የጥያቄ ሳጥን
◼ ኒው ዮርክ ውስጥ በብሩክሊን፣ በፓተርሰንና በዎልኪል እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉትን የቅርንጫፍ ቢሮዎች ስንጎበኝ ለአለባበሳችንና ለፀጉር አያያዛችን ልዩ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?
ክርስቲያኖች ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን አለባበሳችንና የፀጉር አያያዛችን የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ጨዋና የተከበሩ መሆናቸውን የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል። በተለይ በኒው ዮርክና በዓለም ዙሪያ ያሉትን የማኅበሩን ቢሮዎች ስንጎበኝ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ልንሰጠው ይገባናል።
በ1998 የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። ከተለያዩ የምድር ክፍሎች የሚመጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን በኒው ዮርክ የሚገኘውን የማኅበሩን ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በሌሎች አገሮች የሚገኙትን የቅርንጫፍ ቢሮዎች ይጎበኛሉ። እነዚህን ቢሮዎች ስንጎበኝ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ራሳችንን በሥርዓታማ አለባበስና የፀጉር አያያዝ ጭምር ‘የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉ በኩል የምንገልጥ’ መሆን አለብን።—2 ቆሮ. 6:3, 4 የ1980 ትርጉም
አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለ ሥርዓታማ አለባበስና ጥሩ የፀጉር አያያዝ አስፈላጊነት በሚናገረው ንዑስ ርዕስ ስር በመስክ አገልግሎት ስንካፈልም ሆነ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስንሄድ አካላዊ ንጽሕናን እንዲሁም የሥርዓታማ አለባበስንና የፀጉር አያያዝን አስፈላጊነት ይናገራል። በተጨማሪም በገጽ 131 አንቀጽ 2 ላይ እንዲህ ይላል:- “በብሩክሊን ወይም በማንኛውም የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘውን ቤቴል ስንጎበኝም ሁኔታችን ልክ ከላይ እንደተገለጸው መሆን አለበት። ቤቴል የሚለው ቃል “የአምላክ ቤት” ማለት መሆኑን አስታውሱ። ስለዚህ ወደ ቤቴል ስንሄድ ልብሳችን፣ ፀጉራችንና ጠባያችን በመንግሥት አዳራሹ ወደሚደረገው ስብሰባ ለአምልኮ ስንሄድ እንድናሳየው ከሚጠበቅብን ጋር አንድ ዓይነት መሆን ይገባዋል።” ከቅርብም ሆነ ራቅ ካለ አካባቢ ቤቴልን ለመጎብኘት ወይም የቤቴል ቤተሰቦችን ለመጠየቅ የሚመጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከላይ የተጠቀሰውን የአቋም ደረጃ ማሟላት አለባቸው።
አለባበሳችን ሌሎች ሰዎች ለይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ጥሩ አመለካከት የሚያሳድርባቸው መሆን ይገባዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የማኅበሩን ቢሮዎች ሲጎበኙ አለባበሳቸው ከመጠን በላይ ግዴለሽነትን እንደሚያሳይ ተስተውሏል። በየትም አገር የሚገኙትን የቤቴል ቤቶች ስንጎበኝ እንዲህ ዓይነቱ አለባበስ ተገቢ አይደለም። እንደ ሌሎች ክርስቲያናዊ የሕይወት ዘርፎች ሁሉ በዚህ ጉዳይም ማንኛውንም ነገር ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ በማድረጋችን የአምላክን ሕዝቦች ከዓለም ልዩ የሚያደርጋቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃ እንከተላለን። (ሮሜ 12:2፤ 1 ቆሮ. 10:31) ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንም ሆነ ቤቴልን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚጎበኙ ሌሎች ሰዎች ሥርዓታማ አለባበስና የፀጉር አያያዝ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሆነ ብንነግራቸው ተገቢ ነው።
ስለዚህ የማኅበሩን ቢሮዎች ስትጎበኝ እንዲህ በማለት ራስህን ጠይቅ:- ‘አለባበሴና የፀጉር አያያዜ ሥርዓታማ ነውን?’ (ከሚክያስ 6:8 ጋር አወዳድር።) ‘የማመልከውን አምላክ በትክክል ያንጸባርቃልን? በአለባበሴና በፀጉር አያያዜ ሥርዓታማ አለመሆን ሌሎች ይሰናከሉ ወይም ቅር ይሰኙ ይሆን? ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚጎበኙ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ መሆን እችላለሁን?’ ዘወትር በአለባበሳችንም ሆነ በፀጉር አያያዛችን ‘ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር የምናስመሰግን’ እንሁን።—ቲቶ 2:10