አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ይኑራችሁ
“አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማር. 10:9
1, 2. ዕብራውያን 13:4 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?
ይሖዋን ማክበር ትፈልጋላችሁ? እንደምትፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም! ደግሞም አምላክ ክብር የሚገባው ከመሆኑም ሌላ የሚያከብሩትን መልሶ እንደሚያከብር ቃል ገብቷል። (1 ሳሙ. 2:30፤ ምሳሌ 3:9፤ ራእይ 4:11) በተጨማሪም አምላክ ለሰዎች፣ ለምሳሌ ለመንግሥት ባለሥልጣናት አክብሮት እንድታሳዩ ይፈልጋል። (ሮም 12:10፤ 13:7) በተለይ ግን ከግል ሕይወታችሁ ጋር በተያያዘ አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነበት አንድ አቅጣጫ አለ። ይህም የጋብቻ ዝግጅት ነው።
2 ሐዋርያው ጳውሎስ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 13:4) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ስለ ጋብቻ ያለውን አስተያየት ለመናገር ያህል ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ክርስቲያን ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማሳየት እንዳለበት ማለትም ይህን ዝግጅት እንደ ውድ ነገር ሊመለከተው እንደሚገባ ለማሳሰብ ነው። እናንተስ ለጋብቻ ዝግጅት እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላችሁ? ባለትዳር ከሆናችሁ ደግሞ ለራሳችሁ ትዳር አክብሮት ታሳያላችሁ?
3. ኢየሱስ ጋብቻን አስመልክቶ ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ፈሪሳውያን ስለ ፍቺ በጠየቁት ጊዜ አምላክ የመጀመሪያውን ጋብቻ አስመልክቶ “ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” እንዳለ ነግሯቸዋል። አክሎም ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏቸዋል።—ማርቆስ 10:2-12ን አንብብ፤ ዘፍ. 2:24
4. ይሖዋ ለጋብቻ ያወጣው መሥፈርት ምንድን ነው?
4 በመሆኑም ኢየሱስ የጋብቻ መሥራች አምላክ እንደሆነና ይህ ጥምረት ዘላቂ ሊሆን እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገልጿል። አምላክ ጋብቻ በፍቺ ሊፈርስ እንደሚችል ለአዳምና ለሔዋን አልነገራቸውም። በኤደን ገነት ያቋቋመው ጋብቻ፣ ትዳር ሊመሠረት የሚገባው በሁለት ሰዎች መካከል ብቻ እንደሆነና ‘የሁለቱ’ ጥምረት እስከ መጨረሻው ሊዘልቅ እንደሚገባ ያሳያል።
የጋብቻ ጥምረት ያጋጠመው ጊዜያዊ ለውጥ
5. ሞት በጋብቻ ጥምረት ላይ ምን ለውጥ ያስከትላል?
5 ሆኖም አዳም የሠራው ኃጢአት በጋብቻ ዝግጅት ላይ አንዳንድ ለውጦችን እንዳስከተለ እናውቃለን። ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዱ ሞት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር እንዳልሆኑ ባብራራበት ወቅት የጻፈው ሐሳብ እንደሚያሳየው ሞት የጋብቻ ጥምረት እንዲፈርስ ያደርጋል። በመሆኑም በሕይወት ያለው ወገን ድጋሚ የማግባት ነፃነት ይኖረዋል።—ሮም 7:1-3
6. የሙሴ ሕግ አምላክ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት የሚያሳየው እንዴት ነው?
6 አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ ጋብቻን አስመልክቶ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። ለምሳሌ አምላክ ለእስራኤላውያን ሕጉን ከመስጠቱ በፊትም እንኳ ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ ተስፋፍቶ ነበር። ሕጉ ይህ ልማድ እንዲቀጥል ቢፈቅድም እንዲህ ባሉ ትዳሮች ውስጥ ሴቶችና ልጆች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከለላ ያደርግ ነበር። ለምሳሌ አንድ እስራኤላዊ አንዲትን ባሪያ ሚስቱ አድርጎ ቢወስድና ከጊዜ በኋላ ሁለተኛ ሚስት ቢያገባ የመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧ፣ ልብሷና የጋብቻ መብቷ እንዳይጓደልባት የማድረግ ግዴታ ነበረበት። አምላክ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላትና እንዲንከባከባት ይጠብቅበት ነበር። (ዘፀ. 21:9, 10) እኛ በሕጉ ሥር ባንሆንም ይሖዋ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት ከዚህ መረዳት እንችላለን። ይህን ማወቃችን ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት እንድናሳይ አያደርገንም?
7, 8. (ሀ) በዘዳግም 24:1 መሠረት ሕጉ ፍቺን አስመልክቶ ምን ይላል? (ለ) ይሖዋ ለፍቺ ምን አመለካከት አለው?
7 ሕጉ ፍቺን በተመለከተስ ምን ይላል? አምላክ ለጋብቻ የሚሰጠው ከፍ ያለ ግምት ባይለወጥም እስራኤላውያን ፍቺ እንዲፈጽሙ ፈቅዶላቸዋል። (ዘዳግም 24:1ን አንብብ።) አንድ እስራኤላዊ በሚስቱ ላይ “ነውር የሆነ ነገር [ካገኘባት]” ሊፈታት ይችላል። ሕጉ “ነውር” ተብሎ የሚቆጠረው ነገር ምን እንደሆነ አይገልጽም። ሆኖም ጉዳዩ ተራ ነገር ሳይሆን አሳፋሪ ወይም ከባድ ጉዳይ እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ዘዳ. 23:14) የሚያሳዝነው ግን በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን “በማንኛውም ምክንያት” ፍቺ ይፈጽሙ ነበር። (ማቴ. 19:3) እኛ እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበር እንደማንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም።
8 ነቢዩ ሚልክያስ አምላክ ለፍቺ ምን አመለካከት እንዳለው ግልጽ አድርጓል። በወቅቱ የነበሩ በርካታ ወንዶች ይሖዋን የማያመልኩ ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሲሉ ክህደት በመፈጸም ‘የወጣትነት ሚስታቸውን’ ይፈቱ ነበር። አምላክ “እኔ ፍቺን እጠላለሁ” በማለት ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት በግልጽ ተናግሯል። (ሚል. 2:14-16) ይህም የአምላክ ቃል የመጀመሪያውን ጋብቻ አስመልክቶ ‘ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ በማለት ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ዘፍ. 2:24) ኢየሱስም “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” በማለት የአባቱን አመለካከት እንደሚጋራ አሳይቷል።—ማቴ. 19:6
ለፍቺ መሠረት የሚሆነው ብቸኛው ምክንያት
9. ኢየሱስ በማርቆስ 10:11, 12 ላይ የተናገረውን ሐሳብ ልንረዳው የሚገባው እንዴት ነው?
9 ሆኖም ‘አንድ ክርስቲያን ፍቺ መፈጸምና ድጋሚ ማግባት የሚችልበት መሠረት ይኖረው ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ኢየሱስ ለፍቺ ያለውን አመለካከት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በማመንዘር ሚስቱን ይበድላል፤ አንዲት ሴትም ብትሆን ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።” (ማር. 10:11, 12፤ ሉቃስ 16:18) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት የነበረው ሲሆን ሌሎችም የእሱ ዓይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ ይፈልጋል። አንድ ወንድ የሆነ ሰበብ ፈልጎ ታማኝ የሆነች ሚስቱን ከፈታ በኋላ ሌላ ቢያገባ ምንዝር እንደፈጸመ ይቆጠራል። (ታማኝ የሆነ ባሏን ከምትፈታ ሴት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።) ይህ መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ስለፈታ ብቻ የጋብቻ ጥምረቱ አይፈርስም። አሁንም ቢሆን ሁለቱ ሰዎች በአምላክ ዓይን “አንድ ሥጋ” ናቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ አንድ ሰው ታማኝ የሆነች ሚስቱን መፍታቱ ሚስቱን ምንዝር ለመፈጸም እንደሚያጋልጣት ተናግሯል። እንዴት? በዚያ ዘመን የነበረች ከባሏ የተፋታች አንዲት ሴት ቁሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ስትል ድጋሚ ለማግባት ትገደድ ይሆናል። እንዲህ ያለው ጋብቻ ደግሞ ምንዝር እንደመፈጸም ይቆጠራል።
10. አንድ ክርስቲያን ፍቺ መፈጸምና ድጋሚ ማግባት የሚችልበት ብቸኛው ምክንያት ምንድን ነው?
