በእምነታቸው ምሰሏቸው
1 ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትን እንደሚከተለው ሲል ገልጾታል:- “እምነትም ተስፋ ስለምናደረገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” በመጨመርም “ያለ እምነት [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም” ብሏል። (ዕብ. 11:1, 6) ጳውሎስ እምነት እንዲኖረን፣ እንዲበዛልንና እምነትን እንድንከተል አጥብቆ መክሮናል።— 2 ቆሮ. 4:13፤ ቆላ. 2:7 አዓት፤ 2 ጢሞ. 2:22
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስደናቂ የሆኑ ብዙ የእምነት ምሳሌዎች ተዘርዝረው እናገኛለን። ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የማያወላውል እምነት ያሳዩ የብዙ ሰዎችን ስም ዝርዝር ጠቅሷል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ለእምነቱ ሲል የመጀመሪያ ሰማዕት የሆነው አቤል ይገኝበታል። ኖኅም ቤተሰዎቹን ለማዳን የሚያስፈልገውን አምላካዊ ፍርሃት በእምነት በማሳየቱ ተጠቅሷል። አብርሃም ባሳየው እምነትና ታዛዥነት ተመስግኗል። ሙሴ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በእምነት በመጽናቱ ሊመሰገን በቅቷል። ምሳሌ የሚሆኑት ሰዎች በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ጳውሎስ የሁሉንም ስም ለመዘርዘር ጊዜ እንደማይበቃው ተናግሯል። ‘ቅዱስ ኑሯቸውንና ለአምላክ በማደር ያደረጓቸውን ነገሮች’ መለስ ብለን በመመርመር እምነታችንን ማጠናከር በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!— 2 ጴጥ. 3:11
3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ አምነትን ያገኝ ይሆንን?” የሚል ጥያቄ አንሥቶ ነበር። (ሉቃስ 18:8) ታዲያ በመካከላችንስ ሕያው የሆኑ የእምነት ምሳሌዎች አሉን? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት እንደነበሩት እውነተኛ የአምላክ ሕዝቦች ሁሉ ዛሬም አረጋውያንም ሆኑ ወጣቶች በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች አሉን?
4 የዘመናችን የእምነት ምሳሌዎች፦ በመካከላችን ግሩም የእምነት ምሳሌዎች አሉልን! ቀዳሚ ሆነው የሚያገለግሉት በመካከላችን ያሉት የበላይ ተመልካቾች የሚያሳዩት እምነት ልንከተለው የሚገባ ነው። (ዕብ. 13:7) ይሁን እንጂ የእምነት ምሳሌ የሆኑት እነርሱ ብቻ አይደሉም። በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ እምነት የሚጣልባቸው ሆነው ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ አብዛኛውን ጊዜም ይህን ያከናወኑት በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ነው።
5 ከተቃዋሚ ባሎቻቸው የሚደርስባቸውን ተቃውሞ ለብዙ ዓመታት ተቋቁመው የጸኑትን የታመኑ እህቶቻችንን ልናደንቃቸው ይገባል። ነጠላ ወላጆች ብቻቸውን ሆነው ልጆችን ለማሳደግ የሚገጥማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታን ለመጋፈጥ ተገደዋል። የሚረዳቸው ቤተሰብ ባይኖራቸውም ከማንኛውም የጉባኤ እንቅስቃሴ ቀርተው የማያውቁ በዕድሜ የገፉ መበለቶች በመካከላችን ይገኛሉ። (ከሉቃስ 2:37 ጋር አወዳድር።) ጽናት የሚጠይቅ ከባድ የጤንነት ችግር ያለባቸው ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩት እምነት የሚደነቅ ነው። ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል ሁኔታቸው የማይፈቅድላቸው ቢሆንም እንኳ በታማኝነት ማገልገላቸውን የቀጠሉ ብዙ ናቸው። በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ተቃውሞ ቢደርስባቸውም በድፍረት እምነት ያሳዩ ወጣቶች አሉ። በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ከዓመት ወደ ዓመት በጽናት የሚያገለግሉትን የታመኑ አቅኚዎች ስንመለከት ለአምላክ የማደር ባሕሪያችን ይጠነክራል። በመንግሥቱ አገልግሎት የተገኙትን ተሞክሮዎች ሁሉና እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያደረጓቸውን ነገሮች እንዘርዝር ብንል እንደ ጳውሎስ ጊዜ አይበቃንም!
6 እነዚህ ምሳሌ የሆኑ ታማኝ ሰዎች መጽናኛና መበረታቻ ይሆኑናል። (1 ተሰ. 3:7, 8) “የታመኑ ሆነው የሚመላለሱ በይሖዋ ዘንድ የተወደዱ” ናቸውና እነርሱን በእምነታቸው መምሰላችን መልካም ነው።— ምሳሌ 12:22 አዓት