ደግነት—በቃልና በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ
የደግነት ተግባር መንፈስን የማረጋጋትና የማጽናናት ኃይል አለው! የሚያስብልን ሰው እንዳለ ስናውቅ ልባችን በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። ሁላችንም ሌሎች በደግነት እንዲይዙን እንፈልጋለን፤ ታዲያ ይህን ማራኪ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
ደግነት ለሌሎች ደህንነት ልባዊ አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል፤ ይህ አሳቢነት ደግሞ ሌሎችን ለመርዳት ብለን በምንናገራቸው ቃላትና በምናደርገው ድርጊት ይገለጻል። ደግነት በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ስለሆነ ለታይታ ብሎ መልካም ምግባርና ትሕትና ከማሳየት የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። እውነተኛ ደግነት ለሌሎች ካለን ጥልቅ ፍቅርና ችግራቸውን እንደ ራሳችን ችግር አድርጎ ከመመልከት የሚመነጭ ባሕርይ ነው። ከዚህም በላይ እንዲህ ዓይነቱ ደግነት ክርስቲያኖች እንዲያዳብሩት የተነገራቸው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22, 23) ደግነት ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ከመሆኑ አንጻር ይሖዋና ልጁ ይህን ባሕርይ ያሳዩት እንዴት እንደሆነና እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን ጠቃሚ ነው።
ይሖዋ ለሁሉም ደግ ነው
ይሖዋ ‘የማያመሰግኑና ክፉዎችን’ ጨምሮ ለሁሉም ሰው ደግና አሳቢ ነው። (ሉቃስ 6:35) ለአብነት ያህል፣ ይሖዋ “በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል . . . በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:45) በመሆኑም የይሖዋን ፈጣሪነት አምነው የማይቀበሉ ሰዎችም እንኳ እሱ ሕይወት እንዲቀጥል ሲል በደግነት ተነሳስቶ ካደረጋቸው ዝግጅቶች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ በተወሰነ መጠን ደስታ ማግኘት ይችላሉ።
ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ያደረገላቸው ነገር ደግነቱን ግሩም በሆነ መንገድ ያሳያል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ “የበለስ ቅጠል በመስፋት የሚያሸርጡት ነገር ለራሳቸው ሠሩ።” ይሁን እንጂ ይሖዋ ከኤደን ገነት ወጥተው “እሾህና አሜኬላ” እንድታበቅል በተረገመች ምድር ላይ ለመኖር ተስማሚ ልብስ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። ስለዚህ በደግነት “ረጅም ልብስ ከቆዳ ሠርቶ” በማልበስ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አሟልቶላቸዋል።—ዘፍ. 3:7, 17, 18, 21
ምንም እንኳ ይሖዋ ‘ለክፉዎችም ሆነ ለጥሩዎች’ ደግ ቢሆንም በተለይ ደግሞ ለታማኝ አገልጋዮቹ ደግነት ማሳየት ይፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ በነቢዩ ዘካርያስ ዘመን አንድ መልአክ በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ግንባታ እንደተቋረጠ ሲመለከት በጣም አዝኖ ነበር። ይሖዋ መልአኩ ያሳሰበውን ነገር ሲናገር ያዳመጠው ከመሆኑም ሌላ “ደግነት በተሞላባቸውና በሚያጽናኑ ቃላት” መልስ ሰጥቶታል። (ዘካ. 1:12, 13) ይሖዋ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። በአንድ ወቅት ነቢዩ በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ይሖዋ እንዲገድለው ለምኖ ነበር። ይሖዋ ለኤልያስ ስሜት እንደሚያስብ በማሳየት አንድ መልአክ ልኮ አበረታታው። ከዚህም በላይ ብቻውን እንዳልቀረ በመንገር አጽናናው። ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ እነዚህን የሚያበረታቱ ቃላት ከነገረውና አስፈላጊውን እርዳታ ከሰጠው በኋላ ኤልያስ በነቢይነት ሥራው ለመቀጠል የሚያስችል ኃይል አግኝቷል። (1 ነገ. 19:1-18) ሆኖም ከአምላክ አገልጋዮች መካከል የይሖዋን ግሩም ደግነት ከሁሉ በላቀ መንገድ ያንጸባረቀው ማን ነው?
