ለአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ልታወጣው የምትችለው ጠቃሚ ግብ
1. ለአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ምን ግብ ልናወጣ እንችላለን?
1 መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ከፈለግን ግቦች ማውጣት ይኖርብናል። ለአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ምን ግቦች አውጥተሃል? ለአንድ ወይም ለሁለት ወር ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ልታወጣው የምትችለው በጣም ጥሩ ግብ ነው። ይህ አስደሳች እንቅስቃሴ ብዙውን ጊዜ ቀደም ብሎ እቅድ ማውጣት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህን ለማድረግ የተሻለው ጊዜ አሁን ነው። ረዳት አቅኚ ለመሆን ግብ ማውጣት ያለብን ለምንድን ነው?
2. ረዳት አቅኚ የመሆን ግብ እንድናወጣ የሚገፋፉን ምን ምክንያቶች አሉ?
2 ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያነሳሱን ምክንያቶች:- ረዳት አቅኚነት፣ በአገልግሎት ተጨማሪ ሰዓታትን በማሳለፍ በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ‘ይበልጥ’ ለማስደሰት ያስችለናል። (1 ተሰ. 4:1) ይሖዋ ያደረገልንን ነገሮች መለስ ብለን ስናስብ ለሌሎች ስለ እሱ እንድንናገር ልባችን ይገፋፋናል። (መዝ. 34:1, 2) ይሖዋ በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ስንል የምንከፍላቸውን መሥዋዕቶች በቁም ነገር የሚያያቸው ከመሆኑም ባሻገር ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ዕብ. 6:10) ከዚህም በላይ የምናከናውነው ትጋት የተሞላበት ሥራ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ማወቃችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል።—1 ዜና 29:9
3, 4. ረዳት አቅኚ መሆናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
3 አብዛኛውን ጊዜ አንድን ሥራ ደጋግመህ በሠራኸው ቁጥር የዚያኑ ያህል እየቀለለህና አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል። በመሆኑም በአገልግሎት ላይ ረዘም ያለ ሰዓት ማሳለፍህ ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ በልበ ሙሉነት ለመስበክ ያስችልሃል። ከሰዎች ጋር ውይይት በመጀመርም ይሁን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ረገድ የተካንህ ትሆናለህ። ለሌሎች ስለምታምንባቸው ነገሮች ብዙ በተናገርህ መጠን የአንተም እምነት ይበልጥ ይጠነክራል። አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያልነበራቸው በርካታ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ በሆኑበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ችለዋል።
4 ረዳት አቅኚነት በዘልማድ የምናደርጋቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ካሉ እነሱን ለማስተካከል የሚያስችል ማበረታቻ ሊሆንልንም ይችላል። ቀደም ሲል በዘወትር አቅኚነት ያገለግል የነበረ አንድ ወንድም ለመደበኛ ሥራው ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ እንዳለ ስለተሰማው ለአንድ ወር በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ወሰነ። ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ረዳት አቅኚ በመሆን ያገለገልኩበት ያ ወር በመንፈሳዊ ምን ያህል እንዳነቃቃኝ ስመለከት በጣም ተገረምኩ! በመሆኑም በረዳት አቅኚነት ለመቀጠል ወሰንኩ፤ ይህ ደግሞ በድጋሚ የዘወትር አቅኚ እንድሆን መንገድ ከፍቶልኛል።”
5. ብቃት የለኝም የሚለውን ስሜት እንዴት ማሸነፍ እንችላለን?
5 እንቅፋቶቹን ማሸነፍ:- አንዳንዶች ረዳት አቅኚ ለመሆን ከማመልከት ወደኋላ የሚሉት ጥሩ የመስበክ ችሎታ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው። ወደኋላ እንድትል የሚያደርግህ እንዲህ ያለው ስሜት ከሆነ ይሖዋ ልክ እንደ ኤርምያስ አንተንም ሊረዳህ ይችላል። (ኤር. 1:6-10) ምንም እንኳ ሙሴ ‘ኮልታፋና ንግግር የማይችል ሰው’ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም ተጠቅሞበታል። (ዘፀ. 4:10-12) አንተም ብቃት እንደሌለህ ከተሰማህ ድፍረት እንዲሰጥህ ይሖዋን ለምነው።
6. የጤንነት ችግር ቢኖርብንም ወይም ፕሮግራማችን በሥራ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ በረዳት አቅኚነት ማገልገል የምንችለው እንዴት ነው?
6 ረዳት አቅኚ ለመሆን የምታመነታው የጤንነት ችግር ስላለብህ አሊያም ፕሮግራምህ የተጣበበ ስለሆነ ነው? አቅመ ደካማ ብትሆንም እንኳ ቋሚ ኘሮግራም አውጥተህ አቅምህ የሚፈቅድልህን ያህል በመሥራት በረዳት አቅኚነት ማገልገል ትችል ይሆናል። ፕሮግራምህ በሥራ የተጣበበ ከሆነ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ አንዳንድ ሥራዎችን ወደ ሌላ ወር ማዛወር ትችል ይሆናል። የሙሉ ቀን ሠራተኛ የሆኑ አንዳንድ ወንድሞች አንድ ወይም ሁለት የእረፍት ቀን በመውሰድ ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስችል ጊዜ አግኝተዋል።—ቈላ. 4:5
7. የረዳት አቅኚነት ግብ የማውጣቱን ጉዳይ በጸሎት ልታስብበት የሚገባው ለምንድን ነው?
