ለመስበክ ብቁ የሆነው ማን ነው?
1 አገልግሎትን በተመለከተ ሙሴ የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? እርሱ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እባክህ ጌታ ሆይ! ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርህበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።” (ዘጸ. 4:10 የ1980 ትርጉም) እንዲህ ያለው ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ወደ ኋላ እንድትል ሊያደርግህ ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ‘ለሕዝብ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዞናል።’ (ሥራ 10:42) ታዲያ ብቁ የምሥራቹ ሰባኪዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
2 ለአገልግሎት ብቁዎች እንድንሆን የሚያስችለን በዓለም ያካበትነው የትምህርት ደረጃ አይደለም። ጳውሎስ “እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ . . .” አልተጠሩም ከማለቱም በተጨማሪ “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 1:26፤ 3:19) ኢየሱስ ሐዋርያቱን የመረጠው ዝቅተኛ ሥራ ከነበራቸው ሰዎች መካከል ነበር። ከእነዚህም መካከል ቢያንስ አራቱ ዓሣ በማጥመድ ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ። ኩሩዎቹ የሃይማኖት መሪዎች “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች” አድርገው በንቀት ይመለከቷቸው ነበር። ሐዋርያት ዓለም በሚያወጣው የአቋም መስፈርት ሲመዘኑ ለመስበክ ብቃት ያላቸው አልነበሩም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ባቀረበው የተዋጣለት ንግግር 3,000 ሰዎች እንዲጠመቁ አነሳስቷል!— ሥራ 2:14, 37-41፤ 4:13
3 ለመስክ ብቁ እንድንሆን ያደረገው ይሖዋ ነው። ጳውሎስ “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው” በማለት ገልጿል። (2 ቆሮ. 3:5) የጥበብ ምንጭ የሆነው ይሖዋ የመንግሥቱን እውነት ለሌሎች እንዲሰብኩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስተምሯል። (ኢሳ. 54:13) የዚህ ሥራ ውጤታማነትና ፍሬያማነት ባለፈው ዓመት በተጠመቁት 338,491 ‘የምስጋና ደብዳቤዎች’ ሊረጋገጥ ችሏል። (2 ቆሮ. 3:1-3) ከይሖዋ ስለተማርናቸው ነገሮች በድፍረትና በጽኑ እምነት ለመስበክ የሚያስችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉን።
4 የአምላክ ድርጅት ለአገልጋዮቹ የሚሆን ዓለም አቀፋዊ የማሠልጠኛ መርሐ ግብር አቋቁሟል። በቅዱሳን ጽሑፎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማካሄድ በሚረዱ የተለያዩ ጽሑፎች አማካኝነት ለስብከቱ ሥራ ‘የተሟላ ችሎታና ትጥቅ’ እንዲኖረን ትምህርትና ሥልጠና አግኝተናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ብዙ ሰዎች የማኅበሩ ጽሑፎች እውቀት ባላቸው ጥልቅ ትምህርቶች በጣም ተደንቀዋል። ለምሳሌ በስዊድን እየታተመ የሚወጣ አንድ መጽሔት “የይሖዋ ምሥክሮች ከሚሰብኩት እምነት በስተኋላ አስደናቂ የሆነ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት አለ” በማለት አትቷል።
5 በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት በምናገኘው መመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት በምናወጣው ፕሮግራም፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚሰጠን ምክር፣ በአገልግሎት ተሞክሮ ያካበቱ በሚሰጡን የግል እርዳታና ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በሚሰጠን ድጋፍ ይሖዋ በተሟላ መንገድ ለስብከት ብቁዎች እንድንሆን አድርጎ እንደሚመለከተን ልንተማመን እንችላለን። “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።”— 2 ቆሮ. 2:17
6 አምላክ በድርጅቱ በኩል የሚሰጠን ቲኦክራሲያዊ ማሠልጠኛዎች ሙሉ በሙሉ ከተጠቀምንባቸው ወደ ኋላ የምንልበት ወይም የምንፈራበት ምንም ምክንያት አይኖረንም። ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን በመተማመን ለሌሎች ሰዎች በደስታ ለመስበክ እንችላለን።— 1 ቆሮ. 3:6