ኢየሱስ ታላቅ ደግነት አሳይቷል
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ደግና ርኅሩኅ በመሆኑ ይታወቅ ነበር። ኃይለኛ ወይም ሌሎችን የሚጫን ሰው አልነበረም። የሰዎችን ችግር እንደራሱ ችግር አድርጎ በመመልከት “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ደግ ስለነበር ሕዝቡ በሄደበት ሁሉ ይከተለው ነበር። ኢየሱስም ‘በጣም ስለሚያዝንላቸው’ ይመግባቸው፣ ሕመምተኞቻቸውን ይፈውስ እንዲሁም ስለ አባቱ “ብዙ ነገር” ያስተምራቸው ነበር።—ማር. 6:34፤ ማቴ. 14:14፤ 15:32-38
ኢየሱስ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት አስተዋይና የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ሰው መሆኑ ደግነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲያውም የተጠየቀው ነገር የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን እሱን ፈልገው የመጡትን ሁሉ “በደግነት” ይቀበላቸው ነበር። (ሉቃስ 9:10, 11) ለምሳሌ ያህል፣ ይፈስሳት በነበረው ደም ምክንያት በሕጉ መሠረት ርኩስ የነበረች አንዲት ሴት ፈውስ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ፈራ ተባ እያለች የልብሱን ጫፍ በነካች ጊዜ አልገሠጻትም። (ዘሌ. 15:25-28) ለ12 ዓመታት ስትሠቃይ ለነበረችው ለዚህች ሴት ርኅራኄ በማሳየት “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” ብሏታል። (ማር. 5:25-34) ይህ እንዴት ያለ ደግነት ነው!
ደግነት ለሌሎች መልካም ማድረግን ይጠይቃል
ከላይ የተገለጹት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት እውነተኛ ደግነት በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ የዚህን አስፈላጊነት አጉልቷል። በሳምራውያንና በአይሁዳውያን መካከል ጠላትነት የነበረ ቢሆንም በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሳምራዊ በመንገድ ላይ ዘራፊዎች ከገፈፉትና ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ትተውት ለሄዱት ሰው ራርቶለታል። በመሆኑም በደግነት ተነሳስቶ እርምጃ ወስዷል። የሰውየውን ቁስል ካከመለት በኋላ ወደ እንግዶች ማረፊያ ይዞት ሄደ። ከዚያም ሳምራዊው ለእንግዶች ማረፊያ ቤቱ ባለቤት የተጎዳውን ሰው ለማስታመም የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሰጠው ሲሆን ተጨማሪ ወጪ ካለ ሲመለስ እንደሚከፍለው ቃል ገባለት።—ሉቃስ 10:29-37
ደግነት ብዙውን ጊዜ የሚገለጸው በተግባር ቢሆንም አሳቢነትን በሚያሳዩና በሚያበረታቱ ቃላትም ሊገለጽ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” በማለት የሚናገረው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 12:25) በደግነትና በጥሩነት ተነሳስተን የሚያንጹ ሐሳቦችን በመናገር የሌሎችን መንፈስ ልናድስ እንችላለን።a የምንናገራቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ለሰዎቹ እንደምናስብላቸው ያሳያሉ። እነሱም ይህን ማወቃቸው ስለሚያበረታታቸው በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ የሚያስችል የተሻለ አቅም ይኖራቸዋል።—ምሳሌ 16:24
ደግነትን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
ሁሉም ሰዎች “በአምላክ መልክ” የተፈጠሩ በመሆናቸው ደግነት ማሳየት ይችላሉ። (ዘፍ. 1:27) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስን ወደ ሮም ይዞ እንዲሄድ የተመደበው ዩልዮስ የሚባል ሮማዊ የጦር መኮንን “ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት” ሲዶና ወዳሉት “ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት [ፈቅዶለታል]።” (ሥራ 27:3) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስና አብረውት የሚጓዙት ሰዎች የመርከብ መሰበር አደጋ ባጋጠማቸው ወቅት የማልታ ነዋሪዎች “የተለየ ደግነት” አሳይተዋቸዋል። እንዲያውም የደሴቲቷ ነዋሪዎች እሳት በማቀጣጠል ከአደጋው የተረፉት ሰዎች እንዲሞቁ አድርገዋል። (ሥራ 28:1, 2) እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ነገር የሚያስመሰግን ነው፤ ሆኖም ደግነት ማሳየት አልፎ አልፎ የደግነት ተግባር ከመፈጸም ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል።
አምላክን በተሟላ ሁኔታ ለማስደሰት ከፈለግን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ደግነት በማሳየት ይህን ባሕርይ የማንነታችን ክፍል ልናደርገው ይገባል። ይሖዋ ደግነትን ‘እንድንለብስ’ የሚመክረን ለዚህ ነው። (ቆላ. 3:12) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህን አምላካዊ ባሕርይ የማንነታችን ክፍል ማድረግ ቀላል አይደለም። ለምን? ዓይናፋርነት፣ በራስ ያለመተማመን ስሜት፣ ተቃውሞ አሊያም ውስጣችን የቀረ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ደግነት ከማሳየት ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ስለሚችል ነው። ያም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠንን እርዳታ በመቀበልና የይሖዋን የደግነት ምሳሌ በመከተል እነዚህን እንቅፋቶች ማሸነፍ እንችላለን።—1 ቆሮ. 2:12
ደግነት በማሳየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገን በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ሌሎች ችግራቸውን ሲነግሩኝ በትኩረት ለማዳመጥና ስሜታቸውን ለመረዳት እሞክራለሁ? ሌሎች በምን በኩል እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በንቃት እከታተላለሁ? የቤተሰቤ አባል ወይም የቅርብ ወዳጄ ላልሆነ ሰው ደግነት ካሳየሁ ምን ያህል ጊዜ ሆኖኛል?’ ከዚያም በዙሪያችን ስላሉት ሰዎች፣ በተለይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስላሉት ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ለማወቅ ግብ ማውጣት እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ስላሉበት ሁኔታና ስለሚያስፈልጋቸው ነገር እንድናውቅ ይረዳናል። በመቀጠል እኛ በእነሱ ቦታ ብንሆን ኖሮ ሌሎች ደግነት እንዲያሳዩን የምንፈልገው እንዴት እንደሆነ በማሰብ በዚያ መሠረት ደግነት ለማሳየት መጣር ይኖርብናል። (ማቴ. 7:12) በመጨረሻም ደግነት ለማሳየት የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን ይሖዋን በጸሎት መጠየቃችን አስፈላጊ ነው።—ሉቃስ 11:13
ደግነት ሌሎችን ይማርካል
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ አንድ የአምላክ አገልጋይ ለይተው የሚያሳውቁትን ነገሮች ሲዘረዝር ደግነትንም ጠቅሷል። (2 ቆሮ. 6:3-6) ጳውሎስ በድርጊቱም ሆነ በአነጋገሩ ለሰዎች ደግነት ያሳይ ስለነበር ሰዎች ወደ እሱ ይቀርቡ ነበር። (ሥራ 28:30, 31) እኛም ደግነት በማሳየት ሰዎችን ወደ እውነት መሳብ እንችላለን። የሚቃወሙንን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም ደግነት በማሳየት ልባቸውን ማራራትና በውስጣቸው ያለውን ጥላቻ ማስወገድ እንችላለን። (ሮም 12:20) እንዲያውም እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ይቀበሉ ይሆናል።
ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ከሞት የሚነሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ምናልባትም በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሌሎች እውነተኛ ደግነት ሲያሳዩአቸው ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት እንችላለን! እነዚህ ሰዎች በአመስጋኝነት ስሜት ከመሞላታቸው የተነሳ እነሱም ለሌሎች ደግነት ለማሳየት ይገፋፋሉ። በዚያን ጊዜ የሚኖር ማንኛውም ሰው ደግነት ለማሳየትና ሌሎችን ለመርዳት እምቢተኛ ቢሆን በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ቦታ አይኖረውም። በሌላ በኩል ደግሞ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ለዘላለም እንዲኖሩ የሚፈቀድላቸው ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና ደግነት ያሳያሉ። (መዝ. 37:9-11) በዚያን ጊዜ ዓለም ሙሉ በሙሉ የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ይሆናል! ሆኖም ደግነት ማሳየታችን በዛሬው ጊዜም እንኳ ጥቅም ያስገኝልናል።
ደግነት ማሳየት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
መጽሐፍ ቅዱስ “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 11:17) ሰዎች ደግ ወደሆነ ሰው መቅረብ የሚቀልላቸው ሲሆን እነሱም ብዙውን ጊዜ በምላሹ ደግነት ያሳዩታል። ኢየሱስ “በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል” ብሏል። (ሉቃስ 6:38) በመሆኑም ደግ ሰው በቀላሉ ጥሩ ወዳጆችን ማፍራትና ወዳጅነቱን ይዞ መቀጠል ይችላል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩ ክርስቲያኖችን “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” በማለት መክሯቸዋል። (ኤፌ. 4:32) የአንድ ጉባኤ አባላት እርስ በርስ የሚደጋገፉና ደግነት የሚያሳዩ እንዲሁም አንዳቸው የሌላውን ስሜት ለመረዳት ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ጉባኤው በእጅጉ ይጠቀማል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ሸካራ ቃላት ከመናገር እንዲሁም የሰላ ትችትና አሽሙር ከመሰንዘር ይቆጠባሉ። አንደበታቸውን ጎጂ ሐሜት ከማሰራጨት ይልቅ ሌሎችን ለማበረታታት ይጠቀሙበታል። (ምሳሌ 12:18) በዚህም የተነሳ ጉባኤው በመንፈሳዊ እየተጠናከረ ይሄዳል።
አዎ፣ ደግነት በቃልና በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ደግነት ስናሳይ አፍቃሪና ለጋስ የሆነውን የአምላካችንን የይሖዋን ባሕርይ እናንጸባርቃለን። (ኤፌ. 5:1) ይህም ጉባኤያችንን ለማጠናከርና ሌሎችን ወደ ንጹሕ አምልኮ ለመሳብ ያስችለናል። እንግዲያው ምንጊዜም ደግነት በማሳየት የምንታወቅ ሰዎች እንሁን!
a ጥሩነት ስለ አምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች በሚያብራራው በዚህ ባለ ዘጠኝ ክፍል ተከታታይ ርዕስ ላይ ወደፊት ይብራራል።