ሌሎች ወደ ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ እርዷቸው
1 ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ማግኘታቸው የአምላክ ፈቃድ መሆኑን’ ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። (1 ጢሞ. 2:4) ሌሎች ሰዎች ይህን እውቀት እንዲቀስሙ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? አንዱ መንገድ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ስናነጋግራቸው ፍላጎታቸው ተነሣስቶ ለነበሩት ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ነው። ይህ ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግልጽ፣ ቀላልና በደንብ ታስቦባቸው በተመረጡ ቃላት ያብራራል። ሁሉም ዓይነት ሰዎች ይህን መጽሐፍ በማጥናት ወደ ሕይወት ጎዳና ሊያመሩ ይችላሉ። ሰዎች ከእኛ ጋር መጽሐፉን እንዲያጠኑ ለማበረታታት ምን ልንል እንችላለን?
2 መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ መመሪያ ነው የሚለውን ሐሳብ ተመርኩዘህ አነጋግረሃቸው ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች እንደሚከተለው በማለት ጥናት እንዲጀምሩ ልትጋብዛቸው ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ እዚህ በመጣሁበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ይገኝበታል ብለን እምነት ልንጥልበት የምንችለው ለምን እንደሆነ ተነጋግረን ነበር። ከክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ እንደጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ በመሆኑ የመጽናኛና የተስፋ ምንጭ ነው። [ሮሜ 15:4ን አንብብ።] ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት መጨረሻ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው እውቀት በግል መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ አንስቼ ነበር።” እውቀት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 11 አንቀጽ 18 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አንብብ። የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት በዓለም ዙሪያ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ላይ እንዳሉ ጥቀስ። በምዕራፍ 1 ውስጥ የሚገኙትን የመጀመሪያ አምስት አንቀጾች በመጠቀም ጥናት የሚመራው እንዴት እንደሆነ በአጭሩ ልታሳየው እንደምትፈልግ ግለጽለት።
3 በመጀመሪያ የተወያያችሁት ጸሎትን በተመለከተ ከነበረ ጥናት ለማስጀመር የሚከተለውን አቀራረብ ልትሞክር ትችል ይሆናል:-
◼ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ ስለ ጸሎት በተወያየነው ነገር እንደተደሰቱ ተስፋ አደርጋለሁ። ወደ አምላክ የሚጸልዩ ሰዎች በተራቸው እርሱን ሊያዳምጡ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተመልሼ ስመጣ እንደምንወያይ ቃል ገብቼልዎት ነበር። በገጽ 158 ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ልብ ይበሉ። [አንቀጽ 18ን አንብብ።] እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን በማጥናት አምላክ የሚነግረንን ማዳመጥ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ ወደ አምላክ የሚያቀርበን ከመሆኑም በላይ በጸሎታችን ውስጥ የምንጠቅሳቸውን የዕለት ተዕለት ችግሮች ለመቋቋም ያስችለናል። ከእርስዎ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ባጠና ደስ ይለኛል።” ግለሰቡ ፈቃደኛ ከሆነ ጥናቱን እውቀት በተባለው መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጀምሩ።
4 ጥናት ለማስጀመር ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመህ ከነበረ በመጀመሪያው ውይይታችሁ ለመቀጠል እንደሚከተለው ማለት ትችል ይሆናል:-
◼ “በነፃ ስለሚደረገው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ተጨማሪ ነገሮችን ልነግርዎ ስለፈለግሁ ወደ እርስዎ ተመልሼ ለመምጣት ልዩ ጥረት አድርጌአለሁ። ለጥናቱ የሚረዳንን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን የዚህን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ትቼልዎት ነበር። የአምላክን ቃል እንድናጠና እንዴት እንደሚያበረታታን ልብ ይበሉ። [በገጽ 22 አንቀጽ 23 ላይ ያለውን ሐሳብ አንብብ።] የራስዎን ቅጂ ሊያመጡት የሚችሉ ከሆነ ባለፈው ጊዜ ካቆምንበት ቀጥለን ማጥናት እንችላለን።” በመጀመሪያው ውይይታችሁ ወቅት ጥናት ካልጀመራችሁ “ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደምናጠና ለማሳየት ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሳይሆን አይቀርም” ልትል ትችል ይሆናል። ጥቂት አንቀጾች ላይ ከተወያያችሁ በኋላ ለሚቀጥለው ጥናት ተመልሰህ የምትመጣበትን የተወሰነ ቀጠሮ ያዝ።
5 እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀማችን ለሌሎች ሰዎች በረከት የሚሆነውን ትክክለኛ እውቀት ለማሰራጨት ያስችለናል። (ምሳሌ 15:7) ይህ እውቀት ቀና ልብ ላላቸው ሰዎች የደስታ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ የሚገፋፋ ኃይል ስለሚሆናቸው ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራቸዋል።