታውሳለሁ። ወንድሞች በከተማው ውስጥ 1.6 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ ወደ እኛ ቤት ተመልሰው መጡ። ደስ የሚለው በሰልፍ ጉዞው ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልገጠማቸውም፤ እንዲያውም ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ሰዎችን አግኝተዋል።
ልጅ ሳለሁ የተደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች
ቤተሰባችን በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ብዙ ጊዜ ከካንሳስ ወደ ቴክሳስ ይጓዝ ነበር። አባባ የባቡር ጣቢያ ድርጅት ሠራተኛ ስለነበር ነፃ ቲኬት ነበረን፤ ስለዚህ አብረን በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ዘመዶቻችንን መጠየቅ እንችል ነበር። የእናቴ ታላቅ ወንድም ፍሬድ ዊዝማርና ባለቤቱ ዩሌሊ የሚኖሩት ቴምፕል፣ ቴክሳስ ውስጥ ነበር። አጎቴ ፍሬድ እውነትን የሰማው በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ገና ወጣት ሳለ ነበር፤ ከዚያም የተጠመቀ ሲሆን የተማረውን ነገር ለእናቴና ለሌሎች እህቶቹ አካፍሏቸዋል። በአንድ ወቅት የዞን አገልጋይ (አሁን የወረዳ የበላይ ተመልካች ይባላል) ሆኖ ይሠራ በነበረበት በማዕከላዊ ቴክሳስ በሚገኙ ወንድሞች ዘንድ በደንብ ይታወቅ ነበር። አጎቴ ደግና ደስተኛ ስለነበር ከእሱ ጋር መሆን ሁሌም ደስ ያሰኛል። ለእውነት ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ሲሆን ይህም ወጣት ሳለሁ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።
በ1941 ቤተሰባችን በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሴንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ በባቡር ተጓዘ። በስብሰባው ላይ ልጆች ለእነሱ ተብሎ በተዘጋጀው ልዩ ቦታ ላይ ተቀምጠው ወንድም ራዘርፎርድ “የንጉሡ ልጆች” በሚል ርዕስ የሚያቀርበውን ንግግር እንዲያዳምጡ ተጋበዙ። ንግግሩ ሲያበቃ ወንድም ራዘርፎርድና ረዳቶቹ ለእያንዳንዳችን፣ ልጆች የሚል ርዕስ ያለውን አዲስ መጽሐፍ ሲሰጡን በጣም ተደሰትን። በቦታው የነበርን ከ15,000 በላይ የምንሆን ልጆች ይህን መንፈሳዊ በረከት ማግኘት ችለናል።
ሚያዝያ 1943 በኮፊቪል፣ ካንሳስ “የሥራ ጥሪ” በሚል ርዕስ አነስ ያሉ ተሰብሳቢዎች የተገኙበት ሆኖም ፈጽሞ የማይረሳ የወረዳ ስብሰባ አደረግን። በዚህ ስብሰባ ላይ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንደሚጀምር የተነገረ ከመሆኑም ሌላ በዚህ ትምህርት ቤት ላይ የምንጠቀምበት 52 ትምህርቶችን የያዘ ቡክሌት ወጣ። በዚያው ዓመት የመጀመሪያውን የተማሪ ክፍሌን አቀረብኩ። ይህ ስብሰባ ለእኔ ልዩ የሆነበት ሌላም ምክንያት ነበር፤ እኔና ሌሎች ሁለት ወንድሞች በስብሰባ ቦታው አቅራቢያ ባለ እርሻ ውስጥ ወደሚገኝ ቀዝቃዛ ኩሬ ሄደን የተጠመቅነው በዚህ ወቅት ነበር።
የምመኘው ሥራ—የቤቴል አገልግሎት
በ1951 መደበኛ ትምህርቴን ስጨርስ የወደፊት ሕይወቴን በሚመለከት ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ። ጄሪ ቀደም ሲል ያገለግል በነበረበት በቤቴል የማገልገል ልባዊ ፍላጎት ነበረኝ፤ በመሆኑም ቤቴል ለመግባት አመለከትኩ። ብዙም ሳይቆይ ማመልከቻዬ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን መጋቢት 10, 1952 የቤቴል አገልግሎቴን ጀመርኩ። ይህን ውሳኔ ማድረጌ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት አስገኝቶልኛል።
በመጽሔቶችና በሌሎች ጽሑፎች ሕትመት ሥራ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማበርከት እንድችል በማተሚያ ክፍል ውስጥ መሥራት እፈልግ ነበር። ሆኖም በዚህ ክፍል ውስጥ የመሥራት መብት አላገኘሁም። መጀመሪያ ላይ በአስተናጋጅነት ከዚያም ኩሽና ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ፤ ሥራው አስደሳች የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። ኩሽና ውስጥ የምንሠራው በፈረቃ ስለነበር በቀኑ መሃል በርካታ መጻሕፍትን ወደያዘው የቤቴል ቤተ መጻሕፍት ገብቼ የግል ጥናት ማድረግ የምችልበት ጊዜ ነበረኝ። ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግና እምነቴ እንዲጠናከር ረድቶኛል። በተጨማሪም ሁኔታዬ እስከፈቀደ ድረስ ይሖዋን በቤቴል ለማገልገል ያለኝን ቁርጠኝነት አጠናክሮልኛል። ጄሪ በ1949 ከቤቴል ወጥቶ ፓትሪሺያ የተባለች እህት አግብቶ ይኖር ነበር፤ ሆኖም የሚኖሩት በብሩክሊን አቅራቢያ ስለነበር ቤቴል ከገባሁ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በጣም ይረዱኝና ያበረታቱኝ ነበር።
ቤቴል ከመጣሁ ብዙም ሳይቆይ በቤቴል ተናጋሪዎች ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ተጨማሪ ወንድሞችን ለማግኘት ሲባል የብቃት መመዘኛ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ወንድሞች ከብሩክሊን እስከ 200 ማይል (322 ኪሎ ሜትር) ድረስ ባለው ርቀት ውስጥ ወደሚገኙ ጉባኤዎች ሄደው የሕዝብ ንግግር እንዲሰጡና ከጉባኤዎቹ ጋር እንዲያገለግሉ ይመደቡ ነበር። እኔም ይህን መብት ካገኙ ወንድሞች መካከል አንዱ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ የሕዝብ ንግግሩ የአንድ ሰዓት ርዝማኔ የነበረው ሲሆን የመጀመሪያ ንግግሬን ስሰጥ በጣም ፈርቼ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጉባኤዎቹ የምሄደው በባቡር ነበር። በ1954 የክረምት ወቅት ላይ ያጋጠመኝን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም፤ እሁድ ከሰዓት በኋላ ወደ ኒው ዮርክ የሚሄድ አንድ ባቡር ተሳፈርኩ። ይህ ባቡር አመሻሹ ላይ ቤቴል መድረስ ነበረበት። ይሁን እንጂ በረዶና ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ መጣል ጀመረ። በዚህ ምክንያት በኤሌክትሪክ የሚሠራው የባቡሩ ሞተር ተበላሸ። በመጨረሻም ባቡሩ ኒው ዮርክ ከተማ ወዳለው ጣቢያው የደረሰው ሊነጋጋ ሲል 11 ሰዓት ገደማ ነበር። ከዚያም ወደ ብሩክሊን የሚሄድ ሌላ ባቡር ይዤ ሰኞ ጠዋት በቀጥታ ወደ ኩሽና በመሄድ ሥራዬን ጀመርኩ፤ በተበላሸው ባቡር ላይ በደረሰብኝ እንግልት ምክንያት ሥራ የገባሁት አርፍጄ ከመሆኑም ሌላ በጣም ደክሞኝ ነበር። እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ላይ ጉባኤዎችን ማገልገል መቻሌና ከብዙ አዳዲስ ወንድሞች ጋር መተዋወቄ የሚያስገኝልኝ ደስታ ይህን ሁሉ የሚያስረሳ ነበር።
ቤቴል ውስጥ ባገለገልኩባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በደብልዩ ቢ ቢ አር የሬዲዮ ጣቢያ ላይ በሚተላለፉት ፕሮግራሞች ውስጥ የመሳተፍ አጋጣሚ አገኘሁ። በዚያን ጊዜ የሬዲዮ ጣቢያው ስቱዲዮዎች የሚገኙት በ124 ኮሎምቢያ ሃይትስ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነበር። የእኔ ምድብ በየሳምንቱ በሚቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ላይ አንዱን ግለሰብ ወክሎ መጫወት ነበር። ለብዙ ዓመታት በቤቴል ያገለገለው ወንድም አሌክሳንደር ማክሚላን በእነዚህ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ዘወትር ይሳተፍ ነበር። ማክ በሚል የቁልምጫ ስም የሚጠራው ወንድም ማክሚላን በይሖዋ አገልግሎት ጽናት በማሳየት ረገድ እንደ እኔ ላሉ ወጣት ቤቴላውያን ግሩም ምሳሌ ነበር።
በ1958 ከጊልያድ ትምህርት ቤት ጋር በቅርበት እንድሠራ ተመደብኩ። ሥራዬ ተመራቂዎቹ ቪዛ እንዲያገኙ መርዳትና ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት ማድረግ ነበር። በዚያን ጊዜ የአውሮፕላን ቲኬት በጣም ውድ ስለነበር በአውሮፕላን የሚጓዙት ጥቂት ሚስዮናውያን ነበሩ። ወደ አፍሪካና ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሚመደቡት አብዛኞቹ ሚስዮናውያን እንዲሄዱ የሚደረገው በጭነት ማመላለሻ መርከብ ነበር። የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ እየቀነሰ ሲመጣ ግን አብዛኞቹ ሚስዮናውያን ወደተመደቡባቸው አገሮች በአውሮፕላን እንዲሄዱ ይደረግ ጀመር።
በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የሚደረግ ጉዞ
በ1960 ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠኝ፤ የተሰጠኝ ሥራ በ1961 በሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ አውሮፓ ለሚሄዱ ወንድሞች የኪራይ አውሮፕላኖችን ማዘጋጀት ነበር። እኔም በዚሁ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከኒው ዮርክ ወደ ሃምቡርግ፣ ጀርመን ከተጓዙት ወንድሞች መካከል አንዱ ነበርኩ። ከስብሰባው በኋላ እኔና ሌሎች ሦስት ቤቴላውያን ወንድሞች አንድ መኪና ተከራይተን ከጀርመን ወደ ጣሊያን በመጓዝ በሮም ያለውን ቅርንጫፍ ቢሮ ጎበኘን። ከዚያም ጉዟችንን በመቀጠል ወደ ፈረንሳይ ከሄድን በኋላ በፒሪኒስ ተራሮች አልፈን በወቅቱ የስብከቱ ሥራችን ወደታገደባት ወደ ስፔን አቀናን። ጽሑፎችን በስጦታ ወረቀት የተጠቀለሉ ዕቃዎች አስመስለን በባርሴሎና ለነበሩ ወንድሞቻችን ማድረስ ችለን ነበር። እነሱን በማግኘታችን በጣም ተደስተን ነበር! ከዚያም በመኪና ወደ አምስተርዳም ከተጓዝን በኋላ ወደ ኒው ዮርክ የሚሄድ አውሮፕላን ተሳፈርን።
ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ በቤቴል ውስጥ የተሰጠኝ የሥራ ምድብ በዓለም ዙሪያ በተከታታይ የሚደረጉ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለተመረጡ ልዑካን ለጉዞ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማዘጋጀትን የሚጨምር ሆነ። በ1963 የተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ “የዘላለም ምሥራች” የሚል ርዕስ ነበረው። በአውሮፓ፣ በእስያና በደቡብ ፓስፊክ በሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለ583 ልዑካን ዝግጅት ተደርጎ ነበር፤ በዓለም ዙሪያ የሚደረገው ይህ ጉዞ የሚጠናቀቀው ሆኖሉሉን፣ ሃዋይንና በካሊፎርኒያ የምትገኘውን ፓሳዴናን በመጎብኘት ነው። በተጨማሪም ጉዞው እንደ ሊባኖስና ዮርዳኖስ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን መጎብኘትን ይጨምር ነበር። የሥራ ድርሻችን የወንድሞችን የበረራ ፕሮግራም ከማመቻቸትና የሚያርፉባቸውን ሆቴሎች ከማዘጋጀት በተጨማሪ በጉዟቸው ወቅት ቆይታ ለሚያደርጉባቸው አገሮች ሁሉ የሚያስፈልገውን ቪዛ እንዲያገኙ ማድረግን ያካትታል።
አዲስ የጉዞ ጓደኛ
በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ሌላው ነገር የተከሰተው በ1963 ነበር። ለሦስት ዓመት ያህል በቤቴል ካገለገለችው ከሊላ ሮጀርስ ጋር ሰኔ 29 ተጋባን፤ ሊላ የመጣችው ከሚዙሪ ነበር። ከተጋባን ከአንድ ሳምንት በኋላ እኔና ሊላ በዓለም ዙሪያ በሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከሚጓዘው ቡድን ጋር በመሆን ሊባኖስን፣ ግሪክንና ግብፅን ጎበኘን። ከዚያም ከቤይሩት በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ዮርዳኖስ በአውሮፕላን ተጓዝን። ዮርዳኖስ ውስጥ እገዳ ስለነበር ለይሖዋ ምሥክሮች ወደ አገሪቱ የሚያስገባ ቪዛ እንደማይሰጣቸው ተነግሮን ነበር፤ በመሆኑም ምን እንደሚያጋጥመን አሳስቦን ነበር። እዚያ ስንደርስ ግን በአውሮፕላን ማረፊያው ሰገነት ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ እንኳን ደህና መጣችሁ!” የሚል ጽሑፍ የያዙ ወንድሞችና እህቶችን ስናይ በጣም ተደነቅን! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ቦታዎች በገዛ ዓይናችን መመልከት በጣም የሚያስደስት ነበር! በጥንት ዘመን የነበሩት የእምነት አባቶች የኖሩባቸውን አካባቢዎች፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ የሰበኩባቸውን ቦታዎች እንዲሁም ክርስትና እስከ ምድር ዳር ድረስ መስፋፋት የጀመረባቸውን አካባቢዎች ጎበኘን።—ሥራ 13:47
ላለፉት 55 ዓመታት ሊላ በተሰጡን የአገልግሎት ምድቦች ሁሉ በታማኝነት አብራኝ ስትሠራ ቆይታለች። የስብከቱ ሥራችን በስፔንና በፖርቱጋል በታገደባቸው ጊዜያት፣ በዚያ ያሉ ወንድሞችን በተደጋጋሚ የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ወንድሞችን ማበረታታት እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን ጽሑፎችና ሌሎች ነገሮች ማድረስ ችለናል። እንዲያውም በአንድ ወቅት በካዲዝ፣ ስፔን በሚገኝ ወታደራዊ እስር ቤት የነበሩ አንዳንድ ወንድሞችን መጠየቅ ችለን ነበር። ለእነዚያ ወንድሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሚያንጽ ንግግር ማቅረብ በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር።
ከ1963 ወዲህ ባሉት ዓመታት በሃዋይ፣ በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ፣ በሩቅ ምሥራቅ፣ በኒው ዚላንድ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካና በፖርቶ ሪኮ በተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ልዑካንን ጉዞ የማደራጀት ትልቅ መብት አግኝቻለሁ። እኔና ሊላ ፈጽሞ የማይረሱ በርካታ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት መብት አግኝተናል፤ ከእነዚህ አንዱ በ1989 በዋርሶ፣ ፖላንድ የተደረገው ስብሰባ ነው። በዚያ ስብሰባ ላይ ከሩሲያ የመጡ በርካታ ወንድሞች ተገኝተው ነበር፤ እንዲህ ባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው! አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች በእምነታቸው ምክንያት በሶቪየት ኅብረት እስር ቤቶች ውስጥ ለብዙ ዓመታት ታስረው ነበር።
በመላው ዓለም የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመጎብኘት የቤቴል ቤተሰብ አባላትንና ሚስዮናውያንን የማነጽ እንዲሁም የማበረታታት አስደሳች መብትም አግኝቻለሁ። በደቡብ ኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ባደረግነው የመጨረሻ ጉብኝታችን ወቅት ሱዎን ባለው እስር ቤት ውስጥ የነበሩ 50 ወንድሞቻችንን ማግኘት ችለን ነበር። ሁሉም አዎንታዊ አመለካከት የነበራቸው ሲሆን እንደገና በአገልግሎት የሚካፈሉበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ከእነሱ ጋር መገናኘታችን በጣም አበረታትቶናል!—ሮም 1:11, 12
