ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መመሥከር
1. ከቤት ወደ ቤት ከሚደረገው አገልግሎት ጋር ተያይዞ ምን ጥያቄ ይነሳል? ለምንስ?
1 “በአሁኑ ጊዜ እውነትን ለመስበክ እጅግ ውጤታማ የሆነው ዘዴ ሚሌኒያል ዶውን የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው የስብከት ዘመቻ እንደሆነ እውነትን በተለያዩ መንገዶች በማሰራጨቱ ሥራ ተሞክሮ ያላቸው [ክርስቲያኖች] ይስማማሉ።” የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በሐምሌ 1, 1893 (እንግሊዝኛ) እትሙ ላይ ያወጣው ይህ ሐሳብ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ያለውን ጠቀሜታ አጉልቶ ያሳያል። በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክን የይሖዋ ምሥክሮች መለያ ምልክት አድርገው ይመለከቱታል። ሆኖም በአንዳንድ አገሮች ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ይህ ዘዴ አሁንም ውጤታማ ይሆን?
2. ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ለመመሥከር መሠረት የሚሆነን የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ነው?
2 ቅዱስ ጽሑፋዊና ጠቃሚ:- ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መመሥከር ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለው። ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት ሆነው ወደ ሰዎች ቤት እንዲሄዱ አዟቸዋል። (ሉቃስ 10:5-7) እርሱ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ . . . ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር” ይላል። (ሥራ 5:42) ሐዋርያው ጳውሎስም ከቤት ወደ ቤት እየሄደ በቅንዓት አስተምሯል።—ሥራ 20:20
3. ከቤት ወደ ቤት መመሥከር ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
3 ዛሬም ቢሆን ምሥራቹን ለማሰራጨት ከቤት ወደ ቤት ሄዶ መመሥከር ጠቃሚ ዘዴ መሆኑን ቀጥሏል። ይህ ደግሞ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ሥርዓት ባለውና በተደራጀ መልኩ ‘ለመፈለግ’ ያስችለናል። (ማቴ. 10:11) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በቤታቸው ሲሆኑ ይበልጥ ዘና ይላሉ። ከእነርሱ ጋር ፊት ለፊት እየተያዩ መነጋገር ማለትም ድምጻቸውን መስማት፣ በፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት ማየትና አካባቢያቸውን መመልከት የሰዎቹን ፍላጎት እንዲሁም የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለማስተዋል ያስችለናል። አብዛኛውን ጊዜ ረዘም ያለ ውይይት ማድረግ የምንችልበትን ጥሩ አጋጣሚም ይሰጠናል።
4. ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን?
4 በግለሰብ ደረጃ ማስተካከያ ማድረግ:- ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ ወንጌል” ብሎ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። (1 ቆሮ. 9:23) ብዙ ሰዎች ቤታቸው በሚገኙበት ጊዜ ማለትም በቀኑ መገባደጃ ላይ፣ ቅዳሜና እሁድ ወይም ደግሞ በበዓል ቀናት ለመስበክ ፕሮግራማችንን ማስተካከል እንችል ይሆናል። ቤታቸው ያልተገኙትን ሰዎች መዝግቦ በመያዝ በሳምንቱ ውስጥ በሌላ ቀን ወይም በቀኑ ውስጥ በተለያየ ሰዓት ሄዶ መሞከር ይቻላል።
5. የጤና እክል ያለባቸው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ መካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?
5 የጤና እክል ያለባቸውም ቢሆኑ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል ይችሉ ይሆናል። ቅርብና አመቺ ወደሆኑ ቤቶች ይዘናቸው በመሄድ ለእነርሱ በሚስማማ ፍጥነት ለማገልገል እቅድ ማውጣት እንችል ይሆናል። የመተንፈስ ችግር ያለባት አንዲት እህት ማነጋገር የምትችለው በየግማሽ ሰዓቱ አንድ ቤት ብቻ ነው። እንደዚህም ሆኖ በቡድን ሆነው ሲሰብኩ አብራቸው ማገልገል በመቻሏ ምን ያህል ተደስታና ረክታ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም!
6. ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት መደበኛ የአገልግሎታችን ዘርፍ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
6 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ አማካኝነት በርካታ በግ መሰል ሰዎች እየተገኙ ነው። አንድ አስፋፊ አንድ በር ሲያንኳኳ እንዲህ የሚል መልስ አግኝቷል:- “ግቡ። ማን እንደሆናችሁ አውቃለሁ። እኔን መርዳት የሚችል ሰው እንዲልክልኝ ወደ አምላክ ስጸልይ ነበር፤ በኋላም በሩ ሲንኳኳ ሰማሁ። እሱም ጸሎቴን ሰምቶ እናንተን ላከልኝ።” ይህን ዓይነቱን የስብከት ዘዴ ይሖዋ እየባረከው እንዳለ ከሚገኘው ውጤት መመልከት ይቻላል። (ማቴ. 11:19) ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በቋሚነት ለመካፈል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።