7 እዚህ ግብ ላይ እንዴት መድረስ ይቻላል? ረዳት አቅኚ ለመሆን ያለህን ፍላጎት አስመልክተህ ጸልይ። አገልግሎትህን ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት እንዲባርክልህ ይሖዋን ጠይቀው። (ሮሜ 12:11, 12) ፕሮግራምህን ማስተካከል የምትችልበትን መንገድ በተመለከተ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። (ያዕ. 1:5) ረዳት አቅኚ የመሆን ፍላጎት ከሌለህ በስብከት እንቅስቃሴህ ደስታ እንድታገኝ እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።—ሉቃስ 10:1, 17
8. በምሳሌ 15:22 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስችልህ እንዴት ነው?
8 በረዳት አቅኚነት የማገልገልን ግብ በቤተሰብ ደረጃ ተወያዩበት። (ምሳሌ 15:22) ምናልባትም ከቤተሰባችሁ አባላት ውስጥ አንዱ፣ ሌሎቹ በሚያደርጉለት ድጋፍ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ይችል ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ላሉ ምናልባትም ከአንተ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ረዳት አቅኚ የመሆን ግብ እንዳለህ ንገራቸው። እንዲህ ማድረግህ እነሱም ረዳት አቅኚ የመሆን ጉጉት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል።
9. ረዳት አቅኚ ለመሆን የትኞቹን ወራት ትመርጣለህ?
9 ለአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ያወጣኸውን የአገልግሎት ፕሮግራም ስትቃኝ ረዳት አቅኚ ለመሆን አመቺ ሆኖ ያገኘኸው ጊዜ የትኛው ነው? የሙሉ ቀን ሠራተኛ አሊያም ተማሪ ከሆንክ በዓል ያለባቸውን ወይም አምስት ቅዳሜዎች አሊያም አምስት እሁዶች ያሏቸውን ወራት ግምት ውስጥ ማስገባት ትፈልግ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል መስከረም፣ ታኅሣሥ፣ መጋቢት እና ነሐሴ አምስት ቅዳሜዎችና እሁዶች አሏቸው። የግንቦት ወር አምስት ቅዳሜዎች ሲኖሩት የሰኔ ወር ደግሞ አምስት እሁዶች አሉት። የጤንነት ችግር ካለብህ ብዙውን ጊዜ ጥሩ የአየር ሁኔታ የሚኖርባቸውን ወራት ለማሰብ ሞክር። በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችሁን በሚጎበኝበት ወር ረዳት አቅኚ ለመሆን ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ካደረግህ በጉብኝቱ ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከዘወትር አቅኚዎች ጋር በሚያደርገው ስብሰባ ላይ የመጀመሪያውን ክፍል የመከታተል ተጨማሪ መብት ታገኛለህ። በቀጣዩ ዓመት የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሚከበረው መጋቢት 22 ስለሆነ መጋቢት፣ ሚያዝያና ግንቦት ረዳት አቅኚ ለመሆን ተመራጭ ወቅቶች ናቸው። ረዳት አቅኚ መሆን የምትችልበትን ወር ወይም ወራት አንዴ ከመረጥክ በኋላ የሚጠበቅብህን ሰዓት ለማሟላት የሚያስችልህን ፕሮግራም በጽሑፍ አስፍር።
10. ረዳት አቅኚ መሆን ካልቻልክ ምን ማድረግ ትችላለህ?
10 በመጪው የአገልግሎት ዓመት ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል እንደማትችል ቢሰማህ እንኳ የአቅኚነት መንፈስ በመያዝ በቅንዓት ማገልገል ትችላለህ። ይሖዋ ለእሱ ምርጥህን ለመስጠት በሙሉ ልብህ በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት በመተማመን በአገልግሎት የአቅምህን ያህል መካፈልህን ቀጥል። (ገላ. 6:4) ረዳት አቅኚ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙትን የምትደግፍና የምታበረታታ ሁን። ምናልባትም ረዳት አቅኚ ከሆኑት ጋር በሳምንቱ ውስጥ አንድ ተጨማሪ ቀን አብረሃቸው ለማገልገል ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችላለህ።
11. የጥድፊያ ስሜት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?
11 የይሖዋ ሕዝቦች የጊዜያችንን አጣዳፊነት ይገነዘባሉ። መሠራት ያለበት ሥራ አለ፤ ይኸውም ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ነው። የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ነው፤ የቀረን ጊዜ ደግሞ በጣም አጭር ነው። (1 ቆሮ. 7:29-31) ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር አቅማችን በፈቀደው መጠን በአገልግሎት ላይ እንድንካፈል ይገፋፋናል። ጥሩ እቅድ በማውጣትና ጥረት በማድረግ በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ቢያንስ ለአንድ ወር ረዳት አቅኚ መሆን እንችል ይሆናል፤ ይህ ደግሞ በእርግጥም ጠቃሚ ግብ ነው!