10 ኢየሱስ የጋብቻ ጥምረትን ለማፍረስ መሠረት የሚሆነው ምን እንደሆነ ተናግሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና [ግሪክኛ፣ ፖርኒያ] ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” (ማቴ. 19:9) ኢየሱስ በተራራው ስብከቱም ላይ ይህንኑ ነገር ተናግሯል። (ማቴ. 5:31, 32) በሁለቱም ወቅቶች ኢየሱስ ‘የፆታ ብልግናን’ ጠቅሷል። ይህ አገላለጽ ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸሙ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ኃጢአቶችን ያመለክታል፤ ይህም ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከእንስሳ ጋር የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ያካትታል። አንድ ሰው የፆታ ብልግና ከፈጸመ ሚስቱ እሱን ለመፍታት ወይም ላለመፍታት ልትወስን ትችላለች። ሚስቱ ልትፈታው ከወሰነች ጋብቻው በአምላክ ዓይን እንደፈረሰ ይቆጠራል።
11. አንድ ክርስቲያን ለመፋታት የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ቢኖረውም ላለመፋታት የሚወስነው ለምን ሊሆን ይችላል?
11 ኢየሱስ አንድ ሰው የፆታ ብልግና (ፖርኒያ) ከፈጸመ የግድ ከሚስቱ ጋር መፋታት አለበት እንዳላለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሚስት ባለቤቷ የሥነ ምግባር ብልግና ቢፈጽምም ትዳራቸውን ላለማፍረስ ትወስን ይሆናል። ይህን ውሳኔ የምታደርገው ባሏን ስለምትወደው እንዲሁም ይቅርታ ለማድረግና በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ፈቃደኛ ስለሆነች ሊሆን ይችላል። ደግሞም ባሏን ከፈታችው በኋላ ሳታገባ ብትኖር ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟት ግልጽ ነው። ለምሳሌ ቁሳዊና ፆታዊ ፍላጎቷን ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው? ብቸኝነት ቢሰማትስ? ልጆች ካሏቸው ደግሞ ውሳኔዋ በእነሱ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ከባሏ ጋር መፋታቷ ልጆቻቸውን በእውነት ቤት ውስጥ ማሳደግ ከባድ እንዲሆንባት ያደርጋል? (1 ቆሮ. 7:14) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በደል የተፈጸመበት ወገን ለመፋታት መወሰኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ሊያስከትልበት ይችላል።
12, 13. (ሀ) በሆሴዕ ትዳር ውስጥ ምን ተከስቶ ነበር? (ለ) ሆሴዕ ጎሜርን መልሶ የወሰዳት ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮች ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት ያገኛሉ?