እድገቱ ያስገኘልን ደስታ
እኔ በተጠመቅኩበት ወቅት ማለትም በ1943 የአስፋፊዎች ቁጥር 100,000 ገደማ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በ240 አገሮች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ8,000,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ፤ ይሖዋ ሕዝቦቹን በዚህ መንገድ ሲባርካቸው መመልከት ችያለሁ። ጊልያድ ተምረው የወጡ ሚስዮናውያን እንዲህ ያለ እድገት እንዲገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። አብዛኞቹ ሚስዮናውያን በውጭ አገር ወዳለው ምድባቸው እንዲሄዱ በመርዳት ለበርካታ ዓመታት ከእነሱ ጋር የመሥራት መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ!
ወጣት እያለሁ ቤቴል ገብቼ ይሖዋን ለማገልገል በመወሰኔ ደስተኛ ነኝ። ይሖዋ ያደረኩትን እያንዳንዱን ነገር አብዝቶ ባርኮልኛል። የቤቴል አገልግሎት ከሚያስገኘው ደስታ በተጨማሪ እኔና ሊላ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በብሩክሊን ከሚገኙ ጉባኤዎች ጋር አብሮ የማገልገል መብት አግኝተናል፤ በዚያም ብዙ እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት ችለናል።
አሁንም በቤቴል እያገለገልኩ ሲሆን የባለቤቴ የሊላ ድጋፍም አልተለየኝም። ዕድሜዬ ከ84 ዓመት በላይ ቢሆንም ከቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር ከሚደረገው የመልእክት ልውውጥ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ሥራ እያከናወንኩ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ።
አስደናቂ የሆነው የይሖዋ ድርጅት አባል መሆን እንዲሁም ይሖዋን በሚያገለግሉትና በማያገለግሉት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት መመልከት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው! ሚልክያስ 3:18 “እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ” ይላል፤ ይህን ጥቅስ ከምንጊዜውም ይበልጥ አሁን በግልጽ መረዳት ችለናል። በእያንዳንዱ ቀን፣ ይህ የሰይጣን ሥርዓት እየፈራረሰ እንዲሁም ተስፋ በሌላቸውና ደስታ በራቃቸው ሰዎች እየተሞላ ሲሄድ እያየን ነው። ይሖዋን የሚወዱና እሱን የሚያገለግሉ ሰዎች ግን በዚህ አስጨናቂ ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት ይመራሉ፤ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ ተስፋ አላቸው። የመንግሥቱን ምሥራች ማወጅ መቻላችን እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! (ማቴ. 24:14) የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ይህን አሮጌ ዓለም የሚያጠፋው ሲሆን ፍጹም ጤንነትና የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ አምላክ የገባልንን ቃል ጨምሮ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸማሉ፤ ሁላችንም ይህን ቀን በጉጉት እንጠባበቃለን። ያን ጊዜ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በዚህ ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ይኖራሉ።