የግል የአገልግሎት ክልል አለህ?
1. የግል የአገልግሎት ክልል ሲባል ምን ማለት ነው?
1 የግል የአገልግሎት ክልል ሲባል ለአንተ የተመደበ ክልል ማለት ነው። ይህ ክልል ለአንተ አማካይ የሆነ ቦታ ላይ የሚገኝ ሊሆን ስለሚችል ቶሎ ወደ ቦታው ደርሰህ ብቻህንም ሆነ ከሌላ አስፋፊ ጋር ማገልገል ትችላለህ። አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ጉባኤው የቡድን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያደርገውን ዝግጅት መደገፉ ጠቃሚ ቢሆንም በሌሎች ጊዜያት ለመሥራት የሚያስችል የግል የአገልግሎት ክልል መኖሩ የተጣራ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላል፤ ይህ ዝግጅት በተለይ በጣም ሰፊ የአገልግሎት ክልል ላላቸው ጉባኤዎች ጠቃሚ ነው።—ሥራ 10:42
2. የግል የአገልግሎት ክልል መውሰድ ያሉት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
2 ጥቅሞቹ፦ አንዳንዶች በሥራ ቦታቸው አቅራቢያ የግል የአገልግሎት ክልል መውሰዳቸው በምሳ እረፍት ወይም ከሥራ እንደወጡ ለመስበክ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ደግሞ ሰፈራቸው ያለን አንድ ክልል ወስደው በቤተሰብ አንድ ላይ መሥራት መቻላቸው አስደስቷቸዋል። ተመላልሶ መጠየቅ የሚደረግላቸውን ሰዎች እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ቅርብ የሆነ ቦታ ላይ ማግኘት ጉልበት፣ ጊዜና ወጪ ይቀንሳል። የግል የአገልግሎት ክልል መውሰድ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ብዙ ለማገልገል ስለሚያስችል፣ አንዳንዶች አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ፣ ሌላው ቀርቶ የዘወትር አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ሊረዳቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ በግል የአገልግሎት ክልል ውስጥ መሥራትና በአካባቢው ካሉ ሰዎች ጋር ይበልጥ መቀራረብ የሰዎቹን አመኔታ እንድናገኝ ከመርዳቱም በላይ አቀራረባችንን እነርሱን ከሚያሳስቧቸው ነገሮች ጋር እንድናስማማ ይረዳናል፤ ይህም ደግሞ በአገልግሎታችን ውጤታማ እንድንሆን ያደርገናል።
3. የግል የአገልግሎት ክልል የወሰደች አንዲት አቅኚ ምን ያገኘችው ተሞክሮ አለ?
3 አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የግል የአገልግሎት ክልል እንድትወስድ ያበረታታት አንዲት አቅኚ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “የሰጠኝን ምክር የተቀበልኩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በአገልግሎት ክልሌ ካሉ ሰዎች ጋር በደንብ መተዋወቅና መግባባት ቻልኩ። የማገለግልበትን ሰዓት ከእነርሱ ሁኔታ ጋር አስተካክያለሁ። በዚህም ምክንያት ሪፖርት የማደርገው የተመላልሶ መጠየቅ ቁጥር ከ35 ወደ 80 በላይ ከፍ ብሏል፤ ሰባት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አግኝቻለሁ።”
4. የግል የአገልግሎት ክልል ማግኘትም ሆነ በክልሉ መሥራት የምትችለው እንዴት ነው?
4 እንዴት ማግኘት ይቻላል? የግል የአገልግሎት ክልል ለማግኘት ከፈለግህ የክልል አገልጋዩን መጠየቅ ትችላለህ። በክልልህ ሌላ አስፋፊ አብሮህ እንዲያገለግል ለመጋበዝ ነጻነት ይሰማህ፤ እንዲሁም ሰው ያላገኘህባቸውን ቤቶች መዝግበህ መያዝህን አትዘንጋ። ክልሉን በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ ከከበደህ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካችህን ወይም ሌላ ሰው እንዲረዳህ መጠየቅ ትችላለህ። አራት ወሩ ሲያበቃ ሠርተህ የጨረስከውን የአገልግሎት ክልል መመለስ አሊያም ደግመህ መሥራት እንደምትፈልግ መጠየቅ ትችላለህ። ይሁን እንጂ አንድ ክልል ለዘላለም ያንተው ሆኖ ይቀጥላል ማለት አይደለም፤ ምናልባት ሌሎችም የጠየቁ ስለሚኖሩ መመለስ ይኖርብሃል። ያለህበት ጉባኤ ያለው የአገልግሎት ክልል ጥቂት ከሆነ የግል የአገልግሎት ክልል ማግኘት አይቻል ይሆናል። በዚህም ወቅት ቢሆን የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ የተወሰነ ክልል እንዲሰጥህ መጠየቅ ትችላለህ።
5. የተሰጠንን የስብከት ሥራ በተሳካ መንገድ መወጣት እንድንችል ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
5 ምሥራቹን “በዓለም ሁሉ” እንድንሰብክ የተሰጠን ሥራ ተፈታታኝ ነው። (ማቴ. 24:14) የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በቡድን ሆኖ ከመስበክ በተጨማሪ በግል የአገልግሎት ክልል ውስጥ መሥራት ብዙ ሰዎችን አግኝተን ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች እንድንናገር ያስችለናል።