12 ነቢዩ ሆሴዕ ካጋጠመው ነገር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አምላክ ጎሜር የተባለችን “ዝሙት አዳሪ ሴት [እንዲያገባ]” ሆሴዕን አዘዘው፤ በተጨማሪም ‘እሷ በምትፈጽመው ምንዝር ልጆች እንደሚወለዱለት’ ነገረው። ጎሜር ‘ፀንሳ’ ለሆሴዕ ‘ወንድ ልጅ ወለደችለት።’ (ሆሴዕ 1:2, 3) ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሁለቱም የተወለዱት በምንዝር ሳይሆን አይቀርም። ሆሴዕ ሚስቱ በተደጋጋሚ ምንዝር ብትፈጽምበትም ትዳሩ እንዲፈርስ አላደረገም። በመጨረሻም ጎሜር ሆሴዕን ጥላው በመሄድ ባሪያ ሆነች። ያም ቢሆን ሆሴዕ መልሶ ገዛት። (ሆሴዕ 3:1, 2) ይሖዋ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ምንዝር ቢፈጽሙበትም ይቅር እንዳላቸው ለማሳየት የሆሴዕን ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። እኛስ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
13 የአንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ የፆታ ብልግና ከፈጸመ በደል የተፈጸመበት ክርስቲያን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ያጋጥመዋል። ኢየሱስ ታማኝ የሆነው ወገን ፍቺ ለመፈጸምና ድጋሚ ለማግባት የሚያስችል መሠረት እንዳለው ተናግሯል። በሌላ በኩል ግን በደል የተፈጸመበት ወገን ይቅርታ ለማድረግ ሊወስን ይችላል። ይህ ውሳኔ ስህተት አይደለም። ሆሴዕ ጎሜርን መልሶ አምጥቷታል። ተመልሳ ከመጣች በኋላ ግን ከሌላ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም አትችልም ነበር። ሆሴዕ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከጎሜር ጋር ‘ግንኙነት አልፈጸመም።’ (ሆሴዕ 3:3) ከጊዜ በኋላ ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ጀምሮ መሆን አለበት፤ ይህም አምላክ ሕዝቦቹን መልሶ ለመቀበልና ከእነሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመቀጠል ያለውን ፈቃደኝነት ያንጸባርቃል። (ሆሴዕ 1:11፤ 3:3-5) ይህ ታሪክ በዛሬው ጊዜ ላሉ ባለትዳሮች ምን ትምህርት ይዟል? አንድ ክርስቲያን በደል ከፈጸመበት የትዳር ጓደኛው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን መቀጠሉ ለትዳር ጓደኛው ይቅርታ እንዳደረገለት ያሳያል። (1 ቆሮ. 7:3, 5) ሁለቱ ሰዎች ግንኙነት መፈጸማቸው ለፍቺ መሠረት የሆነው ነገር እንዲወገድ ያደርጋል። በመሆኑም ከዚያ በኋላ እርስ በርስ በመደጋገፍ አምላክ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜም ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማሳየት
14. አንደኛ ቆሮንቶስ 7:10, 11 ላይ እንደተገለጸው በጋብቻ ውስጥ ምን ሊያጋጥም ይችላል?
14 ሁሉም ክርስቲያኖች የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ለማሳየት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይሁንና የሰው ልጆች ፍጽምና የጎደላቸው ስለሆኑ አንዳንዶች እንዲህ ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። (ሮም 7:18-23) ከዚህ አንጻር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በጋብቻቸው ውስጥ ችግር አጋጥሟቸው የነበረ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ጳውሎስ “ሚስት ከባሏ አትለያይ” ሲል ጽፎ ነበር፤ ሆኖም ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያላደረጉ ባለትዳሮች ነበሩ።—1 ቆሮንቶስ 7:10, 11ን አንብብ።
15, 16. (ሀ) በትዳር ውስጥ ችግሮች ቢያጋጥሙም የባለትዳሮቹ ግብ ምን ሊሆን ይገባል? ለምንስ? (ለ) አንደኛው የትዳር ጓደኛ የማያምን በሚሆንበት ጊዜ ይህ ምክር የሚሠራው እንዴት ነው?
15 ጳውሎስ እነዚህ ባለትዳሮች የተለያዩት በምን ምክንያት እንደሆነ አልገለጸም። ሆኖም ባልየው የፆታ ብልግና ፈጽሞ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ይህ ቢሆን ኖሮ ሚስትየው ለመፋታትና ድጋሚ ለማግባት የሚያስችል መሠረት ይኖራት ነበር። ጳውሎስ ከባሏ ጋር የተለያየች ሚስት ‘ሳታገባ መኖር ወይም ከባሏ ጋር መታረቅ’ እንዳለባት ጽፏል። በመሆኑም ሁለቱ በአምላክ ዓይን አሁንም የተጣመሩ ናቸው ማለት ነው። ጳውሎስ የተፈጠረው ችግር ምንም ይሁን ምን የፆታ ብልግና እስካልተፈጸመ ድረስ የሁለቱ ሰዎች ግብ መታረቅ መሆን እንዳለበት መክሯል። ለዚህ የሚረዳቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለማግኘት የጉባኤ ሽማግሌዎችን ሊጠይቁ ይችላሉ። ሽማግሌዎች የትኛውንም ወገን ሳይደግፉ ለባልና ሚስቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሊሰጧቸው ይገባል።
16 ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ጥረት የሚያደርገው አንደኛው የትዳር ጓደኛ ብቻ ከሆነ ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ሊሆን ይችላል። ታዲያ እንዲህ ባሉ ትዳሮች ውስጥ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ መለያየት ተገቢ ነው? ቀደም ሲል እንደተገለጸው ቅዱሳን መጻሕፍት የፆታ ብልግና ለፍቺ መሠረት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፤ ሆኖም ለመለያየት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉት የትኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ አይዘረዝሩም። ጳውሎስ “አንዲት ሴት አማኝ ያልሆነ ባል ካላትና ባሏ አብሯት ለመኖር ከተስማማ አትተወው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 7:12, 13) ይህ ምክር ለዘመናችንም ይሠራል።
17, 18. አንዳንድ ክርስቲያኖች በትዳራቸው ውስጥ ችግር ቢያጋጥማቸውም ላለመለያየት የወሰኑት ለምንድን ነው?
17 አንዳንድ ጊዜ ግን አንድ “አማኝ ያልሆነ ባል” ከሚስቱ ጋር ‘አብሮ ለመኖር እንደማይስማማ’ የሚያሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በሚስቱ ላይ ከባድ አካላዊ ጥቃት ከማድረሱ የተነሳ ሚስቱ ጤንነቷ ወይም ሕይወቷ አደጋ ላይ እንደወደቀ ሊሰማት ይችላል። አሊያም ደግሞ ባልየው ለእሷም ሆነ ለቤተሰቡ ቁሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ላይሆን ወይም መንፈሳዊነቷን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛቸው አብሮ መኖር እንደሚፈልግ ቢናገርም ድርጊቱ ‘አብሮ ለመኖር እንዳልተስማማ’ ስለሚያሳይ ለመለያየት የራሳቸውን ውሳኔ አድርገዋል። ሌሎች ክርስቲያኖች ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ከባድ ችግር ቢያጋጥማቸውም ከመለያየት ይልቅ ችግሩን ተቋቁመው መኖርና ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ወስነዋል። ለምን?
18 አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ባለ ምክንያት ቢለያዩም ይህ ትዳራቸውን አያፈርሰውም። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ተለያይተው መኖራቸው ሁለቱም ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲያጋጥሟቸው ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ባለትዳሮች አብረው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ጠቅሷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አማኝ ያልሆነ ባል ከሚስቱ ጋር ባለው ዝምድና የተነሳ ተቀድሷል . . . አማኝ ያልሆነች ሚስትም ከወንድም ጋር ባላት ዝምድና የተነሳ ተቀድሳለች፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው።” (1 ቆሮ. 7:14) የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች በጣም ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ላለመለያየት ወስነዋል። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ፣ ባሳዩት ጽናት የተነሳ የትዳር ጓደኛቸው የኋላ ኋላ ይሖዋን ማምለክ እንደጀመረ ተመልክተዋል፤ ይህም ባደረጉት ውሳኔ ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:16ን አንብብ፤ 1 ጴጥ. 3:1, 2
19. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በርካታ ስኬታማ ትዳሮች ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው?
19 ኢየሱስ ለፍቺ ምን አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ተናግሯል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ መለያየትን አስመልክቶ በመንፈስ መሪነት ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል። የሁለቱም ዓላማ የአምላክ አገልጋዮች የጋብቻ ዝግጅትን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳት ነው። በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ስኬታማ ትዳር ያላቸው በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። በጉባኤያችሁ ውስጥም እንዲህ ያሉ ባለትዳሮች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ባሎች ታማኞችና ሚስቶቻቸውን የሚወዱ ስለሆኑ ሚስቶችም አፍቃሪና ባሎቻቸውን የሚያከብሩ ስለሆኑ ነው። እነዚህ ጥንዶች ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማሳየት እንደሚቻል ያረጋግጣሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት እውነት መሆናቸውን በገዛ ሕይወታቸው እያሳዩ ስላሉ በጣም ደስተኞች ነን፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።”—ኤፌ. 5:31, 33